ግንቦት
ቅዳሜ፣ ግንቦት 1
የሚወለደውን ልጅ በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለብን መመሪያ [ስጠን]።—መሳ. 13:8
ወላጆች፣ ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱ ማስተማር የሚችሉት እንዴት ነው? እንደ ማኑሄ የይሖዋን እርዳታ በጸሎት ጠይቁ። በተጨማሪም ምሳሌ በመሆን አስተምሯቸው። ወላጆች በአንደበታችሁ ለልጃችሁ ብዙ ትምህርት መስጠት ትችላላችሁ፤ ሆኖም በልጃችሁ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ተግባራችሁ ነው። ዮሴፍና ማርያም፣ ኢየሱስን ጨምሮ ለሁሉም ልጆቻቸው ግሩም ምሳሌ እንደነበሩ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ዮሴፍ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ለማቅረብ ተግቶ ይሠራ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ቤተሰቡ ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት እንዲኖረው ለማድረግ ይጥር ነበር። (ዘዳ. 4:9, 10) ዮሴፍ “በየዓመቱ” በሚከበረው የፋሲካ በዓል ላይ ለመገኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ መላ ቤተሰቡን ይዞ ይጓዝ ነበር። (ሉቃስ 2:41, 42) በዚያ ጊዜ የነበሩ አንዳንድ አባቶች መላውን ቤተሰብ ይዞ እንዲህ ያለ ጉዞ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ፣ ጊዜ የሚፈጅና ብዙ ገንዘብ የሚያስወጣ እንደሆነ ተሰምቷቸው ይሆናል። ዮሴፍ ግን ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት ነበረው፤ ልጆቹም እንዲህ እንዲያደርጉ ያስተምራቸው ነበር። ማርያምም ብትሆን ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ ታውቅ ነበር። ልጆቿ የአምላክን ቃል እንዲወዱ በቃልም ሆነ በተግባር እንዳስተማረቻቸው ምንም ጥርጥር የለውም። w19.12 24-25 አን. 9-12
እሁድ፣ ግንቦት 2
ለኃጢአት የተሸጥኩ ሥጋዊ ነኝ።—ሮም 7:14
ይሖዋ በምድራዊ ቤተሰቡ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ችግር በተፈጠረበት ወቅት የወሰደው እርምጃ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያረጋግጥ ነው። አዳም በሰማያዊ አባቱ ላይ ባመፀበት ወቅት፣ ደስተኛ በሆነው የይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ የነበረውን ቦታ ያጣ ሲሆን ዘሮቹም ይህን መብት እንዲያጡ አድርጓል። (ሮም 5:12) ይሁን እንጂ ይሖዋ ሁኔታውን ለማስተካከል እርምጃ ወሰደ። ይሖዋ አዳምን ቢቀጣውም በአብራኩ ውስጥ ያሉ ዘሮቹ ያለተስፋ እንዲቀሩ አላደረገም። ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች እንደገና የቤተሰቡ አባል እንዲሆኑ እንደሚያደርግ ወዲያውኑ ቃል ገባ። (ዘፍ. 3:15፤ ሮም 8:20, 21) ይሖዋ፣ የሚወደው ልጁ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት እንዲሆን በማድረግ ይህ ዓላማው እንዲፈጸም ዝግጅት አድርጓል። ይሖዋ ልጁን ለእኛ ሲል በመስጠት ምን ያህል እንደሚወደን አረጋግጧል። (ዮሐ. 3:16) እንደ እሱ ያለ አባት የለም። ይሖዋ ጸሎታችንን ይሰማል፤ እንዲሁም ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ያሟላልናል። ሥልጠና ይሰጠናል እንዲሁም ይደግፈናል። ከዚህም ሌላ ለወደፊቱ ጊዜ አስደናቂ በረከቶች አዘጋጅቶልናል። አባታችን እንደሚወደንና እንደሚያስብልን ማወቃችን ምንኛ የሚያስደስት ነው! w20.02 6 አን. 16-17፤ 7 አን. 20
ሰኞ፣ ግንቦት 3
በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ።—መዝ. 94:19
በጭንቀት የተዋጥክበት ጊዜ አለ? ለጭንቀትህ መንስኤ የሆነው፣ ሌሎች የተናገሩት ወይም ያደረጉት ነገር አሊያም ደግሞ አንተ ራስህ የተናገርከው ወይም ያደረግከው ነገር ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ አንድ ስህተት ሠርተህ ከሆነ ይሖዋ መቼም ይቅር እንደማይልህ በማሰብ ትጨነቅ ይሆናል። ይህም እንዳይበቃ ደግሞ በጭንቀት መዋጥህ እምነት እንደጎደለህና መጥፎ ሰው እንደሆንክ የሚጠቁም እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት። የነቢዩ ሳሙኤል እናት የሆነችው ሐና ታላቅ እምነት ያላት ሴት ነበረች። ይሁንና አንዲት የቤተሰቧ አባል ያደረሰችባት በደል በጭንቀት እንድትዋጥ አድርጓት ነበር። (1 ሳሙ. 1:7) ሐዋርያው ጳውሎስ ጠንካራ እምነት ቢኖረውም ‘በጉባኤዎች ሐሳብ’ የተነሳ በጣም ተጨንቆ ነበር። (2 ቆሮ. 11:28) ንጉሥ ዳዊት ጠንካራ እምነት ያለው ሰው በመሆኑ ይሖዋ በጣም ይወደው ነበር። (ሥራ 13:22) ያም ቢሆን ዳዊት በፈጸማቸው ስህተቶች የተነሳ በከባድ ጭንቀት ተደቁሶ ነበር። (መዝ. 38:4) ይሖዋ ሦስቱንም አገልጋዮቹን አጽናንቷቸዋል እንዲሁም አረጋግቷቸዋል። w20.02 20 አን. 1-2
ማክሰኞ፣ ግንቦት 4
ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ።—ማቴ. 16:24
ራስህን ወሰንክ የሚባለው ለይሖዋ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ሕይወትህን በሙሉ እሱን እንደምታገለግለው ቃል ስትገባ ነው። ራስህን ለአምላክ ስትወስን ‘ራስህን ትክዳለህ።’ በዚህ ጊዜ የይሖዋ ንብረት ትሆናለህ፤ ይህ ደግሞ ትልቅ መብት ነው። (ሮም 14:8) ከዚያ ጊዜ አንስቶ ራስህን በማስደሰት ላይ ሳይሆን እሱን በማገልገል ላይ ያተኮረ ሕይወት እንደምትመራ ለይሖዋ ቃል ትገባለህ። ራስህን ስትወስን ለአምላክ ስእለት ትሳላለህ። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ስእለት እንድንሳል አያስገድደንም። አንዴ ከተሳልን በኋላ ግን ቃላችንን እንድናከብር ይጠብቅብናል። (መዝ. 116:12, 14) ራስን መወሰን በአንተና በይሖዋ መካከል ብቻ ያለ ጉዳይ ነው፤ ይህን ውሳኔ ማድረግህን ሌላ ሰው ሊያውቅ አይችልም። ጥምቀት ደግሞ በሕዝብ ፊት የሚፈጸም ክንውን ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የሚካሄደው በወረዳ ወይም በክልል ስብሰባ ላይ ነው። በምትጠመቅበት ጊዜ ሌሎች ሰዎችም ራስህን ለይሖዋ መወሰንህን ማየት ይችላሉ። ስለዚህ መጠመቅህ ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ እንደምትወደው እንዲሁም እሱን ለዘላለም ለማገልገል እንደወሰንክ ሰዎች እንዲያዩ ያደርጋል።—ማር. 12:30፤ w20.03 9 አን. 4-5
ረቡዕ፣ ግንቦት 5
ማንም ሰው . . . አያሳስታችሁ።—2 ተሰ. 2:3
ሰይጣን፣ ሰዎች ስለ ይሖዋ ያላቸው አመለካከት እንዲዛባ ያደርጋል። የኢየሱስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ፣ ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንድ ሰዎች የሐሰት ትምህርቶችን ማስፋፋት ጀመሩ። (ሥራ 20:29, 30) እነዚህ ከሃዲዎች፣ እሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ የሆነው የይሖዋ ማንነት እንዲሰወር አደረጉ። ለምሳሌ፣ ከሚያዘጋጇቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ውስጥ መለኮታዊውን ስም በማውጣት “ጌታ” እንደሚሉት ባሉ መጠሪያዎች ተኩት። በአምላክ የግል ስም ፋንታ “ጌታ” የሚለውን መጠሪያ መጠቀማቸው መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብ ሰው፣ በይሖዋና በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተጠቀሱት ሌሎች “ጌቶች” መካከል ያለው ልዩነት እንዲምታታበት ያደርጋል። (1 ቆሮ. 8:5) ለይሖዋም ሆነ ለኢየሱስ “ጌታ” የሚለውን መጠሪያ መጠቀማቸው ደግሞ ይሖዋና ልጁ ያላቸው የተለያየ ማንነትና ቦታ እንዳይታወቅ አድርጓል። (ዮሐ. 17:3) ይህ የፈጠረው ግራ መጋባት፣ ሥላሴ የተባለው በአምላክ ቃል ውስጥ የማይገኝ መሠረተ ትምህርት እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በዚህም የተነሳ ብዙዎች አምላክን ሚስጥራዊና ሊታወቅ የማይችል አካል እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ይህ እንዴት ያለ አስከፊ ውሸት ነው!—ሥራ 17:27፤ w19.06 5 አን. 11
ሐሙስ፣ ግንቦት 6
አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም።—2 ጢሞ. 4:5
አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም የምንችልበት አንዱ መንገድ በስብከቱ ሥራ ችሎታችንን ማሻሻል ነው። (ምሳሌ 1:5፤ 1 ጢሞ. 4:13, 15) ይሖዋ ከእሱ ጋር ‘አብረን እንድንሠራ’ የጋበዘን መሆኑ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! (1 ቆሮ. 3:9) “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች [ለይተህ] በማወቅ” በክርስቲያናዊ አገልግሎት ላይ ትኩረት የምታደርግ ከሆነ ‘ይሖዋን በደስታ ማገልገል’ ትችላለህ። (ፊልጵ. 1:10፤ መዝ. 100:2) ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥምህ ወይም የአቅም ገደብ ቢኖርብህ የአምላክ አገልጋይ ስለሆንክ እሱ አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም የሚያስችልህን ኃይል እንደሚሰጥህ እርግጠኛ ሁን! (2 ቆሮ. 4:1, 7፤ 6:4) ያለህበት ሁኔታ በስብከቱ ሥራ ሰፊ ጊዜ እንድታሳልፍ ፈቀደልህም አልፈቀደልህ አገልግሎትህን በሙሉ ነፍስ እስካከናወንክ ድረስ ‘እጅግ የምትደሰትበት ነገር’ ታገኛለህ። (ገላ. 6:4) አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ስትፈጽም ለይሖዋና ለሰዎች ፍቅር እንዳለህ ታሳያለህ። “ይህን በማድረግ ራስህንም ሆነ የሚሰሙህን ታድናለህ።”—1 ጢሞ. 4:16፤ w19.04 6 አን. 15፤ 7 አን. 17
ዓርብ፣ ግንቦት 7
[ሰይጣን] መላውን ዓለም እያሳሳተ [ነው]።—ራእይ 12:9
ሰይጣንና አጋንንቱ ሰዎችን ለማታለል የሚሞክሩበት ዋነኛው መንገድ መናፍስታዊ ድርጊት ነው። በመናፍስታዊ ድርጊቶች የሚካፈሉ ግለሰቦች፣ የሰው ልጆች ሊያውቋቸው ወይም ሊቆጣጠሯቸው የማይችሉ ነገሮችን የማወቅ ወይም የመቆጣጠር ችሎታ እንዳላቸው ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች በጥንቆላ አሊያም በኮከብ ቆጠራ አማካኝነት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማወቅ እንደሚችሉ ይገልጻሉ። ሌሎች ደግሞ ከሞቱ ሰዎች ጋር መነጋገር የሚችሉ ያስመስላሉ። የአስማት ድርጊቶች የሚፈጽሙና በሌሎች ላይ ድግምት የሚያደርጉ ሰዎችም አሉ። በላቲን አሜሪካና በካሪቢያን ደሴቶች ባሉ 18 አገሮች ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በጥናቱ ከተካፈሉት መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በአስማት፣ በጥንቆላ ወይም በመተት ያምናሉ፤ ከዚህ ጋር ተቀራራቢ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ደግሞ ከመናፍስት ጋር መነጋገር እንደሚቻል ያምናሉ። በአፍሪካ ውስጥ በሚገኙ 18 አገሮች ላይም ጥናት ተካሂዶ ነበር። በጥናቱ ከተሳተፉት ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በጥንቆላ እንደሚያምኑ ተናግረዋል። እርግጥ ነው፣ የምንኖረው የትም ሆነ የት ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ለመራቅ ጥረት ማድረግ አለብን። w19.04 20-21 አን. 3-4
ቅዳሜ፣ ግንቦት 8
በመካከላችሁ ሴሰኛ ሰው . . . እንዳይገኝ ተጠንቀቁ።—ዕብ. 12:16
ይሖዋ አምላክ ማንኛውንም ዓይነት ክፋት ይጠላል። (መዝ. 5:4-6) ሕፃናትን እንደማስነወር ያለውን ጭካኔ የሚንጸባረቅበትና እጅግ ዘግናኝ የሆነ ድርጊትማ ምንኛ ይጸየፈው ይሆን! እኛም የእሱ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ይህን ድርጊት አጥብቀን የምንጸየፈው ሲሆን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በምንም ዓይነት በቸልታ አናልፈውም። (ሮም 12:9) ሕፃናትን ከማስነወር ጋር የተያያዘ ማንኛውም ድርጊት ‘ከክርስቶስ ሕግ’ ጋር ፈጽሞ ይጋጫል! (ገላ. 6:2) ኢየሱስ በቃልም ይሁን ምሳሌ በመሆን ያስተማራቸው ትምህርቶች በሙሉ በፍቅር ላይ የተመሠረቱ ከመሆኑም ሌላ ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋሉ። እውነተኛ ክርስቲያኖች በዚህ ሕግ ስለሚመሩ ልጆችን የሚይዙት የደህንነት ስሜት እንዲያድርባቸውና ከልብ እንደሚወደዱ እንዲሰማቸው በሚያደርግ መንገድ ነው። በልጆች ላይ የሚፈጸመው ፆታዊ ጥቃት ግን ልጆች ስጋት እንዲያድርባቸውና እንደማይወደዱ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ፍትሕ የጎደለው ብሎም ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት ነው። የሚያሳዝነው፣ ይህ ጉዳይ እውነተኛ ክርስቲያኖችንም ነክቷል። ምክንያቱም “ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች” ከቀን ወደ ቀን እየበዙ የሄዱ ሲሆን አንዳንዶቹ ወደ ክርስቲያን ጉባኤም ጭምር ሰርገው ሊገቡ ይችላሉ። (2 ጢሞ. 3:13) ከዚህም በተጨማሪ፣ ይሖዋን እንደሚያገለግሉ የሚናገሩ አንዳንድ የጉባኤው አባላት ተገቢ ላልሆነ የፆታ ምኞት በመሸነፍ ልጆችን አስነውረዋል። w19.05 8 አን. 1-3
እሁድ፣ ግንቦት 9
ጻድቅ ሰው የሚያቀርበው ምልጃ ታላቅ ኃይል አለው።—ያዕ. 5:16
መንፈሱ የተደቆሰ ሰው ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ብቁ እንዳልሆነ ይሰማው ይሆናል። እንዲህ ያለውን ሰው ለማጽናናት አብረነው በመሆን ስሙን ጠቅሰን ልንጸልይ እንችላለን። በጸሎታችን ላይ፣ እኛም ሆንን ጉባኤው ይህን ግለሰብ ምን ያህል እንደምንወደው ልንገልጽ እንዲሁም ይሖዋ ውድ የሆነውን በጉን እንዲያረጋጋውና እንዲያጽናናው ልንለምን እንችላለን። እንዲህ ያሉት ጸሎቶች ግለሰቡን በእጅጉ ሊያጽናኑት ይችላሉ። ከመናገራችሁ በፊት አስቡ። ሳይታሰብባቸው የሚነገሩ ቃላት ሊጎዱ ይችላሉ። ደግነት የተንጸባረቀባቸው ቃላት ደግሞ የመፈወስ ኃይል አላቸው። (ምሳሌ 12:18) በመሆኑም ሊያጽናኑ፣ ሊያበረታቱና ሊያረጋጉ የሚችሉ ቃላትን መምረጥ እንድትችሉ ይረዳችሁ ዘንድ ወደ ይሖዋ ጸልዩ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ይሖዋ ራሱ ከተናገራቸው ቃላት የበለጠ ኃይል ያላቸው ቃላት ሊኖሩ እንደማይችሉ አስታውሱ። (ዕብ. 4:12) ሌሎችን ስናጽናና ይሖዋ እንደሚወዳቸው እንዲያስታውሱ እንረዳቸዋለን። ደግሞም ይሖዋ የፍትሕ አምላክ እንደሆነ ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። ከእሱ ሊሰወር የሚችል ምንም ዓይነት የክፋት ድርጊት የለም። ይሖዋ ሁሉንም ነገር የሚያይ ሲሆን ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች የእጃቸውን እንዲያገኙ ያደርጋል።—ዘኁ. 14:18፤ w19.05 18 አን. 18፤ 19 አን. 19, 21
ሰኞ፣ ግንቦት 10
በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።—ቆላ. 2:8
ሰይጣን ለይሖዋ ጀርባችንን እንድንሰጥ ይፈልጋል። ይህን ግቡን ለማሳካት ሲል ደግሞ አስተሳሰባችንን ለማዛባት ይኸውም አእምሯችንን በመማረክ እሱን እንድንታዘዘው ለማድረግ ይሞክራል። ሊማርኩን የሚችሉ ነገሮችን በማቅረብ የእሱን አመለካከት እንድንቀበል ሊያግባባን አሊያም ደግሞ ተታልለን እሱን እንድንከተል ሊያደርገን ይጥራል። (ቆላ 2:4) የሰይጣን ማታለያዎች ያን ያህል ሊያሳስቡን ይገባል? አዎን! ጳውሎስ በቆላስይስ 2:8 ላይ የሚገኘውን ማስጠንቀቂያ የጻፈው ለማያምኑ ሰዎች እንዳልሆነ እናስታውስ። ደብዳቤውን የጻፈው በመንፈስ ቅዱስ ለተቀቡ ክርስቲያኖች ነው። (ቆላ. 1:2, 5) በዚያ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በሰይጣን የመታለል አደጋ ተደቅኖባቸው ነበር፤ እኛም የምንገኘው ከዚያ በባሰ አደገኛ ዘመን ውስጥ ነው። (1 ቆሮ. 10:12) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ሰይጣን ወደ ምድር የተወረወረ ሲሆን የአምላክን ታማኝ አገልጋዮች ለማሳት ቆርጦ ተነስቷል። (ራእይ 12:9, 12, 17) በተጨማሪም የምንኖረው ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች “በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ” በሚሄዱበት ዘመን ውስጥ ነው።—2 ጢሞ. 3:1, 13፤ w19.06 2 አን. 1-2
ማክሰኞ፣ ግንቦት 11
አሁንስ በቅቶኛል! ይሖዋ ሆይ፣ . . . ሕይወቴን ውሰዳት።—1 ነገ. 19:4
ኤልያስ፣ ንግሥት ኤልዛቤል እንደምትገድለው ስትዝትበት በፍርሃት ተዋጠ። በመሆኑም ወደ ቤርሳቤህ ሸሸ። በጣም ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ ‘እንዲሞት መለመን ጀመረ።’ ኤልያስ ይህን ያህል ተስፋ የቆረጠው ለምንድን ነው? ይህ ነቢይ “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው” ፍጹም ያልሆነ ሰው ነበር። (ያዕ. 5:17) በጣም ከመጨነቁና ከመዛሉ የተነሳ ሁኔታዎች ከአቅሙ በላይ እንደሆኑ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ኤልያስ፣ ሕዝቡ ይሖዋን እንዲያመልክ የሚያደርገው ጥረት መና እንደቀረ፣ በእስራኤል ያለው ሁኔታ ምንም እንዳልተሻሻለና ይሖዋን እያገለገለ ያለው እሱ ብቻ እንደሆነ አስቦ ሊሆን ይችላል። (1 ነገ. 18:3, 4, 13፤ 19:10, 14) ይሖዋ የኤልያስን ስሜት ተረድቶለታል፤ ስሜቱን አውጥቶ በመናገሩ አልተቆጣውም። እንዲያውም ኃይሉ እንዲታደስ አድርጓል። (1 ነገ. 19:5-7) ከዚያም ይሖዋ፣ ታላቅ ኃይሉን ለኤልያስ በማሳየት ይህ ነቢይ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል በደግነት ረድቶታል። በኋላም ይሖዋ፣ ባአልን ለማምለክ ፈቃደኛ ያልሆኑ 7,000 አገልጋዮች በእስራኤል እንዳሉት ለነቢዩ ነገረው። (1 ነገ. 19:11-18) ይሖዋ ኤልያስን እንደሚወደው በእነዚህ መንገዶች አሳይቶታል። w19.06 15-16 አን. 5-6
ረቡዕ፣ ግንቦት 12
ለሽማግሌዎች ተገዙ። . . . እርስ በርስ ባላችሁ ግንኙነት ሁላችሁም ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል።—1 ጴጥ. 5:5
በራስ የመመራት መንፈስን አስወግዱ። እምነት የሚጣልባቸው ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የሚሰጡንን መመሪያ የምንከተል ከሆነ ችግሮች እንዳይፈጠሩ መከላከል እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ሥራችን በታገደበት አንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች፣ አስፋፊዎች በአገልግሎት ላይ ጽሑፎች እንዳያበረክቱ መመሪያ ሰጥተው ነበር። በዚያ አካባቢ የሚኖር አንድ አቅኚ ወንድም ግን ይህን መመሪያ በመጣስ ጽሑፎችን አበረከተ። ታዲያ ይህ ምን አስከተለ? እሱና ሌሎች አስፋፊዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ያከናወኑትን አገልግሎት ጨርሰው ሲሄዱ ፖሊሶች ለምርመራ ያዟቸው። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ከመንግሥት የተላኩ ሰዎች ይከታተሏቸው የነበረ ሲሆን ወንድሞች ካነጋገሯቸው ሰዎች ጽሑፎቹን መውሰድ ችለው ነበር። ከዚህ ተሞክሮ ምን እንማራለን? የተሰጠውን መመሪያ ባንስማማበትም እንኳ መታዘዝ አለብን። ይሖዋ በመካከላችን ሆነው አመራር እንዲሰጡ ከሾማቸው ወንድሞች ጋር ስንተባበር ምንጊዜም የእሱን በረከት እናገኛለን።—ዕብ. 13:7, 17፤ w19.07 12 አን. 17
ሐሙስ፣ ግንቦት 13
የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል።—2 ጢሞ. 3:12
ጌታችን ኢየሱስ፣ የእሱ ደቀ መዛሙርት መሆን የሚፈልጉ ሁሉ እንደሚጠሉ ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ተናግሯል። (ዮሐ. 17:14) እውነተኛውን አምልኮ የሚቃወሙ ሰዎች፣ ታማኝ በሆኑ ክርስቲያኖች ላይ ከዚያ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ስደት እያደረሱባቸው ነው። የዚህ ሥርዓት መጨረሻ እየተቃረበ ሲሄድ ደግሞ ከጠላቶቻችን የሚደርስብን ተቃውሞ እየባሰ እንደሚሄድ እንጠብቃለን። (ማቴ. 24:9) ስደት ሲደርስብን ለመጽናት ከአሁኑ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? በስደት ጊዜ ሊደርሱብን በሚችሉ መጥፎ ነገሮች ላይ ማውጠንጠን አያስፈልገንም። እንዲህ ካደረግን በፍርሃትና በጭንቀት ልንዋጥ እንችላለን። በአእምሯችን የፈጠርናቸው አስጨናቂ ሁኔታዎች ገና ፈተናው ሳይመጣ በፍርሃት ተሸንፈን እጅ እንድንሰጥ ሊያደርጉን ይችላሉ። (ምሳሌ 12:25፤ 17:22) ፍርሃት ‘ጠላታችን ዲያብሎስ’ እኛን ለማሸነፍ የሚጠቀምበት ኃይለኛ መሣሪያ ነው። (1 ጴጥ. 5:8, 9) በመሆኑም አሁኑኑ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ማጠናከራችን አስፈላጊ ነው። w19.07 2 አን. 1-3
ዓርብ፣ ግንቦት 14
ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።—ማቴ. 28:19
ሐዋርያቱ በአንድ ተራራ ላይ ተሰብስበዋል፤ በወቅቱ ልባቸው በጉጉት ተሞልቶ መሆን አለበት። ኢየሱስ በዚህ ተራራ ላይ ከእሱ ጋር እንዲገናኙ ከሞት ከተነሳ በኋላ ነግሯቸው ነበር። (ማቴ. 28:16) “በአንድ ጊዜ ከ500 ለሚበልጡ ወንድሞች” የታየውም በዚህ ወቅት ሳይሆን አይቀርም። (1 ቆሮ. 15:6) ኢየሱስ በዚህ ቦታ እንዲሰበሰቡ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው ለምንድን ነው? “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚለውን አስደሳች ተልእኮ ሊሰጣቸው ስለፈለገ ነው። (ማቴ. 28:18-20) ኢየሱስ ይህን ተልእኮ ሲሰጥ የሰሙት ደቀ መዛሙርት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ሆነዋል። የዚያ ጉባኤ ዋነኛ ተልእኮ ደግሞ ተጨማሪ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ማፍራት ነበር። በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ እውነተኛ የክርስቲያን ጉባኤዎች ያሉ ሲሆን የእነዚህ ጉባኤዎች ዋነኛ ተልእኮም አልተለወጠም። w19.07 14 አን. 1-2
ቅዳሜ፣ ግንቦት 15
ምድር . . . ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።—መክ. 1:4
በኖርዌይ የሚያገለግል አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንደተናገረው ስለ አምላክ መወያየት የማይፈልጉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ስለ ዓለም ሁኔታ ለመወያየት ፈቃደኞች ናቸው። ይህ ወንድም ሰዎችን ሲያነጋግር ሰላምታ ከሰጣቸው በኋላ እንዲህ ይላቸዋል፦ “ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን እንደሚሰማህ ማወቅ ፈልጌ ነበር። የወደፊቱ ጊዜ የተሻለ እንዲሆን ማድረግ የሚችለው ማን ይመስልሃል? ፖለቲከኞች፣ የሳይንስ ሊቃውንት ወይስ ሌሎች?” የሚሰጡትን ምላሽ በትኩረት ካዳመጠ በኋላ ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ የሚናገር ጥቅስ ያነብላቸዋል አሊያም ጥቅሱን በቃሉ ይነግራቸዋል። ምድር እንደማትጠፋ እንዲሁም ጥሩ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ የአንዳንዶችን ትኩረት ይስባል። (መዝ. 37:29) በአገልግሎት ላይ ሰዎችን ስናነጋግር ምሥራቹን በተለያየ መንገድ ለመስበክ ጥረት ማድረጋችን ጠቃሚ ነው። ለምን? ምክንያቱም የአንዳንዶችን ትኩረት የሚስበው ነገር ሌሎችን ላያስደስታቸው ይችላል። አንዳንድ ሰዎችን በቀጥታ ስለ አምላክ ወይም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብናወያያቸው አይከብዳቸው ይሆናል፤ ሌሎችን ግን መጀመሪያ ላይ ስለ ሌሎች ጉዳዮች ብናወያያቸው የተሻለ ሊሆን ይችላል። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ለማነጋገር ጥረት ማድረግ አለብን። (ሮም 1:14-16) የጽድቅ ዝንባሌ ባላቸው ሰዎች ልብ ውስጥ እውነት እንዲያድግ የሚያደርገው ይሖዋ ነው።—1 ቆሮ. 3:6, 7፤ w19.07 22-23 አን. 10-11
እሁድ፣ ግንቦት 16
አምላክ የወደደን በዚህ መንገድ ከሆነ እኛም እርስ በርሳችን የመዋደድ ግዴታ አለብን።—1 ዮሐ. 4:11
አምላክ ያሳየን ታላቅ ፍቅር ወንድሞቻችንን እንድንወድ ያነሳሳናል። (1 ዮሐ. 4:20, 21) ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መውደድ ያን ያህል ጥረት የሚጠይቅብን ነገር እንዳልሆነ ይሰማን ይሆናል። ደግሞስ ሁላችንም ይሖዋን ለማምለክና ግሩም ባሕርያቱን ለመምሰል ጥረት እናደርግ የለ? በተጨማሪም ሕይወቱን ለእኛ እስከ መስጠት የሚያደርስ ታላቅ ፍቅር ያሳየንን የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን። ይሁን እንጂ እርስ በርስ እንድንዋደድ የተሰጠንን ትእዛዝ ማክበር አንዳንድ ጊዜ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ኤዎድያን እና ሲንጤኪ ከሐዋርያው ጳውሎስ ‘ጎን ተሰልፈው’ በቅንዓት ያገለገሉ እህቶች ናቸው። ሆኖም እነዚህ እህቶች በመካከላቸው በተፈጠረ ቅራኔ የተነሳ ተራርቀው የነበረ ይመስላል። ጳውሎስ እነዚህ እህቶች ለነበሩበት ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ኤዎድያንን እና ሲንጤኪን በስም ጠቅሶ “አንድ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራቸው” ቀጥተኛ ምክር ሰጥቷቸዋል። (ፊልጵ. 4:2, 3) ጳውሎስ ለመላው ጉባኤም “ምንጊዜም ማንኛውንም ነገር ሳታጉረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ” የሚል ምክር መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶታል።—ፊልጵ. 2:14፤ w19.08 9 አን. 6-7
ሰኞ፣ ግንቦት 17
አንዳችሁ የሌላውን ከባድ ሸክም ተሸከሙ።—ገላ. 6:2
ደስ የሚለው ነገር፣ በርካታ ጉባኤዎችና ወንድሞች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈሉ ክርስቲያኖች በአገልግሎት ምድባቸው ላይ እንዲቀጥሉ ለመርዳት የቻሉትን ያህል ያደርጋሉ። ይህን የሚያደርጉት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮቹ በአገልግሎታቸው እንዲቀጥሉ በማበረታታት፣ በገንዘብ ወይም በሌሎች ቁሳዊ ነገሮች እነሱን በመደገፍ፣ የሚያገለግሉት ራቅ ባለ ቦታ ከሆነ ደግሞ የቤተሰባቸውን አባላት በመንከባከብ ነው። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ይካፈሉ የነበሩ ወንድሞች በጉባኤያችሁ እንዲያገለግሉ ከተመደቡ፣ ምድባቸው የተለወጠው የሆነ ጥፋት ስለሠሩ ወይም ተግሣጽ ስለተሰጣቸው እንደሆነ አድርጋችሁ አታስቡ። ከዚህ ይልቅ ለውጡን መልመድ ቀላል እንዲሆንላቸው እርዷቸው። ሞቅ አድርጋችሁ ተቀበሏቸው፤ እንዲሁም በጤንነታቸው ምክንያት በአሁኑ ወቅት ማድረግ የሚችሉት ነገር ውስን ቢሆንም እንኳ ያከናወኑትን አገልግሎት እንደምታደንቁ ግለጹላቸው። ከእነሱ ጋር በደንብ ለመተዋወቅ ጥረት አድርጉ። ካካበቱት እውቀት፣ ካገኙት ሥልጠና እንዲሁም ከተሞክሯቸው ትምህርት ለማግኘት ሞክሩ። በአዲስ ምድብ እንዲያገለግሉ የተመደቡ ክርስቲያኖች መኖሪያ ቤት፣ መጓጓዣ፣ ሥራ እና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት መጀመሪያ ላይ የእናንተ እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። w19.08 23 አን. 12-13
ማክሰኞ፣ ግንቦት 18
ጎግ ሆይ፣ . . . በአንተ አማካኝነት በፊታቸው ራሴን [እቀድሳለሁ]።—ሕዝ. 38:16
ጎግ ‘በሥጋ ክንዱ’ ማለትም በወታደራዊ ኃይሉ ይታመናል። (2 ዜና 32:8) እኛ ግን በአምላካችን በይሖዋ እንታመናለን። እርግጥ ይህ በብሔራት ዓይን እንደ ሞኝነት የሚቆጠር ነገር ነው፤ ምክንያቱም በአንድ ወቅት ኃያል የነበረችው የታላቂቱ ባቢሎን አማልክት ‘ከአውሬው’ እንዲሁም ‘ከአሥሩ ቀንዶች’ ሊታደጓት አልቻሉም! (ራእይ 17:16) በመሆኑም ጎግ የአምላክን ሕዝቦች በቀላሉ ሊያጠፋቸው እንደሚችል ያስባል። “ምድርን እንደሚሸፍን ደመና” በመሆን በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራል። ብዙም ሳይቆይ ግን ወጥመድ ውስጥ እንደገባ ይረዳል። ፈርዖን በቀይ ባሕር እንዳጋጠመው ጎግም ከይሖዋ ጋር እየተዋጋ እንዳለ ይገነዘባል። (ዘፀ. 14:1-4፤ ሕዝ. 38:3, 4, 18, 21-23) ክርስቶስና በሰማይ ያለው ሠራዊቱ ጎግን በማጥፋት የአምላክን ሕዝቦች ይታደጋሉ። (ራእይ 19:11, 14, 15) ሆኖም በውሸት ፕሮፓጋንዳው ብሔራት ወደ አርማጌዶን እንዲሰበሰቡ ያደረገው የአምላክ ቀንደኛ ጠላት ሰይጣንስ ምን ያጋጥመዋል? ኢየሱስ እሱንም ሆነ አጋንንቱን ወደ ጥልቁ ወርውሮ ለሺህ ዓመት ይዘጋባቸዋል።—ራእይ 20:1-3፤ w19.09 11-12 አን. 14-15
ረቡዕ፣ ግንቦት 19
በተስፋ ጠብቀው! ያላንዳች ጥርጥር ይፈጸማልና።—ዕን. 2:3
ይሖዋ ቃል የገባቸው መልካም ነገሮች ሲፈጸሙ ለማየት መጓጓታችን ተገቢ ነው። ሆኖም የጠበቅነው ነገር ሳይፈጸም እንደዘገየ ሲሰማን ቅንዓታችን ሊቀዘቅዝ ይችላል። እንዲያውም ተስፋ እንቆርጥ ይሆናል። (ምሳሌ 13:12) በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የኖሩ ወንድሞቻችን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። በዚያ ወቅት የኖሩ ብዙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በ1914 ሰማያዊ ሽልማታቸውን እንደሚያገኙ ይጠብቁ ነበር። ታዲያ ታማኝ የሆኑት ክርስቲያኖች የጠበቁት ነገር ሳይፈጸም መቅረቱ ያሳደረባቸውን ስሜት የተቋቋሙት እንዴት ነው? በሕይወት ሩጫ መካፈላቸውን አላቆሙም፤ ትኩረታቸው በዋነኝነት ያረፈው ሽልማታቸውን በማግኘታቸው ላይ ሳይሆን የአምላክን ፈቃድ በታማኝነት በመፈጸማቸው ላይ ነበር። የሕይወትን ሩጫ በጽናት ለመሮጥ ቆርጠው ነበር። አንተም ይሖዋ በስሙ ላይ የተሰነዘረውን ነቀፋ ሲያስወግድ፣ ሉዓላዊነቱ ትክክለኛ መሆኑን ሲያረጋግጥና ቃል የገባቸውን ነገሮች በሙሉ ሲፈጽም ለማየት በጣም እንደምትጓጓ ጥርጥር የለውም። እነዚህ ነገሮች ይሖዋ በወሰነው ጊዜ እንደሚፈጸሙ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። እስከዚያው ድረስ ግን በአምላክ አገልግሎት እንጠመድ፤ እንዲሁም የምንጠብቀው ነገር ባሰብነው ጊዜ አለመፈጸሙ ተስፋ እንዲያስቆርጠን አንፍቀድ። w19.08 4-5 አን. 9-10
ሐሙስ፣ ግንቦት 20
እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ።—ማቴ. 11:29
ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘ሌሎች የሚመለከቱኝ ገርና ትሑት እንደሆንኩ አድርገው ነው? ሌሎችን ለማገልገል ስል ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን ለመሥራት ፈቃደኛ ነኝ? ለሰዎች ደግነት አሳያለሁ?’ ኢየሱስ ተከታዮቹ ከእሱ ጋር ሲሠሩ ሰላምና ደስታ እንዲያገኙ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ እነሱን ማሠልጠን ያስደስተው ነበር። (ሉቃስ 10:1, 19-21) ደቀ መዛሙርቱን ጥያቄ እንዲጠይቁ ያበረታታቸው የነበረ ሲሆን እነሱ የሚሰጡትን ሐሳብ የመስማት ፍላጎትም ነበረው። (ማቴ. 16:13-16) በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ አመቺ በሆነ ቦታ ላይ እንደተተከለ ተክል ሊያብቡ ችለዋል። ኢየሱስ ያስተማራቸውን ትምህርቶች በሚገባ ስለቀሰሙ መልካም ሥራዎችን በመሥራት ፍሬ ለማፍራት በቅተዋል። ኃላፊነት ያለህ ሰው ነህ? ከሆነ ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ፦ ‘አብረውኝ የሚሠሩትን ሰዎች ወይም የቤተሰቤን አባላት የምይዘው እንዴት ነው? ሰላማዊ ሁኔታ እንዲሰፍን አደርጋለሁ? ሌሎች ጥያቄ እንዲጠይቁ አበረታታለሁ? እነሱ የሚሰጡትን ሐሳብ ለመስማትስ ፈቃደኛ ነኝ?’ ጥያቄ የሚጠይቋቸውን ሰዎች የሚጠሉትንና ከእነሱ የተለየ ሐሳብ የሚሰነዝሩ ሰዎችን እንደ ጠላት አድርገው የሚመለከቱትን ፈሪሳውያንን መምሰል ፈጽሞ እንደማንፈልግ የታወቀ ነው።—ማር. 3:1-6፤ ዮሐ. 9:29-34፤ w19.09 20 አን. 1፤ 23 አን. 9-11
ዓርብ፣ ግንቦት 21
“ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ሲሉ ምጥ እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል።—1 ተሰ. 5:3
አንዳንድ ጊዜ የዓለም መሪዎች በአገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ስለ ማሻሻል ሲናገሩ እንደነዚህ ያሉ አገላለጾችን ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸው “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” የሚለው አዋጅ ከዚህ የተለየ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ይህ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት ብዙ ሰዎች፣ በዓለም ላይ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ የዓለም መሪዎች እንደተሳካላቸው ይሰማቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በዚያ ወቅት ‘ታላቁ መከራ’ ስለሚጀምር “ያልታሰበ ጥፋት” ይመጣል። (ማቴ. 24:1) ይህ አዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት የሚሆኑትን ነገሮች ወይም አዋጁ የሚታወጅበትን መንገድ አናውቅም። አዋጁ የሚተላለፈው በአንድ ማስታወቂያ አማካኝነት ነው? ወይስ በተከታታይ በሚነገሩ መግለጫዎች? ይህን በተመለከተም የምናውቀው ነገር የለም። በዚያ ጊዜ የሚኖረው ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ የዓለም መሪዎች በእርግጥ ዓለም አቀፍ ሰላም እንዳስገኙ በማሰብ መታለል የለብንም። እንዲያውም ይህ አዋጅ መነገሩ “የይሖዋ ቀን” ሊጀምር መሆኑን የሚጠቁም ምልክት ነው!—1 ተሰ. 5:2፤ w19.10 8-9 አን. 3-4
ቅዳሜ፣ ግንቦት 22
በዚያን ወቅት ሕዝብህ . . . ይተርፋል።—ዳን. 12:1
የአርማጌዶን ጦርነት፣ የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ታላቅ ፍጻሜ ይሆናል። ይሁንና አርማጌዶንን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። ለምን? ምክንያቱም አርማጌዶን የአምላክ ጦርነት ነው። (ምሳሌ 1:33፤ ሕዝ. 38:18-20፤ ዘካ. 14:3) ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ይሖዋ የሚሰጠውን መመሪያ በመከተል ሠራዊቱን ለውጊያ ያዘምታል። ከሞት የተነሱ ቅቡዓንና እልፍ አእላፋት መላእክት አብረውት ይሆናሉ። በአንድነት ሆነው ከሰይጣን፣ ከአጋንንቱና በምድር ላይ ካሉት ግብረ አበሮቻቸው ጋር ይዋጋሉ። (ራእይ 6:2፤ 17:14) ይሖዋ፣ ሕዝቦቹን “ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ [እንደሚከሽፍ]” ዋስትና ሰጥቶናል። (ኢሳ. 54:17) “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የሚሆኑ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ‘ታላቁን መከራ በሕይወት ያልፋሉ!’ ከዚያ በኋላም ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረባቸውን ይቀጥላሉ። (ራእይ 7:9, 13-17) በእርግጥም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው ሐሳብ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንድንጠባበቅ የሚያደርግ ነው! ‘ይሖዋ ታማኞችን እንደሚጠብቅ’ እናውቃለን! (መዝ. 31:23) ይሖዋን የሚወዱና እሱን የሚያወድሱ ሁሉ ቅዱስ ስሙን ከነቀፋ ነፃ ሲያደርግ በማየት ይደሰታሉ።—ሕዝ. 38:23፤ w19.10 18-19 አን. 17-18
እሁድ፣ ግንቦት 23
እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው።—ምሳሌ 17:17
‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ማብቂያ ይበልጥ እየተቃረበ ሲሄድ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። (2 ጢሞ. 3:1) ለምሳሌ ያህል፣ በምዕራብ አፍሪካ ባለች አንዲት አገር ውስጥ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ አገሪቱ በነውጥና በዓመፅ ታመሰች። በግጭቱ የተነሳ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከስድስት ወር ለሚበልጥ ጊዜ በነፃነት መንቀሳቀስ አልቻሉም ነበር። ታዲያ ይህን ከባድ ሁኔታ እንዲቋቋሙ የረዳቸው ምንድን ነው? አንዳንዶቹ፣ የተሻለ መረጋጋት ባለበት አካባቢ በሚኖሩ ወንድሞቻቸው ቤት አረፉ። አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ያለ ሁኔታ ባጋጠመኝ ወቅት፣ የሚያስጠጉኝ ወዳጆች ያሉኝ በመሆኑ በጣም ተደስቼ ነበር። እርስ በርስ ተበረታተናል።” ‘ታላቁ መከራ’ ሲጀምር፣ የሚወዱን ጥሩ ወዳጆች ካሉን እንደምንደሰት ጥያቄ የለውም። (ራእይ 7:14) በመሆኑም ከአሁኑ ወዳጅነታችንን ማጠናከራችን በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ጴጥ. 4:7, 8) ለምን? ምክንያቱም ጠላቶቻችን ውሸትና የተሳሳተ መረጃ በመጠቀም እኛን ለመከፋፈል መሞከራቸው አይቀርም። በመካከላችን መተማመን እንዳይኖር ለማድረግ ይጥራሉ። ሆኖም የሚያደርጉት ጥረት ትርፉ ልፋት ብቻ ነው። በመካከላችን ያለውን ጠንካራ ፍቅር ማጥፋት አይችሉም። w19.11 2 አን. 1-2፤ 7 አን. 19
ሰኞ፣ ግንቦት 24
የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ማምከን [ትችላላችሁ]።—ኤፌ. 6:16
“የውሸት አባት” የሆነው ሰይጣን በእሱ ቁጥጥር ሥር ባሉት ሰዎች በመጠቀም ስለ ይሖዋ እንዲሁም ስለ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሐሰት ወሬ ያዛምታል። (ዮሐ. 8:44) ለምሳሌ ከሃዲዎች በኢንተርኔት፣ በቴሌቪዥንና በሌሎች መገናኛ ብዙኃን በመጠቀም ስለ ይሖዋ ድርጅት የሐሰት ወሬዎችንና የተዛቡ መረጃዎችን ያሰራጫሉ። እነዚህ ውሸቶች የሰይጣን ‘የሚንበለበሉ ፍላጻዎች’ ናቸው። አንድ ሰው እንዲህ ያሉ የሐሰት ወሬዎችን ሊነግረን ቢሞክር ምን ማድረግ ይኖርብናል? ፈጽሞ ልንሰማው አይገባም! ለምን? ምክንያቱም በይሖዋ ላይ እምነት አለን፤ በወንድሞቻችንም እንተማመናለን። እንዲያውም ከከሃዲዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዲኖረን አንፈልግም። ምን እንደሚሉ ለማወቅ በመጓጓትም እንኳ ስለ ማንኛውም ጉዳይ ከእነሱ ጋር ለመከራከር ፈቃደኞች አንሆንም፤ ማንም ሰው ወይም ምንም ነገር እምነታችንን እንዲያዳክመው አንፈቅድም። የከሃዲዎችን የሐሰት ወሬ ለመስማት ወይም ከእነሱ ጋር ለመከራከር ብትፈተንም ፈተናውን መወጣት ችለሃል? ይህ የሚያስመሰግን ነው። ያም ቢሆን መዘናጋት የለብህም፤ ምክንያቱም ሰይጣን እኛን ለማጥቃት የሚጠቀምባቸው ሌሎች ዘዴዎችም አሉ። w19.11 15 አን. 8፤ 16 አን. 11
ማክሰኞ፣ ግንቦት 25
ይሖዋ . . . ውስጣዊ ዓላማን ይመረምራል።—ምሳሌ 16:2
ውሳኔ ስታደርግ የተነሳሳህበትን ዓላማ ገምግም። ይሖዋ በሁሉም ነገር ሐቀኞች እንድንሆን ይፈልጋል። ስለዚህ አንድን ውሳኔ ለማድረግ የተነሳሳንበትን ትክክለኛ ዓላማ በሐቀኝነት መመርመር ይኖርብናል። እንዲህ ካላደረግን በውሳኔያችን መጽናት ሊከብደን ይችላል። አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ አንድ ወጣት ወንድም የዘወትር አቅኚ ለመሆን ወሰነ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን የሰዓት ግቡ ላይ መድረስ የከበደው ከመሆኑም ሌላ ከአገልግሎቱ የሚያገኘው ደስታም እየቀነሰ ሄደ። ይህ ወንድም አቅኚ ለመሆን ያነሳሳው ዋነኛ ምክንያት ይሖዋን ለማስደሰት ያለው ፍላጎት እንደሆነ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ዋነኛ ምክንያቱ ወላጆቹን ወይም አንድ የሚያደንቀውን ሰው ለማስደሰት ያለው ፍላጎት ይሆን? ሲጋራ ማጨሱን ለማቆም የወሰነን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትም እናስብ። ለአንድ ወይም ለሁለት ሳምንት ያህል እንደምንም ታግሎ ሱሱን መቆጣጠር ቢችልም በኋላ ላይ አገረሸበት። ውሎ አድሮ ግን ይህን ልማዱን በማሸነፍ ረገድ ተሳካለት! ለይሖዋ ያለው ፍቅርና እሱን ለማስደሰት ያለው ፍላጎት ይህን ልማዱን ለማሸነፍ ረድቶታል።—ቆላ. 1:10፤ 3:23፤ w19.11 27 አን. 9፤ 29 አን. 10
ረቡዕ፣ ግንቦት 26
ዜጎች እንደመሆናችሁ መጠን ስለ ክርስቶስ ከሚገልጸው ምሥራች ጋር በሚስማማ መንገድ ኑሩ።—ፊልጵ. 1:27 ግርጌ
ሐዋርያው ጳውሎስ ሩጫውን እንደሚያጠናቅቅና ግቡ ላይ እንደሚደርስ እርግጠኛ ነበር። ቅቡዕ ክርስቲያን እንደመሆኑ መጠን “የሰማያዊውን ሕይወት ሽልማት” እንደሚያገኝ ይጠብቅ ነበር። ሆኖም ጳውሎስ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ምንጊዜም ‘መጣጣር’ እንዳለበት ያውቅ ነበር። (ፊልጵ. 3:14) ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ምንጊዜም ግባቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ለመርዳት ግሩም ንጽጽር ተጠቅሟል። ጳውሎስ፣ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችን “የሰማይ ዜጎች” እንደሆኑ አስታውሷቸዋል። (ፊልጵ. 3:20) ይህን ማስታወሳቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በዚያ ዘመን የሮም ዜግነት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ግን ከዚህ የላቀ ዜግነት የነበራቸው ሲሆን ይህም ከሮም ዜግነት የበለጡ ጥቅሞች ያስገኝላቸዋል። ከዚህ አንጻር የሮም ዜግነት ከቁጥር የሚገባ ነገር አልነበረም። በዛሬው ጊዜ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ግባቸው ላይ ለመድረስ ምንጊዜም በመጣጣር ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። w19.08 6-7 አን. 14-15
ሐሙስ፣ ግንቦት 27
ወልድ ነፃ ካወጣችሁ፣ በእርግጥ ነፃ ትሆናላችሁ።—ዮሐ. 8:36
ይህ ነፃነት በእስራኤል ይከበር የነበረው የኢዮቤልዩ ዓመት ከሚያስገኘው ነፃነት እጅግ የላቀ እንደሆነ ጥርጥር የለውም! (ዘሌ. 25:8-12) አንድ ምሳሌ እንውሰድ፦ በኢዮቤልዩ አማካኝነት ከባርነት ነፃ የወጣ ሰው መልሶ ባሪያ ሊሆን ይችላል፤ ደግሞም ይህ ሰው ከሞት ባርነት ማምለጥ አይችልም። በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት፣ ይሖዋ ሐዋርያትን እንዲሁም ሌሎች ታማኝ ወንዶችንና ሴቶችን በመንፈስ ቅዱስ ቀባቸው። ልጆቹ አድርጎ የተቀበላቸው ሲሆን ይህም ከጊዜ በኋላ ትንሣኤ አግኝተው በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ለመግዛት ያስችላቸዋል። (ሮም 8:2, 15-17) እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ በናዝሬት በሚገኘው ምኩራብ ካወጀው ነፃነት የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚዎች ናቸው። (ሉቃስ 4:16-19, 21) እነዚያ ወንዶችና ሴቶች፣ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ከሚያስተምሯቸው የሐሰት ትምህርቶችና ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ወጎች ባርነት ነፃ ወጥተዋል። በተጨማሪም አምላክ፣ እነዚህን ሰዎች ወደ ሞት ከሚመራው የኃጢአት ባርነት ነፃ እንደወጡ አድርጎ ቆጥሯቸዋል። ምሳሌያዊው ኢዮቤልዩ የጀመረው በ33 ዓ.ም. የክርስቶስ ተከታዮች በመንፈስ ቅዱስ ሲቀቡ ሲሆን በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ ያበቃል። w19.12 11 አን. 11-12
ዓርብ፣ ግንቦት 28
መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል።—1 ቆሮ. 15:33
ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ጥሩ ጓደኞች እንዲመርጡ እርዷቸው። እናቶችም ሆኑ አባቶች፣ ልጆቻቸው ከእነማን ጋር እንደሚቀራረቡና ከእነሱ ጋር ሲሆኑ ምን እንደሚያደርጉ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ይህም ልጆቻቸው በማኅበራዊ ድረ ገጾችና በሞባይል ስልኮቻቸው አማካኝነት ከእነማን ጋር እንደሚገናኙ ማወቅን ይጨምራል። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በልጆቹ አስተሳሰብና ድርጊት ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም። ብዙ ወላጆች፣ ልጆቻቸው አምላክን በማገልገል ረገድ ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኑ ክርስቲያኖች ጋር መቀራረብ የሚችሉበትን አጋጣሚ ለመፍጠር ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በኮት ዲቩዋር የሚኖሩት ነደኒ እና ቦሚን የተባሉ ባልና ሚስት፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ብዙ ጊዜ ቤታቸው እንዲያርፍ ያደርጉ ነበር። ነደኒ “ይህ በልጃችን ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ከጊዜ በኋላ ልጃችን አቅኚነት ጀመረ፤ አሁን ደግሞ ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ እያገለገለ ነው” ሲል ተናግሯል። ወላጆች ልጆቻቸውን ገና ከሕፃንነታቸው ማሠልጠን መጀመራቸው የተሻለ ነው። (ምሳሌ 22:6) የጢሞቴዎስን ሁኔታ ለማሰብ ሞክሩ። እናቱ ኤውንቄ እና አያቱ ሎይድ ጢሞቴዎስን ‘ከጨቅላነቱ’ ጀምሮ አሠልጥነውታል።—2 ጢሞ. 1:5፤ 3:15፤ w19.12 25 አን. 14፤ 26 አን. 16-17
ቅዳሜ፣ ግንቦት 29
ከወንድም ይበልጥ የሚቀርብ ጓደኛ አለ።—ምሳሌ 18:24
ታማኝ ወዳጅ ሁኑ። ለምሳሌ፣ ችግር የገጠማቸውን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንደምንረዳቸው ቃል በመግባት ብቻ ሳንወሰን እነሱን በተግባር መርዳት ይኖርብናል። (ማቴ. 5:37፤ ሉቃስ 16:10) እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ወንድሞች በቃላችን እንደምንገኝ ማወቃቸው በእጅጉ ያጽናናቸዋል። አንዲት እህት ይህ የሆነበትን ምክንያት ስትገልጽ “‘እንደሚረዳን ቃል የገባልን ሰው በሰዓቱ መጥቶ የተናገረውን ነገር ይፈጽም ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ ሌላ ሐሳብ አይጨምርባችሁም” ብላለች። አስቸጋሪ ሁኔታ ወይም ያልጠበቁት መጥፎ ነገር ያጋጠማቸው ሰዎች፣ እምነት ለሚጥሉበት ወዳጃቸው የልባቸውን አውጥተው መናገራቸው ብዙውን ጊዜ ያጽናናቸዋል። ሆኖም ሌሎች እምነት የሚጥሉብንና ሚስጥራቸውን የሚያካፍሉን ወዳጅ ለመሆን ትዕግሥትን ማዳበር ያስፈልገናል። ዣና ባለቤቷ ጥሏት በሄደበት ወቅት ለቅርብ ወዳጆቿ ስሜቷን አውጥታ መናገሯ አጽናንቷታል። “አንድ ዓይነት ነገር በተደጋጋሚ ጊዜ ብናገርም እንኳ በትዕግሥት ያዳምጡኝ ነበር” ብላለች። አንተም ጥሩ አድማጭ በመሆን እውነተኛ ወዳጅ መሆንህን ማሳየት ትችላለህ። w20.01 10-11 አን. 9-11
እሁድ፣ ግንቦት 30
ከመወለዱ በፊት እንኳ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል።—ሉቃስ 1:15
መንፈስ ቅዱስ የተሰጣቸው በርካታ የእምነት ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰዋል፤ ያም ሆኖ እነዚህ ሰዎች በሰማይ የመኖር ተስፋ አልነበራቸውም። ዳዊት ከመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያገኘ ሰው ነበር። (1 ሳሙ. 16:13) መንፈስ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ጥልቅ ነገሮች መረዳት እንዲችል እንዲሁም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን እንዲጽፍ ረድቶታል። (ማር. 12:36) ያም ቢሆን ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደተናገረው ዳዊት “ወደ ሰማያት አልወጣም።” (ሥራ 2:34) መጥምቁ ዮሐንስም ‘በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ’ ሰው ነበር። (ሉቃስ 1:13-16) ኢየሱስ፣ ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ሰው እንዳልተነሳ ተናግሯል፤ ይሁንና የሰማያዊው መንግሥት ወራሽ እንደማይሆን ገልጿል። (ማቴ. 11:10, 11) ይሖዋ ለእነዚህ ወንዶች ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት አስደናቂ ነገሮችን ማከናወን እንዲችሉ ረድቷቸዋል፤ ሆኖም በሰማይ ሕይወት እንዲያገኙ በመንፈሱ አማካኝነት አልመረጣቸውም። ታዲያ እነዚህ ሰዎች በበቂ መጠን ታማኝ አልነበሩም ማለት ነው? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ፣ ከሞት ተነስተው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር ተስፋ ሰጥቷቸዋል ማለት ነው።—ዮሐ. 5:28, 29፤ ሥራ 24:15፤ w20.01 23 አን. 15
ሰኞ፣ ግንቦት 31
እሱ አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን።—1 ዮሐ. 4:19
ይሖዋ የእሱን አገልጋዮች ያቀፈው ቤተሰብ አባል እንድንሆን ጋብዞናል። የዚህ ቤተሰብ አባላት፣ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑና በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች ናቸው። ቤተሰባችን ደስተኛ ነው። በዛሬው ጊዜ ትርጉም ያለው ሕይወት የምንመራ ከመሆኑም ሌላ ወደፊት በሰማይ ወይም ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ስላለን ደስተኞች ነን። ይሖዋ ከፍተኛ መሥዋዕት መክፈል ቢጠይቅበትም በፍቅር ተነሳስቶ የቤተሰቡ አባል መሆን የምንችልበትን መንገድ ከፍቶልናል። (ዮሐ. 3:16) በእርግጥም ‘በዋጋ ተገዝተናል።’ (1 ቆሮ. 6:20) ይሖዋ በቤዛው አማካኝነት ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት የምንችልበት አጋጣሚ ሰጥቶናል። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀውን አካል፣ አባታችን ብለን የመጥራት መብት አግኝተናል። ደግሞም እንደ ይሖዋ ያለ አባት የለም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንዳለው “ላደረገልኝ መልካም ነገር ሁሉ ለይሖዋ ምን እመልስለታለሁ?” ብለን እንጠይቅ ይሆናል። (መዝ. 116:12) እንደ እውነቱ ከሆነ መቼም ቢሆን የሰማያዊ አባታችንን ውለታ መክፈል አንችልም። ያም ቢሆን እሱ ያደረገልን ነገር በምላሹ እንድንወደው ያነሳሳናል። w20.02 8 አን. 1-3