የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 1/1 ገጽ 25-29
  • የሚያስደስት ጽናት በመካከለኛው ምሥራቅ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የሚያስደስት ጽናት በመካከለኛው ምሥራቅ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • “ጠቃሚ ጎኑ”
  • “የይሖዋ ስም ሕይወቴን አዳነልኝ”
  • “የይሖዋ ጥበቃ በዙሪያችን ነበር”
  • አስቸኳይ እርዳታ ተደረገ!
  • “እናንተ ምን ዓይነት ሕዝቦች ናችሁ?”
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 1/1 ገጽ 25-29

የሚያስደስት ጽናት በመካከለኛው ምሥራቅ

ይህ ስሜት የሚነካ ሪፖርት የመጣው በሊባኖስ ከሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ነው።

የ1990ው የአገልግሎት ዓመታችን የጀመረው በቤይሩት ላይ በወረደ ኃይለኛ የመድፍ ድብደባ ነበር። ከዚያም ከመስከረም 1989 መጨረሻ አንስቶ እስከ ጥር 1990 የቆየ የተረጋጋ ሁኔታ ቀጠለ።

በ1989 የአገልግሎት ዓመት ከነበረው 2,467 የአስፋፊዎች ቁጥር ጋር ሲወዳደር በነዚያ ወራት የተገኘው አዲስ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር (በህዳር ወር) 2,659 ደርሶ ነበር። አርባ አራት ሰዎች ተጠምቀዋል፤ በየወሩም በአማካይ 65 አስፋፊዎች በረዳት አቅኚነት አገልግሎት ተካፍለዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ከ2,000 በላይ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንደተመሩ ሪፖርት ተደርጓል። ለመጪው ጊዜ ምን ነገሮች እንደሚከናወኑ በጉጉት መጠባበቅ ጀምረናል።

ይሁን እንጂ ብዙ ጉባኤዎች በሚገኙበት በቤይሩት ጦርነቱ እንደገና በመፈንዳቱ ብዙ ወንድሞች ወደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች መሸሽ አስፈልጓቸዋል። ለብዙ ቀናትም ጉዳቱ በደረሰበት ቦታ ከሚገኙት ጉባኤዎች ጋር ምንም ግንኙነት ወይም መጠያየቅ ልናደርግ አልቻልንም ነበር። የመስክ ሪፖርቶችም ያልተሟሉ ነበሩ። ይሁን እንጂ የተበተኑት ወንድሞች በሸሹባቸው አካባቢዎች ካሉ ጉባኤዎች ጋር ተገናኝተው ነበር። መልካም ውጤቶችን የሚያስገኘው ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎትም በአገሪቱ በሙሉ ቀጠለ። እስከዚያ ድረስ ግን የብዙዎቹ ወንድሞቻችን ቤቶች በቦምብ ተደብድበው ተቃጥለው ወይም ጉዳት ደርሶባቸው ነበር። አንዲት እህትም ሕይወቷን አጥታለች።

እርዳታና አመራር ለማግኘት በትምክህት ወደ ይሖዋ ተመልክተን ነበር። ደፋር የሆኑ አቅኚዎች በተከበቡት አካባቢዎች ለሚገኙ ወንድሞቻችን ከምግብና ውሃ ጋር መንፈሳዊ ስንቆችን ለማድረስ በፈቃደኝነት ራሳቸውን አቀረቡ። ለይሖዋና ለወንድሞቻቸው ባላቸው ፍቅር በመገፋፋት ቦምብ የተቀበረባቸውን መንገዶች ለማቋረጥ እንኳን ሳይቀር በሕይወታቸው ቆረጡ። ለወንድሞቻችን ቤተሰቦች የሚመጣውን እርዳታ በአካባቢው ያሉ ሰዎች ይመለከቱ ስለ ነበር ጥሩ የሆነ ምሥክርነት ለመስጠት ተቻለ። ሁሉም በእውነተኛው አንድ አምላክ በይሖዋ አምልኮ የተባበሩ በመሆናቸው እውነተኛ ፍቅር ምን ሊሠራ እንደሚችል ተመልከቱ።​—ዮሐንስ 13:34, 35፤ 15:13

በዚህ የአገልግሎት ዓመት ውስጥ ወንድሞቻችን አንድም የመጽሔታችን እትም አላመለጣቸውም። እንደ መጠበቂያ ግንብ ሁሉ ንቁ! መጽሔትም ከጥር 8, 1990 ጀምሮ በአረብኛ ቋንቋ ከእንግሊዝኛው ጋር አንድ ላይ መውጣት ጀምሯል። ምሥክሮችና ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችም ከመጠን በላይ ተደስተዋል። በሥላሴ ማመን አለብህን? የሚባለውን ብሮሹርና መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን የያዘው መጽሐፌ የመሳሰሉትን አዳዲስ ጽሑፎች በአረብኛ ቋንቋ ማየቱም በደስታ የሚያስፈነድቅ ነበር።

ምንም እንኳን በቤሩት ብዙ ፋብሪካዎችና ተቋሞች እየተዘጉ ቢሆንም እነዚህ መንፈሳዊ ስጦታዎች ሊዘጋጁ ችለዋል። በመላዋ አገሪቱ ውስጥ ያለው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ተበላሽቷል። ብዙዎቹ ቦታዎች የኤሌክትሪክ መብራት፣ የውሃ፣ እንዲሁም የቴሌፎን አገልግሎት የላቸውም። ጦርነቱ ለአሥራ አምስት ዓመታት ሲካሄድ ካስከተለው ጥፋት ጋር እየታገሉ ደስታ እንዴት ሊያገኙ እንደቻሉ እስቲ አንዳንድ ወንድሞች ይንገሩን።

“ጠቃሚ ጎኑ”

በቤሩት የሚኖር ወንድም እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “ከሁሉ አስቀድሜ የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም በንጹሕ የአምልኮ ድርጅት ውስጥ ጠብቆ ላቆየን ለይሖዋ ልባዊ ምስጋና አቀርባለሁ። በቅርቡ በተፈጸሙት ሁኔታዎች ውስጥ ደስታን ያመጡልኝ አንዳንድ ተሞክሮዎች አሉ። እነዚህንም የጦርነቱ ጠቃሚ ጎን እንደሆኑ እቆጥራቸዋለሁ።

“በከባዱ የቦምብ ድብደባ ወቅት የመድፍ ድብደባ ሲደረግ የተሻለ ቦታ በመሆኑ ከጎረቤቶቻችን ጋር በደረጃዎች ላይ እንቀመጥ ነበር። ለሰው ዘር ችግሮች ብቸኛዋ መፍትሔ የአምላክ መንግሥት መሆኗንም ሳናቋርጥ እንነግራቸዋለን። ወደ አምላካችን ወደ ይሖዋም በተደጋጋሚ እንጸልይ ነበር። ይህም በሁሉም ዘንድ የታወቀ ሆነ።

“አንዳንድ ጊዜ ድብደባው ለተከታታይ ቀናት ይቆይ ስለነበር በስብሰባዎች ላይ መገኘት አንችልም ነበር። ስለዚህ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ይዤ እወጣና በደረጃዎቹ ላይ ተቀምጠን እናጠናው ነበር። ይህም የጎረቤቶቻችን ፍላጎት አነሣሣ፤ ከእነሱ አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆንን ብቻ አያነጋግሩንም ነበር። ይሁን እንጂ ቤታችን በቦምብ በተመታበት ጊዜ ወንድሞቻችን ባሳዩት ፍቅር በጣም ተገረሙ። አሁን ከእኛ ጋር መነጋገር ፈለጉ። ይህም ጥቂት የንቁ! መጽሔቶችን እንድናበረክትላቸው አስቻለን።

“እነዚህ ተሞክሮዎች ስለ እውነት መናገሬን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እንዳደርግ አስችለውኛል። ለይሖዋ ሁሉም አምልኮታችንና ሁሉም ክብር ይገባዋል።”

“የይሖዋ ስም ሕይወቴን አዳነልኝ”

የራስ ቤሩት ጉባኤ አባል የሆነ አንድ ወንድም እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል፦ “ሚስቴ፣ ሁለት ትናንሽ ወንዶች ልጆቼና እኔ ዕለቱን በምዕራባዊው ቤይሩት ክፍል ባደረግነው ከቤት ወደቤት አገልግሎት ጀመርነው። ከሰዓት በኋላ በቤቴ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ጉባኤ ነበረን። ከምሽቱ በ12:30 ላይ ቀኑ ጭልም ብሏል። በጎዳናው ላይ የሚታዩት የጦር መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች ብቻ ናቸው። ቦምቦች ይዘንባሉ። በሕንፃችን ያሉ አብዛኞቹ ነዋሪዎች ሸሽተዋል። ውሃም ሆነ መብራት አልነበረም። ከዚያም በራችን ሲንኳኳ ሰማን።

“ውሃ ወይም ዳቦ የሚፈልግ ከጎረቤቶቻችን አንዱ ይሆናል ብላ በማሰብ ሚስቴ በሩን ከፈተች። በደጅ የቆሙት አራት የጦር መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች ነበሩ። ጠመንጃዎቻቸውን በሚስቴ ላይ በመደገን እኔን በስሜ ጠርተው ጠየቋት። በዚያ ሳምንት ውስጥ ዘጠኝ ሰዎች በዚህ አኳኋን ከቤታቸው ተወስደው ወዲያዉኑ ተገድለዋል። ባለ ትጥቆቹ ሰዎች እኔን ሲያዩ አውቶማቲክ ሽጉጦቻቸውን በራሴ ላይ ደገኑና ከእነሱ ጋር እንድሄድ አዘዙኝ። ‘እሺ እሄዳለሁ፣ መጀመሪያ ግን ልብሴን እንድለብስ ፍቀዱልኝ’ አልኳቸው። እርዳታውን ለመለመን በሙሉ ልቤ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ጸሎቴን እንደጨረስኩ በጣም ተረጋጋሁና እነዚህን የታጠቁና የሚያስፈሩ ሰዎች እንደተራ ሰዎች መመልከት ጀመርኩ። ያለ ፍርሃት ከእነርሱ ጋር መነጋገር ቻልኩ።

“እንዲህ ብዬ ጠየቅኋቸው፦ ‘ከእኔ የምትፈልጉት ምንድን ነው? ከመሄዳችን በፊት እቤት ቁጭ ብለን ትንሽ እንነጋገር!’ ወደቤት ከገቡ በኋላ አለቃቸው እንዲህ ሲል ጠየቀኝ፦ ‘ወደየቤቱ እየገባህ ለሰዎች ለመስበክ ምን መብት አለህ?’ እኔም እንዲህ ስል መለስኩላቸው፦ ‘እናንተ ፈቃዳችሁን ለማስፈጸም ጠመንጃ ይዛችኋል። በፊታችሁም ለመቆም የሚደፍር የለም። እኔ ደግሞ ኢየሱስ እንድንሰብክ ያዘዘንን የሰላም ወንጌል ይዣለሁ።’ ከዚያም የይሖዋ ምሥክሮችን እምነትና ሥራ ገለጽኩላቸው። ይሖዋ የሚለውን ስም ስጠቅስ እንዲህ አሉ፦ ‘እዚሁ ብንመረምርህ በቂያችን ነው። ከእኛ ጋር መሄድ አያስፈልግህም።’ እንደተረዳሁት ከእነሱ አንዱ የሚያውቀው አንድ ወንድም አለ። ስለዚህ ‘ይኼም እንደ ጃርጆራ ነው’ አላቸው።

“ለእነዚህ መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች በመመስከርና ጥያቄአቸውን በመመለስ አንድ ሰዓት ተኩል አሳለፍን። ከዚያም በሌሎች እንዳደረጉት እኔን በመኪናቸው ዕቃ መጫኚያ ውስጥ ጭነው በመውሰድ ፋንታ ይቅርታ ጠየቁኝ፤ ሳሙኝና እርዳታቸውን የምፈልግ ከሆነ ፈቃደኛነታቸውን ገልጸውልኝ ሄዱ። በዚህ ሁሉ የይሖዋ ጥበቃ እንዳለ ተሰማኝ። በዚያን ዕለት ጠዋት ከቤት ወደ ቤት በተደረገው ሥራ መካፈሌና ከሰዓት በኋላም በስብሰባ መገኘቴ ጸንቼ እንድቆም አበርትቶኛል። በእውነትም የይሖዋ ስም ሕይወቴን አዳነልኝ።”​—ምሳሌ 18:10

“የይሖዋ ጥበቃ በዙሪያችን ነበር”

ሌላ ወንድምም ከቤይሩት እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “ዕለቱ ረቡዕ ጥር 31, 1990 ነበር። ከወንድሜ ጋር ባንዲት እህት ቤት ስሠራ ውጊያው እንደገና ጀመረ። በሁሉም ስፍራ ቦምብ ይፈነዳ ጀመር። የተፋፋመ ውጊያ በመካሄዱ ምክንያት ወደ ቤታችን መመለስ አልቻልንም። ያች እህት የነበራት ጥቂት ቁራሽ ዳቦ ቢሆንም በሚገባ አስተናገደችን።

“ሚስቴ የፊሊፒንስ ተወላጅ በመሆኗና የጦርነትን ሁከት ስላልለመደች ለሷ ተጨንቄ ነበር። ቢሆንም በሁለተኛው ቀን ወደቤቴ መመለስ ቻልኩ። የቤት ቁሳቁሶች ክምር መንገዱን ዘግቶታል። ይሁን እንጂ ለይሖዋ ምሥጋና ይድረሰውና ቤተሰቤ ደህና ነበር። ከጥቂት ጊዜ ጸጥታ በኋላ የቦምብ ድብደባው እንደገና ጀመረ። ከቤታችን አጠገብ ባለ በአንድ ወንድም ቤት ተሸሸግን። አምስታችንም ማለትም ሚስቴ፣ የሁለት ዓመት ወንድ ልጄ ወንድሜና ሚስቱ እዚያው አንድ ላይ ነበርን። ቦምቡና የመድፍ ተኩስ በዙሪያችን ሁሉ ይወድቅ ነበር፤ ይሁን እንጂ የይሖዋ ጥበቃ በዙሪያችን ነበር። የቦምቡን ጭስ እያሸተትን በምድር ላይ እዝያው ተኝተን የሁለቱ ቀን ከባድ የመድፍ ድብደባ አለፈ።

“ፍንዳታውን እያዳመጥን እያለን በመዝሙር 18:1-9, 16-22, 29, 30 ላይ ያሉትን የዳዊትን ቃላት አስታወስን። በእነዚያ አስቸጋሪ ወቅቶችና ሁኔታዎች ሥር ብንሆንም እንኳን ደስተኞች ነበርን፤ ፈገግታም አልተለየንም። መሞት ካለብንም ሳንሰቃይ በቀላሉ እንሞት ዘንድ ወደ ይሖዋ ጸለይን። በትንሣኤ ያለን ተስፋ ጠንካራ ነበር።

“በተከታዩ ቀን የሆነው ጭራሽ የማይታመን ነበር። ወደ ሃያ አምስት የሚሆኑ ቦምቦች በተደበቅንበት ቤት አጠገብ ወደቁ። ሆኖም ማንኛችንም አልተጎዳንም። የይሖዋን ጥበቃ ስናስተውል የተሰማንን ስሜት መገመት ትችሉ ይሆን? በተከታዩ ቀን ጠዋት በቶሎ ለመሸሽ ወሰንን። በጎዳናው ላይ ሳትቃጠል የቀረችው መኪና የኔ ብቻ ነበረች። በተቀበሩና በተጣሉ ቦምቦች መሃል እየነዳሁ አለፍኩ። ለይሖዋ ምስጋና ይድረሰውና የተሻለ መረጋጋት ወዳለው ቦታ ሸሽተን ለማምለጥ ቻልን። እዚያም ወንድሞቻችን በልብስ፣ በምግብና በገንዘብ ፍቅራዊ ቸሮታ አደረጉልን።

“እነዚያን ሁሉ ችግሮች ብናይም ይሖዋ ከእኛ ጋር በመሆኑ ደስታ ይሰማን ነበር። ቦምብ ወደኛ እንዳይቀርብ ለማድረግ መልአኩን የላከ ያህል ነበር። (መዝሙር 34:7) አዎ፣ ደስታችን ታላቅ ነበር። ይሁን እንጂ አርማጌዶንን በሕይወት ስናልፍ ደስታችን ይበልጥ ታላቅ ይሆናል።”

አስቸኳይ እርዳታ ተደረገ!

በቤይሩት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች የምድር መናወጥ የመታቸው መስለዋል። ብዙዎቹ የወንድሞቻችን ቤቶች ተጎድተዋል። ወይም ተደምስሰዋል። በቅርቡ የደረሰው ችግር ሲጀምር ለወንድሞቻችን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማቅረብ የቅርንጫፍ ቢሮው ኮሚቴ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አደራጀ። ችግሩ ወደደረሰባቸው ቦታዎች ልንሄድ በምንችልበት ወቅት ይኸውም በየካቲት 16, 1990 ሥራውን ጀመረ። የኮሚቴው ዓላማ ሦስት ገጽታ ነበረው። ይኸውም ለወንድሞች መንፈሳዊ ማበረታቻ መስጠት፣ የገንዘብ፣ የምግብና የውሃ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላትና፣ ቤቶቻቸውን በመጠገን ወይም እንደገና በመሥራት መርዳት ነበር።

ፈቃደኛ ሠራተኞችን መጥራት አላስፈለገም ነበር። ብዙ ሰዎች በሥራው እርዳታ ለመስጠት በየዕለቱ ማልደው ይመጡ ነበር። እርዳታ የተደረገላቸው ሰዎች ከሰጧቸው አስተያየቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፦

አንዲት እህት ቤቷ ሲጸዳና ሲጠገንላት እንዲህ አለች፦ “አደጋ ሲደርስ በወንድሞች ስለሚሰጠው እርዳታ ሰምቼ ነበር። አሁን ግን ይኸው እኔው ራሴ አየሁት ዳሰስኩትም።” የዚህች እህት ጎረቤት የሆነች አንዲት እስላም ሴትም እንኳን እንዲህ አለች፦ “በእርግጥ እርስ በርስ ትዋደዳላችሁ። እውነተኛው ሃይማኖት የእናንተ ነው። አሁን ወደ ተወለድኩበት ገጠር ሄጄ እዚህ እየሠራችሁት ስላላችሁት ነገር ለሁሉም ሰው እነግራለሁ።” ይህች ጎረቤት የሆነች ሴት ለፈቃደኛ ሠራተኞቹ ምግብ አመጣችላቸው።

አንዲት በዕድሜ የገፋች እህትም እንደሚከተለው ስትል አስተያየቷን ሰጠች፦ “ልትጎበኙኝ እንደምትመጡ ጠብቄ ነበር። ይሁን እንጂ ማህበሩ ውሃ እንዲያመጣልኝ ሰው ይልካል ብዬ አላሰብኩም ነበር።” ሊረዳት የመጣውን ወንድም ስትስመው እንባዋ ይወርድ ነበር።

አንድ ባልና ሚስት የሆኑ ያልተጠመቁ አስፋፊዎችና ትንሽ ወንድ ልጅ አባል ለሆኑበት ቤተሰብ ጉብኝት ተደርጎላቸው አንድ ትልቅ ሣጥን ወተት፣ ዳቦ፣ የመጠጥ ውሃና ገንዘብ ተሰጥቷቸው ነበር። ይህን ዝግጅት ያደረጉት የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ሲነገራቸው ባልዬው እንዲህ አለ፦ “ለአሥራ አንድ ዓመት ንቁ ተሳታፊ የሆንኩ የኢቫንጄሊካል ቤተክርስቲያን አባል ነበርኩ። ይሁን እንጂ በሊባኖስ ጦርነት በተደረገባቸው በእነዚህ አሥራ አምስት ዓመታት ለአባሎቻቸው እንዲህ ዓይነት ነገር ለማድረግ አስበው አያውቁም።” በመቀጠልም “እውነትም የአምላክ ድርጅት ይህ ብቻ ነው።” ባልና ሚስቱ በግንቦት 1990 ተጠመቁ።

አንድ ሽማግሌ እንዲህ ሲል አስተያየቱን ገለጸ፦ “ጉዳት ለደረሰባቸው ወንድሞች ስላደረጋችሁት የፍቅር ሥራዎች ምሥጋናችንን ለመግለጽ ቃላት ያጥሩኛል። ሁሉም ፈቃደኛ ሠራተኞች የሆኑ የወጣት ወንድሞችን ቡድን የወላጆቼን ቤት እንደገና ሲሠሩ ባየሁ ጊዜ በጣም ከመመሰጤ የተነሣ እንባዬ ፈሰሰ። ምሥክሮች ያልሆኑ ጎረቤቶቻችንም እንኳ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ለተሰጠው ተግባራዊ ድጋፍ ለይሖዋና ለድርጅቱ በጣም አመስጋኞች ነን። በመዝሙር 144:15 ላይ የሠፈሩት “ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው” የሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት እንዴት እውነተኞች ናቸው!

“እናንተ ምን ዓይነት ሕዝቦች ናችሁ?”

አንዲት ቤተሰብ ያላት እህት እንዲህ ስትል ጻፈች፦ “ስለ ይሖዋና ስለ ድርጅቱ ፍቅር ያለኝን ጥልቅ አድናቆት ልገልጽ እወዳለሁ። ቤቴ በብዙ የመድፍ ድብደባ ተመትቶ ተቃጥሎ ነበር። ብዙ ሰዎች ሊጠገን እንደማይችል ነገሩን። ይሁን እንጂ ይኸውና አሁን ሙሉ በሙሉ ተጠግኖ በተቃጠሉ ወይም በተጎዱ በመቶ በሚቆጠሩ ቤቶች መሃል ምንም ያልደረሰበት መስሎ ቆሟል።

“የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ጎረቤቶቻችንም እንኳ እንዲህ በማለት እየጠየቁ ነው፦ ‘ይህ ፍቅር ከየት ነው የሚመጣው? እናንተ ምን ዓይነት ሕዝቦች ናችሁ? እነዚህ እንዲህ ጸጥተኛ የሆኑና መልካም ጠባይ ያላቸውና በእንዲህ ዓይነት ቅንዓት የሚሠሩ ግለሰቦች እነማን ናቸው? ይህ ፍቅርና ራስን የመሠዋት መንፈስ የሰጣችሁ አምላክ የተባረከ ይሁን።’ የመዝሙር 84:11, 12 ቃላት እንዴት ተስማሚ ናቸው! ‘(ይሖዋ) ጠባቂያችንና ጋሻችን’ ስለሆነ ሞገስንና ክብርን ይሰጣል። እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም። የሠራዊት አምላክ ሆይ በአንተ የታመነ ሰው ምስጉን (ደስተኛ) ነው።’”

ሚስቱና ልጆቹ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “ቤታችንን ለመጠገን ላደረጋችሁልን እርዳታ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። ሥራችሁ በአሁኑ ጊዜ በጣም ብርቅ የሆነውን እውነተኛ የክርስቲያን ፍቅር አሳይቷል። አምላክ ጥረታችሁን ይባርክላችሁ።”

አንድ ሽማግሌ ቤቱ ከተጠገነለት በኋላ እንዲህ አለ፦ “አፋችን በልባችን ውስጥ ያለውን መግለጽ አይችልም። ለይሖዋና ለድርጅቱ ያለንን አድናቆት ለእናንተ ለመግለጽ ቃላት አናገኝም። ይሖዋ በችግራችን በቅርብ ከእኛ ጋር መሆኑ ተሰምቶናል። ፍቅራችሁ ሁሉንም የቤተሰቤን አባሎች ሌሎችን በሚያስፈልጋቸው በመርዳት እንዲካፈሉ አበረታቷል።”

በሊባኖስ በሚያዝያው ወር 194 ሰዎች በረዳት አቅኚነት ሥራ ተካፍለዋል። የመታሰቢያው ምሽት ከሌሎች ምሽቶች ይልቅ የተረጋጋ ነበር። በመታሰቢያውም በዓል በጠቅላላው 5,034 ሰዎች ተገኝተዋል። የታቀዱት ታላላቅ ስብሰባዎች በሙሉ ተደርገዋል። በአገሪቱ ውስት ምስቅልቅል ሁኔታ ቢኖርም እንኳ በየዓመቱ የተጠመቁት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር 121 ነበር። በጉባኤዎቹ ውስጥ የነበሩ ብዙ ቤተሰቦች አገሪቱን እስከ መጨረሻ ድረስ ለቅቀው ሄደዋል። ይሁን እንጂ ፍላጎት ያሳዩ ብዙ አዳዲስ ሰዎች እስከመጠመቅ ድረስ እድገት በማድረግ ላይ ናቸው። 2,726 የሚሆኑት የመንግሥት አስፋፊዎችም ማደጋቸውን ቀጥለዋል። በ1990ው የአገልግሎት ዓመት በሊባኖስ የሚገኙ ሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች በዚህ ሁከት በበዛበት ጊዜ ውስጥ ሲንከባከበንና ሲመራን በመመልከታቸው የይሖዋን ታማኝነት ለማረጋገጥ አጋጣሚ አግኝተዋል።​—መዝሙር 33:4, 5፤ 34:1-5

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ