የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 1/15 ገጽ 10-15
  • በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት አስተምሩ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት አስተምሩ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሐዋርያዊው ዘዴ
  • ምትክ የማይገኝለት ዘዴ ነው
  • ሽማግሌዎች ግንባር ቀደም መሆን ይኖርባቸዋል
  • እያንዳንዱ ክርስቲያን ምሥክር ነው
  • ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መመሥከር
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2006
  • ከቤት ወደ ቤት የሚከናወነው አገልግሎት በአሁኑ ጊዜ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ያለማሰለስ ከቤት ወደ ቤት መሄድ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1994
  • ምሥራቹን በሚገባ ለመመሥከር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 1/15 ገጽ 10-15

በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት አስተምሩ

“በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት ከማስተማር ዝንፍ አላልኩም።”​—ሥራ 20:20 ባይንግተን ትርጉም

1. አንድ የካቶሊክ ቄስ የይሖዋ ምስክሮች ስለሚያደርጉት የቤት ወደ ቤት አገልግሎት ውጤታማነት ምን ብለዋል?

ዘ ፕሮቪደንስ ሳንደይ ጆርናል የተባለው ጋዜጣ በጥቅምት 4, 1987 እትሙ ላይ “ካቶሊኮች ወንጌልን ከቤት ወደ ቤት እየወሰዱ ነው” የሚል ርዕስ አውጥቶ ነበር። ጋዜጣው እንደዘገበው ይህ ሥራ የተጀመረበት ዋና ዓላማ “ከቀዘቀዙ ምዕመናን አንዳንዶቹን መልሶ ለማንቃት ነው።” በፀጋ ሰበካ የወንጌላዊነት ሥራ ዲሬክተር የሆኑት ቄስ ጆን አላርድ የሚከተለውን እንደተናገሩ ተገልጾአል፦ “ብዙ ትችት እንደሚቀሰቀስ የታወቀ ነው። ሰዎች ‘እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት መሄድ ጀመሩ’ ይሉናል። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ ሥራቸው የተሳካ ውጤት አግኝተዋል። በዚህ ክፍለ ሀገር [በሮድ ደሴት ዩ.ኤስ.ኤ.] ወደ ማንኛውም የመንግሥት አዳራሽ ብትሄዱ ከዚህ ቀደም ካቶሊኮች በነበሩ ሰዎች የተሞሉ ጉባዔዎች እንደምታገኙ እርግጠኛ ነኝ።”

2. ምን ተገቢ ጥያቄ ይነሳል?

2 አዎ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት በሚያደርጉት አገልግሎት በደንብ ታውቀዋል። ይሁን እንጂ ከቤት ወደ ቤት የሚሄዱት ለምንድ ነው?

ሐዋርያዊው ዘዴ

3. (ሀ) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምን ሥራ ሰጥቶአል? (ለ) የጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች የተሰጣቸውን ሥራ የፈጸሙት በምን ዋነኛ ዘዴ ነበረ?

3 ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ የሚከተለውን ከፍተኛ ትርጉም ያለው ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፦ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው። እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28:19, 20) ይህ ሥራ የሚከናወንበት ዋነኛ መንገድ በ33 እ.ዘ.አ. ከዋለው የጴንጠቆስጤ በዓል በኋላ በግልጽ ታወቀ። “ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው [ከቤት ወደ ቤት] ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተውም ነበር።” (ሥራ 5:42) ሃያ ዓመት ከሚያክል ጊዜ በኋላም ሐዋርያው ጳውሎስ ከቤት ወደ ቤት ያገለግል ነበር። በኤፌሶን ከተማ ይኖሩ ለነበሩ ሽማግሌዎች “በጉባዔም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም” ሲል ያሳሰበው በዚህ ምክንያት ነበር።​—ሥራ 20:20

4. ሥራ 5:42 እና ሥራ 20:20 የኢየሱስ ተከታዮች ስብከት ከቤት ወደ ቤት የሚዳረስ መሆኑን ይገልጻሉ ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

4 በሥራ 5:42 ላይ “ከቤት ወደ ቤት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ካትኦይኮን ነው። እዚህ ላይ ካታ የተባለው ቃል በየ__ የሚል ትርጉም አለው። ስለዚህ የደቀመዛሙርቱ ስብከት በየቤቱ ይዳረስ ነበር ማለት ነው። ራንዶልፍ ኤ ዬገር ስለ ሥራ 20:20 ሲያብራሩ የሚከተለውን ጽፈዋል። ጳውሎስ “በሕዝባዊ ስብሰባዎችም [ዴሞሲያ] ሆነ ከቤት ወደ ቤት ([ካታ] የተባለው ጠቃሽ አመልካች ያለበት መስተዋድድ ተጨምሮበታል) አስተምሮአል። ጳውሎስ ሶስት ዓመት ለሚያክል ጊዜ በኤፌሶን ከተማ ኖሮ ነበር። እያንዳንዱን ቤት ጎብኝቶ ነበር፣ ወይም ቢያንስ ቢያንስ ለሁሉም ሰው ሰብኮ ነበር። (ሥራ 20 ቁጥር 26) ይህም ከቤት ወደ ቤት የሚደረገውም ሆነ በሕዝባዊ ስብሰባዎች የሚደረገው ወንጌላዊ ሥራ ትክክል ለመሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ ነው።”

5. ጳውሎስ በሥራ 20:20 ላይ የተናገረው ለሽማግሌዎች ስለተደረገ ማህበራዊ ጥየቃ ወይም ስለ እረኝነት ጥየቃ ነበር ለማለት የማይቻለው ለምንድን ነው?

5 በሉቃስ 8:1 ላይም ካታ በተመሳሳይ ትርጉም ተሠርቶበታል። ኢየሱስ “ከከተማ ወደ ከተማ፣ ከመንደር ወደ መንደር” እንደሰበከ ይናገራል። ጳውሎስ በሥራ 20:20 ላይ የተጠቀመው ካትኦይኩስ የሚለውን የብዙ ቁጥር ነው። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህንን ቃል “በቤታችሁ ውስጥ” ብለው ተርጉመዋል። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ለሽማግሌዎች ማህበራዊ ጥየቃ ወይም ለእምነት ባልደረቦቹ የእረኝነት ጥየቃ ስለማድረጉ ብቻ መናገሩ አልነበረም። ምክንያቱም “ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንሥሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች” መሰከርሁ ብሎአል። (ሥራ 20:21) የእምነት ባልደረቦቹ ቀድሞውኑ ንሥሐ ገብተው በኢየሱስ አምነዋል። ስለዚህ የሐዋርያት ሥራ 5:42ም ሆነ 20:20 የሚናገሩት “ከቤት ወደ ቤት” ወይም ከበር ወደ በር ለማያምኑ ሰዎች ስለመስበክ ነው።

ምትክ የማይገኝለት ዘዴ ነው

6. ጳውሎስ በኤፌሶን ስለፈጸመው የስብከት ሥራ ምን ተብሎአል?

6 አቢል አቦት ሊቨርሞር በ1844 ሐዋርያት ሥራ 20:20 ላይ ስለሚገኘው የጳውሎስ ቃል ሲያብራሩ እንዲህ ጽፈዋል፦ “ታላቁን ሥራውን በየቤቱ ለግለሰቦች በማድረስና የሰማይን እውነት ለኤፌሶን ሰዎች ቃል በቃል በየጎጆአቸውና በየልባቸው ተሸክሞ በመውሰድ በትጋት ይፈጽም ነበር እንጂ በሕዝባዊ ስብሰባዎች ንግግር በማድረግ ብቻ በቃኝ ብሎ ሌሎቹን የመስበኪያ መሣሪያዎች አልተወም።” በቅርብ ጊዜ እንደተገለጸው “ወንጌልን ከቤት ወደ ቤት መስበክ ከመጀመሪያ ጀምሮ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ተለይተው የታወቁበት ሥራ ነበር። (ከሥራ 2:46 እና 5:42 ጋር አወዳድር). . . . [ጳውሎስ] በኤፌሶን ይኖሩ ለነበሩ አይሁዳውያንም ሆን ለአሕዛብ የነበረበትን ኃላፊነት በሚገባ ስለተወጣ እነዚህ ሰዎች ቢጠፉ የሚያመካኙበት ሰበብ አይኖራቸውም።”​—ዘ ዌስልያን ባይብል ኮሜንተሪ ጥራዝ 4 ገጽ 642-3

7. አምላክ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጉትን ከቤት ወደ ቤት አገልግሎት ተቀብሎታል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

7 ለተሰበሰበ ሕዝብ ንግግር ማድረግ ምሥራቹን በማሳወቅ ረገድ የራሱ ቦታ ቢኖረውም በየበራፉ ሰዎችን በግል ለማነጋገር ምትክ ሊሆን አይችልም። በዚህ ረገድ ምሑሩ ጆሴፍ አዲሰን አሌክሳንደር “ቤተክርስቲያን የቤተክርስቲያንና የቤት ውስጥን ስብከት የሚተካ ወይም የሚተካከል ዘዴ አልፈለሰፈችም” ብለዋል። ምሑሩ ኦ.ኤ.ሒልስ እንዳሉት “በሕዝብ ስብሰባ ማስተማርና ከቤት ወደ ቤት ማስተማር ጎን ለጎን መሄድ ይገባቸዋል።” የይሖዋ ምሥክሮች በሣምንታዊ የሕዝብ ስብሰባዎች በሚሰጡ የሕዝብ ንግግሮች አማካኝነት ትምህርት ይሰጣሉ። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከቤት ወደ ቤት የማዳረሱ ሐዋርያዊ ዘዴ ጥሩ ውጤት ስለማስገኘቱ በቂ ማስረጃ አላቸው። ይሖዋም ይህን ሥራ እንደሚደግፈው የተረጋገጠ ነው። ምክንያቱም በዚህ አገልግሎት አማካኝነት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከፍ ወዳለው የአምልኮ ቦታው በየዓመቱ እንዲጎርፉ በማድረግ ላይ ነው።​—ኢሳይያስ 2:1-4፤ 60:8, 22

8. (ሀ) ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎት ውጤታማ ስለሆነበት ምክንያት ምን ተብሎአል? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች በየደጃፉ በሚያደርጉት ስብከትና በሌሎቹ ምሥክርነት የመስጠት ሥራዎች ረገድ ከጳውሎስ ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?

8 ሌላ ባለሥልጣን “ሰዎች በአብያተ ክርስቲያናት ደጆች ከሚሰጣቸው ትምህርት ይልቅ በቤታቸው ደጃፍ የሚሰጣቸውን ትምህርት ማስታወስ ይቀላቸዋል” ብለዋል። ጳውሎስም አዘውትሮ በየደጃፉ በመሄድ ጥሩ የአገልጋይነት አርዓያ ትቶልናል። “በምኩራቦችና በገበያ ቦታዎች በመስበክና ዲስኩር በማድረግ ብቻ በቃኝ ብሎ አያውቅም” ሲሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ኤድዊን ደብልዩ ራይስ ጽፈዋል። “ሁልጊዜ ከቤት ወደ ቤት በትጋት ያስተምር ነበር። በኤፌሶን ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ለመመለስ ከክፋት ጋር ከቤት ወደ ቤት፣ እጅ ለእጅ፣ ፊት ለፊት ተጋድሎአል።” የይሖዋ ምሥክሮች በየደጃፉ ከሰዎች ጋር በነፍስ ወከፍ መነጋገር ውጤታማ መሆኑን ተገንዝበዋል። ከዚህም በላይ ተመላልሶ መጠየቅ ያደርጋሉ። ከተቃዋሚዎች ጋር እንኳን ቢሆን በምክንያታዊነት ሊወያዩ ከፈለጉ ለመነጋገር ፈቃደኞች ናቸው። ልክ እንደ ጳውሎስ ናቸው። ኤፍ ኤን ፔሉቤት ስለ ጳውሎስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የጳውሎስ ሥራ በስብሰባዎች ብቻ የተወሰነ አይደለም። ጠያቂ ሰው ወይም ፍላጎት ያለው ወይም ተቃዋሚ እንኳን ቢሆን ስለ ሃይማኖት ለመነጋገር ፈቃደኛ የሆነ ሰው ሲያገኝ በነፍስ ወከፍ እያነጋገረ በየቤቱ ይዘዋወር እንደነበረ አያጠራጥርም።”

ሽማግሌዎች ግንባር ቀደም መሆን ይኖርባቸዋል

9. ጳውሎስ ለሽማግሌዎች ምን ምሳሌ ትቶአል?

9 ጳውሎስ ለሽማግሌዎች ምን ምሳሌ ትቶአል? ደፋርና ታከተኝ የማይሉ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የምሥራቹን የሚሰብኩ መሆን እንደሚገባቸው አመልክቶአል። ጄ ግሌንትዎርዝ በትለር በ1879 እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ጳውሎስ በሚሰብክበት ጊዜ አደጋ ይደርስብኛል ወይም ሰዎች ምን ይሉኛል ብሎ እንዳላሰበ [የኤፌሶን ሽማግሌዎች] አሳምረው ያውቁ ነበር። አስፈላጊ የሆነውን እውነት ከመናገር ወደኋላ አላለም። ለተወሰነ የእውነት ገጽታ የተለየ አድልዎ ሳያሳይ ለመመገብ ወይም ለማነጽ የሚያስፈልገውን ሁሉና፣ ይህንንም ብቻ ይመክር ነበር። የአምላክን ምክር ሁሉ በሙላትና በጥራት ይናገር ነበር። ይህን የክርስትና እውነት በትጋትና በግለት የማሳየትና የማስተማር ልማዱን በጢራኖስ ትምህርት ቤትና በሌሎች የደቀመዛሙርት መሰብሰቢያ ቦታዎች ሳይወስን ባገኘው ቤት ሁሉ ያዳርስ ነበር። ከዕለት እስከ ዕለት ከቤት ወደ ቤትና ከነፍስ ወደ ነፍስ የክርስቶስን በመሰለ ፍላጎትና ናፍቆት አስደሳቹን ምሥራች ያዳርስ ነበር። ለየትኛውም የሰዎች ክፍልና ነገድ፣ ጠላት ለሆኑ አይሁዳውያንም ሆነ፣ ለአሽሟጣጭ ግሪኮች የስብከቱ ዋና መልዕክት ሕይወት አዳኝ የሆኑትን እውነቶች በሙሉ የሚያጠቃልለው ወደ እግዚአብሔር ንሥሐ መግባትና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ብቻ ነበር።”

10, 11. (ሀ) በክርስቲያናዊ አገልግሎት ረገድ ጳውሎስ ከኤፌሶን ሽማግሌዎች ምን ይጠብቅ ነበር? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሽማግሌዎችም ጭምር የጳውሎስን አርዓያ በመከተል እንዴት ባለው አገልግሎት ይካፈላሉ?

10 ስለዚህ ጳውሎስ ከኤፌሶን ሽማግሌዎች ምን ይጠብቅ ነበር ለማለት ይቻላል? ምሑሩ ኢ ኤስ ያንግ ሐዋርያው የተናገረውን ቃል በራሳቸው ቋንቋ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፣ “ከሁሉም ዐይነት ሰዎች ጋር፣ ከአይሁዳውያንም ሆነ ከአሕዛብ ጋር ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ደከምኩ እንጂ ሰው በተሰበሰበበት ብቻ በመናገር አልተወሰንኩም። ለሁሉም አይነት ሰዎች የሰበክሁት አጠቃላይ መልዕክት ’ወደ እግዚአብሔር ንሥሐ መግባትና በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነበር።’” ደብልዩ ቢ ራይሌ ደግሞ የጳውሎስን ቃል በሌላ አነጋገር ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል፣ “ትርጉሙ ግልጽ ነው፤ ’እኔ የጀመርኩትን እንድትቀጥሉ፣ እኔ ያደረግኩትን እንድታደርጉና እኔ ያስተማርኩትን እንድታስተምሩ እጠብቅባችኋለሁ። በተጨማሪም እኔ የተቃወምኩትን እንድትቃወሙ፣ እኔ እንዳደረግኩ በየመንገዱና ከቤት ወደ ቤት በያደባባዩም እንድታስተምሩና ለአይሁድም ሆነ ለግሪክ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ንሥሐ መግባትንና በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን እንድትመሰክሩ እጠብቅባችኋለሁ። ዋነኞቹ መሠረታዊ ነገሮች እነዚህ ናቸውና።”

11 ጳውሎስ በሥራ ምዕራፍ 20 ላይ እንደ እርሱ ሽማግሌዎች የነበሩት ወንድሞች ከቤት ወደ ቤት የሚሄዱ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲሆኑ ይጠብቅባቸው እንደነበረ ማመልከቱ እንደነበረ ግልጽ ነው። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ሽማግሌዎች በዚህ ረገድ ለተቀሩት የጉባኤ አባሎች ጥሩ አርዓያ በመሆን ግንባር ቀደም መሆን ነበረባቸው። (ከዕብራውያን 13:17 ጋር አወዳድር) ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮችም እንደ ጳውሎስ ለአሕዛብ ሁሉ ስለ አምላክ መንግሥት፣ ወደ አምላክ ንሥሐ ስለመግባትና በኢየሱስ ክርስቶስ ስለማመን እየተናገሩ ከቤት ወደ ቤት ይሰብካሉ። (ማርቆስ 13:10፤ ሉቃስ 24:45-48) በዘመናዊዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚገኙ የተሾሙ ሽማግሌዎችም በዚህ ረገድ ግንባር ቀደም እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል።​—ሥራ 20:28

12. አንዳንድ የቀድሞ ሽማግሌዎች ምን ለማድረግ እምቢተኞች ሆነዋል? በአሁኑ ጊዜ ግን ሽማግሌዎች በየትኛው ሥራ በግምባር ቀደምትነት ይሰማራሉ?

12 ቻርልስ ቴዝ ራስል አሁን የይሖዋን መንግሥት የሚያውጅ መጠበቂያ ግንብ የተባለውንና ያን ጊዜ የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ ይባል የነበረውን መጽሔት በ1879 ማተም ጀመረ። ራስልና ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የመንግሥቱን መልእክት ሐዋርያዊውን ዘዴ በመጠቀም ይናገሩ ነበር። ይሁን እንጂ ቆየት ባሉት ዓመታት አንዳንድ የጉባኤ ሽማግሌዎች የመመስከር ኃላፊነታቸውን ቸል አሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ምስክር እንዲህ በማለት ጽፎአል፣ “ክርስቲያኖች ጽሑፎች ይዘው ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት በተለይም እሁድ እሁድ በሚደረገው ሥራ መካፈል እንደሚኖርባቸው ማስታወቂያ እስከተነገረበት እስከ 1927 ድረስ ሁሉም ነገር በደህና ይቀጥል ነበር። በአባላት ምርጫ የተሾሙት ሽማግሌዎች ተቃወሙትና የጉባኤ አባላት በሙሉ በዚህ ሥራ በምንም ዓይነት እንዳይካፈሉ ለመከልከል ሞከሩ።” ከጊዜ በኋላ ከቤት ወደ ቤት በመስበክ ሥራ የማይካፈሉ ሁሉ በሽምግልና የማገልገል መብታቸው ተወሰደባቸው። ዛሬም ቢሆን በሽምግልናና በዲቁና የሚያገለግሉ ሁሉ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው የምሥክርነት ሥራና በሌሎቹ የክርስቲያናዊ አገልግሎት መስኮች በግንባር ቀደምትነት እንዲካፈሉ ይጠበቅባቸዋል።

እያንዳንዱ ክርስቲያን ምሥክር ነው

13. (ሀ) ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ባይሰሙም እንኳን ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) ጳውሎስ ከሕዝቅኤል ጋር የሚመሳሰለው በምን መንገድ ነው?

13 ክርስቲያኖች ሁሉ የመንግሥቱን መልእክት ሰዎች በአድናቆት ባይቀበሉትም እንኳን በይሖዋ እርዳታ ከቤት ወደ ቤት መስበክ ይኖርባቸዋል። ሕዝቅኤል የአምላክ ጉበኛ እንደመሆኑ መጠን ሰዎች ቢሰሙትም ባይሰሙትም ማስጠንቀቅ ነበረበት። (ሕዝቅኤል 2:5-7፤ 3:11, 27፤ 33:1-6) ኢ ኤም ብሌይክሎክ ሕዝቅኤልንና ጳውሎስን በማነፃፀር የሚከተለውን ጽፈዋል፤ “[ጳውሎስ በሥራ ምዕራፍ 20 ላይ ከተናገረው] በኤፌሶን ስለተከናወነው አገልግሎት በግልጽ ለመረዳት እንችላለን። የሚከተለውን አስተውሉ፣ በመጀመሪያ ደረጃ ጳውሎስ ታማኝ ነበር። በሰዎች ዘንድ ለመወደድ ወይም ዝና ለማትረፍ የሚፈልግ ሰው አልነበረም። ልክ እንደ ሕዝቅኤል በጉበኝነት ሥራ ላይ የተመደበ ስለነበረ የሥራ ግዴታውን በቅንዓትና ከሚናገረው ቃል ጋር በሚስማማ ጠባይ ፈጽሞአል። በሁለተኛ ደረጃ ፍቅራዊ አዛኝነት ነበረው። ምንም ዓይነት ስሜት የሌለው የጥፋት መልእክት አድራሽ አልነበረም። በሶስተኛ ደረጃ ደከመኝ የማይል ወንጌላዊ ነበር። በአደባባይም ሆነ ከቤት ወደ ቤት በከተማዎችም ሆነ በየገጠሩ ወንጌልን ሰብኮአል።”

14. በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ራሱን ለይሖዋ አምላክ የወሰነ ሁሉ የመመስከር ኃላፊነት የተጣለበት ለምንድን ነው?

14 አምላክ በዘመናዊ አገልጋዮቹ ላይ ያፈሰሰው በረከትና ብልጽግና የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው በመጠራታቸው የተደሰተባቸው መሆኑን ያረጋግጣል። (ኢሳይያስ 43:10-12) ከዚህም በላይ ኢየሱስ ለተከታዮቹ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሎ ስለነበር የክርስቶስም ምሥክሮች ናቸው። (ሥራ 1:8) ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በመፀለይ ራሱን ለይሖዋ የወሰነ ሁሉ የመመስከር ኃላፊነት አለበት።

15. ስለጥንቶቹ ክርስቲያኖች የመመስከር ሥራ ምን ተብሎአል?

15 ስለ ምሥክርነት ሥራ የሚከተለው ተብሎአል፣ “መላውን ቤተክርስቲያን የሚመለከት ሥራ ነበር። የጥንቱ ቤተክርስቲያን ሚሲዮናዊ ሥራ ለሴቶች ሚሲዮናዊ ማኅበር ወይም ለውጭ አገር ሚሲዮናዊ ቦርድ የተተወ ኃላፊነት አልነበረም። የመመስከር ሥራ እንደ ሽማግሌዎች፣ ዲያቆናት ወይም ሐዋርያት ለመሰሉት የሙያ ሰዎች ብቻም የተተወ አልነበረም። . . . በዚያ የጥንት ዘመን መላው ቤተክርስቲያን ሚስዮናዊ ነበር። የጥንቱ ቤተክርስቲያን ሚስዮናዊ ፕሮግራም በሁለት እምነቶች ላይ የተመሠረተ ነበር። (1) የቤተክርስቲያን ዋነኛ ሥራ ወንጌልን በዓለም በሙሉ ማዳረስ ነው። (2) ይህን ሥራ የመፈጸም ኃላፊነት የተጫነው በመላው የክርስቲያን ማኅበረሰብ ላይ ነው።”​—ጄ ኸርበርት ኬን

16. የሕዝበ ክርስትና ጸሐፊዎች እንኳን ስለ ክርስቲያኖችና ስለ ምሥክርነት ሥራ ምን ነገር አምነዋል?

16 የዘመናችን የሕዝበ ክርስትና ፀሐፊዎች ከመንግሥቱ መልእክቱ ጋር የማይስማሙ ቢሆንም አንዳንዶቹ ክርስቲያኖች የመመስከር ግዴታ እንዳለባቸው ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል ኦስካር ኢ ፎይክት ሁሉም አገልጋይ ነው በተባለው መጽሐፋቸው “ማንም ካህን አምላክ ለእያንዳንዱ አማኝ የሰጠውን አገልግሎት ሊፈጽም አይችልም። የሚያሳዝነው ግን ለብዙ መቶ ዓመታት በቤተክርስቲያን ውስጥ ተስፋፍቶ በኖረው የተሳሳተ አስተሳሰብ ምክንያት የ500 ምዕመናን ሥራ ለአንድ ካህን ብቻ መተው ነው። በጥንቱ ቤተክርስቲያን ግን እንዲህ አልነበረም። ያመኑ ሁሉ በየደረሱበት ቃሉን ይሰብኩ ነበር።”

17. የምሥክርነቱ ሥራ በጥንት ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ስለነበረው ቦታ ምን ሊባል ይችላል?

17 በጥንት ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ የመመስከሩ ሥራ ከፍተኛ ቦታ ይሰጠው ነበር። በዘመናችን የይሖዋ ምሥክሮችም እንዲሁ ነው። የሐርቫርድ ዩኒቨርስቲው ኢድዋርድ ካልድዌል ሙር የሚከተለውን ጽፈዋል፣ “በአጠቃላይ የመጀመሪያዎቹ ሶስት መቶ ዓመታት የክርስትና እንቅስቃሴ እምነቱን ለማስፋፋት ይታይ በነበረው ከፍተኛ ግለትና ፍላጎት ተለይቶ ይታወቃል። የክርስትና ምኞትና ፍላጎት ወንጌላዊነት፣ የመዳንን መልእክት መናገር ነበር። . . . ይሁን እንጂ በጥንቱ ዘመን የኢየሱስን ትምህርትና እምነት በማስፋፋት ረገድ ሚስዮናውያን ተብለው ሊጠሩ የሚችሉ ሰዎች ያበረከቱት ድርሻ በጣም አነስተኛ ነበረ። ከተለያየ የሥራ መስክ፣ ከተለያየ የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ የተለያዩ ሰዎች የሥራ ውጤት ነበር። በራሳቸው ተሞክሮ ደኅንነት እንደሚያስገኝ ያመኑበትን ያንን የውስጣዊ ሕይወት ምሥጢር፣ ያንን አዲስ ዓይነት የዓለም አመለካከት እስከ ሮማ መንግሥት የመጨረሻ ድንበር አደረሱት። . . . [የጥንቱ ክርስትና] የዚህ ዓለም ሥርዓት እንደሚጠፋ ጥልቅ እምነት ነበረው። አዲስ የሆነ የዓለም ሥርዓት በድንገት በተአምር እንደሚቋቋም ያምን ነበር።”

18. የፖለቲካ መሪዎች በሕልማቸው እንኳን ከሚያስቡት በጣም የሚበልጠው ታላቅ ተስፋ ምንድን ነው?

18 የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት በመመስከርና በሌሎቹ የአገልግሎት ዘዴዎቻቸው አማካኝነት አድማጮቻቸውን የአምላክ ቃል ወደገባለት አዲስ ዓለም በደስታ ይመራሉ። በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረው ፍጻሜ የሌለው ሕይወት አዲስ ዓለም አቀፍ ሥርዓት እንገነባለን የሚሉ ሰዎች በሕልማቸው እንኳን ከሚያስቡት በጣም የበለጠ ይሆናል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:1-4) ሁሉም ሰው በአምላክ አዲስ ዓለም ውስት ለመኖር ይፈልጋል ብሎ ለማሰብ ይቻላል። ይሁን እንጂ ይህን የሚፈልጉት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። ቢሆንም የይሖዋ አገልጋዮች የዘላለም ሕይወት የሚፈልጉ ሰዎችን ለማስተማር ስለሚጠቀሙባቸው አንዳንድ ጥሩ ዘዴዎች ቀጥለን እንመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ሥራ 5:42 እና ሥራ 20:20 የኢየሱስ ተከታዮች ከቤት ወደ ቤት መስበክ እንደሚገባቸው ይናገራሉ ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

◻ አምላክ የይሖዋ ምሥክሮችን ከቤት ወደ ቤት አገልግሎት እንደተቀበለው እንዴት እናውቃለን?

◻ በአገልግሎት ረገድ ከሽማግሌዎችና ከዲያቆናት ምን ይጠበቃል?

◻ ምሥክርነት መስጠት በአንድ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ምን ቦታ ሊኖረው ይገባል?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ33 እዘአ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሳያቋርጡ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስክረዋል

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ ከቤት ወደ ቤት እየሄደ መስክሯል፤ ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮችም በዚህ የአገልግሎት ዘዴ ይጠቀማሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ