አምላክ በሚሰጠው ኃይል ታመን
ከ2ኛ ጢሞቴዎስ የተገኙ ዋና ዋና ነጥቦች
ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በስደትና በፈተና እንዲጸኑ የሚያስችላቸውን ኃይል ይሰጣቸዋል። ጢሞቴዎስና ሌሎቹ ክርስቲያኖችም ይህ ከአምላክ የሚገኘው ኃይል በጣም ያስፈልጋቸው ነበር። በ64 እዘአ የሮማ ከተማ በእሳት ጋየች። ቃጠሎውን ያስነሳው አጼ ኔሮ ነበር የሚል ወሬ አለ። ኔሮም ራሱን ለመሸፈን ሲል ክርስቲያኖች ናቸው ያቃጠሉት አለ። በዚህም ምክንያት በክርስቲያኖች ላይ ከባድ ስደት ተነሳ። በዚህ ጊዜ (በ65 እዘአ አካባቢ) ሐዋርያው ጳውሎስ በሮማ ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ ታሰረ። ሞት ተደቅኖበት እንደነበረ ቢያውቅም እንዲህ ባለው ጊዜ ሁለተኛ መልእክቱን ለጢሞቴዎስ ጻፈ።
የጳውሎስ ደብዳቤ ጢሞቴዎስ ከሃዲዎችን እንዲቃወምና የሚመጣበትን ስደት ጸንቶ እንዲቋቋም አዘጋጅቶታል። በመንፈሣዊ ማደጉን እንዲቀጥል ከመምከሩም በላይ ጳውሎስ በእሥር ቤት የሚኖርበትን ሁኔታ ገልጾለታል። በተጨማሪም ይህ ደብዳቤ አንባቢዎች ሁሉ አምላክ በሚሰጠው ኃይል እንዲታመኑ ይረዳቸዋል።
መከራ መቀበልና በየዋህነት ማስተማር
የምሥራቹ ሰባኪዎች በመሆን የሚደርስብንን ስደት ለመቋቋም የሚስችለንን ኃይል አምላክ ይሰጠናል። (2ጢሞ 1:1-18) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በጸሎቱ ዘንግቶት አያውቅም። ግብዝነት የሌለበትንም እምነቱን ያስታውሳል። አምላክ ለጢሞቴዎስ የሰጠው የኃይል፣ የፍቅርና የአእምሮ ጤናማነት መንፈስ ነው እንጂ የፍርሐት መንፈስ አልነበረም። ስለዚህ በመመስከሩና ለምሥራቹ ሲል መከራ በመቀበሉ ማፈር አይገባውም። በተጨማሪም ከጳውሎስ የሰማውን ጤናማ ቃል አጥብቆ እንዲይዝ ተመክሮአል። እኛም ብንሆን ሌሎች ቢያፈገፍጉም እንኳን እውነተኛውን የክርስትና እውነት አጥብቀን መያዝ ይኖርብናል።
ጳውሎስ ያስተማራቸው ነገሮች ሌሎችን ለሚያስተምሩ ሰዎች አደራ መስጠት ነበረባቸው። (2:1-26) ጢሞቴዎስ ጎበዝ የክርስቶስ ወታደር እንዲሆንና መከራ ሲደርስበት በታማኝነት እንዲጸና ተመክሮአል። ጳውሎስ ራሱ ምሥራቹን በመስበኩ በእሥራት ሰንሰለት በመሰቃየት ላይ ነው። ጢሞቴዎስ ቅዱስ የሆነውን ከሚቃወም ባዶ ልፍለፋ እየራቀ ራሱን የማይነቀፍ የአምላክ አገልጋይ አድርጎ ለማቅረብ እንዲተጋ አበረታቶታል። በተጨማሪም የጌታ ባሪያ ሌሎችን በየዋህነት ማስተማር እንደሚገባው ነግሮታል።
ቃሉን ስበክ!
የመጨረሻዎቹ ቀናት የሚያመጡትን ችግሮች ለመቋቋምና ለቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች ጸንቶ ለመቆም ከአምላክ የሚገኘው ኃይል የግድ ያስፈልጋል። (3:1-17) አምላክ የለሽ ከሆኑ ሰዎች መካከል ሁልጊዜ እየተማሩ እውነቱን ወደማወቅ ሊደርሱ የማይችሉ ሰዎች ይነሳሉ። እንደነዚህ ያሉት ክፉና አታላይ ሰዎች እየሳቱና እያሳቱ እያደር ክፋታቸውን ይጨምራሉ። ጢሞቴዎስ ግን በተማረው መጽናት ነበረበት። እኛም ‘ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነትና አነሳሽነት እንደተጻፉና ለማስተማር፣ ለመገሰጽ፣ ልብን ለማቅናትና በጽድቅ ላለው መንገድ ሁሉ እንደሚጠቅም’ አውቀን በተማርነው መጽናት ይኖርብናል።
ጢሞቴዎስ ከሃዲዎችን መቃወምና አገልግሎቱን መፈጸም ነበረበት። (4:1-22) ይህንንም የሚያደርገው ቃሉን በመስበክና በዚህም በመጽናት ነው። አንዳንዶች የሐሰት ትምህርት በማስተማራቸው የተነሳ ጉባኤው በአስቸጋሪ ጊዜ ላይ ይገኝ ስለነበረ ይህን ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮችም በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ቃል በጉባኤ ውስጥም ሆነ ከጉባኤ ውጭ ላሉት በጊዜውም አለጊዜውም እየሰበኩ በአምላክ ቃል ይጸናሉ። ጳውሎስ አንዳንዶች ጥለውት ቢሄዱም እምነቱን ጠብቆአል። ይሁን እንጂ ስብከቱ በእርሱ እንዲፈጸም ጌታ ኃይል ሰጥቶት ነበር። እኛም አምላክ በሚሰጠን ኃይል ታምነን ምሥራቹን በመስበክ እንቀጥል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በጎ ወታደር፦ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ አብረኸኝ መከራ ተቀበል። የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም” ሲል መክሮታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) አንድ እግረኛ የሮማ ወታደር ከባድ የጦር መሣሪያዎች፣ አንድ ቅርጫት፣ ለሶስት ቀን የሚበቃ ስንቅና ሌሎች ነገሮች ተሸክሞ ሲጓዝ መከራ ይቀበል ነበር። (ጆሴፈስ የአይሁድ ጦርነት 3ኛ መጽሐፍ ምዕራፍ 5) አለቃውን ስለማያስደስተውና ወጪውም ስለሚሸፈንለት በንግድ ሥራ አይሰማራም ነበር። በተመሳሳይም አንድ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር በመሆኑ ምክንያት ፈተናና መከራ ይደርስበታል። ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታዎቹን ለመወጣት ሥጋዊ ስራ መስራት ቢኖርበትም በቁሳዊ ነገሮች ተጠላልፎ መንፈሳዊ ውጊያ ከማካሄድ ወደኋላ ማለት አይኖርበትም። (1 ተሰሎንቄ 2:9) ከቤት ወደ ቤት እየመሰከረ የመንፈስ ሠይፍ የሆነውን ‘የአምላክ ቃል’ ይዞ ሰዎችን ከመንፈሳዊ ስህተት ይመልሳል። (ኤፌሶን 6:11-17፤ ዮሐንስ 8:31, 32) የብዙ ሰዎች ሕይወት በአደጋ ላይ ስለሆነ ክርስቲያን ወታደሮች ሁሉ በዚህ ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስንና ይሖዋ አምላክን በማስደሰት ይቀጥሉ።