ቦሊቪያ ውስጥ ወዳሉ ሩቅ ቦታዎች ብርሃኑን ማድረስ
ከቦሊቪያ ከፍተኛ ተራሮች በስተሰሜንና በስተምሥራቅ በዕፀዋት የለመለሙ ሞቃትና ለጥ ያሉ ሜዳዎች ተንጣለዋል። እነዚህም ሜዳዎች በጫካዎችና ዛፍ በሌለባቸው ሜዳዎች እየተጠማዘዙ በሚሄዱ ኃይለኛ ወንዞች ተከፋፍለዋል። በእነዚህ ሩቅ ቦታዎች የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ ምን ይመስላል?
ራስህን ከአንድ ግንድ ተቦርቡሮ በተሰራና ከበስተኋላው በሞተር በሚነዳ ታንኳ ውስጥ እንዳለህ አድርገህ አስብ። በቦሊቪያ የኤል ቤኒ ክፍለ ሀገር ዋና ከተማ የሆነችው የትሪኒዳድ ነዋሪዎች የሆኑ ስድስት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ተሞክሮ ይህን የመሰለ ነበር። ይህን ጉዞ ያቀዱት “የመንግሥቱ ምሥራች” ከዚህ በፊት ደርሶባቸው ለማያውቅ በወንዝ ዳር የሰፈሩ መንደርተኞች ለመመስከር ይችሉ ዘንድ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) ሠፊና አንጸባራቂ ወንዝ ካቋረጡ በኋላ ታንኳቸው ወደ ማሞር ወንዝ በሚያመለክት ጠባብ ወንዝ ውስጥ መጓዝ ጀመሩ።
በቡድኑ ውስጥ ከነበሩት አንዱ እንዲህ ይላል፦ “የወንዙ ጫፍ ደረቅ መሆኑን በተገነዘብንበት ወቅት ወደ ማሞር በጣም ተቃርበን ነበር። ከጀልባዋ በወጣን ጊዜ እስከ ጭናችን በሚውጥ ማጥ ውስጥ ሰጠምን። ሚስቴ ከማጡ ለመውጣት ስትሞክር ጫማዎችዋ ተውጠው ቀሩ። በመንገድ ተላላፊዎች እርዳታ ከባዷን ታንኳ ከጭቃው ወደ ደረቅ መሬት ጎትተን ለማውጣት ቻልን። ከሁለት አድካሚ ሰዓቶች በኋላ ማሞር ደረስን።
ከዚያም በግራና በቀናችን የሐሩር አውራጃ ዕፀዋት በሞሉባቸው ከፍተኛ የወንዝ ዳርቻዎች ታጅበን ያለምንም ችግር በወንዙ ሽቅብ ነዳን። አንዳንዴ የሞተሩን ድምፅ ሲሰሙ ትላልቅ ዔሊዎች ከተንሳፈፉ ግንዶች ላይ ይወርዱ ነበር። ደስ የሚሉ ዶልፊን የተባሉ ዓሣዎች ደግሞ ከውሃው ውስጥ ወደ ላይ ይዘሉ ነበር። የምንቆምበትን ቦታ የጠቆመን ነፍሳትን ለማባረር ተብሎ ከተቀጣጠለ እሳት የሚወጣ የጭስ አምድ ነበር። ጀልባችንን በወደቡ ላይ በተጠላለፉ የዛፍ ቅርንጫፎች መካከል ካሳረፍን በኋላ የወዳጅነት አቀባበል ካደረጉልን ሰዎች ጋር ስለመጪዎቹ የመንግሥቲቱ በረከቶች ተነጋገርን። በአድናቆት ተገፋፍተው ፍራፍሬና ዕንቁላል አሸከሙን።
ቀኑ እየመሸ ሲሄድ የእውነትን ዘር ለመትከል በሌሎች ቦታዎች ላይ ተጨማሪ ቆይታዎች አደረግን። ሳን አንቶኒዮ በደረስንበት ሰዓት ቀኑ ጨልሞ ነበር። መንደርተኞቹ ተኝተው ነበር። ሆኖም ፊልም እንደሚታይ በተሰማ ጊዜ መብራቶች በየቤቱ መለኮስ ጀመሩ። ጓዛችንን ወደ ከተማዋ የሚያደርስልን የፈረስ ጋሪ መጣልን። ብዙ ሰዎችም በፊልምና በግንባር ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተዋወቁ።
በተከታዩ ቀን አዳዲስ ቦታዎችን መጎብኘታችንን ቀጠልን። በአንድ ከፍታ የወንዝ ዳርቻ ሴቶች ግዙፍ በሆነ የዔሊ ቅርፊት ላይ ልብሶችና ሕጻን ልጅ ሳይቀር ያጥቡ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክታችንን ፈጽሞ ሰምተው አያውቁም ነበር። አንድ ቦታ ትናንሽ ዓሣዎች ከውሃው ውስጥ ዘለው በመውጣት ከጀልባችን አጠገብና ብዙዎቹም በጀልባዋ ውስጥ አረፉ። ስለዚህ ፊልሙን ማሳየት ከፈጸምን በኋላ ከመሰናበታችን በፊት ጥብስ አሣ በላን። ጉዞው ባበቃበት ወቅት በዚህ ሩቅ ቦታ ብዙ ጽሑፍ ተበርክቶ እኛም ለመጀመሪያ ጊዜ የምሥራቹን እንዲሰሙ ብዙዎችን በመርዳታችን ረክተን ነበር።—ከሮሜ 15:20, 21 ጋር አወዳድር።
መላእክት ይመሩን እንደነበር የሚጠቁሙ ነገሮች
አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ በምትጎበኝዋት 12,000 ሕዝብ የሚኖርባት ከተማ ውስጥ አንድ ሴት ለመፈለግ እንደተላካችሁ አድርጋችሁ አስቡ። ከሴትዬዋ ስም በስተቀር የምታውቁት ነገር የለም። ከዚህ በፊት በሌላ ከተማ መጽሐፍ ቅዱስ ታጠናና በስብሰባዎችም ትገኝ የነበረች አሁን ግን ወደዚህ ከተማ የተዛወረች ሴት ለማግኘት ተስፋ በማድረግ ጓያሪመሪን የምትባል ከተማ የደረሱት ሁለት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን የገጠማቸው ችግር ይህ ነበር። ማረፊያቸውን ካመቻቹ በኋላ አቅኚዎቹ ባልና ሚስት ብዙ ሰዎች ቁጭ ብለው ሲጨዋወቱ ወደሚያገኙበት ወደ ማዕከላዊ ከተማው ለመዘዋወር ወሰኑ። አንድ ሰው በድንገት ወዲያውኑ ወደነሱ ቀረበና ጭውውት አነሳ። የሚፈልጓትን ሴት ያውቃት እንደሆነ ጠየቁት። “አላውቃትም፣ ግን አማቴ የይሖዋ ምሥክር ናት”አላቸው። እነርሱ እስከሚያውቁት ድረስ በዚያ ከተማ የይሖዋ ምሥክሮች የሉም ብለው ስለሚያስብ ነገሩ አልገባው ይሆናል ብለው አሰቡ።
ይሁን እንጂ በሚቀጥለው ቀን እግራቸው ተሰብሮ የአልጋ ቁራኛ ሆነው የተኙትን እኒህን በዕድሜ የገፉ ሴት ሄደው ጠየቋቸው። “የይሖዋ ምሥክር ነኝ። ግን ገና አልተጠመቅሁም” አሉአቸው። እውነትን ማን እንዳስተማራቸው ሲጠየቁ በግድግዳው ላይ የተሰቀለውን የልጅ ልጃቸውን ፎቶግራፍ እያመለከቱ “እስዋ ናት” አሉ። ባልና ሚስቱ ዐይናቸውን ማመን አቃታቸው። ይፈልጓት የነበሩት ወጣት ሴት እርስዋ ነበረች። “ታዲያ ለምንድን ነው አማችዎ አላውቃትም ያለው?” ብለው ጠየቁ። “አሁን ስላገባች እሱ የሚያውቀው የጋብቻ ስሟን ብቻ ነው” ብለው መለሱ። በዚያ ጊዜ የልጅ ልጃቸው የምትኖረው ርቃ ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በደብዳቤ ሊመራላት ጀመረ። ውጤቱስ? እሷና አያትዋ ሁለቱም መሻሻል አድርገው ለመጠመቅ በቁ። ቤታቸው እያደገ ለሚሄድ ጉባኤ የመንግሥት አዳራሽ ሆኖ አገለገለ። ያቺ ወጣት ሴትም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በመሆን ብዙዎችን ወደ ይሖዋ ድርጅት መራች።
በሐሩር አካባቢዎች መስበክ
ቀጥላችሁ የተሳፈራችሁበት አይሮፕላን በቦሊቪያ በረሐዎች መካከል የሚገኘውን በሳር የተሸፈነ የሳን ጆክዊን የአይሮፕላን ማኮብኮቢያ ሲነካ ይታያችሁ። ከሁለት ዓመት ቀደም ብሎ የዚህን ከተማ ሕዝብ አንድ አምስተኛ ስለጠራረገው እንግዳ ወረርሽኝ ስታስቡ የመረበሽ ስሜት ያድርባችኋል።
ከትሪኒዳድ በአይሮፕላን የመጡት ባልና ሚስት አቅኚዎች የሕዝቡን መልካም እንግዳ አቀባበል እየቀመሱ ነው። ባልዬው እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “በበረራው ወቅት ያደረግነው የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ሳንከፍል በግል ቤት ውስጥ እንድናድር ወደመጋበዝ አመራ። አስተናጋጆቻችን ምግባችንን ሳይቀር በቅናሽ ዋጋ ያቀርቡልን ስለነበር ጊዜያችንን ሁሉ በስብከቱ ሥራችን ላይ እንድናውል አስችሎናል። ወዲያው ከመድረሳችን ወደ ጦር ሰፈሩ ሄደን ሪፖርት እንድናደርግ ተነገረን። እኛ የይሖዋ ምሥክሮች እንጂ ዐመጽ ቀስቃሾች ያለመሆናችንን ባለሥልጣኑ ባወቁ ጊዜ ልዩ ፍላጎት በማሳየት መጽሐፍ ቅዱስ ገዛ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችንም ተቀበለ። እንዲሁም ለመጠበቂያ ግንብና ንቁ! መጽሔቶች ኮንትራት ገባ። ከዚህ በኋላ ማንኛውም ሰው በቅርቡ ስለሚመጣው የመጽሐፍ ቅዱስ የፍጹም ጤንነት ተስፋ በጥሞና ያዳምጥ ነበር ማለት ይቻላል።—ራዕይ 21:4
አራት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ከሳን ጆክዊን ወደ ሳን ራሞን ለመሄድ ፈለጉ። የነበረው የመጓጓዣ ዘዴ በበሬ የሚጎተት ጋሪ ብቻ ነበር። ለመቀመጫነት የተጠቀሙት ጽሑፎቻቸውን የያዙትን ካርቶኖች ነበር። ከረዥሞቹ የእንጨት መንኮራኩሮች መንጠርና መንገጫገጭ የተነሳ ካርቶኖቹ ተጨረማመቱ። ሠረገላው ላይ ተጭነው የነበሩት ዶሮዎችም እንኳን በንቅናቄው የተነሣ ዝለው ይታዩ ነበር።
ጥቅጥቅ ባለ ደን መካከል ለአሥር ሰዓት ያህል ከተጓዝን በኋላ መንገዱን የሚያመለክት ምንም ዱካ የሌለበት ቦታ ደረሱ። ደግሞ እየመሸ ነበረ። ነጂው “ጠፋን መሰለኝ” ብሎ ቡድኑን አስደነገጠው። በዚህ እባብና አደገኛ የዱር አውሬዎች የተወረረ ዱር ውስጥ እንዴት ልናድር ይሆን እያሉ ማሰብ ጀመሩ። ነጂው ጨምሮ “ግን አይዞአችሁ፣ በሬዎቹ ከዚህ በፊት የሄዱበት መንገድ ነውና ያውቁታል” አለ። እውነትም በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ ከደኑ ውስጥ ወጥተው ሳን ራሞን ላይ ብቅ ማለት ጀመሩ።
እዚህም ቢሆን ከዚህ በፊት ሰምተው ለማያውቁ ጆሮዎች ስለመጪዋ ገነት እየተናገሩ ብዙ ቀናት አሳለፉ። ማንም ምሥክር እዚህ ኖሮ አያውቅም። ይሁን እንጂ ሁኔታውን የለወጠ አንድ ነገር ተፈጸመ።
አንዲት የካቶሊክ ሚስዮናዊ ምሥክሮቹ ከቤት ወደ ቤት ሲሄዱ ተከተላቸው ነበር። መንገድ ላይ ካለፉአት በኋላ ቀጥሎ የሄዱበት ቤት ውስጥ አገኙአት። ባሳየችው የወዳጅነት አቀራረብ በመገረም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የሚለውን መጽሐፍ ትተውላት ሄዱ። እሷ ራስዋ ፍላጎት ባይኖራትም መጽሐፉን ለወንድምዋ ሚስት ሰጠቻት። እርሷም መጽሐፉን በሙሉ በጉጉት አነበበችው። አጠናችና በኋላ የተጠመቀች ምሥክር ሆነች።
ጭንቀት በሐሩር ቀበሌ ወንዞች ላይ
እስቲ አሁን ደግሞ አደገኛና ሞገደኛ ውሃ ባለው ወንዝ ላይ ጀልባ እያንሳፈፋችሁ እንዳላችሁ አድርጋችሁ አስቡ። በድንገት የሚመጣ ታላቅ አዙሪት፣ የተደበቁ አለቶች፣ ማጥ የሆኑ የወንዝ ዳርቻዎችና የዛፍ ግንዶች ከአደጋዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው። በእነዚህ ውሃዎች ውስጥ በሥጋ በሊታ አሣዎች፣ ኤሌክትሪክ የሚረጩ ምዥልግ አሣዎችና በጅራታቸው የሚወጉ አሣዎች ሞልተዋል። በወንዝ አካባቢ ለሠፈሩ ሕዝቦች ለመመስከር ወደ ሪበራልታ የሄዱ ወንድሞችን ያጋጠሙአቸው ችግሮች እነዚህን ይመስሉ ነበር።
ወደነዚህ ራቅ ያሉ ቦታዎች ለመድረስ ወንድሞች የወንዞች መብራት የተባለ ትልቅ ሞተር ጀልባ ሰሩ። የወረዳና የክልል የበላይ ተመልካቾች ጉብኝት ሲያደርጉ ጀልባውን ለሙከራ እንዲወስዱ ተወሰነ። የጀልባው ጣሪያ በአንድ የዘመመ ቅርንጫፍ እስከተያዘበት ጊዜ ድረስ ያላንዳች ችግር ሲሠራ ቆየ። ኃይለኛ ሞገድ መጣና ጀልባውን ከወደቀ ዛፍ ጋር አጋጨው። አንድ የተሰበረ ሹል የዛፍ ቅርንጫፍ ልክ እንደ ሰይፍ የጀልባውን ጎን በስቶ ገባና የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ሚስት ሊወጋት ለትንሽ ዳነች። በቀዳዳው ውሃ ገባና ጀልባው ሲገለበጥ ተሳፋሪዎቹን በፍጥነት በሚወርደው ወንዝ ውስጥ ጣላቸው። የወረዳ የበላይ ተመልካቹና ሚስቱ ደግሞ መዋኘት በሚችሉት ወንድሞች እርዳታ በደህና ወደ የብሱ ወጡ። ጀልባው ግን ፈጽሞ ከዐይን ጠፋ። ከሶስት ቀን በኋላ አምስት ኪሎ ሜትር ያህል በወንዙ ተወስዶ ተገኘ። የግል ንብረታቸው በሙሉ ከ20 ካርቶን ጽሑፍ ጋር ጠፍቶ ነበር።
የቦሊቪያ ባሕር ኃይል ጀልባውን ከውሃው ውስጥ ተንሳፍፎ እንዲወጣ እርዳታ አደረገና ከሳምንታት ጥገና በኋላ ጀልባው የመጀመሪያ ጉዞውን ለመፈጸም እንደገና ተዘጋጀ። የጭንቀት ጉዞው ከመጥፎ የአየር ሁኔታና የሞተር ችግር ጋር እንደገና ተጀመረ።
ወንድሞች ጀልባቸውን ባሳረፉበት የመጀመሪያ የወደብ ሥፍራ “ትንሽዋ ጀልባችሁ ለዚህ ወንዝ ምንም አትጠቅምም” ብለው ካሾፉባቸው የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን ቡድን ጋር ተገናኙ። ስላይድ ፊልሞችን ለማሳየት ያደረጉት ሙከራ መሣሪያው በመበላሸቱ ምክንያት ከሸፈ። ምሥክሮቹ የመልስ ጉዞአቸውን ሲጀምሩ ሌሎች ባለጀልባዎች የድምጽ ማጉያ ይዘው። ‘ሐሰተኛ ነቢያት መጥተዋል’ ብለው ለማስጠንቀቅ ወደ መንደሩ መጥተው እንደነበር ሰሙ። ይህም የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን ሥራ እንደሆነ ግልጽ ነበር። ይሁን እንጂ የሕዝቡን ጉጉት የበለጠ አነሳሳው።
ይህ ጉብኝት የእውነተኞቹ የሐሰት ነቢያት ፕሮፓጋንዳ ለማክተም ምክንያት ቢሆንም ወንድሞች ፎርታሌዛ ለመድረስ በፊታቸው ገና የ21 ቀናት ጉዞ ይጠብቃቸው ስለነበር ጭንቀት ተሰማቸው።
በመንገዳቸው ላይ ራቅ ብሎ የሚኖር የአንድ ጎሣ ሹም ለሆነ ሰው መሰከሩለት፤ እርሱም በጥሞና አዳመጠ። ከአቅኚዎቹ በአንዱ በተሰጠ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር አማካኝነት በአንድ ገለልተኛ ገላጣ ቦታ የነበሩ ከቀብር የተመለሱ አልቃሾች በእውነተኛው የሙታን ተስፋ ተጽናኑ። ነጭ ጺም ያላቸው አንድ በዕድሜ የገፉ ሰው ልባዊ አድናቆታቸውን ገለጹ። እንዲሁም ለመጽሔቶቻችን ለአሥር ዓመት እንዴት ኮንትራት መግባት እንደሚችሉ ጠየቁ። በፎርታሌዛ 120 ሰዎች የማኅበሩን ስላይድ ፊልም በማየት ተጠቀሙ።
እነዚህ አቅኚዎች ለሩቅ ቦታዎች የእውነትን ብርሃን በማምጣታቸው እንዴት ያለ እርካታ አገኙ! በእውነትም የራስን ሕይወት የሕይወት ፈጣሪ የሆነውን ይሖዋ አምላክን በማገልገል ከማሳለፍ አስተማማኝና አርኪ ሊሆን አይችልም!—መዝሙር 63:3, 4
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕሎች]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ቦሊቪያ
ጉያራመሪን
ሪበራልታ
ፎርታሌዛ
ሳን ጆኣኩዊን
ሳን ራሞን
ትሪኒዳድ
ሳን አንቶኒዮ