የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 3/1 ገጽ 2-5
  • ታላቁ ጥያቄ ምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ታላቁ ጥያቄ ምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ታላቁ ጥያቄ ጉዳይ
  • አጽናፈ ዓለም ከየት መጣ?
  • ሕይወት ከየት መጣ?
  • ለአሳሳቢው ጥያቄ የሚሰጠው መልስ
  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኑክሌር ጦርነት ምን ይላል?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
  • ፈጣሪ ሕይወትህን ትርጉም ያለው ሊያደርግልህ ይችላል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ፍጥረት
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
  • ፕላኔቷ ምድራችን ወደፊት ምን ትሆናለች?
    በሕይወት ተርፎ ወደ አዲስ ምድር መግባት
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 3/1 ገጽ 2-5

ታላቁ ጥያቄ ምንድን ነው?

በእያንዳንዳችን ፊት የቆመው ታላቁ አሳሳቢ ጥያቄ ምንድን ነው? ባሕር እየሞላ መሄዱ ወይም በምድር አቀፍ ሙቀት የተነሣ እንግዳ የሆነ የአየሩ መለዋወጥ ነውን? ወደ አደገኛው የጸሐይ ጐጂ አልትራቫዮሌት ጨረሮች መጋለጥ የሚመራው የኦዞን ድርብርብ መመናመን ነውን? እንደ ድህነትና ወንጀል የመሳሰሉት ምድር አቀፍ ችግሮች የሚያባብሰው የሕዝብ ቁጥር ፍንዳታ ነውን? ወይስ ደግሞ በኑክሌር ጦርነት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መደምሰስና ከእልቂቱ የሚተርፉ ቢኖሩም በብርድ፣ በረሃብ ወይም በጨረር (ራዲየሽን) በአሰቃቂ ሁኔታ በመጨረሻው የሚሞቱ መሆናቸው ነውን?

በ1989 ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተባለው ጋዜጣ ይህንና ሌሎች ጉዳዮችን ካብራራ በኋላ እንዲህ በማለት ደመደመ፦ “የኑክሌር ጦርነት ሊነሣ መቻሉ ከእልቂት የመትረፉን ጉዳይ ያለአንዳች ጥርጥር ይበልጥ አስጊ የሆነ አደጋ ያለው ነው።” ታዲያ ከፊታችን የተደቀነብን ታላቅ አሳሳቢ ጥያቄ የኑክሌር ጦርነት ነውን?

ታላቁ ጥያቄ ጉዳይ

ከ1989 ጀምሮ የፖለቲካው ሁኔታ ለውጥ በማድረጉ የኑክሌር ጦርነት አስጊነት ቀንሷል። ያም ሆኖ የኑክሌር መሣሪያዎች እስካሉ ድረስ በሰው ልጅ ፊት አሳሳቢ ስጋት መኖሩ አይቀርም። ይሁን እንጂ በ1990 ብሪታኒካ ቡክ ኦቭ ዘ ይር ውስጥ የሚገኘው መረጃ ሌላ አሳሳቢ ጥያቄ ይጠቁማል። በዚህ ጽሑፍ መሠረት ከ230 ሚልዮን የሚበልጡ የምድር ነዋሪዎች አምላክ የለሾች ናቸው። ሌሎች ምንጮችም ተጨማሪ ብዛት ያላቸው ሕዝቦች ፈጣሪ የለም የሚለውን አመለካከት በሚያስፋፉት የምሥራቅ አገሮች ፍልስፍናዎች ተጽዕኖ ያደረባቸው መሆናቸውን ያመለክታሉ። ከዚህም ሌላ በብዙ መቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በፈጣሪ የሚያምኑ ቢሆኑም ስለሱ ያላቸው አስተያየት በጣም የተለያየ ነው። አብዛኛውን ጊዜም አድራጎታቸው እናመልከዋለን በሚሉት አምላክ ላይ ታላቅ ነቀፌታ ያመጣል።​—2 ጴጥሮስ 2:1, 2

አምላክ ካለ (በእርግጥ አለ) በአሁኑ ጊዜ ያለው አሳሳቢ ጥያቄ እሱን የሚመለከት መሆን ይኖርበታል። ሰውን ለምን ፈጠረ? ለእሱ ያለብን ኃላፊነትስ ምንድን ነው? ሰው እንደዚህ አድርጎ ምድርን ሲያበላሻት እሱ ምን ያደርግ ይሆን? ብዙ ሰዎች በሱ ለማመን ወይም ለፈቃዱ ለመገዛት አሻፈረን በማለታቸው ምክንያት በተዘዋዋሪ ለተደቀነበት ግድድሮሽ ምላሹ ምን ይሆን? እንዲያውም በእያንዳንዳችን ፊት የተደቀነው ታላቁ አሳሳቢ ጥያቄ “ስሙ ብቻውን ይሖዋ የሆነውን” የአምላክን የበላይ ገዥነት መቀበል ወይም አለመቀበል ነው።​—መዝሙር 83:18 ኪንግ ጀምስ ቨርሽን

አጽናፈ ዓለም ከየት መጣ?

በእርግጥ፣ በአምላክ ለማያምኑ ሰዎች ለሱ ኃላፊነት ያለብን የመሆኑ ጉዳይ አሳሳቢ አይደለም። ይሁን እንጂ መኖሪያችን ወይም ቤታችን የሆነችውን የምድርን አሠራርና ውበት በጥሞና የሚመለከት ማንኛውም ሰው ታላቅ ሞዴል አውጭ ያለ መሆኑን እንዲቀበል ይገደዳል። አብዛኞቹ ሳይንቲስቶች በዙሪያችን ስላሉት የተፈጥሮ ድንቆች ለማብራራት በሚሞክሩበት ጊዜ አምላክን በነገሩ ውስጥ እንደሚያስገቡት የተረጋገጠ ነው። ለምሳሌ ያህል ብዙዎቹ ጽንፈ ዓለም ፈጣሪ ሳያስፈልገው ከአንዲት የእስፒል ጫፍ በጣም የምታንስ ነገር ተነስቶ እንዲሁ በራሱ የመጣና በአጋጣሚ አሁን ያለውን መጠን እስኪይዝ ድረስ ያደገ ነው ብለው ያምናሉ። ይሁን እንጂ ጽንፈ ዓለም እንዴት እንደመጣ የሚገልጸው አንድ አዲስ ዝነኛ ቴዎሪ ወይም ሃሳብ ካብራሩ በኋላ ፊዚስት ሀንበርግ ብራውን የሳይንስ ጥበብ በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ሲሉ አምነዋል፦ “ይህ ገለጻ ለአብዛኞቹ ሰዎች ከማብራሪያ ይልቅ የጥንቆላ ማታለል እንደሚመስላቸው እገምታለሁ።” ፕሮፌሰር ብራውን ሲደመድሙም “የዓለም አመጣጥና ዓላማ” ዓለም ሊፈታቸው የማይችል “ታላቅ ምሥጢሮች ናቸው” ብለዋል።

የሳይንስ ሊቃውንት ‘ማተር’ እና ‘ኤነርጂ’ (‘ቁስ-አካል’ እና ‘ኃይል’) የተሳሰሩ ነገሮች መሆናቸውንና ቁስ አካል ወደ ኃይል ኃይልም ወደ ቁስ አካል ሊለወጡ የሚችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል። በኑክሌር ፍንዳታዎች እንደታየው በጣም አነስተኛ መጠን ያለው ‘ማተር’ (‘ቁስ አካል’) ከፍተኛ መጠን ያለው ፍንዳታን (ኤነርጂ) አለው። ታዲያ እኛ ባለንበት የከዋክብት ረጨት ውስጥ ያሉት 100,000 ሚልዮን ከዋክብትና በሚታየው ጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉ ሌሎች 1,000 ሚልዮን የከዋክብት ረጨቶች ውስጥ የሚገኙ ከዋክብቶች ሁሉ የያዘው ‘ኤነርጂ’ (ኃይል) ሁሉ ምንጭ የት አለ?

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።” ይህ አካል ማነው? “እኔ (ይሖዋ)ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም።” በማለት የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ ይመልስልናል።​—ኢሳይያስ 40:26፤ 42:5, 8

ምድር ከሌላው ጽንፈ ዓለም ጋር ባጋጣሚ መጣች የሚለው ግምታዊ ሐሳብ ለፈጣሪዋ ለይሖዋ አምላክ የሚገባውን ክብር ያስቀርበታል። (ራእይ 4:11) እንዲሁም በምድር ረገድ ሰዎች ጠንካራ የኃላፊነት ስሜት እንዳያድርባቸው ያደርጋል። ሰዎች በፍጥረቱ ላይ ለሚፈጽሙት ነገር በአምላክ ተጠያቂዎች መሆናቸውን ጠንቅቀው ቢያውቁ ኖሮ ምድርን መበከልን፤ የኦዞን ድርብርቧን ማጥፋትና ምድር አቀፍ ሙቀት መፍጠርን በመሳሰሉት ጉዳዮች ይበልጥ ጠንቃቆች ሊሆኑ ይችሉ ነበር።

ሕይወት ከየት መጣ?

ሕይወት እንዴት ጀመረ? የሚለውንም ጥያቄ እስቲ አስቡት። ሰዎች ሕይወት ያለ አምላክ ጣልቃ ገብነት ራሱ መጣ ተብለው ተምረዋል። ይሁን እንጂ ይህ በደንብ የታወቀውን አንድ የሳይንስ መሠረታዊ ሥርዓት ይቃረናል። በአንድ ወቅት ጥንዚዛዎች ከእበት፣ ትሎች ከበሰበሰ ሥጋ እንዲሁም አይጦች ደግሞ ከጭቃ ይፈጠራሉ ተብሎ ይታመን ነበር። እስካለፈው መቶ ዘመንም እንኳን ሳይቀር የሳይንስ ሊቃውንት በአጉሊ መነጽር የሚታዩ በጣም ጥቃቅን ፍጥረታት ሕይወት ከሌላቸው ነገሮች ይመጣሉ ብለው ያስተምሩ ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቶቹ ሐሳቦች በሬዲ፣ በፓስተርና ሌሎችም ሳይንቲስቶች ስህተት መሆናቸው ተረጋግጧል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ (1990 እትም) እንዲህ ይላል፦ “ፓስተር በላቦራቶሪ ካደረገው ሙከራ በኋላ አብዛኞቹ ባዮሎጂስቶች ሕይወት የመጣው ከዚያ በፊት ይኖር ከነበረ ሕይወት ነው የሚለውን ሐሳብ ተቀብለዋል።”

ሆኖም ግን የሳይንስ ሊቃውንት በጥንት ጊዜ ሁኔታዎቹ የተለዩ ነበሩ የሚል ቲዮሪ አላቸው። ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ የኬሚካል ቅመሞችን ከያዘ የመጀመሪያው ሾርባ ብለው ከሚጠሩት ሕይወት የለሽ ቅልቅል የመጀመሪያው ባለ አንድ ሴል ሕይወት ባጋጣሚ ተነሣ ብለው ይናገራሉ። ኤ ጋይድ ቱር ኦቭ ዘ ሊቪንግ ሴል በተባለው መጽሐፋቸው ክርስቲያን ዴ ዱዌ “ከመጀመሪያው ሾርባ ተነስቶ ሰው እስከመሆን ያለውን ነገር ሁሉ ያመጣው አጋጣሚና አጋጣሚ ብቻም ነው” ብለዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ሲናገር “የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና” ይላል። (መዝሙር 36:9) ይህ አባባል በእውነት በምርምር ከተረጋገጠው ማለትም ሕይወት ሊመጣ የሚችለው ቀድሞ ከነበረ ሕይወት ብቻ ነው ከሚለው ሐሳብ ጋር ይስማማል። ይሁን እንጂ ዋናው ሳይንስ ከአምላክ እጅ ከተገኙት ውድ ስጦታዎች አንዱ የሆነውን ሕይወት ባጋጣሚ እንደመጣ ነገር አድርጎ ማየትን ስለሚመርጥ ብዙ ሰዎች ሕይወታቸውን ስለሚጠቀሙበት መንገድ ለፈጣሪ ኃላፊነት ወይም ተጠያቂነት እንዳላቸው ሆኖ አይሰማቸውም። በመሆኑም እርስ በርሳቸው በመጨቋቆን፣ በመሰራረቅ፣ በመገዳደል፣ እንዲሁም ከፍተኛ ገንዘብ፣ ጊዜና ችሎታቸውን በአስፈሪ ፍጥነት የሚገድሉና የሚያወድሙ አጥፊ መሣሪያዎችን ለመሥራት በማዋል የአምላክን ሕጎች ይጥሳሉ።

ለአሳሳቢው ጥያቄ የሚሰጠው መልስ

ከአምላክ የለሾችና ከዘመናውያንም ሌላ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ሰዎች የአምላክን የበላይ ገዥነት አይቀበሉም። በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በአምላክ እናምናለን ይላሉ። እንዲሁም ከ1,700 ሚልዮን የሚበዙ ራሳቸውን ክርስቲያኖች ብለው ይጠራሉ፤ ለብዙ ዓመታት የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በቅዳሴዎቻቸው አማካኝነት አምላክን በሰው ፊት አመስግነዋል። ይሁን እንጂ በአምላክ የበላይ ገዥነት ጉዳይ ላይ እነዚህ 1,700 ሚልዮን ሕዝቦች አብዛኞቹ አቋማቸው ምንድን ነው?

ግለሰቦችም ሆኑ ሕዝቦች ከአምላክ ግልጽ ሕጎች ተቃራኒ በመሄድ ለአምላክ ልዕልና ያላቸውን ንቀት አሳይተዋል። ክርስቲያን ነን የሚሉ መንግሥታት በሰው ልጅ ታሪክ ተወዳዳሪ የሌላቸውን ሁለት የዓለም ጦርነቶች ጨምሮ አምላክ የለሽ የአመጽ ድርጊቶችን ፈጽመዋል። በሁለቱ ወገን የነበሩ “ክርስቲያኖች” ቀሳውስትም እነዚያን ጦርነቶች ባርከዋል! በዚህ ዓይነት ግብዝነታቸውም አምላክን በውሸት በመወከል አስነቅፈውታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “አምላክን እንደሚያውቁ በግልጥ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በሥራቸው ይክዱታል።”​—ቲቶ 1:16

የሆነው ሆኖ አምላክ “ራሱን ሊክድ አይችልም።” (2 ጢሞቴዎስ 2:13) በሕዝቅኤል 38:23 “እኔ ‘ይሖዋ’ እንደሆንኩ ማወቅ ይኖርባቸዋል” ብሎ ከገለጸው ዓላማው ጋር በመስማማት ለዚህ የበላይ ገዥነቱ ጥያቄ ገጽታዎች በሙሉ መፍትሔ የሚያስገኝበት ወይም ውሳኔ የሚያስተላልፍበት ጊዜ መምጣት አለበት። ታዲያ ለምን ይህን ያህል ጊዜ ዘገዬ? አከራካሪው ጥያቄስ በመጨረሻው መፍትሔ የሚያገኘው እንዴት ነው? በዚህ ከሁሉ የበለጠ አሳሳቢ በሆነ ጉዳይ ላይ አንተ ትክክለኛ ውሳኔ ልታደርግ የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Cover background: U.S. Naval Observatory photo

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Background: U.S. Naval Observatory photo

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ