የአንባብያን ጥያቄዎች
◼ መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰው “ጄኔራል” የነበረው የተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ነው
ስለ አምላክ ቃል የሚያብራራው ያ ጠቃሚ መጽሐፍ በገጽ 10 ላይ እንዲህ ይላል፦ “መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ ልዩ የሆነበት ሌላው ምክንያት ብዙዎቹ ጸሐፊዎቹ የተናገሩትን ነገር ነው። ነገሥታትን፣ በግ እረኞችን፣ ዓሣ አጥማጆችን፣ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ ካህናትን፣ ቢያንስ አንድ ጄኔራልንና ሐኪምን ጨምሮ 40 የሚያህሉ ግለሰቦች የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በመጻፍ ተካፍለዋል። ይሁን እንጂ ጸሐፊዎቹ የጻፉት የራሳቸውን ሐሳብ ሳይሆን የአምላክን ሐሳብ መሆኑን ደጋግመው ተናግረዋል።”
እነዚህ የተለያየ ሥራ የነበራቸው ሰዎች እነማን ናቸው ብለው የሚጠይቁ ሰዎች አሉ። ይህን ለማወቅ እስቲ የሚከተለውን ተመልከቱ።
ነገሥታት፦ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ነገሥታት ነበሩ። ቶሎ ወደ አእምሮ የሚመጡት ዳዊትና ሰለሞን ሊሆኑ ይችላሉ። (መዝሙር 3 በምዕራፉ መግቢያ ላይ የተጻፈውን መግለጫ፤ ምሳሌ 1:1፤ መክብብ 1:1ን ተመልከቱ) ይሁን እንጂ በኢሳይያስ 38 ላይ ያለው መዝሙር ቁጥር 10-20 የተጻፈው በሕዝቅያስ ነው። (ቁጥር 9ን ተመልከት) ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን መዝሙር 119ንም (ምናልባት ንጉሥ ከመሆኑ በፊት ሳይሆን አይቀርም) ያጠናቀረው እሱ ነው ብለው ያምናሉ። እንደዚሁም ሕዝቅያስ ምሳሌ ምዕራፍ 25 እስከ 29 ያለውን በማዘጋጀት ድርሻ ነበረው። (ምሳሌ 25:1) የመጨረሻው የምሳሌ መጽሐፍ ምዕራፍ የተዘጋጀው “በንጉሥ ልሙኤል” ነው። አንዳንዶች ይህ ልሙኤል ሕዝቅያስ ነው ሲሉ ሌሎች ግን ንጉሥ ሰለሞን ነበር ብለው ያስባሉ።—ምሳሌ 31:1
የበግ እረኞች፦ ዳዊትና ነቢዩ አሞጽ በግ ጠባቆች ሆነው ሠርተዋል። (1 ሳሙኤል 16:11-13፤ 17:15, 28, 34፤ አሞጽ 1:1) አሞጽ በስሙ የተጠራውን መጽሐፍ ሲጽፍ ዳዊት ደግሞ ብዙ መዝሙራትን ጽፏል። ዝነኛው መዝሙር 23 ያለጥርጥር ዳዊት ከበግ ጥበቃ ጋር ይተዋወቅ እንደነበረ ያንጸባርቃል።
ዓሣ አጥማጆች፦ ዓሣ አጥማጆች ከነበሩት የኢየሱስ ሐዋርያት መካከል ዮሐንስና ጴጥሮስ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን እንዲጽፉ በመንፈስ ተገፋፍተዋል። (ማቴዎስ 4:18-22) በመለኮታዊ መንፈስ አነሣሽነት ዮሐንስ ወንጌሉንና ሦስቱን መልእክቶቹን እንዲሁም የራእይን መጽሐፍ ጽፏል። ጴጥሮስም በመንፈስ መሪነትና አነሳሽነት ሁለቱን መልእከቶቹን ጽፏል
የመንግሥት ሠራተኞች፦ ዳንኤልና ነህምያ ሁለቱም በአምላክ ሕዝቦች ላይ ይገዙ ለነበሩ የውጭ መንግሥታት ሠራተኞች ነበሩ። (ነህምያ 1:1, 11፤ 2:1, 2፤ ዳንኤል 1:19፤ 2:49፤ 6:1-3) ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የእነዚህን ሰዎች ስም ይዘዋል።
ካህናት፦ መጽሐፍ ቅዱስን ለመጻፍ ያገለገሉ ሁለት የአምላክ ነቢያት ካህናት ነበሩ። እነሱም ኤርምያስና ሕዝቅኤል ናቸው። (ኤርምያስ 1:1፤ ሕዝቅኤል 1:1-3) በተጨማሪም “በሙሴ ሕግ ፈጣን ጸሐፊ” የነበረው ዕዝራ አሮናዊ ካህን ነበር። እሱም “[የይሖዋን (አዓት)] ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።”—ዕዝራ 7:1-6, 10, 11
ጄኔራል፦ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡና ከብዙ ጠላት ሕዝቦች ጋር ሲዋጉ ሠራዊቱን በመምራት የተጫወተው ሚና ኢያሱን ለጄኔራልነት ብቁ ያደርገዋል። (ኢያሱ 1:1-3፤ 11:5, 6) የኢያሱን መጽሐፍ ለመጻፍ መበት አግኝቷል። እንደዚሁም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ዳዊት ንጉሥ ከመሆኑ በፊት ጄኔራል ሆኖ እንደ ሠራ አድርገው ሊመለከቱት ይችላሉ።—1 ሳሙኤል 19:8; 23:1-5
ሐኪም፦ በመጨረሻም ቆላስይስ 4:14 “የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ” በማለት ይጠቀሳል። ሉቃስ በስሙ የተጠራውን ወንጌል ጽፏል። እንዲሁም የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍንም እሱ እንደ ጻፈው ግልጽ ማስረጃ አለ።