በኒው ዚላንዱ “የፖሊኔሽያ ብሔረሰብ ከተማ” የምሥራቹን ማወጅ
“ከዓለም ታላቁ የፖሊኔሽያ ብሔረሰብ ከተማ።” ይህ አንዳንድ ሰዎች ለኒው ዚላንዱ ትልቅ ከተማ ለኦክላንድ የሰጡት ስም ነው። ለምን? ማኡሪ የተባሉት የኒው ዚላንድ የራሷ የፖሊኔሽያ ብሔረሰብ መኖሪያ ስለሆነች ብቻ ሳይሆን በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የሌሎች የፖሊኔሽያ ብሔረሰብ እዚያ ስለሚኖሩ ጭምር ነው። በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከምዕራብ ሳሞአ፣ ከኩክ ደሴቶች፣ ከቶንጋ፣ ከኒዩና ከሌሎችም የፓሲፊክ ደሴቶች ፈልሰው መጥተዋል። እንዲያውም ባሁኑ ጊዜ በኩክ ደሴቶች ውስጥ ከሚኖሩት የሚበልጡ የማኦሪ ብሔረሰብ በኒው ዚላንድ ውስጥ አሉ። በተመሳሳይም በኦክላንድ የሚገኙ የኒዩ ነዋሪዎች በኒዩ ካሉት በቁጥር ይበልጣሉ።
እነዚህ የፓሲፊክ ደሴት ነዋሪዎች ወደ ኦክላንድ የሄዱበት ዋና ምክንያት ኤኮኖሚያዊ ቢሆንም መሟላት የሚያስፈልጋቸው ሌሎች ፍላጎቶችም አሏቸው። ለእነዚህ በመሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ አፍቃሪ የሆኑ ሕዝቦች ዋናው ፍላጎታቸው መንፈሳዊ ፍላጎት ነው። (ማቴዎስ 5:3) ይህንን በመገንዘብ በኒው ዚላንድ የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች “የመንግሥቱን ምሥራች” ለእነዚህ ደሴት ነዋሪዎች ለማወጅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። (ማቴዎስ 24:14) በዚህ ረገድ ምን ሥራ ሲከናወን ቆይቷል? የደሴት ነዋሪዎቹስ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነበር?
ሳሞአውያን ወደፊት ሲገፉ
በሳሞአ የሚኖር አንድ ሚስዮናዊ የሰጠው ሐሳብ የደሴት ነዋሪዎቹ ለመንፈሳዊ ነገሮች ስላላቸው አመለካከት የሚነግረን አንድ ነገር አለ። “በኒው ዚላንድ ለመጀመሪያ ጊዜ ካንድ ሰው ጋር ስትተዋወቁ ስለ ዓለማዊ ሥራው መጠየቅ የተለመደ ነው” በማለት ያብራራል። “በሳሞአ በመጀመሪያ የሚጠየቀው ጥያቄ አብዛኛውን ጊዜ የየትኛው ሃይማኖት ተከታይ ነህ የሚል ነው።” እንግዲያውስ በኒው ዚላንድ ከሚገኝ አማካይ ጉባኤ ይልቅ በኦክላንድ የሚገኙ ሁለት የሳሞአንኛ ቋንቋ ተናጋሪ የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎች በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ መሆናቸው አያስደንቅም።
በኦክላንድ የመጀመሪያው የሳሞአ ጉባኤ የተቋቋመው በ1977 ነበር። አምላክ በሰጣቸው ዕድገት ምክንያት ሁለተኛው ጉባኤ ከሰባት ዓመት በኋላ ተቋቋመ። (ከ1 ቆሮንቶስ 3:6 አወዳድሩ) በነዚህ ሁለት ጉባኤዎች በጠቅላላው 154 የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ያሉ ሲሆን 12ቱ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በንቃት የሚሳተፉ ናቸው። መካከለኛ ተሰብሳቢ ተገኘ በሚባልበት እሁድ በመንግሥት አዳራሹ በሚደረገው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ስብሰባ ላይ ከ275 በላይ የሆኑ ሰዎች ይገኛሉ።
የሳሞአ ወንድሞችና እኅቶች ደቀ መዛሙርት በማድረግ ሥራቸው ባላቸው ቅንዓትና ቆራጥነት እንደሚታየው እምነታቸውን በቁም ነገር ይይዛሉ። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይህንም ከሚከተለው የአንዲት የሳሞአ እኅት ተሞክሮ ለማየት ይቻላል፦
ከቤት ወደ ቤት አገልግሎት ላይ ያገኘቻት አንዲት ሴት ሁሉም ሃይማኖቶች ግብዞች ናቸው ብላ በመንቀፍ በሯን ዘጋችባት። ያች እኅትም በመደንገጥና በመበሳጨት ምን ብታደርግ እንደሚሻል አሰበች። “የይሖዋ ምስክሮችም ግብዞች ናቸው ብላ እንድታስብ አልተዋትም” ብላ አሰበች። ስለዚህ ማስታወሻ ልትተውላት ወሰነች። “ስለ ሥራዬ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ባጭሩ አብራራሁና መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚሰጠው ተስፋ እንዳብራራላት ጊዜ ትሰጠኝ እንደሆነ ጠየቅኋት። የስልክ ቁጥሬንም ጨምሬ ጻፍኩላት።”
ከዚያ ያች እኅት ሌሎች ቤቶችን በማንኳኳት አገልግሎቷን ቀጠለች። አራተኛው ቤት ላይ እንደደረሰች ቀደም ሲል በቁጣ ቤቷን ወደ ዘጋችባት ሴት ተመልሳ እንድትጠይቃት የስልክ ጥሪ ተደረገላት። “ሴትየዋ መጀመሪያ ላሳየችው ጠባይ ይቅርታ ጠየቀች” ትላለች እኅት ስትናገር። “ለተውኩላት ማስታወሻም አድናቆቷን ገለጸች። ፍሬያማ ውይይት ተከተለና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ።”
በአንዳንድ የሳሞአ ምስክሮች የሚታየውን የግል ጥቅምን የመሰዋትና የሚስዮናዊ መንፈስ መመልከትም የሚያስደስት ነው። በ1981 በሳሞአ ሕዝብ መካከል የሚሠራ አንድ አነስተኛ ቡድንን ለመርዳት አንድ ወንድም ከቤተሰቡ ጋር በኦክላንድ ወደ ዌሊንግተን ተዛወረ። በዚያን ጊዜ ከነበሩት 11 የመንግሥት አስፋፊዎች ጀምሮ 47 ሰዎች የያዘ ጉባኤ ወደመሆን አድጓል። “ከተደረገው መሥዋዕት የተገኘው በረከት ያመዝናል” አለ ወንድም። በቅርቡ እሱና ቤተሰቡ “ለመቄዶንያዊው ጥሪ” ምላሽ በመስጠት ከነቤተሰቡ ወደ ምዕራብ ሳሞአ ተመልሰዋል። (ሥራ 16:9, 10) ሌሎችም እንደዚሁ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው በመመለስ የልዩ አቅኚነት፣ የሚሲዮናዊነት ወይም የቤቴል አገልግሎት ሥራ ይዘዋል።
የኒዩዋውያን ምላሽ
በኦክላንድ ውስጥ በኒዩዋውያን (የኒዩ ደሴት ተወላጆች) መካከልም የስብከቱ ሥራ ወደፊት እየገፋ ነው። ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “ከቤት ወደ ቤቱ በሚደረገው አገልግሎት ላይ ወደ ቤት ግቡ የሚል ግብዣ ማግኘት የተለመደ ነው። አብዛኛውን ጊዜም የቤተሰቡ መጽሐፍ ቅዱስ በቅርብ ይገኛል። ስለሱ መወያየቱ ተገቢ ነገር እንደሆነ ነገር ይቆጠራል።”
ባሁኑ ጊዜ በኦክላንድ በጣም ንቁ የሆነ የኒዩዋውያን ጉባኤ አለ። ባለፈው ዓመት በተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት ወቅት የዚያ ጉባኤ አባላት የሆኑት 76 የመንግሥት አስፋፊዎች እሁድ ዕለት ለተደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ የሕዝብ ንግግር 127 ሰዎችን ለመጋበዝ ችለዋል። በወንድሞችና በእኅቶች መካከልም መልካም መንፈስ አለ።
“ጉብኝቱ በሁሉም ዘንድ እንደ ልዩ የመበረታቻ ሳምንት ተደርጎ ይታያል” ይላል ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ። “ምግብ ሲዘጋጅ መላው ጉባኤ ወደ ቤቱ ይመጣል። እነዚህ ወቅቶችም የኒዩዋውያን ተወዳጅ ምግቦች የሆኑት ‘ታኪሒ’ (የፓፓያ ምግብ)፣ ‘ታሮስ’ (የበረሃ አገር የአትክልት ስር)፣ በሙዝ ቅጠል የተጠቀለለ የኮከናት ክሬም፣ ‘ፒታኮ’ (ከታሮስ የሚሠራ ዳቦ)፣ ሙዞችና ታፒዮካ (ከካሳቫ ዱቄት የሚሠራ ምግብ) እንዲሁም አንዳንዴ በቀልድ የደሴት ነዋሪዎቹ ምርጥ ቁርጥ ሥጋ በመባል የሚጠቀሰው ፑኑ ፓቪ (በጨው ታሽቶ በቆርቆሮ የታሸገ ሥጋ) የመሳሰሉት የሚቀርቡባቸው ናቸው።”
የፖሊኔሽያን ቋንቋ ጽሑፎች
በኦክላንድና በሌላም ቦታ የሚኖሩትን የፖሊኔሽያን ሕዝብ መንፈሳዊ ፍላጎት ለማርካት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በፖሊኔሽያን ቋንቋዎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን ለማቅረብ ዝግጅት አድርጓል። ለምሳሌ መጠበቂያ ግንብ በራሮቶንጋን ወይም ኩክ ደሴት ማኦሪ ቋንቋ በወር ሁለት ጊዜ ታትሞ ይወጣል። ወርሐዊው ኒዩዋዊ መጠበቂያ ግንብም በደንብ ይቀርባል። ባሁኑ ጊዜ የራሮቶንጋንና ኒዩዋን መጠበቂያ ግንብ እትሞች ስርጭት እያንዳንዳቸው 1,000 ቅጂ ያህል ነው። 900 የሳሞአን ቅጂዎችም በኒው ዚላንድ ውስጥ በመሰራጨት ላይ ናቸው።
ከመጠበቂያ ግንብ በተጨማሪ በርካታ መጻሕፍትና ብሮሹሮች በተለያዩ የፖሊኔሽያን ቋንቋዎች ይገኛሉ። በ1989 በኒዩዋን ቋንቋ የታተመው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተሰኘው መጽሐፍ በዚያ ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች ለማቅረብ የመጀመሪያው ጽሑፍ ነው። በኩክ ደሴት የማኦሪ (ራሮቶንጋን) መስክም በዚያ ቋንቋ በተለይ ውጤታማ የሆነው “በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ” የሚለው መጽሐፍ ነው። ሁሉም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የሚመሩት በዚህ መጽሐፍ ረዳትነት ነው ለማለት ይቻላል። “ውጤታማ የማስተማሪያ መርጃ ወይም መሣሪያ የመሆኑ ምስክር” ይላል አንድ ሽማግሌ “ተማሪዎቹ በጉባኤ ስብሰባዎች መገኘት ለመጀመር ቶሎ ዝግጁ መሆናቸው ነው።”
እነዚህን ጽሑፎች ዘወትር ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ከማበርከታቸውም በተጨማሪ የይሖዋ ሕዝቦች መንገድ ለመንገድ በሚያደርጉት የምስክርነት ሥራቸውም ላይ ብዙ ጽሑፎችን ገበያተኛ በጣም ጥቅጥቅ ባለባቸው ገበያዎች ያበረክታሉ። በቅርብ ዓመታት በኦክላንድ ባለው የሕዝብ ፍንዳታ ሳቢያ በፓሲፊክ ደሴት ምግቦችና ዕደ ጥበባት ልዩ ችሎታ ያላቸው ጊዜያዊ መደብሮች ያሉባቸው ትላልቅ ገበያዎች ብቅ ብቅ ብለዋል። ቅዳሜ ቅዳሜ ጠዋት ወደነዚህ ገበያዎች እስከ 25,000 የሚደርስ ሕዝብ ሊመጣ ይችላል። ይህንን አጋጣሚ በጥበብ በመጠቀም ምስክሮቹ ወደነዚህ ገበያዎች በመሄድ ለባለመደብሮቹና ለገበያተኞቹ ስለ አምላክ መንግሥት ይነግሯቸዋል።
በአገልግሎታቸው አማካኝነት የይሖዋ ምስክሮች የመንግሥቱን ዘር በብዛት ለመዝራትና ከፍተኛ መጠን ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችንም ለፖሊኔሽያኑ ሕዝቦች ለማበርከት ችለዋል። የመጠበቂያ ግንብ ቅርንጫፍ ቢሮ በ1990 የአገልግሎት ዓመት ወቅት 23,928 የፖሊኔሽያን ቋንቋ ጽሑፍ ቅጂዎች ከፋብሪካው እንደተጫኑ ሪፖርት አድርጓል።
በአንድ መንፈሳዊ ገበታ ተቀምጦ መደሰት
ለመንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸው ንቁ በመሆን የፖሊኔሽያን ምስክሮች ለሳምንታዊው ክርስቲያናዊ ስብሰባ በመንግሥት አዳራሾች ለመገኘትና በታላላቅ ስብሰባዎችም ለመገኘት ከፍተኛ የቀዳሚነት ቦታ ይሰጣሉ። (ዕብራውያን 10:23-25) በ1988 በኦክላንድ በተደረገው የ“መለኮታዊ ፍትሕ” ስብሰባ ላይ ትምህርቶቹ በሳሞአን፣ በኒዩዋንና በኩክ አይላንድ ማኦሪ ቋንቋዎች ለየብቻ ተሰጥተዋል። የሳሞአን ፕሮግራም ልዩ ገጽታ ጥሩ ልምምድ የተደረገበት በታላቅ ስሜት የቀረበው የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ ነበር። የኦክላንድ፣ የኒዩዋንና የኩክ ደሴት ምስክሮች ከትውልድ ደሴቶቻቸው ለመጡት እንግዶች ለጋስ አስተናጋጆች በመሆን ክርስቲያናዊ እንግዳ ተቀባይነታቸውን አሳይተዋል። ስብሰባው በይሖዋ መንፈሳዊ ገበታ ላይ ተቀምጠው የሚጋበዙበትና የሚደሰቱበት ወቅት ሆኗል። በኦክላንዱ የ1990 “ንጹሕ ልሳን” ስብሰባ በሳሞአኑ ፕሮግራም ላይ 503 ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ተገኝቷል።
ለመንግሥቱ መልእክት ያሳዩት አዎንታዊ ምላሽ የደቡብ ፓሲፊክ ፖሊኔሽያን ደሴቶች “የይሖዋን ሕግ ይጠባበቁ” እንደነበረ ግልጽ ማስረጃ ነው። (ኢሳይያስ 42:4, 12) በምላሹም በኒው ዚላንዱ “የፖሊኔሽያን ብሔረሰብ ከተማ” የምሥራቹን በማወጅ በደስታ ይካፈላሉ።