በደቡባዊ ቺሊ ውስጥ የመንግሥቱን ዘር ለመዝራት የሚያጋጥመው ትዕግሥትን የሚፈትን ሁኔታ
በደቡባዊ ቺሊ ጸጥ ባለ የገጠር መንገድ ላይ በእግር መጓዝ እንዴት አስደሳች ነው! ከማዶ ግርማ ያላቸውና ጫፋቸው ላይ በበረዶ የተሸፈኑ የእሳተ ጎሞራ ተራሮች ያሉ ሲሆን በዛፎች በተከለሉ የግጦሽ ሜዶች ላይ መንጎች በሰላም ይሰማራሉ። ነፋሱ በቀስታ ሲነፍስ ወፎች ሲዘምሩ ቅጠሎችም ሲንኰሻኰሹ መስማት ይቻላል። ይህ አካባቢ አመቺ ቢመስልም የመንግሥቱን እውነት ዘሮች ለሚዘሩት ሰዎች የሚፈታተኑ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል።
ከአቅኚዎቻችን ወይም ከሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ ሰባኪዎቻችን ውስጥ አንዳንዶቹን ለመተዋወቅ ትፈልጋለህን? ምሥራቹን ሲሰብኩ ከእነርሱ ጋር አንድ ወይም ሁለት ቀን ለምን አናሳልፍም? እስቲ በመጀመሪያ በደቡባዊ ቺሊ ውስጥ ጄይምና ኦስካር በቀን ውስጥ የሚያጋጥሙአቸውን አስደሳችና ፈታኝ ሁኔታዎች ሲገልጹልን እንስማ።
በስብከቱ ሥራ አንድ ቀን ማሳለፍ
“ሌሊት ላይ ስንነቃ ወደ ትንሽዋ መኖሪያችን ጠልቆ የገባ ብርድ መኖሩን ተገነዘብን። ኦስካር የሱፍ የእግር ሹራቡን አጥልቆ ኮፍያውን ከራሱ ላይ ሳያወልቅ ከአልጋው ዘሎ ወጣ። በክፍሉ ውስጥ ያለውን ቅዝቃዜ ለማስወጣት በምድጃ ውስጥ እሳት አቀጣጠለ፤ ትንሹን የጋዝ ማሞቂያ ለኰሰ። ከዚያም ወደ ሞቀው አልጋው ተመለሰ። ውጪው ገና ጨለማ ነው፤ ሌሊቱን ሙሉ ያላባራው ዝናብ አሁንም ሲዘንብ ይሰማናል። በመስኮት ወደ ውጭ ተመለከትን ከዚያም እርስ በርሳችን ተያየን። በዚህ ቀን እረፍት መውሰዱ ምንኛ ቀላል በሆነ ነበር! ከዚያም ለቀኑ ያወጣነውን ዕቅድና ባለፈው ዓመት ሊደረስባቸው ወዳልተቻለ ራቅ ብለው የሚገኙ ክልሎች ሄደን ለማገልገል እንዳለብን አስታወስን። ከአልጋ ተነስተን የዕለት ተግባራችንን ለመጀመር ተገፋፋን።
“ከሁለት ሰዓት በፊት በጀመርነው ጉዞአችን ራቅ ብለው ወደሚገኙ ቤቶችና መንደሮች ቶሎ ለመድረስ በዚያ የሚያልፍና እኛን ለማሳፈር ፈቃደኛ የሚሆን ባለ መኪና ለማግኘት ወይም አውቶቡስ እንደሚመጣ ተስፋ በማድረግ በፍጥነት ተጓዝን። አንድ ትራክተር ከነተጐታቹ ጥቂት ሠራተኞችን ጭኖ መጣ። ሹፌሩ አቆመና እንድንሳፈር ፈቀደልን። ሌሊት ዝናብ ሲዘንብ በማደሩ ተደሰትን፣ ምክንያቱም ዛሬ ዘወትር ከሚያጋጥመን በሚቦን አቧራ ውስጥ ከሚደረግ ጉዞ ድነናል። ትራክተሩ ወደላይ እያነጠረን ጉዞአችንን ስንቀጥል ለእርሻ ሠራተኞቹ ምሥራቹን አካፈልን። የመውረጃችን ጊዜ ሲደርስም ጥቂት መጽሔቶችን ሰጠናቸው። የትራክተሩ ጉዞ የ11 ኪሎሜትር የእግር ጉዞ ስለቀረልን እንዴት አመሰገንን!
“የሚገባቸውን ሰዎች በመፈለግ የገጠሩን አካባቢ ለማካለል ረጅም ጊዜ ይወስዳል። በተመደበልን ክልል ደርሰን ሥራችን ስንጀምር ሰዎች ከምንናገረው ነገር ጋር እየተስማሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን ለመቀበል ግን ለምን ወደ ኋላ እንደሚሉ ለመረዳት አልቻልንም ነበር። በአብዛኛው ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ማንበብ ስለማይችሉ እንደሆነ ተገነዘብን። ስለዚህ የእኛ ጽሑፍ በውስጡ ያለውን ሐሳብ ሊያካፍሉአቸው ለሚችሉት ለልጆቻቸውና ለዘመዶቻቸው አስደናቂ ስጦታ እንደሆነ መጠቆሙን ጠቃሚ ሆኖ አገኘነው። ከምናነጋግራቸው ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ ብዙ የዚህ ዓለም ንብረት የሌላቸው ነበሩ። ሆኖም ያላቸውን ለማካፈል ደስተኞች ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ሲቀበሉ ብዙውን ጊዜ እንቁላል፣ ድንች፣ ቀይ ሥር፣ ሽንኩርት፣ ባቄላ፣ ምሥርና የመሳሰሉትን ይሰጡን ነበር።”
ጄይም አንድ ሰው ለተሰጠው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ አንድ ዕቃ ለመስጠት በሚፈልግበት ጊዜ ምን ቢሰጠው እንደሚመርጥ ሐሳብ መስጠትን ተምሯል። ለምን? ምክንያቱም አንድ ጊዜ አቅኚዎቹ 13 ተኩል ኪሎ የሚመዝን አትክልት ይዘው ተመልሰው ነበር፤ ጓደኛውም በሕይወት ያለች ዶሮ በመጽሐፍ መያዣ ቦርሳው ተሸክሞ ቀኑን ሲዞር ውሎ ነበር። ጄይም ብዙውን ጊዜ ሜርኩዌን ቢሰጠው እንደሚመርጥ አሳብ ያቀርባል፤ ይህም ከሚያቃጥል በርበሬና ቅመም ተደባልቆ የተሠራ ጣፋጭ ምግብ ነው። ትረካው ይቀጥላል፦
“ሜዳውን ከተሻገርን በኋላ ወደ አንዳንድ የማፑቼ [ትርጉሙ “የአገሩ ሰዎች”] ሩካዎች [ቤቶች] ደረስን። ከሸመገሉት ማፑቼዎች ጋር መነጋገሩ አስቸጋሪ ነው፤ ምክንያቱም ብዙዎቹ የሚናገሩት የትውልድ ቋንቋቸውን ብቻ ነው። ወጣቶቹ በአካባቢው ካሉ እንደ አስተርጓሚ ሆነው ያገለግላሉ። ወደ ገጠሩ ጠለቅ ብለን ስንገባ መጽሐፍ ቅዱስ በጭራሽ አይተው የማያውቁ ወይም የክፍለ ሐገሩ ዋና ከተማ እንደሆነው እንደ ቴሙኮ ያሉትን ትልልቅ ከተማዎች አይተው የማያውቁ ሰዎች አጋጠሙን። ይህም የዓለም ሁኔታዎች እንዴት እየተባባሱ እንደመጡ እንዲያስተውሉ ለመርዳት ትዕግሥትን የሚፈታተን ሁኔታ ይፈጥራል። ይህንን ማስረዳት ያለብን ቀስ በቀስ ነው፤ የአካባቢው ችግሮች በሌሎች ቦታዎች ያለውን ሁኔታ እንደሚያንጸባርቁ እንገልጻለን።
“ቀኑ እየገፋ ሲሄድ የደከሙት እግሮቻችን እረፍት ስጡን ይላሉ። አየሩ ከደማቅ የፀሐይ ብርሃን ጃንጥላ ወደሚያስጥልበት ኃይለኛ ዝናብ ይለወጣል። በቅርቡ የታረሱት ሜዳዎች ጫማችን ትልቅ ጭቃ ተሸክሞ እንዲነሳ ያደርጉታል። ፓሴ ኖ ማስ (ግቡ) የሚለውን ቃል ስንሰማ አመስግነን ወደ ወጥ ቤቱ እንገባና የእንጨት ምድጃውን እሳት እንሞቃለን። ከእህል የተዘጋጀውንም ‘ቡና’ እንጠጣለን፤ በቤት የሚዘጋጀውን አይብ በቤት ከተጋገረ ዳቦ ጋር እንበላለን። የትኩስ ዳቦው ሽታ አይረሳም።
“እንደገና በታደሰ ኃይል ከመሸ በኋላ አጥር እምብዛም የሌላቸውን የእርሻ መሬቶች እንሻገራለን። አንዳንዶቹ የስንዴ ማሳዎች ፒካ ፒካ በሚባል ሁል ጊዜ ልምላሜ ባለው የቢጫ አበባ የሚያወጣ ተክል የተከለሉ ሆነው ታገኙአቸዋላችሁ። ፀሐይ የምትጠልቅበት ጊዜ ስለደረሰ ወደ ከተማ የሚሄደውን የመጨረሻ አውቶቡስ ለመያዝ ወደ ዋናው መንገድ ቶሎ መድረስ ይኖርብናል። የ19 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞአችን ሊያከትም ነው።
“በደህና ያለምንም ችግር ተመለስን፤ ደክሞናል ቢሆንም ደስተኞች ነን። ምክንያቱም በግ መሰል ከሆኑ ሰዎች ጋር ብዙ አስደሳች የሆኑ ውይይቶችን አድርገናል። የምንበላውን ከበላን በኋላ የቀኑን ሁኔታ እንከልስና የደከመ ሰውነታችንን በአልጋ ላይ እናሳርፋለን።”
ወደ ኪሎኤ መሄድ
የኪሎኤ የደሴቶች ክምችት ብዙ ትንንሽ ደሴቶች የሚገኙበት አካባቢ ነው። ትልቁ ደሴት 176 ኪሎሜትር ርዝመት ሲኖረው በትናንሽ ሐይቆች የሚለዩ ለም የሆኑ ኮረብቶች አሉት። በምትሄዱበት በየትኛውም ቦታ ማራኪ የባሕር ዳርቻዎችንና ልዩ የሆኑ የዓሣ ማጥመጃ መንደሮችን ልታዩ ትችላላችሁ።
ከትልቁ ደሴት አጠገብ በሚገኘው አቻኦ በሚባለው ከተማ ውስጥ ሩቤንና ሰቺልያን እናገኛለን። እነርሱ በመጋቢት ወር 1988 ወደዚህ አካባቢ ሲመጡ የአካባቢው ቄስ ‘በደሴቱ ሁሉ እየዞረ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገሩትን ሁለት ሰዎች አትስሙ’ ብሎ አስጠንቅቆ ነበር። አፍራሽ የሆነው አስተያየቱ የጥቂቶችን አእምሮ ለመዝጋት ቢችልም የብዙዎቹን የማወቅ ፍላጎት ግን ቀስቅሷል። ሩቤንና ሰቺልያ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻቸው 28 ደረሱ። ከሚያጠኑት ውስጥ አብዛኞቹ አስተማሪዎች ነበሩ። ከእነዚህ ውስጥ አራቱ በትምህርት ቤታቸው የሃይማኖት ትምህርት ሲሰጡ “ቅዱሳን ጽሑፎች ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉና ጠቃሚ ናቸው” በተሰኘውና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን የያዘው መጽሐፌ በሚባለው የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች አማካኝነት ይጠቀሙ ነበር።
ይሖዋ ለእነዚህ በመንግሥቱ ስብከትና በደቀመዛሙርት ማድረጉ ሥራ በየቀኑ 32 ኪሎሜትር በመጓዝ ጠንክረው ለሚሠሩ አቅኚዎች እንክብካቤ ያደርግላቸዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) አንድ ቀን ሩቤንና ሰቺልያ በአንድ ባሕር ዳርቻ ባለ መንገድ ላይ ሲጓዙ በጣም አነስተኛ በሆነ ማዕበል አማካኝነት ብዛት ያላቸው ቾሪቶስ (የሚበሉ ውሀ ውስጥ የሚገኙ ፍጥረታት) እነርሱ በቀላሉ ሊያገኙአቸው ወደሚችሉባቸው ቦታዎች እየተገፉ ሲመጡ ተመለከቱ። ሩቤን መሰብሰቡን ቀጠለ፤ ነገር ግን ወደ ቤት እንዴት ይዘዋቸው ይሂዱ? ሰቺልያ መፍትሄ አገኘች። የእግር ሹራብዋ እንደ ከረጢት ሆኖ አገለገለ። አቅኚዎቹ አሁን ጣፋጭ የሆነ የባሕር ምግብ አዘጋጁ!
ከአቻኦ በስተሰሜን በኩል ልዩ አቅኚዎች በመባል የሚታወቁ ሁለት የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ ሰባኪዎች በሊናኦ በሚገኝ አንድ ትንሽ ጉባኤ ውስጥ ይገኛሉ። በዚያ አካባቢ የስብከቱ ሥራ የተጀመረው በ1968 ሲሆን በሊናኦ የመጀመሪያው የይሖዋ ምሥክር የተጠመቀው በ1970 ነው። ይህ ወንድም ለአራት ዓመታት በስብከቱ ሥራ የሚሳተፈው ብቻውን ነበር። ስለዚህ የቤተሰቡ አባሎችና የሚያውቃቸው ሰዎች ሲያሾፉበት መጽናት ነበረበት። በመጨረሻም በ1974 ሚስቱ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀበለችና ተጠመቀች። ከዚያም ቀጥሎ አራት ሥጋዊ ወንድሞቹ፣ አራት እህቶቹ፣ አራት አጎቶቹ፣ ስድስት የአጎቶቹ ልጆችና አማቹ እስከነሚስቱ ተጠመቁ። በዚያ የተቋቋመው ጉባኤ አንድ ትልቅ ቤተሰብ ነበር። ከጊዜ በኋላ ከአምስቱ ወንድማማቾች ውስጥ ሦስቱ ሽማግሌዎች አንዱ ደግሞ ዲያቆን ሆነው ማገልገል ጀመሩ።
ሉዊስና ጁዋን ከሊናኦ ከተማ 32 ኪሎሜትሮች ርቃ በምትገኘው ትንሽ ከተማ በኩኤምቺ የመንግሥቱን ዘር በመዝራቱ ሥራ ላይ ያተኮሩ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች ናቸው። በየዕለቱ ነፋስንና ዝናብን የዘወትር ጓደኛቸው በማድረግ አጥር እየዘለሉ፣ በአትክልት ጥቅጥቅ ብለው የተሞሉ ማሳዎችን እየተሻገሩና ኮረብታዎችን እየወጡና እየወረዱ ያገለግላሉ። በአቅራቢያው ወደሚገኙት ደሴቶች ለመድረስ በሣምንት ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ ወደ ኪሎኤ ደሴት በሚጓዙ ትንንሽ ጀልባዎች ይጠቀማሉ። በአንድ ደሴት ላይ ለሁለት ቀን ያህል ይቆያሉ። ከአንዱ ደሴት ወደ ሌላው የሚደረገው ጉዞ ብዙ የጀልባ ጉዞ አድርጎ ለማያውቅ ሰው የጭንቀት ስሜት የሚፈጥርበት ቢሆንም የደሴቱ ነዋሪዎች የሚያሳዩት የእንግዳ አቀባበልና ደግነት ይህንን ያካክሰዋል። ሉዊስና ጁዋን ሌላ የመንግሥቱ ሰባኪ ተጨመረላቸው። ከእርሱም ጋር በመሆን በክልላቸው ውስጥ የሚገኙትን 11,500 ነዋሪዎች ለማዳረስ ይጥራሉ። ዕድገቱ ዝግተኛ ቢሆንም በ1989 በተከበረው የመታሰቢያው በዓል ላይ 36 ሰዎች በመገኘታቸው ሉዊስና ጁዋን በጣም ደስ አላቸው።
ወደ ዋናው ደሴት መመለስ
ወደ ሰሜን ጉዞአችንን ስንቀጥል የቻካኦን የባሕር ወሽመጥ አቋርጠን ወደ ዋነኛው ደሴት እንመጣለን። በዚህም አካባቢ አቅኚዎች ሆነው የሚያገለግሉት ራሞንና አይሪን በአንድ ትልቅ ክልል ውስጥ ይሠራሉ። ይህም ራቅ ብለው በሞሊን፣ በካረልማፑና በፓርጉአ የሚገኙትን ቡድኖች ይጨምራል። ቢሎኤ ደሴት የሚኖሩት ምሥክሮች አራት ሰዓት በእግር ከሄዱ በኋላ የባሕር ወሽመጡን በጀልባ አቋርጠው በፓርጓ በሚደረጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። ራሞን አብዛኛውን ጊዜ ከአስፋፊዎቹ ሁለት እጥፍ የሚሆኑ ሰዎች የሚገኙባቸውን ስብሰባዎች ለመምራት ከሞሊን በአውቶቡስ ለአንድ ሰዓት ከሃያ ደቂቃ ያህል ይጓዛል። የ38 ኪሎ ሜትር ርቀት ብቻ ወዳለው ቦታ ለመድረስ ይህን ያህል ጊዜ የሚወስድበት ለምንድን ነው? ምክንያቱም አውቶቡሱ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን የተሞሉ ሻንጣዎችን፣ በጆንያ የተሞላ ድንችና ሽንኩርት እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ አሳሞችንና ዶሮዎችን የያዙ ተሳፋሪዎችን ለመጫን በየመንገዱ ስለሚቆም ነው። በአውቶቡሱ ዕቃ መጫኛ ላይ ሊወጣ ያልቻለው ነገር ሁሉ ወደ ውስጥ ይገባል። ይህም ከብዙ ሽታ፣ ለማየት ደስ የማይሉ ነገሮችና ከጫጫታ ጋር ረጅም ጉዞን የሚያስከትል ይሆናል።
ከእነዚህ አቅኚዎች ውስጥ መኪና ያላቸው በጣም ጥቂቶቹ ስለሆኑ አንዴ አውቶቡስ ካመለጣቸው የሚያደርሳቸው ሰው ካላገኙ በየከተማው ረጅም የእግር ጉዞ ለማድረግ ይገደዳሉ። ራሞንና አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከአንድ ባለ መኪና ጋር አብረው ሲጓዙ “ሰዎች ለሥራችሁ የሚሰጡት ምላሽ እንዴት ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። በመገረም እርስ በርስ መተያየታቸውን ሲመለከት እንዲህ አላቸው፤ “የዚህ አካባቢ ቄስ እኔ ነኝ፤ እናንተ የይሖዋ ምስክሮች ናችሁ። ሥራችሁን በደንብ አውቀዋለሁ መጽሔቶቻችሁንም እወዳቸዋለሁ።” ለስብሰባው ሰዓት ፓርጓ አድርሶ እስኪያወርዳቸው ድረስ ጥሩ የሆነ የጥያቄና መልስ የውይይት ጊዜ አሳለፉ። ቄሱ መጽሔቶቻችንን እያነበበ በቀጠለ መጠን ሌሎች ጥያቄዎቹም እንደሚመለሱለት አያጠራጥርም።
ራሞንና አይሪን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወደሚመሩባቸው 20 ቤቶች መድረሱ ሁልጊዜ ቀላል አይሆንላቸውም። አንዳንዶቹ ቤቶች የሚገኙት ከሞሊን ወንዝ ባሻገር ወይም ራቅ ብለው በሚገኙት ዓሣ በሚጠመድባቸውና በትንሽ ጀልባ መሄድ በሚያስፈልግባቸው መንደሮች ነበር። ከባድ ዝናብ ሲዘንብ ተስፋ ሊያስቆርጥ የሚችል ቢሆንም በመታሰቢያው በዓል ላይ 77 ተሰብሳቢዎች በመገኘታቸው እነርሱና በገጠሩ ክልሎች ውስጥ ተበታትነው የሚገኙት ሌሎች 18 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ድካማቸው ፍሬ እያፈራ እንዳለ በግልጽ ማየት ይቻላል።
ጁዋንና ግላዲስ የተባሉት የመንግሥቱ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች 23 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመራሉ። ጭቃ በሆኑ መንገዶች ላይ የተደረገው ረጅም ጉዞ የመንግሥቱ ዘር ለመማር በሚችሉ ግለሰቦች ልብ ውስጥ በመብቀሉ ተክሷል። ቢስታኩላ አጠገብ በሚገኝ የተራራ ሰንሰለት ውስጥ ባለ ራቅ ብሎ የሚገኝ ክልል ጁዋንና ግላዲስ ቀደም ሲል ጉብኝት ተደርጎለት በማያውቅ አካባቢ ይሠሩ ነበር። በዚያም አንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ፈረሱን ለዚያን ቀን እንዲያውሳቸው ጠየቁት። “በሚገባ” ብሎ ከመለሰ በኋላ “አብሬአችሁ ልሂድ?” ሲል ጠየቀ። ጁዋን ይህ የይሖዋ አመራር እንዳለበት ወዲያውኑ ተገነዘበች። በዚያ ጥቅጥቅ ባለ ጫካ ውስጥ ለመጥፋት ቀላል ነበር፤ ሆኖም ይህ ለምሥራቹ ፍላጎት ያሳየ ሰው አካባቢውን በደንብ ስለሚያውቀው ከተራራማው መንገድ ሊታዩ ወደማይችሉት ቤቶች አደረሳቸው። በእግርና በፈረስ ጀርባ ላይ ሆነው ለዘጠኝ ሰዓታት አድካሚ ጉዞ ካደረጉ በኋላ ከልዩ አቅኚዎቹ አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ምን እንደተሰማው ጠየቀው። ሰውየውም “የምጠይቃችሁ ነገር ቢኖር በሚቀጥለው ጊዜ ይዛችሁኝ እንድትሄዱ ነው” ብሎ መለሰላቸው። ይህ አድናቂ ሰው መንፈሳዊ ዕድገት ማድረጉን ቀጥሎ ጥር 1988 ተጠመቀ። ሚስቱም ብዙ ሳትቆይ በክልል ስብሰባ ላይ ተጠመቀች።
የክልል የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት በሚያደርግበት ወቅት በኤስታኩላ የሚገኙት 11 አስፋፊዎች የሕዝብ ንግግሩን ለመስማት 110 ተሰብሳቢዎች በመገኘታቸው ተደስተው ነበር። ከሎስ ሙርሞስ አጠገብ በምትገኘው 1,000 ሰዎች የሚኖሩባት ትንሽ ከተማ ለመታሰቢያው በዓል 66 ሰዎች ተሰብስበው ነበር። ስለዚህ በዚህ ሰፊ መስክ ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ።—ማቴዎስ 9:37, 38
ወደ ሰሜን ስንሄድ አለንና ፌርናንዶ የተባሉትን አቅኚዎች እናገኛለን። አንድ ቀን በአቧራማው መንገድ በእግራቸው ሲጓዙ አንድ ሹፌር በጭነት መኪናው ላይ አሳፈራቸው። ሲወርዱ ሳቁ፤ ምክንያቱም አቧራ ከራሳቸው ጀምሮ እስከ እግር ጣታቸው ድረስ በወፍራሙ ተቆልሎባቸው ነበር። ችግሮችን ሳቅ እያሉ የመቻል ዝንባሌና 20 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት ያስገኘላቸው ደስታ እንደነዚህ ያሉትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለማሸነፍ ረድተዋቸዋል። በመታሰቢያው በዓል ላይ 65 ሰዎች ሲገኙና በሚቀጥለው ቀን የአካባቢው ሰዎች በስብከቱ ሥራ ከእነርሱ ጋር ሲካፈሉ የተሰማቸውን ደስታ ገምቱት!
ባዮ-ባዮን መሻገር
በአንዴስ ተራሮች አካባቢ ወደሚገኙት በግ መሰል ሰዎች ለመድረስ 150 ጫማ ጥልቀት ያለውንና የባዮ-ባዮ ወንዝ የሚያስተጋባ ውኃ ያለበትን ሸለቆ መሻገሩ አስፈላጊ ነው። ይህም የሚደረገው በሸለቆው ላይ ተሻግሮ በተወጠረው የሽቦ ገመድ ላይ በተሠራ ደካማ የእንጨት መንሸራተቻ ሣጥን ላይ ነበር። ትንሽ ካንገራገርክ በኋላ መጓጓዣው ላይ ትወጣና ማስለቀቂያውን ዘንግ ትገፋዋለህ። በሸለቆው መካከል በፍጥነት በሚጓዘው ሣጥን መሰል መጓጓዣ ስትጓዝ መደገፊያውን አጥብቀህ ትይዘዋለህ። ስትቆምም ትወዛወዛለህ። ትንፋሽህን ለመቆጣጠር ከቻልክ በኋላ ሌላውን ዘንግ ወደ ኋላና ወደ ፊት ቀስ በቀስ ታንቀሳቅሰዋለህ። ልባቸው በድንጋጤ ለሚደክም ሰዎች እንደማይሆን የተረጋገጠ ነው! ቢሆንም አንዲት እህት ሩቅ ወዳለ ተራራማ መንደር ወደሚገኝ አንድ በግ መሰል ሰው ለመሄድ በየሣምንቱ ይህንን ታደርጋለች!
አቅኚዎችና ሌሎች የመንግሥቱ አስፋፊዎች የሚያሳዩት መልካም ምሳሌ አድናቂ ልብ ያላቸውን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ተመሣሣይ ጥረት እንዲያደርጉ አበረታቶአቸዋል። (ዕብራውያን 10:24, 25) አንድ ቤተሰብ እስከ ባዮ-ባዮ ወንዝ ድረስ 40 ኪሎሜትር በፈረስ፣ ከዚያ እስከ መንግሥት አዳራሹ ድረስ ደግሞ 7 ኪሎ ሜትር በእግር ይጓዛል።
አቅኚዎቹ እነዚህን ሁሉ ዓመታት ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲያስቡ ትዝ የሚላቸው ምንድን ነው? ጫፋቸው በበረዶ የተሸፈኑ የእሳተ ጎሞራ ተራሮች፣ ያማሩ መስኮችና በኃይል የሚፈሱ ወንዞች ናቸውን? አቧራው፣ ዝናቡ፣ ጭቃውና ረጅም የእግር ጉዞ ማድረጉ ነውን? አዎን፤ በተለይ የሚያስታውሱት ግን ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ የሰጡትን ወዳጃዊ የሆኑ ሰዎችን ነው። እነዚህ በግ መሰል ሰዎች ምንም ዓይነት ጥረት ቢደረግላቸው የሚገባ መሆኑን አስመስክረዋል። በደቡባዊ ቺሊ ውስጥ የመንግሥቱን ዘር መዝራት እንዴት አስደሳች ነው!