የተለያዩ ሁኔታዎች በሚታዩባት በፈረንሳይ ምስክርነት መስጠት
ፈረንሳይ የተለያዩ ዓይነት ነገሮች የሚገኙባት አገር ነች። ግርማ ያላቸው ተራሮች፣ ሸንተረሮች፣ በማዕበል የተቦረቦሩ ዐለታማ ገደሎች፣ ደስ የሚል ሙቀት ያላቸው አሸዋማ የባሕር ዳርቻዎች፣ ለጥ ያሉ የእህል ማሳዎች፣ ባጭሩ የታጠሩ የእርሻ ቦታዎች፣ ሰፊ የወይን ተክል ቦታዎች፣ የግጦሽ መሬቶች፣ ቅጠለ ቀጫጭንና ወቅት ጠብቀው የሚያድጉ ዛፎች ጫካ፣ የገጠር መንደሮች፣ የገጠር ከተሞች፣ ዘመናዊ የሆኑ ትላልቅ ከተሞች፤ ፈረንሳይ እነዚህ ሁሉና ሌሎች ነገሮችም ያሉባት ነች።
አብዛኛው የገጠር ክፍል ውበቱን እንደያዘ ቢሆንም የፈረንሳይ ማኅበራዊ መልክ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ፈጣን ለውጥ አሳይቷል። የ1989ኙ ፍራንኮስኮፒ ዕትም “የፈረንሳይ ኅብረተሰብ መልክ በመጓዝ ላይ ያለው በአስቸጋሪ ወቅት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በኃይለኛ ማዕበል ውስጥ ነው። ማኅበራዊ መዋቅሮች፣ ግብረገብ፣ ባሕላዊ ሥርዓቶችና ዝንባሌዎች በከፍተኛ ፍጥነት በጥልቅ በመለወጥ ላይ ናቸው” ብሏል።
እነዚህ ከፍተኛ ለውጦች የሃይማኖቱንም ክልል ነክተውታል። አብዛኛው ሕዝብ የሚከተለው ሃይማኖት የካቶሊክን እምነት ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ሃይማኖት ከመሆን ይልቅ በአብዛኞቹ አባሎቹ ሕይወት ላይ እውን የሆነ ለውጥ ለማምጣት የማይችል ባሕላዊ ልማድ ብቻ ሆኖአል። ሕዝቡ ለመንፈሳዊ አስተሳሰቦች ግድየለሽነቱ እየጨመረ መምጣቱ የአብያተ ክርስቲያናትን ዕድገት ተገትቷል።
በፈረንሳይ ውስጥ የይሖዋ ምስክሮች የሚያከናውኑት ሥራ ግን ሁኔታው ከዚህ በጣም የተለየ ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በፍጥነት ወደፊት ተጉዟል። በሰሜናዊ ምሥራቅ ከምትገኘው ከአልሴስ በአትላንቲክ እስከምትገኘው እስከ ብሪታኒ፣ ከፍታ ካላቸው የአልፕስ ተራሮች ዝቅ ብሎ እስከሚገኘው የሏር ሸለቆ፣ በሜዲትራኒያን ላይ በምትገኘው የኮርሲካ ደሴትም እንኳ ሳይቀር ምሥክሮቹ የተለያዩ ዓይነት ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል፤ የተለያየ አስተዳደግና ታሪክ ካላቸውም ሰዎች ጋር ይገናኛሉ። እስቲ ሥዕላዊ ጉብኝት በማድረግ የተለያዩ ነገሮች በሚገኙባት በፈረንሳይ ውስጥ የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ ምን እንደሚመስል እንመልከት።—ማቴዎስ 24:14
አልሴስ
ከጀርመን ጋር የምትዋሰነው አልሴስ በወይን የአትክልት ቦታዋና በአበባ በተሞሉት አስደሳች ገጠሮችዋ የታወቀች ክፍለ ሀገር ናት። ዋና ከተማዋ ስትራስበርግ ከሃይማኖት ተሃድሶ ዘመን (ሪፎርሜሽን) ጀምሮ የፕሮቴስታንት ጠንካራ ምሽግ ሆና ቆይታለች፤ የአልሴስ ነዋሪዎችም በአጠቃላይ ሲታዩ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጤናማ አክብሮት አላቸው። የይሖዋ ምስክሮች ከዚህ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ በዚህ ክልል ውስጥ የመንግሥቱን ምሥራች ሲሰብኩ ቆይተዋል። በትምህርት ቤቱ ውስጥ ለመስበክ ያገኘውን አጋጣሚ ከተጠቀመበት ሲልቪ ከሚባለው አንድ ወጣት ተሞክሮ ለማየት እንደሚቻለው ዛሬ ሥራው በጥሩ ሁኔታ ተቋቁሟል።
ሲልቪ ከአያሌ የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር ባደረገው ውይይት ስለ ሕይወት ዓላማና ለወደፊት ስላሉት ተስፋዎች ገለጸ። አንዱ ልጅ ሲልቪና ሌላ ምሥክር ቤቱ ድረስ ሄደው ቢያነጋግሩት ደስ እንደሚለው አሳየ። “ይህ ካቶሊክ የሆነ ወጣት በቤተክርስቲያን ሥነ ስርዓቶች የሚያገለግል የነበረ ቢሆንም መልስ ያላገኙ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩት” በማለት ሲልቪ ተናገረ። “አንዳንዶቹን ጥያቄዎቹን በመጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም መለስንለት፤ የዘወትር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግለትም ፈቃደኛ ሆነ።” ይህ ወጣት ከአንድ ዓመት በኋላ ተጠምቆ የዘወትር አቅኚነትን ብቃቶች በማሟላት ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገባ። ሲልቪም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህንን የአገልግሎት መብት ይዟል።
ብሪታኒ
ብሪታኒ ወደ አትላንቲክ ገባ ብላ የምትገኝ ጠንካራ የካቶሊክ ባሕል የተስፋፋባት ክፍለ ሀገር ነች። ይሁን እንጂ ምስክሮቹ ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት በዚህ አካባቢ የሚገኙ በርካታ ሰዎች የእውነትን መልዕክት እየተቀበሉ ነው። በዚህ ሰሜናዊ ምዕራብ የፈረንሳይ ግዛት ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ የሚያስረዳ ምሳሌ ቀጥለን እንመልከት።
አንድ በዚያ አገር ውስጥ የሚኖር ምሥክር እንዲህ ሲል ገለጸ፦ “ወጣት ባልና ሚስት ቤት በመቀየር እኔ ካለሁበት አፓርታማ ክፍል በላይ ወዳለው ፎቅ መጡ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወጣት የሆነችውን ሴት ሕፃን ልጅዋን እንዳቀፈች በደረጃው ላይ አገኘኋት። ስሙ ዮናታን መሆኑን ካወቅሁ በኋላ የዚህን ስም አመጣጥ ታውቀው እንደሆነ ጠየቅኋት። ‘ከመጽሐፍ ቅዱስ የመጣ ይመስለኛል፣ የማውቀው ይህን ብቻ ነው’ ብላ መለሰችልኝ። የሰጠኋትን ማብራሪያ በደንብ አዳመጠች፤ ከዚያም እርስዋም ሆነች ባልዋ መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚወዱ ነገር ግን እንደማይገባቸው ጠቀሰች። ተጨማሪ ውይይት ብናደርግም በዚያን ጊዜ ተጨባጭ የሆነ ነገር አልታየም።
“ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባልና ሚስቱ ለነበሩባቸው አንዳንድ ችግሮች ምክር እንድሰጣቸው ጠየቁኝ። መልስ ለመስጠት በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቀምኩ፤ እነርሱም መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ምክር በጣም ተገረሙ። እንደገና መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ደግሜ ጠየቅኳቸው። በሚቀጥለው ቀን ወጣትዋ ሴት እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ ተቀበለችው። ከጥቂት ሣምንታት በኋላም ባልዋም በጥናቱ ላይ መገኘት ጀመረ። አሁን ሁለቱም የተጠመቁ ምሥክሮች ሆነዋል።”
የአልፕስ ተራሮች
አልፕስ የሚባሉት ወጣ ገባ ተራሮች በአስገራሚ ውበታቸው ዝነኛ የሆኑ የሚጎበኙ ቦታዎች ናቸው። ሰዎች ግርማ ያላቸውን ከፍተኛ ቦታዎች፣ በተለይም በምዕራባዊ አውሮፓ ከፍተኛውን ተራራ ሞንት ብላንን አይተው ለማድነቅ ወደዚያ ይሄዳሉ። በዚህ ክልል ውስጥ ፈጣሪን የሚያከብሩ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥርም በመጨመር ላይ ነው። የሚከተለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው በሁሉም የዕድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ የተለያየ ዓይነት አኗኗር ያላቸው ሰዎች ከእነርሱ ጋር በመሰለፍ ላይ ናቸው።
በዚያ አካባቢ በወንጀል ድርጊታቸው ሬኮርድ ያላቸው አራት ወጣቶች ነበሩ። እነርሱም መኪናና ሌሎች ዕቃዎችን ይሠርቁ፣ ብዙ ጊዜ ይሰክሩ፣ በዕፅ ይጠቀሙ፣ ዕፅ ያሰራጩ፣ በአመንዝራነትና በመናፍስታዊነት ድርጊት ይሳተፉ ነበር። ሥራ ፈቶች በመሆናቸው ከፖሊስ ጋር ብዙ ጊዜ ይጋጩ ነበር። ሁሉም እስር ቤት ገብተዋል። ሆኖም የአራቱም ቤተሰቦች በተለያየ ጊዜ ከይሖዋ ምስክሮች ጋር ያጠኑ ስለነበረ በልጅነታቸው እውነትን ሰምተዋል።
በእንደዚህ ዓይነቱ የአውሬነት ኑሮ ለበርካታ ዓመታት ከኖሩ በኋላ ከወጣቶቹ አንዱ የልብ ለውጥ አደረገና ይሖዋን ለማገልገል ወሰነ። ይህም እንደ ሰንሰለት የተያያዘ ውጤት አስከተለ። አንድ ቀን ፖሊሶች እየዞሩ ፍተሻ ሲያደርጉ ከወጣቶቹ አንዱን ቦርሳውን እንዲከፍት ጠየቁት። ዕፅ ወይም የተሰረቀ ዕቃ እናገኛለን ብለው ሲጠብቁ መጽሐፍ ቅዱስና አንዳንድ ትንንሽ ጽሑፎችን ብቻ በማግኘታቸው ተገረሙ። ወጣቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሞ በሕይወቱ ላይ ለውጥ ለማድረግ የረዳው ምን እንደሆነ ገለጸ። አንዱ ፖሊስ ነገሩን ለማመን ስለተቸገረ፦ “ሲጋራ ማጨስ፣ መጠጣት፣ ወይም ዕፅ መውሰድ አቁሜአለሁ ማለትህ ነውን?” ብሎ ጠየቀው። በመጨረሻም ፖሊሶቹ የነገራቸውን ቃል አምነው ጭቅጭቅ ሳያበዙ ለቀቁት። ዛሬ እነዚህ አራት ወጣቶች ተጠምቀዋል፤ ሁሉም በጉባኤው ውስጥ ዲያቆናት ሆነው ያገለግላሉ፤ ሦስቱ የዘወትር አቅኚዎች ናቸው።
የሏር ሸለቆ
የሏር ሸለቆ የፈረንሳይ የአትክልት ቦታ ተብሎ ይጠራል። ይህም ከፓሪስ ደቡብ 112 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ከኦርሊንስ በአትላንቲክ ዳርቻ እስከሚገኘው የሏር ወንዝ አፍ ድረስ የተዘረጋ ነው። ይህ ክልል በብዙ ጥንታዊ ግንቦቹና በቀድሞ ነዋሪዎቹ እንዲሁም በንጉሣዊው ቤተሰብ የአደን ቦታ የታወቀ ነው። በዚህ አካባቢ ባሉ በሁሉም ዋነኛ ከተሞች የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎች ይገኛሉ።
ተግባቢ የሆነችው የስድስት ዓመቷ ልጅ ኤማ በትምህርት ቤቱ የእረፍት ጊዜ ላይ አስተማሪዋን ሰላም ለማለት ወደ ክፍልዋ ተመለሰች። አስተማሪዋ ሲጋራ ስታጨስ በማየቷ በጣም ደንግጣ እያለቀሰች ሮጠች። አስተማሪዋም ሮጣ ተከተለቻትና ለምን እንደምታለቅስ ጠየቀቻት። ኤማ ዝም አለች። አስተማሪዋ አጥብቃ ስትጠይቃትም ኤማ እየተንሰቀሰቀች፦ “ሲጋራ ስለምታጨሺ ነው። አሁን ልትታመሚና ልትሞቺ ስለሆነ ነው” ብላ መለሰችላት።
በሚቀጥለው ቀን ልጅቷ ባሳየችው ሁኔታ ምን ያህል እንደተነካች ለመናገር አስተማሪዋ የኤማን እናት አስጠራቻት። በዚህም እናትየዋ የይሖዋ ምስክሮች ስለ ትንባሆ ያላቸውን አቋም ገለጸችላት። አስተማሪዋም ቤተሰቦችዋ ሲጋራ እንድታቆም ጠይቀዋት እንደነበረና እንዳልቻለች ተናገረቻት። ሆኖም አሁን ግን በኤማ ልባዊ ስሜት ተነክታ በሁለት ቀን ውስጥ ሲጋራ ማጨስዋን አቆመች።
ኮርሲካ
“የሚያውድ ሽታ ያላት ደሴት” ተብላ የምትጠራው የኮርሲካ ትንሽ ደሴት ጠንካራ መንፈስ ባላቸው ነዋሪዎችዋም ትታወቃለች። ብዙ ጊዜ ደም መፋሰስ ያስከተሉ የበቀል እርምጃዎች ይወስዳሉ። ለብዙ ዓመታት ምስክሮቹ “ከመሐል አገር” የመጣ ሃይማኖት እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ ነበር። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለው ኃይል እዚያ ያሉትን የብዙ ሰዎችን ልብ በመለወጥ ላይ ነው።
አንድ በቅርቡ የተጠመቀ የይሖዋ ምስክር አንድ ጊዜ ለእረፍት ወደ ሽርሽር ከሄደበት ቦታ ሲመለስ ከእርሻ ቦታው ላይ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉት ዕቃዎቹ ሁሉ ተሰርቀው እንደጠበቁት ይናገራል። “በይሖዋ በመታመን ቀደም ሲል እወስደው ከነበረው እርምጃ የተለየ እርምጃ ለመውሰድ ቻልኩኝ” በማለት አሳቡን ገለጸ። ለጎረቤቶቹ ስለ ጠፋበት ዕቃ ሲነግራቸው በረጋ መንፈስ ነበር።
“ከጊዜ በኋላ አንዳንዶቹ ጎረቤቶች ችግሮች አጋጠሟቸው። ችግራቸውን ለመፍታት እነርሱን ሄጄ ለመርዳት ሥራዬን ተውኩ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ከእነርሱ መካከል አንዱ ስልክ ደወለልኝና በተቻለ ፍጥነት እንድመጣ ጠየቀኝ። እንደገና ችግር አጋጥሞት ይሆናል ብዬ በማሰብ ወዲያውኑ ሄድኩ። እንድቀመጥ ከጋበዘኝ በኋላ እንዲህ በማለት ጠየቀኝ፦ ‘ለምን እንደጠራሁህ ታውቃለህ? ስለጠፉብህ ዕቃዎች ጉዳይ ልነግርህ ነው። የሰረቅሁት እኔ ነኝ። ሆኖም ያሳየኸውን የደግነትና ወዳጃዊ ዝንባሌ ስመለከት ለራሴ “በእርሱ ላይ ይህንን ማድረግ የለብኝም!” ብዬ አሰብኩ። ችግራችንን እንድንወጣው ከረዳኸን በኋላ በፍጹም እንቅልፍ ሊወስደኝ አልቻለም።’” እውነተኛ ክርስትና በተግባር ሲገለጥ ጥሩ ውጤት ያስገኛል።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲያበቃና የመንግሥቱ ምስክርነት ሥራ በፈረንሳይ እንደገና ሲጀመር በአገሪቱ ሁሉ 1,700 የሚያክሉ ምስክሮች ብቻ ነበሩ። የመንግሥቱን መልዕክት ለመላው ሕዝብ የማዳረሱ ሥራ የማይቻል መስሎ ነበር። ይሁን እንጂ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ይሖዋ በፈረንሳይ የሚኖሩትን ሕዝቦቹን የሚያስፈልጉትን መሣሪያዎች ማለትም የማተሚያ ፋብሪካዎችን፣ የመንግሥት አዳራሾችን፣ ትልልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾችንና የመሳሰሉትን እንዲያገኙ በማድረግ እንዲሁም ሥራውን ለማከናውን የፈቃደኝነት መንፈስ በመስጠት ባርኮአቸዋል። ዛሬ ከ117,000 የሚበልጡ ንቁ ምስክሮች ያሉ ሲሆን ለሰው ዘር ብቸኛ የሆነው ተስፋ በኢየሱስ ክርስቶስ የምትመራው የይሖዋ መንግሥት መልዕክት በዚህች የተለያዩ ነገሮች ባሉባት አገር ውስጥ በመሰበክ ላይ ይገኛል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ፈረንሳይ
ብሪታኒ
የሏር ሸለቆ
አልፕስ
አልሴስ
አትላንቲክ ውቅያኖስ
ሜድትሬንያን ባሕር
እንግሊዝ ካናል
ኰርሲካ