አስደሳች ዜና ከሶቪየት ሕብረት
የአንድ መቶ ዓመት ምስክርነት አስደሳች መደምደሚያ ላይ ደረሰ
“በተባበሩት የሶቪየት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምስክሮችን ሃይማኖታዊ ድርጅቶች አስተዳደር ማዕከል መተዳደሪያ ደንብ ስለ መመዝገብ”
በዚህ ገጽ ላይ የሚታየው የሩሲያ ቋንቋ ሰነድ የመጀመሪያዎቹ ቃላት ትርጉም ይህ ነው። እውነትም እነዚህ ቃላት የብዙ ጸሎቶችን መልስ ያመለክታሉ። ሰነዱ በሞስኮ የተፈረመውና በማኅተም የታተመው በሩሲያ ሶቪየት ሕብረት መንግሥታት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ የፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ነበር። ይህ ማለት የይሖዋ ምስክሮች በተባበሩት የሶቪየት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ውስጥ ሕጋዊ እውቅና ያላቸው የሃይማኖት ድርጅቶች ናቸው ማለት ነው። በመሆኑም በዚያ ሰፊ አገር የአንድ መቶ ዓመት ታሪካቸው የሚለወጥበት ጊዜ ደረሰ።
በጣም ትንሽ አጀማመር
የአንድ መቶ ዓመት ታሪክ? አዎን። እስካሁን በሚታወቀው መሠረት በዘመናችን በዚያ አገር የምሥራቹን ለመስበክ የመጀመሪያው ሰው ያን አገር በ1891 ጐብኝቶ እንደነበረ የገለጸው ቻርለስ ቴዝ ራስል ነው። በጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አብሳሪ የመስከረም 1891 እትም ላይ የአውሮፓ ጉዞው ወቅት ወደ ኪሽኔቭ ሩሲያ እንደተጓዘ ይዘረዝራል። እዚያም ዮሴፍ ራቢኖዊች የተባለ በክርስቶስ የሚያምንና በዚያ አካባቢ ለነበሩ አይሁድ ቤተሰቦች ለመስበክ ይሞክር የነበረ አንድ ሰው አገኘ። ራስል ከራቢኖዊች ጋር ባደረገው ጉብኝት ወቅት ስለ መንግሥቱ ጥልቅና አስደሳች ውይይቶች ስለማድረጋቸው በሰፊው ገልጿል።
የምሥራቹ እንደገና ተሰማ
ከራስል ጉብኝት በኋላ በአሁኑ የተባበሩት ሶቪየት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ውስጥ ስለተደረገ ምስክርነት እምብዛም አይታወቅም። ይሁን እንጂ ምንም አልተሠራም ማለት አይደለም። በ1927 በሶቪየት ሕብረት ውስጥ ሦስት ጉባኤዎች የመታሰቢያ ስብሰባቸውን ሪፖርት ወደ ማኅበር ልከዋል። ይሁን እንጂ እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ድረስ እድገቱ ፈጣን የነበረ አይመስልም። ያ ጦርነት በአውሮፓ የብዙ ሰዎችን ከፍተኛ ከአገር ወደ አገር መፍለስ አስከትሏል። የእነዚህ ከቦታ ቦታ የመዛወር አንዱ ያልታሰበ ውጤትም የመንግሥቱ ሰባኪዎች ወደ ሶቪየት ሕብረት በብዛት መግባት ነበር።
ለምሳሌ የየካቲት 1, 1946 መጠበቂያ ግንብ እትም እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “በፊት በምሥራቃዊ የፖላንድ ክፍል በኡክሬይንኛ ቋንቋ ይሰብኩ የነበሩ ከሺህ የሚበልጡ አስፋፊዎች አሁን ወደ ሩሲያ መሃል አገር ተዛውረዋል። . . . እንዲሁም ቀደም ሲል የሩማንያ ክፍል በነበረው ቤሳራቢያ ይኖሩ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድሞች አሁን የሩሲያ ነዋሪዎች ናቸው። አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራቸውንም ቀጥለዋል።”
በተጨማሪም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ብዙ የሶቪየት ዜጐች በማጐሪያ ካምፖች ውስጥ ገብተው ይሠቃዩ ነበር። ይህ ከባድ ተሞክሮ ለአንዳንዶቹ ወዳልተጠበቁ በረከቶች አምርቷል። አንድ ዘገባ በራቬንስብሩክ ማጐሪያ ካምፕ በርካታ ሩሲያውያን ወጣት ሴቶች ታስረው እንደነበረ ይነግረናል። እዚያም የይሖዋ ምስክሮችን አገኙ ለእውነት አዎንታዊ ምላሽ ሰጡና ዕድገት እያደረጉ በመሄድ እስከ መጠመቅ ደረሱ። በሌሎች ካምፖችም ተመሳሳይ ነገር ተፈጽሟል። እነዚህ አዲስ የተጠመቁ ምስክሮች ከጦርነቱ በኋላ ከእስር ሲለቀቁ የመንግሥቱን ምሥራች ወደ ሶቪየት ሕብረት ይዘው ገቡ። በዚህ መንገድ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሶቪየት ግዛት በመንግሥቱ ሰባኪዎች ቁጥር ላይ ፈጣን ጭማሪ አምጥቷል። በ1946 በትጋት ይሠሩ የነበሩ 1,600 አስፋፊዎች እንደነበሩ ተገምቷል።
በእስር ቤት መስበክ
በሶቪየት ሕብረት ምሥራቹን በማስፋፋት ረገድ እስር ቤቶች ዋነኛ መንገድ ሆነው ቀጠሉ። ከጦርነቱ በኋላ ባለ ሥልጣኖቹ በስሕተት ምስክሮቹን እንደ አስጊ ስለተመለከቷቸው ብዙዎቹ ይታሰሩ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ስብከታቸውን አላስቆመውም። ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው መልእክት ለሰው ዘር ከሁሉ የበለጠ ዜና መሆኑን በእርግጥ ያምኑ ስለነበረ እስራት እንዴት ሊያቆማቸው ይችላል? ስለዚህ ለብዙዎቹ እስር ቤት የአገልግሎት ክልል ሆነላቸው፤ የሰሟቸው በርካታ እስረኞችም እሺ ብለው ተቀበሉ። የ1957 ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “ባሁኑ ጊዜ በሩሲያ በእውነት ውስጥ እንዳሉ ከሚታወቁት ውስጥ 40% እውነትን የተቀበሉት በእስር ቤቶችና ካምፖች ውስጥ እንደነበረ መደምደሚያ ላይ ተደርሷል።”
በዚህ የማያቋርጥ የእስራት ስጋት ምስክሮቹ ተስፋ ቆርጠው ነበርን? ፈጽሞ! የ1964 ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “ከተፈቱ በኋላ መልእክቱን መስበካቸውን ስላላቆሙ ለሁለተኛ ወይም ለሦስተኛ ጊዜ የታሰሩ የይሖዋ ምስክሮች በእነዚያ ካምፖች ውስጥ አሉ።” ሌሎች ወደ እስር ቤት ወይም ወደ ካምፖች የገቡት ወንጀለኞች የነበሩና እዚያ እያሉ የይሖዋ ምስክሮችን ያገኙ ሰዎች እንደነበሩም ቀጥሎ ይገልጻል። እውነትን ተቀበሉና ዕድገት እያደረጉ በመሄድ ከመለቀቃቸው በፊት እስከ መጠመቅ ደረሱ።
የተጽእኖ መቀነስ
በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ባለ ሥልጣኖቹ ለምስክሮቹ ከወትሮው የላላ አቋም እየያዙ መጡ። እንዲህ ሊሆን የቻለው ምስክሮቹ በምንም መንገድ ለሕግና ለሥርዓት ምንም ስጋት የማይፈጥሩ ሰዎች መሆናቸውን እየተገነዘቡ ስለመጡ ነው። ስለዚህ የእነዚህ ትሑት ክርስቲያኖች እንቅስቃሴ ሕጋዊ አይሁን እንጂ ተይዘው መታሰራቸውና ቤታቸው መፈተሹ እየቀነሰ መጣ። ለዚህ የተጽእኖ መላላትም አመስጋኞች ነበሩ። ዋና ምኞታቸው በክርስቲያናዊ አኗኗራቸውና ሥራቸው በራሳቸው በኩል የሚችሉትን ያህል ጸጥና ዝግ ብለውና ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ መቀጠል ነበር።—ሮሜ 12:17-19፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2
በሳይቤሪያ ለረጅም ጊዜ በግዞት ላይ የቆዩ በ1966 ነፃ ተለቀቁና በአገሪቱ ውስጥ ወደፈለጉበት ቦታ እንዲሄዱ ተፈቀደላቸው። ብዙዎቹ ከቤታቸው ተለይተው ለረጅም ጊዜ ከቆዩ በኋላ ሲመለሱ አንዳንዶቹ ግን በዚያ ፍሬያማ መስክ መቆየትን መረጡ። ወደ ቤታቸው ከተመለሱት ውስጥ በዚያው ለመቆየት የመረጡት ሁሉም አልነበሩም። በሕፃንነቷ ከቤተሰቧ ጋር ወደ ሳይቤሪያ ተግዛ የነበረች አንዲት እኅት ከወላጆቿ ጋር ወደ ምዕራብ ሩሲያ ተመልሳ ነበር። ግን የቆየችው በጣም አጭር ለሆነ ጊዜ ነበር። የሳይቤሪያን ትሑትና እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ በጣም ከመውደዷ የተነሣ ቤተሰቧን ትታ ለነዚያ ጥሩ የእውነት ተቀባይ ለሆኑ ሕዝብ መስበኳን ለመቀጠል ወደ ምሥራቅ ተመልሳ ሄደች።
በዚህ ወቅት የነበረው ዓይነተኛ ተሞክሮ አንድን ከከተማ ወደ ከተማ የሚዘዋወርን ወንድም የሚመለከት ነበር። ከጊዜ በኋላ ሌሎች ሁለት ምስክሮችን አገኘ። ሦስቱም እርዳታ ለማግኘት ጸለዩና ወዲያውኑ መሠረቷ የግሪክ ኦርቶዶክስ ከሆነች ሴት ጋር ተገናኙ። እርሷም ወዲያውኑ እውነትን ተቀበለችና ወንድሞችን ወደ ሌሎች ፍላጐት ያላቸው ሁለት ሰዎች ማለትም ወደ እናቷና ታናሽ እኅቷ ወሰደቻቸው። ዘገባው እንዲህ በማለት ይደመድማል፦ “ባሁኑ ጊዜ ከነዚያ ወንድሞች ጋር የሚተባበሩ ዐርባ ሰዎች አሉ። ከእነርሱም ውስጥ ሠላሳዎቹ እውነትን የተማሩት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ነው።”
የሆነ ሆኖ የይሖዋ ምስክሮች ሕጋዊ እውቅና በማጣታቸው የተነሣ በእንቅስቃሴያቸው መሰናክል ይገጥማቸው ነበር። ስብሰባዎች የሚደረጉት በጥንቃቄ ነበር። ስብከትም እንደዚሁ። መታሰር አሁንም ገና ሊያጋጥም የሚችል ነበር። ግልጽ የሆነ የከቤት ወደ ቤት ምስክርነት የማይቻል ነበር። ይሁን እንጂ ከዚህ ሁሉ ጋር እነዚህ የሶቪየት ታማኝ ክርስቲያኖች አምላካቸውን በታማኝነት በማገልገልና ላገራቸው ጥሩ ዜጐች በመሆን ቀጠሉ። (ሉቃስ 20:25) የነበራቸውን አመለካከት በመግለጽ ከነሱ አንዱ እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “በፈተናዎች ሁሉ ጸንቶ ለይሖዋ መኖርና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከይሖዋ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት አምላክን በሕይወት ዘመን ሁሉ ለዘላለም ማክበር ታላቅ መብት ነው።” እነዚህ የሶቪየት ምስክሮች እንዴት ዓይነት የጽናትና የታማኝነት ምሳሌዎች ሆነው ቆመዋል!
በመጨረሻ ሕጋዊነት ማግኘት!
በ1988 ከሶቪየት ሕብረት ጋር ግንኙነት ባላቸው አገሮች ነገሮች መለወጥ ጀመሩ። የታላቅ ነፃነት ንፋስ መንሰራፋት ጀመረና የይሖዋ ምስክሮችን ሥራ አግደው የነበሩ አገሮች አዲስ አመራር መያዝ ጀመሩ። ፖላንድ፣ ሀንጋሪ፣ ሮማኒያና ሌሎች አገሮች ለነዚህ ቅን ክርስቲያኖች ምንም ዓይነት ቅጣት ሳይፈሩ ሥራቸውን በግልጽ እንዲያከናውኑ በመፍቀድ ሕጋዊ እውቅና ሰጧቸው። እነዚህ ያለፉት ሦስት ዓመታት በምሥራቅ አውሮፓ እንዴት ዓይነት የደስታ ዓመታት ነበሩ! በዚያ ያሉ ወንድሞችም አዲስ የተገኘ ነፃነታቸውን የመንግሥቱን ሰላማዊ መልእክት ለማሰራጨት እንዴት ጥሩ አድርገው ተጠቀሙበት! በቀረው የዓለም ክፍል ያሉ የይሖዋ ምስክሮችም ከነሱ ጋር አብረው ምን ያህል ደስ አላቸው!
የሶቪየት ምስክሮች እየሰፋ ባለው ነፃነታቸው ቀደም ብሎም መጠቀም ጀምረው ነበር። በሺህ የሚቆጠሩ አንዳንዶች የእስያ ፓሲፊክ ዳርቻ አጠገብ ሳይቀር አዲስ ምዕራፍ ከፋች በሆነው በ1989 በፖላንድ ስብሰባ ተካፍለዋል። አሁን እንደገና በ1990 በዋርሶ በተደረገው ስብሰባ ከሶቪየት ሕብረት 17,454 ምስክሮች ተገኝተዋል። እንዴት ዓይነት ትዝታ ወዳገራቸው ይዘው ተመለሱ! አብዛኞቹ ከጥቂት አማኝ ክርስቲያኖች በስተቀር በብዛት ለአምልኮ ተሰብስበው አያውቁም ነበር። አሁን ግን በአሥር ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ ሆነው ተሰበሰቡ!
ከጊዜ ወደ ጊዜ የቁጥጥር ገመዱን እያላላ ወደመጣው ወደ ሶቪየት ሕብረት ተመለሱ። በዓለም ዙሪያ ያሉ ምስክሮች በሶቪየት ሕብረት ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምስክሮች ሕጋዊ እውቅና የሚያገኙት መቼ ይሆን እያሉ ይጠባበቁ ነበር። ይህም በ1991 መጣ። ቻርልስ ቴዝ ራስል በዚያ ጉብኝት ካደረገ ልክ በመቶ ዓመቱ መሆኑ ነው! መጋቢት 27/1991 “በተባበሩት የሶቪየት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምስክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅቶች አስተዳደር ማዕከል” በተባበሩት የሶቪየት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ የፍትሕ ሚኒስትር ሞስኮ ውስጥ በፈረሙበት ሰነድ ላይ ተመዘገበ። ለምስክሮቹ ምን ዓይነት ነፃነት ተሰጣቸው!
አዲስ የተመዘገበው አካል ሕጋዊ መተዳደሪያ ደንብ የሚከተለውን መግለጫ ይጨምራል፦ “የሃይማኖት ድርጅቱ ዓላማ የይሖዋ አምላክን ስምና በኢየሱስ ክርስቶስ በሚተዳደረው ሰማያዊ መንግሥቱ በኩል ለሰው ዘር ሁሉ የሚያመጣላቸውን ፍቅራዊ ዝግጅቶቹን የማሳወቅን ሃይማኖታዊ ሥራ ማራመድ ነው።”
ይህስ ሥራ የሚከናወነው እንዴት ነው? በመዝገቡ ላይ የተዘረዘሩት መንገዶች ለሕዝብ በግልጽ መስበክንና ሰዎችን እቤታቸው ሄዶ ማነጋገርን፣ ለማዳመጥ ፈቃደኞች ለሆኑ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ማስተማርን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት (ለመማር) በሚረዱ ጽሑፎች ረዳትነት ነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግን፣ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሶችን መተርጐምን፣ ከውጭ ማስመጣትን፣ ማቅረብን፣ ማተምንና ማሰራጨትን ይጨምራሉ።
ሰነዱ በአስተዳደር አካሉ ስር የይሖዋ ምስክሮችን ድርጅታዊ መዋቅር ይዘረዝራል። የሽማግሌዎች አካል ያሏቸው ጉባኤዎች፣ በአገሪቱ ውስጥ ሥራውን የሚቆጣጠር ሰባት የአመራር [የቅርንጫፍ] አባላት ያሉት ኰሚቴ፣ የክልልና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች መኖራቸውን ጨምሮ ይዘረዝራል።
በግልጽ እንደሚታየው የይሖዋ ምስክሮች በሌሎች ብዙ አገሮች እንደሚያደርጉት በሶቪየት ሕብረት ውስጥም በነፃና በግልጽ መሥራት ይችላሉ። ከሰባቱ የቅርንጫፍ ቢሮ የአመራር ኮሚቴ ውስጥ አምስቱ አባሎችና ይህን ታሪካዊ ሰነድ ለመፈረም ልዩ መብት ያገኙት ለረጅም ጊዜ በእውነት ውስጥ የቆዩ አምስት የጉባኤ ሽማግሌዎች በሕዝብና ሃይማኖታዊ ማሕበራት መዝገብ ቤት ኃላፊው ማህተም ሲደረግበት ሲመለከቱ የተሰማቸውን ደስታ ገምቱ! የይሖዋ ምስክሮች የአስተዳደር አካል አባላት የሆኑት ሚልተን ሔንሸልና ቴዎዶር ጃራዝም ለዚህ ከፍ ያለ ትርጉም ያለው ሁኔታ የዓይን ምስክሮች ለመሆን መገኘታቸው ተገቢ ነበር። በሶቪየት ሩሲያ ፌዴራል ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ፈቃድ ካገኙት ውስጥ የመንግሥት ምዝገባ ሰነዱን ለመቀበል የይሖዋ ምስክሮች የመጀመሪያዎቹ ነበሩ። ይህን ያህል ብዙ ዓመታት በትዕግሥት ጸንተው ከቆዩ በኋላ እነዚህ ታማኝ የሩሲያ ወንድሞች እንዴት ዓይነት ሽልማት አገኙ!
የትም ቦታ ያሉ የይሖዋ ምስክሮች ይህን ሕጋዊነት ለሰጡት የሶቪየት ባለ ሥልጣኖች አመስጋኞች ናቸው። በተለይም ደግሞ የሶቪየት ወንድሞቻቸው ላገኙት አዲስ ነፃነት ይሖዋን በሙሉ ልባቸው ያመሰግኑታል። በሶቪየት ሩሲያ ሶሻሊስት ሪፑብሊክና በሌሎች የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች አሁን እንደዚህ እጅግ በጣም ይፋ በሆነ መንገድ ይሖዋ አምላክን እያገለገሉ ካሉ አማኝ ምስክሮች ጋር አብረው ደስ ይላቸዋል። ይህን ነፃነታቸውን ሙሉ በሙሉ የይሖዋን ቅዱስ ስም ለማክበር ሲጠቀሙበት ይሖዋ አብዝቶ ይባርካቸው።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመስኮቡ ክሬምሊን
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1990 ከሶቪየት ሕብረት ውጭ በተደረገ ስብሰባ ላይ የተገኙ ሩሲያውያን ተሰብሳቢዎች