የጸሎት ትርጉም
“በዕብራይስጥ ቋንቋ ጸሎት ለሚለው ቃል ዋናው ግሥ የመጣው “መፍረድ” ከሚል ቃል ሲሆን የተለመደው አገባቡ ቃል በቃል ‘ራስን መፍረድ’ የሚል ነው” ይላል ዘ ኦቶራይዝድ ዴይሊ ፕሬየር ቡክ የተሰኘ መጽሐፍ። ይህም ማለት የጸሎት አንዱ ሥራ አንድ ሰው የአምላክን የጽድቅ ደረጃዎችና ብቃቶች ያሟላ እንደሆነ ራሱን እንዲያይ መርዳት አለበት ማለት ነው።
በዚህም ምክንያት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ድረስ አንድ ሰው የአምላክን ፈቃድ እየፈጸመ ያለ ካልሆነ በቀር ጸሎቱ ተቀባይነት እንደማያገኝ ይነግረናል። “ይሖዋ ከኃጥአን ይርቃል። የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል።”—ምሳሌ 15:29፤ 1 ዮሐንስ 5:14
በይሖዋ ፊት ራስን መመርመር የሚጸልየውን ሰው ያለጥርጥር ትሑትና መንፈሱን የሚሰብር ሊያደርገው ይገባል። ይህም ሊጸልዩ ወደ ቤተ መቅደስ ስለመጡት ጉረኛው ፈሪሳዊና የተጸጸተው ቀራጭ ኢየሱስ የሰጠውን ምሳሌ የበለጠ ኃይል ይጨምርለታል።—ሉቃስ 18:9-14
ስለዚህ ወደ ይሖዋ የምንጸልየው ለማመስገን ይሁን ለማወደስ ወይም ለመማለድ ጸሎት ሁልጊዜ ራስን የመመርመሪያ ወቅት ነው። በዚህ መንገድ ጸሎት ወደ ይሖዋ ያቀርበናል። ከሱ ጋር ያለንን ዝምድናም ያጠነክርልናል።