የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 7/15 ገጽ 23-26
  • ክርስቲያን ወጣቶች በእምነት ጥብቅ ሁኑ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ክርስቲያን ወጣቶች በእምነት ጥብቅ ሁኑ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጠንካራ እምነት ለምን እንደሚያስፈልግ
  • ‘መከላከያ መልስ ለመስጠት ዝግጁ ሁኑ’
  • ‘በሁሉም ፊት መከላከያ መልስ ስጥ’
  • የምታገኘው እርዳታ
  • ታማኝነት በረከቶችን ያመጣል
  • የሌሎችን ፌዝ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—1999
  • ወጣቶች—ይሖዋ ያደረጋችሁትን ሥራ አይረሳም!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • አብረውኝ ለሚማሩት ልጆች መስበክ የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2002
  • ወጣቶች ሆይ፣ የይሖዋን ልብ አስደስቱ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1993
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 7/15 ገጽ 23-26

ክርስቲያን ወጣቶች በእምነት ጥብቅ ሁኑ

“እያንዳንዱ ተማሪ መገኘት አለበት።” ማስታወቂያው ይህ ነበር። በአንድ የጃፓን ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች በሙሉ በአንድ የስብሰባ አዳራሽ መገኘት ነበረባቸው። አንድ ወጣት ክርስቲያን ተማሪ በትምህርት ቤቱ መዝሙር ውስጥ የተገለጹትን አንዳንድ ሐሳቦች አይቀበላቸውም ነበር። እንዲህ ብሎ አሰበ፦ “የትምህርት ቤቱ መዝሙር እንደሚዘመር አውቃለሁ፤ ግን ምንም ችግር አይገጥመኝም። እንደወትሮው ከኋላ በኩል እቀመጣለሁ።”

ወጣቱ የይሖዋ ምሥክር ወደ አዳራሹ ሲገባ የፋኩልቲው አባሎች በሙሉ የኋላውን ረድፍ በሙሉ ተቀምጠውበት ያገኛል። ስለዚህ ከእነሱ ፊት ለመቀመጥ ተገደደ። ሌሎቹ ተማሪዎች ለመዝሙር ሲቆሙ እሱ ግን በአክብሮት እንደተቀመጠ ቀረ። ይሁን እንጂ መምህራኑ በዚህ በኃይል ተናደዱ። በግድ ጐትተው ሊያስነሱት ሞከሩ። ራስህን በዚያ ሁኔታ እንዳለህ አድርገህ ልትገምት ትችላለህን? ምን ታደርግ ነበር?

ጠንካራ እምነት ለምን እንደሚያስፈልግ

ሰዎች ክርስቲያኖችን ቢተዉአቸውና በመጽሐፍ ቅዱስ ከሰለጠነው ሕሊናቸው ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ቢፈቅዱላቸው መልካም ነበር። ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ይህም ሊያስደንቀን አይገባም፤ ምክንያቱም ራኡ የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔን አሳደውኝ እንደሆኑ እናንተንም ደግሞ ያሳድዷችኋል” ብሏል። (ዮሐንስ 15:20) ከቀጥተኛ ስደት ሌላ የይሖዋ አገልጋዮች የተለያዩ ሌሎች የእምነት ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል።

ክርስቲያን ወጣቶች በትምህርት ቤት የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ለመቋቋም ብዙውን ጊዜ ጠንካራ እምነት ያስፈልጋቸዋል። ስድ አነጋገር ወይም አምላክን የሚያዋርድ ዝንባሌ ካላቸው የክፍል ጓደኞች ጋር ይገናኙ ይሆናል። ወጣት ክርስቲያኖች በብሔራዊ ስሜት፣ በክበቦች፣ በትምህርት ቤት ፖለቲካና በመንፈሳዊ ሊጎዱአቸው በሚችሉ ሌሎች እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፉ እየጨመረ የሚሄድ ግፊት ያጋጥማቸው ይሆናል። መምህራን ወይም ተማሪዎች ጓደኞቻቸው በወጣት ክርስቲያኖች ላይ አቋማቸውን ለማስለወጥ ተጽዕኖ ሊያደርጉባቸው ይሞክሩ ይሆናል። ስለዚህ አምላካዊ ወጣቶች ስለ ተስፋቸው ግልጽ የሆነ መከላከያ መልስ ለመስጠት የሚያስፈልገውን እምነት እንዲያገኙ በይሖዋ መንፈስ ላይ መተማመን አለባቸው።​—ማቴዎስ 10:19, 20፤ ገላትያ 5:22, 23

‘መከላከያ መልስ ለመስጠት ዝግጁ ሁኑ’

የሐዋርያው ጴጥሮስ ምክር ለወጣቶችም ሆነ ለጐልማሳ ክርስቲያኖች ተገቢ ነው። እንዲህ አለ፦ “በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያት ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ [መከላከያ] መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ። ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት (በጥልቅ አክብሮት) ይሁን።” (1 ጴጥሮስ 3:15) እንዲህ ዓይነቱ መከላከያ መልስ ለመስጠት ዝግጁ ለመሆን ምን ይጠይቃል? መጀመሪያ ቅዱሳን ጽሑፎች ምን እንደሚያስተምሩ መረዳት አለባችሁ። በትምህርት ቤት ውስጥ ለሚነሱ እንደ ብሔራዊ ስሜት፣ ፖለቲካ፣ በአደንዛዥ ዕጽ መጠቀም፣ ወይም ሥነ ምግባርን የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ አቋም ለመውሰድ ለዚያ ክርስቲያናዊ አቋም በመጀመሪያ ምክንያቱን መረዳት በተጨማሪም ከልብ የምታምኑበት መሆን አለባችሁ።

ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያን መሰሎቹ እንዲህ ሲል ነገራቸው፦ “አትሳቱ፣ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን ዐመል ያጠፋል።” (1 ቆሮንቶስ 15:33) ከዚያ ምክር ጋር ትስማማለህን? ጳውሎስ እንዳመለከተው በባልንጀርነት ጉዳይ መሳሳት ቀላል ነው። ሰውየው ወዳጃዊና ተስማሚ ጠባይ ያለው ይመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ አንተ ለይሖዋ አገልግሎት ያለህ ዓይነት ፍላጎት ከሌለው ወይም ጭራሽ በመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች የማያምን ከሆነ መጥፎ ባልንጀራ ነው። ለምን? ምክንያቱም ሕይወቱ የተመሠረተው በተለዩ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ስለሆነና ለአንድ ክርስቲያን በጣም አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ለሱ ጉዳዩ ስለማይሆኑ ነው።

ኢየሱስ ስለተከታዮቹ “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ እነሱም ከዓለም አይደሉም” ብሎ ስለተናገረ ይህ አያስደንቅም። (ዮሐንስ 17:16) ለአንድ ሰው እውነተኛ ክርስቲያን መሆንና ወዲያውም አብሮ አምላኩ ሰይጣን የሆነለት የዚህ ዓለም ክፍል መሆን አይቻልም። (2 ቆሮንቶስ 4:4) እንዲህ ዓይነቱ ከዓለም መለየት አንድን ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ ብዙዎችን ከወረረው ብልሹ ጠባይና ጠበኝነት እንዴት እንደሚጠብቃቸው ይታይሃልን? ከሆነ የተለየህ ሆነህ መቆየትህ በአንዳንድ የትምህርት ቤት እንቅስቃሴዎች መካፈል አትችልም ማለት ቢሆንም እንኳ ለምን የተለየህ መሆን እንዳለብህ ሊገባህ ይችላል።a

በእምነት ጥብቅ የመሆንና የመንግሥቱን ፍላጎቶች በሕይወት ውስጥ ቅድሚያ የመስጠት አስፈላጊነት በአንዲት ወጣት ክርስቲያን ልጃገረድ ላይ በደረሰው ሁኔታ ላይ ታይቷል። (ማቴዎስ 6:33) የትምህርት ቤት የምረቃ ሥነ ሥርዓት ልምምድ መቼ እንደሚሆን ማስታወቂያ ሲነገር ቀኑ በይሖዋ ምሥክሮች የክልል ስብሰባ ላይ ከምትካፈልበት ቀን ጋር ተገጣጠመባት። ከልምምዱ የምትቀርበትን ምክንያት በአክብሮት ጽፋ መምህሯ ወደ ክፍል ከመግባቱ በፊት ሰጠችው። ከክፍል በኋላ መምህሩ ለብቻዋ ገለል አድርጎ ለልምምዱ ለምን እንደማትገኝ ምክንያቷን እንደገና እንድታስረዳ ጠየቃት። ልጅቱ “ቃሌ ያው መሆኑን መረዳት ነበረ የፈለገው። በደብዳቤው ላይ የጻፍኩት የራሴን ስሜት መሆኑን ወይም የናቴ ሐሳብ መሆኑን ማረጋገጥ ፈለገ። በጉዳዩ ላይ የራሴ እምነት እንዳለበት ሲመለከት አልተቃወመም።”

‘በሁሉም ፊት መከላከያ መልስ ስጥ’

ክርስቲያን ወጣቶች አከራካሪው ጉዳይ ከመነሣቱ በፊት ለፋኩልቲ አባሎቹና ለተማሪዎች አቋማቸውን በይፋ ካስታወቁ ችግሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ተጽዕኖው ያን ያህል ከባድ እንደማይሆን ያገኙታል። አንዲት ጃፓናዊት ወጣት ክርስቲያን የ11 ዓመት ዕድሜ በነበረች ጊዜ ትምህርት ቤቱ ሁሉም ተማሪዎች በገና ጊዜ በሚዘጋጀው ግብዣ ላይ እንዲገኙ እንደጠየቀ ትናገራለች። የከፍተኛ ትምህርት ክፍሏ ተማሪዎች እንድትሳተፍ ተጽዕኖ አደረጉ፤ እሷ ግን አልተገኘችም ነበር። መምህሯም አቋሟን ተረድቶላት ነበር። ለምን? ምክንያቱም ገና ትምህርት ቤቱ እንደተከፈተ አካባቢ ምስክሯና ወላጆቿ ከመምህሩ ጋር ተገናኝተው ስለ ክርስቲያናዊ አቋማቸው የተለያዩ ገጽታዎች አስረድተው ስለነበረ ነው።

በመስክ አገልግሎት በሚካፈሉበት ጊዜ አንዳንድ ወጣት ክርስቲያኖች የክፍል ጓደኞቻቸውን ወይም መምህሮቻቸውን እንዳያገኙ ይፈራሉ። አንተም እንደዚያ ይሰማሃልን? ከሆነ ከቤት ወደቤት እንደምትሰብክና ለምን እንደምትሰብክ አስቀድመህ ለምን አትነግራቸውም? አንድ የ14 ዓመት የይሖዋ ምሥክር እንዲህ በማለት ገለጸ፦ “በትምህርት ቤቴ እያንዳንዱ ሰው እንደ ክርስቲያን መጠን ያለኝን አቋም ያውቃል። ይህን በደንብ ስለሚያውቁ በመስክ አገልግሎት ስካፈል የክፍል ጓደኞቼን ባገኝ ሃፍረት አይሰማኝም። አብረውኝ የሚማሩም አብዛኛውን ጊዜ ያዳምጡኛል። ብዙ ጊዜም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ይቀበላሉ።” የ12 ዓመት ልጅ እንደተናገረው በአገልግሎት ሲሳተፍ የክፍል ጓደኞቹን እንደሚያገኝ በመጠበቅ አስቀድሞ ዝግጅት ያደርጋል። ገና በሐሳብ ከመደናገጥ ይልቅ ሲያጋጥሙት ምን እንደሚላቸው በልቡ ያሰላስላል። ስለዚህ ለእምነቱ ጠንካራ ምክንያት ለመስጠት ዝግጁ ነው።

በብዙ ትምህርት ቤቶች ከትምህርት ሰዓት ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የምርጫ ጉዳይ ናቸው ይባላል። በተግባር ግን መምህራንና ተማሪዎች በእንዲህ ዓይነቶቹ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፉ ከፍተኛ ግፊት ያደርጋሉ። የ20 ዓመት ክርስቲያን ይህን ግፊት ለመቋቋም ጥሩ ዘዴ አገኘች፤ እንዲህ ትላለች፦ “የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ሁሉ በረዳት አቅኚነት አገለግል ነበር። እያንዳንዱ ሰው እኔ በሃይማኖታዊ የሥራ እንቅስቃሴዎች ጊዜየ እንደተያዘ ያውቅ ነበር።” የዚህች ምሥክር ታናሽ እህት ተመሳሳይ መንገድ ተከተለች። አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች በትምህርት ቤት ዘመናቸው በረዳት አቅኚነት ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ በቀጥታ የሙሉ ጊዜ የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ሆነዋል።

የምታሳየው ጥሩ ጠባይና በድፍረት የምትሰጠው ምሥክርነት የሚያስከትለውን መልካም ውጤት ፈጽሞ ችላ አትበለው። ዝም ከማለት ይልቅ በአክብሮት ሆኖ በድፍረት በመናገር በእምነት ጥብቅ መሆንህን ለምን አታሳይም? በምርኰ ተወስዳ በሦርያዊው የጦር አዛዥ በንዕማን ቤት የነበረችው እሥራኤላዊት ልጃገረድ ያደረገችው ይህንኑ ነበር። (2 ነገሥት 5:2-4) ያች ወጣት ልጃገረድ ሳትጠየቅ ባቀረበችው ሐሳብ ምክንያት የይሖዋ ስም ሊከበር ችሏል። ባንተም በኩል ተመሳሳይ እምነት ማሳየትህ ለአምላክ ክብርን ሊያመጣና ሌሎችም የስሙ አክባሪዎች በመሆን አቋም እንዲወስዱ ሊረዳ ይችላል።

ሐቁ እምነታችንን አላልተን በመያዝ ክርስቲያን ሆነን ለመቀጠል ያለመቻላችን ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ። በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።” (ማቴዎስ 10:32, 33) የኢየሱስ ተከታይ በመሆን በእምነት ጥብቅ መሆን ከባድ ኃላፊነት አይደለምን?

የምታገኘው እርዳታ

እንደ አንድ የይሖዋ ምስክር መጠን ጥብቅ አቋም ለመያዝ ጠንካራ እምነት ያስፈልግሃል። ለዚህም ሲባል መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናት፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መገኘትና በመስክ አገልግሎት መካፈል አለብህ። አሁንም የጐደለህ ነገር እንዳለ የሚሰማህ ከሆነ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ አለ፦ “ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጐድለው ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን ለእርሱም ይሰጠዋል።” (ያዕቆብ 1:5) ችግርህን ለይሖዋ በጸሎት ንገረው፤ እሱም መከራን ወይም የእምነትህን መፈተን እንድትቋቋም ሊያጠነክርህ ይችላል።

አንድ ወጣት ክርስቲያን ሌላስ ምን ሊያደርግ ይችላል? የምሳሌ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “የወለደህን አባትህን ስማ፤ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት።” (ምሳሌ 23:22) ጳውሎስም “ልጆች ሆይ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ” ስላለ ይህን የምሳሌ ምክር ደግፎታል። (ቆላስይስ 3:20) ክርስቲያን ወላጆች በእምነት ጥብቅ እንድትሆን ሊረዱህ ይችላሉ። በእነርሱ እየተረዳህ በቅዱሳን ጽሑፎችና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎች ላይ ጠቃሚ ሐሳቦችን፣ ምክሮችንና ተሞክሮዎችን ፈልግ። አንተና ወላጆችህ እንደዚህ ስታደርጉ በዚህ ልትደሰቱ ትችላላችሁ፤ ይህም ዓይነ አፋርነትን ወይም ፍርሃትን እንድታሸንፍ ሊረዳህ ይችላል።​—2 ጢሞቴዎስ 1:7

ይሖዋ አምላክ በክርስቲያን ጉባኤ በኩል ያደረጋቸውን ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ተጠቀምባቸው። ለስብሰባዎች በሚገባ ተዘጋጅ። አሁን አንተን እያጋጠሙህ ካሉት ሁኔታዎች ጋር የሚመሳሰሉ ተሞክሮዎችን ካሳለፉ የተሾሙ ሽማግሌዎችና ሌሎች ሰዎች ጋር ተነጋገር። ሰለሞን እንዲህ አለ፦ “ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብን ይጨምራል። አስተዋይም መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል።” (ምሳሌ 1:5) ስለዚህ ከእነዚህ ከታላላቆችህ ተማር። በተጨማሪም ያንተን ዓይነት ችግሮች በተሳካ ሁኔታ እየተቋቋሙ ካሉ ወጣት ክርስቲያኖች ልትማር ትችላለህ።

ታማኝነት በረከቶችን ያመጣል

በእምነት ጥብቅ ሆነህ በመቆም “የምትደላደሉ የማትነቃነቁም የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ” የሚለውን የጳውሎስን ምክር በሥራ ላይ ታውላለህ። (1 ቆሮንቶስ 15:58) የሚያጋጥምህን ችግር ይሖዋ ያውቃል፣ ይረዳልሃልም። ተመሳሳይ ችግሮች ያጋጠሟቸውን ብዙዎችን አጠንክሯቸዋል፤ አንተንም ያጠነክርሃል። በአምላክ ላይ ከተመካህ እርሱ ይደግፍሃል፤ ምክንያቱም መዝሙራዊው “ትካዜህን በይሖዋ ላይ ጣል። እርሱም ይደግፍሃል። ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም” ብሏል።​—መዝሙር 55:22

ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጐ ሕሊና ይኑራችሁ።” (1 ጴጥሮስ 3:16) የአምላክን ጻድቅ ሕጐችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በተመለከተ አቋምህን ለመለወጥ ወይም ለማላላት እምቢ ካልክ ጥሩ ሕሊና ይኖርሃል። ይህም ከይሖዋ የሚገኝ ግሩም በረከት ነው። ከዚህም በላይ እምነታቸው ደከም ለሚል ለአንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች ጥሩ ምሳሌ ትሆናለህ። (1 ጢሞቴዎስ 4:15, 16) የምታሳየው ጠባይ እነሱም በእምነት ጥብቅ እንዲሆኑና በፈተናዎች ለመጽናት ጥረት እንዲያደርጉ ሊያበረታታቸው ይችላል።

እንዲያውም መጀመሪያ ላይ ክርስቲያናዊ አቋምህን ይቃወሙ የነበሩትንም እንኳ ልትረዳቸው ትችል ይሆናል። “ወይም ይህ ወይም ያ ማናቸው እንዲበቅል ወይም ሁለቱ መልካም ይሁኑ አታውቅምና በማለዳ ዘርህን ዝራ በማታም እጅህን አትተው” የሚሉትን እነዚህን በተስፋ የሚሞሉ ቃላት አስታውሳቸው። (መክብብ 11:6) በታማኝነት ሥራዎችህ በምትዘራው ዘር የሚመጡትን መልካም ውጤቶች ማን ያውቃል?

ከምታጭዳቸው ታላላቅ በረከቶች መካከል ከይሖዋ ጋር ጥሩ አቋም መያዝህ ነው። በእምነት ጥብቅ መሆንህ በመጨረሻም የዘላለም ሕይወትን ያመጣል። (ዮሐንስ 17:3፤ ከያዕቆብ 1:12 ጋር አወዳድር) አቋምን በማላላት ከፈተና ምንም ዓይነት ጊዜያዊ ፋታ ለማግኘት መሞከር ያንን ስጦታ ማጣት ማለት ስለሆነ ከባድ ኪሣራ ነው።

በዚህ ርዕሰ ትምህርት መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው ወጣትስ? በዚህ ፈታኝ ጊዜ ጸንቷል። የትምህርት ቤቱ ስብሰባ ካለቀ በኋላ አቋሙን በጥበብ ለመምህራን ለማስረዳት ሞከረ። ሰሚ ጆሮ ባያገኝም የይሖዋን ልብ እንዳስደሰተ በማወቁ እርካታ አግኝቷል። (ምሳሌ 27:11) ትምህርቱን እስኪጨርስ ድረስ ለእምነቱ መከላከያ መልስ መስጠቱን ቀጠለ። ከዚያም አቅኚ ሆነ። ያንተም የታማኝነት ጽናት እንዲህ ዓይነት አስደሳች ውጤት የሚያስገኝ ይሁን። በእምነት ጥብቅ ከሆንክ እንደዚያ መሆኑ አይቀርም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስለ እነዚህና እነዚህን ስለመሳሰሉ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የተብራራ ሐሳብ ለማግኘት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች፣ ሊሠሩ የሚችሉ መልሶቻቸው የተባለውን በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር፣ ኒው ዮርክ የታተመውን መጽሐፍ ተመልከት።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የምታገኘው እርዳታ

◻ ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን የወላጆችህን የጥበብ ምክር አድምጥ።

◻ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ካሉት መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ተጠቀም።

◻ ያንተ ዓይነት ችግር ከደረሰባቸው የተሾሙ ሽማግሌዎችና ሌሎች ጋር ተነጋገር።

◻ ተመሳሳይ መሰናክሎችን በተሳካ ሁኔታ እየተቋቋሙ ካሉ ሌሎች ወጣት ክርስቲያኖች ጋር ተነጋገር።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ