የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 8/15 ገጽ 8-12
  • ነፃነት ለማግኘት የተደረገ ጥረት—ሴኔጋል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ነፃነት ለማግኘት የተደረገ ጥረት—ሴኔጋል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ‘ይሖዋ ይህን ሕንፃ እንድታገኙ ፈልጎአል’
  • ከሚሲዮናውያን ጋር በመስክ ማገልገል
  • በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ነፃ መሆን
  • ከአንድ በላይ ማግባት ክርስቲያናዊ ከሆነው የአንድ ለአንድ ጋብቻ ጋር ሲነፃፀር
  • የመናፍስት አምልኮ ከእውነተኛው አምልኮ ጋር ሲነፃፀር
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 8/15 ገጽ 8-12

ነፃነት ለማግኘት የተደረገ ጥረት—ሴኔጋል

የሴኔጋል ዘመናዊ ዋና ከተማ ከሆነችው ከዳካር የባሕር ዳርቻ ትንሽ ራቅ ብሎ ትንሹ የጎሪ ደሴት ይገኛል። በእርሱም ላይ የጨለማውን የታሪክ ዘመን የሚያስታውስ በ1776 የተሠራ የባሪያዎች ቤት ቆሞ ይታያል።

ይህ ከ150 እስከ 200 ባሮች ወደ ሩቅ አገሮች በመርከብ እስኪላኩ ድረስ እስከ ሦስት ለሚደርሱ ወራት በአሳዛኝ ሁኔታ ከሚታፈጉባቸው ቤቶች መካከል አንዱ ነው። የቤተሰብ አባሎች እንደገና ሊገናኙ በማይችሉበት ሁኔታ ይለያያሉ። አባትየው በሰሜን አሜሪካ ወደሚገኘው ወደ ሉዚያና ሊላክ ይችላል፤ እናትየዋ ደግሞ ወደ ብራዚል ወይም ወደ ኩባ እንዲሁም ልጆቹ ወደ ሃይቲ፣ ጋያና ወይም ማርቲኒክ ሊላኩ ይችላሉ። ይህ ለሰብዓዊ ነፃነት አክብሮት የጎደለው ድርጊት ነው። በተጨማሪም ነፃነት ሁሉም ሰው ያላገኘው ውድ መብት መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ነው።

ይህንን ለማወቅ የቻልኩት በአፍሪካ ምዕራባዊ ጫፍ ወደምትገኘው ወደ ሴኔጋል በአውሮፕላን ስሄድ ካነበብኩት የቱሪስት ብሮሹር ነው። ሴኔጋል በሰሜንና በምሥራቅ ባሉት በረሃዎች እንዲሁም በደቡብ በሚገኘው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ መካከል የምትገኝ ሣርማ ወይም የሳቫና ምድር ነች። በዚህ አገር ግርማ ያለውን ባለ ረጅም ዕድሜ የባኦባብ ዛፍ የጦጣ ዳቦ ተብሎ ከሚታወቀው የሚያጓጓ ፍሬው ጋር ልታገኙት ትችላላችሁ። የታርታር ክሬም የሚሠራው ከዚህ ፍሬ ነው። በተጨማሪም ይህ የጦጣዎችና የተለያየ ቀለም ያላቸው ወፎች እንዲሁም በማንጎ ዛፎች ሥር የተሠሩ ለየት ያሉ መንደሮች አገር ነው።

ለብዙ ጊዜ በናፍቆት ስጠብቀው የቆየሁትን ይህንን የምዕራብ አፍሪካ በር በሆነችው አገር የማደርገውን ጉብኝት ቁጭ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። ዛሬ ከብዙ የተለያዩ ዘሮች የተውጣጡ ሰባት ሚልዮን ሰዎች የሚኖሩባት ሴኔጋል ሙሉ ነፃነት አግኝታለች። ይሁን እንጂ አንድ ሰው በአካል ነፃ ሆኖ እውነተኛውን ነፃነት ለሚያሳጡ ልማዶችና አጉል እምነቶች ባሪያ ሊሆን ይችላልን? ከመንፈሳዊ ወንድሞቼ ጋር ለመገናኘትና በዚህ ዓለም ክፍል ውስጥ ሰዎችን ነጻ የሚያወጣው እውነት ምን ያህል እንደተስፋፋ ለማወቅ በጉጉት እጠባበቅ ጀመር።​—ዮሐንስ 8:32

‘ይሖዋ ይህን ሕንፃ እንድታገኙ ፈልጎአል’

በአጀንዳዬ ላይ መጀመሪያ የያዝኩት በዳካር የሚገኘውን የመጠበቂያ ግንብ የቅርጫፍ ቢሮና የሚሲዮናውያንን ቤት ለመጎብኘት ነው። በከተማው ዳርቻ ወደሚገኘው ዘመናዊ መልክ ያለው ሕንጻ ስንደርስ ከፊት ለፊት በትልቁ የተጻፈ J የሚል ምልክት አየሁ። የቅርጫፍ ቢሮውን ስጎበኝ መጀመሪያ ያነሳሁት ጥያቄ J የተባለው ፊደል ለምን የቆመ ነው የሚል ነበር።

አስጎብኚዬ “ይህ በጣም የሚያስገርም ነው። በ1985 ለቅርንጫፍ ቢሮአችን የሚያገለግል ሰፋ ያለ ሕንጻ ስንፈልግ ያን ጊዜ ገና በመሠራት ላይ የነበረውን ይህን ሕንፃ አይተነው ነበር። ሆኖ እኛ ከምንፈልገው በላይ በጣም ትልቅ እንደሆነ ተሰማን። ባለቤቱ የይሖዋ ምስክሮች መሆናችንን ሲሰማ ሐቀኝነታችንን ስለሚያውቅ ሕንፃውን ለእኛ ለማከራየት በጣም ፈለገ። ‘አምላካችሁ ይሖዋ ይህን ሕንፃ እንድታገኙ ፈልጓል’ አለን። ‘ተመልከቱ በፊት ለፊት ላይ በትልቁ J የሚል ፊደል ይታያል! ይህ ፊደል እዚህ ላይ እንዲቀመጥ ያደረግኩት ጆን ለሚለው ስሜ ምልክት እንዲሆን ነበር፤ አሁን ግን ይሖዋ ለሚባለው አምላክ ስም ምልክት ይሆናል!’ በዚህ ጥሩ ሕንፃ ውስጥ ባሳለፍናቸው አምስት ዓመታት ብዙ ተደስተናል።”

ቀጥሎ በሴኔጋል ውስጥ የስብከቱ ሥራ እንዴት እንደተጀመረ ለማወቅ ፈለግሁ።

“ነጻ የሚያወጣው የእውነት ውሃ ወደ ሴኔጋል የገባው በ1950ዎቹ አመታት መጀመሪያ ለኮንትራት ሥራ ከፈረንሳይ መጥቶ በነበረ አንድ የይሖዋ ምስክር አማካኝነት ነበር። በ1965 የፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆኑትን የሴኔጋልን፣ የማሊንና የሞሪታኒያን እንዲሁም የእንግሊዝኛ ተናጋሪ አገር የሆነችውን የጋምቢያን ሥራ የሚከታተል አንድ የቅርንጫፍ ቢሮ በዳካር ተከፈተ። ከ1986 ጀምሮም የፖርቹጋል ቋንቋ በሚነገርባት በጊኒ ቢሳው ውስጥ ላለውም ሥራ እርዳታ በማድረግ ላይ እንገኛለን።”

በዚህ አገር ከሚኖሩት ሰዎች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ክርስቲያኖች አለመሆናቸውን በአእምሮዬ በመያዝ ምን እድገት እንደተደረገ ጥያቄ አቀረብኩ። አስጎብኚዬ እንዲህ አለ፦ “በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አለመተዋወቃቸው እውነት ነው፤ ነገር ግን ሥራው ያለማቋረጥ ወደፊት በመግፋት ላይ ነው። በጥር 1991 የመንግሥቱ አስፋፊዎች 596 በመድረሳቸው በጣም ተደስተናል። ይህም የአገሪቱ ተወላጆች የሆኑ ወንድሞችና ሚሲዮናውያን ጠንክረው እንደሚሠሩ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።”

“እዚህ የሚያገለግሉ ብዙ ሚሲዮናውያን እንዳሉ ተረድቼአለሁ” አልኩ።

“አዎን፣ በእኛ ሥር ባሉ የተለያዩ ክልሎች የተመደቡ 60 የሚሆኑ ሚሲዮናውያን አሉን፤ እነርሱም ከ13 አገሮች የመጡ ናቸው። ተግተው የሚሠሩ በመሆናቸው ምክንያት ሥራው ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋጽዎ አድርገዋል። ይህም መንፈስ የአገሩ ተወላጆች የሆኑ ወንድሞች ለእውነት በሚያሳዩት ፍቅርና ቅንዓት ታይቶአል። ብዙ ወንድሞች እንደ ሥራ ማጣትና ቁሳዊ ድህነት ያሉ ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም እንኳ በመስክ አገልግሎት በየወሩ ከ15 ሰዓት በላይ ያሳልፋሉ። በጉብኝትህ ወቅት ከእነዚህ ቀናተኛ ሠራተኞች ጋር እንደምትገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።”

ከእነዚህ ወንድሞች ጋር ለመገናኘት በጣም ጓጉቼ ነበር።

ከሚሲዮናውያን ጋር በመስክ ማገልገል

ማርጋሬት (እስከሞተችበት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለ20 ዓመታት ያህል ሚሲዮናዊ ሆና ያገለገለች) በከተማው መካከል ወዳለው ክልልዋ ይዛኝ ለመሄድ ፈቃደኛ ሆነች። የአገሪቱን ሰዎች አኗኗር ለመቅመስ ስንል ፈጣን መኪና በሚባለው መጓጓዣ ተሳፍረን ሄድን። በተደጋጋሚ ብዙ ቦታ የሚቆም ትንሽ አውቶቡስ ነበር። 25 ተሳፋሪዎችን ይይዛል። ሁሉም ተሳፋሪዎች ቀጫጭኖች ቢሆኑ ኖሮ ጉዞው የተሻለ ምቾት ይኖረው ነበር። እኔ በተቀመጥኩበት አግዳሚ ወንበር ላይ የተቀመጡት ሁለት ሴቶች ግን ቀጭኖች አልነበሩም፤ ቢሆንም ሁኔታውን በፈገግታ ተቀበልኩት።

ወደ መውረጃችን ስንደርስ ማርጋሬት “በመሐል ከተማ በሚገኘው ክልሌ ውስጥ ብዙ የሚያስደንቁ ነገሮችን ለመመልከት ትችላለህ” በማለት ገለጸችልኝ። በእግረኛ መንገድ ላይ ወዳሉ ጫማ ሠሪዎች እያመለከተች “እነዚያ የሚያምሩ ነጠላ ጫማዎች ይታዩሃል?” በማለት ጠየቀችኝ። “ቀለም ከተቀቡ የበግና የፍየል ቆዳዎች የተሠሩ ናቸው።” ወደ ነጠላ ጫማ ሠራተኞቹ ቀረብን፤ ማርጋሬት ዎሎፍ በሚባለው ቋንቋቸው መልዕክቱን አቀረበችላቸው። በትኩረት ያዳምጡ ነበር፤ አስደሳች መልክ ባለው ብሮሹር ውስጥ ያለውን የአዳምንና የሔዋንን ሥዕል ሲመለከቱ በጣም ተደነቁ።

ወዲያውኑ የተለያዩ ዓይነት ዕቃዎችን የያዙ በዚህ አካባቢ የባና ባና ሰዎች እየተባሉ የሚታወቁ ሱቅ በደረቴዎች መጡ። አንዳንዶቹ መጥረጊያ ይዘዋል፤ ሌሎቹም ልብስ፣ ቁልፎች፣ መድሃኒት፣ ቦርሳዎች፣ ብርቱካንና ከነነፍሳቸው ያሉ ወፎችን ሳይቀር ይዘዋል። አንዱ እኩል ለእኩል ከተከፈለ ቅልና ከበትር ተሠርቶ በሁለቱም እጆች የሚጫወቱበትን ኮራ የሚባለውን የጅማት የሙዚቃ መሣሪያ ሊሸጥልኝ መጣ። ከሙዚቃ መሣሪያው በስተጀርባ ከቆዳ፣ ከፍየል ቀንድና ከትንንሽ “የመልካም ዕድል” ሼሎች የተሰራ አንድ ምስል እንዳለ ተመለከትኩ። ከጥንቆላ ወይም ክርስቲያናዊ ካልሆኑ የአምልኮ ሥርዓቶች ጋር ግንኙነት ባላቸው ምስሎች ያጌጠ ምንም ነገር እንደማንገዛ ገለጥንለት። ባና ባናው ሰውዬ እርሱ ራሱ እስላም እንደሆነ በመግለጽ በዚህ መስማማቱ አስገረመን። ኮራውን ቦቡ ከሚባለው ቀሚሱ ሥር ደብቆ ማርጋሬት በአረብኛ የተዘጋጀውን ብሮሹር ስታሳየው በጥንቃቄ ያዳምጥ ነበር። በጣም ስሜቱ ስለተነካ ብሮሹሩን ወስዶ እዚያው ማንበብ ጀመረ። ምስጋናውን በሰፊው ከገለጸልን በኋላ ብሮሹሩንና ያልተሸጠውን ኮራ ይዞ ሄደ። ብሮሸሩን በቤቱ እንደሚያጠናው እርግጠኞች ነበርን።

ከዚህ በኋላ ለ20 ዓመታት ሚሲዮናዊ ሆኖ ያገለገለውን ጆንን አነጋገርኩት።

“የዚህ አገር ሰዎች ሰው ወዳዶች ናቸው። ያገኘኸውን ሰው ሁሉ ልታነጋግር ትችላለህ” በማለት ጆን ነገረኝ። “‘አሳላም አሌኩም’ የሚለው የተለመደ ሰላምታ‘ሰላም ለአንተ ይሁን’ ማለት ሲሆን አብዛኞቹ ሰዎችም ሰላማውያን ናቸው። ይህ ቴራንጋ ወይም እንግዳ ተቀባይ አገር ነው። እንግዳ ተቀባይነታቸውም በደግነታቸው፣ ሞቅ ባለ ስሜታቸውና ደስተኞች በመሆናቸው ይታያል።” አሁን ብዙ ወጣት የሆኑ ከሌላ አገር የመጡ ምስክሮች ቤተሰቦቻቸውንና ጓደኞቻቸውን ትተው በዚህ ሚሲዮናዊ መስክ ለብዙ ዓመታት እንዴት ለማገልገል እንደቻሉ ገባኝ።

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ነፃ መሆን

የሚሲዮናውያኑ መንፈስ የአገሪቱ ተወላጆች በሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ጥልቅ የሆነ ተጽዕኖ አሳድሯል። በተለይ የሥራ መጥፋት በጣም የተስፋፋ በመሆኑና የሙሉ ጊዜ አቅኚነት አገልግሎት መቀበል ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን ስንመለከት ያላቸውን የአቅኚነት መንፈስ ለማድነቅ እንችላለን። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በመማር ከብዙ ጎጂ ልማዶች ነፃ የወጡት ማርሴልና ሉሲየን እንዲህ ሲሉ ይገልጻሉ፦

“አድናቆታችንን የአቅኚነትን አገልግሎት በመቀበል ለማሳየት ፈለግን። ሆኖም የትርፍ ሰዓት ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ሆነ። የአትክልተኝነት ሥራ ሞከርን ነገር ግን አላዋጣንም። ልብሶችን ማጠብ ደግሞ ብዙውን ጊዜያችንን ወሰደብን። አሁን አንዳንድ ዳቦ ቤቶችን የዘወትር ደንበኞቻችን በማድረግ በዳቦ ጋጋሪነት ሥራ ላይ እንገኛለን፤ ይህም ጥሩ ውጤት እያስገኘ ነው።” በግልጽ እንደሚታየው ከፍተኛ የሆነ እምነትና ውሳኔ እንዲሁም ልባዊ ጥረትን የሚጠይቅ ነው፤ ሆኖም የኤኮኖሚ ሁኔታዎች አስቸጋሪ በሚሆኑበትም ጊዜ እንኳ ቢሆን ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት እንደሚቻል የሚያሳይ ምሳሌ ነው።

ሚሼል ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በጀመረበት ጊዜ በዳካር ዩንቨርሲቲ ውስጥ ይማር ነበር። ሚሼል “አብዛኞቹ ተማሪዎች በሚያሳዩት የብልግና መንፈስ እጨነቅ ነበር፤ ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎችም ያስቸግሩኝ ነበር” በማለት ይናገራል። “ሰው እንደነዚህ ላሉት ጎጂ ልማዶችና ሁኔታዎች ባሪያ የሆነው ለምንድነው? መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን ሰጠኝ። ከትከሻዬ ላይ ከባድ ሸክም እንደወረደልኝ ያህል ነበር። ወላጆቼ ትምህርቴን በትጋት እንድቀጥል ቢጨቀጭቁኝም ወደ ረዳት አቅኚነት አገልግሎት ገባሁ፤ ከዚያም በዩንቨርሲቲው በቆየሁበት በቀረው ጊዜ የዘወትር አቅኚ ሆኜ አገለገልኩ። በቅርቡ ከሥፍራው በሚወገደው ሥርዓት ውስጥ የሚገኘውን የሥራ እድገት መከታተል ሳይሆን አቅኚ በመሆን ምሥራቹን ለሌሎች ሰዎች ማካፈል ከፍተኛ ደስታ አመጣልኝ።” ሚሼል አሁን በማቦር ልዩ አቅኚ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

ከአንድ በላይ ማግባት ክርስቲያናዊ ከሆነው የአንድ ለአንድ ጋብቻ ጋር ሲነፃፀር

የአገሩ ልማዶች ከክርስቲያን መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጩበት ጊዜ አለ። ይህም ልዩ የሆኑ ፈታኝ ሁኔታዎችን ሊያመጣ ይችላል። በትልቁ ዳካር ከሚገኙት ስድስት ጉባኤዎች ውስጥ በአንዱ መሪ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው አሊውን እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ነፃ የሚያወጣውን እውነት በመጀመሪያ ስሰማ ሁለት ሚስቶች ነበሩኝ። እስላም ስለነበርኩ ሃይማኖቴ ከዚህም በላይ እንዳገባ ይፈቅድልኛል። አባቴ አራት ሚስቶች አሉት፤ ብዙዎቹ ጓደኞቼም አያሌ ሚስቶች አሏቸው። ይህ ልማድ እዚህ አፍሪካ ውስጥ ተቀባይነት ያለው ነው።” ይሁን እንጂ ይህ የአኗኗር መንገድ ምን ችግር ያስከትላል?

“ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት ብዙ ችግሮችን ሊፈጥር ይችላል” በማለት አሊዩን ይገልጻል፦ “በተለይም ልጆችን በተመለከተ ብዙ ችግር ያጋጥማል። ከመጀመሪያዋ ሚስቴ አሥር ልጆች ከሁለተኛዋ ደግሞ ሁለት ልጆች ወልጄአለሁ። በእንደዚህ ዓይነቶቹ ቤተሰቦች ውስጥ ብዙውን ጊዜ አባትየው ለልጆቹ እንግዳ ይሆናል። ስለዚህ እሱ ከሚሰጣቸው እርዳታና ተግሣጽ ሊጠቀሙ አይችሉም። በነገራችን ላይ ሁለት ሚስቶች ማግባቴ ከዝሙትም ቢሆን አልጠበቀኝም። ከዝሙት እንድጠበቅ የረዳኝ የአምላክ መንፈስ ፍሬ የሆነው ራስን መግዛት ነው።” ታዲያ አሊዮን ምን አደረገ?

እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “ሁለተኛዋን ሚስቴን ወደ ወላጆችዋ ቤት እንድትመለስ አደረግሁ። ይህን ያደረግሁት እርስዋን የምጠላበት ነገር ስላገኘሁ ሳይሆን ከአምላክ ብቃቶች ጋር ለመስማማት እንደሆነ በዘዴ ገለጽኩላት። አሥሩን ልጆቼን በሙሉ በሥጋዊና በመንፈሳዊ ለመንከባከብ ልዩ ዝግጅት አደረግሁኝ። ስለዚህ ዛሬ እነርሱም ጭምር ይሖዋን እያገለገሉ በመሆናቸው አመስጋኝ ነኝ። አስፋፊዎች ከሆኑት ከዘጠኙ ውስጥ አምስቱ ተጠምቀዋል፤ ሁለቱ ልዩ አቅኚዎች ሆነው ያገለግላሉ፤ ሌሎቹ ሦስቱ ደግሞ የዘወትርና ረዳት አቅኚዎች ናቸው። እውነት ልጆችን ከማሳደግ ጋር ከተያያዙ ከብዙ ችግሮች ነፃ አውጥቶኛል።”

የመናፍስት አምልኮ ከእውነተኛው አምልኮ ጋር ሲነፃፀር

የሚቀጥለው ጉዞዬ በደቡብ የሚገኘውን የካሳማንስ ግዛት ለመጎብኘት ነው። የሚታየው ነገር ሁሉ ለምለምና አረንጓዴ በመሆኑ በጣም ተገረምኩ። 288 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው አካባቢ ከትልቁ የካሳማንስ ወንዝ የመስኖ ውሃ የሚያገኝ በመሆኑ ሩዝ፣ በቆሎና ኦቾሎኒ በብዛት ይመረትበታል። በገጠሩ ክልል ክብ የሆኑ ሁለት ፎቅ ያላቸው ባለ ሣር ክዳን ጎጆዎች ተበታትነው ይገኛሉ፤ የጣሪያቸው ቅርጽ ለደረቁ የበጋ ወቅት ዝናብ ለማጠራቀም ሲባል እንደ ማንቆርቆሪያ ሆኖ የተሠራ ነው። ዋና ከተማዋ ዚጉኢንኮር በሰፊ የዘንባባ ዛፎች ጥላ ውስጥ የተገነባች ነች። በዚህም አካባቢ ቅንዓት ካላቸው የይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤ ጋር ለመገናኘት በመቻሌ በጣም ተደስቻለሁ።

በዚጉኢንኮርና በአካባቢው የሚሠራው ሚሲዮናዊው ዶሚኒክ በዚያ አካባቢ የሚከናወነው የስብከት ሥራ በሚያስደስት ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ነግሮኛል። እንዲህ አለ፦ “ከአሥር ዓመታት በፊት በዚጉኢንኮር ጉባኤ 18 አስፋፊዎች ነበሩ። አሁን 80 አስፋፊዎች ይገኛሉ። በዚህ ከፍተኛ ጭማሪ ምክንያት አዳራሹ በተሠራበት ቦታ በሚገኘው ቀይ የሸክላ አፈር በመጠቀም አንድ ቆንጆ የሆነ የመንግሥት አዳራሽ ሰርተናል። ይህም የግንባታ ሥራ ለአካባቢው ነዋሪዎች ትልቅ ምስክር ሆኖ ተገኝቷል። ከብዙ የተለያዩ ጎሣዎች የመጡ ሰዎች በሰላም በአንድነት አብረው ሲሠሩ የተመለከቱ ሰዎች ጥሩ የሆኑ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። በቅርቡ በተደረገው የክልል ስብሰባ ላይ የነበረው ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር 206 ሲሆን 4 ሰዎችም ተጠምቀዋል።”

በዚህ የሴኔጋል ክልል የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ቅድመ አያቶቻቸው ይከተሏቸው የነበሩትን የመናፍስት አምልኮ ይከተላሉ። ክርስቲያኖች ወይም እስላሞች ነን ቢሉም ጣዖቶችን ማምለካቸው አልቀረም። በዚጉኢንኮር ጉባኤ ሽማግሌ የሆነው ቪክቶር የነገረኝን ታሪክ በጥሞና አዳመጥኩ።

“እኔ የተወለድኩት በጊኒ በሚገኝ አንድ ትልቅ ጣዖት አምላኪ ቤተሰብ ውስጥ ነበር። ስወለድ አባቴ ለአንድ መንፈስ ወይም ጋኔን የተወሰንኩ እንድሆን አደረገ። የዚህን ጋኔን ሞገስ ለማግኘትም ከአልጋው ሥር ዘወትር ጥቁር የልብስ ሻንጣ አወጣና ትንሽ መሠዊያ ከሠራሁ በኋላ ጠባቂዬ የሆነው ጋኔን ምስል ለሆነው ቀንድ የደም መስዋዕት አቀርብ ነበር። ካቶሊክ ከሆንኩኝ በኋላም እንኳ ቢሆን ገና ባሪያ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር። ወደ ሴኔጋል ከሄድኩ በኋላ የይሖዋ ምስክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠኑኝ ጀመር። ሚስቴና እኔ ‘ከይሖዋና ከአጋንንት ማዕድ መብላታችንን’ መቀጠል እንደማንችል ተረዳን። (1 ቆሮንቶስ 10:21) ይሁን እንጂ መስዋዕት ማቅረቤን ሳቆም አጋንንት ያስጨንቁኝ ጀመሩ። ጥቁሩን የልብስ ሻንጣ ከያዛቸው አጋንንታዊ ዕቃዎች ጋር አውጥቼ ለመጣል ፈራሁ፤ ምክንያቱም እንዲህ በማድረጉ ምክንያት ሙሉ በሙሉ አእምሮውን የሳተ አንድ ሰው ስለማውቅ ነው።” ቪክቶር እንዴት ባለ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ገባ!

“በመጨረሻም በሮሜ 8:31, 38, 39 ላይ የሚገኙት ቃላት ከአጋንንታዊ አምልኮ ጋር ግንኙነት ያለውን ነገር ሁሉ ለማስወገድ የሚያስፈልገውን ኃይል ሰጡን። አሁን ትምክህታችንን በይሖዋ አምላክ ላይ ጥለናል። በእርግጥም ነፃ ወጥተናል። መላው ቤተሰቤ ሁሉም ሰው ከክፉ አጋንንት ተጽዕኖ ነፃ በሚሆንበት ምድራዊ ገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አስደናቂ ተስፋ አለው።”

በመጨረሻም የምሄድበት ጊዜ ደረሰ። ዕቃዎቼን ሳዘገጃጅ የማይረሳውን የሴኔጋል ጉብኝቴን እንደገና በአእምሮዬ ከለስኩት። ከዕፅ ሱሰኝነት፣ ከጾታ ብልግናና ከአጉል ልማዶች ነፃ ሆነው አሁን እውነተኛውን ነፃነት ካገኙ ከብዙ ሰዎች ጋር መገናኘትና መነጋገር እምነቴን የሚያጠነክርልኝ ሆኗል። ከባድ የሆኑ የኤኮኖሚ ችግሮች ቢኖሩባቸውም በገነት ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘትን የተረጋገጠ ተስፋ እንዲያገኙ ያደረጋቸውን ይሖዋን በማገልገል ደስታና እርካታ እያገኙ ናቸው። ‘በይሖዋ የበጎ ፈቃድ ዓመት ውስጥ’ እንዲህ ያለውን ምሥራች በሴኔጋል ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው ምድር ላይ እንዲሰበክ ላደረገው አምላክ ምንኛ አመስጋኞች ነን! (ኢሳይያስ 61:1, 2)​—አስተዋጽኦ።

[ገጽ 8 ላይ የሚገኘው ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሴኔጋል

ሴንት ሎወስ

ሎወጋ

ቲስ

ዳካር

ካዎላክ

ጋምቢያ

ባንጁል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ነፃ አውጪው የእውነት ውሃ በገጠሮቹ ውስጥ በነፃ ይታደላል

በዳካር ሴኔጋል የሚገኘው የይሖዋ ምስክሮች የሚሲዮናውያን ቤትና የቅርንጫፍ ቢሮ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በባሕሩ ዳርቻም ጭምር የሴኔጋል ሕዝብ ክርስቲያናዊውን መልዕክት ይሰማል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ