መልስ ማግኘታቸው የተረጋገጠላቸው ጸሎቶች
መልስ ማግኘታቸው የተረጋገጠላቸው ጸሎቶች አሉ። የእነዚህ ጸሎቶች ፍሬ ሐሳብ ኢየሱስ “እናንተስ እንዲህ ጸልዩ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” በማለት ለደቀመዛሙርቱ በተናገረው የናሙና ጸሎት ላይ ተገልጾአል።—ማቴዎስ 6:9-13
የኢየሱስ የናሙና ጸሎት አካል የሆኑት እነዚህ ቃላት በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠር ጊዜ ተደጋግመው ተጸልየዋል። ክርስቶስ የሱ እውነተኛ ተከታዮች ይህን ጸሎት ቃል በቃል እንዲደግሙ ባይጠይቃቸውም ተመሳሳይ ስሜቶችን የሚገልጸው ጸሎታቸው መልስ እንደሚያገኝ እርግጠኛ ነገር ነው። (ማቴዎስ 6:7, 8) የአምላክ ስም መቀደስ ምን ማለት ነው? መንግሥቱ እንድትመጣ የሚጸለየውስ ለምንድነው? የአምላክ ፈቃድ እንዲደረግ የሚለመነውስ ለምንድነው?
“ስምህ ይቀደስ”
ኢየሱስ “በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ” ብሎ የጠራው “በምድር ሁሉ ላይ ልዑል” የሆነውን ይሖዋን ነው። (መዝሙር 83:18) አምላክ እሥራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነፃ አድርጎ ከነሱ ጋር የቃል ኪዳን ዝምድና በተጋባ ጊዜ አባት ሆኖአቸዋል። (ዘዳግም 32:6, 18፤ ዘፀአት 4:22፤ ኢሳይያስ 63:16) በአሁኑ ጊዜ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይሖዋን እንደ አባታቸው አድርገው በጥልቅ ያከብሩታል። (ሮሜ 8:15) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ባልንጀሮቻቸውም ወደ ይሖዋ የሚጸልዩት አባታችን ሆይ! በማለት ነው።—ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 7:1-9
ይሁን እንጂ የአምላክ ስም እንዲቀደስ የሚጸልዩት እነማን ናቸው? የመጀመሪያዎቹ ሰብዓውያን ጥንዶች በኤደን ገነት ካመጹበት ጊዜ ጀምሮ በመለኰታዊው ስም ላይ ስድብ ሲከመርበት ቆይቷል። ይሖዋ ለዚህ ጸሎት መልስ ሲሰጥ በመታሰቢያ ስሙ ላይ የተጣለበትን ስድብ በሙሉ ያነጻል። (መዝሙር 135:13) ይህንንም የሚያደርገው ክፋትን ከምድር ላይ በማስወገድ ነው። አምላክ ይህንን ጊዜ በሚመለከት በነቢዩ ሕዝቅኤል በኩል እንዲህ ብሏል፦ “ታላቅ እሆናለሁ፤ እቀደስማለሁ፤ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ። እኔም ይሖዋ እንደሆንሁ ያውቃሉ።”—ሕዝቅኤል 38:23
ይሖዋ አምላክ ቅዱስና ንጹሕ ነው። ስለዚህ ስሙም ሊቀደስ ወይም ቅዱስ ሆኖ ሊለይ ይገባዋል። በፍጥረት ሁሉ ፊት ራሱን ለመቀደስ እርምጃ በመውሰድ ቅድስናውን ያሳያል። (ሕዝቅኤል 36:23) ሞገሡንና የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ይሖዋን በአክብሮታዊ ፍርሐት ሊመለከቱና ስሙን ከሌሎች ሁሉ ለይተውና ከፍ አድርገው በመያዝ ሊቀድሱት ይገባል። (ዘሌዋውያን 22:32፤ ኢሳይያስ 8:13፤ 29:23) በመሆኑም ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ስምህ ይቀደስ” ወይም “ቅዱስ ተደርጎ ይያዝ” “እንደ ቅዱስ ይቆጠር” ብለው እንዲጸልዩ ነገራቸው። አምላክ የኢየሱስ የናሙና ጸሎት ክፍል የሆነውን ይህን ጸሎት እንደሚመልስ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
“መንግሥትህ ትምጣ”
ኢየሱስ ለተከታዮቹ “መንግሥትህ ትምጣ” ብለውም እንዲጸልዩ ነግሯቸዋል። ለአምላክ መንግሥት መምጣት የሚደረጉት ጸሎቶች በእርግጥ መልስ ያገኛሉ። መንግሥቲቱ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስና በተባባሪዎቹ “ቅዱስ” እጅ በምትመራው በሰማያዊ መሲሐዊት መንግሥት በኩል የሚገለጸው የይሖዋ ሉዓላዊ አገዛዝ ነው። (ዳንኤል 7:13, 14, 18, 22, 27፤ ኢሳይያስ 9:6, 7) የይሖዋ ምሥክሮች ከረዥም ጊዜ በፊት ኢየሱስ ከ1914 ጀምሮ በሰማያዊ ንጉሥነት በዙፋን ላይ መቀመጡን በቅዱሳን ጽሑፎች አረጋግጠዋል። ታዲያ አንድ ሰው “መንግሥቲቱ እንድትመጣ” የሚጸልየው ለምንድነው?
መንግሥቲቱ እንድትመጣ መጸለይ ማለት በምድር ላይ ባሉት የመለኰታዊ አመራር ተቃዋሚዎች ላይ እንድትመጣ መለመን ማለት ነው። አሁን በቅርቡ “[የአምላክ] መንግሥት እነዚያን [ምድራዊ] መንግሥታት ትፈጫቸዋለች፣ ታጠፋቸውማለች። ለዘላለምም ትቆማለች።” (ዳንኤል 2:44) ይህ ሁኔታም ለይሖዋ ቅዱስ ስም መቀደስ ይረዳል።
“ፈቃድህ ትሁን”
ኢየሱስ በተጨማሪ ደቀመዛሙርቱ “ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። ይህም ይሖዋ ለምድር ካለው ፈቃድ ጋር በመስማማት እርምጃ እንዲወስድ መለመን ነው። መዝሙራዊው በመዝሙር 135:6-10 ላይ ከተናገረው ጋር ተመሳሳይ ነው፦ “በሰማይና በምድር በባሕርና በጥልቆች ሁሉ ይሖዋ የወደደውን ሁሉ አደረገ። ከምድር ዳር ደመናትን ያመጣል። በዝናብ ጊዜ መብረቅ አደረገ። ነፋሳትንም ከመዛግብቱ ያወጣል። የግብጽን በኩር ልጆች ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ መታ። ግብጽ ሆይ በመካከልሽ በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ ላይ ተአምራትንና ድንቅን ሰደደ። ብዙ ሕዝብን መታ፤ ብርቱዎቹንም ነገሥታት ገደለ።”
የይሖዋ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲሆን መጸለይ ለዚች ሉል ያለውን ዓላማውን እንዲፈጽም መለመን ነው። ይህም በጥንት ጊዜ በመጠኑ እንዳደረገው የተቃዋሚዎቹን ለዘለቄታው መወገድ ይጨምራል። (መዝሙር 83:9-18፤ ራእይ 19:19-21) የይሖዋ ፈቃድ በመላው ምድርና በጽንፈ ዓለሙ በሙሉ እንዲፈጸም የሚቀርበው ጸሎት በእርግጥ መልስ ያገኛል።
መንግሥቲቱ ስትገዛ
የአምላክ መንግሥት ስትገዛና መለኰታዊው ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድር ላይ ሲሆን ወይም ሲደረግ በአሁኑ ጊዜ በሰብዓዊው ሕብረተሰብ ላይ በተንሰራፋው ክፋት ፋንታ ምን እንደሚሆን ሊጠበቅ ይችላል? ሐዋርያው ጴጥሮስ በተናገረው መሠረት “ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።” (2 ጴጥሮስ 3:13) “አዲስ ሰማያት” ጻድቅ የሆኑ መንፈሳውያን የአመራር ኃይሎች ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስና በሰማያዊው መንግሥት አብረው ወራሾች የሆኑት 144,000ዎች ናቸው። (ሮሜ 8:16, 17፤ ራእይ 14:1-5፤ 20:4-6) “አዲሱ ምድር” ሌላ ምድራዊ ሉል አይደለም። ከዚህ ይልቅ በምድር ላይ የሚኖሩ ጻድቃን የሆኑ ሰዎች ሕብረተሰብ ነው።—ከመዝሙር 96:1 ጋር አወዳድር።
በመንግሥቲቱ አገዛዝ ሥር ምድር ወደ ዓለም አቀፍ ገነትነት ትለወጣለች። (ሉቃስ 23:43) በዚያ ጊዜ ታዛዥ የሰው ዘሮች ሁሉ እውነተኛ ሰላምና ብልጽግና ያገኛሉ። (መዝሙር 72:1-15፤ ራእይ 21:1-5) ታዛዥ በሆኑ ምድራዊ ተገዥዎች ላይ የምትገዛው መሲሐዊት አገዛዝ ታማኝ ደጋፊ ከሆንክ ከዚህ ደስተኛ ሠራዊት መካከል ልትሆን ትችላለህ። የዚህ አገዛዝ ደጋፊዎች ለይሖዋ ስም መቀደስ፣ ለመንግሥቱ መምጣትና ለፈቃዱ መፈጸም ከልብ ይጸልያሉ። ልባዊ ጸሎቶቻቸው መልስ እንደሚያገኙ እርግጠኛ ነገር ነው።