የአንባብያን ጥያቄዎች
◼ ኢሳይያስ 11:6 እንደ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም “ተኩላም ከበግ ጠቦት ጋር ለጊዜው ይቀመጣል” የሚለው ለምንድን ነው? ይህ ዓይነቱ ሰላም ዘላቂ ወይም ቋሚ አይደለምን?
ይህ በኢሳይያስ 11:6-9 ላይ በእንስሳት ፍጥረት ላይ የተተነበየው አስደሳች ሰላም ቋሚ ነው። ይሁን እንጂ በጥንቃቄ የተተረጐመው ኢሳይያስ 11:6 እንዲህ ዓይነቶቹ እንስሳት (በይና ተበይ የሆኑ ማለት ነው)ያለማቋረጥ አንድ ላይ እንደማይሆኑ ግልጽ ያደርገዋል።
በአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ኢሳይያስ 11:6 እንዲህ ይነበባል፦ “ተኩላም ከበግ ጠቦት ጋር ለጊዜው ይቀመጣል። ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል። ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል።”
በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ንባቡ “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይኖራል” የሚለውን የመሰለ ነው። እንዲህ ዓይነት አተረጓጎም ተኩላና የበግ ጠቦት በአንድ አዲስ ቤተሰብነት ወይም የአኗኗር ሥርዓት ያለማቋረጥ አብረው የሚሆኑ ጓደኞች እንደሚሆኑ ዓይነት ሐሳብ ያስተላልፋል።
ይሁን እንጂ “መቀመጥ” ወይም “መኖር” ተብሎ የተተረጐመው የዕብራይስጥ ቃል “ጉር” ነው። በመዝገበ ቃላት ጸሐፊው ዊሊያም ጄስኒያስ መሠረት “መቆየት” “ለጊዜው መቀመጥ” ማለት “በባለቤትነት ሳይሆን በእንግድነት መኖር” ማለት ነው። (ኤ ሄብሪው ኤንድ ኢንግሊሽ ልክሲኰን ኦቭ ዘ ኦልድ ቴስታመንት በኤድዎርድ ሮቢንሰን የተተረጐመ)በኤፍ ብራውን ኤስ ድሪቨር እና ሲ ብሪግስ የተዘጋጀው መዝገበ ቃላት “መቆየት፣ ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ መኖር፣ . . . ከቀድሞው ባለመብት ሳይሆን እንደ አዲስ መጥ ሆኖ መኖር” የሚሉ ትርጉሞችን ሰጥቶታል።
አምላክ አብርሃምን በከነዓን ምድር “በእንግድነት” እንዲቀመጥ ሲነግረው የተጠቀመው “ጉር” የሚለውን ቃል ነው። ያ አበው የምድሪቱ ባለቤት አይሆንም ነበር። ግን በጥገኝነት ነዋሪ ነበር። (ዘፍጥረት 26:3፤ ዘፀአት 6:2-4፤ ዕብራውያን 11:9, 13) በተመሳሳይም ያዕቆብ “በካራን በስደተኛነት (መጻተኛነት) እንደተቀመጠ” ተናግሯል። ምክንያቱም ወደ ከነዓን ተመላሽ ስለ ነበር።—ዘፍጥረት 29:4፤ 32:4
አምላክ በቅርቡ በሚያቋቁማት ገነት ውስጥ እንስሳትና ሰዎች በሰላም ይኖራሉ። የበግ ጠቦት ከተኩላ ጋር በመሆኑ ወይም ፍየል ከነብር ጋር በመሆኑ ምንም አደጋ አያጋጥመውም። ከአሁኑ ጊዜ ጋር ያለውን ልዩነት ወይም ንጽጽር ለመግለጽ እንደተፈለገ ሁሉ አነጋገሩ እንደውም ተኩላ መጻተኛ ወይም እንግዳ ሆኖ የበግ ጠቦት እንደሚያስጠጋው የሚገልጽ ሐሳብ ይዟል።—ኢሳይያስ 35:9፤ 65:25a
ሆኖም እንዲህ ዓይነት እንስሳት የተለዩ መኖሪያዎች ይኖራቸው ይሆናል። አንዳንድ እንስሳት ጫካ ይስማማቸዋል፤ ሌሎች ሜዳ፣ ሌሎችን ደግሞ የባሕር ዳርቻ ወይም ተራራ። የመጀመሪያዋ ገነት ሳለችም እንኳ አምላክ “ለሜዳ እንስሳትና የዱር አራዊት” (በእንግሊዝኛውና በበኩረ ጽሑፉ)ተናግሯል። (ዘፍጥረት 1:24) በግልጽ እንደሚታየው ለማዳ እንስሳት ማለት ወደ ሰዎችና ወደ መኖሪያቸው የሚቀርቡት ናቸው። የዱር አራዊቱ አስፈሪ ባይሆኑም ከሰዎች ርቀው መኖር ይመርጡ እንደነበረ ግልጽ ነው። ስለዚህ የኢሳይያስ ትንቢት እንደተነበየው “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ለጊዜው ይቀመጣል” እንጂ ባለማቋረጥ በእነዚህ ለማዳ እንስሳት አጠገብ አይኖርም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የሊቪንግ ኢንግሊሽ መጽሐፍ ቅዱስ ኢሳይያስ 11:6ን እንዲህ በማለት ተርጉሞታል፦ “ተኩላ የበግ ኪራይተኛ ይሆናል።”
[በገጽ 31 ላይ የሚገኘው ሥዕል ምንጭ]
Zoological Research Center, Tel-Aviv Hebrew University