የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 9/15 ገጽ 28-30
  • ምሳሌዎች​—ልብ ለመንካት ይረዳሉ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ምሳሌዎች​—ልብ ለመንካት ይረዳሉ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ትምህርት ሰጪ ምሳሌዎች
  • ምሳሌዎችን ማግኘት
  • መጽሐፍ ቅዱስን ሕያው ማድረግ
  • “ያለምሳሌ አይነግራቸውም ነበር”
    “ተከታዬ ሁን”
  • ተስማሚ ምሳሌዎች
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • “ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • ትምህርት አዘል ምሳሌዎች
    ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 9/15 ገጽ 28-30

ምሳሌዎች​—ልብ ለመንካት ይረዳሉ

ዳዊት ሕይወቱን ለማዳን ይሸሽ ነበር። ጠላቱ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የተቀባው ሳኦል ነበር። ሳኦል ግን ለዳዊት ባለው ጥላቻ ተሞልቶና በቅናት ተቃጥሎ ነበር። በነፍስ አጥፊነት ሩጫውም ንጉሡ 3,000 ወታደሮች አስከትሎ መጣ። ዳዊትና ከሱ ጋር ያሉት ሰዎች ጠላቶቻቸው በቁጥር ይበልጡአቸው ስለነበረ በምድረ በዳ በዋሻ ውስጥ ተሸሸጉ።

ዳዊትና ሰዎቹ ጨለማ ውስጥ እፍግፍግ ብለው ተቀምጠው ሳሉ ሳኦል ለመጸዳዳት ወደዚሁ ዋሻ በመግባቱ አስደናቂ ሁኔታ ተፈጠረ። ዳዊት መሣሪያ በእጁ ይዞ በሰዓቱ ምንም አይነት መከላከያ በሌለው ጠላቱ ላይ ቀስ ብሎ መጣበት። ነገር ግን አብረው ለነበሩት ሰዎች ይግረማችሁ ብሎ ንጉሡን ሳይገድለው ተመለሰ። የሳኦልን የልብሱን ጫፍ ብቻ ቆርጦ አስቀረ። ይህን በማድረጉም እንኳ ተጸጽቶ ዳዊት እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ የቀባው ነውና ይሖዋ በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር አደርግ ዘንድ እጄንም እጥልበት ዘንድ ይሖዋ ከእኔ ያርቀው።”​—1 ሳሙኤል 24:1-6

ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ከአምላክ የተሰጠውን ስልጣን ስለማክበር ጥልቅ የሆነ ትምህርት ያስተምራል። ምናልባትም ቀጥተኛ ከሆነ ምክር ይበልጥ ልብን ይነካል። በአምላክ ቃል ውስጥ የተመዘገቡት ታሪኮች ለትምህርታችን የሚሰጡት ኃይል ይህን ያህል ታላቅ ነው።​—ሮሜ 15:4

በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን ሲሰብኩ፣ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲመሩ፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ንግግር ሲሰጡ ወይም የአጋጣሚ ምሥክርነት ሲሰጡ እውነቱን እንዳለ ከመንገር የበለጠ ነገር ያደርጋሉ። ተሞክሮዎችን በመናገርና ምሳሌዎችን በመጠቀም ልብን ለመንካት ይጥራሉ። የቲኦክራቲካዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የመምሪያ መጽሐፋቸው እንዲህ በማለት ያብራራል፦ “ምሳሌዎች ፍላጎት ይቀሰቅሳሉ፤ ዋና ዋና ሐሳቦችንም አጉልተው ያሳያሉ። የአንድን ሰው የማሰብ ችሎታ አነሳስተው አዳዲስ ሐሳቦችን ለመቀበል ቀላል ያደርጋሉ። በደንብ የተመረጡ ምሳሌዎች ምሁራዊ አቀራረብንና ስሜታዊ ተጽእኖን አጣምረው ይይዛሉ። አንዳንዴ ምሳሌዎች አግባብ የሌለው ጥላቻን ወይም አድልዎን ለማስተው ሊያገለግሉ ይችላሉ።a​—ገጽ 168

ዋረን ዱቦዋ ለሕዝብ ንግግር የሚያስፈልጉ ዋና ዋና ነገሮች በተሰኘ መጽሐፍ ላይ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ጸሐፊው ወይም ተናጋሪው በሰው ልጆች እንቅስቃሴ ወይም ቃላት አማካኝነት ሐሳቡን ይግለጽ፤ በጣም አሰልቺ የሆነው ርዕስ ሕይወትና ኅብረ ቀለማት ይኖረዋል።” በመሆኑም በፊቱኑ የሚያስተጋባ ለሆነው መልእክት ሕይወትና ኅብረ ቀለም መጨመሩ ክርስቲያን አገልጋዮችን ልብ እንዲነኩ እንደሚረዳቸው የተረጋገጠ ነው።

ትምህርት ሰጪ ምሳሌዎች

ጥሩ ውጤት የሚያስገኘው ምን ዓይነት ምሳሌ ነው? አብዛኛውን ጊዜ አድማጮች ሊያዛምዱት ወይም ሊያገናዝቡት በሚችሉት ነገር ላይ የተመሠረተ ሲሆን ነው። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ምሳሌ ትቷል። በተራራው ስብከቱ ላይ ጨው፣ መብራትና ወፎች ስለመሳሰሉት ተራ ነገሮች ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:1 እስከ 7:29) ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ጊዜ በመቅረዝ ላይ ስለሚቀመጠው በወይራ ዘይት የሚነድ መብራት ሁሉም ሰው ያውቅ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ “መብራትም አብርተው ከእንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል። በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” ብሎ በነገራቸው ጊዜ መንፈሳዊ ብርሃን ያዦች ወይም ተሸካሚዎች መሆን እንዳለባቸው መናገሩ እንደሆነ ተገንዝበው መሆን አለባቸው። (ማቴዎስ 5:15, 16) ከርዕሰ ትምህርቱ ጋር የሚስማሙ ያልተወሳሰቡ ምሳሌዎች ክርስቲያን አገልጋዮችን ሐሳቦችንና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ለማብራራት ይረዷቸዋል።

ምናልባትም ኢየሱስ የተጠቀመባቸው ከፍተኛ ኃይል ያላቸው ምሳሌዎች ያተኰሩት በሰዎች ላይ ነበር። በሉቃስ ምዕራፍ 15 እና 16 ላይ የተመዘገቡትን ተመልከት። ጸሓፍትና ፈሪሳውያን ኢየሱስ ኃጢአተኞችንና ቀራጮችን በመቀበሉ ነቅፈውት ነበር። በምላሹም የሰዎችን ልብ የሚነኩ ታሪኮችን ነገራቸው። የጠፋውን በጉን ስላገኘው የበግ እረኛ፣ የጠፋ ድሪሟን ስላገኘችው ሴት፣ ወደ አባቱ ቤት ስለተመለሰው አባካኝ ልጅና ስለ አመጸኛው መጋቢ ተናገረ።

በእውነት ላይ የተመሠረቱ ምሳሌዎችና እውነተኛ የሕይወት ተሞክሮዎች ለአንድ ክርስቲያን አገልጋይ በጣም ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በሕዝብ ተናጋሪነት ለ60 ዓመታት በሰፊው የተጓዘው አሌክሳንደር ኤች ማክሚላን ሙታንን በሚመለከት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዴት እንዳብራራ አስተውል። ነፍስ ፈጽሞ አትሞትም ብሎ ያምን የነበረው አባቱ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ማክሚላን ከእሱ ጋር እንደሚከተለው ተጨዋውተው ነበር፦

“አባቴ፦ ‘ልጄ ሆይ የአምላክ መንግሥት ምድርን በፍጽምና የመሙላት ሥራዋን እስክትጀምር ድረስ በመቃብር ውስጥ ሆኜ ስጠባበቅ ብቸኛ እሆናለሁን?’ ብሎ ቀጥተኛ ጥያቄ አቀረበልኝ።

“ያ ጥያቄ አንድ ወጣት ሰው ያን የመሰለ አሳብ አስቦ ለማያውቅ በዕድሜ የገፋ ሰው ወዲያውኑ ሊመልስለት የሚችል ጥያቄ አልነበረም።

“ስመልስለትም እንዲህ ብዬ ጠየቅሁት፦ ‘ባለፈው ሌሊት ጥሩ እንቅልፍ ተኝተህ ነበር?’

“እሱም፦ ‘አዎ፣ ልጄ፣ ሐኪሙ የሆነ የእንቅልፍ ክኒን ከሰጠኝ በኋላ ደህና ተኛሁ።’

“‘ተኝተህ ሳለህ ብቸኛ ነበርህን?’

“‘የለም አልነበርኩም፤ ሁልጊዜ እንደዚያ ባንቀላፋ ደስ ይለኝ ነበር። ምክንያቱም ያኔ ምንም ስቃይ አይሰማኝም ነበር።’”

ኤ ኤክ ማክሚላን ኢዮብ 14:13-15ን እና ኢዮብ 3:17-19 ላባቱ አነበበለትና እንዲህ አለው፦ “ስለዚህ አየህ አባቴ ሙታን በሞት እንቅልፍ ውስጥ ስለሆኑ በዚያ ሁኔታ እያሉ ምንም አያውቁም። ታዲያ እንዴት ብቸኞች ሊሆኑ ይችላሉ?”

እንዴት ያለ ውጤታማ የማስተማር ዘዴ ነው! ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ከሆንክ አእምሮንና ልብን ለመማረክ ቅዱስ ጽሑፎችንና ምሳሌዎችን ልትጠቀም ትችላለህ።

ምሳሌዎችን ማግኘት

ግን ውጤታማ ምሳሌዎችንና እውነተኛ የሕይወት ተሞክሮዎችን የት ልታገኛቸው ትችላለህ? ብዙዎቹን ከራስህ የግል ተሞክሮ ልታገኝ ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል የእምነት በረከቶች፣ የጸሎትን ኃይል ወይም የአገልግሎትን ደስታ ለመግለጽ ትፈልጋለህን? ውስን ክርስቲያን ከሆንክ በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን የተለያዩ ሁኔታዎች ልታዛምዳቸው ትችል ይሆናል። በጉባኤ ስብሰባ ላይ ወይም ከአንድ መሰል ክርስቲያን ጋር ስታወራ አንድ ጥሩ ተሞክሮ ትሰማ ይሆናል። ወይም ደግሞ በይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ላይ የሚያበረታታ ተሞክሮ ታነብ ይሆናል። እንዲያውም የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ ከዓለም ዙሪያ በሙሉ የታተሙ ተሞክሮዎችን በቀላሉ እንድታገኝ ይረዳሃል።

አንድን ተሞክሮ ውጤታማ በሆነ መንገድ ልትናገር የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ በአድማጮችህ ውስጥ መጠነኛ የጉጉት መንፈስ መፍጠር ትኩረታቸውን ለመሳብ ይረዳሃል። አንድን ተሞክሮ እንዲህ በማለት ልትጀምር ትችላለህ፦ “አንድ አቅኚ ይሖዋ በእሱ የሚታመኑ ሰዎችን እንዴት እንደሚባርክ ከራሱ ተሞክሮ ተማረ።” ወዲያውኑ አድማጮችህ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነው የመንግሥቱ ሰባኪ ምን በረከቶች እንዳገኘ ለመስማት በመገረም ይጠባበቁ ይሆናል። ልትነግራቸው እንደምትችል እርግጠኛ ሁን።

አንድን ተሞክሮ በራስህ ቃላት ለመናገር ሞክር። ዝርዝሮችን አቅርብ። ምክንያቱም እንዲህ ማድረጉ ለትረካው ኃይል ይጨምርለታል። የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ግልጽ ሥዕላዊ መልክ በማቅረብ አድማጮችህን በቀላሉ ልታነቃቃ ትችላለህ። ይሁን እንጂ ተሞክሮውን ለምን እንደምትነግራቸው ሳይረዱት እንዳይቀሩ ታሪኩን በመናገር ብቻ ከልክ በላይ አትዋጥ። እንዲሁም ከማጋነን ተቆጠብ፤ ምክንያቱም ይህ ትረካውን ይበልጥ አስደሳች ሊያደርገው ቢችልም እውነት የምትናገር መሆኑን አጠራጣሪ ሊያደርገው ይችላል። ለዚሁ ሲባልም የስሚ ስሚ አሉባልታን ከማስተላለፍ ወይም ልታረጋግጠው የማትችለውን ተሞክሮ ከመናገር ተቆጠብ።

መጽሐፍ ቅዱስን ሕያው ማድረግ

ከሁሉ የበለጠ ትምህርት ሰጪ ተሞክሮዎች የሚገኙት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። ለምሳሌ ለአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ወይም አድማጭ ልጆች ለይሖዋ አምላክ አቋም ሊወስዱ እንደሚችሉ ለመግለጽ ፈለግህ እንበል። ለንዕማን ሚስት ስለ ይሖዋ ነቢይ ስለ ኤልሳዕ የተናገረችውን በስም ያልተጠቀሰች ልጃገረድ ታሪክ ልትጠቀምበት ትወስን ይሆናል። በመጀመሪያ በሁለተኛ ነገሥት 5:1-5 ላይ ያለውን ታሪክ አንብብ። ከዚያም እንዲህ ብለህ መጠየቅ ትችላለህ፦ “የሐሰት አምላኪዎች ብቻ ባሉበት አገር ለይሖዋ ፍጹም አቋምን መጠበቅ ለዚህች ልጃገረድ የቱን ያህል አስቸጋሪ ይመስልሃል? ስለ ይሖዋና ስለ ነቢዩ በአሳማኝነት ለመናገር ድፍረት አልጠየቀባትምን?”

ታሪኩን ሕያው ለማድረግ ቅድመ ጥናት ማድረግ ሊረዳህ ይችላል። በመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ኢንዴክስ (ማውጫ) ውስጥ ንዕማን፣ ሶሪያ እና ኤልሳዕ በሚሉት ርዕሶች ሥር ጠቃሚ መረጃ አግኝተህ ሊሆን ይችላል። በአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ውስጥ ያለው ማመሣከሪያ በ2 ነገሥት ላይ ካለው ታሪክ ወደ መዝሙር 148:12, 13 መርቶህ ይሆናል። መዝሙር 148:12, 13 እንዲህ ይላል፦ “ጐልማሶችና ቆነጃጅቶች ሽማግሌዎችና ልጆች [የይሖዋን (አዓት)] ስም ያመስግኑ። ስሙ ብቻውን ከፍ ከፍ ብሎአልና ምስጋናውም በሰማይና በምድር ላይ ነው።” ወጣቶች የአምላክን ቃል በድፍረት ይናገሩ ዘንድ ይህ እንዴት ግሩም ማበረታቻ ነው!​—ሥራ 4:29-31

ክርስቲያን አገልጋይ ከሆንክ በዚህ ረገድ “ለትምህርትህ ተጠንቀቅ።” (1 ጢሞቴዎስ 4:16) እንዲሁ እውነትን መናገር ብቻ ሳይሆን በምሳሌ አብራራ። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኰችን ሕያውና ትርጉም ያላቸው አድርግ። ተስማሚ ተሞክሮዎችንና ምሳሌዎችን ተጠቀም። ልብን ለመንካት የሚያስችሉ መንገዶች እነዚህ ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a Published by the Watchtower Bible and Tract Society of New York, Inc.

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልክ እንደ ኢየሱስ ዘመናዊ ክርስቲያን አገልጋዮችም መልእክታቸውን በትክክል ለማስተላለፍና ልብን ለመንካት በግልጽ በሚታዩ ምሳሌዎች ሊጠቀሙ ይችላሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ