“ሸክምን ሁሉ እናስወግድ”
“በጣም አዝኛለሁ ተስፋም ቆርጫለሁ” በማለት ሜሪ አጉረመረመች። ይህች ክርስቲያን ሴት ስለ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶች ሸክም ስትናገር “ጓደኞቼ ዝለው ሲወድቁ አያለሁ። እኔም ድካምና ጭንቀት ይሰማኛል። እባካችሁ ምክንያቱን እንድረዳ እርዱኝ” አለች።
አንተም እንደዚሁ እንደተጨነቅህና አምላካዊ ኃላፊነቶችህን ለመፈጸም እስከማትችል ድረስ በጣም እንደደከምህ ይሰማሃልን? ክርስቲያናዊ አገልግሎት አንዳንዴ ከባድና የማይቻል ሸክም መስሎ ይሰማሃልን? በየጊዜው ደስታችንን በሚቀንሱ አፍራሽ ኃይሎች ስለምንከበብ ብዙ ታማኝ ክርስቲያኖች ተስፋ የሚቆርጡባቸው ጊዜዎች ያጋጥሟቸዋል። በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያን መሆን በእርግጥ ትግል የሚጠይቅ ነገር ነው። በመሆኑም አንዳንዴ አንዳንድ ክርስቲያኖች ክርስቲያናዊው አገልግሎት ከባድ ሸክም ሆኖ ይሰማቸዋል።
መንስኤውን መፈለግ
ይሖዋ ምክንያታዊ ያልሆን ትዕዛዝ እንደማይጭንብን ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ ያሳያሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ የአምላክ “ትዕዛዞች ከባዶች አይደሉም” ብሏል። (1 ዮሐንስ 5:3) ኢየሱስም በተመሣሣይ ተከታዮቹን “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ። እኔ የዋሕ በልቤም ትሁን ነኝና ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 11:29, 30) በእርግጥም ለእርሱ የምናቀርበው አገልግሎት ከልክ ያለፈ ከባድ ሸክም ሆኖ እንዲሰማን የይሖዋ ፈቃድ አይደለም።
ታዲያ አንድ ታማኝ ክርስቲያን ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቹን እንደ ከባድ ሸክም የሚመለከተው እንዴት ነው? አያሌ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህን የሐዋርያው ጳውሎስን ቃላት ልብ በላቸው፦ “ሸክምን ሁሉ . . . , አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ።” (ዕብራውያን 12:1) የጳውሎስ ቃላት አንድ ክርስቲያን አንዳንድ ጊዜ በራሱ ላይ አስፈላጊ ያልሆነ ሸክም ሊጭን እንደሚችል ያመለክታሉ። ይህ ሸክም የግድ ከባድ ኃጢአቶችን አያመለክትም። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን በማስተዋል ጉድለት ሕይወቱን በጣም ሊያወሳስቡበትና በፊታችን ያለውን ሩጫ ለመሮጥ በጣም አስቸጋሪ ሊያደርጉበት የሚችሉ ስሕተቶችን ሊሠራ ይችላል።
ለቁሳዊ ሀብት ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
ለምሳሌ ያህል ሥጋዊ ሥራን እንውሰድ። በብዙ አገሮች ኤኮኖሚያዊ ሁኔታዎች አንድን ክርስቲያን ረጅም ሰዓቶች እንዲሠራ ሊያስገድዱት ይችላሉ። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ብዙ የሚሠሩት ልቀው ለመታየት ወይም ቅንጦት ለማግበስበስ ሲሉ ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ፍላጎታቸውን ከመረመሩ በኋላ በሥራቸው ረገድ አንዳንድ ማስተካከያ ማድረግ ጥበብ ሆኖ አግኝተውታል። የይሖዋ ምስክሮች የሆኑት ደቢና ባልዋ እንዲህ አድርገዋል። እንዲህ ትላለች፦ “በገንዘብ ረገድ የነበረን ሁኔታ ተለወጠና የእኔ ሙሉ ጊዜ መሥራት የማያስፈልግ እንደሆን ተገነዘብን። ነገር ግን ሥራ ማቆሙ ከባድ ነበር።” ወዲያውኑ ብዙ የምትሠራው ሥራ የመኖሩ ጭነት ይሰማት ጀመር። እንዲህ በማለት ትገልጻለች፦ “የቤቴን ሥራ ለመሥራት የነበረኝ ነፃ ቀን ቅዳሜ ብቻ ነበር። ብዙውን ጊዜ ወደ መስክ አገልግሎት ሂጂ ሂጂ አይለኝም ነበር። ይህም ይረብሸኝና ሕሊናዬም ይወቅሰኝ ነበር። ሆኖም ሥራዬን በጣም እወድ ነበር። በመጨረሻ ከሐቁ ጋር መጋፈጥ ነበረብኝ። የነበረው መፍትሔ አንድ ብቻ ነበር። ሥራውን ተውኩ።” ያለ ጥርጥር ይህን የሚያህል ከፍተኛ ማስተካከያ ማድረግ ለአንዳንዶች የማይቻል ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የሥራ ሰዓትህን በጥንቃቄ መመርመር አንዳንድ ለውጦች ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሊያሳይህ ይችላል።
ራሳችንን ከማያስፈልጉ ሸክሞች ነፃ የምናደርግባቸው ሌሎች መንገዶችም ይኖሩ ይሆናል። የሽርሽር ጉዞአችንን፣ የእስፖርት እንቅስቃሴዎችን፣ ወይም ቴሌቪዥን በማየት የሚጠፋውን ጊዜ ጨምሮ ሌሎች መዝናኛዎችን ማዘውተራችንን ብንቀንስስ? በእነዚህ መስኮች ተፈላጊውን ሚዛን ካገኘን በኋላም እንኳን እንዲህ ዓይነቱን ሚዛን ለመጠበቅ በየጊዜው ማስተካከያዎችን ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል።
ምክንያታዊነት አስፈላጊ ነው
ይህን በመሰሉ ጉዳዮች ምክንያታዊ መሆናችን ከሚያጋጥሙን አዳዲስ ሁኔታዎች ጋር እንድንለማመድ ይረዳናል። ስለዚህ ስለ አገልግሎታችን አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ እንችላለን።—ኤፌሶን 5:15-17፤ ፊልጵስዩስ 4:5
በአምላክ አገልግሎት ሌሎች ከሚሠሩት ጋር እኩል ለመሥራት ስትል ጭንቀት ላይ ወድቀሃልን? እንዲህ ያለው ስሜት በሕይወትህ ላይ ጭንቀትንና ተስፋ መቁረጥን ሊጨምር ይችላል። የሌሎች ጥሩ ምሳሌነት የበለጠ እንድትሠራ ሊያበረታታህ የሚችል ቢሆንም ምክንያታዊ መሆን ከራስህ ሁኔታና ችሎታ ጋር የሚስማሙ ግቦችን እንድታደርግ ይረዳሃል። ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲህ በማለት ይነግሩናል፦ “ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፣ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል። እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና።”—ገላትያ 6:4, 5
የአካባቢው ባሕሎችና ልማዶችም በሸክማችን ላይ ሌላ ተጨማሪ ሸክም ሊጨምሩብን ይችላሉ። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ሰዎች በጣም ብዙ የሆኑትን ሃይማኖታዊ ሕጎችና ልማዶች ለመፈጸም ሲሞክሩ በጣም ደክመው ነበር። በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች ከሐሰት ሃይማኖታዊ ልማዶች ነፃ ወጥተዋል። (ከዮሐንስ 8:32 ጋር አወዳድር) ሆኖም አንድ ክርስቲያን ባካባቢው ባሕሎች ከልክ በላይ ሊጠላለፍ ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንዳንዴ እንደ ሠርግ ያሉ ጉዳዮች በጣም በተንዛዙ ባሕሎች የተዋጡ ናቸው። እነዚህ ባሕሎች ስህተት ላይሆን ይችላሉ። እንዲያውም የሚስደስቱ ሊሆን ይችላሉ። ይህን እንጂ ክርስቲያኖች እነዚህን ባሕሎች ለማክበር ጊዜውም ሆነ ገንዘቡ አይኖራቸው ይሆናል። በዚህም ምክር እነዚህን ባሕላዊ ሥርዓቶች ለማክበር ሲሞክሩ የማያስፈልጉ ጭነቶችን ሊጨምሩ ይችላሉ።
ኢየሱስ ማርታ የተባለችውን ሴት በጎበኘ ጊዜ የሆነውን ተመልከት። ማርታ ከኢየሱስ መለኮታዊ ጥበብ ሙሉ በሙሉ ከመጠቀም ይልቅ “አገልግሉት (ሥራ) ስለበዛባት ባከነች።” (ሉቃስ 10:40) ኢየሱስ ግን ከትምህርቱ እንድትጠቀም የምግብ ዝግጅቱን ቀላል ማድረግ እንደምትችል በደግነት ሐሳብ አቀረበላት። (ሉቃስ 10:41, 42) ይህም የማመዛዘን ችሎታና ምክንያታዊነት በክርስቲያናዊ አገልግሎትህ ተገቢ ሚዛንህን እንድትጠበቅ ሊረዳህ እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ነው።—ያዕቆብ 3:17
ባልንጀሮችህን ለመምረጥም ጥሩ ማመዛዘን ወይም ማስተዋል ያስፈልጋል። ምሳሌ 27:3 እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል፦ “ድንጋይ ከባድ ነው። አሸዋም ሸክሙ ጽኑ ነው። ከሁለቱ ግን የሰነፍ (የሞኝ) ቁጣ ይከብዳል።” ምንጊዜም ቢሆን የቅርብ ጓደኞችህ ባስተሳሰብህ ላይ ከባድ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል። ስሕተት ለመለቃቀምና ሌሎችን ለመተቸት ፈጣኖች ከሆኑ የጉባኤ አባሎች ጋር መቀራረብ የተስፋ መቁረጥና የአፍራሽ አስተሳሰብ ዘር በውስጥ ሊተከልብህ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ችግሩ ይህ መሆኑን ከተገነዘብክ በምትቀርባቸው ሰዎች ረገድ አንዳንድ ጥበባዊ ለውጥ ማድረጉ ሸክምህን ሊያቃልልህ ይችላል።
ከአምላክ ጋር ስትሄድ ትሁን ሁን
በሚክያስ 6:8 ላይ አሳሳቢ ጥያቄ እናገኛለን፦ “ይሖዋ ካንተ ዘንድ የሚሻው . . . ከአምላክህም ጋር በትህትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን ?” የትሕትና ትርጉም አቅምን ማወቅ ተብሎ ተገልጿል። አቅማቸውን የማይገነዘቡ ሰዎች ራሳቸውን በብዙ ግዴታዎች ይተበትባሉ። ይህ በብዙ የጎለመሱ ክርስቲያኖች፣ የበላይ ተመልካቾችም ላይ ሳይቀር ደርሶባቸው ተስፋ መቁረጥ፣ መሰልቸትና ደስታ ማጣት አስከትሎባቸዋል። ኬኔዝ የሚባል አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ እንዲህ በማለት አምኗል፦ “ወደ ጭንቀት እየሄድኩ እንዳለሁ ተመለከትኩና ‘ይህ እንዲደርስብኝ አልፈቅድለትም’ አልኩኝ። ስለዚህ አንዳንድ ኃላፊነቶቼን ቀነስኩና ልሠራ በምችለው ላይ አተኮርኩ።”
በጣም ትሑት የነበረው ነቢዩ ሙሴም ሳይቀር አቅሙን መገንዘብ ተስኖት ነበር። ስለዚህ ብቻውን ሊሠራው ይሞክር የነበረውን የሥራ ብዛት በሚመለከት የአማቱ የዮቶር ማስገንዘቢያ አስፈልጎት ነበር። ዮቶር እንዲህ አለው፦ “ይህ በሕዝቡ የምታደርገው ምንድን ነው?. . . ይህ ነገር ይከብድብሃልና አንተም ካንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ። አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም. . . . ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎችን ምረጥ። አውራውንም ነገር ሁሉ ወደ አንተ ያምጡት። ታናሹንም ነገር ሁሉ እነሱ ይፍረዱ። እነሱም ከአንተ ጋር ሸክሙን ይሸከማሉ። ላንተም ይቀልልሃል።” ሙሴም ወዲያውኑ ከፊሉን ሥራውን ለሾማቸው ሰዎች አከፋፈለና የማይቻል ሸክም ሊሆንበት ከነበረው ሥራ እፎይታ አገኘ።—ዘፀዓት 18:13-26
በሌላ ወቅት ሙሴ ለይሖዋ “እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ልሸከም አልችልም” ብሎታል። ያኔም የተሰጠው መልስ ሥልጣኑን ለሌሎች ሰዎች እንዲያካፍል ነበር። አንተም በብዙ ኃላፊነት የተተበተብክ መስሎ ከተሰማህ መፍትሔው ይኸው ሊሆን ይችላል።—ዘኁልቁ 11:14-17
ሸክማችንን እንድንሸከም ይሖዋ ይረዳናል
ኢየሱስ ቀንበሩ ልዝብ ሸክሙ ቀላልና የማይከብድ እንደሆነ ተናግሯል። ኢየሱስ እንድንሸከም የጋበዘን ቀንበር የሥራ ፈትነት ቀንበር አይደለም። የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዝሙር በመሆን ሕይወትን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ የመስጠት ቀንበር ነው። ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያን ከመሆን ጋር የሚመጣ የተወሰነ መጠን ያለው ሸክም ወይም ጭነት አለ። (ማቴዎስ 16:24-26፤ 19:16-29፤ ሉቃስ 13:24) የዓለም ሁኔታዎች ይበልጥ እየተበላሹ ሲሄዱ ጭነቶች ይበዛሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ቀንበሩን እንዲሸከሙ ያቀረበው ግብዣ እርሱ ከተሸካሚዎቹ ጋር ሆኖ ቀንበሩን እንደሚሸከምና እንደሚያግዛቸው የሚያመለክት ስለሆነa ባመለካከታችን ይሆናል ባዮች ለመሆን ምክንያት አለን። ስለዚህ የክርስቶስን መመሪያ እስከተከተልን ድረስ እሱ ስለሚረዳን ሽክማችን ቀላል ይሆናልና።
አምላክ ለሚወዱት ሰዎች ያስብላቸዋል። በጸሎት አማካኝነት ሸክማቸውን ሁሉ በእሱ ላይ የሚጥሉትንም ሁሉ ልባቸውንና አሳባቸውን (የማሰብ ኃይላቸውን) ይጠብቃል። (መዝሙር 55:22፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7) መዝሙራዊው “ሽክማችንን በየዕለቱ የሚሸከምልን እውነተኛው የመድሃኒታችን አምላክ ይሖዋ ይባረክ” ብሏል። (መዝሙር 68:19) አዎን ሸክምን ሁሉ አስወግደህ በፊትህ ያለውን ሩጫ በትዕግሥት ከሮጥክ አምላክ ያንተንም ሸክም በየዕለቱ እንደሚሸከምልህ እርግጠኛ ሁን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የግርጌ ማስታወሻው ንባብ “ከኔ ጋር ቀንበሬን ተሸከሙ” ይላል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥበበኛ የሆኑ ሽማግሌዎች አንዳንድ ሥራዎችን ለሌሎች ለመስጠትና ሸክሙን ለመካፈል ፈቃደኞች ናቸው