የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
እውነት ፈላጊዎች አጋጣሚ ምስክርነት ይቀበላሉ
መጽሐፍ ቅዱስ በግ መሰል ሰዎች የመልካሙን እረኛ ድምፅ እንደሚሰሙ ይነግራል። (ዮሐንስ 10:27) ይህም ብሪታኒያን ጨምሮ በብዙ አገሮች ተፈጽሟል።
◻ ለምሳሌ ያህል በ1988 ከገና በዓል ጥቂት ቀደም ብሎ ከይሖዋ ምስክሮች አንዷ የሆነችው ፓሜላ በምትሠራበት ቢሮ የቴሌፎን ጥሪ ተቀበለችና በሌላው የኢንግላንድ ክፍል የሚሠራ የዚሁ እሷ የምትሠራበት ኩባንያ አሻሻጭ የሆነ ሰው አነጋገረች። በስልክ ንግግሩ መጨረሻ ላይ ሰውየው “ለገና በዓል ተዘጋጅተሻል?” ሲል ጠየቃት ፓሜላ “አልተዘጋጀሁም” ብላ መለሰችለት ሰውየው መልሶ “ታዲያ ጥቂት አልዘገየሽም?” ሲል ጠየቀ። ፓሜላ “ገናን አላከብርም” ስትል መለሰች። ሰውየውም ይህ ያልተለመደ ነገር እንደሆነ ተናገረና ለምን እንደማታከብር ጠየቃት። ፓሜላ ከይሖዋ ምስክሮች አንዷ መሆኗን ነገረችውና የኢየሱስ ልደት ቀን እንዲከበር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳልታዘዘና በተጨማሪም ኢየሱስ ታህሣስ 25 እንዳልተወለደ ከዚህም በላይ ገና ጥንት የአረማውያን ክብረ በዓል እንደነበረ ማብራራቷን ቀጠለች። ሰውየው ይህ ነገር በጣም አስደናቂ እንደሆነ ተናገረ።
ከሦስት ወር በኋላ ፓሜላ የቴሌፎን ጥሪ ተቀበለችና ጠሪው ሰው “ከገና በፊት እንዳነጋገርሽኝና የገና በዓልን እንደማታከብሪ እንደነገርሽኝ ታስታውሻለሽ? እውነትን አገኘሁት!” አላት። ያ ሰውዬ ከገና በዓል በኋላ ሁለት ሳምንት ቆይቶ ሁለት ምስክሮች እቤቱ መጥተው ሲያነጋግሩት እንዲገቡ እንደጋበዛቸውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንደተጀመረለት ገለጸላት። በጥናቱ ፈጣን ዕድገት እያደረገ እንዳለ ነገራት። አብራው ለምትኖረው የሴት ጓደኛው አኗኗራቸው ይሖዋን እንደማያስደስተው ነገራትና ተለያይተው ሁለቱም በመንግሥት አዳራሹ በስብሰባዎች እንደሚገኙ ተናገረ።
በዓመቱ መጨረሻ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች እንዲሆኑ ተቀባይነት አገኙ። በ1990 መጀመሪያ ላይ ተጋቡ። ከዚያም አብረው ተጠመቁ። በቴሌፎን የተደረገ አጭር ያጋጣሚ ምስክርነት ያስገኘው ግሩም ውጤት!
◻ በእንግሊዝ አገር ባጋጣሚ የመሰከረችን አንዲት ሌላ እኅት ይሖዋ ባርኳታል። የመድህን ድርጅት ሠራተኛ የሆነ ሰው ወደቤቷ መጣና ጥሩ ጤንነት፣ ደስታና የዘላለም ሕይወት ዋስትና ቢያገኝ ደስ ይለው እንደሆነ ጠየቀችው። አዎ አላትና ስለየትኛው የሕይወት ዋስትና ውል እየተናገረች እንዳለች ጠየቃት በገነት ምድር ላይ የአምላክን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስታሳየው በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተሰኘውን መጽሐፍ ተቀበለና መጽሐፉን በሞላ በአንድ ምሽት አነበበው። ያችን እህት እንደገና ሊጠይቃት ሲሄድ ያነበበው መልእክት ግሩም እንደሆነና ቢያምንበት ደስ እንደሚለው ገለጸላት። እህትም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግና በመንግሥት አዳራሹ በስብሰባ መገኘት እንደሚያስፈልገው ገለጸችለት። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ዝግጅት ተደረገለትና በስብሰባዎችም መገኘት ጀመረ። በዚያው ዓመት ማለቂያ ላይ ተጠመቀ። አንድ ዓመት ቆይቶ ደግሞ መጀመሪያ የመሠከረችለትን እኅት ሴት ልጅ አገባ። ስለዚህ ይህች እኅት “በሰጠሁት የአጋጣሚ ምስክርነት ወንድምም አማችም አገኘሁ” ብላለች።
እውነት ፈላጊዎች በአጋጣሚ ምስክርነት አማካኝነት የሚተላለፍላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መቀበላቸው እውነተኛ ነገር ነው። ኢየሱስ እንዳለው በጎቹ ድምፁን ይሰማሉ።