ገና ለእርስዎ ያለው ትርጉም ምንድን ነው?
ገና ምንድን ነው ተብሎ ቢጠየቅ ምን ብለው ይመልሳሉ? (1) ከቤተሰቦችዎ ጋር የሚሆኑበት ጊዜ (2) የግብዣ ጊዜ (3) ሃይማኖታዊ ጊዜ (4) የውጥረት ጊዜ (5) ልዩ ትዝታ የሚጥል ጊዜ (6) ንግድ የሚጦፍበት ጊዜ
ምንም እንኳን ነገሩ የሚያስገርም ቢመስልም እንግሊዝ ውስጥ ጥናት ከተደረገባቸው ከ1000 የሚልቁ ሰዎች መካከል 6 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ገናን ይበልጡን ሃይማኖታዊ ወቅት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። በአንፃሩ 48 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች ገና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚያሳልፉበት ጊዜ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ብዙዎች ገና ለልጆች ልዩ ወቅት እንደሆነ አድርገው እንደሚመለከቱትም የታወቀ ነው። ዓይነተኛ ምሳሌ የምትሆነን አንዲት የ11 ዓመት ልጅ የገና በዓልን በተመለከተ በይበልጥ የወደደችው ምን እንደሆነ ስትጠየቅ “ፍንደቃው፣ የደስታ ስሜቱ፣ [እና] ስጦታ መለዋወጡ” ብላ መልሳለች። ዘ ሜኪንግ ኦቭ ዘ ሞደርን ክሪስማስ የተባለው መጽሐፍ “‘የባሕላዊ’ ገና ትኩረት በቤት፣ በቤተሰብና በተለይ በልጆች ላይ እንደሆነ ጥርጥር የለውም” በማለት ተናግሯል።
በተለይ በምዕራቡ የሕዝበ ክርስትና አገሮች ዘንድ ቤተ ዘመድ፤ ስጦታ ለመለዋወጥ በሚሰባሰብበት ጊዜ ገና የቤተሰብ ክብረ በዓልነትን መልክ ይይዛል። የምሥራቁ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሥር በሰደደባቸው አገሮች ያሉ ሕዝቦች ለፋሲካ በዓል ላቅ ያለ ትኩረት የሚሰጡ ሲሆን ገና በአብዛኛው የዕረፍት ወቅት ተደርጎ መታየቱ አልቀረም።
“የንግድ እንቅስቃሴ”
የገና በዓል “ . . . የንግዱን ሂደት ሞቅ ደመቅ ያደርገዋል” በማለት ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ ይገልጻል። ምናልባትም በዚህ በኩል በአገር ደረጃ ጃፓንን የሚተካከላት የለም።
“ጃፓናውያኑ የሃይማኖት ሐሳቡን ወደጎን በመተው ገናን ወደ ደንበኛ የንግድ ማንቀሳቀሻነት ለውጠውታል” በማለት ዋሽንግተን ዴይሊ ሬኮርድ አስታውቋል። ሆኖም ገና በጃፓን “ለንግድ እንቅስቃሴ ጫን ያለ ክብደት የሚሰጥ በሃይማኖታዊነቱ እጅግም የማይታወቅ ክብረ በዓል ነው በማለት መጽሔቱ ሐተታውን ቀጥሏል።”
ሌላው ቀርቶ ክርስቲያን ተብለው በሚጠሩት አያሌ አገሮች በበዓሉ ላይ ‘ሃይማኖታዊ መልክ ማየት’ ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ነው። አርባ ከሚያክሉ ዓመታት በፊት ፀረ–ገና የሆነ በራሪ ወረቀት እንዲህ በማለት ሐዘኑን አሰምቶ ነበር። “ገናን የንግዱ ዓለም ያጧጡፈዋል። የዓመቱ ከፍተኛ ትርፍ ማግበስበሺያ ወቅት ነው። ክርስቲያን ነን በሚሉ የንግድ ሰዎች ላይ በግልጽ እንደሚታየው ገናን በከፍተኛ ጉጉት የሚጠብቁት ለኢየሱስ ሲሉ ሳይሆን ለኪስ ማደለቢያነቱ ነው።” እነዚህ ቃላት ዛሬም እንዴት ያለ እውነትነት ያዘሉ ናቸው! በብዙ የምድር ክፍሎች ለሚቀጥለው ገና ስጦታ ለመግዛት ምን ያህል ቀን እንደቀረው የሚያስታውሱ መልእክቶችን ሳንሰማ በዓሉ የሚደርስበት ጊዜ በጣት የሚቆጠር ነው። ከመደብሩ ሩብ በላይ የሚሆን ሸቀጥ የሚነሣበት የዓመቱ (የፈረንጆች ዓመት) መገባደጃ ዓመታዊው የደራ ገበያ በገና ወቅት ይመጣል።
ገና ለአንተ የትኛውም ዓይነት ትርጉም ቢኖረው አጀማመሩ ግን ሳያስገርምህ አይቀርም። በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ የገና ስጦታ ማበርከትን ይደግፋል? የዛሬዎቹስ የገና በዓል አከባበሮች እውነት ክርስቲያናዊ ልማዶች ናቸውን? እስቲ እንመልከት።
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ሽፋን፦ Thomas Nast/Dover Publications, Inc., 1978