የይሖዋን ምድራዊ ድርጅት ታደንቃለህን?
በጥሩ ሁኔታ ተስተካክላ የተከረከመችና የምታንፀባርቅ ዕጹብ ድንቅ አልማዝ ተመልከት። ታዲያ ምን ይታይሃል? እውነተኛ ውበት ያለው ክቡር “ድንጋይ” ነው። እስቲ ይህን አልማዝ በማይክሮስኮፕ (አጉሊ መነጽር) ተመልከተውና ምን ይታይሃል? የተጫጫሩ ጭረቶች፣ ስንጥቅጥቆች፣ ሌሎች ጭምርማሪ ነገሮችና የተለያዩ እንከኖች ሳይታዩህ አይቀርም።
ታዲያ ይህችን አልማዝ በአጉሊ መነጽሩ ስታያት ጉድለቶች ስላየህባት ታበላሻታለህን? ወይስ ትጥላታለህን? በእርግጥ አትጥላትም! ከአጉሊ መነጽሩ ርቃ ስትታይ የሚኖራትን ውበትና አንጸባራቂነት አሁንም ታደንቀዋለህ። ከሌሎች ክቡር ድንጋዮች መሃል ታስቀምጣታለህ።
የይሖዋ ምድራዊ ድርጅትም እንደ አልማዙ በብዙ መንገዶች የሚያክላት ድርጅት የለም። በምድር ላይ ከእሷ በቀር ከፈጣሪ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ያገኘ ሌላ ድርጅት የለም። ሐዋርያው ጴጥሮስ ሰማያዊ ተስፋቸውን ይጠባበቁ ለነበሩት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ይህን ልዩ ዝምድና ጠቅሶ ተናግሯል። እንዲህ አለ፦ “የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ።” (1 ጴጥሮስ 2:9) በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ያላቸው የ “ሌሎች በጎች” ታላቅ ጭፍራ ከዚህ “ቅዱስ ሕዝብ” ቀሪዎች ጋር ይሖዋን በማምለክ ተባብረዋል። (ዮሐንስ 10:16) እነዚህ ሁለት ቡድኖች በአንድ ላይ ሆነው ውብ እንደሆነችና ከመጠን በላይ አንጸባራቂ እንደሆነችው ክቡር ድንጋይ ልዩ ሆኖ የሚታይ ድርጅት አቋቁመዋል።
ሌሎችን በስሕተት ፈላጊነት ዓይን ከመመልከት ራቅ
ነገር ግን ይህ ዓለም አቀፍ ድርጅት ፍጹም ያልሆኑ ሰዎችን ያየዘ መሆኑን መገንዘብ አለብን። ታዲያ ይህን ድርጅት በምሳሌያዊ አጉሊ መነጽር ብንመለከት ምን ነገር ሊታየን ይችላል? የዚህ ድርጅት አባሎች በሆኑት ግለሰቦች ላይ የኃጢአት ዝንባሌዎችንና የባሕርይ ጉድለቶችን እናገኛለን።—ሮሜ 3:23
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ጉድለት እንዳለበት አምኗል። እንዲህ አለ፦ “መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ ክፉ የሆነው በውስጤ አለ።” (ሮሜ 7:21) እያንዳንዱ ክርስቲያን ይኸው ትግል አለበት። ሁሉም ክርስቲያኖች ስሕተት ይሠራሉ። ከዚህም በላይ ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ ብዙ ሰዎች በሌላ ሰው ስሕተት ምክንያት ችግር ያጋጥማቸዋል። ታዲያ የክርስቲያን ባልንጀሮቻችን እንከንና አለፍጽምና ግልጽ ሆኖ ሲታይ ተስፋ እንቆርጣለንን? ወይም ቅር እንሰኛለንን? ይህስ ለይሖዋ ድርጅት ያለንን አድናቆት ሊቀንስብን ይገባልን? በእርግጥ አይገባም! በዚህ ፋንታ ከአጉሊ መነጽሩ መራቅ ማለትም በግለሰቦች አለፍጽምናዎች ላይ ማተኮርን መተው አለብን።
ቅዱሳን ጽሑፎች መንፈስ ቅዱስ በላያቸው ላይ የሚሠራባቸው ሰዎች የሚለዩባቸውን በርካታ ባሕርዮች ይዘረዝራሉ። ከእነዚህም ባሕርዮች አንዳንዶቹ “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ የዋህነት፣ ራስን መግዛት” ናቸው። (ገላትያ 5:22, 23) በአንጻሩ ደግሞ የዚህ ዓለም የሃይማኖት፣ የፖለቲካና የንግድ ድርጅቶች ብዙውን ጊዜ የሚያሳዩት መጽሐፍ ቅዱስ የሥጋ ሥራ ብሎ የሚጠራቸውን ባሕርያት ነው፦ “ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር ዘፋኝነት (ፈንጠዝያ) ይህንም የሚመስል ነው።” (ገላትያ 5:20, 21) በመሆኑም በተራ ዓለቶች ወይም ድንጋዮች መሃል አንጸባራቂ አልማዞች ተለይተው እንደሚታዩ ሁሉ የይሖዋ ሕዝቦችም በመንፈሳዊ በረከሰ ዓለም መሃል ተለይተው ይታያሉ። —ማቴዎስ 5:14-16
“በአንድ አሳብ መተባበር”
የአልማዝ አንዱ ታላቅ ገጽታ የአተሞቹ አቀማመጥና ቅንጅት በጣም የተጠጋጋና በኃይል የተቆራኘ መሆኑ ነው። በተመሳሳይም የይሖዋ ምድራዊ ድርጅት በመሠረተ ትምህርትና በወንድማማችነት ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው አንድነት ይታይበታል። የዚህ ድርጅት ክፍል የሆኑት ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በ1 ቆሮንቶስ 1:10 ላይ እንደሚከተለው በማለት የተነገረውን ምክር በተግባር ያውላሉ፦ “ወንድሞች ሆይ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።”
የይሖዋ ምስክሮች የዘር ጥላቻንና ብሔራዊ ኩራትን አሸንፈዋል። “የላይኛይቱ ጥበብ” ስላላችሁ “አድልዎ አያደርጉም።” (ያዕቆብ 3:17) ይሖዋ ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች በተመሠረተ ድርጅት ውስጥ ይህን ለመፈጸም በመቻሉ ክብር ሊሰጠው ይገባል።
በአንጻሩ ዘ ክርስቲያን ሴንቸሪ የተሰኘው መጽሔት ስለ 1990 ዓመት ሲናገር “ዓለም ከምን ጊዜውም የበለጠ በሃይማኖታዊ ወገኖችና ከሃይማኖታዊ እምነቶች ጋር በቅርብ በተሣሰሩ የጎሣና ብሔራዊ ስሜቶች የተከፋፈለች ትመስላለች። ከሕንድ እስከ አውሮፓና ከመካከለኛው ምሥራቅ እስክ ፓስፊክ ውቅያኖስ ሃይማኖት ከጎሣና ከብሔራዊ ስሜት ጋር ተቀላቅሏል። በዚህም ምክንያት ፖለቲካዊ ለውጥና አለመረጋጋት በዝቷል” ብሏል። በግልጽ እንደሚታየው አምላክን ለማገልገል የሚፈልጉ ሰዎች የይሖዋን መንፈስና በረከት ወዳገኘው አንድ ብቸኛ ድርጅት ሊመለከቱ ይገባል።
“እንደ አልማዝም ግምባርህን አጠንክሬአለሁ”
ሰው ከሚያውቃቸው ተፈጥሮ ያፈራቸው ነገሮች ሁሉ በጣም ጠንካራው አልማዝ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አልማዝ ጠንካራ ነገሮችን ለመፋቅ ወይም ሥዕሎችንና ጽሑፎችን ለመቅረጽ ያለውን አገልግሎት ይጠቅሳል። (ኤርምያስ 17:1) ይሖዋ ለሕዝቅኤል “እነሆ ፊትህን በፊታቸው ግምባርህንም በግምባራቸው አጠንክሬያለሁ። ከቡላድ ድንጋይ ይልቅ እንዳለ አልማዝ ግምባርህን አጠንክሬአለሁ” በማለት የተናገራቸውንም ቃላት አስታውስ። (ሕዝቅኤል 3:8, 9) ይሖዋ ለሕዝቅኤል ለእልከኛ ሕዝብ ትንቢት ለመናገር ያስቻለውን እንደ አልማዝ የጠነከረ ቆራጥነት ሰጥቶታል።—ሕዝቅኤል 2:6
በአሁኑ ጊዜም በተመሳሳይ ይሖዋ ለሕዝቦቹ የሚያጋጥማቸውን ታላቅ ተቃውሞ ለመቋቋም የሚያስችል የአልማዝ ዓይነት ጥንካሬ ሰጥቷቸዋል። የይሖዋ ምስክሮች ሕጋዊ ዕገዳዎች፣ የሕዝብ ረብሻዎች፣ ሕጋዊ ያልሆኑ ግድያዎች፣ ድብደባዎች፣ ተገቢ ያልሆኑ እስራቶች፣ የድብደባ ሥቃዮች፣ የሞት ፍርድ ሳይቀር ደርሶባቸው ጸንተዋል።
“ባሪያዎቼ ይደሰታሉ”
መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች “የአምልኮ መልክ” የሚኖራቸውና “ኃይሉን ግን የሚክዱበት ጊዜ” እንደሚመጣ ትንቢት ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 5) አንድ ጋዜጣ “ፕሮቴስታንቶች፣ የሮማ ካቶሊኮችና አይሁዶች በሞላ በቤተክርስቲያኖቻቸውና በምኩራቦቻቸው እያጋጠማቸው ያለው የቁጥር ማሽቆልቆል እያሳሰባቸው” መሆኑን ይዘግባል። በሌላ በኩል ግን የይሖዋ ምስክሮች ትጉህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ናቸው። በቁጥር እየጨመሩ በመሄድ ወጣቶችና አረጋውያን፣ ወንዶችንና ሴቶች በየሳምንቱ በሚደረጉት አያሌ ስብሰባዎች ይካፈላሉ። ለአንድ ጋዜጣ የተጻፈ ደብዳቤ ስለእነሱ “ሃይማኖታቸው ካላቸው ነገር ሁሉ የበለጠ ክቡር ነገር መሆኑና የሚያሳስባቸውም ይህን ሃይማኖታቸውን ለሌሎች ማካፈሉ ብቻ ነው በማለት ተናግሯል።”
እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ የይሖዋን ድርጅት እንደ አንዲት ክቡር አልማዝ ተለይታ እንድትታይ ያደርጋታል። በዚህም ምክንያት ክብር ሊሰጠው የሚገባው ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎችን በመንፈስ ቅዱስ ለሚያጠነክረውና ለሚመራው አምላክ ነው።
ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ተንብዮአል፦ “እነሆ ባሪያዎቼ ይበላሉ። . . . እነሆ ባሪያዎቼ ደስ ይላቸዋል። . . . እነሆ ባሪያዎቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ።”—ኢሳይያስ 65:13, 14
በዛሬው ጊዜ የዚህን ትንቢት ፍጻሜ እየተመለከትን ነው። አምላክ ለሕዝቡ ልዩ በሆነ መንገድ እንክብካቤ ያደርጋል። ስለዚህ ከእነሱ ጋር የምትተባበር ከሆንክ ምንም ዓይነት አፍራሽ አስተሳሰብ ደስታህን እንዲቀማህ አትፍቀድ። ጠቅላላውን ሥዕል ተመልከት። የአምላክ ልዩ እንክብካቤና ጥበቃ ያገኘ ሌላ ድርጅት በምድር ላይ የለም። የዚህ ድርጅት ክፍል ለመሆን በመቻልህ ያገኘኸውን መብት ከፍ አድርገህ ተመልከተው።