ራስን መግዛት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጐነትን ጨምሩ። በበጐነትም ዕውቀትን በዕውቀትም ራስን መግዛት ... ጨምሩ።—2 ጴጥሮስ 1:5, 6
1. በ19ኛው መቶ ዘመን የራስ መግዛትን ባሕርይ የሚያሳይ ምን አስደናቂ ትዕይንት ተፈጽሟል?
ያለ ጥርጥር በጣም አስገራሚ የሆነ ሰውነትን የመቆጣጠር ችሎታ በ19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ላይ ይኖር በነበረው በቻርለስ ብሎንዲን ታይቷል። አንድ ዘገባ እንደሚለው 1,100 ጫማ ከፍታ ያለውን የኒያጋራ ፏፏቴ ከውሃው በላይ 160 ጫማ ከፍታ ላይ በተወጠረ ገመድ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሻገረው በ1859 ነበር። ከዚያም በኋላ ችሎታውን በተለያዩ ትዕይንቶች አሳይቷል። ዓይኑን ታስሮ ወይም ተሸፍኖ፣ በጆንያ ውስጥ ሆኖ፣ ጋሪ እየገፋ፣ ምርኩዝ ይዞና በጀርባው ላይ ሰው ተሸክሞ ተሻግሯል። በሌላ ቦታ ከመሬት በላይ 170 ጫማ ከፍታ ላይ በተዘረጋ ገመድ ላይ ምርኩዝ ይዞ ተገለባብጧል። እንዲህ ባለ ሁኔታ ሚዛን ለመጠበቅ ከፍተኛ የሆነ ሰውነትን ወይም አካልን የመቆጣጠር ችሎታ ያስፈልጋል። ከዚህም ድካሙ ከፍተኛ ዝናና ብዙ ሀብት አግኝቶበታል።
2. አካላዊ ቁጥጥርን ወይም ብቃትን የሚጠይቁ ምን ዓይነት ሌላ ሥራዎች አሉ?
2 እነዚህን ትዕይንቶች ሊሞክሩ እንኳ የሚቃጡ ሰዎች በጣም ጥቂቶች ቢሆኑም ሙያ ነክ ወይም የስፖርት ችሎታዎችን ለማዳበር ሰውነትን መቆጣጠር አስፈላጊ መሆኑን ሁላችንም እንገነዘባለን። ለምሳሌ አንድ ሙዚቀኛ ስመጥሩ የፒያኖ ተጫዋች የነበረውን የቭላድሜር ሆሮዊዝን ማራኪ አጨዋወት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እኔን በጣም የሚያስደንቀኝ ነገር ራሱን በተሟላ ሁኔታ ለመቆጣጠር መቻሉ . . . ለማመን አዳጋች የሆነ ከፍተኛ ኃይል ያለው መሆኑ ነበር።” ስለ ሆሮዊዝ የተጻፈ ሌላ ዘገባ “ጣቶቹ በፍጹም ቁጥጥር ስለተውለበለቡባቸው 80 ዓመታት” ተናግሯል።
3. (ሀ) ከሁሉ የበለጠው ዓይነት ራስ መግዛት ምንድን ነው? እንዴትስ ተገልጾአል? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ራስን መግዛት” ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል ትርጉም ምንድን ነው?
3 እንዲህ ዓይነቱን ጥበብ ለማዳበር ታላቅ ጥረት ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ከዚህ የበለጠ አስፈላጊና በጣም አስቸጋሪ የሆነው ራስን መግዛት ነው። ራስን መግዛት “በገዛ ራስ ግፊት፣ ስሜት ወይም ምኞት ላይ የሚደረግ ጥብቅ ቁጥጥር” የሚል ፍች ተሰጥቶታል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በ2 ጴጥሮስ 1:6 እና በሌሎችም ቦታዎች “ራስን መግዛት” ተብሎ የተተረጐመው ቃል ትርጉም “ምኞቱንና ስሜቱን በተለይም የሥጋ ፍላጎቱን የሚገታ ሰው ምግባር” እንደሆነ ተገልጾአል። በነፍስ ወከፍ ደረጃ ራስን መግዛት “የሰው ልጅ ክንዋኔ ከፍተኛው ደረጃ” ተብሎም ተጠርቷል።
ራስን መግዛት ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4. የራስ መግዛት መታጣት ምን መጥፎ ፍሬ አፍርቷል?
4 የራስ መግዛትን ባሕርይ ማጣት መጥፎ ዓይነት ምርት ያሳጭዳል። ዛሬ በዓለም ያሉት ብዙ ችግሮች ዋና መንስኤያቸው የራስ መግዛት ባሕርይ መታጣቱ ነው። እውነትም የምንኖረው “የሚያስጨንቅ ዘመን” ባለበት “የመጨረሻ ቀን” ውስጥ ነው። ሰዎች “ራሳቸውን የማይገዙ” የሆኑበት ምክንያት ብዙውን ጊዜ ከስግብግብነት የተነሣ ነው። ስግብግብነት ከሚገለጥባቸው መንገዶች አንዱ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላ ወዳድ” መሆን ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ባለፈው የአገልግሎት ዓመት በጠቅላላው ከፍ ያለ መጥፎ ምግባር በመፈጸማቸው ምክንያት 40,000 ጥፋተኞች ከክርስቲያን ጉባኤ መወገዳቸው ስለዚህ ጉዳይ በጥብቅ እንድናስብ ያደርገናል። በእነዚህም ላይ በአብዛኛው የጾታ ብልግና ስለፈጸሙ ተግሳጽ የተሰጣቸውን ብዙ ሰዎች መጨመር ይቻላል። ይህ ሁሉ ጥፋት የተሠራው የራስ መግዛት ባሕርይ በማጣት ምክንያት ነው። በተጨማሪም ለብዙ ጊዜ ሽማግሌዎች የነበሩ ወንድሞች በዚሁ ምክንያት የበላይ ተመልካችነት መብታቸውን ጨርሰው ማጣታቸው የሚያሳስብ ነገር ነው።
5. ራስን የመግዛት ባሕርይ አስፈላጊነት እንዴት ሊገለጽ ይችላል?
5 ራስን የመግዛት አስፈላጊነት በአንድ አውቶሞቢል ሊመሰል ይችላል። አውቶሞቢሉ ለመንቀሳቀስ የሚያስችሉ አራት ጐማዎች አሉት፤ እነዚህን አራት ጐማዎች በፍጥነት ማሽከርከር የሚችል ኃይለኛ ሞተር እንዲሁም እንዲቆሙ የሚያስችል ፍሬን አለው። ይሁን እንጂ በነጂው መቀመጫ ላይ ተቀምጦ የነዳጅ መስጫውን፣ ፍሬኑንና መሪውን በመቆጣጠር ጐማዎቹ ወዴት መሄድ እንዳለባቸውና መቼ መቆም እንዳለባቸው የሚወስን ሰው ከሌለ አደጋ ሊደርስ ይችላል።
6. (ሀ) ለራስ መግዛት ሊሠሩ የሚችሉ ፍቅርን የሚመለከቱ መመዘኛዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ማስታወስ የሚገባን የትኛውን ተጨማሪ ምክር ነው?
6 የራስን መግዛት አስፈላጊነት ከመጠን በላይ አጋንኖ መናገር አይቻልም። ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 13:1-3 ላይ ስለ ፍቅር አስፈላጊነት የተናገረው ስለ ራስ መግዛትም ሊባል ይችላል። በሕዝብ ተናጋሪነት የቱንም ያህል አንደበተ ርቱዕ ብንሆን፣ በጥሩ የጥናት ልማድ አማካኝነት የቱንም ያህል ዕውቀትና እምነት ብናገኝ ሌሎችን ለመጥቀም ምንም ዓይነት ሥራ እየሠራን ብንሆን፣ ራስን መግዛት ካላሳየን ይህ ሁሉ ከንቱ ነው። ጳውሎስ “በእሽቅድድም ሥፍራ የሚሮጡት ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙም ዘንድ ሩጡ። የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ማስታወስ ይኖርብናል። (1 ቆሮንቶስ 9:24, 25) በሁሉም ነገር የራስ መግዛት ባሕርይ እንድናሳይ የሚረዳን ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 10:12 ላይ “እንደቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” በማለት የተናገረው ማስጠንቀቂያ ነው።
የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች
7. (ሀ) ራስን የመግዛት ባሕርይ መታጣቱ ሰብአዊውን ዘር ገና ከጅምሩ ወደታች እንዲያሽቆለቁል ያደረገው እንዴት ነው? (ለ) ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ሌሎች የራስ መግዛት ባሕርያት የታጣባቸውን የቀድሞ ምሳሌዎች ይሰጡናል?
7 አዳም በምክንያታዊ አስተሳሰብ ከመመራት ይልቅ በስሜቱ ብቻ ስለተመራ የራስ መግዛት ባሕርይ ሳያሳይ ቀርቷል። በዚህም ምክንያት “ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፣ በኃጢአትም ሞት።” (ሮሜ 5:12) ይሖዋ አምላክ ቃየንን “ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? ኃጢአት በደጅ ታደባለች። አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት” ብሎ አስጠንቅቆት ስለነበር ያ የመጀመሪያ ነፍስ ግድያም ቢሆን መንስኤው የራስ መግዛት እጦት ነበር። ቃየን በኃጢአት ላይ ስላልነገሠበት ወንድሙን አቤልን ገደለ። (ዘፍጥረት 4:6-12) የሎጥ ሚስትም የራስ መግዛት ባሕርይ ሳታሳይ ቀርታለች። ወደኋላ የመመልከትን ተፈታታኝ ፍላጎት ልትቋቋም አልቻለችም። የራስ መግዛት ባሕርይ ማጣቷ ምን ነገር አሳጣት? የገዛ ሕይወቷን ነዋ!—ዘፍጥረት 19:17, 26
8. ራስን ስለመግዛት አስፈላጊነት ማስጠንቀቂያ የሚሰጠን ምን የሦስት ጥንታዊ ሰዎች ተሞክሮ ነው?
8 የያዕቆብ የመጀመሪያ ልጅ የነበረው ሮቤል በራስ መግዛት እጦት ምክንያት ብኩርናውን አጥቷል። ከያዕቆብ ቁባቶች ከአንዷ ጋር ሩካቤ ሥጋ በመፈጸም የአባቱን መኝታ አረከሰ። (ዘፍጥረት 35:22፤ 49:3, 4፤ 1 ዜና 5:1) እሥራኤላውያን ሙሴን በማጉረምረም፣ በማማረርና በማመጽ በፈተኑት ጊዜ በእነሱ ላይ ስለተቆጣ በጣም ይመኘው የነበረውን ወደ ተስፋይቱ ምድር የመግባት መብት ተከለከለ። (ዘኁልቅ 20:1-13፤ ዘዳግም 32:50-52) “ለአምላክ ልብ ተስማሚ” የነበረው ታማኙ ንጉሥ ዳዊት እንኳ በአንድ ወቅት ራሱን መግዛት ስላቃተው ከባድ ጣጣ ውስጥ ገብቷል። (1 ሳሙኤል 13:14፤ 2 ሳሙኤል 12:7-14) እነዚህ ሁሉ ምሳሌዎች የራስ መግዛት ባሕርይ እንድናሳይ ጥሩ ማስጠንቀቂያ ይሰጡናል።
ራሳችንን ለመግዛት የሚያስፈልገን ምንድን ነው?
9. የራስን መግዛት አስፈላጊነት የሚያጐሉ አንዳንድ ጥቅሶች ምንድን ናቸው?
9 ከሁሉ አስቀድሞ ራስን መግዛት ሐሳባችንንና ስሜታችንን የሚነካ ነገር ነው። እነዚህም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ብዙውን ጊዜ “ልብ” እና “ኩላሊት” በሚሉት ምሳሌያዊ አጠራሮች ተጠቅሰዋል። ሐሳባችን እንዲያተኩርበት የምናደርገው ነገር ይሖዋን ለማስደሰት በምናደርገው ጥረት አንድም ሊረዳን ወይም ሊያደናቅፈን ይችላል። በፊልጵስዩስ 4:8 ላይ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ምግባረ ሰናይ የሆነውን ነገር ሁሉ እንድናስብ የተሰጠንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር እንድንፈጽም ከተፈለገ ራስን መግዛት ያስፈልጋል። መዝሙራዊው ዳዊት በጸሎት “አቤቱ ረድኤቴ መድኃኒቴም የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን” በማለት ተመሳሳይ ስሜት ገልጿል። (መዝሙር 19:14) ‘የባልንጀራቸው ንብረት የሆነውን ማንኛውንም ነገር እንዳይመኙ’ የሚያዘው አሥረኛው ትዕዛዝ አንድ ሰው ሐሳቡን እንዲቆጣጠር የሚጠይቅ ነበር። (ዘፀአት 20:17) ኢየሱስ “አንዲትን ሴት በመመኘት ወደ እሷ የሚመለከት በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል” ባለ ጊዜ ሐሳባችንንና ስሜታችንን የመቆጣጠርን አሳሳቢነት አጉልቶ ገልጿል።—ማቴዎስ 5:28
10. ንግግራችንን የመቆጣጠርን አስፈላጊነት አጥብቀው የሚገልጹልን የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ናቸው?
10 ራስን መግዛት ቃላቶቻችንን ማለትም ንግግራችንንም ይነካል። ምላሳችንን እንድንቆጣጠር የሚመክሩን ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥቅሶች በእርግጥ ብዙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል “እግዚአብሔር በሰማይ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን። በእግዚአብሔር ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኩል። ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ይሁን” ይላል። (መክብብ 5:2) “በቃል ብዛት ውስጥ ኃጢአት ሳይኖር አይቀርም። ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው።” (ምሳሌ 10:19) “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፣ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጐ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ አይውጣ። . . . መራርነት ንዴት፣ ቁጣም፣ ጩኸትም፣ መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ።” ጳውሎስ በመቀጠልም ማንኛውንም የሞኝነት ንግግርና የሚያሳፍር ነገርን እንድናስወግድ ይመክረናል።—ኤፌሶን 4:29, 31፤ 5:3, 4
11. ያዕቆብ ምላስን የመቆጣጠርን ችግር የገለጸው እንዴት ነው?
11 የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ልቅ የሆነ ንግግርን በማውገዝ ምላስን መቆጣጠር የቱን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ይገልጻል። እንዲህ ይላል፦ “አንደበት ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። . . . እነሆ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል። አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል አመጸኛ ዓለም ሆኖአል። ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና። የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል። በገሃነምም ይቃጠላል። የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል። ደግሞም ተገርቷል። ነገር ግን አንደበትን ሊገታ ማንም ሰው አይችልም። የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው። በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን። ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም።”—ያዕቆብ 3:5-10
12, 13. ድርጊታችንና ጠባያችንን የመቆጣጠርን አስፈላጊነት የሚገልጹት አንዳንድ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?
12 እርግጥ ራስን መግዛት ድርጊታችንንም ይነካል። ራስን የመግዛት ባሕርይ በከፍተኛ ደረጃ ከሚያስፈልግበት የኑሮ ዘርፍ አንዱ ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ሰዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ይመለከታል። ክርስቲያኖች። “ከጾታ ብልግና ሽሹ” ተብለው ተመክረዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:18, ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን) ባሎች በምሳሌ 5:15-20 ላይ በከፊል “ከጉድጓድህ ውሃ ከምንጭህም የሚፈልቀውን ውሃ ጠጣ” ተብለው ስለተነገሩ የጾታ ፍላጎታቸውን ከሚስቶቻቸው ጋር ብቻ እንዲወስኑ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። “ሴሰኞችንና አመንዝሮችን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” በማለት በግልጽ ተነግሮናል። (ዕብራውያን 13:4) በተለይ ደግሞ የነጠላነት ስጦታ የሚኮተኩቱ ራስን የመግዛት ባሕርይ ይፈለግባቸዋል።—ማቴዎስ 19:11, 12፤ 1 ቆሮንቶስ 7:37
13 ለሌሎች ሰዎች ልናደርግላቸው የሚገባንን ነገር በሚመለከት ኢየሱስ “ወርቃማው ሕግ” በመባል የሚታወቀውን ሕግ “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” በማለት በሰጠ ጊዜ ጉዳዩን በአጭሩ ገልጾታል። (ማቴዎስ 7:12) የራስ ወዳድነት ዝንባሌያችን ወይም ውጪያዊ ግፊቶች ወይም ፈተናዎች ሰዎች ለእኛ እንዲያደርጉልን እንደምንፈልገው እንዳናደርግላቸው እንዲያደርጉን ላለመፍቀድ እውነትም ራስን የመግዛት ባሕርይ በጣም ያስፈልጋል።”
14. የአምላክ ቃል መብልና መጠጥን በተመለከተ ምን ምክር ይሰጣል?
14 ከዚህም በቀር ምግብንና መጠጥን በሚመለከት ራስን የመግዛት ጉዳይም አለ። የአምላክ ቃል እንደሚከተለው በማለት ጥበብ የተሞላበት ምክር ይሰጣል፦ “የወይን ጠጅ ከሚጠጡ ጋር አትቀመጥ። ለሥጋም ከሚሳሱ ጋር።” (ምሳሌ 23:20) በተለይ የእኛን ዘመን በሚመለከት ኢየሱስ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል፦ “ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና ያለ ልክ በመብላት፣ ስለትዳርም በማሰብ (ስለኑሮ በመጨነቅ) እንዳይከብድ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና።” (ሉቃስ 21:34, 35) አዎ ራስን መግዛት ሐሳባችንንና ስሜታችንን እንዲሁም ቃላችንንና ድርጊታችንን ሁሉ ይነካል።
ራስን መግዛት ይህን ያህል አስቸጋሪ የሆነበት ምክንያት
15. ክርስቲያኖች የራስ መግዛትን ባሕርይ እንዳያሳዩ ከዲያብሎስ ተቃውሞ እንደሚያጋጥማቸው ቅዱሳን ጽሑፎች የሚገልጹት ነው?
15 ራስን የመግዛት ባሕርይ በቀላሉ የሚገኝ ነገር አይደለም። ሁላችንም ክርስቲያኖች እንደምናውቀው ራስን የመግዛት ባሕርይ እንዳናሳይ የተጋረጡብን ሦስት ኃይለኛ ጠላቶች አሉን። ከሁሉ በፊት ሰይጣንና የሱ አጋንንት አሉ። ሰይጣንና አጋንንት መኖራቸው አጠራጣሪ እንዳልሆነ ቅዱሳን ጽሑፎች በማያሻማ ሁኔታ ይገልጹልናል። በዚህም ምክንያት የአስቆሮቱ ይሁዳ ኢየሱስን ከመካዱ ጥቂት ሰዓት ቀደም ብሎ “ሰይጣን እንደገባበት” እናነባለን። (ዮሐንስ 13:27) ሐዋርያው ጴጥሮስ ሐናንያን “መንፈስ ቅዱስን ታታልል ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለምን ገባ?” በማለት ጠይቆታል። (ሥራ 5:3) በዚህም ምክንያት ጴጥሮስ “በመጠን ኑሩ ንቁም ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና” በማለት በጣም ተገቢ በሆነ መንገድ አስጠንቅቋል።—1 ጴጥሮስ 5:8
16. በዚህ ዓለም ረገድ ክርስቲያኖች ራስ የመግዛትን ባሕርይ ማሳየት ያለባቸው ለምንድን ነው?
16 ክርስቲያኖች ራስን የመግዛት ባሕርይ ለማሳየት በሚያደርጉት ጥረት ከዚህ “በክፉው” ሰይጣን ዲያብሎስ ከተያዘው ዓለም ጋር መታገል አለባቸው። ይህን በሚመለከት ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት ጽፏል። ራስን የመግዛት ባሕርይ ካላሳየንና ማንኛውንም ዓለምን የመውደድ ዝንባሌ ጠንክረን ካልተቋቋምን በአንድ ወቅት ከጳውሎስ ጋር አብሮ ያገለግል እንደነበረው እንደ ዴማስ በዓለም ተጽዕኖዎች እንሸነፋለን።—1 ዮሐንስ 2:15-17፤ 5:19፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:10
17. ራስን በመግዛት በኩል አብሮን የተወለደ ምን ዓይነት ችግር አለብን?
17 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በውርሻ ያገኘናቸውን ሥጋዊ ድካሞቻችንና ድክመቶቻችንን በተሳካ ሁኔታ እንድንቋቋም ከተፈለገ ራስን የመግዛት ባሕርይ ያስፈልገናል። “የሰው ልብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ” መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም። (ዘፍጥረት 8:21) እንደ ንጉሥ ዳዊት ‘በዓመፅ ተጸነስን እናቶቻችንም በኃጢአት ወልደውናል።’ (መዝሙር 51:5) አዲስ የተወለደ ሕፃን ልጅ ራስን ስለመግዛት ምንም አያውቅም። አንድ ነገር በሚፈልግበት ጊዜ እስኪያገኘው ድረስ ሳያቋርጥ ያለቅሳል። ሕፃናትን ማሠልጠንን በሚመለከት አንድ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ሕፃናት የሚያስቡት አዋቂዎች ከሚያስቡት ፈጽሞ በተለየ መንገድ ነው። ሕፃናት ራስ ወዳዶች ስለሆኑ ‘ራሳቸውን በሌላው ሰው ቦታ ማስቀመጥ” (ወይም ሌላው እንደሚያስበው አድርገው ማሰብ)ስለማይችሉ በጣም ምክንያታዊ በሆነ መንገድ እንኳ ማግባባት አስቸጋሪ ይሆናል።” እውነትም “ስንፍና (ሞኝነት) በሕፃን ልብ ታስሯል።” ይሁን እንጂ “የተግሳጽ በትር” በመጠቀም ሊታዘዛቸው የሚገቡ ደንቦች እንዳሉና ራስ ወዳድነት መገታት ያለበት ነገር መሆኑን ቀስ በቀስ ይማራል።—ምሳሌ 22:15
18. (ሀ) ኢየሱስ በተናገረው መሠረት በምሳሌያዊው ልብ ውስጥ የሚቀመጡት ምን ዝንባሌዎች ናቸው? (ለ) ጳውሎስ የትኞቹን ራስን የመግዛት ባሕርይ የማሳየት ችግር መገንዘቡን የሚያሳዩ ቃላትን ተናግሯል?
18 አዎን አብሮን የተወለደው የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ራሳችንን ለመግዛት ስንፈልግ እንቅፋት ሆኖ ይፈታተነናል። እነዚህ ዝንባሌዎች የሚቀመጡት በምሳሌያዊው ልብ ውስጥ ነው። ይህን ምሳሌያዊ ልብ በሚመለከት ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ከልብ ክፉ አሳብ፣ መግደል፣ ምንዝር፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በውሸት መመስከር፣ ስድብ ይወጣልና።” (ማቴዎስ 15:19) ጳውሎስ “የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና፣ ዳሩ ግን የምወደውን በጐውን ነገር አላደርገውም። የማልወደውን የማደርግ ከሆንሁ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም። በእኔ የሚኖር ኃጢአት ነው እንጂ” በማለት የጻፈው በዚህ ምክንያት ነው። (ሮሜ 7:19, 20) ይሁን እንጂ ጳውሎስ “ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛለሁ” በማለት ስለጻፈ በውጊያው ድል አልተነሣም። ሥጋውን ለመጐሰም ራሱን መግዛት አስፈልጎታል።—1 ቆሮንቶስ 9:27
19. ጳውሎስ ሥጋውን እንደሚጎስም መናገሩ ተገቢ የነበረው ለምንድን ነው?
19 ጳውሎስ ሥጋዬን ጐሰምሁ ማለቱ ጥሩ አባባል ነው። ምክንያቱም ራስን መግዛት እንደ ደም ግፊት መጨመር፣ የነርቭ ሕመም፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ራስ ምታትና የምግብ አለመፈጨት በመሳሰሉ ሁኔታዎች ቀውስ ሊደርስበት ይችላል። በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት የራስ መግዛትን ባሕርይ ለማሳየት የሚረዱንን ጠባዮችና እርዳታዎች እንመረምራለን።
ታስታውሳላችሁን?
◻ ራስን የመግዛት ባሕርይ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ራስ የመግዛት ባሕርይ በማጣታቸው ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች አንዳንድ ምሳሌዎች ምንድን ናቸው?
◻ ራስ የመግዛትን ባሕርይ ማሳየት የሚገባን በምን በምን ዘርፎች ነው?
◻ ራስ የመግዛትን ባሕርይ ለማሳየት አስቸጋሪ የሚያደርጉብን ሦስት ጠላቶች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች በምግብና በመጠጥ ረገድ ራሳቸውን መግዛት ያስፈልጋቸዋል
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ራስን የመግዛት ባሕርይ ከጎጂ ሐሜት እንድንርቅ ይረዳናል
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Historical Pictures Service