የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 11/15 ገጽ 24-26
  • በደቡብ አፍሪካ ገጠሮች ምሥራቹ ተዳረሰ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በደቡብ አፍሪካ ገጠሮች ምሥራቹ ተዳረሰ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • “የእሁድ ትምህርት ቤት” በዙሉላንድ
  • በአቧራማው ቁጥቋጦማ አካባቢ
  • አንድ ባላባት አዋጅ አወጣ!
  • ብዙ እውነት ፈላጊዎችን በደስታ መርዳት
  • የጥረቱ ውጤት
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 11/15 ገጽ 24-26

በደቡብ አፍሪካ ገጠሮች ምሥራቹ ተዳረሰ

ቁጣ የተሞላባቸው የሕዝብ ረብሻዎች፣ ረብሻ በታኝ ፖሊሶች፣ የሚያስለቅስ ጭስ በደቡብ አፍሪካ ትናንሽና ትላልቅ ከተሞች የሚኖሩ ሕዝቦች በየዕለቱ የሚያጋጥሟቸው ነገሮች ናቸው። ከአርባ በመቶ የሚበልጠው ሕዝብ የሚኖርባቸው ውብ ገጠሮችም ቢሆኑ ፖለቲካዊ ዓመፅ ከሚያስከትላቸው ጥፋቶች አላመለጡም። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ሁኔታ እያለ የይሖዋ ምስክሮች “የሰላምን ወንጌል” መስበካቸውን ቀጥለዋል።​—ኤፌሶን 6:15

ምስክሮቹ ለብዙ ዓመታት የገጠሩን ሕዝብ ለማዳረስ ታስበው የሚደረጉ ዓመታዊ የሦስት ወር ዘመቻዎችን አካሂደዋል። ለምሳሌ ያህል በ1990 ከ334 ጉባኤዎች የተውጣጡ 12,000 የመንግሥት አስፋፊዎች በዘመቻው ተካፍለዋል። መገመት እንደሚቻለው በደቡብ አፍሪካ እነዚህን የተበታተኑ የገጠር ኗሪዎች ለማዳረስ ብዙ መሰናክሎች መታለፍ አለባቸው።

ምስክሮቹን ከሚያጋጥማቸው መሰናክሎች አንዱ በጣም ብዙ የሆኑ የተለያዩ ባሕሎችና ቋንቋዎች መኖራቸው ነው። በጣም የተለያዩ ቋንቋዎችና ባሕሎች ይገኛሉ፤ ለምሳሌ ያህል የእንግሊዝኛና የአፍሪካንስ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሆኑ ገበሬዎች፣ የፔዲስ፣ የሶቶስ፣ የሶንጋስ፣ የስዋናስ፣ የቬንዳስ፣ የቆሳና የዙሉ ጐሳዎች ይገኛሉ። እያንዳንዱ ጐሳ ደግሞ የራሱ የሆነ የተለየ ባሕልና ቋንቋ አለው። ከፍተኛ ርቀት ያላቸውና ኮሮኮንች መንገዶችም አሉ። ይህ ሁሉ ሁኔታ ራስን መሥዋዕት የማድረግ መንፈስና በቀላሉ የማይገመት የጊዜና የገንዘብ ወጪን የሚጠይቅ ነው። ሆኖም ይሖዋ የተደረጉትን ጥረቶች ሁሉ ባርኳል። ይህ ልዩ የሆነ የስብከት ሥራ ስላጋጠመው ችግርና ስላስገኘው መልካም ውጤት ጥቂት እንንገራችሁ።​—ከሚልክያስ 3:10 ጋር አወዳድር።

“የእሁድ ትምህርት ቤት” በዙሉላንድ

ከፊል በረሃ በሆነው በዙሉላንድ ውስጥ የኡምቪቲ ወንዝ ተንጣልሎ ተኝቷል። ከአፋፉ ላይ ሆኖ የሣር ክዳን ያላቸው ችብችብ ያሉ የዙሉ መኖሪያ ቤቶች እስከ ርቀት ድረስ ተንጣለው ይታያሉ። በ1984 አንድ እሁድ ቀን ሁለት የመንግሥት አስፋፊዎች በጠመዝማዛውና በአቧራማው መንገድ ወርደው ወደዚህ ሸለቆ መጡ። ቦታው በጣም ሞቃትና እርጥበት የበዛበት ከመሆኑ የተነሣ ክዋ ሳታን (የሰይጣን ቦታ) የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል። በሰይጣን ዲያብሎስ በተጠነሰሰው የሲኦል እሳት ሐሰተኛ ትምህርት ላይ የተመሠረተ አጠራር ነው።

ወንድሞች በላብ ተጠምቀው የእሁድ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ታስተምር ወደነበረች ዶሪስ የምትባል ሴት ቀረቡ። ዶሪስ የመንግሥቱን መልእክት እንደሰማች ወዲያውኑ አርባ ወጣቶች የሚገኙበትን የተማሪዎቿን ቡድን እንዲያነጋግሩ ጋበዘቻቸው። ውጤቱስ ምን ሆነ? ወንድሞች በሚቀጥለው ሳምንት በዚያ ቦታ ላለው ትምህርት ቤት የሚያገለግል የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መጽሐፌ 70 ይዘው ተመለሱ። በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የእሁድ ትምህርት ቤት መሆኑ ቀርቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ሆነ። በቤተክርስቲያን መዝሙሮች ፋንታ የመንግሥቱ መዝሙሮች የአፍሪካን ተፈጥሯዊ ውበት በሚያንፀባርቅ ሁኔታ ተዘመሩ። ብዙ ሳይቆይ ቡድኑ ወደ 60 ከፍ አለ። አንድ ወንድም “ይህን የእሁድ ትምህርት ቤት ወደ እውነተኛ አምልኮ ቦታነት መለወጥ ልብን በደስታ የሚሞላ ትልቅ ተሞክሮ ነበር!” በማለት በአድናቆት ተናግሯል።

በአቧራማው ቁጥቋጦማ አካባቢ

አብያተ ክርስቲያናት በፖለቲካዊው ብጥብጥ ውስጥ ጣልቃ ስለሚገቡ ብዙ ነጭ ገበሬዎች ማንም ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ይዞ ሲቀርባቸው ስለሚጠራጠሩ ሰውነታቸው ፈታ ብሎ አያነጋግሩም። በትራንስቫል ክፍለ ሀገር ምሥራቹን ለመስበክ ከጆሃንስበርግ 640 ኪሎ ሜትር ተጉዘው የሄደ አንድ ቡድን ያቀረበውን ዘገባ ተመልከቱ፦

“እስከ አሁን ለአራት ሰዓት ያህል በስተ ሰሜን በኩል የሚገኘውን ቁጥቋጦ የሞላበት ወጣ ገባ መንገድ ተጉዘናል። ቀጥሎ ባለው መንገድ ከፍተኛ ሐሩር በመኖሩ የፀሐዩ ብርሃን ሲያርፍበት የሚታየው ነፀብራቅ ትልቅ ባሕር መስሎ ይታያል። በድንገት የአስፋልቱ መንገድ በአቧራማ መንገድ ተተክቶ የተቆፋፈረና ስርጓጉጥ የበዛበት መንገድ ሆነ። በመጨረሻም አሸዋማው መንገድ ወደ አንድ እርሻ ወሰደን።

“እንደምን አደሩ ሜኒር (ጌታው)” በማለት ለአንድ ወፍራም ገበሬ ሰላምታ ሰጠን።

“እንደምን አደራችሁ” የሚል የጐርናና ድምጽ መልስ መጣ። “ልረዳችሁ እችላለሁ?”

ራሳችንን ካስተዋወቅን በኋላ የመጣንበትን ምክንያት አስረዳን። ገና ቃላችንን ከአፋችን አውጥተን ሳንጨርስ “ቄሱ ስለእናንተ አስጠንቅቆኛል! ፀረ-ክርስቶሶች ናችሁ። አሁን . . .  ከሰፈሬ ቶሎ ውጡ!” አለን።

“የገበሬው አኳኋን በማንኛውም ሰዓት በኃይል ለመጠቀም እንደሚሞክር ያሳያል። አማራጭ ስላልነበረን ‘የእግራችንን ትቢያ አራግፈን’ ለመሄድ ወሰንን። (ማቴዎስ 10:14) እውነትም ቃል በቃል የሚራገፍ አቧራ ሞልቷል።

“በሚቀጥለውም እርሻ ያጋጠመን መልስ ከዚህ የተለየ አልነበረም። ከዚያም በኋላ የዳች ተሐድሶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ በአካባቢው እየቀረበ ስላለው “አደጋ” “ለመንጎቹ” እየደወለ ለማስጠንቀቅ የቴሌፎን መስመሩን ይዞት እንደነበረ አስታወስን። በመጨረሻ ራሱ ፍላጎት ባያሳይም “አዎን ለሠራተኞቼ መናገር ትችላላችሁ” የሚል ገበሬ አገኘን።

“ስንጠብቅ የቆየነው አጋጣሚ ነበር። ከጥቂት የግራር ዛፎች ቀጥሎ አሥር የሚሆኑ ከቀይ አፈር የተሠሩ አልባሌ ጎጆዎች እጅብጅብ ብለው ይታያሉ። ብዛት ያላቸውን ጽሑፎቻችንን በመኪናችን የፊት ክዳን ላይ አሳምረን ስንደረድር ከጎጆዎቹ ጉጉት የተሞሉ ዓይኖች ከጎጆዎቹ ውስጥ እየሰረቁ እንደሚመለከቱን ተረዳን። አንድ ድርድር መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ሌላ ድርድር በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ መጽሐፍ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መጽሐፌ ድርድርና የተለያዩ ብሮሹሮች ይታያሉ። አንድ የዚያ አካባቢ ልጅ መምጣታችንን ለመንደርተኞቹ ለመንገር ሮጠ። ወዲያውኑ 30 የሚሆኑ ሰዎች መልእክቱን ለመስማት በመኪናችን ዙሪያ ተሰበሰቡ።

“በስዋና ቋንቋ የተቀዳ ንግግር በቴፕ ማጫወቻ አሰማናቸው። እነዚህ ሰዎች በራሳቸው ቋንቋ የአምላክን መንግሥት የምሥራችና የገነትን ተስፋ ሲሰሙ በጣም ተደሰቱ! ጽሑፎቹ ሲታደሉ በደስታ ስሜት ይንጫጩ ነበር። በአጭር ጊዜ ውስጥ ጽሑፎቻችንን ስለጨረስን በደንብ ሳናዳርስ ቀረን። አንድ የሸመገሉ ሰው የቴፕ ማጫወቻዎቻችንንም ከፍለው ለመውሰድ ጠይቀው ነበር። ለምሥራቹ ያላቸው አድናቆት በብዙ ጥቃቅን መንገዶች ማለትም በፈገግታ፣ እጃቸውን በላያችን በመጫን፣ በለሰለሰ አነጋገር “እናመሰግናለን” በማለት ይገለጽ ስለነበረ በጣም ልባችን ተነካ።

“በድንገት ሕፃናቱ በሠልፍ ዓይነት መሥመር ቆሙና የባሕል የመሰነባበቻ መዝሙር ዘመሩልን። ወዲያውኑ ለአቧራማውና ለአስቸጋሪው መንገድና አንዳንዴ ላጋጠሙን መጥፎ ምላሾች የነበረን ትውስታ በኖ ጠፋ። ያደረግነው ጥረት ሁሉ አለዋጋ አልቀረም።”

አንድ ባላባት አዋጅ አወጣ!

በስዌቶ የሚገኝ አንድ ጉባኤ ፒት ረቲፍ በተባለች ምሥራቃዊ ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ አንድ ጎሣ ለሚኖርበት አካባቢ የመስበክ የሥራ ምድብ ተሰጠው። በዚያ አካባቢ ባለው ባሕል መሠረት አንድ እንግዳ ከመጣ መጀመሪያ ለአካባቢው ‘ኢንዱና’ (ባላባት) የመጣበትን ጉዳይ መግለጽ አለበት። ወንድሞች ከባሕሉ ጋር ተስማምተው ለባላባቱ የመጡበትን ጉዳይ ገለጹለት። ባላባቱም ሞቅ ባለ ስሜት ተቀብሎ እንዲያውም በቤቱ እንዲያርፉ ሲፈቅድላቸው በጣም ተደነቁ። በተጨማሪም የራሱ ማህተም ያለበት ወንድሞች ከቤት ወደ ቤት ሲሄዱ የሚያሳዩት ማስታወሻ ጻፈላቸው። ማስታወሻው “እነዚህ የአምላክ መንግሥት ሰባኪዎች ናቸው። ወደቤታችሁ አስገቧቸውና አዳምጧቸው” ይላል።

ወንድሞች በጣም ብዙ ተቀባይ ሰዎች ስላገኙ በዚያው እሁድ ቀን ከሰዓት በኋላ በባላባቱ ግቢ ውስጥ የሕዝብ ንግግር ለመስጠት ዝግጅት አደረጉ። በጣሪያ ያልተከለለው ክፍት “አዳራሽ” ጢም ብሎ ሞላና ስብሰባው በመዝሙርና በጸሎት ተጀምሮ ተዘጋ። በሌሎች ገጠርማ ቦታዎችም ይህን በመሰሉ አስደሳች ተሞክሮዎች አጋጥመዋል።

ከእንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች አንዱ ድርቅ ባጠቃው በቦፋታስ አካባቢ ፒሴዲሱልጃንግ በተባለች ትንሽ መንደር ውስጥ የሚኖረው ናትናኤል ነበር። እሱ ሰዎቹ የእርሻ ምርታቸውን እንዴት ሊያሻሽሉ እንደሚችሉ የሚያስተምር የማኅበራዊ ኑሮ ሠራተኛ ነበር። በአካባቢያቸው ያለውን የተራቆተ ቦታ ወደ ገነትነት ለመለወጥ ከልቡ ያስብ ነበር። ነገር ግን ምድር አቀፍ ገነት ሊመጣ መሆኑን ሲሰማ ዓይኑ በደስታ በራ። አስፋፊዎቹ ያሳዩትን ጥቅስ ሁሉ በጉጉት ጻፈ። ናትናኤል ወዲያውኑ 32 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ከሚገኝ ያቅራቢያው ጉባኤ ጋር እንዲገናኝ ተደረገ።

ብዙ እውነት ፈላጊዎችን በደስታ መርዳት

ሞኒካ የምትባል አንዲት አቅኚ ወይም የመንግሥቱ የሙሉ ጊዜ ሰባኪ “ድህነት በመንፈስ የተራበ ሰው እውነትን እንዳይማር ሊያግደው እንደማይችል ይሖዋ አሳየን” በማለት ትናገራለች። እሷ የአገሪቱ መካከለኛ ክፍለ ሀገር በሆነው በኦሬንጅ ፍሪ ስቴት ባሉት የገጠር ሜዳዎች ከእርሻ ወደ እርሻ እንዲሰብኩ ከተመደቡት አቅኚዎች አንዷ ነበረች። አቅኚዎቹ የምሥራቹን ወደ እነዚህ ሕዝቦች ለማዳረስ ብዙ በመድከማቸው ምን ተሰማቸው? “ያጋጠሙን ነገሮች በገንዘብ ሊተመኑ የማይችሉ ናቸው” በማለት መልስ ሰጥተዋል። እውነትም አቅኚዎቹ ለጥረታቸው ሁሉ የሚገባውን መንፈሳዊ ሽልማት አግኝተዋል።

ማንበብ አለመቻል እንኳ ቢሆን በመንፈስ የተራበን ሰው ቅዱስ ጽሑፋዊውን እውነት እንዳይማር ሊያግደው አይችልም። በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተሰኘው ጥሩ ስዕላዊ መግለጫ ያላት ብሮሹር መሃይማን በሆኑና እምብዛም ማንበብ በማይችሉ ሰዎች ዘንድ ጥሩ አቀባበል አግኝታለች። ወጣቶችም ሆኑ ሽማግሌዎች በቀለም ባጌጠው የገነት ሥዕል ይማረካሉ። ይህችን ብሮሹር በማተሙ ሥራ የሚያግዝ አንድ የሙሉ ጊዜ ሠራተኛ “ይህች ብሮሹር ገነት እውነት እንደሆነች እንዲገነዘቡ ሰዎችን ትረዳለች። ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸውን አድናቆትና አክብሮታዊ ፍርሐት ትጨምርላቸዋለች” ብሏል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መጽሐፌ የተሰኘው መጽሐፍም በሰፊው የታወቀና የተወደደ የሆነውም በዚሁ ምክንያት ነው። የሌቦዋ ጐሣ በሚኖርበት ራቅ ያለ አካባቢ ሁለት መንፈሳዊ እህቶቻችን አንድ ዓይኑ በከፊል የታወረ ሽማግሌ ሰውና ሚስቱ በሴፔዲ ቋንቋ የተዘጋጀ የዚህ መጽሐፍ ቅጂ እንዳላቸው ሲመለከቱ በጣም ተገርመዋል። እነዚህ ባልና ሚስት ይህን መጽሐፍ ያካባቢውን ልጆች ለማስተማር ተጠቅመውበታል። እንዲያውም መጽሐፉ በደንብ የተጠናና ብዙ ምልክት የተደረገበት ከመሆኑ የተነሣ መገነጣጠል ጀምሮ ነበር። አዲስ ቅጂ ባገኙ ጊዜ ከመጠን በላይ ተደሰቱ!

ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ጽሑፎች እውነትን የተራቡ ሰዎችን በመርዳት ላይ ናቸው። በደቡብ አፍሪካ ባሉ ቋንቋዎች ከታተሙት ጽሑፎች አብዛኞቹ የተዘጋጁት በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር መሆኑ በጣም ያስደስታል። በ1990ዎቹ ብቻ በማኅበሩ የታተሙ 113,529 ብሮሹሮችና መጽሔቶች በደቡብ አፍሪካ ገጠሮች ተሠራጭተዋል።

የጥረቱ ውጤት

እነዚህ አስደሳች ተሞክሮዎችና የጽሑፍ ዕደላዎች በደቡብ አፍሪካ ገጠሮች ዘላቂ ውጤት አስገኝተዋልን? በእርግጥ አስገኝተዋል። ከ1989 ወዲህ በደቡብ አፍሪካ ገጠሮች አራት ጉባኤዎችና ዘጠኝ ቡድኖች ተቋቁመዋል። ይህም ምሥራቹን በደቡብ አፍሪካ ገጠሮች ከመስበክ የተገኘ ውጤት ነው። ይህን ሥራ በግምባር ቀደምትነት የሚመሩት ጊዜያዊ ልዩ አቅኚዎችና የዘወትር አቅኚዎች ናቸው።

ራቅ ብሎ በሚገኘው ዙሉላንድ ሸለቆ የምትኖረውን ዶሪስንና የእሁድ ትምህርት ቤቷን ታስታውሳላችሁ? ዛሬ እሷ ሕይወቷን የወሰነችና የተጠመቀች የይሖዋ ምስክር ሆናለች። ከዚህም በላይ በዚያ ቦታ ዘጠኝ ፍሬያማ የመንግሥት አስፋፊዎች የሚገኙበት ቡድን አለ። በዶሪስ ቤት በሚደረገው ስብሰባ ብዙ አዳዲስ ሰዎች ይካፈላሉ። እሷ ያስጠናቻቸው ሰባት ሰዎችም በታህሣሥ ወር 1990 በደርባን በተደረገው የወረዳ ስብሰባ ላይ ተጠምቀዋል።

እንደነዚህ ያሉት ፍሬዎች በደቡብ አፍሪካ ያሉትን የመንግሥት አስፋፊዎች የሚያስደስቱና የሚያነቃቁ ናቸው። “ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ መልካም እናድርግ” የሚሉትን የሐዋርያው ጳውሎስን ቃላት በተግባር አሳይተዋል። (ገላትያ 6:10) አዎ፣ የይሖዋ አገልጋዮች መልእክቱን ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ሁሉ፣ በዚህ “የምድር ዳርቻ” ገጠሮች ለሚኖሩት ጭምር ለማዳረስ ቆርጠዋል።​—ሥራ 1:8

[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ካርታዎች/ሥዕሎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሌቦዋ

ትራንስቫል

ሶዌቶ

ፒት ረቲፍ

ቦፉታትስዋና

ኦሬንጅ ፍሪ ስቴት

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ