የምታመልከው የትኛውን አምላክ ነው?
እኛ ሰዎች የማምለክ ችሎታ ስላለን ከእንስሳት የተለየን ነን። ይህም ከተወለድንበት ጊዜ ጀምሮ አብሮን የሚኖር የተፈጥሮ ባሕርያችን ክፍል ነው። ትክክለኛ ሥነ ምግባርን የመለየት ችሎታ፣ ትክክልና ስህተት ስለሆኑ ነገሮች የሚመራን ሕሊና አለን። ሁላችንም በተለያዩ መንገዶች ይህን ሕሊና እንከተላለን። በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች ከአምላክ ወይም ከአማልክት አመራር ለማግኘት ይፈልጋሉ።
ባለፉት አንድ ወይም ሁለት መቶ ዓመታት አንዳንድ ዓለማዊ ምሁራን ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክና ፈጣሪ የለም ብለዋል። ካርል ማርክስ በ1884 ሃይማኖት “የሕዝብ ማደንዘዣ መርዝ ነው” ብሎአል። በኋላም ቻርልስ ዳርዊን የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ አምጥቶአል። ከዚያም የቦልሼቪክ አብዮት ተጀመረ። በምሥራቅ አውሮፓ አምላክ የለሽነት ይፋ የሆነ የመንግሥት መርሕ ሆነ። ሃይማኖት በ1917 ከነበረው ትውልድ ጋር አብሮ ይሞታል ተብሎ ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ አምላክ የለሾች የሰዎችን የተፈጥሮ ባሕርይ ሊለውጡ አልቻሉም። ይህም በአሁኑ ጊዜ ሃይማኖት በምሥራቅ አውሮፓ እንደገና በማንሰራራቱ ተረጋግጦአል።
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ‘በሰማይም ሆነ በምድር ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች እንዳሉ ሁሉ አማልክት ተብለው የሚጠሩ ብዙ’ እንዳሉ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 8:5) በዘመናት ሁሉ የሰው ልጅ ሕልቈ መሣፍርት የሌላቸውን አማልክት አምልኳል። የመዋለድ፣ የፍቅር፣ የጦርነት፣ የወይንና የፈንጠዝያ አማልክት ነበሩ። በሂንዱ ሃይማኖት ብቻ የአማልክት ቁጥር በሚልዮን የሚቆጠር ነው።
የአማልክት ሦስትነት ወይም ሥላሴዎች በባቢሎን፣ በአሦርና በግብፅ እንዲሁም በቡድሂስት አገሮች በጣም በዝተው ነበር። ሕዝበ ክርስትናም የራሷ “ቅድስት” ሥላሴ አላት። እስልምና ሥላሴን ስለማይቀበል “ከአላህ በቀር ሌላ አምላክ” የለም ይላል። ከዚህም በላይ የማይታይና ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ አለ በሚለው እምነት ላይ የሚያሾፉ ሰዎችም እንኳ ቢሆኑ የየራሳቸው አማልክት አሏቸው። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ በፊልጵስዩስ 3:19 ላይ ሀብትን በማሳደድ ስለተጠመዱ ሰዎች ሲናገር “ሆዳቸው አምላካቸው ነው” ይላል።
ብዙ ሰዎች በተወለዱበት አገር ወይም ሕብረተሰብ የሚመለከውን አምላክ ወይም አማልክት ያመልካሉ። ይህም ጥያቄዎችን ያስነሣል። ሁሉም የአምልኮ አይነቶች ወደ አንድ ተራራ ጫፍ እንደሚመሩ የተለያዩ መንገዶች ወደ አንድ ሥፍራ የሚመሩ ናቸውን? ወይስ ብዙ የሆኑት የሃይማኖት ምስጢራዊ መንገዶች ወደ ገደል እንደሚመሩ ጎዳናዎች ወደ ጥፋት የሚመሩ ናቸው? ትክክል የሆኑት የአምልኮ አይነቶች ብዙ ናቸው ወይስ አንድ ብቻ? ሊወደሱ የሚገባቸው የተለያዩ አማልክት አሉ ወይስ ፍጹም የሆነ አምልኮ ሊሰጠው የሚገባ አንድ አምላክ ብቻ አለ?
የሐሰት አማልክት አነሣስ
ከላይ የተጠቀሱት ጥያቄዎች በጥብቅ ሊመረመሩ የሚገባቸው ናቸው። ምክንያቱም ስለ ሃይማኖት ከተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ የበለጠ ረዥም እድሜ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሐሰተኛ አምላክ በእባብ ተጠቅሞ የመጀመሪያዎቹን ቅድመ አያቶቻችንን አሳስቶ ወደ ጥፋት መንገድ እንዳስገባቸው ስለሚገልጽልን ነው። የሱ ስልት ያመጣቸው አስጨናቂ ውጤቶች አሁንም አሉ። (ዘፍጥረት 3:1-13, 16-19፤ መዝሙር 51:5) የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን አመጸኛ አምላክ “የዚህ ዓለም ገዥ” ሲል ጠርቶታል። ከኢየሱስ ሐዋርያት አንዱ ደግሞ “የዚህ ዓለም አምላክ” ብሎታል። (ዮሐንስ 1:34፤ 12:31፤ 16:11፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4) በራእይ 12:9 ላይ “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እሱም የቀድሞው እባብ” በማለት ተገልጿል። የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሚመራው በእሱ ቁጥጥር ሥር ነው።
ሰይጣን ቀንደኛ አታላይ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:14) ብዙ ዓይነት አማልክት፣ ለምሳሌ ያህል በዘር የሚወረሱ መናፍስት፣ ጣኦቶች፣ ቅዱሳን ናቸው የሚባሉ ሰዎችን ምስሎች፣ እመቤቶች እንዲመለኩ በማድረግ በሰው ልጆች የማምለክ የተፈጥሮ ባሕርይ ይጫወታል። ኃያል መሪዎች፣ ድል አድራጊ ጄኔራሎችና የፊልምና የስፖርት ኮከቦች እንዲመለኩ በማድረግ የሰብአዊ አማልክትን አምልኮ አስፋፍቶአል። (ሥራ 12:21-23) ‘ከእያንዳንዳችን ያልራቀውን’ ብቸኛና እውነተኛ አምላክ ፈልገን ለማምለክ ቁርጥ ውሳኔ ብናደርግና ብንጠነቀቅ መልካም እናደርጋለን።—ሥራ 17:27
ታዲያ ይህ ልናመልክ የሚገባን ልዩ አምላክ ማነው? ይህን አምላክ የመጽሐፍ ቅዱሱ መዝሙራዊ ከ3,000 ዓመታት በፊት “ልዑል . . . . ፣ ሁሉን የሚችል . . . ፣ የምተማመንበት አምላኬ” ካለ በኋላ በገናናው ስሙ በመጠቀም “ይሖዋ” በማለት ጠርቶታል። (መዝሙር 91:1, 2) ቀደም ብሎም ሙሴ ስለዚህ አምላክ እሱ “ይሖዋ አምላካችን አንድ ይሖዋ ነው” በማለት ተናግሯል። (ዘዳግም 6:4) ነቢዩ ኢሳይያስም አምላክ ራሱ “እኔ ይሖዋ ነኝ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም” ብሎ እንደተናገረ ጠቅሶአል።—ኢሳይያስ 42:8
ይሖዋ አምላክ ሐሰተኛው አምላክ ሰይጣን በስሙ ላይ ያላከከውን ነቀፌታ በሙሉ ለማጽዳት ዓላማ አለው። ይህንም እንዴት እንደሚያደርገው በ1513 ከዘአበ የእሥራኤልን ሕዝብ ከግብፃውያን ጭቆና ነፃ እንዲያወጣ ነቢዩን ሙሴን በተጠቀመበት ጊዜ በምሳሌ አሳይቶአል። በዚያ ወቅት አምላክ ይሖዋ የተባለውን ስሙን “የምሆነውን እሆናለሁ” ከሚሉት ቃላት ጋር አዛምዶአል። (ዘጸአት 3:14, 15) ማንነቱን ለግብጹ ፈርኦን ያረጋግጣል። በመጀመሪያ ግን ለዚህ ክፉ መሪ እንዲህ አለው፦ “ኃይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነስቼሃለሁ፣ (አቆይቼሃለሁ)።”—ዘጸአት 9:16
ዛሬም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የዚህ ዓለም አምላክ የሆነው ሰይጣን እንደ ጥንቱ ፈርዖን ይሖዋ አምላክን ይቃወማል፤ ጽድቅንና እውነትን በሚያፈቅሩ ሰዎች ላይም በተንኮል መንፈሳዊ ውጊያ ያካሂድባቸዋል። (ኤፌሶን 6:11, 12, 18) አምላክ አሁንም እንደገና በሰይጣን ተቃውሞ ላይ የራሱን ስም ከፍ ሊያደርግ አስቧል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሰይጣንንና ሥራዎቹን ሁሉ በማጥፋት ኃይሉን ከማሳየቱ በፊት በምድር በሙሉ ስሙን እንዲያውጁ አምላኪዎቹን ይልካል። ይህ ስለ ስሙ የሚሰጠው ምሥክርነት የእውነተኛ አምልኮ አንዱ አቢይ ክፍል ነው።
አምላክ ራሱ እነዚህ አምላኪዎቹ የሱ ምሥክሮች፣ ማለትም የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚሆኑ መናገሩ ተገቢ ነው። “ምስጋናዬን እንዲናገሩ ለእኔ የፈጠርሁት ሕዝብ፣ የመረጥሁት ሕዝቤ” በማለት ስለእነዚህ ሕዝቦች ተናግሯል። (ኢሳይያስ 43:10-12, 21) የይሖዋን ምሥጋና የሚናገሩት እንዴት ነው? በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የምትተዳደረው የይሖዋ መንግሥት በዚህ ምድር ላይ ላሉ ታዛዥ የሰው ልጆች ዘላለማዊ በረከቶችን እንደምታመጣ የምሥራቹን እየተናገሩ ከቤት ወደቤት በመሄድ ለሕዝብ ይሰብካሉ። ስለዚህ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ያደርጉት እንደነበረው አምላክን “ያለማቋረጥ” ያመልኩታል። (ሥራ 5:42፤ 20:20, 21) ታዲያ ይህን በማድረጋቸው መለኮታዊ በረከት አግኝተዋልን? ተከታዮቹ ገጾች መልሱን ይሰጡናል።