በውጊያ በፈራረሰችው ላይቤሪያ ክርስቲያናዊ ታማኝነት መጠበቅ
አንድ የዓይን ምስክር እንደተናገረው
“ዝሆኖች ሲጣሉ የሚጐዳው ሣሩ ነው።” ይህ የምዕራብ አፍሪካ ምሳሌያዊ አነጋገር በቅርቡ በላይቤሪያ በተደረገው ጦርነት ላይ የደረሰውን ሁኔታ በአጭር ቃላት ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው። 20,000 የሚያህሉ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከአገሪቱ 2.6 ሚልዮን ሕዝብ መካከል ግማሾቹ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች አብዛኞቹ ወታደሮች ያልነበሩ ናቸው። እንደ “ሣሩ”፣ ማንንም የማይጎዱ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ነበሩ።
ጦርነቱ በታህሣሥ ወር 1989 ሲፈነዳ ወደ 2,000 የሚጠጉት የላይቤሪያ የይሖዋ ምሥክሮች የማያቋርጥ ጭማሪ ሲያገኙና መጪውን ጊዜም በመተማመን ማለትም በእርግጠኝነት ሲጠባበቁ ነበር። የሚያሳዝነው ግን እነሱም ‘የተጐዳው ሣር’ ክፍል መሆናቸው ነው።
የጦርነቱ መዛመት
ጦርነቱ የጀመረው በላይቤሪያና በኮት ዲቩዋር መካከል ባለው ድንበር ነበር። ወዲያው ስደተኞች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ወዳሉባት ወደ ዋና ከተማዋ ወደ ሞኖሮቪያ መሸሽ ጀመሩ። ከመጋቢት እስከ ግንቦት 1990 ባለው ጊዜ ውጊያው ወደ ደቡብ ሲዞር የይሖዋ ምሥክሮች ሚሲዮናውያን መጀመሪያ ከጋንታ ከዚያም ከግባርንጋ ለቀው እንዲወጡ ተደረጉ። እነዚህን ከተሞች ለቀው ለመውጣት የመጨረሻ ከሆኑት ሰዎች መሃል ነበሩ። የታጠቁ ኃይሎች ሐምሌ 2, 1990 ሞንሮቪያ ውስጥ ሲገቡ ጦርነቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ።
ከዚያ በኋላ የታዩት ሁኔታዎች ከተጠበቀው በላይ በጣም የሚያሰቅቁ ነበሩ። ሦስት የተለያዩ ሠራዊቶች በከባድ መሣሪያ በሮኬቶችና በቦምብ ወንጫፊዎች መንገድ ለመንገድ ተዋጉ። የጠላት ጐሣ አባል በመሆናቸው ምክንያት ከመገደል ሊያመልጡ ቢችሉም ከማያቋርጥ ጭንቀትና ብርበራ አላመለጡም። አንድ ቀን በነሐሴ ወር ውስጥ በቅዱስ ጴጥሮስ ሉተራን ቤተክርስቲያን ውስጥ ለመጠለል የሄዱ 600 ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ጦርነት ባሳበደው የግድያ ጓድ ተገድለዋል።
በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ከውጊያው ቦታ ሲሸሹ ከለበሱት ልብስ ሌላ የያዙት ነገር አልነበራቸውም። ቤተሰቦች ተነጣጥለው ለብዙ ወራት ሳይገናኙ ቆይተዋል። መላው የሞንሮቪያ ሕዝብ ቤት የሚለውጥ ይመስል ነበር። ባዶ በቀረው ቤት ውስጥ ወታደሮችና ከሌላው የከተማ ክፍል ሸሽተው የመጡ ሰዎች ይገቡበት ነበር። ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሞንሮቪያ ሕዝብ ከመኖሪያው ተፈናቅሎ ነበር። አብዛኞቹም ንብረታቸውን በሙሉና እጅግ ቢያንስ አንድ ዘመድ በሞት አጥተዋል። አንዳንዶች ብዙ ዘመድ ሞቶባቸዋል።
ሁኔታው በጣም አስጊ ደረጃ ላይ በመድረሱ የሌሎች አምስት የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ሰላምን ለመመለስ እንዲሞክሩ ወታደሮቻቸውን ላኩ። በ1990 ጥቅምት መጨረሻ ላይ ውጊያው በአብዛኛው በርዶ ነበር። ይሁን እንጂ በድን በሆነችው ከተማ ላይ የረሀብ ሥጋት ጥላውን አጠላባት። የእርዳታ ድርጅቶች አንድ ወቅት ላይ የሞንሮቪያ አንድ ሦስተኛ ልጆች የምግብ እጥረት እንዳላቸውና በየቀኑ ከ100 የሚበልጡ ሰዎች እየሞቱ እንደነበረ ገልጸው ነበር። አትራፊ ነጋዴዎችም ቢሆኑ ሁኔታውን ማባባሳቸው አልቀረም። ብዙ ሰዎች ለእርዳታ የሚከፋፈለውን ሩዝ ሰርቀው አንዱን ኩባያ ሩዝ በ20 ዶላርና ከዚያም በላይ ይሸጡ ነበር። የከተማዋ ውሃ፣ ጽዳትና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፈጽሞ ጠፍቶ ስለነበር በሽታ በተለይም ኮሌራ ተለይቶ አያውቅም።
በሞንሮቪያ የሚኖሩ በግምት አንድ ሺህ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮችም በአስከፊ ሁኔታ ተጎድተው ነበር። አብዛኞቹ ከከተማዋ ሸሽተው ወደ አገር ቤት ሲሄዱ ሌሎቹ ደግሞ በመርከብ ወደ ጋናና ወደ ናይጄሪያ ወይም ደግሞ በመኪና ወደ ኮት ዲቩዋር ወይም ወደ ሴራሊዮን ሄደው ነበር። ከሐምሌ እስከ ታህሣሥ 1990 ከ30 የሚበልጡ ምሥክሮች ሕይወታቸውን አጥተዋል። አንዳንዶች በተኩሱ ሲሞቱ ሌሎች ደግሞ የሞቱት በበሽታና በረሃብ ምክንያት ነበር። የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ተመርቀው በሚሲዮናዊነት ያገለግሉ የነበሩት አሜሪካውያን አለን ባቲና አርተር ላውሰን ከተገደሉት መሃል ነበሩ። በዚያ አሰቃቂ ጊዜ ዘመዶቻቸውን ወይም ጓደኞቻቸውን በሞት ላጡ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው የትንሣኤ ተስፋ ትልቅ መጽናኛ ሆኖላቸዋል።—ሥራ 24:15
ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት በተግባር ሲገለጽ
ውጊያው እንደተጧጧፈ ብዙ የተፈናቀሉ ምሥክሮች መጠጊያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮና በከተማዋ ሌላ ወገን ወዳለው የሚስዮናዊያን ቤት ሸሹ። አንዳንዶች መጠጊያ ማግኘት ያስፈለጋቸው የተጠላውና ይገደል የነበረው ጐሣ አባሎች ስለነበሩ ነበር። አብዛኞቹ በቅርንጫፍ ቢሮው ሥራ ተሰጥቷቸው ምግብ በማብሰልና በጽዳት ሥራ ከፍተኛ እርዳታ ሲሰጡ ቆይተዋል። ሌሎች ደግሞ በውጭ ያለው ሁኔታ ሲፈቅድ በአቅራቢያው ወዳለው ረግረግ ሄደው የሚበላ ቅጠላቅጠል እንዳለ እንዲፈልጉ ይላኩ ነበር።
በሚሲዮናውያኑ መኝታ ቤት፣ በመተላለፊያ ኮሪደሮች፣ በመጫኛ ክፍሉና በቢሮዎቹ ሁሉ ሰዎች ይተኙባቸው ነበር። ሽንት ቤቶች ቆፍረን በሚገባ እየጠበቅን እንጠቀም ነበር። ሴቶች በነርስነት እንዲያገለግሉ ተመድበው ነበርና ብዙ የወባና የትኩሳት በሽታዎችን በተሳካ ሁኔታ አክመዋል። ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥመው ችግር ተቅማጥ ነበር።
ልዩ የቤት ውስጥ ዝግጅትም አደረግን። ቦምብ ሲወረወርብን እንዴት እንደምንሸሽ ጭምር ተለማመድን። ስለዚህ ተቃዋሚ ኃይሎች እርስ በርሳቸው ከባድ መሣሪያ ሲወራወሩ መከለያ ወዳላቸው የቅርንጫፍ ቢሮው አካባቢዎች በፍጥነት እንድንሸሽ ማሠልጠኛ ተሰጠን። አሥር ጫማ ከፍታ ያለው ግድግዳችን በመጠኑ ሊከላከልልን ቢችልም ከጣራው ላይ የሚዘንቡትን ጥይቶች ግን ለመከላከል የሚበቃ አልነበረም። ጣራችን በመበሳሳቱ ምክንያት የጨው መነስነሻ መሰለ።
ብዙ ወንድሞች የጠላት ጎሣ አባሎች በመሆናቸው ምክንያት ብቻ ሊገደሉ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ለማዳን የራሳቸውን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለዋል። አንድ ቀን አንዲት እህት ከሞት ከተረፉት ልጆቿ ጋር እያለቀሰች ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው መጣች። አንደኛው ልጅዋ ከተወለደ ገና ሁለት ሳምንቱ ነበር። ባሏና በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኝ ልጅዋ ባይኗ እያየቻቸው ተረሽነዋል። እሷንና ሌሎቹን ልጆቿን እንደገና ሊወስዷቸው ሲመጡ ሌላዋ ምሥክር ደብቃቸው ስለነበር ሊያመልጡ ቻሉ።
ወደ ቅርንጫፍ ቢሮ የመጣው ሌላ ቤተሰብ ደግሞ አንዲት ያልተጠመቀች አስፋፊ ከራስዋ ጎሣ የሆኑ ሰዎች እንዳይገድሉአቸው አድና ያመጣችው ነበር። ከዚያ በኋላ ደግሞ ሁኔታው ተለውጦ ያች ያልተጠመቀች አስፋፊ ሕይወቷ አደጋ ላይ ሊወድቅ ሲል ያ የረዳችው ቤተሰብ ከራሳቸው ጎሣ የሆኑ ሰዎች እንዳይገድሏት አድነዋታል።
የታጠቁ ሰዎች ቅርንጫፍ ቢሮውን ሊፈትሹ ወይም ሊዘርፉ ሲመጡ ሚሲዮናውያኑ ከእነሱ ጋር በመነጋገር ብዙ ጊዜ ከበር ይመልሷቸው ነበር። አንድ ጊዜ አንድ የተናደደ ቡድን አባሎች በላያችን ላይ የጠመንጃ አፈሙዝ ደግነው አንድ እነሱ የሚፈልጉት ጐሣ አባሎች እንደደበቅን በመናገር ገፍትረውን ገቡ። በጊዜው ስብሰባ ላይ ስለነበርን የአካባቢው ምሥክሮች ረጋ ብለው በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ በጸጥታ ተቀምጠው ሲያዳምጡ በማየታቸው በጣም ተደነቁ። ቤቱን ፈተሹ፤ ግን የሚፈልጉትን አላገኙም ነበር። ለመጡብን ሰዎች ሁሉ እኛ ወታደሮችን ወይም የእነሱ ጠላት የሆነ ሰው እንዳልደበቅን ለማሳመን እንችል ነበር። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ገለልተኞች ነበርን።
አንድ ጊዜ ከባድ ውጊያ በነበረበት ጊዜ አንድ የምሥክሮች ቡድን በካንሰር በሽታ ምክንያት ሊሞት የተቃረበ አንድ ወንድም ይዘው ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው መጡ። ይህ ወንድም ብዙም ሳይቆይ ወዲያው ሞተ። መቃብሩ በአጥር ግቢው ውስጥ ተቆፈረ። በጣም ስሜት የሚነካ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተደረገለት። ይህ ወንድም ለብዙ አመታት በታማኝነት ያገለገለና በአካባቢው ከነበሩን ጥሩ ሽማግሌዎች አንዱ ነበር። መቶ የሚያክሉ ተፈናቃይ ወንድሞች የተኩስ ድምጽ እየተሰማ የቀብር ንግግሩን ለማዳመጥ በሳሎኑ ውስጥ ተሰብስበው ነበር።
ምግብና ውሃ ማግኘት
ያለን የምግብ አቅርቦት በጣም አነስተኛ ነበር። ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊትም ቢሆን ነጋዴዎች ሸቀጥ ወደ ከተማው ማስገባት አቁመው ነበር። ስለዚህ በከተማው ውስጥ የቀረው የምግብ ሸቀጥ በጣም ጥቂት ነበር። የነበረን ምግብ 12 አባሎች ላሉት ቤተሰባችን ለብዙ ወራት ሊያቆይ ይችል ነበር። ነገር ግን አንዳንዴ እርዳታ በጣም የሚያስፈልጋቸው ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎችን ጨምሮ እስከ 200 የሚደርሱ ሰዎች አብረውን ይኖሩ ነበር። ማንኛውም ሰው የሚበላው በቀን አንድ ጊዜ ጥቂት ምግብ ብቻ ነበር። በእንዲህ ዓይነቱ አመጋገብ ለብዙ ወራት መቆየት ቻልን። ሁሉም ሰው ረሐብተኛ ነበር። ሕፃናት ቆዳና አጥንት ብቻ ሆነው በወላጆቻቸው እቅፍ ጠውልገው ይታዩ ነበር።
የምግብ አቅርቦታችን ማለቅ ጀመረ። ተጨማሪ ምግብ ከየት እናገኝ ይሆን? በሞንሮቪያ ክፍት የሆነ መደብር አልነበረም። በሁሉም ቦታ የሚታዩት ውሾችን፣ ድመቶችንና አይጦችን ጨምሮ ምግብ ፍለጋ መንገድ ለመንገድ የሚንቀዋለሉ የተራቡ ሰዎች ብቻ ነበሩ። ከቅርንጫፍ ቢሮው ሚሲዮናውያን መካከል ሁለቱ 64 ኪሎሜትር ርቆ ወደሚገኘውና ጦርነቱ ወዳቆመበት ካካታ የሚባል ከተማ ለመሄድ ወሰኑ።
የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ለማሳወቅ በመኪናቸው መስኮት ላይ መጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችንና ምልክቶችን ለጥፈው ሄዱ። የተለያዩ የፍተሻ ጣቢያዎችን ካለፉ በኋላ ቦምብ በደረቱ ላይ ያንጠለጠለና ሽጉጥ የታጠቀ አንድ ትልቅ ጠብደል ሰው አቁሞ ጠየቃቸው። የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ከገለጹ በኋላ ምግብ ፍለጋ ወደ ካካታ እንደሚሄዱ ነገሩት።
“ተከተሉኝ። እኔ የዚህ ጦር አዛዥ ነኝ” አላቸውና ወደ ጠቅላይ ሠፈሩ ወሰዳቸው። ተፈናቃይ ሰዎችን እንዳስጠጉ ሲያውቅ እያንዳንዱ 50 ኪሎ የሚመዝን 20 ጆንያ ሩዝ ለቅርንጫፋችን እንዲያደርሱ ሰዎቹን አዘዘ! በተጨማሪም ወደ ካካታ እንዲሄዱ የፈቃድ ወረቀት ወጣላቸውና በቀሩት ፍተሻ ጣቢያዎች ያለአንዳች ችግር እንዲያልፉ እንዲረዳቸው አንድ የታጠቀ ዘብ ተመደበላቸው።
ካካታ ሲደርሱ መደብር ያለው አብርሃም የሚባል ክርስቲያን ወንድማችንን አገኙት። እሱም ዱቄት ወተት፣ ስኳር፣ በቆርቆሮ የታሸጉ አትክልቶችንና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ጨምሮ ብዙ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን በካርቶን ውስጥ ከመረልን። ወንድሞቻችን በመንገዳቸው ላይ ይህን የመሰለ እንክብካቤ ማግኘታቸው በእውነትም የሚያስገርም ነበር። ይሖዋ የምግብ ክምችታችንን እንደገና እንድናሟላ ያስቻለን የነበረንን ቀለብ ከወዳጆቻችንና ከጐረቤቶቻችን ጋር በመካፈላችን ተደስቶ ሳይሆን አይቀርም።—ምሳሌ 11:25
በሞንሮቪያ ሌላ ክፍል በሚገኘው የሚሲዮናውያን ቤት የሚኖሩት ሚሲዮናውያንም ለተፈናቃዮች እንክብካቤ ያደርጉ ነበር። እነሱም ካልተጠበቀ ምንጭ ዕርዳታ አግኝተዋል። ለምሳሌ ያህል አንድ ሚሲዮናዊ ከ16 ዓመታት በፊት ጀምሮ በወታደሩ ሠፈር አካባቢ ሲያገለግል ያውቀው ከነበረ አንድ ወታደር ሦስት ጆንያ ሩዝ አግኝቷል። ሌላ ሚስዮናዊም ከአንደኛው ተዋጊ ወገን መሪ ጋር በግል ከተነጋገረ በኋላ አራት ጆንያ ሩዝ አግኝቷል።
አንድ ወቅት ላይ በውኃ እጥረት ምክንያት ቅርንጫፉን መልቀቅ የሚኖርብን መስሎን ነበር። የአካባቢው ሰዎች ሁሉ የሚጠጣ ውኃ የሚያገኙት ከእኛ የውኃ ጉድጓድ ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ ለውሃ መግፊያ ሞተራችን የምንጠቀምበት ነዳጅ ማለቅ ጀመረ። በውጊያው መጀመሪያ ቀኖች ላይ በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ ተጠልሎ የነበረ አንድ ሰው ችግራችንን ሲሰማ ለሱ ላደረግንለት ነገር ባለው አድናቆት ተነሣሥቶ ነዳጅ ፈልጎ አመጣልን። ከዚያ በኋላ ውኃ አጥተን አናውቅም።
መንፈሳዊ ጥንካሬያችንን መጠበቅ
ጥቅምት 1990 የቀረነው ሚሲዮናውያን በሙሉ ለቅቀን እንድንወጣ ሲነገረን አእምሮአችንን ከሁሉ በላይ ያስጨነቀው ወንድሞቻችን እንዴት ይቋቋሙታል? የሚለው ሐሳብ ነበር። በአገልግሎት ተግተው በመሥራት ላይ መሆናቸውን ከዚያ ጊዜ ወዲህ ከሰማነው ሪፖርት ማረጋገጥ ችለናል።
ከጦርነቱ በፊት እያንዳንዱ ምሥክር በየወሩ በአገልግሎት የሚያሳልፈው ሰዓት በአማካይ 17 ነበር። ሆኖም በጦርነቱ ወቅት ምግብ ለመለቃቀም ያለማቋረጥ ወደ ጫካዎች መሄድ ቢያስፈልጋቸውም በአንዳንድ ጉባኤዎች እያንዳንዱ አስፋፊ በአማካይ 20 ሰዓት ያገለግል ነበር። ከዚህም በላይ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት እጥረት ስለነበረ እሁድ ለሚደረገው ጥናት የሚደርስ ተጨማሪ ቅጂዎች እንዲኖሩአቸው የሚጠኑትን ርዕሰ ትምህርቶች እህቶች በእጃቸው ይገለብጡ ነበር።
ለሞንሮቪያ ቅርብ የሆኑት አራት ጉባኤዎች ከከተማው ውጊያ ሸሽተው በሄዱ ምሥክሮች ሞልተው ነበር። እነዚህ ወዳጆች ምንም ነገር ለማንሣት ወደ ቤታቸው መመለስ ስላልቻሉ የነበራቸውን ነገር ሁሉ አጥተዋል። እንዲያውም ለበርካታ ወራት ከገዛ ልጆቻቸውና ከወላጆቻቸው ተነጣጥለው ጦርነቱ ከሚካሄድባቸው ቦታዎች ተቃራኒ በሆኑ አቅጣጫዎች ቆይተዋል! መጋቢት 30 ለዋለው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በእነዚህ አራት ጉባኤዎች የተገኙት ሰዎች በድምሩ 1,473 ነበሩ።
በሞንሮቪያ የቀሩት 300 ወይም ከዚያ የሚበልጡ ምሥክሮች ምንም እንኳን ከጥቂት ሣምንታት ቀደም ብሎ በረሃብ ምክንያት መራመድ እስኪሳናቸው ድረስ በአካል የተጎሳቆሉ ቢሆንም በመታሰቢያው ወር ላይ በረዳት አቅኚነት ለማገልገል ልዩ ጥረት አድርገዋል። ወደ መታሰቢያው በዓል ሰዎችን ለመጋበዝ ተግተው ስለሠሩ 1,116 ሰዎች ተገኝተው ነበር።
በሞንሮቪያ የሚኖር አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “ከታህሣሥ 1990 ጀምሮ በመንግሥት አዳራሻችን መሰብሰብ ለመጀመር ወሰንን። መጀመሪያ የተገኘነው 17 ነበርን። በኋላ ወደ 40 ከፍ አለንና ለጥቂት ጊዜ ቁጥራችን በዚያው ቀጠለ። ከዚያ በኋላ የካቲት 24 ቁጥራችን ወደ 65 ቆይቶም ወደ 85 አደገ። በመጋቢት ወር በረዳት አቅኚነት እንዲያገለግሉ የቀረበላቸውን ጥሪ የተቀበሉት ሁሉም አስፋፊዎች ነበሩ ማለት ይቻላል።”
ሌሎችን መንከባከብ
አንድ ራሱ ምሥክር ያልሆነ የአንድን የይሖዋ ምሥክር ዘመድ ሲገልጽ “የቤተክርስቲያናችን ወንድሞች በጦርነቱ ወቅት እርስ በርሳቸው (አንደኛው ጎሣ ሌላውን ጐሣ) በመገዳደል ሥራ ተጠምደው ነበር። ለእምነት መሰሎቻቸው ምንም ጊዜ አልነበራቸውም” ብሎአል። የይሖዋ ሕዝቦች ግን ከዚህ የተለዩ ነበሩ።!
ለምሳሌ ያህል የጎረቤቶች እርዳታ ሰጭ ቡድን ሊቀ መንበር በየካቲት 1991 የቅርንጫፍ ቢሮውን ሥራ ይመሩ ለነበሩት ወንድሞች እንደሚከተለው ሲል ጻፈ፦ “ይህ ደብዳቤ የተጻፈው ለሕዝቦቻችን ምግብ በምናድልበት ጊዜ ሁልጊዜ ስለምትሰጡን የመጋዘን አገልግሎት ለእናንተና ለድርጅታችሁ የምሥጋናና የአድናቆት መግለጫ እንዲሆን ነው። በሰብአዊ ስሜት ተነሳስታችሁ የምታደርጉት ነገር ሁሉ ማህበራችሁ ለአገሪቱ ሰላምና በጐ ፈቃድ ለማምጣት ያለውን ፈቃደኝነት ያሳያል። እባካችሁ ይህን የግብረሰናይ አገልግሎታችሁን ቀጥሉበት።”
በሌሎች አገሮች ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ለላይቤሪያ ወንድሞቻቸው ችግር ምላሽ ለመስጠት ፈጣኖች ነበሩ። በምዕራብ አፍሪካ ካሉት ከሴራሊዮንና ከኮት ዲቩዋር፣ ከአውሮፓ ደግሞ ከኔዘርላንድስና ከኢጣሊያ እንዲሁም ከዩናይትድ ስቴትስና ከመሳሰሉት አገሮች እርዳታ ቀርቧል።
እናቷ የጠላት ጐሣ አባል ስለሆነች የተገደለችባት አንዲት ትንሽ ልጅ ለተሰጣት እርዳታ ምሥጋናዋን ገልጻለች። እንዲህ ስትል ጻፈች፦ “ለምትልኩልኝ ነገር ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ። እናቴ ጋር እንዳለሁ ሆኖ እንዲሰማኝ አድርጋችሁኛል። በውጊያው እናቴንና ትንሽ ወንድሜን አጥቻለሁ። ይሖዋ ሁላችሁንም እንዲባርካችሁ እለምናለሁ። ዕድሜዬ 11 ዓመት ነው።”
የጠላት ጎሣ አባል በመሆንዋ ምክንያት ለብዙ ወራት ተደብቃ ለመኖር የተገደደች ሚስት ያለችው የስድስት ቤተሰብ ራስ የሆነ አንድ ወንድም ለተሰጠው ዕርዳታ ምሥጋናውን እንደሚከተለው በማለት ገልጿል፦ “የሰዎችን ንብረት ለመዝረፍና ለመሸጥ የሰዎችን ቤት አልሰበርንም። ሆኖም ያለንን ጥቂት ነገር እንዴት በጥበብ እንደምንጠቀምበት ስለምናውቅ እንደ ጐረቤቶቻችን የሚበላ ነገር አላጣንም። ይህንም የተማርነው ከይሖዋ ነው።”
ከሚስቱና ከሁለት ልጆቹ ጋር ወደ ኮት ዲቩዋር ሸሽቶ የነበረ ወንድም ያሳየው መንፈስም በጣም የሚያስደንቅ ነበር። ትቶ የሄደው ጥሩ ቤት ተቃጥሎና ፈርሶበት ነበር። ሆኖም በጣም ያሳዘነው ነገር የቤቱ መቃጠል ሳይሆን የቲኦክራቲካዊ መጻሕፍቱ መጥፋት ነበር።
የተገኙት ጠቃሚ ትምህርቶች
ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ ይሖዋ ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን እንዳስተማረን እገነዘባለሁ። ታማኝነታቸውን ጠብቀው በሕይወት ከቆዩት ወንድሞች ብዙዎቹንና ታማኝነታቸውን ጠብቀው ከሞቱት ጥቂቶቹን በግል ስለማውቃቸው “በሕይወት ሆነን ብንኖር ለይሖዋ እንኖራለንና ብንሞትም ለይሖዋ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የይሖዋ ነን” በማለት የተናገረውን የሐዋርያው ጳውሎስን አስተሳሰብ የመያዝን አስፈላጊነት ማድነቅ ተምሬያለሁ።—ሮሜ 14:8
ለረዥም ጊዜ ሚሲዮናዊ ሆኖ ሲያገለግል የቆየ አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ገለጸ፦ “በዚህ ሁሉ ችግር ይሖዋ ተወዳዳሪ የሌለው ረዳት መሆኑን ተምረናል። ልክ ጳውሎስ እንዳለው “ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር።” (2 ቆሮንቶስ 1:9፤ መዝሙር 30:10) በተጨማሪም “ጦርነቱ የይሖዋ ሕዝቦች በእርግጥ ወንድማማቾች እንደሆኑ፣ ኢየሱስ የገለጸውን ራሱን የሚሰዋ ፍቅር የተላበሱ እንደሆኑ አስገንዝቦናል” ብሏል።—ዮሐንስ 13:35
አንዲት ላይቤሪያዊት እህት ጥቅምት 1990 በጦርነቱ ወቅት አገሪቱን መልቀቅ እንዳለብን ለተገለጸልን አንዳንድ ሚሲዮናውያን የጻፈችው ደብዳቤ የክርስቲያናዊ ወንድማማችነታችንን ጥንካሬ በሚገባ ይገልጻል፦ “ሁላችሁም እንደገና ወደ ላይቤሪያ ቶሎ ተመልሳችሁ እንድትመጡና ትልቅ ስብሰባ እንዲኖረን ጸሎቴ ነው፤ ግን ያ ቀን ራቀብኝ። ስለዚህ ቀን ማሰቡ ብቻ ያስደስተኛል” በማለት ጻፈች።
አዎን የተለመደው ክርስቲያናዊ ሥራ ሙሉ በሙሉ በላይቤሪያ ተመልሶ ማየት በጣም የሚያስደስት ነገር ይሆናል። እህታችን ትክክል ናት። ሚሲዮናውያንና ሌሎችም ስደተኞች ከተመለሱ በኋላ በሞንሮቪያ የሚደረገው የመጀመሪያው የወረዳ ስብሰባ የሚያስደስት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም!
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ላይቤሪያ
ሞንሮቪያ
ካካታ
ባርና
ጋንታ
ሲየራ ሊዮን
ጊኒ
ኮት ዲቩዋር
አትላንቲክ ውቅያኖስ
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጦርነቱ ወቅት በቅርንጫፍ ቢሮው ይኖሩ የነበሩት ተፈናቃይ ምሥክሮች ልጆች
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የላይቤሪያ ስደተኞች የኮት ዲቩዋር ምሥክሮች ከላኩላቸው የእርዳታ ልብሶች መሃል ሲመርጡ