የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 2/15 ገጽ 13-18
  • ለኢየሱስ ፍቅር አጸፋውን ትመልሳለህን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለኢየሱስ ፍቅር አጸፋውን ትመልሳለህን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ለኢየሱስ ፍቅር ተገቢ ምላሽ መስጠት
  • ኢየሱስ ምን እንድናደርግ ይፈልጋል?
  • የኢየሱስን አርዓያ ተከተል
  • የተሟላ ምሥክርነት ለመስጠት ሠልጥነዋል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • “ያላያችሁትም እንኳ ቢሆን ትወዱታላችሁ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • በፍቅር በማስተማር ኢየሱስን ምሰሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • ‘የክርስቶስን ፍቅር ማወቅ’
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 2/15 ገጽ 13-18

ለኢየሱስ ፍቅር አጸፋውን ትመልሳለህን?

“የኢየሱስ ፍቅር ግድ ይለናልና።”—2 ቆሮንቶስ 5:14

1. የኢየሱስ ፍቅር እንዴት ሊገለጽ ይችላል?

እውነትም የኢየሱስ ፍቅር በጣም አስደናቂ ነው። የዘላለም ሕይወት የምናገኝበት ብቸኛ መንገድ የሆነውን የቤዛ ዝግጅት ሊያስገኝልን ሲል የተቀበለውን በቃላት ሊገለጽ የማይችል መከራ ስናስብ ልባችን በአድናቆት ይሞላል። አስቀድመው የወደዱን ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ናቸው። ገና ኃጢአተኞች ሳለን ወደውናል። (ሮሜ 5:6-8፣ 1 ዮሐንስ 4:9-11) ሐዋርያው ጳውሎስ “ለማወቅ የሚያዳግተው የክርስቶስ ፍቅር” ሲል ጽፎአል። (ኤፌሶን 3:19 የ1980 ትርጉም) በእርግጥም የኢየሱስ ፍቅር አንጎል ሊረዳ ከሚችለው ተራ ዕውቀት የላቀ ነው። የሰው ልጅ ካየውና ካጋጠመው ከማንኛውም ነገር ሁሉ የሚያልፍ ነው።

2. ኢየሱስ እንዳይወደን ምን ነገር ሊያግደው አይችልም?

2 ጳውሎስ በሮም ለነበሩ ክርስቲያኖች ሲጽፍ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፣ ወይስ ጭንቀት፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሐት፣ ወይስ ሠይፍ ነውን?” በማለት ጠይቋል። ከእነዚህ ነገሮች አንዱም ቢሆን ክርስቶስ እንዳይወደን ሊያግደው አይችልም። ጳውሎስ በመቀጠል “ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ” ብሎአል።—ሮሜ 8:35-39

3. ኢየሱስና አባቱ እንዲተዉን የሚያደርጋቸው ምን ነገር ብቻ ነው?

3 ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ለእናንተ ያላቸው ፍቅር ይህን ያህል ኃይለኛ ነው። እንዳይወዱአችሁ የሚያደርጋቸው አንድ ነገር ብቻ አለ። እሱም ይሖዋና ኢየሱስ እንድታደርጉ የሚያዝዙአችሁን ነገር ለመፈጸም እምቢ በማለት በገዛ ፈቃዳችሁ ፍቅራቸውን ሳትቀበሉ ብትቀሩ ብቻ ነው። አንድ ጊዜ አንድ የአምላክ ነቢይ ለአንድ የአይሁድ ንጉሥ “እናንተ [ከይሖዋ (አዓት)] ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ነው። ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል” ብሎታል። (2 ዜና 15:2) ታዲያ በእኛ መሐል እንደ ይሖዋ አምላክና እንደ ልጁ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሰሉ ግሩምና ርኅሩኅ ወዳጆች ዞር ለማለት የሚፈልግ ማነው?

ለኢየሱስ ፍቅር ተገቢ ምላሽ መስጠት

4, 5. (ሀ) ኢየሱስ ለእኛ ያለው ፍቅር ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን ዝምድና የሚነካው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ለእኛ ባለው ፍቅር ምክንያት ማንንም ጭምር እንድንወድ እንገፋፋለን?

4 ይሁን እንጂ እያንዳንዳችሁ ዳርቻ በሌለው የኢየሱስ ፍቅር በግል የተነካችሁት እንዴት ነው? እንዴትስ ልትነኩ ይገባል? በእርግጥ ኢየሱስ የእርሱ ምሳሌነት ከሰዎች ጋር ያለንን ዝምድና እንዴት ሊነካ እንደሚገባ ገልጾልናል። የሐዋርያቱን እግር በማጠብ በትህትና ካገለገላቸው በኋላ “እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ” ብሎአቸዋል። ቀጥሎም “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፣ እንደወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትዕዛዝ እሰጣችኋለሁ” አላቸው። (ዮሐንስ 13:15, 34) ደቀ መዛሙርቱም ይህ ትምህርት ወደ ልባቸው ስለገባ ኢየሱስ እንዳደረገው ለማድረግ ተገፋፍተዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ ሲጽፍ “እርሱ ስለእኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል” ብሎአል።—1 ዮሐንስ 3:16

5 ይሁን እንጂ የእርሱ ምሳሌነት ሌሎች ሰዎችን እንድንወድና የሚጠቅማቸውን ነገር እንድናደርግላቸው ብቻ የሚገፋፋን ከሆነ የኢየሱስን የሕይወቱንና የአገልግሎቱን ዓላማ ስተናል ማለት ነው። ኢየሱስ ለእኛ ያሳየው ፍቅር እሱን መልሰን እንድንወድና በተለይም ኢየሱስ ያወቃቸውን ነገሮች ሁሉ ያስተማረውን የኢየሱስን አባት እንድናፈቅር ሊገፋፋን አይገባምን? ለኢየሱስ ፍቅር አጸፌታውን በመመለስ ልክ ኢየሱስ እንዳደረገው አባቱን አታገለግሉምን?—ኤፌሶን 5:1, 2፣ 1 ጴጥሮስ 1:8, 9

6. ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሱስ ፍቅር የተነካው እንዴት ነበር?

6 በኋላ ጳውሎስ በመባል የታወቀውን ሳውልን ያጋጠመውን ሁኔታ እስቲ እንመልከት። በአንድ ወቅት “የጌታን ደቀመዛሙርት እንዲገድላቸው ዝቶ” ነበር። (ሥራ 9:1-5፣ ማቴዎስ 25:37-40) ኢየሱስን ባወቀ ጊዜ ግን ምህረት በማግኘቱ ከፍተኛ አመስጋኝነትና ባለውለታነት ስለተሰማው ለኢየሱስ ሲል ለመሰቃየት ብቻ ሳይሆን ለመሞትም እንኳን ዝግጁ ሆኖ ነበር። “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም። . . . አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው” በማለት ጽፎአል።—ገላትያ 2:20

7. የኢየሱስ ፍቅር ምን እንድናደርግ ያስገድደናል?

7 ኢየሱስ ለእኛ ያለው ፍቅር በሕይወታችን ውስጥ ምንኛ ታላቅ አስገዳጅ ኃይል መሆን ይኖርበታል! ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሲጽፍ “በሕይወት ያለነው ሁሉ ስለእኛ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ለራሳችን እንዳንኖር የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል” ብሎአል። (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) በእርግጥም ኢየሱስ ሕይወቱን ስለእኛ በመስጠቱ አመስጋኞች መሆናችን እሱ የሚፈልግብንን ሁሉ እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል። በእውነት እንደምንወደው ልናረጋግጥ የምንችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው። እርሱ “ብትወዱኝ ትዕዛዜን ጠብቁ” “ትዕዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው” ብሎአል።—ዮሐንስ 14:15, 21፣ ከ1 ዮሐንስ 2:3-5 ጋር አወዳድር

8. የኢየሱስ ፍቅር የብዙ ክፉ አድራጊዎችን ሕይወት የለወጠው እንዴት ነበር?

8 በጥንትዋ የቆሮንቶስ ከተማ የነበሩ አመንዝሮች፣ ዘማውያን፣ ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች፣ ሌቦች፣ ሰካራሞችና ቀማኞች ስለ ኢየሱስ ትዕዛዛት በተማሩ ጊዜ ይፈጽሙአቸው የነበሩትን ተግባሮች በመተው ለኢየሱስ ፍቅር አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። ጳውሎስ ስለ እነርሱ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል” በማለት ጽፎአል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ክርስቶስ እንደነዚህ ላሉት ሰዎች ያሳየው ፍቅር በዘመናችንም ቢሆን ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ እንዲያደርጉ አስገድዶአቸዋል። ጆን ሎርድ የተባሉት ታሪክ ፀሐፊ “እውነተኛዋ የክርስትና ሃይማኖት ድል ያገኘችው ትምህርቶችዋን እንከተላለን የሚሉ ሰዎች ተለውጠው ጥሩ ሰዎች ለመሆን በመቻላቸው ነው። ነውር የሌለበት ኑሮ ስለመኖራቸው፣ በማይነቀፍ ሥነምግባር ስለመመላለሳቸው፣ ጥሩ ዜጎች ስለመሆናቸውና ስለ ክርስቲያናዊ ጨዋነታቸው በቂ ማስረጃ አለን” ሲሉ ጽፈዋል። በእርግጥም የኢየሱስ ትምህርት በሰዎች አኗኗር ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቶአል።

9. ኢየሱስን ማዳመጥ ምን ማድረግን ያጠቃልላል?

9 በአሁኑ ጊዜ ማንም ሰው ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ከማጥናት ይበልጥ አስፈላጊ ስለሆነ ሌላ ነገር ሊያጠና አይችልም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ኢየሱስን ተመልከቱ . . . የጸናውን አስቡ” ሲል መክሮአል። (ዕብራውያን 12:2, 3) ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ መልኩ በተለወጠበትም ጊዜ አምላክ ራሱ “እርሱን ስሙት” ሲል አዝዞአል። (ማቴዎስ 17:5) ይሁንና ኢየሱስን ማዳመጥ እርሱ የሚናገረውን ከመስማት የበለጠ ነገርን እንደሚጨምር ግልጽ ሊሆን ይገባል። መመሪያዎቹን በመቀበል፣ አዎን እሱ ያደረጋቸውን ነገሮች እሱ ባደረገበት መንገድ ማድረግ ይገባናል። እሱን እንደ አርዓያችን አድርገን በመቀበልና የእርሱን ፈለግ በመከተል ለፍቅሩ አዎንታዊ ምላሽ እንሰጣለን።

ኢየሱስ ምን እንድናደርግ ይፈልጋል?

10. ኢየሱስ እነማንን አሰለጠነ? ለምንስ ዓላማ?

10 ኢየሱስ ከአምላክ የተሰጠው ተልእኮ ስለ አባቱ መንግሥት መስበክ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም ይህንኑ ሥራ እንዲሠሩ አሠልጥኖአቸዋል። ለመጀመሪያዎቹ ደቀመዛሙርቱ “በዚያ ደግሞ ልሰብክ ወደሌላ ሥፍራ በቅርብ ወዳሉ መንደሮች እንሂድ ስለዚህ ወጥቻለሁና” ብሎአቸዋል። (ማርቆስ 1:38፣ ሉቃስ 4:43) በኋላም 12ቱን ሐዋርያት በሰፊው ካሰለጠናቸው በኋላ “ሄዳችሁም መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ” የሚል መመሪያ ሰጥቶአቸዋል። (ማቴዎስ 10:7) ከጥቂት ወራት በኋላም ሌሎች 70 ደቀመዛሙርት ካሰለጠነ በኋላ “የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀረበች በሉአቸው” በማለት ልኮአቸዋል። (ሉቃስ 10:9) ኢየሱስ ተከታዮቹ ሰባኪዎችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ይፈልግ እንደነበረ ግልጽ ነው።

11. (ሀ) የኢየሱስ ደቀመዛሙርት እሱ ካደረገው የሚበልጥ ነገር የሚያደርጉት እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ከተገደለ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ምን ሆኑ?

11 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለዚህ ሥራ ማሠልጠኑን አላቋረጠም ነበር። ከመሞቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ምሽት “በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል” በማለት አበረታቷቸል። (ዮሐንስ 14:12) የተከታዮቹ ሥራ ከእሱ የሚበልጥበት ምክንያት አገልግሎታቸው እጅግ በጣም ሠፊ በሆነ አካባቢ ለሚኖር ሕዝብና ከፍተኛ ርዝማኔ ላለው ጊዜ የሚዳረስ ስለሆነ ነው። ሆኖም ኢየሱስ ከተገደለ በኋላ ደቀመዛሙርቱ በፍርሐት ምክንያት እንደ በድን ሆነው ነበር። ተደበቁ እንጂ እሱ እንዲሠሩ ያሠለጠናቸውን ሥራ በመሥራት አልቀጠሉም። እንዲያውም አንዳንዶቹ ወደ ዓሣ ማጥመድ ሥራቸው ተመለሱ። ይሁን እንጂ ለሰባቱ ሐዋርያትም ሆነ ለሌሎቹ ተከታዮቹ ሁሉ እንዲሠሩ የሚፈልገውን ሥራ ሊረሳ በማይችል መንገድ አስገንዝቦአል።

12. (ሀ) ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ምን ተአምር ፈጸመ? (ለ) ኢየሱስ “ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?” ብሎ ሲጠይቅ ምን ማለቱ ነበር?

12 ኢየሱስ ሰብዓዊ አካል ለብሶ በገሊላ ባሕር አጠገብ ታየ። ዓሣ ለማጥመድ ጀልባቸውን ይዘው የወጡት ሰባቱ ሐዋርያት ግን ሌሊቱን በሙሉ ምንም ዓሣ ሳይዙ አድረዋል። ኢየሱስም ባሕሩ ዳር ላይ ሆኖ በመጣራት “መረቡን በታንኳይቱ በስተቀኝ ጣሉት ታገኙማላችሁ” አላቸው። መረቡ ለመቀደድ እስኪደርስ ድረስ በተአምር በዓሣ በተሞላ ጊዜ በባሕሩ ዳር ያለው ኢየሱስ መሆኑን ተገነዘቡ። እሱ ወዳለበት ቦታም እየተቻኮሉ ሄዱ። ኢየሱስ ቁርስ ካበላቸው በኋላ፣ ወደተጠመዱት ብዙ ዓሦች እየተመለከተ ሳይሆን አይቀርም፣ ጴጥሮስን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?” ብሎ ጠየቀው። (ዮሐንስ 21:1-15) ኢየሱስ እኔ እንድትሠራ ካዘጋጀሁልህ ሥራ ይልቅ ዓሣ የማጥመዱን ሥራ ይበልጥ ትወዳለህን? ማለቱ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም።

13. ኢየሱስ ተከታዮቹ ለፍቅሩ ጥሩ ምላሽ ስለሚሰጡበት መንገድ ያስገነዘበው እንዴት ነበር?

13 ጴጥሮስም “አዎን ጌታ ሆይ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” በማለት መለሰ። ኢየሱስ መልሶ “ግልገሎቼን አሰማራ” አለው። ሁለተኛ ጊዜም ኢየሱስ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን?” ብሎ ጠየቀው። ጴጥሮስም እንደገና ፍጹም በሆነ የእርግጠኝነት መንፈስ “አዎን ጌታ ሆይ፣ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” ብሎ መለሰ። ኢየሱስም እንደገና “ጠቦቶቼን ጠብቅ” አለው። ሦስተኛ ጊዜ ኢየሱስ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ትወደኛለህን?” ብሎ ጠየቀው። አሁን ጴጥሮስ በጣም አዘነ። ኢየሱስን አላውቀውም ብሎ ሦስት ጊዜ የካደው ከጥቂት ቀናት በፊት ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ስለ ታማኝነቱ ጥርጣሬ ተሰምቶታል ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ጴጥሮስ ለሦስተኛ ጊዜ ምናልባትም የልመና ሁኔታ ባለው ድምጽ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” በማለት መለሰ። ኢየሱስም “በጎቼን አሰማራ” ብቻ ብሎ መለሰለት። (ዮሐንስ 21:15-17) ኢየሱስ ጴጥሮስና ባልንጀሮቹ ምን እንዲያደርጉ እንደሚፈልግ የሚያጠራጥር ነገር አልነበረም። እነርሱም ሆነ ዛሬ የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ሊሆኑ የሚፈልጉ ሁሉ ኢየሱስን ከወደዱት ደቀመዛሙርት በማድረጉ ሥራ መካፈል እንደሚኖርባቸው ሊረሳ በማይችል ሁኔታ እንዲገነዘቡ አድርጎአል።

14. ኢየሱስ በሌሎች ጊዜያትም ደቀመዛሙርቱ ለፍቅሩ ምላሽ ስለሚሰጡበት መንገድ ያመለከተው እንዴት ነው?

14 ይህ በባሕር ዳር የተደረገ ውይይት ካለፈ ከጥቂት ቀናት በኋላ ኢየሱስ በገሊላ በሚገኝ አንድ ተራራ ላይ ተገለጠና 500 ደስተኛ ተከታዮቹ ለተገኙበት ትልቅ ስብሰባ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው” የሚል ትዕዛዝ ሰጠ። (ማቴዎስ 28:19, 20፣ 1 ቆሮንቶስ 15:6) እስቲ አስበው! ይህን ትዕዛዝ የተቀበሉት ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆችም ጭምር ናቸው። ከዚያም ቆየት ብሎ ወደ ሰማይ ከማረጉ ጥቂት ቀደም ብሎ ለደቀመዛሙርቱ፦ “እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሎአል። (ሥራ 1:8) ጴጥሮስ ከዚህ ሁሉ ማሳሰቢያ በኋላ በርካታ ዓመታት ቆይቶ “ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን” ማለቱ አያስደንቅም።—ሥራ 10:42

15. ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ሊኖር የማይችለው ስለምን ነገር ነው?

15 ለኢየሱስ ፍቅር ጥሩ ምላሽ ስለምንሰጥበት መንገድ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ሊኖር አይችልም። ለሐዋርያቱ እንደነገራቸው “ትዕዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። . . . ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ።” (ዮሐንስ 15:10-14) እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ኢየሱስ ደቀመዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንድትካፈል የሰጠውን ትዕዛዝ በመፈጸም ለኢየሱስ ፍቅር አድናቆት እንዳለህ ታሳያለህን? የሚለው ነው። እውነት ነው፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ይህን ትዕዛዝ መፈጸም ለአንተ ቀላል ላይሆንልህ ይችላል። ለኢየሱስም ቢሆን ቀላል አልነበረም። ኢየሱስ ምን ዓይነት ለውጦችን ማድረግ አስፈልጎት እንደነበረ ተመልከት።

የኢየሱስን አርዓያ ተከተል

16. ኢየሱስ ምን ግሩም የሆነ አርዓያ ትቶልናል?

16 የአምላክ አንድያ ልጅ ከመላእክት ሁሉ የበለጠ የሰማያዊ ክብር ቦታ ነበረው። በእርግጥም ባለጠጋ ነበር! ሆኖም በፈቃደኝነት ራሱን ባዶ በማድረግ ተወልዶና የድሃ ቤተሰብ አባል ሆኖ በሽተኛና ሟች በሆኑ ሰዎች መካከል አደገ። ሐዋርያው ጳውሎስ “የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን እናንተ በእሱ ድህነት ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሃ ሆነ” በማለት እንደገለጸው ኢየሱስ ይህን ሁሉ ያደረገው ለእኛ ሲል ነው። (2 ቆሮንቶስ 8:9፣ ፊልጵስዩስ 2:5-8) ምንኛ ታላቅ አርዓያ ነው! እንዴትስ ያለ ታላቅ የፍቅር መግለጫ ነው! ለሌሎች ጥቅም ሲል የራሱ የሆነውን የተወ ወይም ከፍተኛ ሥቃይ የተቀበለ ከኢየሱስ ሌላ ማንም የለም። ሌሎች የበለጠውን ሀብት፣ አዎን ፍጽምናና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ያደረገ ሌላ ማንም የለም!

17. በፊታችን የተከፈተልን ወይም የተዘረጋው ምን ዓይነት ጎዳና ነው? እርሱንስ ከመከተል እንዴት ያለ ውጤት ይገኛል?

17 እኛም የኢየሱስን አርዓያ በመከተል ለሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ ጥቅም ልናስገኝ እንችላለን። ኢየሱስ ሰዎች የእሱ ተከታዮች እንዲሆኑ በተደጋጋሚ ያሳስባቸው ነበር። (ማርቆስ 2:14፣ ሉቃስ 9:59፣ 18:22) እንዲያውም ጴጥሮስ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና” በማለት ጽፎአል። (1 ጴጥሮስ 2:21) ኢየሱስ እንዳደረገው አባቱን ለማገልገል ስትል መከራ እስከመቀበል ድረስ ለክርስቶስ ፍቅር አዎንታዊ ምላሽ ትሰጣለህን? እንዲህ ብታደርግ ለሌሎች ሰዎች ከፍተኛ ጥቅም ልታስገኝ ትችላለህ። በእርግጥ የኢየሱስን ምሳሌ ተከትለህ ከአባቱ የተቀበላቸውን ትምህርቶች ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ ብታውል “ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ።”—1 ጢሞቴዎስ 4:16

18. (ሀ) ኢየሱስ ለሰዎች በነበረው ዝንባሌ ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል? (ለ) ሰዎች የኢየሱስን ባሕርይ እንዴት ተቀብለው ነበር?

18 ሰዎችን በይበልጥ ለመርዳት እንድንችል ከፈለግን ኢየሱስ ለሰዎች የተሰማው ዓይነት ስሜት ሊኖረን ይገባል። ስለ ኢየሱስ የተነገረ አንድ ትንቢት “ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል” ብሎአል። (መዝሙር 72:13) ኢየሱስ ይናገራቸው ለነበሩት ሰዎች “የፍቅር ስሜት” እንደነበረውና ሊረዳቸውም ይፈልግ እንደነበረ ተከታዮቹ ሊያስተውሉ ችለው ነበር። (ማርቆስ 1:40-42፣ 10:21) መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፣ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀውና ተጥለውም ነበረና አዘነላቸው” ይላል። (ማቴዎስ 9:36) ከባድ ኃጢአት የሠሩ ሰዎችም እንኳን ሳይቀሩ እንደሚወዳቸው ይሰማቸውና ወደ እርሱ ይሳቡ ነበር። በድምጹ ሁኔታ፣ በሚያሳያቸው ጠባይና በትምህርት አሰጣጡ እንዲረጋጉና እንዲዝናኑ ያደርግ ነበር። በዚህም ምክንያት የተናቁ ቀራጮችና አመንዝሮችም እንኳን ሳይቀሩ ፈልገው ያነጋግሩት ነበር።—ማቴዎስ 9:9-13፣ ሉቃስ 7:36-38፣ 19:1-10

19. ጳውሎስ የኢየሱስን አርዓያ የተከተለው እንዴት ነበር? እኛም እንዲሁ ብናደርግ ምን ዓይነት ውጤት እናገኛለን?

19 የመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም የእሱን ፍቅራዊ ምሳሌ ተከትለው ነበር። ጳውሎስ ላገለገላቸው ሰዎች “ሞግዚት የራሷን ልጆች እንደምትንከባከብ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን። . . . እየመከርንና እያጸናን እየመሰከርንላችሁም አባት ለልጆቹ እንደሚሆን ለእያንዳንዳችሁ እንደሆንን ታውቃላችሁና” በማለት ጽፎአል። (1 ተሰሎንቄ 2:7-11(አዓት)) በክልልህ ውስጥ ላሉት ሰዎች አፍቃሪ ወላጆች ለተወደዱ ልጆቻቸው እንደሚሰማቸው ዓይነት እውነተኛ አሳቢነት ይሰማሃልን? እንዲህ ዓይነቱን አሳቢነት በድምጽህ ሁኔታ፣ በፊትህና በተግባርህ ብታሳይ የመንግሥቱ መልእክት ለበግ መሰል ሰዎች ማራኪ ሊሆን ይችላል።

20, 21. የኢየሱስን አርአያ ተከትለው ፍቅርን ያሳዩ ዘመናዊ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?

20 በእስፓኝ አገር ሁለት ምሥክሮች በአንድ ብርዳማ ቀን እንጨት ስላለቀባት ቤቷ በጣም የቀዘቀዘባት በምርኩዝ የምትሄድ አንዲት በዕድሜ የገፋች ሴት አገኙ። ልጅዋ ከሥራ ሲመለስ እንጨት እንዲፈልጥላት እየጠበቀችው ነበር። ምሥክሮቹ እንጨቱን ፈለጡላትና የሚነበብ መጽሔት ትተውላት ሄዱ። ልጅዋ ሲመለስ ምሥክሮቹ ለእናቱ ባሳዩት አሳቢነት በጣም በመደነቁ ጽሑፎቹን አነበበ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረና ወዲያውኑ በመጠመቅ የአቅኚነት አገልግሎት ጀመረ።

21 በአውስትራሊያ አገር አንድ ሰውና ሚስቱ ቤተሰባቸውን የሚመግቡበት ገንዘብ እንደሌላቸው ሊያነጋግሩአቸው ለመጡት ምሥክሮች ነገሩአቸው። ምሥክሮቹ ባልና ሚስት ሄዱና የምግብ ሸቀጣ ሸቀጥና ለልጆች የሚሆን ጥቂት ጣፋጭ ገዝተው መጡ። ወላጆቹ በጣም ልባቸው ተነካና አለቀሱ። በጣም ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሣ ሕይወታቸውን ሊያጠፉ እያሰቡ እንደነበሩ ተናገሩ። ሁለቱም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩና ሚስቲቱ በቅርቡ ተጠመቀች። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር የይሖዋ ምሥክሮችን አለምክንያት በወሬ ብቻ የምትጠላ አንዲት ሴት ከአንዲት ምሥክር ጋር ከተገናኘች በኋላ “የተነጋገርነውን ነገር አላስታውስም። የማስታውሰው ግን ምን ያህል ደግ እንደነበረች፣ እንዴት ዓይነት አቀባበል እንዳደረገችልኝና ምን ያህል ትሁት እንደነበረች ነው። በእውነት ወደ እሷ ተስቤአለሁ። እስከዛሬም ድረስ የወዳጅነት አቀራረቧን በአክብሮት አስታውሳለሁ” ብላ ተናግራለች።

22. የኢየሱስን ሕይወት ከመረመርን በኋላ እሱን በሚመለከት ምን ዓይነት መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን?

22 ኢየሱስ የሠራውን ሥራ እሱ በሠራበት መንገድ በማከናወን ለፍቅሩ አዎንታዊ ምላሽ ስንሰጥ ብዙ ግሩም በረከቶችን እናገኛለን። ኢየሱስ ታላቅ ሰው መሆኑ ግልጽና የማያጠያይቅ ነው። “እነሆ ሰውዬው!” ያለውን ሮማዊ ገዥ የጴንጤናዊው ጲላጦስን ቃላት ለማስተጋባት እንገፋፋለን። አዎን በእርግጥም “ሰውዬው” በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የበለጠ ታላቅ ሰው ነበር።—ዮሐንስ 19:5

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ የኢየሱስ ፍቅር ምን ያህል ታላቅ ነው?

◻ የኢየሱስ ፍቅር እነማንን እንድንወድ ሊገፋፋን ይገባል? ይህስ ፍቅር ምን እንድናደርግ ግድ ይለናል?

◻ ኢየሱስ ምን ሥራ እንድንሠራ ይፈልጋል?

◻ ኢየሱስ ሀብታም የነበረው እንዴት ነው? ድሃ የሆነውስ ለምንድነው?

◻ ኢየሱስ ሰዎችን ያገለገለበትን መንገድ ልንመስል የሚገባን እንዴት ነው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍቅር የምናሳይበትን አርዓያ የተወልን ኢየሱስ ነው

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ ለእሱ ያላቸውን ፍቅር እንዴት መግለጽ እንዳለባቸው ጉልህ በሆነ መንገድ አስረድቷል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ