የምትመኘው ምን ዓይነት ደህንነት እንዲኖር ነው?
የተለያዩ ሰዎች ስለደህንነት የተለያየ አስተያየት አላቸው። አንዳንዶች ደህንነትን የሚመለከቱት በተቃራኒ ወገን ባሉ ወታደራዊ ኃይሎች መሃል እንደተፈጠረ የተረጋጋ ሁኔታ አድርገው ነው። ለምሳሌ ያህል የዓለምን መድረክ የሚቆጣጠሩት ልዕለ ኃያላን ተባባሪዎቻቸው ከሆኑት የአውሮፓ አገሮች ጋር ሆነው አነስተኛ ግጭቶች ተባብሰው ምድር አቀፍ የኑክሌር ጦርነት ወደመሆን ደረጃ ሊደርሱ የሚችሉበትን አደጋ ለመቀነስ በሚያስችሉ በብዙ ሐሳቦች ላይ ተስማምተዋል። የ1990 የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም የዓመት መጽሐፍ “በሌሎች የዓለም ክፍሎች” የሚኖሩ ሕዝቦች ለእነዚህ ጉዳዮች ብዙም ትኩረት አለመስጠታቸው የሚያስገርም መሆኑን ገልጿል።
ይሁን እንጂ በድሃ አገሮች ለሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “ደህንነት” ማለት በቂ ምግብና የጤና እንክብካቤ ማግኘት ማለት ነው። ያሽ ታንደን የሚባሉ የፖለቲካ ሳይንስ ሊቅ ሲገልጹ “ስለሰላምና ደህንነት የማሰብ ጉዳይ ሲነሣ ድቅን የሚልብን ከምዕራባዊው ባሕል የተወረሰው ጎልቶ የሚታየው አስተሳሰብ ነው። . . . ‘ደህንነት’ ሲባል ወደ አእምሮ የሚመጣው ሁለት ሦስተኛውን የዓለም ሕዝብ የሚያሳስበው የምግብና የቤት ችግር ሳይሆን እንደ ጦር መሣሪያና የጦር መሣሪያ ቅነሳ እንደማድረግ የመሳሰሉት ጉዳዮች ብቻ ናቸው” ብለዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ግን በአምላክ መንግሥት አስተዳደር ውስጥ ጦርነት እንደማይኖር ተስፋ ይሰጣል። “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል፤ ቀስትን ይሰብራል፣ ጦርንም ይቆርጣል፣ በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።” (መዝሙር 46:9፤ ኢሳይያስ 2:4) አካላዊ ሕመም ጊዜ ያለፈበት ነገር ይሆናል። “በዚያም የሚቀመጥ ታምሜያለሁ አይልም፣ በእርሷም ለሚቀመጡ ሰዎች በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል።”—ኢሳይያስ 33:24
በዚህች መንግሥት ሥር የኤኮኖሚ ችግር የሚያስፈራው ሰው አይኖርም። “ቤቶችን ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተክሉም።”—ኢሳይያስ 65:21, 22
ከሁሉ ይበልጥ ግን መንግሥቲቱ ለሰላምና ደህንነት መታጣት ዋና መንስኤ የሆነውን ነገር ታስወግዳለች። በሰው ልጅ ረዥም ታሪክ በሙሉ ምንም አይነት የተሳካ ውጤት ባላገኙትና ጨቋኝ በሆኑት መንግሥታት በስተጀርባ ሆኖ ሲሠራ የቆየው ማነው? እነዚህ መንግሥታት እንዲኖሩ የፈቀደላቸው አምላክ ነው። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዓለምም በሞላው በክፉው ተይዟል’ ስለሚል መንግሥታቱ ላደረሱት ጭቆና በኃላፊነት የሚጠየቀው ሰይጣን መሆን አለበት።—1 ዮሐንስ 5:19
በአምላክ መንግሥት ሥር ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች “የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል” በማለት የጻፈላቸው ቃላት ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ምን ዓይነት ታላቅ እፎይታ ይገኛል! (ሮሜ 16:20) ይህን አይነቱን ነገር ልታከናውን የምትችለው በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ የምትተዳደረው የአምላክ ሰማያዊት መንግሥት ብቻ ናት። ስለዚህ ምድር ወደ ገነትነት የምትለወጠው በዚያች መንግሥት ሥር ብቻ ነው።—ዘፍጥረት 1:28፤ ሉቃስ 23:43
አዎን፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው የደህንነት ተስፋ የሰው ልጅ ከሚያቅደው ከማንኛውም ነገር የላቀና ብዙ ነገሮችን የሚያጠቃልል ነው። ሌላው ቀርቶ “ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ስቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም” የሚል ተስፋ እናነባለን! (ራእይ 21:4) እንደዚህ ያለውን ተስፋ በእርግጠኝነት ልናምን እንችላለንን? አዎን እንችላለን። ምክንያቱም ተስፋዎቹ የመነጩት “ከአፌ የሚወጣ ቃሌ . . . የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም” ብሎ ከተናገረው ሁሉን ቻይ ፈጣሪ ከይሖዋ አምላክ ነው። (ኢሳይያስ 55:11) አሁንም እንኳን ይሖዋ አምላክ ለዘላለማዊ ልዕልናው መረጋገጥ ሲል ለሰው ልጅ ዘላቂና አስደሳች ሰላም፣ ደህንነትና ብልጽግና ለማምጣት የሚወስዳቸው እርምጃዎች የተሳካ ውጤት በማስገኘት ላይ ናቸው።