ዓለም አቀፍ ደህንነት ለማምጣት የወጡት ዕቅዶች ይሳኩ ይሆን?
አንድ ዓለም የተባለው የዓለም አብያተክርስቲያናት ጉባኤ (World Council of Churches) መጽሔት “ዓለምን አንቆ ይዞ የነበረው ቀዝቃዛ ጦርነት አሁን በአምላክ ምህረት ያበቃ ይመስላል” በማለት ዘግቧል። በመንፈሳዊ ትምህርት ፕሮግራም ላይ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ የሃይማኖታዊ ትምህርት ፕሮግራም ባልደረባ የሆኑት አንግሊካኑ ጸሐፊ ጆን ፖቤም “በማዕከላዊና በምሥራቅ አውሮፓ የተፈጸሙት ታላላቅ ክንውኖች . . . በአውሮፓና በቀረውም ዓለም ሰላም እንደሚመጣ የሚያበስሩ ምልክቶች ይመስላሉ” ብለዋል።
አምላክ የሰው ልጅ ለዓለም አቀፍ ደህንነት ከሚያወጣው ዕቅድ ጋር ተባባሪ መሆኑን የሚገልጹት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ተጠሪዎች ብቻ አይደሉም። ሊቀ ጳጳስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሚያዝያ ወር 1991 የፋርስ ባሕረሰላጤ ጦርነት እንዳበቃ ያኔ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ለነበሩት ለያቪየር ፔሬዝ ዴ ኩዌላ የሚከተለውን መልዕክት ልከው ነበር፦ “የመካከለኛው ምሥራቅና የምዕራብ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሶች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚያከናውናቸው ሥራዎች የጠበቀ እምነት አላቸው። . . . በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በሥሩ በሚተዳደሩት የተለያዩ ድርጅቶች አማካኝነት ጦርነቱ ችግር ላይ የጣላቸው ወገኖች ዓለም አቀፍ ኀዘኔታና ትብብር ሳያገኙ እንደማይቀሩ ተስፋ ያደርጋሉ።”
በተጨማሪም በ1975 የተደረገውን የሄልስንኪ ስምምነትና በ1986 የተደረገውን የስቶክሆልም ሰነድ ካዘጋጁትና ከፈረሙት 35 አገሮች አንዷ ቫቲካን ነች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 1986ን “ዓለም አቀፍ የሰላም ዓመት” ብሎ ሲያውጅ ሊቀጳጳሱ “ለዓለም ሰላም ጸሎት የሚደረግበት ቀን” አውጀው የዓለምን ዋና ዋና ሃይማኖቶች ተጠሪዎች በመጋበዝ የድርጅቱን ውሣኔ ደግፈዋል። በጥቅምት ወር 1986 የቡዲስት፣ የሂንዱ፣ የእስላም፣ የሺንቶ፣ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን፣ የሉተራን፣ የግሪክ ኦርቶዶክስ፣ የአይሁድና የሌሎችም እምነቶች ተጠሪዎች በኢጣሊያ አገር በአሲሲ አንድ ላይ ተቀምጠው በየተራ ለዓለም ሰላም ጸልየዋል።
ጥቂት ዓመታት ቆይቶም የካንተርበሪው የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ በሮማ ከተማ በተናገሩት የስብከት ቃል ከላይ የተጠቀሰውን ወቅት (“ለዓለም ሰላም የተደረገውን የጸሎት ቀን”) አስታውሰው ሲናገሩ “የሮሙ [ሊቀ ጳጳስ] የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናትን ሊያሰባስቡ እንደቻሉ በአሲሲ አይተናል። ለሰው ልጅ ሰላምና ደህንነት አንድ ላይ ለመጸለይ፣ አንድ ላይ ለመናገርና አንድ ላይ ለመሥራት ችለናል። . . . ለዓለም ሰላም የቀረበው ያ ጸሎት ሲጀመር ‘አዲስ ነገር እየሠራሁ እንዳለሁ ተመልከቱ’ ብሎ በተናገረው አምላክ ፊት እንዳለሁ ሆኖ ተሰምቶኝ ነበር” ብለዋል።
ሌሎች ሃይማኖቶችም ወኪሎቻቸውን ወደ አሲሲ ባይልኩም ሰው ለዓለም አቀፍ ደህንነት ያወጣቸው ዕቅዶች እንደሚሳኩ ሙሉ እምነት አላቸው። የደቡብ አፍሪካው የዳች ተሐድሶ ቤተ ክርስቲያን ይፋዊ መጽሔት የሆነው የዲ ከርክቦድ አዘጋጅ “ወደ አዲስ የዓለም ሥርዓት በመሸጋገር ላይ ነን። ከጥቂት ዓመታት በፊት የማይታሰብ ነገር ይመስል የነበረው ዛሬ ሲፈጸም እናያለን። በሠፊው የዓለም መድረክ በሶቪየት ህብረትና በምዕራቡ ዓለም መሃል ሲፈጸም የሚታየው እርቅ በአካባቢ ግጭቶችም ላይ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል። በራሳችን አካባቢ እንኳን ለረዥም ዘመናት በጠላትነት ይተያዩ የነበሩ ወገኖች እርስ በርሳቸው መነጋገር ጀምረዋል። ‘የሰላም’ ፍላጎት የትም ቦታ እየታየ ነው። . . . ክርስቲያኖች በሙሉ በሕዝቦች መሃል ሰላም ለማምጣት የሚደርገውን ጥረት በሙሉ ደስታ ሊቀበሉት ይገባል። በዘመናችን ሰላም እንዲመጣ ልንጸልይ እንችላለን” ብሏል።
የሰው ልጅ ለዓለም አቀፍ ደህንነት ያወጣቸውን ዕቅዶች አምላክ እየባረከ ነውን?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በሰው ጥረቶች ላይ መመካትን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ቀጥተኛ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፦ “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ። [መንፈሱ (አዓት)] ትወጣለች ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ ያን ጊዜ ምክሩ ሁሉ ይጠፋል።” (መዝሙር 146:3, 4) በዛሬው ጊዜ ለሰላም የሚደረገው ጥረት የሚያበረታታ መስሎ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ ተጨባጩን ሁኔታ መዘንጋት የለብንም። የሰው ኃይል በጣም ውስን ነው። አብዛኛውን ጊዜ ሁኔታዎችን በውጭ ከሚታዩት ይበልጥ ጥልቀትና ውስብስብነት ያላቸው ናቸው። ሰዎች ተጠንቅቀውና አሳምረው የነደፉአቸውን ዕቅዶች የሚያጨናግፉባቸውን የተዳፈኑና የተደበቁ ኃይሎች ለማስተዋል አይችሉም።
የአይሁድ መሪዎች በነቢዩ ኢሳይያስ ዘመን ማለትም ከኢየሱስ ዘመን ሰባት መቶ ዓመታት አስቀድሞ ዛሬ ከሚደረገው ጋር በሚመሳሰል መንገድ ከአጎራባች አገሮች ጋር የስምምነት ውሎችን በማድረግ ሰላምና ደህንነት ለማምጣት ዕቅድ ማውጣት ጀምረው ነበር። በዚያ ዘመንም ሃይማኖታዊ መሪዎች የፖለቲካ ሰዎች የሚያደርጉትን ጥረት ደግፈው ነበር። ኢሳይያስ ግን “ተመካከሩ፣ ምክራችሁም ይፈታል’ ቃሉን (ማንኛውንም ቃል) ተናገሩ፤ ቃሉም አይጸናም” በማለት አስጠንቅቆ ነበር። (ኢሳይያስ 8:10) ዕቅዶቻቸው ውድቅ ሆነው ቀርተዋል። ዛሬስ ይህን የሚመስል ሁኔታ ይፈጸም ይሆን?
አዎን፤ አምላክ በዚሁ ነቢይ በኩል ለምድር ሰላምና ደህንነት የሚያመጣበት የራሱ መንገድ እንዳለው ስላስታወቀ ዛሬም የሰው ልጆች ዕቅድ ውድቅ ይሆናል። አምላክ ለምድር ደህንነት የሚያመጣው በማንኛውም ሰብአዊ ድርጅት አማካኝነት ሳይሆን የእሥራኤል ንጉሥ በሆነው በዳዊት ዘር አማካኝነት ነው። (ኢሳይያስ 9:6, 7) ይህ የንጉሥ ዳዊት ወራሽ በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት ቀርቦ ሲመረመር ንጉሥ መሆኑንና ‘መንግሥቱ ግን ከዚህ ዓለም አለመሆኗን’ የገለጸው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ዮሐንስ 18:36፤ ሉቃስ 1:32) እንዲያውም የኢየሱስ መንግሥት ሰማያዊ መንግሥት ነች። ለዚህች ምድር ዘላቂና አስተማማኝ የሆነ ሰላምና ደህንነት የምታመጣው ይህች መንግሥት ነች እንጂ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወይም ማንኛውም ምድራዊ የፖለቲካ መንግሥት አይደለም።—ዳንኤል 2:44
ኢየሱስ ክርስቶስ የሱ መንግሥት በሰማይ መግዛት የምትጀምረው “ጦርና የጦርም ወሬ” በሚኖርበትና “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ” በሚነሣበት ዘመን እንደሚሆን ትንቢት ተናግሮ ነበር። ይህ የተፈጸመው በ1914 መሆኑንና ከዚያ ጊዜ ወዲህ ያሉት ዓመታት “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን” (አዓት) መሆናቸውን የትንቢቱ ፍጻሜ ያመለክታል።—ማቴዎስ 24:3, 6-8
ታዲያ ይህ መሆኑ ምን ያመለክታል? ለአሁኑ የዓለም ሥርዓት የቀረው ጊዜ የተወሰነ መሆኑንና በቅርቡም የሚያልቅ መሆኑን ነው። ይህ የሚያስጨንቅ ወይም የሚያሳዝን ነገር ነውን? በዚህ ሥርዓት ውስጥ ተስፋፍቶ የሚገኘውን ጭካኔ፣ የፍትሕ መጓደል፣ ጭቆና፣ ጦርነትና ስቃይ ካስታወስን የዚህ ሥርዓት ቀኖች በቅርቡ የሚያልቁ መሆናቸው አያሳዝነንም ወይም አያስጨንቀንም። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ “[የይሖዋ (አዓት)] መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፣ የእውቀትና [ይሖዋን (አዓት)] የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል” ብሎ በሚገልጸው ገዢ ሥር መተዳደር ያለጥርጥር እፎይታ ያመጣልናል።—ኢሳይያስ 11:2
በምድር ላይ የሚሰፍነው እውነተኛ ደህንነት
እንደ እውነቱ ከሆነ በአምላክ መንግሥት ሥር “እነሆ፣ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም” የሚለው የኢሳይያስ ትንቢት በዓለም በሙሉ ሳይፈጸም በምድር ላይ እውነተኛ ደህንነት ሊገኝ አይችልም። (ኢሳይያስ 65:17) የሃይማኖት መሪዎች የቱንም ያህል ለዚህ ዓለም ቢጸልዩ ሰው ዓለም አቀፍ ደህንነት ለማምጣት ያወጣቸው ዕቅዶች አምላክ ሰላምና ደህንነትን ለማምጣት የሚጠቀምበትን መንገድ ሊተኩ አይችሉም።
የአምላክ መንግሥት የምታመጣው ዘላቂ ዓለም አቀፍ ደህንነት በጣም ታላቅ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት መግለጫዎች አንዱ እንዲህ ይላል፦ “ሠይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሠይፍ አያነሣም፣ ከእንግዲህም ወዲህ ጦርነት አይማሩም። የሠራዊት ጌታ የይሖዋ አፍም ተናግሯልና እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።”—ሚክያስ 4:3, 4
ዘላቂና አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው ሰላም አምላክ ራሱ ዋስትና የሰጠበት ሰላም ብቻ ነው። ስለዚህ እምነትህን በአለቆች ላይ ከማድረግ ይልቅ ለምን በአምላክ ላይ አትጥልም? እንዲህ ካደረግህ “የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ ተስፋውም ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱ ውስጥ ያለውንም ሁሉ በፈጠረ፣ እውነትን ለዘላለም በሚጠብቅ በአምላኩ በይሖዋ የሆነ ሰው ደስተኛ ነው” የሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት እውነት መሆናቸውን ታረጋግጣለህ።—መዝሙር 146:5, 6አዓት
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና ዓለም አቀፍ ፖለቲካ
“ክርስቶስ መንግሥቱ ‘ከዚህ ዓለም አይደለችም’ ቢልም ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸው ቀሳውስትና መንበረ ጵጵስናው ከቆስጠንጢኖስ ዘመን ጀምሮ በዓለም አቀፍና በብሔራዊ የፖለቲካ ትግሎች ውስጥ በጋለ ስሜት ተካፍለዋል።”—የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ፖለቲካ ውስጥ የተጫወተችው ሚና የተሰኘው በሳንታ ክላራ ዩኒቨርሲቲ ኢየሱሳዊ ፕሮፌሰር የሆኑት ኤሪክ ሀንሰን ከጻፉት መጽሐፍ የተወሰደ።