‘የአምላክንና የኢየሱስን እውቀት ሳያቋርጡ ማግኘት’
“ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን የአንተንና የላክኸውን የኢየሱስ ክርስቶስን ዕውቀት ሳያቋርጡ ማግኘት የዘላለም ሕይወት ማለት ነው።” (ዮሐንስ 17:3 (አዓት)) ኢየሱስ ይህን የተናገረው ለሰማያዊ አባቱ በሚጸልይበት ጊዜ ነበር። በዚህም ቃሉ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚያስፈልገውን አንድ አቢይ ጉዳይ አመልክቶአል። ይሁንና አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ከአብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በመለየት ከላይ እንደተመለከተው በማለት የተረጎመው ለምንድን ነው?—የዮሐንስ 17:3ን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
እዚህ ላይ “ማወቅ” ወይም “እውቀት ማግኘት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ጊኖስኮ ከተባለው ግሥ በእርባታ የተገኘ ቃል ነው። የአዲሲቱ ዓለም አተረጓጎምም በተቻለ መጠን የዚህን ግሥ ትርጉም ግልጽ ለማድረግ የታሰበ ነው። ጊኖስኮ የተሰኘው ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ “ማወቅ” ማለት ቢሆንም ይህ የግሪክኛ ቃል የተለያዩ ተዛማጅ ትርጉሞች አሉት። የሚከተሉትን ፍቺዎች ተመልከት።
“ጊኖስኮ (-------) ዕውቀት ማግኘትን፣ ወደ ማወቅ መድረስን፣ መገንዘብን፣ መረዳትን፣ ወይም ሙሉ በሙሉ መረዳትን ያመለክታል። (ኤክስፖዚተር ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ኦቭ ኒው ቴስታመንት ወርድስ፤ ደብልዩ ኢ ቫይን) በመሆኑም የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ጊኖስኮን ‘ሳያቋርጡ እውቀት ማግኘት’ ብሎ መተርጎሙ ተቺዎች እንደሚሉት መጽሐፍ ቅዱስን መለወጥ አይደለም። ዕውቅ የመዝገበ ቃላት ጸሐፊ የሆኑት ጀምስ ሆፕ ሞልተን ይህ ቃል የሚያጠቃልላቸውን የተለያዩ ተዛማጅ ትርጉሞች ሲገልጹ “አሁን የተሠራበት ነጠላ ቃል (--------) ከጊዜ አንፃር ሲታይ ቀጣይ ወይም የማያቋርጥ ሂደትን የሚያመለክት ሲሆን ‘እውቀት የማግኘት ወይም የመሰብሰብ’ ትርጉም አለው” ብለዋል።—ኤ ግራመር ኦቭ ኒው ቴስታመንት ግሪክ
ኤ ግራማቲክ አናሊሲስ ኦቭ ዘ ግሪክ ኒው ቴስታመንት በዮሐንስ 17:3 ላይ ጊኖስኮ የተሠራበት መንገድ “ቀጣይ ሒደትን የሚያመለክት” እንደሆነ ይገልጻል። በዚህ የግሪክኛ ቃል ላይ የተሰጠ ተጨማሪ ማብራሪያ በማርቪን አር ቪንሰንት በተዘጋጀው ወርድ እስተዲዝ ኢን ዘ ኒው ቴስታመንት በተሰኘው ጽሑፍ ላይ ይገኛል። እሱም እንዲህ ይላል፦ “አሁን የተሠራበት ግሥ የጊዜ አገባብ የሚያመለክተው መቀጠልን፣ በየደረጃው እያደገ የሚሄድን መረዳት ስለሆነ የዘላለም ሕይወት የሚገኘው በእውቀት፣ ወይም እውቀትን በመከታተል ነው።” በኤ ቲ ሮበርትሰን የተዘጋጀው ወርድ ፒክቸርዝ ኢን ዘ ኒው ቴስታመንት ይህን ቃል “ሳያቋርጥ ማወቅ ይኖርበታል” ተብሎ መተርጎም እንዳለበት ሐሳብ ያቀርባል።
ስለዚህ በጥንቱ ግሪክኛ ኢየሱስ በዮሐንስ 17:3 ላይ የተናገራቸው ቃላት እውነተኛውን አምላክና ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማወቅ የማያቋርጥ ጥረት ማድረግን ያመለክታሉ። ይህም በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ላይ ግልጽ ሆኖ ሠፍሯል። እኛም ይህን እውቀት የአምላክን ቃል በትጋት በማጥናትና ሕይወታችንንም ከደንቦቹ ጋር በታዛዥነት በማስማማት ልናገኝ እንችላለን። (ከሆሴዕ 4:1, 2፤ 8:2፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ከአምላክና ከልጁ ባሕርይ ጋር ራሳቸውን የሚያስተዋውቁና እነሱንም ለመምሰል የሚጥሩ ሰዎች ምን አይነት ሽልማት ያገኛሉ? የዘላለም ሕይወት ነዋ!