የአምላክ ቃል አፍቃሪዎች ትልቅ ግምት የሚሰጡት ክንውን
በ1998 የአምላክ ቃል አፍቃሪዎች ሁሉ ትልቅ ግምት የሚሰጡት አንድ ነገር ተከናውኗል። በዚያ ዓመት የቅዱሳን ጽሑፎች የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም 100 ሚልዮንኛ ቅጂ ታትሞ ወጣ። ከዚህም የተነሳ በዚህ ምዕተ ዓመት ከተዘጋጁትና እጅግ በስፋት ከተሠራጩት መጽሐፍ ቅዱሶች አንዱ ሊሆን በቅቷል!
በተለይ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ በወጣበት ወቅት ከተሰነዘረበት ኃይለኛ ትችት አንጻር ሲታይ ይህ ቀላል ክንውን አይደለም። ደግሞም የተሰነዘረበትን ትችት መቋቋም ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ በሚልዮን ወደሚቆጠሩ ሰዎች ቤትና ልብ በመዝለቅ ረገድ ተሳክቶለታል! የዚህ ድንቅ ትርጉም መሠረት ምንድን ነው? እንዲተረጎም ያደረገው ማን ነው? አንተስ ይህን ትርጉም በማንበብ ልትጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?
አዲስ ትርጉም ለምን አስፈለገ?
የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ወኪል የሆነው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ከአንድ መቶ ዓመት በላይ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያሰራጭ ቆይቷል። ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች ሌላ የአምላክ ቃል ትርጉም ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ የታያቸው ለምንድን ነው? በሶኬዬ ኩምቦ እና በዎልተር ስፔክት የተዘጋጀው ሶ ሜኒ ቨርሽንስ? የተባለው መጽሐፍ እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “የመጨረሻ ነው ሊባል የሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀት እድገትና ከቋንቋ ለውጥ ጋር እኩል መራመድ አለበት።”
መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የተጻፈባቸውን ማለትም ዕብራይስጥ፣ ግሪክኛና አረማይክ ቋንቋዎችን በመረዳት ረገድ በዚህ መቶ ዘመን ብዙ እድገት ታይቷል። በተጨማሪም በቀደሙት ትውልዶች የነበሩ ተርጓሚዎች ከተጠቀሙባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ የብራና ቅጂዎች ይበልጥ ጥንታዊና ትክክለኛ የሆኑ ቅጂዎች ተገኝተዋል። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ቃል ከምንጊዜውም በተሻለ መንገድ በትክክል መተርጎም ይቻላል! በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በዘመናዊ ቋንቋዎች ለመተርጎም የአዲሲቱ ዓለም መጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ኮሚቴ መቋቋሙ ተገቢ ነበር።
በ1950 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ታትሞ ወጣ። ርዕሱ ራሱ የተለመደውን መጽሐፍ ቅዱስን “ብሉይ” እና “አዲስ” ኪዳን ብሎ የመሰየም ፈሊጥ ያልተከተለ መሆኑ ትልቅ ድፍረት የሚጠይቅ ነበር። በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በተለያዩ ክፍሎች ታተመ። በ1961 ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ጥራዝ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ታትሞ ወጣ።
ለመሆኑ ይህን አስደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ ያከናወኑት እነማን ናቸው? የመስከረም 15, 1950 መጠበቂያ ግንብ እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “የትርጉም ኮሚቴው አባላት ማንነታቸው እንዳይገለጽ . . . የሚፈልጉ መሆናቸውን አመልክተዋል። በሕይወት እያሉም ሆነ ከሞቱ በኋላ ስማቸው በጽሑፉ ላይ እንዲጠቀስ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። የዚህ ትርጉም ሥራ ዓላማ ሕያውና እውነተኛ የሆነውን አምላክ ስም ከፍ ከፍ ማድረግ ነው።” አንዳንድ ተቺዎች ይህ ሥራ በአማተር ተርጓሚዎች የተሠራ ስለሆነ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም ሲሉ ቢከራከሩም እንዲህ ዓይነት ምክንያታዊ ያልሆነ አመለካከት የነበራቸው ሁሉም አልነበሩም። አለን ኤስ ደስኢ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የአንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ተርጓሚዎች ወይም አሳታሚዎች ማንነት ማወቃችን ትርጉሙ ጥሩ ነው ወይም መጥፎ ነው ብለን ለመወሰን ይረዳናልን? በቀጥታ እንደዚያ ወደሚል ውሳኔ እንድንደርስ ሊረዳን አይችልም። እያንዳንዱን ትርጉም በቅርብ ከመመርመር የተሻለ ሌላ አማራጭ የለም።”a
ለየት ያሉ ገጽታዎች
በሚልዮን የሚቆጠሩ አንባብያን ይህን በማድረግ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ሲያነቡት የሚስብ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ጥንቃቄ በትክክል የተተረጎመ መሆኑን ለመገንዘብ ችለዋል። ተርጓሚዎቹ በጊዜው የነበሩትን ከሁሉ የተሻሉ ጥንታዊ ቅጂዎች በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ ከተጻፈባቸው ከዕብራይስጥ፣ ከግሪክኛና ከአረማይክ ቋንቋዎች በቀጥታ ተርጉመዋል።b በተጨማሪም በተቻለ መጠን ጥንታዊዎቹን ቅጂዎች ቃል በቃል ለመተርጎም ከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገ ቢሆንም ሲያነቡት ለመረዳት የሚያስቸግር አይደለም። የጥንቶቹን ቅጂዎች በታማኝነት የተከተለ ትክክለኛ ትርጉም በመሆኑ አንዳንድ ምሁራን አወድሰውታል። ለምሳሌ ያህል ጥር 1963 የወጣው አንዶቨር ኒውተን ኳርተርሊ የተባለው መጽሔት “የአዲስ ኪዳን ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎም ረገድ የሚያጋጥሙ በርካታ ችግሮችን በዘዴ የመፍታት ብቃት ያላቸው ምሁራን በድርጅቱ ውስጥ መኖራቸውን ያመለክታል” ሲል ገልጿል።
እነዚህ ተርጓሚዎች መጽሐፍ ቅዱስን በመረዳት ረገድ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል። ቀደም ሲል በደንብ ግልጽ ያልነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በሚያስገርም ሁኔታ ግልጽ ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁአን ናቸው” (ኪንግ ጀምስ ቨርሽን) የሚለው በማቴዎስ 5:3 ላይ የሚገኘው ግራ የሚያጋባ ጥቅስ “ለሚያስፈልጋቸው መንፈሳዊ ነገር ንቁዎች የሆኑ ደስተኞች ናቸው” በሚል ይበልጥ ትርጉም በሚሰጥ መንገድ ተተርጉሟል። በተጨማሪም የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ቁልፍ ለሆኑ ቃላት የሰጠው ፍቺ ተለዋዋጭ ሳይሆን አንድ ዓይነት ነው። ለምሳሌ ያህል ፕስሂ የሚለው የግሪክኛ ቃል በሁሉም ቦታ “ነፍስ” ተብሎ ተተርጉሟል። ስለዚህ አንባብያን ከሃይማኖታዊ ፅንሰ ሐሳቦች በተለየ መልኩ ነፍስ ሟች መሆኗን በቀላሉ ሊገነዘቡ ይችላሉ።—ማቴዎስ 2:20፤ ማርቆስ 3:4፤ ሉቃስ 6:9፤ 17:33
የአምላክን ስም ወደ ቀድሞ ቦታው መመለስ
የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም አንዱ ለየት ያለ ገጽታ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ወደ ቀድሞ ቦታው መመለሱ ነው። በጥንቶቹ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ውስጥ መለኮታዊው ስም የሐወሐ ወይም ጀሐቨሐ ተብለው ሊተረጎሙ በሚችሉ ተነባቢ ፊደላት ተጽፎ ይገኛል። ብሉይ ኪዳን እየተባለ በሚጠራው ውስጥ ብቻ እንኳ ይህ ልዩ ስም 7,000 ያህል ጊዜ ሰፍሮ ይገኛል። (ዘጸአት 6:3 የ1879 እትም፤ መዝሙር 83:18 NW) ፈጣሪያችን አምላኪዎቹ ይህን ስም እንዲያውቁትና እንዲጠቀሙበት ይፈልግ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም!
ሆኖም ከአጉል እምነት የመነጨ ፍርሃት የአይሁድ ሕዝብ በዚህ መለኮታዊ ስም መጠቀምን እንዲተው አደረጋቸው። የኢየሱስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን የሚገለብጡ ሰዎች የአምላክን የግል ስም ኪሪዮስ (ጌታ) ወይም ቴኦስ (አምላክ) በሚሉት የግሪክኛ ቃላት መተካት ጀመሩ። የሚያሳዝነው ደግሞ ዘመናዊ ተርጓሚዎችም የአምላክን ስም ከአብዛኛው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማውጣት ይህን ለአምላክ ክብር የማይሰጥ እርምጃ የተከተሉ ሲሆን ጭራሽ አምላክ ስም ያለው መሆኑ እንኳ እንዲሰወር አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል በዮሐንስ 17:6 ላይ ኢየሱስ “ስምህን ገለጥሁላቸው” ብሏል። ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን ግን “አንተን አስታወቅሁ” ሲል ተርጉሞታል።
አንዳንድ ምሁራን የመለኮታዊው ስም ትክክለኛ አጠራሩ ስለማይታወቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲወጣ መደረጉ ተገቢ ነው ብለው ይከራከራሉ። ሆኖም እንደ ኤርምያስ፣ ኢሳይያስ እና ኢየሱስ ያሉት የተለመዱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ስሞች ከመጀመሪያው የዕብራይስጡ አጠራራቸው ጋር ብዙም በማይመሳሰል መንገድ ተተርጉመው ይገኛሉ። መለኮታዊውን ስም ይሖዋ ብሎ መተርጎም ተገቢ ከመሆኑም በላይ በብዙዎቹ ሰዎች ዘንድ የተለመደ አጠራር ስለሆነ በዚህ ስም መጠቀም ተገቢ አይደለም ብሎ መከራከር ምክንያታዊ አይሆንም።
የአዲሲቱ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አዘጋጅ ኮሚቴ በዕብራይስጥም ሆነ በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ይሖዋ የሚለውን ስም በመጠቀም ድፍረት የሚጠይቅ እርምጃ ወስዷል። ከእነሱ በፊት የነበሩት ለመካከለኛው አሜሪካ፣ ለፓስፊክና ለሩቅ ምሥራቅ ሕዝቦች መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎም ቀደምት የሆኑት ተርጓሚዎችም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደው ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ መንገድ የአምላክን ስም መጠቀም በትክክል ከመተርጎም አንፃር ብቻ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። የአምላክን ማንነት በትክክል ለመረዳት ስሙን የግድ ማወቅ ያስፈልጋል። (ዘጸአት 34:6, 7) የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በአምላክ ስም እንዲጠቀሙ አበረታትቷል!
እንግሊዝኛ ለማያነቡ ሰዎች ማዳረስ
ከ1963 እስከ 1989 ድረስ ባሉት ዓመታት የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ሙሉው ወይም በከፊል በአሥር ተጨማሪ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። ሆኖም የትርጉም ሥራው በጣም አድካሚ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች 20 ወይም ከዚያ የሚበልጡ ዓመታት ፈጅተዋል። ስለሆነም በ1989 በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የትርጉም አገልግሎት ዲፓርትመንት ተቋቋመ። ይህ ዲፓርትመንት በአስተዳደር አካል የጽሑፍ ኮሚቴ አመራር ሥር በመሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ እንዲፋጠን ማድረግ ጀመረ። የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ምርምርን ከኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀት ለትርጉም ሥራ የሚረዳ ዘዴ ተፈጠረ። ይህ ዘዴ የሚሠራው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አንድ አዲስ ቋንቋ እንዲተረጎም የጽሑፍ ኮሚቴ ፈቃድ ከሰጠ መላ ጊዜያቸውን ለዚህ ሥራ የሚያውሉ የተወሰኑ ክርስቲያኖችን በመመደብ የትርጉም ቡድን ያቋቁማል። በአንድ ግለሰብ ብቻ እንዲሠራ ከማድረግ ይልቅ በቡድን እንዲሠራ ማድረጉ የተሻለ የትርጉም ሥራ ያስገኛል። (ከምሳሌ 11:14 ጋር አወዳድር።) በአጠቃላይ ሲታይ እያንዳንዱ የቡድኑ አባል የማኅበሩን ጽሑፎች በመተርጎም ረገድ ልምድ ያዳበረ ነው። ከዚያም ቡድኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መሠረታዊ ሥርዓቶችንና ለዚህ ሥራ ሲባል የተዘጋጀውን የኮምፒዩተር ፕሮግራም በተመለከተ የተሟላ ሥልጠና ይሰጠዋል። ምንም እንኳ ኮምፒዩተሩ በቀጥታ የትርጉም ሥራውን የሚሠራ ባይሆንም ቡድኑ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችን እንዲያገኝና ቡድኑ የደረሰባቸውን ውሳኔዎች መዝግቦ እንዲያስቀምጥ ይረዳል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሁለት ደረጃዎች አሉት። በመጀመሪያው ደረጃ ላይ በእንግሊዝኛው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ውስጥ የሚገኙ ቃላትና አገላለጾች ዝርዝር ለተርጓሚዎቹ ይሰጣል። “አቶን፣” “አቶንመንት፣” እና “ፕሮፒሺየሺን” እንደሚሉት ያሉ ተቀራራቢ የእንግሊዝኛ ቃላት በአንድ ላይ ይመደባሉ። ይህም ተርጓሚዎቹ በጣም ተቀራራቢ ትርጉም ያላቸውን ቃላት በሚተረጉሙበት ጊዜ ንቁዎች እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። ከዚያም ተመጣጣኝ ቃላትን ያሰባስባሉ። ሆኖም አልፎ አልፎ አንድ ተርጓሚ አንድን ጥቅስ እንዴት አድርጎ እንደሚተረጉመው ሊቸገር ይችላል። የኮምፒዩተሩ ምርምር ማድረጊያ ዘዴ ተርጓሚው የግሪክኛና የዕብራይስጥ ቃላትን በተመለከተ ተጨማሪ ሐሳብ እንዲያገኝ ከማስቻሉም በላይ በመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ላይ ምርምር እንዲያደርግም ያስችለዋል።
ፕሮጀክቱ ወደ ሁለተኛ ደረጃው ሲሸጋገር የተመረጡት ቃላት በቀጥታ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል። ይህም የትርጉም ሥራው ትክክለኛና ወጥ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ይሁን እንጂ በኮምፒዩተር አማካኝነት “ቃላቱን እየፈለጉ መተካት” ብቻውን ጥቅሱን ትርጉም በሚሰጥ ሁኔታ ያስቀምጠዋል ማለት አይደለም። ቃላቱን ለንባብ በሚያመች ሁኔታ አቀነባብሮና አሰካክቶ መጻፍ ቀላል ሥራ አይደለም።
ይህ የትርጉም ሥራ ዘዴ በጣም ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል። አንድ ቡድን መላውን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተርጉሞ ሊጨርስ ችሏል። አንድ ሌላ ቡድን ግን ያለ ኮምፒዩተር እርዳታ በሌላ ተዛማጅ ቋንቋ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለመተርጎም 16 ዓመት ፈጅቶበታል። ከ1989 ጀምሮ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በ18 ተጨማሪ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። በአሁኑ ጊዜ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በሙሉ ወይም በከፊል በ34 ቋንቋዎች ይገኛል። ስለዚህ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ቢያንስ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን በቋንቋቸው ማግኘት ይችላሉ።
የዩናይትድ ባይብል ሶሳይቲስ ሪፖርት እንደሚያስረዳው ከሆነ 6,500 ከሚያክለው የዓለም ቋንቋ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ በከፊል የሚገኘው በ2,212 ቋንቋዎች ብቻ ነው።c ስለዚህ 100 የሚያክሉ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በ11 የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ደግሞ በ8 ቋንቋዎች ለማዘጋጀት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። የአምላክ ፈቃድ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና ወደ ትክክለኛው የእውነት እውቀት እንዲመጡ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:4 NW) የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በዚህ ረገድ ትልቅ ሚና መጫወቱን እንደሚቀጥል ምንም ጥርጥር የለውም።
ስለዚህ ይህ ትርጉም የታተመበት ቅጂ ብዛት 100 ሚልዮን መድረሱን ስንሰማ ደስ ይለናል፤ ወደፊትም በሚልዮን የሚቆጠሩ ተጨማሪ ቅጂዎች እንዲታተሙ ጸሎታችን ነው። ይህን ትርጉም በግልህ እንድትመረምረው እናበረታታሃለን። ለየት ያሉ በርካታ ገጽታዎች ታገኝበታለህ። ለማንበብ የማያስቸግር፣ በየገጹ አናት ላይ አጠር ያሉ መግለጫዎች (page headings) ያሉት ከመሆኑም በላይ የተለመዱ ጥቅሶችን ለማግኘት የሚያስችል ማውጫ (index)፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ቦታዎችን አንድ በአንድ የሚያመለክት ካርታ እና በጣም ግሩም የሆነ ተጨማሪ መግለጫ (appendix) አለው። ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላክ ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልእክት በቋንቋህ በትክክል ስለሚያስቀምጥ ይህን መጽሐፍ ቅዱስ በትምክህት ማንበብ ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ኒው አሜሪካን ስታንዳርድ ባይብል የተባለው በ1971 የታተመው የማመሳከሪያ ጽሑፍ በሽፋኑ ላይ ባሰፈረው አስተያየት “በአምላክ ቃል ማንም ሊወደስ አይገባም የሚል እምነት ስላለን ለምስጋናም ሆነ ለሌላ ምክንያት የማንንም ምሁር ስም አልጠቀስንም” ሲል መግለጹ ትኩረት የሚስብ ነው።
b እንደ መሠረታዊ የግሪክኛ ጥንታዊ ቅጂ ሆኖ ያገለገለው በዌስትኮት እና በሆርት የተዘጋጀው ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ዚ ኦሪጂናል ግሪክ ሲሆን ለዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች እንደ መሠረታዊ ቅጂ ሆኖ ያገለገለው ደግሞ በአር ኪትልስ የተዘጋጀው ቢብሊያ ሄብሬይካ ነው።
c አብዛኛው ሰው ሁለት ቋንቋ መናገር ስለሚችል መጽሐፍ ቅዱስ 90 ከመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ሊያነበው በሚችለው ቋንቋ በሙሉ ወይም በከፊል ተተርጉሟል ተብሎ ይታመናል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“የአዲስ ኪዳን ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎም ረገድ የሚያጋጥሙ በርካታ ችግሮችን በዘዴ የመፍታት ብቃት ያላቸው ምሁራን በድርጅቱ ውስጥ መኖራቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ነው።”—አንዶቨር ኒውተን ኳርተርሊ ጥር 1963
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀት እድገትና ከቋንቋ ለውጥ ጋር እኩል መራመድ አለበት”
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የምሁራንን አድናቆት አትርፏል
የግሪክኛውን “አዲስ ኪዳን” ወደ አን አሜሪካን ትራንስሌሽን የተረጎሙት ኢድገር ጄ ጉድስፒድ የአዲሲቱ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉምን አስመልክተው ታኅሣሥ 8, 1950 በጻፉት ደብዳቤ እንዲህ ብለው ነበር:- “የእናንተ ሰዎች የሚሠሩት ሥራና የሥራው ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያስደስተኛል። እንዲሁም ለዛ ያለው፣ ያልተድበሰበሰውና ግልጽ የሆነው ትርጉማችሁ በጣም አርክቶኛል። ብዙ ቁምነገር ግልጽ እንዲሆን የሚያደርግ ነው ብዬ ለመናገር እችላለሁ።”
የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቋንቋ ምሁር የሆኑት አሌክሳንደር ቶምሰን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ይህ ትርጉም ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው ምሁራን የሥራ ውጤት መሆኑ ግልጽ ነው፤ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሊገልጽ የሚችለውን ያክል በትክክል የጥንታዊውን የግሪክኛ ቅጂ ስሜት እንዲያንጸባርቅ ለማድረግ ሞክረዋል።”—ዘ ዲፈረንሺየተር ሚያዝያ 1952 ገጽ 52-7
በእስራኤል ዕብራዊ ምሁር ፕሮፌሰር ቤንጃሚን ከዳር በ1989 እንደሚከተለው ብለው ነበር:- “ከዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስና ትርጉም ጋር በተያያዘ በማደርገው የቋንቋ ምርምር አብዛኛውን ጊዜ የማመሳክረው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም እየተባለ ከሚጠራው የእንግሊዝኛ ትርጉም ነው። ይህንንም ማድረጌ ይህ ትርጉም ጥንታዊውን ቅጂ በተቻለ መጠን በትክክል ለመረዳትና ለማስቀመጥ ልባዊ ጥረት የተደረገበት ሥራ መሆኑን በተደጋጋሚ ለማረጋገጥ አስችሎኛል።”