የሚያዳምጠን ሰው እንፈልጋለን
ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ከሕይወት ደስታና እርካታ ለማግኘት እንጥራለን። ይሁንና የግል ችግሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ችግራችንን የምናዋየው ሰው ማግኘት ምን ያህል እፎይ የሚያሰኝና የሚያጽናና ነው!
ዶክተር ጆርጅ ኤስ እስቴቨንሰን እንዲህ ይላሉ፦ “ችግራችንን ማዋየት ጭንቀታችንን ያቃልልልናል፣ ያስጨነቀን ነገር ይበልጥ ግልጽ ሆኖ እንዲታየን በማድረግ አብዛኛውን ጊዜም ምን ማድረግ እንደምንችል መፍትሔው እንዲታየን ይረዳናል።” ዶክተር ሮዝ ሂልፈርዲን ደግም “ሁላችንም ችግራችንን ማካፈል ያስፈልገናል። ጭንቀታችንን ማካፈል አለብን። ሊያዳምጠን ፈቃደኛ የሆነና ችግራችንን ሊረዳልን የሚችል ሰው በዓለም ላይ እንዳለ እንዲሰማን ያስፈልጋል።”
በእርግጥ ይህን ፍላጎታችንን ሙሉ በሙሉ ሊያሟላልን የሚችል ሰው አይኖርም። ምስጢረኞቻችን የሆኑ ሰዎች በጊዜና በሌሎችም ምክንያቶች የተነሣ በጣም በምንፈልጋቸው ጊዜ ላይገኙ ይችላሉ። በተጨማሪም አንዳንድ ነገሮችን ለቅርብ ወዳጆቻችንም እንኳን ለማዋየት ላንፈልግ እንችላለን።
ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስቲያኖች ምንጊዜም ክፍት ሆኖ የሚጠብቃቸው የጸሎት በር ስላላቸው ሰሚ ጆሮ ሊያጡ አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስ ስሙ ይሖዋ ወደሆነው ፈጣሪ አምላካችን እንድንጸልይ በተደጋጋሚ ያበረታታናል። በኢየሱስ ስምና ከአምላክ ፈቃድ ጋር ተስማምተን ልባዊ ጸሎት እንድናቀርብ ታዝዘናል። የግልና ተራ ስለሆኑ ጉዳዮችም እንኳን መጸለይ ይቻላል። በፊልጵስዩስ 4:6 ላይ “በነገር ሁሉ . . . በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ” ተብለናል። ጸሎት ምንኛ አስደናቂ ስጦታ ነው! የጽንፈ ዓለሙ ልዑል ገዥ የሆነው አምላክ ትሑትና ዝቅተኛ የሆኑ አገልጋዮቹ ወደ እርሱ ለመቅረብ በፈለጉበት ጊዜ ሁሉ ሊቀበላቸውና ጸሎታቸውን ሊያዳምጥ ዝግጁ ነው።—መዝሙር 83:18፤ ማቴዎስ 6:9-15፤ ዮሐንስ 14:13, 14፤ 1 ዮሐንስ 5:14
ሆኖም አምላክ በእርግጥ ጸሎት ይሰማልን? አንዳንድ ሰዎች ጸሎት የሚያስገኘው ውጤት በሰው ችሎታ ላይ የተመካ እንዳይሆን ይሰጋሉ። ‘አንድ ሰው ሲጸልይ ሐሳቡን አቀናብሮ በቃላት ለመግለጽ ይችላል። ይህን በማድረጉም ሰውየው ችግሩን በትክክል ለመተንተን ስለሚችል ተስማሚ መፍትሔ ለማፈላለግና መፍትሔውን ለማግኘት የሚረዳውን ማንኛውንም ነገር ነቅቶ ለመጠበቅ ይችላል። ችግሩ መፍትሔ በሚያገኝበት ጊዜ አምላክ መፍትሔ እንደሰጠው በማሰብ ያመሰግነው ይሆናል። ነገር ግን ተፈላጊውን ውጤት ያስገኘው የራሱ ብልኅነትና ጥረት ነው’ ብለው ያስባሉ።
በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ጸሎት ከዚያ ያለፈ ኃይል የለውም ብለው ያስባሉ። አንተስ የምታስበው እንዲህ ነውን? የጸሎት ኃይል ይህን ያህል ውስን ነውን? እርግጥ አንድ ሰው ከጸሎቱ ጋር ተስማምቶ የሚያደርገው የአእምሮና የአካል ጥረት የጸሎቱን መልስ በማግኘት ረገድ የማይናቅ ድርሻ ይኖረዋል። ይሁን እንጂ አምላክ በጉዳዩ ላይ ያለው ድርሻስ ምንድን ነው? አምላክ የምታቀርበውን ጸሎት ይሰማሃልን? በጸሎትህ ለምትጠይቀው ነገር ክብደት በመስጠትና መልሱንም በመለገስ ጸሎትህን ከቁም ነገር ይቆጥረዋልን?
የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ትልቅ ትርጉም አለው። ምክንያቱም አምላክ ለጸሎታችን ትኩረት የማይሰጥ ከሆነ ጸሎት የሥነ ልቦና ጥቅም ከመስጠት የበለጠ የሚያደርግልን ነገር የለውም ማለት ነው። በሌላ በኩል ግን አምላክ እያንዳንዱን ጸሎት የሚቀበልና በስሜት የሚያዳምጥ ከሆነ ለእንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት ምን ያህል አመስጋኞች መሆን ይኖርብናል! ይህም በየዕለቱ በዚህ ዝግጅት እንድንጠቀም ሊገፋፋን ይገባል።
ስለዚህ ይህ ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ ውይይት ስለሚደረግበት ማንበብህን እንድትቀጥል እንጋብዝሃለን።