በዓለም ከሚገኙት ታላላቅ የባሕር ወደቦች በአንዱ ውስጥ ትዕግሥት የሚጠይቅ የስብከት ሥራ ማከናወን
ሮተርዳም ከአውሮፓ ወንዞች በሙሉ ብዙ መርከቦች የሚመላለሱባት የራይን ወንዝ ከሰሜን ባሕር ጋር በሚገናኝበት ቦታ ላይ የሚገኝ፤ በዓለም ውስጥ በግዙፍነታቸው ከሚታወቁት የባሕር ወደቦች አንዱ ነው። የሮተርዳም ወደብ ከ800 በላይ ከሚሆኑ በዓለም የሚገኙ የባሕር ወደቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ሲኖረው ከ500 በላይ የሚሆኑ የመርከብ ጉዞ ድርጅቶች በዚህ ወደብ ይጠቀማሉ። በእውነትም ዓለም አቀፍ የባሕር ወደብ ነው።
ይሁን እንጂ ይህ ከ650 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው የዳች የመርከቦች መተላለፊያ በመሆን ብቻ የተወሰነ አይደለም። የተለያዩ ሕዝቦችም የሚገናኙበት ሥፍራ ነው። ከሁሉም የዓለም ማዕዘናት መርከበኞች ቀንም ሆነ ሌሊት ወደዚህ ወደብ ይጐርፋሉ። ኔዘርላንድ ውስጥ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን የባሕር ሰዎች ችላ አላሏቸውም። በሌሎች አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ምሥክሮች እንደሚያደርጉት ሁሉ በዓለም ከሚነገሩት ዜናዎች በሙሉ ይበልጥ አስደሳች የሆነውንና በኔዘርላንድ የሚኖሩትም የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ምድራችንን ወደ ገነትነት እንደምትለውጥ የሚገልጸውን የምሥራች ለሁሉም ሕዝቦች ለመርከበኞችም ጭምር ለመስበክ የሚያስችላቸውን መንገድ ይፈልጋሉ።—ዳንኤል 2:44፤ ሉቃስ 23:43፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:10
“አቅጣጫው የዞረ የሚሲዮናዊነት ሥራ”
ከጥቂት ዓመታት በፊት በኔዘርላንድ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ለስድስት የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች ወይም አቅኚዎች በሮተርዳም የባሕር ወደብ ላይ ከመርከብ ወደ መርከብ እየሄዱ እንዲያገለግሉ ጥያቄ አቀረበላቸው። አቅኚዎቹ ባገኙት አጋጣሚ በጣም ተደሰቱ። መረጃዎቹን ከወደቡ ባለሥልጣኖች ካሰባሰቡ በኋላ መርከቦቹ የሚቆሙባቸውን ሥፍራዎች በሚገባ አጠኑ። ብዙም ሳይቆይ ትዕግሥታቸውን የሚፈትን ሥራ እንደተሰጣቸው ተገነዘቡ።
በመርከቡ ላይ የሚደረገውን የስብከት ሥራ የሚያስተባብረው ማይናርድ “አቅጣጫው የዞረ የሚስዮናዊነት ሥራ ይመስላል” ብሎአል። ምን ማለቱ ነበር? “አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሚሲዮናዊ ወደሚሰብክላቸው ሰዎች ለመድረስ ረዥም ጉዞ ይጓዛል። በእኛ ረገድ ግን የምንሰብክላቸው ሰዎች ወደ እኛ ለመምጣት ረዥም ጉዞ ያደርጋሉ።” በተጨማሪም “የምንሰብክበት ክልል ከየትኛውም ቦታ የበለጠ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ሳይኖረው አይቀርም” ብሏል። በ1985 የወጣው የሮተርዳም ዩሮፖርት የዓመት መጽሐፍ በ1983 (አቅኚዎቹ ይህን ልዩ ሥራ በጀመሩበት ዓመት ማለት ነው) የሮተርዳም ወደብ ከ71 የተለያዩ አገሮች የመጡ 30,820 መርከቦችን እንዳስተናገዱ ገልጿል። በእርግጥም ዓለም አቀፍ ወደብ ነው!
ባሕረተኞቹ “የወደብ ሚስዮናውያን” ብለው የሚጠሩአቸው በወደቡ ላይ የሚያገለግሉ አቅኚዎችም ዓለም አቀፋዊነት ይታይባቸዋል። ጊርት፣ ፒተር እና ባለቤቱ ካሪን የዳች ዜጎች ናቸው። ዳንኤልና ሚናርይ ከኢንዶኖዥያ የመጡ ሲሆኑ ሰለሞን ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነው። ከአውሮፓ ከእስያና ከአፍሪካ የመጡ በመሆናቸው በመካከላቸው የሚገኙትን ስምንት የቋንቋ ድንበሮች መወጣት ነበረባቸው። ይሁን እንጂ ከሥራቸው የተሳካ ውጤት ለማግኘት መወጣት የሚኖርባቸው ሌሎች እንቅፋቶች ነበሩ።
“በብስክሌት የምትዘዋወረው ቤተክርስቲያን”
“ከዚህ በፊት መርከበኛ የነበረው የ32 ዓመት ዕድሜ ያለው ፒተር “በወደቡ ዳርቻ ተረማምዶ፣ መርከቡንና ወደቡን በሚያገናኘው መሸጋገሪያ ላይ ወጥቶ መርከቡ ውስጥ መግባት አይቻልም” ይላል። “በቅድሚያ የወደቡ የውስጠኛው ክፍል ወደሆነው የባሕር ዳርቻ ለመግባትና መርከቡ ላይ ለመውጣት የሚያስችል ፈቃድ ማግኘቱ ያስፈልጋል። ብዙ ውጣ ውረድ የጠየቀ ቢሆንም ፎቶግራፍና የመንግሥት ቴምብሮች ያሉባቸውን ስምንቱን ፈቃዶቻችንን ካገኘን በኋላ እንደ ልባችን ወዲያና ወዲህ ለመዘዋወር ዝግጁ ሆንን” በማለት ፒተር ያስታውሳል። የ36 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውንና መርከቦቹ የሚቆሙበትን የባሕር ዳርቻ ሦስት ቦታ በመክፈል በእያንዳንዱ ክፍል ላይ 2 አቅኚዎች ተመደቡ።
ይሁን እንጂ ከብዙ አገሮች የመጡትና የተለያየ ቋንቋ ከሚናገሩት መርከበኞች ጋር እንዴት መግባባት ይቻላል? አቅኚዎቹ በብስክሌቶቻቸው ላይ በ30 ቋንቋዎች የተተረጎሙ በቂ ጽሑፎችን ቢይዙም አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ጽሑፎች በቂ አይሆኑም። የሰላሳ ዓመት ወጣት የሆነው ሰለሞን ፈገግ ብሎ “በየትኛው ቋንቋ የተዘጋጀ ጽሑፍ እንደሚያስፈልግ በቅድሚያ ማወቅ አይቻልም” ይላል። “መርከበኞቹ ብዙ ጊዜ አያስፈልግም ብለን በተውነው ቋንቋ የተዘጋጀውን ጽሑፍ ይጠይቁናል። በተጨማሪም መርከባቸው ከሦስት ሰዓት በኋላ ወይንም ከዚህ ባነሰ ጊዜ እንደሚንቀሳቀሱ ይነግሩናል” መርከበኞቹን ላለማሳዘን ሲባል ከአቅኚዎቹ መካከል አንዱ የሚፈልጉትን መጽሐፍ ለማምጣት ወደቤቱ ይገሰግሳል። ይዞ ከተመለሰ በኋላ መጽሐፉን ለማግኘት ጉጉት ላደረባቸው ለእነዚያ መርከበኞች ያስረክባል። “የሦስት ሰዓት የብስክሌት ጉዞ ርቆ በሚገኝ የወደብ ክፍል በምናገለግልበት ጊዜ ይህን የመሰለ ችግር አጋጠመን። በዚህ ጊዜ ሌላ ዓይነት ዘዴ መፈለግ እንደሚኖርብን ተገነዘብን” ይላል ፒተር።
አንድ ቀን በወደቡ ዳርቻ አካባቢ የሚኖሩ ምሥክሮች ለአቅኚዎቹ ሁለት የመታጠቢያ ገንዳ የሚያህል ስፋት ያላቸው ሁለት የብስክሌት ተሳቢዎችን ሰጡአቸው። አቅኚዎቹ በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ ጽሑፎቻቸውን በተሳቢዎቹ ከሞሉ በኋላ ከብስክሌቶቻቸው ጋር አገናኝተው መርከቦቹ ወደሚቆሙበት የባሕር ዳርቻ ያመራሉ። ብዙም ሳይቆይ ተጐታቾቹ ለዓይን ተለመዱ እና “የመጠሪያ ካርዳችን ሆኑ” በማለት ከአቅኚዎች አንዱ ይናገራል። “የወደቡን በር የሚጠብቀው ዘበኛ መምጣታችንን ሲያይ በሩን እየከፈተ እጁን በማወዛወዝ ‘በብስክሌት የምትጐተተዋ ቤተክርስቲያን!’ በማለት ይጮኻል። በሌላ ጊዜ ደግሞ በር ጠባቂው “ተጎታቿ ቤተክርስቲያን” መምጣቷን ሲያይ በሩን እየከፈተ “ሁለት ፖላንዶችና አንድ ቻይናዊ!” በማለት ጮኾ ይናገራል። ይህን የመሳሰሉት ጠቃሚ መረጃዎች አቅኚዎቹ ተገቢውን ጽሑፍ በተገቢው ቋንቋ ይዘው እንዲሄዱ ይረዷቸው ነበር። ይሁን እንጂ የሚሄዱበትን ተስማሚ ሰዓት መምረጥ ይኖርባቸዋል። ለምን?
ወቅታዊ የሆነውን መልእክት በትክክለኛው ጊዜ ማቅረብ
አቅኚዎቹ ከመርከብ ሠራተኞች ጋር ሊነጋገሩ የሚችሉት ቡና በሚጠጡበት የዕረፍት ሰዓታቸው ወይም በምሳ ሰዓት ላይ ብቻ ነው። የወጥ ቤት ሠራተኛው ግን የተለያዩ የሥራ ሠዓት ስላለው እንደ አመቺነቱ ማነጋገር ሲቻል ካፒቴኑና ሌሎቹን መኰንኖች ቀኑን ሙሉ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። በተጨማሪም አቅኚዎቹ የእንግሊዝ መርከቦች የሚመሩት በእንግሊዝ የሰዓት አቆጣጠር እንደሆነ ተገንዝበዋል። (የእንግሊዝ ሰዓት አቆጣጠር ከዳች አቆጣጠር የአንድ ሰዓት ያህል ልዩነት አለው)። ስለዚህ እንግሊዛዊ ያልሆኑ መርከበኞች ሥራ በሚጀምሩበት ሰዓት የእንግሊዝ የመርከብ ሠራተኞች ደግሞ ወደ ምግብ አዳራሽ ይገባሉ። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሣ በባሕር ላይ የሚያገለግል አቅኚ ጥሩና አስተማማኝ ሰዓት ያስፈልገዋል።
ይሁንና መርከበኞቹ የእረፍት ሰዓታቸውን ለመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ለመጠቀም ፈቃደኞች ይሆናሉን? “አብዛኛውን ጊዜ የመንግሥቱን መልእክት ለማዳመጥ የሚያስችል ክፍት አእምሮ ያላቸው ናቸው” በማለት የ31 ዓመት ዕድሜ ያለው ጊርት ገልጿል። “ምናልባት ለዚህ ጥሩ ምክንያት የሆናቸው የሰብዓዊ መንግሥታትን ውድቀት በቅርብ ለማየት ስለቻሉ ሳይሆን አይቀርም።” ለምሳሌ ያህል አንዳንድ መርከበኞች ጊርትን እንዳጫወቱት በድርቅ ለተጐዱ ኢትዮጵያውያን ይውል ዘንድ ከመርከባቸው የተራገፈውን የጥራጥሬ ክምችት ከወራት በኋላ ሲመለሱ እዚያው ተቀምጦና በአይጦች ተበልቶ፣ በስብሶ እንደተመለከቱ ነግረውታል። ጊርት “ብዙ መርከበኞች በፖለቲካ ላይ እምነት ማጣታቸው የሚያስደንቅ አይደለም። ስለዚህ ለሰው ዘሮች በጠቅላላ አንድ መንግሥት የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ያስደስታቸዋል”ይላል።
አንድ ጀርመናዊ ካፒቴን “ከአሥር ዓመት በፊት ብታነጋግራቸው ኖሮ የመርከቡ ሠራተኞች መልእክቱን ለማዳመጥ ፈቃደኞች አይሆኑም ነበር። አሁን ግን እየተለወጠ ያለው የዓለም ሁኔታ የመጽሐፍ ቅዱስን ወቅታዊ መልእክት ለማዳመጥ ፍላጎታቸውን አነሳስቶታል” ብሎ እንደነገረው ፒተር ይናገራል። በአንድ የኮሪያ መርከብ ላይ በወጥ ቤትነት የሚሠራ ሰው ያጋጠመውን ሲገልጽ፦ ኢራንና ኢራቅ በሚዋጉበት ወቅት ይሠራባት የነበረችው ነዳጅ ጫኝ መርከብ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ እንዳለች በሮኬት ትመታና በእሳት ትያያዛለች። በዚህ ጊዜ ከሞት ከተረፍኩ አምላክን እፈልጋለሁ ብሎ ይሳላል። ምንም ሳይሆን ከአደጋው ይተርፍና አቅኚዎቹ ሮተርዳም ውስጥ አግኝተው ሲያነጋግሩት ያሏቸውን በኮሪያ ቋንቋ የታተመ መጻሕፍት በሙሉ እንዲያመጡለት ነገራቸው።
አብዛኞቹ መርከቦች በወደቡ ዳርቻ ለብዙ ቀናት ቆመው ይቆያሉ። ይህም ለአቅኚዎቹ ከሥራ ሰዓት በኋላ ባለው ጊዜ ሁለቴ፣ ሦስቴ ወይንም ከዚያ በላይ ተመላልሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ለማድረግ እንዲችሉ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል። መርከቧ የሞተር ብልሽት ካጋጠማት ደግሞ ሦስት ሣምንት ለሚያህል ጊዜ ወደቡ ላይ ለመቆየት ትገደዳለች። “ይህ ለመርከቡ ኩባንያ መጥፎ አጋጣሚ ሲሆን ለእኛ ሥራ ግን ጥሩ ነው” በማለት አንድ አቅኚ ፈገግ አለ። አቅኚዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ከማድረጋቸውም ሌላ “መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ትውልድ የሚጠቅም መጽሐፍ ነው።” የሚለውን የማኅበሩን የማይንቀሳቀስ ፊልም በመርከቡ ላይ በሚገኘው የመመገቢያ አዳራሽ ውስጥ ያሳያሉ። በተጨማሪም አንዳንድ መርከበኞች የይሖዋ ምሥክሮች በሮተርዳም ውስጥ በተለያዩ የውጭ አገር ቋንቋዎች በሚያደርጉአቸው ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። የመርከቧ ሞተር ተጠግኖ ካለቀ በኋላ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ይዘጋል፣ መርከቧ ከታሠረችበት ገመድ ትፈታለች፣ ከባሕሩ ወደብ ከዓይን ተሰውራ ትጓዛለች። ከአቅኚዎቹ አእምሮ ግን አትሠወርም።
የሚያጽናኑ የመርከበኞች ታሪኮች
የወደቡ አቅኚዎች የጐበኟቸው መርከቦች እንደገና መጥተው እንደሆነ ለማወቅ በጋዜጦችና በወደቡ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት የሕዝብ ኮምፒውተር አማካኝነት ይከታተላሉ። የጐበኙአቸው መርከቦች ተመልሰው ከመጡ አቅኚዎቹ መርከቦቹን ተገናኝተው የመጨረሻ ጉብኝት ካደረጉላቸው በኋላ ምን ነገሮች እንዳጋጠሟቸው ለመጠየቅ ይጓጓሉ። መርከበኞቹ የሚናገሩአቸው ታሪኮች በጣም የሚያጽናኑ ናቸው!
አንድ መርከበኛ መርከቧ ጉዞዋን ከጀመረች በኋላ “በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ” የሚሉትን አምስት መጽሐፍት አውጥቶ ለአምስት የሥራ ባልደረቦቹ ካደላቸው በኋላ ስድስቱም አንድ ላይ መርከቧ ላይ ሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አደረጉ። እንዲሁም ከዚሁ መጽሐፍ ላይ ስለቤተሰብ የሚናገረውን ምዕራፍ በቴፕ ቀድቶ በመመገቢያ አዳራሹ ውስጥ ለመርከቧ ሠራተኞች በሙሉ በካሴት ያሰማቸው ነበር። በሌላ መርከብ ላይ የሚሠራ ሌላ መርከበኛ በሮተርዳም አቅራቢያ በሚገኘው በአንትወርፕ ወደብ ላይ በነበረ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮችን የመንግሥት አዳራሽ ጐብኝቶ ነበር። ወደ መርከቧ ከተመለሰ በኋላ በጽሑፍ ሰሌዳ ላይ በትልቁ “የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ” ብሎ ጻፈበት። በኋላም የመመገቢያ አዳራሽ ውስጥ በማንጠልጠል እርሱ ራሱ በሚመራው የመጽሐፍ ቅዱስ ስብሰባ ላይ የመርከቧ ሠራተኞች እንዲገኙ ጋበዛቸው። ስብሰባው አልቆ ሰሌዳውን ከማውረዱ በፊት በሚቀጥለው ሳምንት ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የመርከቡን ሠራተኞች ጋበዘ። በተከታዩም ሣምንት ሰሌዳውም ሆነ የመርከቧ ሠራተኞች በስብሰባው ቦታ ተገኙ።
በተጨማሪም አቅኚዎቹ አንዳንድ መርከበኞች መጻሕፍቶቻቸውን በመደርደሪያ ላይ እንደማያስቀምጡ ተመልክተዋል። “የምዕራብ አፍሪካ የሬዲዮ ኦፕሬተር በሆነው በአይዛክ ክፍል ውስጥ መቀመጫ ለማግኘት በጣም ያስቸግራል። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር መጻሕፍቶች፣ መጽሔቶችና ኮንኮርዳንስ በየቦታው ተከፍተው ተቀምጠው ነበር” በማለት ሚይናርድ ይናገራል። በተጨማሪም አቅኚዎቹ ሲጐበኙት የሚጠይቃቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች አዘጋጅቶ ይጠባበቅ ነበር።
አንዳንድ መርከበኞች ግን አቅኚዎቹ እንደገና መጥተው እስኪጐበኟቸው ድረስ አይጠብቁም። አንድ ሌሊት ላይ የጊርት ስልክ እርሱ ከተኛ በኋላ አቃጨለ። “በዚህ ሰዓት የሚደውለው ማን ነው?” ብሎ እያጉረመረመ ስልኩን አነሣ።
“ሀሎ፣ እኔ ወዳጅህ ነኝ!” የሚል በደስታ የተሞላ ድምጽ ሰማ።
ጊርት ማን መሆኑን ለማወቅ ሞከረ።
“በመርከቡ ላይ የምሠራው ወዳጅህ ነኝ” በማለት እንደገና ገለጸለት።
“ታዲያ አሁን እኮ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ነው” በማለት ጊርት መለሰ።
“አዎን አውቃለሁ፣ ነገር ግን ልክ ሮተርዳም እንደደረስክ ደውልልኝ ብለህ አልነበረም እንዴ! አሁን መጥቻለሁ!” አለው።
ብዙም ሳይዘገይ ጊርት ወደዚህ ስለ አምላክ ቃል ለማወቅ ብርቱ ፍላጎት ያሳየውን ሰው ለመገናኘት ወጣ።
“እንጀራህን በውኃ ላይ ጣል”
መርከበኞቹ የተበረከተላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች እንደሚያደንቁ የሚገልጹ ደብዳቤዎችን ለአቅኚዎቹ ይጽፉላቸዋል። ከደብዳቤዎቹ አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው።
“በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የሚለውን መጽሐፍ ማንበብ ጀምሬአለሁ። . . . ከዚህ በፊት ያልገቡኝን በርካታ ነገሮች አሁን አውቄአለሁ። መርከባችን በቅርቡ ወደ ሮተርዳም እንደምትመለስ ተስፋ አደርጋለሁ”—አንጀሎ።
“መጽሐፉን በሚገባ አንብቤያለሁ። በደብዳቤ የምትመልሱልኝን ጥያቄዎች ልኬላችኋለሁ”—አልበርት።
“አሁን መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ማንበብ ጀምሬአለሁ። የእናንተ ወዳጅ በመሆኔ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነው።”—ኒኪ።
እነዚህን የመሳሰሉ የሚያስደስቱ ደብዳቤዎች አቅኚዎቹ በመክብብ 11:1 ላይ የሚገኘውን “እንጀራህን በውኃ ላይ ጣለው ከብዙ ቀንም በኋላ ታገኘዋለህና” የሚል የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል። በተለይ ደግሞ አንዳንዶቹ ከይሖዋ ጐን መቆማቸውን አቅኚዎቹ ሲሰሙ በጣም ይደሰታሉ።
ስታኒስለቭ የተባለ ፖላንዳዊ መርከበኛ ከማኅበሩ መጻሕፍት ባገኘው ዕውቀት በጣም ተደስቷል። ወዲያውኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን ሰበሰበና በባሕር ላይ ጉዞው አንድ በአንድ ማጥናት ጀመረ። “በሌላ ጊዜ ደብዳቤ ሲጽፍልን እንደተጠመቀ ነገረን” ይላል ማይናርድ።”
ፎልከርት የተባለ የመርከብ አዛዥ በመጀመሪያ የመንግሥቱን መልእክት የሰማው ሮተርዳም ውስጥ ነው። በየሁለት ወሩ ወደ ወደቡ ይመጣና ለሳምንት ያህል እዚያው ይሰነብታል። እዚያ በሚቆይባቸው ሰባት ቀናት በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስን በተከታታይ ያጠና ነበር። ለሌላ የሁለት ወር የባሕር ጉዞ ከመነሣቱ በፊት አቅኚዎቹ እርሱ በሚያርፍበት የባሕር ወደብ አካባቢ ያሉትን የመንግሥት አዳራሾች ዝርዝር ይሰጡታል። ፎልከርት በሚሄድበት የመንግሥት አዳራሽ ሁሉ በሚደረግለት የሞቀ አቀባበል ልቡ ይነካል። ብዙም ሳይዘገይ ይህ የመርከብ አዛዥ ተጠምቆ አሁን ይሖዋን በቅንዓት በማገልገል ላይ ይገኛል።
የእንግሊዝ የባሕር ኃይል መኮንን የሆነው ማይክ የተባለ መርከበኛ ደግሞ ከዚህ በፊት ከምሥክሮቹ ጋር ይገናኝና በባሕር ላይ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይጀምራል። አንድ ጊዜ ይሠራባት የነበረችው አነስተኛ የጦር መርከብ በሮተርዳም ወደብ ቆማ ሳለች የምትተጣጠፈውን ብስክሌቱን እየነዳ ወደ መንግሥት አዳራሽ መጣ። በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ባየው ፍቅርና መተባበር በጣም በመነካቱ ሥራውን ሊያቆም መወሰኑን ለጓደኞቹ ይነግራቸዋል። ጥሩ የጡረታ አበል ለመቀበል አራት ዓመት ብቻ የቀረው ቢሆንም በውሣኔው ጸናና ተጠመቀ።
“የማይክን፣ የስታኒስቭን፣ የፎልከርትንና የሌሎቹንም የይሖዋን የማገልገል ጉጉት ስንመለከት እነርሱን መሰል መርከበኞችን በወደቡ ለማግኘት እንገፋፋለን” ሲል ማይናርድ ይናገራል።
በዚህ ሥራ ልትካፈል ትችላለህን?
በዓለም ከሚገኙት ታላላቅ የባሕር ወደቦች በአንዱ ውስጥ ትዕግሥት የሚጠይቅ ሥራ ለአሥር ዓመታት ሲያከናውኑ የቆዩት “የወደብ ሚስዮናውያን” ሥራው አድካሚ ቢሆንም የሚያስደስት መሆኑን ስድስቱም በአንድ አሳብ ይስማማሉ። “ከእያንዳንዱ የስብከት ቀን በኋላ በብስክሌቶቻችን ወደቤት ስንመለስ ከመርከበኞቹ አንዳንዶቹ የእኛን ጉብኝት በናፍቆት ይጠባበቁ እንደነበረ ይሰማናል” በማለት ሚናርድ ይገልጻል።
አንተ በምትኖርበት አካባቢ ባለ የባሕር ወደብ ጉብኝት እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ መርከበኞች ይኖራሉን? በጉባኤህ ውስጥ ያሉት ሽማግሌዎች ዝግጅት አድርገው ከሆነ አንተም ብትሆን በዚህ ትዕግሥት በሚፈትነው ነገር ግን ጥሩ ውጤት በሚያስገኘው ሥራ ልትካፈል ትችላለህ።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የስብከቱ ሥራ በታገደባቸው አገሮች የምሥራቹን ማዳረስ
በቅርቡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ሥር ከታገደባቸው አገሮች የመጡ ከ2,500 የሚበልጡ መርከቦች በሮተርዳም የባሕር ወደብ አርፈዋል። በዚህ ምክንያት በወደቡ ላይ የሚያገለግሉት አቅኚዎች ወደነዚህ ክልሎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልዕክት ለማዳረስ ጥሩ አጋጣሚ እንደተፈጠረላቸው ተረዱ።
ከጐበኟቸው የእስያ መርከቦች የመጀመሪያ በሆነችው መርከብ ላይ የነበሯቸውን 23 መጽሐፎች በሙሉ አበረከቱ። ከመርከቡ ሠራተኞች መካከል አንዳንዶቹ መጻሕፍቶች ስላልደረሳቸው ተበሳጭተው ነበር። በሌላ የእስያ መርከብ ላይ የሚሠራ አንድ ወጣት ብልህ ነበር። መጽሐፉን ከአቅኚው ተቀበለና በወረቀት ጠቅልሎ ካሸገው በኋላ በላዩ ላይ አድራሻውን ፅፎ ለአቅኚው መለሰለት። አቅኚው ልጁ ለምን እንደዚህ እንዳደረገ ወዲያው ገባው። እነዚህን የመሳሰሉትን መጻሕፍት ይዞ መሄድ አደገኛ ስለሚሆንበት በዚያው ቀን በፖስታ ቤት በኩል ወደ ሩቅ ምስራቅ ላከለት።
ከአፍሪካ በመጣ መርከብ ላይ የሚሠራ አንድ መርከበኛ ደግሞ ወደ አገሩ ሲመለስ በአገሩ ለሚገኙ ምሥክሮች የሚሰጣቸውን የመጻሕፍት ስም ዝርዝር ይዞ መጣ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ መርከበኛ ወደ አገሩ ሲመለስ ሻንጣው በመፃሕፍት ይሞላ ነበር። ከሌላ የአፍሪካ አገር የመጣ መርከበኛ ደግሞ ከእርሱ ጋር የሚያጠናው አቅኚ የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው የሚለውን መጽሐፍ 3 ቅጂ ብቻ ሊያገኝለት ስለቻለ አዝኖ እጆቹን እያወራጨ ተስፋ በቆረጠ ስሜት “ይህ ብቻ ምን ያደርግልኛል? አገር ቤት ያሉት ወንድሞቼ የሚያስፈልጋቸው አንድ ሺህ ነው!” አለ። በኋላ ግን ወንድሞች ለጊዜው 20 መፃሕፍት ብቻ ቢወስድ ለራሱ ደህንነት እንደሚበጅ አግባቡት።
በአንድ ሌላ ወቅት ደግሞ አንዲት መርከብ ወደዚሁ የባሕር ወደብ ትመጣለች። መርከቧ የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታቸው ምክንያት ብቻ ተሰድደው ብዙዎች ሥራቸውንና ንብረታቸውን ካጡባት አገር መምጣቷን አቅኚዎቹ ሲረዱ እጅግ በጣም አዘኑ። መርከቧ ላይ በአስተናጋጅነት የሚሠራው ሰው የይሖዋ ምሥክር መሆኑን ሲያውቁ የመርከቧን ካፒቴን በመቅረብ የእርዳታ ዕቃዎች ይልኩ ዘንድ ፈቃደኝነቱን ጠየቁት። በጉዳዩ መስማማቱን ገለፀላቸው። ከጥቂት ቀናት በኋላ በመቶ ታላላቅ ጆንያዎች የተሞሉ ልብሶች፣ ጫማዎችና ሌሎች ዕቃዎች በዚያ አገር ለሚገኙ ምስክሮች ተላኩላቸው።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዲት ሴት ከመርከብ ወደ መርከብ እየሄዱ ስለ መስበክ የሰጠችው አስተያየት
“በመጀመሪያ ፒተር ጋር አብሮ ለመሥራት አመነታሁ” ትላለች ከአቅኚዎቹ መካከል ብቸኛ ሴት የሆነችው ካሪን። ምክንያቱን ስትገልጽ “ምክንያቱም መርከበኞች ፀባየ ሸካራና ሰካራሞች እንደሆኑ ወሬ እሰማ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ትሁቶች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። አብዛኛውን ጊዜ መርከበኞቹ እኔና ፒተር ባልና ሚስት መሆናችንን ሲያውቁ የሚስታቸውንና የልጆቻቸውን ፎቶግራፍ ያወጡና ስለ ቤተሰቦቻቸው ማውራት ይጀምራሉ። በዚህ ምክንያት የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው የሚለውን መጽሐፍ በብዛት ልናበረክት ችለናል”።
ባልና ሚስት ሆኖ መርከቦችን መጐብኘት የመርከብ ሠራተኞቹን ሚስቶችና እንዲሁም አልፎ አልፎ በመርከቡ ላይ ነርስ ሆነው የሚያገለግሉ ሴቶችን ለማየት ይቀላል። ካሪን እንደምትለው፦“ብዙውን ጊዜ አዲስ ሰው ሲያዩ ቶሎ አይቀርቡም ነገር ግን ከተቀራረብን በኋላ ብዙ ለመጫወትና ለማውራት ይፈልጋሉ” ብላለች።
የካሪንን ትዕግስት የፈተነባት ምን ነበር? “የገመድ መሰላሎች ናቸው፣ እነዚያን ዝልግልግ ነገሮች አልወዳቸውም” ስትል ትመልሳለች ነገር ግን ፍርሐቷን ተወጣችውን? “አዎን አንድ ጊዜ አንዱን የገመድ መሰላል ለመውጣት እያመነታሁ ሳለሁ ከፓራጓይ የመጡ መርከበኞች በአንድ ላይ በአምላክ እመኚ እንጂ ትወጪያቸዋለሽ ሲሉ ጮኹ። ከዚያ በኋላ ምንም አማራጭ ስለሌለኝ ወጣሁት” ስትል ካሪን እየሳቀች ትናገራለች። ባልዋም በአድናቆት “በአራት ዓመታት ውስጥ ብዙ የገመድ መሰላሎችን ከወጣች በኋላ ልክ እንደ መርከበኛ በቀላሉ መውጣት ችላለች” ይላል።
ካሪንና ባለቤቷ ፒተር በዩናይትድ እስቴትስ በሚገኘው የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤት 89ኛ ኰርስ ከተከታተሉ በኃላ መስከረም 28, 1990 ላይ አዲሱን ምድባቸው ወደሆነውና ትልቅ ወደብ ወዳለው አገር ወደ ኢኳዶር ሄደዋል። እዚያም ልክ አገራቸው እንዳሉ ሆኖ ይሰማቸዋል።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መርከበኛ ነህን?
መርከብህ በዓለም ከሚገኙት ትላልቅ የባሕር ወደቦች በአንደኛው በምትቆምበት ጊዜ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚደረግ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመገኘት ትፈልጋለህን? የምትፈልግ ከሆነ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን አድራሻ ተመልክተህ በሚያመችህ ጊዜ መሰብሰብ ትችላለህ።
Hamburg, Schellingstr. 7-9; Saturday, 4:00 p.m.; phone: 040-4208413
Hong Kong, 26 Leighton Road; Sunday, 9:00 a.m.; phone: 5774159
Marseilles, 5 Bis, rue Antoine Maille; Sunday, 10:00 a.m.; phone: 91 79 27 89
Naples, Castel Volturno (40 km north of Naples), Via Napoli, corner of Via Salerno, Parco Campania; Sunday, 2:45 p.m.; phone: 081/5097292
New York, 512 W. 20 Street; Sunday, 10:00 a.m.; phone: 212-627-2873
Rotterdam, Putsestraat 20; Sunday, 10:00 a.m.; phone: 010-41 65 653
Tokyo, 5-5-8 Mita, Minato-ku; Sunday, 4:00 p.m.; phone: 03-3453-0404
Vancouver, 1526 Robson Street; Sunday, 10:00 a.m.; phone: 604-689-9796