“በፍጻሜው ዘመን” ነቅታችሁ ኑሩ
“ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ ትጉ ጸልዩም።”—ማርቆስ 13:33
1. በዚህ የፍጻሜ ዘመን ስሜት የሚቀሰቅሱ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
በዚህ “የፍጻሜ ዘመን” ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ክርስቲያኖች ምን ማድረግ ይገባቸዋል? (ዳንኤል 12:4) ማድረግ ስለሚገባቸው ነገር ግራ ሊገባቸው አይችልም። ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን በመፈጸም ላይ የሚገኘውን የጥምር ምልክቶች ትንቢት ተናግሯል። ከ1914 ወዲህ ያለውን ዘመን ከሌሎቹ ለየት የሚያደርጉትን ብዙ ገጽታዎች ተንብዮአል። ኢየሱስ ‘የፍጻሜውን ዘመን’ አስመልክቶ ዳንኤል የተናገረውን ያውቅ ስለነበረ ደቀመዛሙርቱ ‘ነቅተው እንዲኖሩ’ በማሳሰብ የራሱን ታላቅ ትንቢት አጠቃሏል።—ሉቃስ 21:36
2. በመንፈሳዊ ነቅተን መኖር በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ነቅተን መኖር ያለብን ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይህ ዘመን ከሰው ልጆች የታሪክ ዘመናት ሁሉ የበለጠ አደገኛ ስለሆነ ነው። በዚህ ጊዜ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ መፍዘዛቸው ወይም ማሸለባቸው ውድቀት ያስከትላል። ግድየለሾች ብንሆን ወይም ደግሞ ልባችን በኑሮ ጭንቀት ቢከብድ አደጋ ያጋጥመናል። ኢየሱስ ክርስቶስ በሉቃስ 21:34, 35 ላይ “ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋል” በማለት አስጠንቅቆናል።
3, 4. (ሀ) ኢየሱስ የአምላክ የቁጣ ቀን በሰዎች ላይ በድንገት “እንደ ወጥመድ” ይደርስባቸዋል ሲል ምን ማለቱ ነበር? (ለ) ወጥመዱን የሚዘረጋው አምላክ ስላልሆነ ያ ቀን ባጠቃላይ ሰዎች ሳይጠብቁት የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?
3 ኢየሱስ የይሖዋ ቀን ‘እንደ ወጥመድ በድንገት እንደሚደርስ’ የተናገረው ጥሩ ምክንያት ስለነበረው ነው። ወጥመድ ብዙ ጊዜ ወፎችን ወይም እንስሳትን ሳይታሰብ አንቆ የሚይዝ አታላይ መሣሪያ ነው። በተጨማሪም ሲነካ ወይም ሲረገጥ ተስፈንጥሮ የሚይዝ ክፍል አለው። ይህ ክፍል ሲነካ ወጥመዱ ይዘጋል፣ ከዚያ በኋላ የተያዘው ወፍ ወይም እንስሳ ሊያመልጥ አይችልም። ይህ ሁሉ የሚፈጸመው ከመቅጽበት ነው። በተመሳሳይም በመንፈሳዊ ያንቀላፉና የቀዘቀዙ ሰዎች በአምላክ የቁጣ ቀን የሚያዙት ይህን በመሰለ ድንገተኛ ሁኔታ እንደሆነ ኢየሱስ ተናግሯል።—ምሳሌ 11:4
4 ወጥመዱን በሰው ፊት ያስቀመጠው ይሖዋ አምላክ ነውን? አይደለም፣ እሱ ሰዎችን በድንገት ይዞ ለማጥፋት ሲል የሚዘናጉበትን ጊዜ አድፍጦ የሚጠብቅ አምላክ አይደለም። ነገር ግን ሰዎች በአጠቃላይ ለአምላክ መንግሥት ቀዳሚ ትኩረት ስለማይሰጡ ያ ቀን በድንገት ይደርስባቸዋል። በዙሪያቸው የሚፈጸሙት ነገሮች ያላቸውን ትርጉም ችላ በማለት የየራሳቸውን የኑሮ ጉዳዮች ያሳድዳሉ። ሆኖም የአምላክ ፕሮግራም በዚህ አይለወጥም። እርሱ ለሰው ሁሉ እንደ ሥራው የሚከፍልበት የራሱ ጊዜ አለው። ቢሆንም ስለሚመጣው የፍርድ ቀን እንድናውቅ በማድረግ ምህረት አድርጎልናል።—ማርቆስ 13:10
5, 6. (ሀ) ሰብዓዊ ፍጥረታት ከመጪው ፍርድ እንዲያመልጡ ፈጣሪ ምን ፍቅራዊ ዝግጅት አድርጎላቸዋል? ይህስ ምን አጠቃላይ ውጤት ያስገኛል? (ለ) ነቅተን እንድንኖር የሚረዱንን ምን ነገሮች እንመለከታለን?
5 ስለዚህ ምሳሌያዊ የእግሩ መረገጫ በሆነችው ምድር ላይ ለሚኖሩት ሰብአዊ ፍጡሮቹ ደህንነት የሚያስበው ታላቁ ፈጣሪ ይህን የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ታላቅ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው። (ኢሳይያስ 66:1) የእግሮቹ ማረፊያ እንደሆነች በተነገረላት በዚች ምድር ላይ ለሚኖሩት የሰው ልጆች አጥብቆ ያስብላቸዋል። በዚህም ምክንያት በምድራዊ አምባሳደሮቹና ልዑካኑ አማካኝነት በፊታቸው ስለሚጠብቃቸው ልዩ ሁኔታ ያስጠነቅቃቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 5:20) ሆኖም ይህ ሁሉ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ይህ ጥፋት የሚደርሰው በወጥመድ እንደተያዙ ያህል በድንገት ሳይታሰብ ነው። ለምን? የሰው ልጆች ባጠቃላይ በመንፈሳዊ አንቀላፍተው ለጥ ብለው ስለተኙ ነው። (1 ተሰሎንቄ 5:6) ማስጠንቀቂያውን ሰምተው በመቀበል ከጥፋት ተርፈው ወደ አዲሱ ዓለም በሕይወት የሚያልፉት ጥቂቶች ብቻ ናቸው።—ማቴዎስ 7:13, 14
6 ታዲያ ከሚድኑት መካከል ለመቆጠር እንድንችል በዚህ የፍጻሜ ዘመን ነቅተን ለመኖር የምንችለው እንዴት ነው? የሚያስፈልገንን እርዳታ ይሖዋ አዘጋጅቶ አቅርቦልናል። ማድረግ የምንችላቸውን ሰባት ነገሮች እንመልከት።
ትኩረታችን ወደሌላ እንዳያዘነብል እንታገል
7. ኢየሱስ ትኩረት ወደ ሌላ መወሰድን በሚመለከት ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል?
7 ከሁሉ አስቀድሞ ትኩረታችን ወደሌላ እንዳያዘነብል መታገል ይኖርብናል። ኢየሱስ በማቴዎስ 24:42, 44 ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ያን ግን እወቁ፣ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ ቤቱም ሊቆፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።” የኢየሱስ አነጋገር እንደሚያመለክተው በዚህ አስጨናቂ ጊዜ ውስጥ ትኩረት የሚስቡ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። ትኩረታችን ወደ ሌላ ከተሳበ ደግሞ ውጤቱ ጥፋት ነው። በኖኅ ዘመን የሰዎችን ትኩረት የሚስቡ ብዙ ነገሮች ነበሩ። በዚህም ምክንያት ሐሳባቸው ተከፋፍሎባቸው የነበሩት ሰዎች የሚሆነውን ነገር ባለማስተዋላቸው የጥፋቱ ውሃ ጠራረጋቸው። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ “የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናል” ሲል አስጠንቅቋል።—ማቴዎስ 24:37-39
8, 9. (ሀ) ዕለታዊ ኑሮን ማሳደድ ትኩረታችንን ወደሌላ በመውሰድ አደጋ ሊያስከትልብን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ጳውሎስና ኢየሱስ ምን ማስጠንቀቂያዎችን ሰጥተውናል?
8 በተጨማሪም ኢየሱስ በሉቃስ 21:34, 35 ላይ የሚገኘውን ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ የተናገረው እንደ መብል፣ መጠጥና የኑሮ ችግሮችን ለመወጣት እንደመጣር ስለመሳሰሉት ተራ የሕይወት ገጽታዎች መሆኑን አስታውሱ። ሰዎች ሁሉ፣ የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም ጭምር የሚያደርጓቸው ነገሮች ነበሩ። (ከማርቆስ 6:31 ጋር አወዳድር) እነዚህ ነገሮች በራሳቸው ምንም ዓይነት መጥፎነት የላቸውም፤ ነገር ግን ከፈቀድንላቸው ትኩረታችንን ሊሰርቁበን፣ አብዛኛውን ጊዜያችንን ሊወስዱብን ይችላሉ። ይህም አደገኛ የሆነ መጥፎ መንፈሳዊ እንቅልፍ እንዲያሸልበን ሊያደርግ ይችላል።
9 ስለዚህ ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ የሆነውን መለኮታዊ ሞገስ ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት ቸል አንበል። በኑሮ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ከመጠላለፍ ይልቅ ለመኖር ያህል የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማግኘት የሚያስችለንን የተወሰነ ትኩረት ብቻ እንስጥ። (ፊልጵስዩስ 3:8) ለመንግሥቱ ጉዳዮች የምንሰጠውን ጊዜ ሊያጣብቡብን አይገባም። ሮሜ 14:17 እንደሚለው “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችም።” ኢየሱስ “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” ሲል የተናገረውን ቃል አስታውሱ። (ማቴዎስ 6:33) በተጨማሪም በሉቃስ 9:62 ላይ “ማንም እርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” በማለት ተናግሯል።
10. ፊት ለፊት ብቻ በመመልከት ዓይናችንን በግባችን ላይ ካላደረግን ምን አደጋ ሊያጋጥመን ይችላል?
10 በምሳሌያዊ አባባል ዕርፉን ጨብጠን ማረስ ከጀመርን በኋላ ቀጥ ብለን ለመሄድ እንፈልጋለን። ወደኋላ ዞር እያለ የሚመለከት አራሽ ቀጥ ያለ ፈር ሊያወጣ አይችልም። ሐሳቡ ስለተከፋፈለበት ከመስመሩ ይወጣል ወይም ማረሻውን የሚይዝበት ነገር ያጋጥመውና ይቆማል። ወደ ኋላዋ በመመልከትዋ ምክንያት የጀመረችውን የመዳን ጉዞ እንዳልጨረሰችው እንደ ሎጥ ሚስት መሆን የለብንም። ቀጥ ብለን ፊት ለፊት እየተመለከትን ዓይናችንን ግባችን ላይ መትከል ይኖርብናል። ይህንን ለማድረግ ከፈለግን ትኩረታችንን ወደ ሌላ የሚያዘነብሉ ነገሮችን መዋጋት ይኖርብናል።—ዘፍጥረት 19:17, 26፤ ሉቃስ 17:32
ከልብ እንጸልይ
11. ኢየሱስ ሐሳባችን እንዳይከፋፈልብን ካስጠነቀቀን በኋላ አጥብቆ ያሳሰበው ስለምን ነገር ነው?
11 ይሁን እንጂ ነቅተን ለመኖር ማድረግ የምንችላቸው ሌሎች ነገሮችም አሉ። በጣም አስፈላጊ የሆነው ሁለተኛው ነገር ከልብ መጸለይ ነው። ኢየሱስ ተራ የሆኑ የኑሮ ጉዳዮችን በማሳደድ ሐሳባችን እንዳይበታተን ካስጠነቀቀ በኋላ “እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁልጊዜ ትጉ” በማለት ምክር ሰጥቶናል።—ሉቃስ 21:36
12. የሚያስፈልገው ምን ዓይነት ጸሎት ነው? ምንስ ውጤት ያስገኛል?
12 ስለዚህ የምንኖርበት ሁኔታ አደገኛ ስለ መሆኑና ነቅተን መኖር አስፈላጊ ስለ መሆኑ አዘውትረን መጸለይ አለብን። ስለዚህ ልባዊ ልመናችንንና ጸሎታችንን ዘወትር ወደ አምላክ እናቅርብ። ጳውሎስ በሮሜ 12:12 ላይ “በጸሎት ጽኑ” ብሏል። በኤፌሶን 6:18 ላይም “በመንፈስ ቅዱስ እየተመራችሁ ዘወትር ጸልዩ። በዚህ ዓይነት ነቅታችሁ ኑሩ” የሚል እናነባለን። (የ1980 ትርጉም) ጸሎት በአጋጣሚ ብቻ እንደሚደረግና በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ እንደማያመጣ መናገሩ አልነበረም። ሕልውናችን ራሱ አደጋ ላይ ወድቋል። ስለዚህ መለኮታዊ እርዳታ እንዲሰጠን ከልብ መለመን ይኖርብናል። (ዕብራውያን 5:7) እንዲህ ካደረግን በይሖዋ ጎን ተሰልፈን ለመኖር እንችላለን። በዚህ ረገድ ‘ዘወትር ከመጸለይና ከመማለድ’ ይበልጥ የሚረዳን ነገር ሊኖር አይችልም። አዘውትረን ከልባችን የምንጸልይ ከሆነ ይሖዋ ይህ ዓለም ወዴት እየሄደ እንዳለ ነቅተን እንድንከታተል ያስችለናል። እንግዲያውስ በጸሎት መጽናት እንዴት አስፈላጊ ነው!
ከአምላክ ድርጅትና ከሥራዎቹ ጋር የሙጥኝ ብለን እንኑር
13. ነቅተን ለመኖር ከምን ጋር መተባበር ያስፈልገናል?
13 በዓለም ላይ ከሚመጣው ከዚህ ሁሉ ነገር ለማመለጥ እንፈልጋለን። በሰው ልጅ ፊት ተቀባይነት አግኝተን ለመቆም እንፈልጋለን። በዚህ ረገድ ማድረግ የምንችለው ሦስተኛ ነገር አለ፦ ከቲኦክራቲካዊው የይሖዋ ድርጅትና ከሥራዎቹ ጋር የሙጥኝ ብለን እንኑር። አለምንም ገደብና ማመንታት ከይሖዋ ድርጅት ጋር እየተባበርን መኖርና በእንቅስቃሴዎቹም መካፈል ያስፈልገናል። በዚህም መንገድ ነቅተን የምንጠባበቅ ክርስቲያኖች መሆናችንን እናሳያለን።
14, 15. (ሀ) ነቅተን እንድንኖር የሚረዳን በምን ሥራ መጠመድ ነው? (ለ) የስብከቱ ሥራ ማብቃቱን የሚወስነው ማን ነው? እኛስ ስለ ስብከቱ ሥራ እንዴት ሊሰማን ይገባል? (ሐ) ከታላቁ መከራ በኋላ የተከናወነውን የስብከት ሥራ መለስ ብለን ስናስብ ምን እናስተውላለን?
14 ከዚህ ጋር የሚዛመድና ነቅተን እንድንኖር ሊረዳን የሚችል አራተኛ ነገር አለ። ስለ መጪው የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ሰዎችን ከሚያስጠነቅቁት ሰዎች መካከል መሆን ይገባናል። “ይህ የመንግሥት ምሥራች” ሁሉን ቻይ አምላክ ባሰበው መጠንና ስፋት ከመሰበኩ በፊት ይህ አሮጌ ሥርዓት አይጠፋም። (ማቴዎስ 24:14) የስብከቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተከናውኗል ብለው የሚወስኑት የይሖዋ ምሥክሮች አይደሉም። ይህን የመወሰን ሥልጣን ያለው ይሖዋ ብቻ ነው። (ማርቆስ 13:32, 33) ስለዚህ የቻልነውን ያህል በትጋትና አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ የሰው ልጅ ሊያገኝ ከሚችለው መንግሥት ሁሉ የምትበልጠውን የአምላክን መንግሥት በመስበክ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። ‘ታላቁ መከራ’ የሚፈነዳው የመንግሥቱን ምሥራች በዓለም በሙሉ የመስበክ ሥራችንን በመፈጸም ላይ እያለን ነው። (ማቴዎስ 24:21) ከዚያ በኋላ በሚመጡት ዘመናት በሙሉ ከመከራው የዳኑት ሰዎች መለስ ብለው ሲመለከቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐሰተኛ ነቢይ እንዳልነበረ ከልብ ያረጋግጣሉ። (ራዕይ 19:11) የስብከቱ ሥራ በሥራው የተካፈሉት ሰዎች ከጠበቁት በጣም በበለጠ መጠን ይከናወናል።
15 በዚህ መሠረት ሥራው አምላክ በሚፈልገው መጠን እንደተሠራ በሚወስንበትና እንዲቆም በሚያዝበት ታሪካዊ ጊዜ ላይ በስብከቱ ሥራ እየተካፈሉ ያሉት ሰዎች ብዛት ከማንኛውም ጊዜ የበለጠ ሆኖ ይገኛል። በዚህ ታላቅ ሥራ ለመካፈል በመታደላችን ምስጋናችን ምን ያህል ታላቅ ነው! ሐዋርያው ጴጥሮስ ይሖዋ “ሰው ሁሉ ወደ ንሥሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዲጠፋ” እንደማይፈልግ ያረጋግጥልናል። (2 ጴጥሮስ 3:9) በዚህም ምክንያት ሁሉን ከሚችለው አምላክ የሚመጣው አንቀሳቃሽ ኃይል ወይም መንፈስ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ በኃይል እየሠራ ነው። የይሖዋ ምሥክሮችም በዚህ መንፈስ አንቀሳቃሽነት በሚካሄደው ሥራ መካፈላቸውን ሊገፉበት ይፈልጋሉ። ስለዚህ ከይሖዋ ድርጅት ጋር የሙጥኝ ብላችሁ ኑሩ። ይህ ድርጅት በሚያከናውነው የስብከት ሥራም በትጋት ተካፈሉ። ይህን ማድረጋችሁ ነቅታችሁ እንድትኖሩ ይረዳችኋል።
ራሳችንን እንመርምር
16. አሁን ስለምንገኝበት መንፈሳዊ ሁኔታ ራሳችንን መመርመር ያለብን ለምንድን ነው?
16 ነቅተን ለመኖር ከፈለግን ማድረግ የሚኖርብን አምስተኛ ነገር አለ። በግላችን በአሁኑ ጊዜ ያለንበትን አቋም መመርመር ይኖርብናል። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ ራሳችንን መመርመራችን በጣም አስፈላጊ ነው። የተሰለፍነው በማን ጎን እንደሆነ በማያወላውል ሁኔታ ማረጋገጥ ይኖርብናል። ጳውሎስ በገላትያ 6:4 ላይ “እያንዳንዱ የገዛ የራሱን ሥራ ይፈትን” ብሎአል። በ1 ተሰሎንቄ 5:6-8 በሚገኙት የጳውሎስ ቃላት መሠረት ራሳችሁን መርምሩ፦ “እንግዲያስ እንንቃ፣ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ። የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉና፣ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉና፣ እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን፣ የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እየለበስን በመጠን እንኑር።”
17. ራሳችንን በምንመረምርበት ጊዜ ራሳችንን ምን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብናል?
17 እኛስ እንዴት ነን? በቅዱሳን ጽሑፎች ብርሃን ስለራሳችን ያደረግነው ምርመራ የመዳንን ራስ ቁር ደፍተን ነቅተን እንደምንኖር ያሳያልን? ከአሮጌው ሥርዓት ፈጽሞ የተለየንና ምኞቶቹንም ለማስተናገድ የማንፈልግ ሰዎች ነንን? የአዲሱ ዓለም መንፈስ በእርግጥ አለንን? ይህ ሥርዓት ወዴት በመጓዝ ላይ እንዳለ ገብቶናልን? በዚህ አቋም የምንገኝ ከሆነ ያ ቀን እንደ ሌባ በድንገት አይመጣብንም።—1 ተሰሎንቄ 5:4
18. ራሳችንን ምን ተጨማሪ ጥያቄዎች መጠየቅ ያስፈልገናል? ይህስ ምን ውጤት ሊያስገኝልን ይገባል?
18 ስለራሳችን ያደረግነው ምርመራ የተንደላቀቀ፣ የተመቻቸ፣ የተዝናናና የሞቀ ኑሮ ለመመሥረት በመጣር ላይ እንዳለን ቢያመለክተንስ? መንፈሳዊ ዓይኖቻችን በእንቅልፍ ከብደውና ፈዝዘው ብናገኛቸውስ? አንድ ዓይነት ዓለማዊ ቅዠት እያሳደድን በሕልም ዓለም ውስጥ እንኖራለንን? ሁኔታችን እንዲህ ያለ ከሆነ አሁኑኑ እንንቃ!—1 ቆሮንቶስ 15:34
የተፈጸሙትን ትንቢቶች እናሰላስል
19. ተፈጽመው ያየናቸው አንዳንድ ትንቢቶች ምንድን ናቸው?
19 አሁን ደግሞ ነቅተን እንድንኖር ወደሚረዳን ስድስተኛ እርምጃ እንምጣ። እሱም በዚህ የፍጻሜ ዘመን የተፈጸሙትን ትንቢቶች ማሰላሰል ነው። የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት ካለቁበት ከ1914 ወዲህ 77 ዓመታት አልፈዋል። ያለፈውን ሦስት ሩብ መቶ ዘመን መለስ ብለን ስንመለከት ትንቢቶቹ በተከታታይ እንዴት እንደተፈጸሙ ለመመልከት እንችላለን፦ የእውነተኛውን አምልኮ ተመልሶ መቋቋም፣ የቅቡአን ቀሪዎችንና የባልንጀሮቻቸውን ወደ መንፈሳዊ ገነት መመለስ፣ የመንግሥቱ ምሥራች በዓለም አቀፍ ደረጃ በመሰበክ ላይ መሆኑንና የእጅግ ብዙ ሰዎችን መምጣት ተመልክተናል። (ኢሳይያስ 2:2, 3፤ ምዕራፍ 35 በሙሉ፣ ዘካርያስ 8:23፤ ማቴዎስ 24:14፤ ራዕይ 7:9) የይሖዋ ታላቅ ስምና ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱ ደምቆ ይታያል። ይሖዋ በዘመኑ ስላፋጠነውም ትንሹ ሺህ ጥቂቱም ብዙ ሕዝብ ሆኖአል። (ኢሳይያስ 60:22፤ ሕዝቅኤል 38:23) ሐዋርያው ዮሐንስ የተመለከታቸው ራዕዮችም ወደ ከፍተኛ መደምደሚያቸው ተቃርበዋል።
20. የይሖዋ ምሥክሮች ምን እምነት አላቸው? በእርግጥስ ምን ሆነው ተገኝተዋል?
20 የይሖዋ ምሥክሮች ከ1914 ወዲህ ያለውን የዓለም ሁኔታ ትርጉም በትክክል የተረዱ ስለመሆናቸው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እርግጠኞች ሆነዋል። እንዲህ ያለ እርግጠኛ እምነት ስላላቸውም በልዑሉ አምላክ እጅ ያሉ መሣሪያዎች መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በዚህ ታሪካዊ ወቅት መለኮታዊውን መልእክት ለሰዎች የማድረስ ኃላፊነት የተሰጣቸው እነርሱ ናቸው። (ሮሜ 10:15, 18) አዎ፣ ይሖዋ ስለ ፍጻሜው ዘመን የተናገረው ሁሉ በትክክል ተፈጽሞአል። (ኢሳይያስ 55:11) ይህም በምላሹ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የገባልን ቃል ሙሉ በሙሉ እስኪፈጸም ድረስ ወደፊት እንድንገፋ ሊያንቀሳቅሰን ይገባል።
መዳናችን ካመንንበት ጊዜ ይበልጥ አሁን እንደቀረበ እንወቅ
21. በመንፈሳዊ ነቅተን ለመኖር የሚረዳን ምን ሰባተኛ ነገር አለ?
21 በመጨረሻም ነቅተን እንድንኖር የሚረዳን ሰባተኛው ነገር ምን እንደሆነ እንመልከት። መዳናችን ካመንንበት ጊዜ ይበልጥ አሁን እንደቀረበ ሁልጊዜ አስታውሱ። ከሁሉ ይበልጥ የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበትና ስሙ የሚቀደስበት ጊዜ በጣም ቀርቦአል። ስለሆነም ንቁ ሆኖ መኖር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ከእንቅልፍ የምትነሱበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን ዕወቁ። ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና” ሲል ጽፎአል።—ሮሜ 13:11, 12
22. መዳናችን ቅርብ መሆኑ እንዴት ሊነካን ይገባል?
22 መዳናችን ይህን ያህል የቀረበ ስለሆነ መንቃት አለብን! የግል ወይም ዓለማዊ ጉዳዮች ይሖዋ በዚህ የፍጻሜ ዘመን ለሕዝቦቹ ለሚያደርጋቸው ነገሮች ያለንን ግንዛቤ እንዲያጨልምብን መፍቀድ የለብንም። (ዳንኤል 12:3) አምላክ በቃሉ ውስጥ ከተለመልን ግልጽ መንገድ እንዳንወጣ ከማንኛውም ጊዜ የበለጠ የአቋም ጽናት ያስፈልገናል። (ማቴዎስ 13:22) ይህ ዓለም በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ማስረጃዎቹ ግልጽ ያደርጉልናል። ስለዚህ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቦታውን ለአዲሱ የጽድቅ ዓለም እንዲለቅቅ ተጠራርጎ ይጠፋል።—2 ጴጥሮስ 3:13
23. ይሖዋ የሚረዳን በምን መንገድ ነው? ከምንስ የተባረከ ውጤት ጋር?
23 እንግዲያውስ በማንኛውም ዓይነት መንገድ ነቅተን እንኑር። በዘመናት ሂደት ውስጥ በየትኛው ነጥብ ላይ እንደምንኖር ከምንጊዜውም ይበልጥ ራሳችሁን አስገንዝቡ። ይሖዋ በዚህ ጉዳይ ፈጽሞ እንደማያንቀላፋ አስታውሱ። ከዚህ ይልቅ በዚህ የፍጻሜ ዘመን ነቅተን እንድንኖር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይረዳናል። ሌሊቱ ሊነጋ ነው። ቀኑ የሚጠባበት ሰዓት ተዳርሷል። ስለዚህ ነቅታችሁ ኑሩ! በቅርቡ የይሖዋ መሲሐዊት መንግሥት ይሖዋ ለምድር ያለውን ዓላማ የምትፈጽምበትን ከቀናት ሁሉ በላይ የተዋበ ቀን ልናይ ነው!—ራዕይ 21:4, 5
ምን ብላችሁ ትመልሳላችሁ?
◻ ኢየሱስ የአምላክ የቁጣ ቀን በሰዎች ላይ በድንገት “እንደ ወጥመድ” ይደርስባቸዋል ሲል ምን ማለቱ ነበር?
◻ ትኩረታችን ወደ ሌላ እንዳይወሰድ መታገል ያለብን ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
◻ ነቅተን ለመኖር የሚያስፈልገው ምን ዓይነት ጸሎት ነው?
◻ በጣም አስፈላጊ የሆነው ከማን ጋር መተባበር ነው?
◻ ስለ መንፈሳዊ ሁኔታችን ራሳችንን መመርመር ያለብን ለምንድን ነው?
◻ ነቅተን እንድንኖር በመርዳት ረገድ ትንቢት ምን ድርሻ አለው?