የጎአሂሮ ሕንዶች ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ ሰጡ
በአንድ ትልቅ ዛፍ ጥላ ሥር መሬት የሚጠርግ ረጅም ጥቁር ልብስ ለብሳ ተቀምጣ የነበረችው አሮጊት ሴት በባህሏ ፈጽሞ ከእኛ የተለየች ነበረች። የምትናገረውን ቋንቋም ሰምተነው የማናውቀው ነው። ሞቅ ባለ ስሜት “እንደገና ተመልሳችሁ ኑ” አለችን። በአጠገብዋ ተቀምጠው ወደ ነበሩት የራሷ ጐሳዎች የሆኑ 50 ሰዎች እያመለከተች “ሁላችንም ተመልሳችሁ እንድትመጡ እንፈልጋለን፣ በየሳምንቱ ኑ” በማለት ደግማ ተናገረች።
እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? ከዚህ በፊት አይተውን የማያውቁ ሰዎች ቢሆኑም ተመልሰን እንድንጠይቃቸው የፈለጉት ለምንድን ነው? ለሰሜን ምዕራብ ቬንዙዌላ ቅርብ በሆነችው በሰሜን ምሥራቅ ኮሎምቢያ በላ ጎአሂራ ምድረ ሰላጤ ከሚኖሩት ከጎአሂሮ ሕንዶች መካከል ተገኝተን ስላሳለፍነው ቀን እንድንነግራችሁ ፍቀዱልን።
በመጀመሪያ እይታችን ያስተዋልናቸው ነገሮች
ከቬንዙዌላ ዋና ከተማ ከካራካስ ተነስተን መጀመሪያ ያረፍነው በማራካይቦ ነበር። መኪናችንን እየነዳን ወደ ከተማው ስንጠጋ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ ረጃጅም ቀሚሶች የለበሱ ሶስት ወጣት ሴቶች በመንገድ ሲሄዱ አየን። ሰፋፊ ፊታቸው፣ ቡና ዓይነት የቆዳ ቀለማቸው እና ዞማና ጥቁር ቀለም ያለው ፀጉራቸው ከአብዛኛዎቹ ቬንዙዌላውያን የተለዩ መሆናቸውን ያመለክት ነበር። ቀላልና ግርማ ያለውን አረማመዳቸውን ስንመለከት ስለ ጎአሂሮ ሕንዶች ለማወቅ ያለን ጉጉት ተቀሰቀሰ።
ወደ ጎአሂሮ ምድረ ሰላጤ የምንሄድበት ማለዳ የጠራና ብሩሕ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በቬንዙዌላ በሚገኙት ሩቅ አካባቢዎች ለማድረስ በሚደረገው አገር አቀፍ ዘመቻ ለመካፈል የጠዋቷ ፀሐይ ማተኮስ ከመጀመሯ በፊት ሀምሳዎቻችንም አውቶቡስ ተሳፍረን ጉዞ ጀመርን። በኮሎምቢያ ጠረፍ ወደምትገኘው ወደ ፓራጉዋቾን አመራን።
የማራካይቦን ከተማ ከኋላችን ትተን በብዙ ከተሞችና መንደሮች መሃል አለፍን። በእነዚህ መንደሮችና ከተሞች ሁሉ የገበያ ቦታዎችና ነጠላ ጫማዎችና ማንታ የሚባሉት ረጃጅምና ደማቅ ቀለም ያላቸው ቀሚሶች የሚሸጡባቸው ዳሶች ነበሩ። እያንዳንዱ መንደር ንፁሕ የሆነ ማዕከላዊ አደባባይና ቤተክርስቲያን ስላለው በጣም ውብ ሆኖ ይታይ ነበር። ሁሉም ሰዎች የሕንድ መልክ ያላቸው ናቸው። ልዩ ሰዎች ሆነው ቢታዩንም የጥንቶቹ የቬንዙዌላ ዜጎች እነዚህ ሕንዶች መሆናቸውን መገንዘብ ነበረብን።
ቤቶችን ለማግኘት ያደረግነው ፍለጋ
በመጨረሻም ወዳሰብንበት ቦታ ደረስን። አውቶቡሳችን ወደ መንገዱ ጠርዝ ተጠጋና አጠር ባለ አጥር አጠገብ በአንድ ረዥም ዛፍ ጥላ ሥር ቆመ። ከአጥሩ ማዶ የመንደሩ ትምህርት ቤት ይገኛል። ቀኑ እሁድ ስለነበረ ትምህርት ቤቱ ዝግ ነበር። በሁለት ቡድን ከተከፈልን በኋላ በተለያየ አቅጣጫ ተሰማርተን ቤቶችን መፈለግ ጀመርን። ያገኘነውን ሰው ሁሉ በዚያው ቀን በዘጠኝ ሰዓት በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በጎአሂሮ ቋንቋ የሚሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር እንዲያዳምጡ መጋበዝ ነበረብን። የጎአሂሮ ሕንዳዊ የሆነችው ኤቬሊንዳ አብራን ትገኝ ነበር። የእርሷ ከእኛ ጋር መኖር በሰዎቹ ዘንድ ተቀባይነት እንድናገኝ ያስችለናል የሚል ተስፋ ነበረን። የእስፓንኛ ቋንቋ ለመናገር የምንችል ብንሆንም ስለ ጎአሂሮ ቋንቋ የምናውቀው ነገር አልነበረም። ከመንደሩ ከወጣን በኋላ ከአንዱ ቤት ወደሌላው ለመድረስ ብዙ ርቀት መጓዝ ነበረብን። ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች በታጠረው ቀጥ ያለ መንገድ መጓዝ ስንጀምር አሥር ዓመት ያህል የሚሆነው አንድ ትንሽ ልጅ ተከትሎን መምጣት ጀመረ። ኤቬሊንም ፈገግ ብላ የመጣንበትን ምክንያት በጎአሂሮ ቋንቋ አስረዳችው። የዚህ ልጅ ስም ኦማር ሲሆን በንግግሩ ላይ እንዲገኝ ከጋበዝነው በኋላ እየሮጠ ተመለሰ። ከዋናው መንገድ ከተገነጠልን በኋላ በዚህ ሰሞን በጣለው ዝናም ምክንያት የረጠበውን የእግር መንገድ ተከትለን ሄድን። እነዚህ መንገዶች የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች በቬንዙዌላ እና በኰሎምቢያ መካከል የሚተላለፉባቸው መንገዶች መሆናቸውን አወቅን። አካባቢው በእፅዋት መዓዛ ታውዶአል። አየሩ በጣም የሚወብቅና እርጥበት ያለው ቢሆንም የጋለውን ስሜታችንን ግን አላረጠበውም። ያም ሆነ ይህ ጥቅጥቅ ባለው ቁጥቋጦ መካከል ያሳለፍነው መንገድ ሠፊ ወደሆነ ገላጣ ሜዳ ሲያደርሰን ድካማችን ሁሉ ተረሳን። የጎአሂሮዎች የመኖሪያ አካባቢ ነበር።
ከጎአሂሮዎች ጋር ፊት ለፊት መገናኘት
የሚያማምሩ ነጭ፣ ጥቁር እና ቀላ ያለ ምልክት ያለባቸው አሥራ ሁለት የሚያክሉ ፍየሎች ከጥላው ሥር ተኝተው ያመነዥካሉ። አንዲት ሴት በሁለት ዛፎች መካከል በተወጠረ የመረብ አልጋ ላይ በጀርባዋ ተኝታ ልጅዋን ታጠባለች። በአጠገቧ ሁለት ሕፃናት ይጫወታሉ። ሴትዮዋ በሽቦና በጭራሮ በታጠረ ግቢ ውስጥ ካለው በቀርከሀና በጭቃ የተሰራ የሣር ክዳን ቤታ ገና መውጣቷ ነበር። በአካባቢው አንዳንድ ጣሪያ የሌላቸው ጎጆዎች ነበሩ። አንደኛው ጎጆ የማብሰያ ቦታ መሆኑ በግልጽ ይታወቃል። ጀበና በሚመስሉ ትላልቅ ድስቶች መካከል እሳት ይነድዳል። በአጠገቡም እንዲደርቁ ተወጥረው የተሰቀሉ የፍየል ቆዳዎች አሉ።
በበሩ አጠገብ ቆሞ የነበረው ሰው ወደ እነርሱ መቅረባችንን ሲመለከት ወደ ውስጥ ሮጦ ሄደና ሁለት በርጩማዎች አምጥቶ ሴትዮዋ ከተኛችበት ቦታ አጠገብ አስቀመጠልን። ኤቬሊንዳ ለሰውየው እና ለሴትዮዋ በቋንቋቸው ሰላምታ አቀረበችላቸውና በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ሥዕላዊ ብሮሹር በመጠቀም ወደ ፊት ስለሚመጣው ቅዱስ ጽሑፋዊ ተስፋ አስረዳቻቸው። በአካባቢው ያለውን ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ ስንመለከት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስላሉት አስጊ ሁኔታዎች ወይም በከተማዎች ውስጥ እየጨመረ ስላለው ድህነትና ሕገወጥነት መናገር ተገቢ እንደማይሆን ተገነዘብን። በቡድኑ ውስጥ የምትገኝ አንዲት እህት የጎአሂሮ ሕንዶች በተፈጥሮአቸው ቶሎ ብለው ሰው የሚቀርቡ ስላልሆኑ መጀመሪያ ላይ ሞቅ ያለ ስሜትና ከልብ የመነጨ አሳቢነት ማሳየት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ነገረችን። “ሁልጊዜ ስለ ቤተሰቡ ጤንነት፣ ስለ እርሻ፣ በቅርብ ጊዜ ዝናብ መዝነቡን እና ስለመሳሰሉት እንጠይቃለን። ይህም ስለ አምላክ መንግሥት ለመናገር መንገድ ይከፍትልናል። ይህ ሁሉ ስቃይና እነርሱ በተለይ የሚፈሩት ሰይጣን ጭምር በቅርቡ እንደሚወገዱ ከመጽሐፍ ቅዱስ እናሳያቸዋለን።”
ኤቬሊንዳ ስትናገር አድማጮቿ በንግግሯ መስማማታቸውን ይገልጹ ነበር። ወዲያው ሌላ ሴት ብዙ ልጆች አስከትላ ወደ እኛ መጣች። በጎአሂሮ ሕግ አንድ ወንድ ብዙ ሚስቶች ሊያገባ የሚችል መሆኑን እናውቅ ነበር። ታዲያ ይህችስ ሴት ሌላይቱ ሚስት ትሆን? ይህ ሁኔታ በማራካይቦ የምትገኘውን የ21 ዓመት የጎአሂሮ ቆንጆ ወጣት የሆነችውን ዬኒን አስታወሰን። አንድ ሀብታም የጎአሂሮ ወንድ ልጃቸውን ቢድሩለት ብዙ ጥሎሽ እንደሚከፍል ለቤተሰቦችዋ ነገራቸው። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑት ወላጆችዋ በሐሳብ ተከፋፈሉ። እናቷ በጋብቻው ቢስማሙም አባቷ ግን አልተስማሙም ነበር። ሊያገባት የፈለገው ሰው ቀደም ብሎ የዬኒን እህት አግብቶ ነበር።
ኤቬሊንዳ መልእክቷን ስትጨርስ ያዳምጥ ለነበረው ሰውዬ አንድ ብሮሹር ሰጠችው። ከእርሱ በኋላ ቆማ የነበረችው ሴትም ለእርስዋም እንዲሰጣት ጠየቀች። እኛም በደስታ ሰጠናት። በዚህ ጊዜ የቀሩት ጓደኞቻችን ትተውን ሄደው ነበር። እኛም በማናውቀው ገጠር ጠፍተን እንዳንቀር በማሰብ ቤተሰቡ ከሰዓት በኋላ ወደሚደረገው ስብሰባ እንዲመጣ ጋበዝንና መንገዳችንን ቀጠልን።
በቡድናችን ውስጥ ከነበሩት ምሥክሮች አንዱ ያጋጠመውን ሁኔታ ነገረን። አንድ ሰው በመረብ አልጋ ላይ ተኝቶ የወንድምን ንግግር በማዳመጥ ላይ ሳለ ሚስቱ ከተፈጨ በቆሎ የተሠራ ቺቻ የተባለ መጠጥ በሁለት ብርጭቆዎች ይዛ መጣች። ወንድምም በትህትና ተቀበለና ጠጣው። ጥቂት ቆይቶ የጎአሂሮ ጎሣ የሆነችው ጓደኛው ማጋልይ መጠጡ እንዴት እንደሚዘጋጅ ነገረችው። በጥርስ ታኝኮ ከሚደቅ በቆሎ የተዘጋጀ መሆኑን ነገረችው። የወንድም ፊት በድንጋጤ አመድ መምሰሉን ስታይ በሳቅ ፈነዳች።
ወንድማችን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት እቤቱ ለማድረስ ባደረገው ጥረት የተነካ አንድ ሌላ ሰው ከመረብ አልጋው ዘሎ ወረደና ሸሚዙን ለብሶ በዛፎች ተከልሎ ወደሚታየው መንደር ራሱ ይዞአቸው ሄደ።
ወደ ሌላ ቦታ ስናልፍ ከጓደኞቻችን አንዳንዶቹ ከትላልቆቹ የቤተሰብ አባሎች ጋር ሲነጋገሩ ራቁታቸውን የሆኑና ሆዳቸው የተነፋ ሕፃናት ተሰብስበው በአንድ ዛፍ ሥር በጸጥታ ቆመው አየን። እንዲህ የሆኑት ከተመጣጠነ ምግብ እጥረትና በጥገኛ ትላትሎች ምክንያት መሆኑን ተረዳን። ከነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ የቧንቧ ውሃና የኤሌክትሪክ መብራት አያገኙም። ማቀዝቀዣ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሊኖራቸው አይችልም ማለት ነው።
ከተጠበቀው በላይ ብዙ ሰዎች ተገኙ
የጠዋቱ ጊዜ ፈጥኖ አለፈ። ምሳችንን ለመብላት ወደ አውቶብሳችን መመለስ ስንጀምር ከሰዓት በኋላ የሚሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ለማዳመጥ ከተጋበዙት መካከል ስንቶቹ ይመጡ ይሆን ብለን አሰብን።
በ8:45 ላይ፣ የጎአሂሮ ወንድማችን በጎአሂሮ ቋንቋ ያዘጋጀውን የ45 ደቂቃ ንግግር የምናዳምጠው በአውቶብስ ውስጥ ያለነው ብቻ እንደምንሆን ተሰምቶን ነበር። ይሁን እንጂ፣ ነገሩ እንዳሰብነው አልሆነም። የፍርሃት ስሜት የሚታይባቸው ጥቂት ቤተሰቦች በመጀመሪያ ወደ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ መጡ። ሁላችንም ጥሩ አቀባበል ስናደርግላቸው ሳይገረሙ አይቀሩም። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሌሎች ብዙ ሰዎች መጡ። አንዳንዶች ከሩቅ ቦታ ተጉዘው የመጡ መሆናቸው ይታወቃል። በርከት ያሉ ፍየሎች የነበሩት ቤተሰብም መጥቶአል። በመረብ አልጋዋ ላይ ተጋድማ ያገኘናት ሴትም ጥቁሩን የክት ቀሚሷን ለብሳ ስናያት ሌላ ሴት መሰለችን። በመንገድ ያገኘነው ትንሹ ኦማር ሳይቀር ብቻውን መጥቷል። ሌሎች ተጨማሪ ሰዎች ስለመጡ እንደ አግዳሚ ወንበር አድርገን የተጠቀምንበት ከስሚንቶ የተሰራው የትምህርት ቤቱ ትልቅ ደረጃ በሰዎች ተሞላ። በዚህ ጊዜ የአውቶብሱ ሾፌር የአውቶብሱን ወንበሮች አውጥቶ ለመቀመጫነት እንድንጠቀምባቸው ሰጠን።
ኤድዋርዶ የሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር 55 የሚሆኑ የጎአሂሮ ሕንዶች አዳምጠዋል። ይሁን እንጂ ያዳመጡት በፍጹም ጸጥታ አልነበረም። ተናጋሪው በሚናገረው ሐሳብ መስማማታቸውንና መቀበላቸውን ለመግለጽ አንድ ዓይነት ድምጽ ያሰሙ ነበር። ወንድም ክፋት የሚጠፋበት ጊዜ መቅረቡን ሲናገር በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው አሮጊት ሴት ሁሉም እንዲሰሟት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “አዎ፣ ብዙ ክፋት አለ። አሁንም እዚህ ብዙ ክፉ ሰዎች ቁጭ ብለዋል። እንደሚያዳምጡም ተስፋ አደርጋለሁ” አለች። ወንድም ኤድዋርዶ ለተሰጠው ሐሳብ በዘዴ ምስጋና አቀረበና ንግግሩን ቀጠለ።
ንግግሩ እንዳለቀ ከመካከላችን አንዱ ፎቶግራፍ አነሳቸው። ፎቶግራፍ መነሳታቸው ጎአሂሮዎቹን አስደስቷቸው ነበር። ለሁለተኛ ጊዜ ፎቶግራፍ ሲያነሳ በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር ወደ ላይ ከፍ አድርገው ለመያዝ ጠየቁት። ከዚያም አንዳንዶቹ ቀስ በቀስ መሄድ ጀመሩ። ከተሰብሳቢዎቹ ግማሽ የሚሆኑት ግን ወደ አውቶቡስ እስክንገባ ድረስ ቆመው ይመለከቱን ነበር። ተመልሰን እንድንጠይቃቸው ቃል አስገቡን። አውቶቡሱ ከዓይናቸው እስኪሰወር ድረስ ቆመው እጃቸውን ያወዛውዙ ነበር።
ከእነርሱ ስንርቅ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለእነዚህ ሰዎች ማድረስ ትልቅ መብት መሆኑን ተገነዘብን። እነዚህ ሰዎች ይህን መልእክት ለመጀመሪያ ጊዜ መስማታቸው ነበር። በማራካይቦ የሚኖሩ ምሥክሮች ለሁለተኛ ጊዜ ስለሚያደርጉት ጉብኝት እቅድ ማውጣት ጀምረው ነበር። ይህ ታሪክ በዚህ ያበቃ ይሆን ወይስ ሌላ ተከታይ ምዕራፍ ይኖረው ይሆን?
የተሳካ ውጤት ያስገኙ ተከታታይ ጉብኝቶች
ከሁለት ሳምንት በኋላ ወንድሞች ተመልሰው ሄዱ። ብዛት ያላቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ተበረከቱ፣ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተመላልሶ መጠይቆች ተደረጉ፣ እንዲሁም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተጀመሩ። ለሁለተኛ ጊዜ በተደረገው ስብሰባ ከ79 በላይ የሚሆኑ ሕንዶች ተገኙ። ወንድሞች የክልል ስብሰባ ስለሚኖራቸው በሁለተኛው ሳምንት ሳይሆን በሶስተኛው ሳምንት እንደሚመለሱ ነገሯቸው። ሕንዶቹ ይህን ሲሰሙ ደነገጡ። ከእነርሱ መካከል አንዱ “እናንተ ከመምጣታችሁ በፊት ብንሞትስ?” አለ። የክልል ስብሰባ ምን እንደሆነ ጠየቁ። ጥሩ ነገር ሳይሆን አይቀርም ብለው በማሰብ በስብሰባው ላይ ለመገኘት እንደሚፈልጉ ተናገሩ። አስፈላጊው ዝግጅት ተደረገላቸውና ከእነርሱ መካከል 34 የሚያህሉት በማራካይቦ በተደረገው ስብሰባ ለመገኘት ቻሉ። በስፓኒሽ ቋንቋ የሚከናወነውን ፕሮግራም መረዳት እንዲችሉ የጎአሂሮ ቋንቋ የሚችሉ ወንድሞች ረዱአቸው።
የይሖዋ ፈቃድ “ሰዎች ሁሉ እውነቱን ወደማወቅ እንዲደርሱ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) በላ ጎአሂሮ ምድረ ሰላጤ የሚኖሩ እውነትን የተጠሙ ሕንዶች ጥሩ ምላሽ መስጠታቸው ምን ያህል አስደሳች ነው!
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሕይወታቸውን አበለጸገው
ኢሪስ እና ማርጋሪታ ሁለቱም በአሥራዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙ የጎአሂሮ ወጣቶች ናቸው። በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር ሲያዩ በጣም ተደስተው ነበር። ነገር ግን አንድ ችግር አለባቸው። ማንበብ አይችሉም። ጉብኝት የምታደርግላቸው ምሥክር ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ረዳቻቸው። ወዲያውም እነዚህ ልጃገረዶች የይሖዋን ስም መጻፍ እና በትክክል መናገር በመቻላቸው በጣም ተደስተው ነበረ።
እድገት እያደረጉ ሲሄዱ መጽሐፍ ቅዱስ ባለው ግሩም ተስፋ ተደነቁ። በተለይ ሁሉም የሰው ዘር በነፃነት የሚደሰት መሆኑን በሚናገረው ተስፋ ተነኩ። “ለእኛ በአሥራዎቹ የእድሜ ክልል ለምንገኝ ወጣቶች እዚህ ያለው ሕይወት በጣም አስከፊ ነው። ብዙውን ጊዜ ገና በልጅነት እድሜያችን እንዳራለን፣ የሴቶች መደፈርም የማያቋርጥ አደጋ ነው” ብለው አስረዱ።
ኢሪስ እና ማርጋሪታን በጣም ያስደሰታቸው ነገር በማራካይቦ በተደረገው የወረዳ ስብሰባ ላይ የደስታ ስሜት በፊታቸው ላይ ሲንፀባረቅ ይታይ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን የምታስጠናቸው ምሥክር ወደ ቤታቸው በምትመጣበት ቀን ሁል ጊዜ በበራቸው ላይ ቆመው በጉጉት ይጠብቋት ነበር። በሰፈራቸው የሚሰጠው የሕዝብ ንግግር አንድም ቀን አምልጦአቸው አያውቅም። እነዚህ ወጣት ልጃገረዶች ይሖዋንና ዓላማውን በማወቃቸው ሕይወታቸው በእርግጥ እንደ በለጸገ ይሰማቸዋል።