ዲዮቅላጥያን ክርስትናን ተቃወመ
የካቲት 23 ቀን 303 እዘአ በትንሽዋ እስያ በምትገኘው የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት አዲስ ዋና ከተማ በሆነችው በኒቆሜዲያ በተከበረው ተርሚነስ የተባለው የሮማ አምላክ በዓል ላይ ሰዎች የሐገር ፍቅር ስሜታቸውን ለመግለጽ እርስ በርሳቸው ይፎካከሩ ነበር። ቀላል ቁጥር ያልነበራቸው የክርስቲያኖች ማኅበረሰብ አባሎች ግን በዚህ በዓል ላይ አልተገኙም።
ንጉሠ ነገሥቱ ዲዮቅላጥያንና የበታቹ የሆነው ገሊሪየስ ቄሣር በቤተ መንግሥታቸው በሚገኝ ከፍተኛ ቦታ ላይ ሆነው በአካባቢው የሚገኘውን የክርስቲያኖች የመሰብሰቢያ ቦታ ተመለከቱ። ወታደሮችና የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች በተሰጣቸው ምልክት መሠረት የክርስቲያኖቹን ሕንጻ ሰብረው በመግባት ከዘረፉት በኋላ ያገኙአቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች በሙሉ አቃጠሉ። በመጨረሻም ቤቱን ፈጽመው አወደሙት።
በዲዮቅላጥያን ዘመነ መንግሥት ላይ ጥቁር ነጥብ የጣለው የስደት ዘመን የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር። የታሪክ ጸሐፊዎች ይህንን ጊዜ “በጣም አስከፊ የሆነ ታላቅ ስደት” እና “የክርስትናን ስም ለማጥፋት የተቃረበ የስደት ዘመን” ብለውታል። ለዚህ አስገራሚ ሁኔታ መከሰት ምክንያት የሆኑትን ሁኔታዎች ከመጀመሪያው አንስቶ መመርመር ጠቃሚ ዕውቀት ይሰጠናል።
የአረማውያን አምልኮና ክርስትና
ዲዮቅላጥያን የተወለደው አሁን ዩጎዝላቪያ ተብሎ በሚጠራው አገር በዳልማቲያ ነው። በሮማ ጦር ሠራዊት ውስጥ በሹመት እያደገ መጥቶ ትልቅ ሥልጣን ላይ ደረሰ። የንጉሠ ነገሥትነት ሹመት የተሰጠው በ284 እዘአ ሲሆን ከፍተኛ ዝና ያተረፈው ግዛቱ እኩል ሥልጣን ባላቸው አራት ገዢዎች እንዲተዳደር በማድረግ ከፍተኛ የፖለቲካ ለውጥ ባመጣ ጊዜ ነበር። ዲዮቅላጥያን የውትድርና ጓደኛው የነበረውን ማክሲሚያን የንጉሠ ነገሥት ግዛቱን ምዕራባዊ ክፍል እንዲያስተዳድር ሥልጣን በመስጠት ምክትል ንጉሠ ነገሥት አድርጎ ሾመው። ዲዮቅላጥያንም ሆነ ማክሲሚያን እያንዳንዳቸው ሥልጣናቸውን ለልጆቻቸው የማውረስ መብት የተሰጣቸው የበታች ቄሣሮች ነበሩአቸው። ኮንስታንቲየስ ክሎረስ ለማክሲሚያን የሚያገለግል ቄሣር ሲሆን የትሬሱ ገለሪየስ ደግሞ በዲዮቅላጥያን ሥር ሆኖ ያገለግል ነበር።
ቄሣር ገለሪየስም እንደ ዲዮቅላጥያን የአረማውያንን አማልክት በጋለ ስሜት የሚያመልክ ሰው ነበር። ገለሪየስ የንጉሠ ነገሥቱን ቦታ ለመውረስ ጽኑ ምኞት ስለነበረው ጦር ሠራዊቱ ይከዳ ይሆናል የሚል ፍርሐት እንዳለው ማስመሰል ጀመረ። ክርስቲያን ነን ይሉ የነበሩ ወታደሮች ከፍተኛ ሥልጣን እያገኙ መሄዳቸው አላስደሰተውም ነበር። በንጉሠ ነገሥቱ አመለካከት በአረማዊ አምልኮት ላይ ላለመገኘት መቁረጣቸው ስልጣኑን እንደመቃወም የሚቆጠር ነበር። ስለዚህ ገለሪየስ ክርስትናን ጨርሶ ለማጥፋት እርምጃ እንዲወስድ ዲዮቅላጥያንን አጥብቆ አሳሰበው። በመጨረሻም በ302/303 የክረምት ወራት ንጉሠ ነገሥቱ ለቄሣር ፀረ ክርስቲያናዊ አቋም በመንበርከክ እነዚህን ሰዎች ከጦሩም ሆነ ከቤተ መንግሥቱ ለማጥራት ተስማማ። ይሁን እንጂ ዲዮቅላጥያን ክርስቲያኖችን በሰማዕትነት መግደል ሌሎች በክርስቲያንነት አቋማቸው እንዲጠነክሩ ያደርጋቸዋል ብሎ ስለሰጋ ማንም ሰው እንዳይገደል ደንግጎ ነበር።
አሁንም ዲዮቅላጥያን ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል በተባለው በዚህ ዘዴ ስላልረካ የጦር አዛዦችንና ባለ ሥልጣኖችን እንዲሁም የጊታንያ ገዢና የፕላቶ ፍልስፍና ተከታይ የነበረውን ሂረክሊስን አማከረ። ይህ ጠንካራ የግሪካውያን ፍልስፍና ተከታይ የነበረ ሰው በሁሉም ክርስቲያኖች ላይ የጭካኔ እርምጃ መወሰዱን ይደግፍ ነበር። ዲዮቅላጥያን ለሮም ባህላዊ አማልክት የነበረው ድጋፍ ከክርስትና ጋር ወደ መጋጨት መራው። ውጤቱም ስቴፈን ዊሊያምስ ዲዮቅላጥያንና የሮም እንደገና ማገገም በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደጻፉት “በሮም አማልክትና በክርስቲያኖች አምላክ መካከል ወሰን የሌለው ጦርነት ሆነ።”
አራቱ አዋጆች
ዲዮቅላጥያን የስደት ዘመቻውን ለማስፈጸም አራት አዋጆች አወጣ። ኒቆሜዲያ በሚኖሩት ክርስቲያኖች ላይ ከደረሰው ጥቃት ማግስት የክርስቲያኖች የመሰብሰቢያ ቦታዎችና ንብረቶች እንዲደመሰሱና ቅዱሳን ጽሑፎቻቸው ተሰብስበው እንዲቃጠሉ ትእዛዝ አወጣ። የመንግሥት ሹመት የነበራቸው ክርስቲያኖች ከሹመታቸው እንዲወርዱ አዘዘ።
በንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት ውስጥ ሁለት የእሳት ቃጠሎዎች በተነሱ ጊዜ ቃጠሎውን ያስነሱት እዚያ ይሠሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ናቸው ተባለ። በዚህም ምክንያት ሁሉም ቀሳውስት፣ ካህናትና ዲያቆናት እንዲያዙና እንዲታሰሩ የሚያዝ ሁለተኛ አዋጅ አወጣ። ሦስተኛው አዋጅ እነዚህን ሰዎች፣ አስፈላጊ ከሆነ በኃይል በመጠቀም ለሮማ አማልክት መስዋዕት እንዲያቀርቡ በማስገደድ ሃይማኖታቸውን ለማስካድ ሞከረ። አራተኛው አዋጅ ከነዚህ አዋጆች በሙሉ አልፎ በመሄድ ክርስቲያን ነኝ ማለት በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል መሆኑን ደነገገ።
የጭካኔው ማዕበል ትራዲቶረስ (“እጃቸውን የሰጡ” ማለት ነው) የተባሉ ሰዎችን ቡድን ፈጥሮአል። ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሉ የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎቻቸውን በማስረከብ አምላክንና ክርስቶስን የካዱ ሰዎች ናቸው። ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት እንደገለጹት “በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ክደዋል። . . . ቢሆንም ስደት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ጸንተው ቆመዋል። ከፍተኛ መከራ ቢደርስባቸውም በታማኝነት የጸኑ ሰዎች መታየታቸውና መሰማታቸው ይወላውሉ የነበሩትን ሰዎች እምነት ከማጠንከሩም በላይ ይታደኑ ለነበሩት ጉባኤዎች አዳዲስ አባላትን አስገኝቶአል።” በፊርግያ፣ በካፓዶቂያ፣ በሜሶጶጣሚያ፣ በፊንቂያ፣ በግብፅ እና በብዙ የሮም ግዛቶች የሚኖሩ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት ሞተዋል።
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ የነበረው የቂሳሪያው ዩሴቢየስ በስደቱ ጊዜ በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች እንደሞቱ ጽፎአል። በሌላ በኩል ደግሞ የሮማ መንግሥት መድከምና መውደቅ [ዘ ዲክላይን ኤንድ ፎል ኦፍ ዘ ሮማን ኢምፓየር] የተባለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ኤድዋርድ ጊቦን በስደቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሺህ እንደሚያንስ ገልጸዋል። አንድ ጸሐፊ “ጊቦን እነዚህ ታሪኮች ሰማዕታቱን ከፍ ለማድረግና ታማኞቹን ለማሞገስ ተብለው ከተጻፉና እጅግ ከተጋነኑ ታሪኮች የተገኙ ናቸው በማለት በጥርጣሬ ይመለከቱአቸዋል” ብለዋል። ሐተታቸውን በመቀጠል እንዲህ ብለዋል፦ “ከፍላጎታቸው ውጭ ሰማዕት በሆኑትና ራሳቸው ሆን ብለው ባነሳሱት ችግር ምክንያት በሚገደሉት ሰዎች መካከል ልዩነት የማያደርጉ፣ በጨዋታ ሥፍራዎች የተለቀቁ አራዊት ሌሎች ወንጀለኞችን በሙሉ ቦጫጭቀው ሲበሉ ክርስቲያኖችን ግን እንዳይነኩ ‘በመለኮታዊ ኃይል’ እንደተከለከሉ የሚገልጹ ጸሐፊዎች ጥቂት ሰዎች ቢሞቱ ‘በብዙ ሺህ’ አባዝተውና አጋንነው መጻፋቸው አይቀርም። ይሁን እንጂ መጠነኛ የሆነ የፈጠራ ታሪክ ይኖራል የሚል ግምት ቢኖርም እውነት ነው የሚባለው ራሱ ከፍተኛ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ነው።” በእንጨት ላይ አስሮ በመግረፍ፣ በማቃጠል፣ ቆዳን በመግፈፍና ለማሰቃያ በሚያገለግል የብረት መውጊያ በመጠቀም በጣም አሰቃቂ የሆነ ስደት ተፈጽሞአል።
አንዳንድ የታሪክ ሊቃውንት ስደቱን ያነሳሳው ዲዮቅላጢያን ሳይሆን ገለሪየስ ነው የሚል አመለካከት አላቸው። ፕሮፌሰር ዊሊያም ብራይት የአባቶች ዘመን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “አረመኔው የዓለም ኃያል መንግሥት የዚህ ዓለም ክፍል ያልሆነውን መንግሥት ሕይወት ረግጦ ለማጥፋት ያደረገው ሙከራ የስደቱ እውነተኛ ጠንሳሽ በሆነው በገለሪየስ ስም ሳይሆን በዲዮቅላጥያን ስም መጠራቱ አለበቂ ሥነ ምግባራዊ ምክንያት አይደለም” ሲሉ አብራርተዋል። መንግሥቱ የአራት ገዢዎች ጥምር መንግሥት ቢሆንም ታሪክ ጸሐፊው ስቲፈን ዊልያምስ እንዳረጋገጡት “እስከ 304 ድረስ በመላው ግዛት ውስጥ የሚፈጸሙትን ዋነኛ ነገሮች በሙሉ የሚቆጣጠረው ዲዮቅላጥያን ነበር። እስከዚህ ዓመት ድረስ ለተፈጸመው ስደት ኃላፊው እርሱ ነው።” ዲዮቅላጥያን ታመመና በ305 እዘአ የነበረውን ሥልጣን በሙሉ አስረከበ። ከዚያ በኋላ በነበሩት ስድስት ዓመታት ያህል በክርስቲያኖች ላይ እየቀጠለ ለሄደው ስደት ምክንያቱ ገለሪየስ ክርስቲያናዊ ለሆነ ነገር ሁሉ ያለው ከፍተኛ ጥላቻ ነበር።
የአራተኛው መቶ ዘመን ክርስትና
እነዚህ በአራተኛው መቶ ዘመን መግቢያ ላይ የደረሱት አሰቃቂ ሁኔታዎች ሐዋርያው ጳውሎስና ጴጥሮስ እንዲሁም ሌሎች በመንፈስ አነሳሽነት የጻፉ ጸሐፊዎች የተናገሩት ትንቢት ፍጻሜ ነው። የዲዮቅላጥያን አዋጆች፣ በተለይም ሁለተኛው አዋጅ በትንቢት የተነገረለት “የአመፅ ሰው” ሥር ሰድዶ እንደነበረ ያመለክታሉ። (2 ተሰሎንቄ 2:3, 4፤ ሥራ 20:29, 30፤ 2 ጴጥሮስ 2:12) በአራተኛው መቶ ዘመን የክህደት ሥራዎች በጣም ተስፋፍተው ነበር። የሮም ጦር ሠራዊት አባሎች የነበሩ ክርስቲያን ነን ባዮች ቁጥር ጥቂት አልነበረም። ታዲያ በዚያ ዘመን ከሐዋርያት የተቀበሉትን “የጤናማ ቃል ምሳሌ” የያዙ ታማኝ ክርስቲያኖች አልነበሩም ማለት ነውን?—2 ጢሞቴዎስ 1:13
ዩሴቢየስ በስደቱ ምክንያት የተሰዉትን ጥቂት ሰዎች በስም ከመዘርዘሩም በላይ የደረሰባቸውን ስቃይና መከራ እንዲሁም በሰማዕትነት የሞቱበትን ሁኔታ ገልጾአል። እነዚህ ሰማዕታን በሙሉ በጊዜያቸው ለተገለጸላቸው እውነት ታማኝነታቸውን ጠብቀው የሞቱ ስለመሆናቸውና ስላለመሆናቸው በአሁኑ ጊዜ የምናውቀው ነገር የለም። አንዳንዶች ኢየሱስ ከኑፋቄ፣ ከመጥፎ ሥነ ምግባርና ታማኝነታቸውን ከሚያስጥስ ከማንኛውም ዓይነት ድርጊት እንዲርቁ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ ብለው እንደነበረ አያጠራጥርም። (ራእይ 2:15, 16, 20-23፤ 3:1-3) አንዳንድ ከስደቱ የተረፉ ታማኝ ሰዎች ከታሪክ ተሰውረው እንደቀሩ የታወቀ ነው። (ማቴዎስ 13:24-30) የክርስትና አምልኮ በአደባባይ እንዳይፈጸም ለማድረግ የተወሰደው እርምጃ የተሳካ ውጤት አስከትሎ ስለነበረ በዘመኑ የተሠራ አንድ የስፓኝ ሐውልት ዲዮቅላጥያን ‘የክርስቶስን አጉል እምነት’ በማጥፋቱ አወድሶታል። ይሁን እንጂ ዲዮቅላጥያን በክርስትና ላይ የፈጸመው ጥቃት ዋነኛ ክፍል የሆነው የቅዱሳን ጽሑፎችን ቅጂዎች ለማጥፋት የተደረገ ሙከራ የአምላክን ቃል ፈጽሞ ለማጥፋት ሳይችል ቀርቶአል።—1 ጴጥሮስ 1:25
የዓለም ገዢ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ክርስትናን ፈጽሞ ለማጥፋት ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካለት ሲመለከት ከ306 እስከ 337 እዘአ በነገሠው በንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ አማካኝነት የተንኮል ድርጊቱን መፈጸም ቀጠለ። (ዮሐንስ 12:31፤ 16:11፤ ኤፌሶን 6:11 የግርጌ ማስታወሻ) አረመኔው ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያኖችን በቀጥታ አልተዋጋም። ከዚህ ይልቅ አረማዊ አምልኮን ከክርስትና እምነት ጋር በመደባለቅ አንድ አዲስ የመንግሥት ሃይማኖት ማቋቋም ይበልጥ አመቺ እንደሚሆን ተገነዘበ።
እዚህ ላይ ለሁላችንም የሚሆን ማስጠንቀቂያ እናገኛለን። ጭካኔ የተሞላበት ስደት በሚያጋጥመን ጊዜ ለጊዜው ከሥቃይ ለመገላገል ብለን እምነታችንን ከመካድ እንድንርቅ ለይሖዋ ያለን ፍቅር ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 5:9) በተመሳሳይም ሰላም በሚኖርበት ጊዜ ክርስቲያናዊ ብርታታችን እንዲዳከም መፍቀድ አይገባንም። (ዕብራውያን 2:1፤ 3:12, 13) የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን አጥብቆ መከተል ሕዝቦቹን ለሚያድነው አምላክ ለይሖዋ ታማኝ ሆነን እንድንኖር ያስችለናል።—መዝሙር 18:25, 48
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Musei Capitolini, Roma