የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 7/15 ገጽ 23-27
  • በፖላንድ “የተመረጡትን ዕቃዎች” መሰብሰብ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በፖላንድ “የተመረጡትን ዕቃዎች” መሰብሰብ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • አቅኚዎች የአገልግሎት በር ከፈቱ
  • የከተማው ወሬ
  • የዓለምን መንፈስ መቋቋም
  • ልማደኛ ወንጀለኞች ተለውጠዋል
  • እምነትና ጽናት ተፈተነ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 7/15 ገጽ 23-27

በፖላንድ “የተመረጡትን ዕቃዎች” መሰብሰብ

ፖላንድ የካቶሊክ አገር እንደሆነች ይነገርላታል። 93 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ካቶሊክ እንደሆነ የሕዝብ ቆጠራ ስታትስቲክስ ያሳያል። ይሁን እንጂ በቅርቡ የደረሰው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ለውጥ በሕዝቡና በሃይማኖታዊ ሕይወቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ አሳድሮአል። አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ከተጠየቁት ሰዎች መካከል በካቶሊክ ሃይማኖት እንመላለሳለን ያሉት 50 በመቶ የሚያክሉት ብቻ እንደሆኑ የሕዝብ ቆጣሪዎች አመልክተዋል።

በግንቦት ወር 1989 የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት በፖላንድ አገር ሕጋዊ እውቅና አገኘ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ 11,000 የሚያክሉ አዳዲስ ሰዎች የመንግሥቱ ምሥራች አስፋፊዎች ሆነዋል። ከ102,000 የሚበልጡ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ከ1,300 በላይ በሚሆኑት ጉባኤዎች ይሰበሰባሉ። በ1991 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ደግሞ 200,422 ሰዎች ተገኝተዋል። ስለዚህ በትንቢት የተነገረው ‘ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጡትን ዕቃዎች የመሰብሰብ ሥራ’ በፖላንድ እየተከናወነ ነው። (ሐጌ 2:7) በቅርቡ ዋነኛ የዜና ርዕስ የሆኑ ዓለም አቀፍ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች በፖላንድ ተደርገዋል። ይሁን እንጂ በአገሪቷ ትናንሽ ከተሞች ውስጥ በመከናወን ላይ የሚገኘውን ሥራ መመልከት በዚህች አገር የመሰብሰቡ ሥራ ምን ያህል እየተስፋፋ እንዳለ ያሳየናል።

አቅኚዎች የአገልግሎት በር ከፈቱ

እስዝቱም የቪስቱላ ወንዝ ወደ ቦልቲክ ባሕር በሚገባበት ቦታ አጠገብ የምትገኝ 10,000 ሕዝብ የሚኖርባት ከተማ ነች። ይህች ከተማ በስብከቱ ሥራ ረገድ ለረዥም ጊዜ ፍሬ የማትሰጥ ድንጋያማ መሬት እንደሆነች ተደርጋ ትታይ ነበር። በ1987 በአካባቢው የነበሩት አስፋፊዎች ስምንት ብቻ ነበሩ። አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ወደ ከተማይቱ በመጡ ጊዜ ግን ሁኔታዎቹ መቀየር ጀመሩ። በፊልም ቤት አዳራሽ ውስጥ በተደረገው አምስተኛ ስብሰባ ላይ 100 ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ተገኙ። ከሁለት ዓመት ትጋት የተሞላበት ጥረት በኋላ አንድ ጉባኤ ተቋቋመ። አሁን በዚህች ከተማ የራሳቸው የመንግሥት አዳራሽ ያላቸው 90 አስፋፊዎች ሲኖሩ 150 ሰዎች በስብሰባዎቻቸው ላይ አዘውትረው ይገኛሉ።

ልክ እንደተጠበቀው ብዙም ሳይቆይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መቃወም ጀመረች። አንዲት “ልዩ ብቃት ያላት” መነኩሲት የይሖዋ ምሥክሮች የሐሰት ትምህርት ያስተምራሉ በማለት የእነርሱን ስም የሚያጠፋ ንግግር አደረገች። ይሁን እንጂ ይህ ንግግርዋ ብዙ ጊዜ እንደሚሆነው ተቃራኒውን ውጤት አስከተለ። ብዙ ሰዎች ሐቁን መርምረው እንዲያውቁ አነሳሳቸው። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ እውነትን አውቀው አሁን የዘወትር አቅኚ ሆነዋል። እነርሱም ‘እውነትን በምናጠናበት ጊዜ ምሥክር ለመሆን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው የአስተማሪውን አርአያ በመከተል አቅኚ መሆን ይገባዋል ብለን እናስብ ነበር’ በማለት ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት የአቅኚነት መንፈስ በጉባኤው በሙሉ ሊስፋፋ ችሎአል።

በዚህም ምክንያት በአካባቢው 180 የሚያክሉ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይመራሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት ንባብ ተምረዋል። በዚያውም እውነትን ለማወቅ ችለዋል። በአካባቢው የሚገኙ እስረኞች መንገድ ለማፅዳት በሚወጡበት ጊዜ ዘወትር የአሥር ደቂቃ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየተመራላቸው ነው። አንዲት በመንገድ የምታልፍ ሴት አንዱዋን ምሥክር መስደብ በጀመረች ጊዜ ከእስረኞቹ አንዱ ሊከራከርላት ተነሳ። ወደ እህት ሮጦ ሄደና ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ከእጁዋ ወስዶ ወደ ላይ አነሳና ተሳዳቢዋን ሴት “እዚህ ላይ የተጻፈው ምን እንደሆነ ለማንበብ አትችይም? በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ! ይላል። ከአሁን በፊት እንደዚህ ያለ ነገር ሰምተሽ ታውቂያለሽ? አምላክንና አምላኪዎቹን የምትሰድቢበት ምን ምክንያት አለሽ?” አላት።

የከተማው ወሬ

በአንድ ወቅት ዝነኛ የፖላንድ ዋና ከተማ የነበረችው ክሩዝቪካ የካቶሊክ እምነት የተስፋፋባት ከተማ ናት። በ1990 አጋማሽ ላይ እንኳን 9,300 ከሚያክሉት የከተማው ነዋሪዎች መካከል የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ነበሩ። ይሁን እንጂ የይሖዋ በረከት ከመንግሥቱ ሰባኪዎች አልተለየም ነበር።

ብዙ ሰዎች፣ በተለይም ወጣቶች የመንፈሳዊ መሪዎቻቸውን ግብዝነት በመመልከታቸው ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለማግኘት ወደ ምሥክሮቹ መሄድ ጀመሩ። በአጭር ጊዜ ውስጥ 20 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ። የአካባቢው ሰበካ ቄስ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚያሳጣ ስብከት ቢሰብኩም ይህ ስብከታቸው ቅን የሆኑ ሰዎች ወደ ስብሰባ እንዳይሄዱ አላደረጋቸውም። ምሥክሮቹ በሱቆች ውስጥና በመዝናኛዎች እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንኳን ሳይቀር የመነጋገሪያ ርዕስ ሆነዋል። ከግማሽ ዓመት በኋላ ሁለት ትልልቅ የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖች ተመሠረቱ። በአሁኑ ጊዜ በክሩዝቪካ 35 የሚያክሉ የይሖዋ አምላኪዎች የሚገኙበት በጣም ንቁ የሆነ ጉባኤ ይገኛል። እነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች 75 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት አንድ ወቅት የሐሰት ሃይማኖት ምርኮኞች የነበሩትን ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ በፍጥነት እየሰበሰቡ ነው።

ከእነዚህ መካከል ቤተሰቦቹ አክራሪ ካቶሊኮች የሆኑት ቦግዳን የተባለ የ23 ዓመት ወጣት ይገኛል። እሱም እንዲህ በማለት የቀድሞ አኗኗሩን ያስታውሳል፦ “እጠጣ፣ አጨስና በመጥፎ ሥነ ምግባር እመላለስ ነበር። በዱርዬነቴና በአመጸኝነቴ የታወቅኩ ሆንኩ። ይሁን እንጂ ስለ እኔ መበላሸት የሚያስብ ማንም አልነበረም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በጀመርኩ ጊዜ ግን እናቴ ራሷን በመርዝ እንደምትገድል አስፈራራችኝ። የእርሷን ዛቻ መቋቋም ስላልቻልኩ ከምሥክሮቹ ጋር የነበረኝን ማንኛውንም ዓይነት ግንኙነት አቆምኩ። በኋላ ግን ልዩ አቅኚዎች ባደረጉልኝ ፍቅራዊ እርዳታ ከመጥፎ ልማዶቼ በሙሉ ነፃ ለመሆን ቻልኩ። በ1991 በተደረገው የነፃነት አፍቃሪዎች የወረዳ ስብሰባ ላይ ተጠምቄ ከተጠመቅኩበት ጊዜ ጀምሮ ረዳት አቅኚ ሆኜ በማገልገል ላይ ነኝ። የሙሉ ጊዜ አገልግሎትንም የሕይወቴ ግብ አድርጌ መርጫለሁ።

የሃያ አንድ ዓመቱ ስላቮሚር ደግሞ በመናፍስትነት ድርጊቶችና በሰይጣን አምልኮ የተጠላለፈ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንደነዚህ ያሉትን ተግባሮች እንደሚያወግዝ በተመለከተ ጊዜ ከዚህ ዓይነቱ ድርጊት ራቀ። ሲናገርም “ነገር ግን ሰይጣን በቀላሉ አልተወኝም። አንድ ቀን ማታ የዘፈን ማጫወቻው ሳይከፈት መዝፈን ጀመረ። ማንኛውንም ከዲያብሎስ አምልኮ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች ከቤት ባስወግድም ሰይጣናዊ ዘፈን እሰማ ነበር። ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። እሱም መንፈሳዊ ሚዛኔን እንድጠብቅ ረዳኝ። በወላጆቼ አሳሳቢነት አማክረው የነበረው የሥነ አእምሮ ሐኪም ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቴን ተመለከተና ሙሉ በሙሉ የዳንኩ መሆኔን አረጋገጠልኝ። በጤንነቴ መከታተያ ካርድ ላይ ‘የይሖዋ ምሥክሮች አድነውታል’ ብሎ ጻፈ።”

የዓለምን መንፈስ መቋቋም

ከክሩዝቪካ ደቡባዊ ምዕራብ እሽሮዳ እሽላስካ ትገኛለች። በዚህች 9,000 ሕዝብ በሚኖርባት ትንሽ ከተማም “የተመረጡ ዕቃዎች” ብቅ ማለት ጀምረዋል። ከአራት ዓመት በፊት በዚህች ከተማ ትኖር የነበረችው አንዲት መንፈሳዊ እህታችን ብቻ ነበረች። አሁን ግን የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ወደ 47 ከፍ ብሏል። ብዙዎቹ ምሥክሮች እንደ አብዛኛዎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች በመናፍስትነት፣ በዕፅ ሱሰኝነትና በመጥፎ ሥነ ምግባር ወጥመድ የተጠላለፉ ነበሩ። ይህ ነገር በብዛት ሊስፋፋ የቻለው ሰዎችን ከመርዳት ይልቅ ማውገዝ ብቻ በምትችለው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተፈጠረው መንፈሳዊ ባዶነት ምክንያት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ከምስክሮቹ እውነተኛ እፎይታ በማግኘት ላይ ናቸው።

በጉባኤው ውስጥ የሚገኙት ወጣቶች የሚማሩበትን ትምህርት ቤት የስብከት ክልላቸው አድርገው ቆጥረውታል። “ሁልጊዜ የክፍል ጓደኞቼ ‘የወጣትነትሽን ጊዜ እያባከንሽ ነው’ ይሉኛል” ስትል የ18 ዓመቷ ካሲያ ትገልፃለች። “እኔ ግን ከብዙ ችግሮች ለመጠበቅ ችዬአለሁ። ሕይወቴም ትርጉም ያለው ሆኖልኛል። የቤት ሥራዬንም ሆነ የግል ጥናቴን ችላ ሳልል በትምህርት ቤት ውስጥ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እመራለሁ። ‘የወጣትነት ጊዜሽን ታባክኛለሽ’ ይሉኝ የነበሩት ልጃገረዶች አሁን የልጅ እናት በመሆናቸው ከባድ የችግር ቀንበር ተጭኖባቸዋል።”

የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች በአካባቢው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በጣም የታወቀ ሆኖአል። ለምሳሌ አንዲት የፖሊሽ ቋንቋ አስተማሪ ተማሪዎችዋ ድርሰታቸውን ሲጽፉ በንቁ! መጽሔታችን ላይ የሚገኘውን ቀላል አገላለጽ እንደ ምሳሌ አድርገው እንዲከተሉ ነግራቸዋለች። ረዳት አቅኚ ሆና የምታገለግለው ኢዋ ትምህርት ቤትና የይሖዋ ምሥክሮች የሚለው ብሮሹር በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝባለች። “ይህንን ጽሑፍ በእርግጥ አደንቀዋለሁ። አስተማሪዎቼ ከዚህ ብሮሹር ጋር በደንብ ተዋውቀዋል። በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እንድችል ፈቃድ እንዲሰጠኝ ስጠይቅ ምንም ዓይነት ችግር ገጥሞኝ አያውቅም።” ወጣቶች የሚያሳዩት ይህን የመሰለ ጥሩ ዝንባሌ የይሖዋን ልብ ደስ አሰኝቶታል።—ምሳሌ 27:11

ልማደኛ ወንጀለኞች ተለውጠዋል

ከእሽሮዳ እሽላስካ በስተ ምስራቅ ስትረስሌኪ ኦፖልስኪ ትገኛለች። በዚህች ከተማ ሁለት እሥር ቤቶች ይገኛሉ። አንደኛው እስር ቤት የማይታረሙ ልማደኛ ጥፋተኞች የሚታሰሩበትና ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት እስር ቤት ነው። ምሥክሮቹ ለእስረኞቹ እውነትን ለመንገር ሲሉ እነዚህን እስር ቤቶች አዘውትረው ይጎበኛሉ። ከእስረኞቹ መካከል አብዛኛዎቹ ዓለም አቀፍ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው የታላቂቷ ባቢሎንም እስረኞች ናቸው።—ራእይ 18:1-5

ምሥክሮቹ ከእስረኞቹ ጋር በግልም ሆነ በትናንሽ ቡድኖች ከፋፍለው መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናሉ። ከነዚህም አንዳንዶቹ ተጠምቀዋል። በእሥር ቤት ሆነው ፍርዳቸውን መጨረስ ቢኖርባቸውም ምሥራቹን ለአዳዲስ እስረኞች በትጋት ይሰብካሉ። አንድ ለጥምቀት እየተዘጋጀ ያለ እስረኛ አስደናቂ የሆነ የጠባይ ለውጥ ስላደረገ የእስር ቤቱ ባለሥልጣኖች በሳምንት አንድ ቀን ወደ ቤቱ እንዲሄድ ፈቅደውለታል። ሌሎቹም ወንጀለኛ ሆነው ሳይሆን የይሖዋ ምስክሮች ሆነው ከእስር ቤት ለመውጣት ቁርጥ ያለ ውሳኔ ማድረጋቸውን ለቤተሰቦቻቸው ጽፈዋል።

የአንደኛው እስር ቤት ኃላፊ የካቶሊክ ካህናት ወደ እስር ቤት ይመጡ እንደነበረና ግን ምንም ውጤት እንዳላገኙ ተናግረዋል። ምሥክሮቹን “እነዚህን ሰዎች ለመለወጥና ለማረም ያስቻላችሁ ምንድን ነው?” ብለው ጠይቀዋል። አንድ እስረኛ ለቤተሰቡ የጻፈው ደብዳቤ መልስ ይሰጣል፦ “እዚህ እስር ቤት ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ በቅርብ ጊዜ ምድርን ሁሉ ስለምትገዛው አዲስ መንግሥት ማለትም ስለ ይሖዋ መንግሥት የሰጠውን አስደናቂ ተስፋ ነግረውኛል። እዚህ ሆኜ የቀደሞውን አኗኗሬን በመጽሐፍ ቅዱስ ብርሃን ለመመርመር ጊዜ አግኝቼአለሁ። ነፃ ሰው ለመሆንና ራሴን የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት አድሮብኛል። ዛሬ የተጠመቅኩ የይሖዋ ምሥክር ሆኜአለሁ።”

በሌላው እስር ቤት ውስጥ ያሉት እስረኞች ብዙዎቹ ነፍስ በመግደላቸው ምክንያት የ25 ዓመት እሥራት የተፈረደባቸው ናቸው። ለ12 ሰዎች የዘወትር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየተደረገ ነው። ከእነርሱ መካከል አንዱ ሕይወቱን ለይሖዋ ወስኖ ተጠምቆአል። ሌሎቹም ተመሳሳይ የሆነ እርምጃ ለመውሰድ አቅደዋል። የእስር ቤቱ ኃላፊ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙበት የማስተማር ዘዴ ያስገኘውን ጥሩ ውጤት በማድነቅ “ያሉኝ እስረኞች 12 ብቻ አይደሉም። 600 ናቸው። የእነዚህንም ጠባይ ለማረም እርዱኝ። ፕሮግራም አውጡልኝ እንጂ የሚያስፈልጋችሁን ማንኛውንም ነገር አቀርባለሁ። ተገቢውን እንክብካቤ አድርጉላቸው።”

ወንድሞችም ያደረጉት ይህንኑ ነበር። ስለ ሕይወት ዓላማ፣ ስለ ወደ ፊቱ ተስፋና መጥፎ ድርጊቶችን ስለመተው አስፈላጊነት የሚገልጽ ፕሮግራም አዘጋጁላቸው። በተጨማሪም እስረኛ ስለነበረና አሁን ግን የጉባኤ ሽማግሌ ስለሆነ አንድ የይሖዋ ምሥክር የሚገልጽ ተሞክሮ ነገሩአቸው። በተጨማሪም ምሥክሮቹ የአልማዝ ሌባና እፅ በድብቅ ያስገባ ስለነበረና አሁን ግን እውነትን ስላወቀ ሰው የሚገልጸውን የሕይወት ታሪክ ተረኩላቸው።a በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት 20 እስረኞች በሰሙት ሁሉ በጣም በመደሰታቸው ብዙ ጥያቄዎችን ጠየቁ። አንዳንዶቹም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

እምነትና ጽናት ተፈተነ

ሉባቾው በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ የምትገኝ 12,000 ሰዎች የሚኖሩባት ትንሽ ከተማ ነች። በ1988 አቅኚዎች እዚያ የሚኖሩትን 12 አስፋፊዎች ለመርዳት በመጡ ጊዜ በዚያች ከተማ የሚከናወነው የስብከት ሥራ ከፍተኛ ግፊት አገኘ። አሁን 72 የሚያክሉ ትጉህ የመንግሥቱ ሰባኪዎች አሉ። አዲስ በተሰራው የመንግሥት አዳራሽ በተከበረው የ1991 የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ 150 ሰዎች ተገኝተዋል።

በሰኔ 1991 ሊቀ ጳጳስ ዳግማዊ ዮሐንስ ጳውሎስ ሉባቾውን ጎብኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ጉብኝት የሕዝቡን እምነት ለማጠናከር አልቻለም። ብዙዎቹ ስለ ህይወት አላማና ስለ ወደ ፊቱ ተስፋ ብዙ ጥርጣሬና ጥያቄ አላቸው። ከቀሳውስቱ የሚያረካ መልስ ማግኘት ስላልቻሉ ወደ ይሖዋ ምሥክሮች መሄድ ጀምረዋል። ለሃይማኖታቸው ጀርባቸውን በመስጠታቸው ምክንያት ሕሊናቸው ቢወቅሳቸውም የተማሩት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የወሰዱት እርምጃ ትክክል መሆኑን እንዲገነዘቡ አስችሎአቸዋል።

በዚህ ረገድ አሁን የዘወትር አቅኚ የሆነችው የኦኖራታ ተሞክሮ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ከአንድ ዓመት በፊት ኃጢአትዋን በምትናዘዝበት ጊዜ ቄሱን የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ጠየቀቻቸው። ቄሱም “አምላክ ፍቅር ነው። ከሁሉም የሚበልጠው ውብ ስሙ ይህ ነው” ብለው መለሱላት። ትንሽ ዝም ካሉ በኋላ በመቀጠል “አንቺ አንድ ሰው የቀለም ጠብታ እንደጨመረበት በባልዲ ውስጥ ያለ ንፁሕ ውሃ ነሽ። ይህን በአንቺ ላይ የደረሰውን ለውጥ መሰረዝ አይቻልም” አሉአት። በዚህ መንገድ የጥያቄዋን መልስ አገኘች። “ወዲያው የይሖዋ ምሥክር መሆን እንደሚገባኝ ወሰንኩ” ትላለች። “ይህም ሊሰረዝ የማይችል ሆነ።”

በሉባቾው እውነትን ያወቁ ሁሉ ከባድና ጭፍን የሆነ ተቃውሞ ለመቋቋም ተገድደዋል። ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አፅንቶ ከመያዝና ከይሖዋ ጎን ከመቆም አላገዳቸውም።

ኤልዛቤታ ስታብራራ “ቤተሰቦቼ በመጀመሪያ እቤት ውስጥ ደበደቡኝ። ከዚያም ወደ መንግሥት አዳራሽ ዘለው ገብተው . . . ወደ ቤት ወሰዱኝና በዱላ ደበደቡኝ። ከምሥክሮቹ ጋር ስለተባበርኩ ብቻ ከራስ ፀጉሬ እስከ እግር ጥፍሬ ተደበደብኩ። በጣም በመደብደቤ አስቸኳይ ህክምና ማግኘት ስላስፈለገኝ ወደ ሆስፒታል ተወሰድኩ። በይሖዋ እርዳታ አገገምኩ። ወላጆቼም አባረሩኝ። ይህንን ሁኔታ ለቄሱ ስነግራቸው በጣም አንቋሽሸው “ትንሽ ጥፊ ተመታሁ ብለሽ ነው አቤቱታ ለማቅረብ የመጣሽው?” አሉኝ።

ሌላዋ እህት ደግሞ በየዓመቱ የመስቀል ጉዞ ለማድረግ ወደ ቼስቶኮዋ እሄድ ነበር። ማንኛውም እውነተኛ ካቶሊክ ይህን ጉዞ ማድረግ ይኖርበታል ብዬ አስብ ነበር። አሁንም በጉልበቶቼ ላይ ያሉት ጠባሳዎች አልጠፉም” ስትል ታስታውሳለች። በ18 ዓመቷ እውነትን አወቀችና ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደማትመለስ ለቄሱና ለቤተሰቦቿ ነገረቻቸው። “በጣም አድርገው ስለ ደበደቡኝ የአእምሮ መናወጥ ደረሰብኝ” ስትል ትናገራለች። “ይሁን እንጂ ሆስፒታል ቆይቼ በሚገባ ስለ ተሻለኝ ‘በነፃነት አፍቃሪዎች’ የወረዳ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ቻልኩ። በዚህ ስብሰባ ላይ በቼስቶኮዋ አይቼ የማላውቀውን ግብዝነት የሌለበት እውነተኛ አንድነትና ፍቅር ለማየት በመቻሌ በደስታ አለቀስኩ። የይሖዋን ጥሩነት በመቅመሴና በእሱ ላይ መታመንን በመማሬ ከፍተኛ ደስታ ተሰማኝ።” ይሖዋ ጭንቀታቸውን በእርሱ ላይ የሚጥሉትን ሁሉ ያጠነክራቸዋል፣ ይደግፋቸዋል።—መዝሙር 55:22

ብዙ የታላቂቱ ባቢሎን ምርኮኞች በዚህች ካቶሊክ አገርም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የሚኖሩ “ከመካከልዋ ውጡ” የሚለውን ጥሪ በመቀበል ላይ ናቸው። የይሖዋ ፈቃድ ከሆነ ደፋር ሕዝቦቹ ገና በፖላንድ አገር ውስጥ ተበትነው የሚገኙትን “የተመረጡ ዕቃዎች” ይሰበስባሉ። በእርግጥም ብዙዎች፦ “ና . . . የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” የሚለውን ጥሪ በመቀበል ላይ ናቸው።—ራእይ 18:4፤ 22:17

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የጥቅምት 8, 1983 ገጽ 16-19 እና የሕዳር 22, 1987 ገጽ 21-3 ንቁ! መጽሔት ተመልከት።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ፖላንድ

እስቱም

ክሩዝቪካ

ፖዝናን

ዋርሶው

እሽሮዳ እሽሌስካ

ቼስቶኮዋ

ስትርዜልኬ ኦፖልስኪ

ሉባቾው

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመንግሥቱ መልእክት በፖላንድ ክሩዝቪካ ሲሰበክ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ