“ወደ እኔ ተመለሱ፣ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ”
ቤተሰቡ በሙሉ ለሽርሽር ሄዶ በአንድ ጫካ ውስጥ አስደሳች ጊዜ እያሳለፈ ነበር። በዚያን ጊዜ ታናሹ ልጅ ፒተር አንዲት ሽኮኮ እያባረረ በኮረብታው ቁልቁለት ርቆ ሄደ። በድንገት ሰማዩ በደመና ተሸፈነና ዝናብ መዝነብ ጀመረ። በመጀመሪያ መጠነኛ ካፊያ ነበር። ይሁን እንጂ እየቆየ ዶፍ መውረድ ጀመረ። ቤተሰቡም በፍጥነት ዕቃዎቻቸውን ሰበሰቡና ወደ መኪናቸው ሮጡ። ሁሉም ፒተር የት ይሆን ብለው ተደናገጡ።
በመካከሉ ፒተር ወደ ቤተሰቦቹ ለመመለስ ሙከራ እያደረገ ነበር። መንገዱን አጥርቶ መመልከት አስቸጋሪ ሆነበት። በዝናቡ ምክንያት የኮረብታው አቀበት የሚያዳልጥ ሆኗል። ተደብቆ ወደነበር ጥልቅ ጉድጓድ በድንገት ሲገባ መሬቱ የከዳው መሰለው። ለመውጣት ሙከራ አድርጎ ነበር። ይሁን እንጂ የገደሉ አፋፍ በጣም የሚያዳልጥ ስለነበረ ለመውጣት አልቻለም።
ጉድጓዱ የዝናቡ ውኃ ከኮረብታው ላይ እያጠበ በሚያመጣው ጭቃ እየሞላ መጣ። በእርግጥ ፒተር የመስጠም አደጋ ላይ ነበር። ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ አባቱ አገኘውና በገመድ ጎትቶ አወጣው። በኋላም ፒተር ርቆ በመሄዱ በጣም ተቆጡት። ሆኖም በብርድ ልብስ ተጠቅልሎና በእናቱ እቅፍ ሆኖ ተግሳጹን መቀበል አልከበደውም ነበር።
ይህ ተሞክሮ ከዚህ በፊት የአምላክ ሕዝብ ከነበሩት መካከል አንዳንዶቹ ያጋጠማቸውን ሁኔታና ደህና አድርጎ የሚያሳይ ምሳሌ ነው። እነዚህ ሰዎች ወደዚህ የነገሮች ሥርዓት ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ጠልቀው ገብተዋል። የይሖዋ ድርጅት ወደሚሰጠው መጠለያ ለመመለስ ከገቡበት ጉድጓድ ለመውጣት ከፍተኛ የጭንቀት ሙከራ ያደርጋሉ። ይሖዋ መሐሪና እነርሱን ወደ ደኅንነት ለመመለስ ‘ገመድ ለመላክ’ ዝግጁ መሆኑን ማወቅ እንዴት ያስደስታል!
የይሖዋ የምሕረት ድርጊቶች
ወደ ኋላ ተመልሰን በእስራኤል ዘመን ቤተ መቅደሱ ተሠርቶ ወዳለቀበት ጊዜ ስንመጣ ሰለሞን ባቀረበው የምረቃ ጸሎት ላይ ይሖዋ ፊታቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ መልሰው ጸሎት የሚያቀርቡትን እንዲሰማ እንዲህ በማለት ልመና አቅርቦ ነበር፦ “(የማይበድል ሰው የለምና) አንተን ቢበድሉ [እስራኤላውያን]፣ ተቆጥተህም ለጠላቶቻቸው አሳልፈህ ብትሰጣቸው . . . በተማረኩበትም አገር ሆነው በልባቸው ንስሐ ቢገቡ፣ በማራኪዎቹም አገር ሳሉ ተመልሰው፦ ኃጢአት ሠርተናል፣ በድለንማል፣ ክፉንም አድርገናል ብለው ቢለምኑህ . . . ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በማደሪያህ በሰማይ ስማ።”—1 ነገሥት 8:46-49
በእስራኤል ታሪክ ውስጥ የሰለሞን ልመና ብዙ ጊዜ መልስ አግኝቶአል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ከአምላክ ዘወር ይሉና እርሱን መከተልን ይተዉ ነበር። ከዚያም ስህተታቸውን ይገነዘቡና እንደገና ተመልሰው እርሱን ይፈልጉ ነበር። ይሖዋም ይቅርታ ያደርግላቸው ነበር። (ዘዳግም 4:31፤ ኢሳይያስ 44:21, 22፤ 2 ቆሮንቶስ 1:3፤ ያዕቆብ 5:11) ለአንድ ሺህ አመታት ይሖዋ ከሕዝቦቹ ጋር የነበረውን ግንኙነት በሚልክያስ አማካኝነት እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፣ እርስዋንም አልጠበቃችሁም። ወደ እኔ ተመለሱ፣ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ።”—ሚልክያስ 3:7
ለመሰናከል ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች
እስራኤላውያን ያደርጉት እንደነበረው ዛሬም በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው የአምላክ ሕዝቦች ከይሖዋ ድርጅት ዘወር ይላሉ። ምክንያቱ ምን ይሆን? አንዳንዶቹ ፒተር ሽኮኮዋን እያባረረ ርቆ እንደሄደ እነርሱም በመጀመሪያ ሲመለከቱት ምንም ጉዳት የሌለው የሚመስልን ነገር በመከተላቸው ነው። አዳን ያጋጠማት ይህ ሁኔታ ነበር። እንዲህ በማለት ገለጸች፦ “በምሳ ሰዓት ሁላችን የሥራ ባልደረቦች ቅርብ ወደሆነው ምግብ ቤት አብረን ሄደን ምሳ መብላትን ልማድ አድርገን ነበር። ስለዚህ ከሥራ ሰዓት በኋላ አብሬአቸው ቡና እንድጠጣ ሲጋብዙኝ ግብዣቸውን ለመቀበል አልከበደኝም። የአገልግሎትና የጉባኤ ጊዜዬን እስካልወሰደብኝ ድረስ ምንም አይደለም ብዬ አሰብኩ። ይህን ማድረጌ በ1 ቆሮንቶስ 15:33 ላይ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት ሊያስጥሰኝ እንደሚችል ግን አልተገነዘብኩም ነበር።
“ብዙም ሳይቆይ ቅዳሜ ቅዳሜ ከእነርሱ ጋር ወደ ፈረስ ግልቢያ መሄድ ጀመርኩ። ከዚያም አብሬአቸው ወደ ሲኒማና ወደ ቲያትር ቤት እሄድ ነበር። ይህም በአንዳንድ ስብሰባዎች ላይ እንዳልገኝ አደረገኝ። በመጨረሻም በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘትንና በስብከቱ ሥራ መሳተፍን አቆምኩ። ምን እያደረግኩ እንዳለ መገንዘብ ስጀምር፣ ከድርጅቱ ጋር የነበረኝ ግንኙነት መቋረጡን ተረዳሁ።”
በሌሎች ሁኔታዎች ግን አንድ ሰው የሚሰናከልበት ምክንያት አምላክን ለማገልገል ብቁ እንዳልሆነ እንዲሰማው የሚያደርገው ከባድ የሆነ ስውር ኃጢአት መሥራት ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 32:3-5) ወይም አንድ ግለሰብ “የማይበድል ሰው የለምና” ብሎ ሰለሞን የተናገረውን ባለመረዳት በክርስቲያን ጓደኛው ንግግር ወይም ድርጊት ምክንያት ይሰናከል ይሆናል።—1 ነገሥት 8:46፤ ያዕቆብ 3:2
ሌሎችም ተግሳጽ ሲሰጣቸው ተስፋ ቆርጠዋል። (ዕብራውያን 12:7, 11) ብዙዎች በዓለማዊ የአኗኗር መንገዶች መሳባቸው አምላክን ማገልገላቸውን እንዲያቆሙ አድርጓቸዋል። ብዙውን ጊዜ በዓለም የተሳካላቸው ለመሆን በሕይወታቸው ውስጥ ለአምላክ አገልግሎት ጊዜ እስከማይኖራቸው ድረስ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ በዓለማዊ ሥራዎች ያስይዛሉ። (ማቴዎስ 13:4-9፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) የእነዚህ ሰዎች ሁኔታ ተስፋ የሌለው ነውን?
ለይሖዋ ጥሪ ምላሽ ትሰጣላችሁን?
በአንድ ወቅት ላይ ኢየሱስ ለመረዳት የሚያዳግት ነገር ተናግሮ ነበር። በዚህ ጊዜ አንዳንዶች ተሰናከሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ወደ ኋላ ተመለሱ፣ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም።” ይሁን እንጂ የተሰናከሉት ሁሉም አልነበሩም። ታሪኩ በመቀጠል፦ “ኢየሱስም ለአሥራ ሁለቱ፦ ‘እናንተም ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን?’ አለ። ስምዖን ጴጥሮስም፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ’” አለ። (ዮሐንስ 6:66-68) የኢየሱስ ሐዋርያት ኢየሱስን ትተው መሄዳቸው መዘዙ ከባድ እንደሚሆን ተገንዝበው ነበር።
ከእውነት እርቀው የነበሩ አንዳንዶች ውሎ አድሮ ተመሳሳይ ወደ ሆነ መደምደሚያ ደርሰዋል። የአምላክን ድርጅት መተዋቸው አደገኛ እርምጃ እንደነበረና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ቃል የሚገኘው ከይሖዋና ከኢየሱስ ብቻ መሆኑን ተገንዝበዋል። አንዴ ወደዚህ ዓይነቱ ግንዛቤ ከደረሱ በኋላ አቅማቸውን እንደገና ለመመርመር፣ ይሖዋን ይቅርታ ለመጠየቅና ወደ እርሱ ተመልሰው ለመምጣት ጊዜው አልፎብኛል ማለት አይኖርባቸውም። “ወደ እኔ ተመለሱ፣ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” የሚለውን ጥሪ ያቀረበው ይሖዋ ራሱ ነው።—ሚልክያስ 3:7
እንደ እውነቱ ከሆነ አንድ ቅን ክርስቲያን ይሖዋን በማገልገል ካልሆነ በስተቀር በሌላ በምን መንገድ ደስታን ሊያገኝ ይችላል? አንድ ሰው ለተወሰነ ጊዜ የአምላክ ድርጅት አባል ሆኖ ከቆየ በኋላ ከአምላክ ዘወር ቢል በውጭ ባለው ዓለም ውስጥ የሚጠብቀው ምንድን ነው? ብዙም ሳይቆይ ዓመፁ እየጨመረ የሚሄደው ዓለም ክፍል መሆኑን ይገነዘባል። ፒተር የተባለውን ወጣት ሕይወት እንደተፈታተነው የጭቃ ጉድጓድ ዓይነት እርሱም የገባው በአደገኛና በማያስደስት ዓለም ግብዝነት፣ ውሸት፣ ማጭበርበርና የፆታ ብልግና በሞላበት ሥርዓት ውስጥ ሆኖ ያገኘዋል። ምንም ጊዜ ሳያባክን ወደ ልቡ ሲመለስና ዘላለማዊ ሕይወቱ በአደጋ ላይ መሆኑን በመገንዘብ ራሱን ከዚህ ዓይነት ሁኔታ ለማላቀቅ እርዳታ መፈለግ ይኖርበታል። አሁንም ቢሆን መመለሱ ቀላል ላይሆንለት ይችላል።
ወደ ይሖዋ ለመመለስ ከሞከሩት ነገር ግን መመለሱ አስቸጋሪ ከሆነባቸው ሰዎች መካከል አንዱ አንተ ነህን? ከሆነ እርዳታ እንደሚያስፈልግህ እወቅ። እንዲሁም በአምላክ ድርጅት ውስጥ ያሉት ወንድሞችህና እህቶችህ አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች እንደሆኑ እመን። ይሁን እንጂ አንተም ይሖዋ ፍላጎትህን እንዲያይልህ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። ‘ወደ ልብህ ተመልሰህ ወደ ይሖዋ’ የምትመጣበት ጊዜው አሁን ነው።—1 ነገሥት 8:47
ለመመለስ እርዳታ አገኙ
አዳ ወደ ይሖዋ እንድትመለስ የረዳት ምን እንደሆነ እንዲህ በማለት አስረዳች፦ “አስጠኚዬ የነበረችው እህት በክልል ስብሰባ ከእርሷ ጋር እንድገኝ በትክክለኛው ወቅት ላይ ጋበዘችኝ። እርሷ በጣም ደስ የምትል ሰው ነች! ምንም ነቀፋ አድርሳብኝ አታውቅም! ብዙ ፍቅር አሳየችኝ። በስብሰባ ለመጨረሻ ጊዜ ከተገኘሁ ዓመት አልፎኛል። ይሁን እንጂ ስለ ዓለም ባዶነት ሳስብ ከአንጸባራቂነቱ በስተጀርባ የያዘው ነገር ቢኖር ሐዘን፣ ብስጭትና ምግባረ ብልሹነት መሆኑን ተገንዝቤ ነበር። ስለዚህ በዚህ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወሰንኩ። ስብሰባው ይካሄድበት ወደነበረው ትያትር ቤት አንዴ ገባሁና በመጨረሻው ረድፍ በሚገኙት ወንበሮች በአንድ ጥግ ላይ ራሴን ደብቄ ተቀመጥኩ። ወንድሞች እንዲያዩኝና እንዲጠይቁኝ አልፈለግሁም ነበር።
“ይሁን እንጂ ከፕሮግራሙ በጣም የሚያስፈልገኝን ምክር አገኘሁ። ፕሮግራሙ ካለቀ በኋላ ወደ ይሖዋ ሕዝቦች መመለስ ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ልቤን ለይሖዋ ለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። ወንድሞችም ‘የጠፋ ሰው’ ሲመለስ በማየታቸው እጃቸውን ዘርግተው ተቀበሉኝ።” (ሉቃስ 15:11-24) ይህ ሁሉ ከሆነ ቆየት ብሎአል። አሁን አዳ ከ25 ዓመታት በላይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ትገኛለች።
ጠፍቶ በነበረ ሌላ ግለሰብ ላይም ተመሳሳይ የሆነ አስደሳች ውጤት ተገኝቶአል። አንዳንድ ሽማግሌዎች ለጆሲ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይልቅ የራሳቸውን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቅ ምክር ሰጡት። ጆሲ ተስፋ በመቁረጥና ቅር በመሰኘት ከጊዜ በኋላ ቀዘቀዘ። ለ8 ዓመታት ያህል ከአምላክ ሕዝቦች ራሱን ለይቶ ቆየ። በዚህ ጊዜ የማታምን ሴት አግብቶ ልጆች ወለደ። አንዱን ልጁንም በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንዲጠመቅ ፈቅዶ ነበር።
በመጨረሻም የክልል የበላይ ተመልካቹ የእረኝነት ጉብኝት ባደረገለት ጊዜና ሽማግሌዎችም ተመሳሳይ ጉብኝት እንዲያደርጉለት የበላይ ተመልካቹ ባሳሰባቸው ጊዜ ጆሲ እርዳታ አገኘ። እርሱም ተመለሰ፤ ባለቤቱም ለእውነት ፍላጎት እንዳሳየች ሲመለከት ደስታ ተሰማው። በአሁኑ ጊዜ ጆሲ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። እነዚህ ሁለት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ይሖዋ ለፍቅራዊ ጥሪው እሺ የሚል ምላሽ የሚሰጡ ሰዎችን ከመባረክ ወደ ኋላ አይልም።
ሆኖም አንድ ሰው እንዲህ ባሉት በረከቶች ለመደሰት ከፈለገ በመጀመሪያ ለቀረበለት እርዳታ አድናቆት ማሳየትና በምላሹ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። በአብዛኞቹ ጉባኤዎች የሚገኙ ወንድሞች የቀዘቀዙትን ያስታውሱአቸዋል፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጎብኘት እርዳታ ሊያደርጉላቸው ይሞክራሉ። እንዲህ ላለው እርዳታ የእሺታ ምላሽ መስጠት ለይሖዋ ምሕረት አድናቆት ማሳየት ማለት ነው።—ያዕቆብ 5:19, 20
በእውነትም “ወደ እኔ ተመለሱ” ለሚለው የይሖዋ ጥሪ የእሽታ ምላሽ የምንሰጥበት ጊዜ አሁን ነው። (ሚልክያስ 3:7፤ ኢሳይያስ 1:18) ከአሁን በኋላ አትዘግይ። በዓለም ላይ የሚከሰቱት ነገሮች በሚያስገርም ፍጥነት በማለፍ ላይ ናቸው። ከፊታችን ባሉት አስቸጋሪ ጊዜያት ከሁሉ የተሻለው ከለላ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ሆኖ ጥበቃውን ማግኘት ነው። ከይሖዋ ታላቅ የቁጣ ቀን ለመሰወር የማያወላውል ተስፋ ያላቸው ወደ ይሖዋ የተጠጉት ብቻ ናቸው።—ሶፎንያስ 2:2, 3
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ወደ እኔ ተመለሱ” ለሚለው የይሖዋ ጥሪ እሺ የሚል ምላሽ ትሰጣላችሁን?