በልሳን የመናገር ስጦታ የእውነተኛ ክርስትና ክፍል ነውን?
“በልሳን ሲጸልይ ስሰማ በአየሩ ውስጥ የሚያስፈነጥዝ የኃይል መሞላት ያለ ሆኖ ተሰማኝ” በማለት ቢል የሚባል ሰው እሱና ሌሎች ስድስት ሰዎች በቤተ ክርስቲያኑ መሠዊያ አጠገብ በሰባኪው ፊት ከተሰበሰቡ በኋላ ተናገረ። እንዲህ ዓይነት ተሞክሮዎች የመጀመሪያውን መቶ ዘመን የመንፈስ ቅዱስ አሠራር የሚደግሙ ናቸውን? የመጽሐፍ ቅዱስን ሃይማኖትስ ለይተው ያሳውቃሉን? ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥንቃቄ በመመርመር አጥጋቢ መልስ ልናገኝ እንችላለን።
ተአምራዊው የመንፈስ ስጦታ ይተላለፍ የነበረው ቢያንስ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ወይም ሐዋርያው ጳውሎስ በተገኘበት እንደነበረ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ ያሳያል። በልሳን መናገር ከተመዘገበባቸው ሦስት አጋጣሚዎች አንዱና የመጀመሪያው የተፈጸመው የኢየሱስ 120 ደቀ መዛሙርት በኢየሩሳሌም በተሰበሰቡበት በጰንጠቆስጤ ዕለት ነበር። (ሥራ 2:1-4) ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ያልተገረዙ ሮማውያን የሐዋርያው ጴጥሮስን ስብከት በማዳመጥ ላይ ላሉ መንፈስን ተቀበሉና “በልሳኖች እየተናገሩ እግዚአብሔርን ማክበር” ጀመሩ። (ሥራ 10:44-48) ከጰንጠቆስጤ በኋላ 19 ዓመታት ቆይቶም በ52 እዘአ ገደማ ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበረ አንድ ቡድን ለነበሩ ቡድኖች ተናገረና በ12 ደቀ መዛሙርት ላይ እጁን ጫነባቸው። እነሱም “በልሳኖች ተናገሩ፣ ትንቢትም ተናገሩ።”—ሥራ 19:6
በልሳን የመናገር ስጦታ ያስፈለገው ለምን ነበር?
ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሊያርግ ሲል ለተከታዮቹ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሏቸዋል። (ሥራ 1:8) ኢየሱስ ይህ ታላቅ የምስክርነት ሥራ እንዴት እንደሚከናወን ማለትም በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ እንደሚከናወን ማመልከቱ እንደነበር አስተውሉ።
በምድር ዙሪያ መልእክቶችን ለመላክ የሚያስችለን ዘመናዊው የመገናኛ ቴክኖሎጂ በዚያን ጊዜ አልነበረም። የምሥራቹ የሚሠራጭበት ዋና መንገድ በአፍ በሚነገር ቃል ስለነበር ለዚህም በውጭ ቋንቋዎች የመናገር ተአምራዊ ስጦታ ለዚህ በጣም ጠቃሚ ነበር። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም ለአይሁድና ወደ ይሁዲነት ለተለወጡ ሰዎች በሰበኩ ጊዜ የሆነው ይኸው ነበር። የጳርቴና፣ የሜድ፣ የኢላሜጤም ሰዎች፣ በሁለት ወንዝም መካከል፣ በይሁዳም፣ በቀጰዶቅያም፣ በጳንጦስም፣ በእስያም፣ በፍርግያም፣ በጵንፍልያም፣ በግብፅም፣ በቀሬናም በኩል ባሉት በሊብያ ወረዳዎች የሚኖሩ፣ በሮሜም የሚቀመጡ፣ አይሁድም ወደ ይሁዲነትም የገቡ የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች “የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ” በገዛ ቋንቋቸው ሰሙ፤ የተነገረውንም ተረዱ። ወዲያውም ሦስት ሺህ ሰዎች አማኞች ሆኑ።—ሥራ 2:5-11, 41
ብዙ ጊዜ የሚዘነጋው ሐቅ በልሳን መናገር ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈላቸው ደብዳቤ ላይ ከጠቀሰላቸው ዘጠኝ የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች አንዱ ብቻ መሆኑ ነው። ጳውሎስ በልሳን መናገርን እንደ አነስተኛ ስጦታ አድርጎ ቢመለከተውም ስለ ሰማያዊው የአምላክ መንግሥት የምሥራቹን ለማሠራጨት ለመጀመሪያው የክርስቲያን ጉባኤ ጠቃሚ ነበር። በቁጥር ረገድ ለተገኘው ዕድገትና ጨቅላውን የክርስቲያን ጉባኤ ለመገንባት አስተዋጽኦ ካደረጉት “ስጦታዎች” አንዱ ነበር።—1 ቆሮንቶስ 12:7-11፤ 14:24-26
በመጀመሪያው መቶ ዘመን በልሳን መናገርን ጨምሮ ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ አሠራሮች አምላክ ከዚያ ወዲህ የ1,500 ዓመት ዕድሜ የነበረውን የእሥራኤል ጉባኤ እንደ ልዩ ሕዝብ አድርጎ የሚጠቀምባቸው አለመሆኑን የሚያስረዱ በዓይን ተጨባጭ የሚታዩ ማስረጃዎች ነበሩ። ሞገሱ ያለው በአንድያ ልጁ አማካኝነት ወደ ተቋቋመው አዲሱ የክርስቲያን ጉባኤ መዛወሩ አጠያያቂ አልነበረም።—ከዕብራውያን 2:2-4 ጋር አወዳድሩ።
እነዚህ የመንፈስ መግለጫዎች ጨቅላው የክርስቲያን ጉባኤ እንዲመሠረትና ወደ ጉልምስና እንዲያድግ ለመርዳት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ነበሩ። እነዚህ ተአምራዊ ስጦታዎች ዓላማቸውን ከፈጸሙ በኋላ እንደሚያቆሙ ጳውሎስ “ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፣ ልሳኖችም ቢሆኑ ይቀራሉ” በማለት ገልጿል።—1 ቆሮንቶስ 13:8
አዎን፣ የልሳን ስጦታ እንደሚቀር መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። ግን መቼ? ሥራ 8:18 የመንፈስ ስጦታዎች የሚገኙት “በሐዋርያት እጅ መጫን አማካኝነት” እንደነበረ ይናገራል። እንግዲያውስ የመጨረሻው ሐዋርያ ሲሞት በልሳን መናገርን ጨምሮ የመንፈስ ስጦታ መተላለፍ እንደሚያቆም ግልጽ ነው። ስለዚህ እነዚህን ስጦታዎች ከሐዋርያት እጅ የተቀበሉት ሰዎች ከምድራዊ መድረክ ሲያልፉ ወይም ሲሞቱ ተአምራዊው ስጦታ ያቆማል። እስከዚያ ድረስ የክርስቲያን ጉባኤ በጥሩ ሁኔታ እንዲመሠረት ጊዜ ሊኖረውና በብዙ አገሮችም ለመሠራጨት ይችል ነበር።
“የማይታወቁ ልሳናት” እና ትርጉማቸው
የዘመናችንን በልሳን መናገር ማንሰራራት “በአንዳንዶች እንደ ተለዋዋጭ የወረት ትርኢቶች ማሳያ ስሜታዊ ማጋነን ተደርጎ ሲታይ ሌሎች ደግሞ በሐዋርያት ዘመን ከነበረው በልሳን መናገር ጋር አንድ አድርገው ይመለከቱታል።” “በማይታወቅ ልሳን” መናገር በሚፈጸምባቸው ዘመናዊ የቤተ ክርስቲያን ስብሰባዎች በልሳን መናገር አብዛኛውን ጊዜ በስሜት ፍንደቃ ትርጉም የሌላቸውን ድምፆች መደንፋት ያለበት ነው። ይህም በመሆኑ አንድ ሰው “በልሳን መናገርን ብዙ ጊዜ የምጠቀምበት በግሌ ለማሰላሰል ብዬ ነው። . . . በሌሎች ሰዎች ፊት ግን ትንሽ ያሳፍረኛል” በማለት የእምነት ቃሉን ሰጥቷል። ሌላ ሰውም “የራሴን ቃላት እሰማለሁ፣ ግን ምን እንደምል አላውቅም፤ ሆኖም አንደበቴ እንዲናገር መገፋፋቱን ሲቀጥል ይታወቀኛል” በማለት ተናግሯል።
በእንዲህ ዓይነቶቹ የማይታወቁ ልሳናት በመናገር እውነተኛ ጥቅም ያለው ምን መልእክት ይተላለፋል? ስለ ንግግሩ ፍቺስ ምን ሊባል ይችላል? እንዲህ ዓይነቱን ንግግር እንፈታለን የሚሉ ሰዎች ትርጉም የማይሰጠውን ያንኑ አንድ ንግግር የተለያየ ፍቺ ይሰጡታል። ለምን እንዲህ ሆነ? ለእንዲህ ዓይነቱ ልዩነት የሚሰጡት ማብራሪያ “ለአንድ ንግግር አምላክ ለአንዱ ሰው አንድ ፍቺ ሲሰጠው ለሌላው ደግሞ ሌላ ፍቺ ይሰጠዋል” የሚል ነው። አንድ ግለሰብ “ፍቺው ትክክል ያልሆነባቸውን ወቅቶች አስተውያለሁ” ሲል አምኖ ተቀብሏል። ዲ. ኤ. ሀይስ የልሳን ስጦታ በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ አንድ ሰው በማይታወቅ ቋንቋ የተናገረች የአንዲት ሴት ንግግር “ቋንቋው በጣም ብልግና የተሞላበት ስለነበር” አልተረጉምም ብሎ እምቢ እንዳለ አመልክተው ነበር። ይህስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በእርግጥ ጉባኤውን ለማነፅ አገልግሎ ከነበረው በልሳን መናገር ምንኛ የተለየ ነው!—1 ቆሮንቶስ 14:4-6, 12, 18
በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ግሩም የሆነ ፍቺ ሲሰጥ እንደሰሙ ይናገራሉ። ስለዚህ አምላክ በእርግጥ “ለሰዎች ቀጥተኛ መልእክት ለመስጠት ሲፈልግ” በዚህ ስጦታ ይጠቀማል ብለው ከልባቸው ያምኑ ይሆናል። ይሁን እንጂ በልሳን የሚነገር መልእክት ያስፈለገን ኢየሱስና ሐዋርያቱ ያልሰጡን ምን መልእክት ቀርቶ ነው? ይህ በልሳን የመናገር የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የነበረው ጳውሎስ ራሱ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሳጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” ብሏል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
ሐቁ የክርስቲያን ጉባኤ በአሁኑ ጊዜ በጨቅላነት ደረጃ ላይ ያለመሆኑና በዚህም ምክንያት ጉባኤው ያለውን ሚና ለማረጋገጥ መለኮታዊ ራእዮች ወይም ተአምራዊ የመንፈስ ስጦታዎች የማያስፈልጉ መሆናቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን” በማለት ያስጠነቅቃል።—ገላትያ 1:8
ተአምራዊ በልሳን መናገር ዛሬ አስፈላጊ አይደለም። በዛሬው ጊዜ የእውነተኛው ክርስትና ክፍል መሆኑን ለማመንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለም። ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ የተሟላና ሁሉም የሚያገኘው በመሆኑ የሚያስፈልገን ሁሉ በአምላክ ቃል ውስጥ አለልን። እርሱም ስለ ይሖዋና ስለ ልጁ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሰውን ትክክለኛ እውቀት እንድናገኝ ያበቃናል።—ዮሐንስ 17:3፤ ራእይ 22:18, 19
በመጀመሪያው መቶ ዘመንም እንኳን ሐዋርያው ጳውሎስ የልሳን ስጦታ ለቀድሞ ክርስቲያኖች ስለተሰጠበት ምክንያት አመለካከታቸውን ለማረም በቆሮንቶስ ለነበረው ጉባኤ ለመጻፍ ተገድዶ ነበር። አንዳንድ ክርስቲያኖች በልሳን ስጦታ በጣም የተመሰጡ የነበሩ ይመስላል። ስለዚህ በመንፈሳዊ እንዳልበሰሉ የሚያሳይ የሕፃናት ሥራ ይሠሩ ነበር። ለ“ልሳን” ከልክ ያለፈ ግምት ተሰጥቶት ነበር። (1 ቆሮንቶስ 14:1-39) ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ሁሉም በተአምራዊ ልሳናት እንደማይናገሩ አጥብቆ ገልጿል። ለመዳናቸውም አስፈላጊ አልነበረም። በልሳን መናገር ይቻል በነበረበት በዚያ ጊዜም እንኳን የልሳን ስጦታ ከተአምራዊ ትንቢት የመናገር ስጦታ በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ነበር። በልሳን መናገር ክርስቲያኖች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ የሚያስፈልግ መሥፈርት አልነበረም፣ አይደለምም።—1 ቆሮንቶስ 12:29, 30፤ 14:4, 5
በአሁኑ ጊዜ ካለው በማይታወቅ ልሳን መናገር በስተጀርባ ያለው ኃይል
ከዛሬዎቹ የልሳን ተናጋሪዎች በስተጀርባ ሆኖ የሚገፋቸው ኃይል ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ሲባል ልዩ ስጦታ የተሰጣቸው ናቸው ተብለው የሚታመኑ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የመንጎቻቸው አባሎች ይህን ችሎታ እንዲያገኙ ስለሚገፋፉ ነው ብለው የሚያምኑ አንዳንድ ሰዎች አሉ። በአንዳንድ ረገድም በልሳን መናገር የሚመጣው በስሜታዊነትና የአእምሮን ሚዛን በማጣት ነው። ሲሪል ጂ. ዊሊያምስ የመንፈስ ልሳናት በተሰኘ መጽሐፋቸው “በብዙ ረገድ በቡድኑ ውስጥ የቁንጮነት ዓርማ” ወይም ምልክት እንደሆነና “በልሳን ለሚናገሩትም በቡድኑ ዓይንና በራሳቸውም ዓይን ክብርና ሥልጣን” እንደሚሰጣቸው ይናገራሉ። ስለዚህ ግፊቱ የሚመነጨው በማይታወቅ ልሳን ከሚናገሩ ምርጥ ሰዎች ቡድን መሃል ከመቆጠር ምኞት የተነሳ ሊሆን ይችላል።
ከዚህም ሌላ የሎዮላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶናልድ ፒ. ሜሪፊልድ “በልሳን መናገር በኃይለኛ የደስታ ወይም የፍርሃት ስሜት ምክንያት የሚመጣ ተሞክሮ ሊሆን ይችላል፣ ወይም እንደ አንዳንዶቹ አስተሳሰብ ዲያብሎሳዊም ሊሆን ይችላል” በማለት ይጠቁማሉ። ካህን ቶድ ኤች. ፋስት “ልሳን አከራካሪ ነው። ዲያብሎስ እኛን የሚያታልልበት ብዙ መንገዶች አሉት” በማለት ተናግረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱም ሰይጣንና አጋንንቱ በሰዎች ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩና ንግግራቸውን ሊቆጣጠሩ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃል። (ሥራ 16:17, 18) ኢየሱስ አንድን ሰው እንዲጮኽና መሬት ላይ እንዲወድቅ ያደረገ የአጋንንት መንፈስን ገስጿል። (ሉቃስ 4:33-35) ‘ሰይጣን የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን እንደሚለውጥ’ ጳውሎስ አስጠንቅቋል። (2 ቆሮንቶስ 11:14) በአሁኑ ጊዜ አምላክ ለሕዝቡ ያልሰጠውን የልሳን ስጦታ የሚሹ ሰዎች “ተአምራትን፣ ምልክቶችንና ሐሰተኛ ድንቆችን” እንደሚጠቀም ማስጠንቀቂያ ለተሰጠን ለሰይጣን ማታለያ ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ።—2 ተሰሎንቄ 2:9, 10
ልሳናትና እውነተኛው የክርስትና እምነት
በልሳን የመናገርን ስጦታ የተቀበሉ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የአምላክን ታላቅ ሥራ ለማስረዳት ተጠቅመውበታል። ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው የተላለፈውን መልእክት ሁሉም እንዲያስተውሉትና ብዙዎች የሚነቃቁበትን ውጤት ያስገኝ ዘንድ በልሳን የተላለፈውን መልእክት በግልጽ ለመተርጎሙ አስፈላጊነት ነበር። (1 ቆሮንቶስ 14:26-33) ጳውሎስ “እንዲሁ እናንተ ደግሞ የተገለጠውን ቃል በአንደበት ባትናገሩ ሰዎች የምትናገሩትን እንዴት አድርገው ያስተውሉታል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁና” በማለት አስጠንቅቋል።—1 ቆሮንቶስ 14:9
የአምላክ መንፈስ ለቀድሞ ክርስቲያኖች በልሳን የመናገርን ስጦታ የሰጣቸው ሲሆን ትርጉም የሌላቸው ወይም ሊተረጎሙ የማይችሉ ጫጫታዎችን እንዲናገሩ አላደረጋቸውም። ከሐዋርያው ጳውሎስ ምክር ጋር በመስማማት መንፈስ ቅዱስ የምሥራቹ በከፍተኛ ፍጥነት “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ” እንዲሆን ያስቻለ ንግግርን ሰጥቷቸዋል።—ቆላስይስ 1:23
የአሁኑን ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች በተመለከተ ኢየሱስ ክርስቶስ “አስቀድሞም [የተቋቋመችው መንግሥት] ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል” በማለት አዟል። (ማርቆስ 13:10) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደሆነው ሁሉ ዛሬም የመንግሥቱን መልእክት ሁሉም ፍጥረት መስማት አለበት። ይህም የሚቻለው ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉም ይሁን በከፊል ወደ 2,000 በሚጠጉ ቋንቋዎች ስለተተረጎመ ነው። የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች በድፍረትና በብርታት እንዲናገሩ ያነቃቃቸው ያው መንፈስ ዘመናዊ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች የሚያደርጉትን ታላቅና አስደናቂ የስብከት ሥራ እየደገፈው ነው። በአፍ በሚነገር ቃልና ቅዱስ ጽሑፋዊውን እውነት በታተሙ ገጾች ለሁሉም ለማዳረስ ዘመናዊውን የሕትመት ቴክኖሎጂ በመጠቀም “ንጹሑን ልሳን” ይናገራሉ። ይህ መልእክት ከ200 በላይ ወደሆኑ አገሮችና ደሴቶች እየተዳረሰ ነው። የአምላክን ታላቅ ሥራ ለሁሉም እንዲያሳውቁ በአምላክ መንፈስ እየተነቃቁ ያሉት ሕዝቦች የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው።—ሶፎንያስ 3:9፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:13
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ፎቶዎች]
ከቤት ወደ ቤት ምስክርነት በጃፓን
ከመርከብ ወደ መርከብ ስብከት በኮሎምቢያ
ከታች፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በጓቴማላ
ከሥር፦ በገጠር ምስክርነት ሲሰጥ በኔዘርላንድስ