የስብከቱ ሥራ በሞዛምቢክ ማራኪ ዋና ከተማ በማፑቶ
በ1991 የይሖዋ ምሥክሮች በሞዛምቢክ ሕጋዊ ዕውቅና ተሰጣቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአምላክ መንግሥት ምሥራች ስብከት ደቡባዊ ጠረፍ ላይ በምትገኘው በዚች ሞቃት አገር በጣም አስደናቂ ዕድገት ሲያደርግ ቆይቷል። ቀጥሎ ያለው ታሪክ የይሖዋ ምሥክሮች በሞዛምቢክ በተለይም ዋና ከተማዋ በሆነችው በማፑቶ አካባቢ መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራቸውን እንዴት በማካሄድ ላይ እንዳሉ የሚገልጽ ነው።
የሞዛምቢክ የአየር ጠባይ የሕንድ ውቅያኖስ ሙቀት ተጽእኖ ስለሚያደርግበት አገሪቱ ለስላሳ የአየር ጠባይ እንድታገኝ አድርጓታል። በባሕር ዳርቻው ላይ ጠርዝ ጠርዙን የተዋቡ የዘንባባ ዛፎችና የዓለት ጉብታዎች ሞልተዋል። የተንጣለለ ውኃ ያለበት ባሕረ ሰላጤ ወደ አገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ገባ ብሎ ይገኛል፤ ይህም ለዋና ከተማዋ ለማፑቶ ተስማሚ አቀማመጥ ሆኖላታል።
ይሁን እንጂ የዚህች አገር ውበትና ሰላም በዓመፅ የጎደፈውን ታሪኳን ይሸፍኑታል። ሞዛምቢክ በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት በባዕድ ግዛት ሥር መጀመሪያ ዐረቦችን፣ በኋላም ፖርቱጋልን ታግላለች። ፖርቱጋሎች የአገሪቱን ሀብት ይኸውም የዝሆን ጥርስ፣ ወርቅና ባሪያዎችን ለመዝረፍ የመጡት ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሙሉ ቡራኬ አግኝተው ነበር። በቅኝ ተገዥነት ጭቆና በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ከቆየች በኋላ በመጨረሻው በ1975 ለአገሪቱ ነፃነት ያስገኘ መራራ የውስጥ ትግል ፈነዳ። ክፋቱ አገሪቱ ለሕዝቡ በተለይም ለንጹሐኑ የገጠር ሕዝብ ብዙ ሥቃይ ያስከተለ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ በመውደቋ የተገኘው ለውጥ ሕይወትን ይበልጥ አስተማማኝ አላደረገውም።
ዋና ከተማዋ ማፑቶ
ባለፈው አሥር ዓመት ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ ሞዛምቢካውያን አንፃራዊ ደህንነት ወደሚገኝባቸው ትናንሽና ትላልቅ ከተሞች ሸሽተዋል። ይህም የሕዝብ ሽሽት በተለይ የፖርቱጋል ጥንታዊ የሕንፃ ጥበብና በቀለማት ያሸበረቀችው አፍሪካ ተቀላቅለው ለከተማዋ ውበቱ የሚያስተጋባ ሁኔታ በሚሰጡባት በማፑቶ ጎልቶ ይታያል። በሠፋፊዎቹና ዛፎች በተርታ በተተከለባቸው በዛሬዋ ማፑቶ አደባባዮች ስትንሸራሸሩ መጀመሪያ የምታስተውሉት ወደየዕለቱ ተግባራቸው የሚጣደፉትን ብዙ ሕዝብ ነው። ይሁን እንጂ ከሌሎች አገሮች ሕዝብ ጥድፊያ ልዩነት አለው። “የየዕለቱ ኑሮ መጨናነቅና ችግር ቢኖርበትም ሕዝቡ ምን ጊዜም በፈገግታ ለመቀበል ዝግጁ ነው” ይላል በማፑቶ የሚያገለግለው ሚሲዮናዊው ሮድሪጎ። “ለሌላው አክብሮት የማያሳዩ ሰዎች እምብዛም አታገኙም!” አዎን፣ ሞዛምቢካውያን ተባባሪና ወዳጅነት የሚያሳዩ በመሆን የሚታወቁ ሕዝቦች ናቸው።
በእርግጥ እንደ ብዙዎቹ የአፍሪቃ አገሮች በሞዛምቢክም ሰዎች የሚገኙበት የተለመደ ቦታ ገበያ ነው። ከገበያው ቦታ ለመድረስም በቻፓ 100 ተሳፍሮ መሄድ ይቻላል። ቻፓ 100 ለሕዝብ መጓጓዣነት የሚያገለግሉ እዚህ ውይይት ተብለው እንደሚጠሩት ያሉ መኪኖች ስም ነው። እንደተለመደው በቻፓ 100 ከሚሳፈሩት ውስጥ የሚበዙቱ ወደ መጓጓዣው ጭነት መኪና ውስጥ ከመግባት ይልቅ ከበስተ ውጭ ተንጠልጥለው የሚሄዱ ይመስላል። ምናልባት በእግር መሄድ ሳይሻል አይቀርም።
ሞዛምቢካውያን የማይሰለቹ ከባድ የንግድ አካሂያጆች ናቸው። ማፑቶን የሚጎበኝ ሰው ምን ያህል ብዙ ሕዝብ አነስተኛ መደብሮችን በጥርጊያ መንገዶችና በመንገድ ማዕዘኖች ላይ በማቋቋም ለራሳቸው ሥራ እንደፈጠሩ ሳያስተውል ሊቀር አይችልም። ትኩስ ፍራፍሬ፣ አትክልቶች፣ ቅጠላ ቅጠሎች፣ ወይም ቅመሞች መግዛት ትፈልጋላችሁን? ተዘዋውራችሁ ልታዩት የምትችሉት ብዙ ነገር አለ። ያልታረዱ ዶሮዎች፣ ኦቾሎኒ፣ ወይም ቤታችሁን የምትሠሩበት ሸምበቆ ትፈልጋላችሁን? ምንም ችግር የለም፣ ሁሉም ነገር በወዳጅነት መንፈስ ይሸጥላችኋል። ጫማችሁን ማስጠረግ ወይም መኪናችሁን ማሳጠብም ቢሆን ይደረግላችኋል። እንዲያውም አንድ ትንሽ ልጅ በጋለ ብረት ተጠቅሞ በጣም ውድ የሆነ ሰነዶቻችሁን ሊያሽግላችሁ ይችላል።
እንደ እውነቱ ከሆነ የመንገድ ላይ ንግድ ሁሉ ሕጋዊ አይደለም። ያም ሆነ ይህ ግን ይደረጋል። ይህን ፈላጊ እያሉ የሚጮኹ ሱቅ በደረቴዎች ዱምባ ኒንጌ ተብለው ይጠራሉ፤ ትርጉሙም “እግሬ አውጪኝ” ማለት ነው። ይህን ስያሜ ያገኙበትም ምክንያት ባለሥልጣኖች ለመቆጣጠር ብቅ ሲሉ አደገኛውን ንግዳቸውን ለማዳን የእግሬ አውጪኝ ሩጫ ስለሚያስፈልግ መሆኑ አያጠራጥርም።
ከሽታው ለመረዳት እንደሚቻለው ወደ ዓሣ ተራ ቀርበን መሆን አለበት! በየቀኑ ወደ ምሽቱ አካባቢ በኮስታ ዶ ሶል የባሕር ዳርቻ ላይ የዓሣ አጥማጆች ጀልባዎች በዕለቱ ያጠመዱትን ዓሣ ሲያመጡ በደራ ገበያ ይከበባሉ። ሁሉም ዓይነት ቅርጽና መጠን ካላቸው ዓሦች በተጨማሪ ሸርጣን ዓሦች፣ ሎብስተር የሚባል የባሕር ፍጥረትና ፕሮንስ የሚባሉ የሞዛምቢክ ታዋቂ ባለእግር የባሕር ፍጥረቶች አሉ። ይሁን እንጂ በማፑቶ ውስጥና ዙሪያ እየተካሄደ ስላለው ሌላ ዓይነት የዓሣ ማጥመድ ሥራ ለማወቅ ትፈልጉ ይሆናል።
“ሰዎችን አጥማጆች”
የይሖዋ ምሥክሮች በሞዛምቢክ ሕጋዊ ዕውቅና ካገኙ ወዲህ ከሕዝቡ ጥሩ ምላሽ አግኝተዋል። አንድ ሰው “ሎንዶን ሳለሁ እናንተን [የይሖዋ ምሥክሮችን] በመንገድ ላይ በብዛት አገኛችሁ ነበር። እንዲያውም በደረስኩበት ቦታ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችን አይቻለሁ። አሁን እዚህም ሳገኛችሁ ደስ ይለኛል” በማለት አድናቆቱን ገለጿል።
የአካባቢው መነጋገሪያ በሆኑት በፖርቱጋልና በሶንጋ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን መቀበላቸው እንደሚያመለክተው ሕዝቡ በእርግጥ መንፈሳዊ ዝንባሌ ያለው መሆኑን ነው። ፓውላ የምትባል ሌላዋ ሚሲዮናዊት በባዛር ወይም በማዕከላዊው ገበያ ቅዳሜ ቅዳሜ ጧት በአማካይ ከ50 በላይ መጽሔቶችን ማበርከት እንደሚቻል ሪፖርት አድርጋለች። የወጣቶች ጥያቄና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶቻቸው የተሰኘው መጽሐፍ በተለይ በጣም ታዋቂ እየሆነ ነው። ብዙ ወጣት ሰዎች በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወይም ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ስለሆኑ ይህ መጽሐፍ የሚሰጠውን ምክር አመራር ያደነቁ ይመስላል።
አንድ ሰው ሲናገር ግልጽነት ባለው የአፍሪካ ባሕል መሠረት ብዙ ቁጥር ያላቸው ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች የሚነገረውን ለመስማት በሚሲዮናዊው ዙሪያ ይሰበሰባሉ። እንዲህ ዓይነት የመንገድ ዳር ስብሰባዎች አብዛኛውን ጊዜ አስደሳች ወደሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት ያድጋሉ። አንዲት እህት የሚከተለው አስደሳች ተሞክሮ ትዝ ይላታል፦
“በአንድ ወቅት የመንገድ ላይ ምሥክርነት ስሰጥ አንድ የወታደር ጂፕ መኪና በአቅራቢያዬ ሲጢጥ ብሎ ሲቆም ፈርቼ ነበር። አንድ ወጣት ወታደር በአካባቢው ወደ ቆሙት ሰዎች ጮኾ ‘እናንተ እዚያ ያላችሁት፣ ያችን ሴት ነይ በሏት’ አላቸው። ወደ እርሱ ስሄድ ወታደሩ ፈገግታ በተላበሰ ፊት ‘እናንተ ጥሩ ሰዎች ናችሁ። እዚህ ስናያችሁ ደስ ይለናል። ወጣት ሰዎችን የሚመለከት መጽሐፍ አላችሁ ብዬ አምናለሁ። እኔም አንድ ባገኝ እወዳለሁ’ አለኝ። እኔም ምንም እንደሌለኝ ነገርኩትና ሳገኝ ግን እቤቱ ድረስ እንደምወስድለት አረጋገጥኩለት።”
ጽሑፎችን ከዴፖ መበተን
እየጨመረ የሚሄደውን የጽሑፍ ፍላጎት ለማሟላት የደቡብ አፍሪካ የመጠበቂያ ግንብ ቅርንጫፍ ቢሮ በማፑቶ ላለው ዴፖ ጽሑፎችን በየሁለት ሳምንቱ ያቀርብለታል። ዴፖውን የሚቆጣጠረውና የጽሑፎችን ሥርጭት በማደራጀቱ ሥራ ኃላፊ የሆነው ማኑኤል የሚባል ሚሲዮናዊ ነው።
አንድ ቀን ጠዋት መካከለኛ ዕድሜ ያለው ሰው ጎራ አለና ቦታው ለምን ዓላማ እንደሚያገለግል ጠየቀ። ማኑኤልም ቦታው የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች ዴፖ መሆኑን ነገረው። ሰውየው ወጥቶ ከሄደ በኋላ ወዲያው በደቂቃ ውስጥ ተመልሶ መጣ።
“እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ናቸው ብለኸኛል፣ አይደል?” ብሎ ጠየቀ።
“አዎን፣ ልክ ነው” ብሎ ማኑኤል መለሰ።
ሰውየውም “ይህ የየትኛው ድርጅት ነው?” ብሎ ጠየቀ።
“የይሖዋ ምሥክሮች” በማለት ማኑኤል መልስ ሰጠና ጨምሮም “ለአካባቢው ጉባኤዎች ይህን ጽሑፍ እናቀርባለን” አለው።
“እንዴ! የይሖዋ ምሥክሮች!” አለና ሰውየው ፊቱ በራ። “እናንተን የምወድበት ብዙ ነገር አለ። የዚያኑ ያህል ግን የማልወድላችሁ አንድ ነገር አለ።”
“የሚወዱን ስለምን ይሆን?” ብሎ ማኑኤል በብልሃት ጠየቀ።
“የምታወጧቸውን አስደሳችና ዕውቀት ሰጪ መጻሕፍት እወዳለሁ” አለ ሰውየው ሲያስረዳ። “የማልወድላችሁ ነገር ደግሞ ጽሑፎቻችሁን በብዛት ማግኘት ስለማልችል ነው። እዚህ ማፑቶ ያለን ሰዎች የእናንተን የመሰሉ ጽሑፎች ምን ያህል እንደምንራብ ልትገምቱ አትችሉም።” ከዚያም ያመለጡትን ያለፉ የመጠበቂያ ግንብና የንቁ! መጽሔት እትሞችን ጨምሮ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተጻፉትን የመጽሐፍ ዝርዝር አወጣ።
“ይህን ዝርዝር ሁልጊዜ ይዤው እዞራለሁ” አለ ሰውየው ለማኑኤል ሲነግረው። “ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስገናኝ ያላቸውን ማንኛውንም ጽሑፍ ለማግኘት እሞክራለሁ። በዝርዝሬ ላይ ያሉትን ጽሑፎች እንዳገኝ ልትረዳኝ ከቻልክ የወርቅ ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ ነኝ።”
ውይይት ተከተለ። ሰውየው መጀመሪያ ከይሖዋ ምስክሮች ጋር የተገናኘው በ1950ዎቹ ውስጥ እንደነበረና ፍጥረት የተባለውን መጽሐፍ እንዳነበበ ማኑኤል ተረዳ። የይሖዋ ምስክሮች ሥራ በፖርቱጋል መንግሥት ከታገደ በኋላ ግን እምብዛም መራመድ አልቻሉም ነበር።
ከዚያ በኋላ ማኑኤል ሰውየውን ወደ ቢሮው ሄዶ ሲጠይቀው የነበሩት የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች በሙሉ በፕላስቲክ ተሸፍነውና በንጽሕና እንደተቀመጡ አስተዋለ። ማኑኤልም ሰውየው ስብስቦቹን ለማሟላት የፈለጋቸውን ጽሑፎች ሰጠውና ከሰውየውና ከቤተሰቡ ጋር የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ዝግጅት አደረገ።
ይህ ሁሉ መንፈሳዊ ተከላና ማጠጣት አምላክ “ማሳደጉን” ስለቀጠለ ብዙ ፍሬ መስጠት ጀምሯል። በሞዛምቢክ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች የማምረቱ ሥራ ከፍተኛ ሰብል እንደሚያስገኝ የሚያሳዩ ግልጽ ምልክቶች አሉ! 1 ቆሮንቶስ 3:6፤ ዮሐንስ 4:36
እንቅፋቶች ቢኖሩም ቲኦክራቲካዊ ዕድገቶችን ማድረግ
በአሁኑ ጊዜ በማፑቶ ከተማና በአካባቢዋ ከ50 የሚበልጡ ጉባኤዎች አሉ። ይሁን እንጂ አንድም የይሖዋ ምስክሮች የመንግሥት አዳራሽ አይገኝም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አንዳንዶቹ ጉባኤዎች ለበርካታ ዓመታት የመሬት ይዞታ ቢኖራቸውም በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ሊሠሩ አልቻሉም።a
ሆኖም እንዲህ ዓይነቶቹ እንቅፋቶች እድገቱን አልገቱትም። በአሁኑ ጊዜ በሞዛምቢክ ደቡባዊ ክፍል ከ5,000 በላይ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እየተመሩ ነው። ጥናት እንዲደረግላቸው የሚጠይቁት ሰዎች ቁጥር በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ይህን ለማሟላት አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች እየተጠየቁ ነው። አንድ ሰው ጥናት እንዲመራለት ከጠየቀ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች መገኘት ያለበት መሆኑ የታወቀ ነው።
በአንድ ረባዳ ቦታ የሚገኝ አንድ ጉባኤ ያሉት የምሥራቹ አስፋፊዎች ቁጥር 71 ብቻ ቢሆኑም በቅርቡ ባደረገው የእሁድ ዕለት ስብሰባው ላይ 189 ሰዎች ተገኝተው ነበር። ይህ ታላቅ ቡድን የሚሰበሰበው በአንድ ቤት አጥር ግቢ ውስጥ እደጅ ነው። ከእያንዳንዱ ስብሰባ በፊት ግቢው በደንብ ይጠረግና ብዙ ትላልቅ ሰዎችን ጨምሮ የሚበዛው ተሰብሳቢ የሚቀመጠው መሬት ላይ በተነጠፈ የሸምበቆ ሰሌን ላይ ነው። ታዲያ ፕሮግራሙን የሚከታተሉት እንዴት ባለ የተመስጦ ትኩረት ነው! ብዙ አዳዲስ ተሰብሳቢዎች የመጠበቂያ ግንብ ጥናቱን ለመከታተል መጽሔቱ ስለሌላቸው ሲነበብ በጥሞና ማዳመጥን ይማራሉ፣ ከዚያም ጥናቱን የሚመራው ወንድም የሚጠይቀውን ጥያቄ ለመመለስ አብዛኞቹ እጆች ይነሳሉ።
59 አስፋፊዎች ያሉት ሌላው ጉባኤ ዘወትር ከ140 በላይ ተሰብሳቢዎች አሉት። አብዛኛውን ጊዜ የሚሰበሰቡት በረንዳ ላይ ነው። በዝናባማው ወቅት ግን በጠባቧ አፓርትማ ሁለት ትናንሽ ክፍሎች ታምቀው ይሰበሰባሉ። ሞልቶ የሚተርፈው ተሰብሳቢ በመተላለፊያዎች፣ በወጥ ቤቱና በፎቁ ሰገነት ላይ ይፈስሳሉ። አሁንም እንደገና አንድ ሰው ይህን ሁሉ ሲያይ ፕሮግራሙን በጥሞና የሚከታተሉትን ብዙ ወጣቶችን ጨምሮ የሁሉንም ሰው አድናቆትና አትኩሮት ሳያስተውል ሊያልፍ አይችልም።
በሞዛምቢክ ለወደፊቱ ሠፊ ዕድገት መኖሩ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የታየውን ያህል የትም ቦታ አልታየም። በቅርቡ በመሃል ከተማው የቀድሞ የኮርማ ውጊያ (ቡል ፋይት) ግቢ ውስጥ የክልል ስብሰባ ተደርጎ ነበር። ከ10,000 በላይ የሆኑ ሰዎች በስብሰባው ላይ ሲገኙ ወደ 3,000 የሚጠጉት አስፋፊዎች ምን ያህል እንደተገረሙ ልትገምቱ ትችላላችሁን?
“መከሩ ብዙ ነው”
እነዚህ ተሞክሮዎች በግልጽ የሚያመለክቱት በሞዛምቢክ ብዙ የሚሠራ ነገር መኖሩን ነው። አንዳንድ ጉባኤዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ከቅርንጫፍ ቢሮው በተላከ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ጉብኝት የተደረገላቸው ገና በቅርቡ ነው። ተገቢ የሆኑ ድርጅታዊ አሠራሮችን በጉባኤው ውስጥ በሥራ ላይ እንዲያውሉ ለመርዳት አስፈላጊ የሆነውን ብዙ እርዳታ እየተቀበሉ ነው።
ጉባኤዎቹ በቅርቡ የጊልያድ ሚሲዮናውያን በመምጣታቸው በጣም ተደስተዋል። ፍራንሲስኮ የሚባል አንድ የማፑቶ ሽማግሌ “ይህ ለእኛ ትልቅ እርዳታ ነው። ቅንዓቱ አለን። ፍቅሩም አለን። ሆኖም ከብዙ ድርጅታዊ ጉዳዮች ጋር ሳንገናኝ ቆይተናል። በእርግጥ የሚያስፈልገን ነገሮች እንዴት መሠራት እንዳለባቸው የሚያስተምረን ከምንጩ የተገኘ ተሞክሮ ያለው ሰው ነው። አሁን ሚሲዮናውያን ከእኛ ጋር በመኖራቸው በጣም ደስ ይለናል” በማለት ተናግሯል።
ሚሲዮናውያኑም በበኩላቸው ወንድሞቻቸውን ለማገልገል በመቻላቸው ደስ ብሏቸዋል። በብራዚል ለ20 ዓመታት ካገለገለ በኋላ በቅርቡ በሞዛምቢክ የተመደበው ሀንስ የሚሲዮናውያኑን ደስታ እንደሚከተለው በማለት አጠቃሎታል፦ “በሞዛምቢካዊው መስክ መሥራት ታላቅ መብት ነው! በጣም ከፍተኛ ጭማሪ በሚገኝበት ቦታ ላይ እንዳለን ይሰማናል። ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ። ሥራው በማፑቶ ብቻ 10 ወይም 20 ሚሲዮናውያን እንዲመደቡልን የሚያስችል ነው።”
አሁን በሞዛምቢክ ፍጥነት እየጨመረ ያለው ዕድገት “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” በማለት የተናገራቸውን የኢየሱስን ቃላት ያስታውሱናል። (ማቴዎስ 9:37, 38) ይሖዋ በሞዛምቢክ ስላሉት አገልጋዮቹ የሚቀርበውን ይህን አስቸኳይ ልመና መልስ እንደሚሰጠው ለማመን በቂ ምክንያት አለ።
በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምስክሮች በሰሜን ምዕራብ ሞዛምቢክ በሚገኙ የግዞት ማዕከሎች 12 ወይም ከዚያ በላይ ዓመታት አሳልፈዋል። አንዳንዶቹ በቅርቡ ወደ ማፑቶ ሲመለሱ የነበራቸው ንብረት ያገለደሙት ቁራጭ ጨርቅ ብቻ ነበር። በብዛት የነበራቸው እምነት ነበር! በአካባቢው በሚገኙ አገሮች ካሉ መሰል ክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የተላከላቸው ብዙ የምግብና ልብስ መዋጮ ለኑሮአቸው አዲስ ጅምር እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እዚህ አገር አንድ ሰው ሥራ ለማግኘት ከታደለ አማካይ ደመወዙ በየወሩ ከ20 እስከ 30 የአሜሪካ ዶላር ድረስ ነው።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጉባኤዎች ሁልጊዜ ቅዳሜ ጧት በሚያደርጉት ክርስቲያናዊ ምሥክርነት ብዙ አስፋፊዎች ይመጡላቸዋል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የ5 ዓመት ዕድሜ ያለውን ጃሚቶን ተመልከቱት። የተወለደው በእስር ቤት ነው። ዛሬ ወላጆቹ ወደ ማፑቶ በመመለሳቸው ደስተኞች ናቸው። የጃሚቶ አባት ፍራንሲስኮ መላውን ቤተሰብ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በየሳምንቱ አንድ ላይ ይሰበስባቸዋል። ሁለቱም ወላጆች ልጆቻቸው በመስክ አገልግሎት ውጤታማ አስተማሪዎች እንዲሆኑ ለማለማመድ ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ። ጃሚቶ በማዕከላዊው የገበያ ሥፍራ ጽሑፎችን ማበርከት ደስ ይለዋል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጉባኤዎች የሚሰበሰቡበት የመንግሥት አዳራሾች የሌላቸው መሆኑ ዕድገታቸውን አያቆመውም። በአብዛኞቹ ጉባኤዎች ከአስፋፊዎች ቁጥር በላይ የሚሆኑ ሰዎች በስብሰባዎቹ ይገኛሉ።