የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 10/1 ገጽ 24-25
  • በዓለም እንደ ብርሃን ማብራት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በዓለም እንደ ብርሃን ማብራት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • የአቅኚነት ትምህርት ቤት በማዕከላዊው አፍሪካ ሪፑብሊክ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 10/1 ገጽ 24-25

በዓለም እንደ ብርሃን ማብራት

በሥነ ምግባር ጠማማነትና ብልሽት በተበከለ ዓለም ውስጥ በምድር ዙሪያ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ብርሃን አብሪዎች መሆን አለባቸው። በጨለመው ዓለም ውስጥ ብርሃን ሰጪዎች መሆን ይኖርባቸዋል። (ፊልጵስዩስ 2:15) በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች በመሆን ብርሃናቸውን ለማብራት ፈቃደኞች ሆነዋል። ከእነርሱም የሚበዙት በዚህ አገልግሎት ረዘም ያሉ ዓመታት ያሳለፉና ሁሉም ዓይነት ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ለመሆን በሕይወታቸው ለውጥ ሲያደርጉ የመመልከትን ደስታ ያገኙ ናቸው።—ማቴዎስ 28:19

እነዚህ አቅኚዎች በዚህ ቅዱስ አገልግሎት እንዲቀጥሉ ለማበረታታትና በማስተማር ችሎታቸውም እንዲሻሻሉ ለመርዳት የይሖዋ ምሥክሮች የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት አደራጅቷል። ይህ ትምህርት ቤት አቅኚዎችን በሦስት መስኮች ለመርዳት የተዘጋጀ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የአሥር ቀን ኮርስ ይሰጣል። እነዚህም ሦስት መስኮች የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች በመሆን ከይሖዋ ጋር መመላለስ፣ ለመላው የወንድማማች ማኅበር በሙላት ፍቅር ማሳየት፣ በዓለም እንደ ብርሃን ማብራት ናቸው።

የአቅኚነት ትምህርት ቤት በማዕከላዊው አፍሪካ ሪፑብሊክ

የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ በሆነችው በባንጉዊ በነሐሴ ወር 1991 48 ተማሪዎችና 2 አስተማሪዎች አንድ ላይ ተሰብስበው ነበር። ተማሪዎቹ ለሥራቸው የሚበጁ ትምህርቶችንና ተግባራዊ ሐሳቦችን ለመቀበል ተዘጋጅተው ነበር። ስለ ባንጉዊ ተማሪዎች ምን የሚያስደንቅ ነገር ነበረ?

መጀመሪያ ነገር 21ዱ ተማሪዎች ገና ዓለማዊ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉ ናቸው። በትምህርት ቤት እያሉ የዘወትር አቅኚነትን አገልግሎት ለማግኘት ሲሉ ፕሮግራማቸውን ለማስተካከል ችለው ነበር። የዕረፍት ጊዜያቸውን፣ ከትምህርት ነፃ የሆኑ የሳምንት መጨረሻዎችንና ከሰዓት በኋላዎችን ለመስበክና ለማስተማር ተጠቅመውባቸዋል።

እነዚህ ወጣቶች ፈጣሪያቸውን አሁኑኑ የማገልገልን አስፈላጊነት ተገንዝበዋል። (መክብብ 12:1፤ ከ1 ቆሮንቶስ 7:29 ጋር አወዳድር።) የሚደነቀው ደግሞ ከእነርሱ ውስጥ 12ቱ የማያምኑ ወላጆች የነበራቸው መሆኑ ነው። በቤታቸው ውስጥ ከእነርሱ በስተቀር በእውነት ውስጥ ያለ ሰው የለም። በሥጋ ወንድማማቾች የሆኑ ሁለት ወጣት ወንዶች የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናቸው ምክንያት ወላጆቻቸው ከቤት አባረዋቸዋል። በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወጣት ባልና ሚስት እነዚህ ሁለት ወንዶች ልጆች ከእነርሱ ጋር እንዲኖሩ በቤታቸው ተቀበሉአቸው።

የመካና የሰላሜት ካሌብ ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነበር። ሁለቱም አቅኚዎች ናቸው። ዓለማዊ ትምህርት ይማራሉ። ወላጆቻቸው ግን የይሖዋ ምስክሮች ናቸው። እንዲያውም አባታቸው በዚያው የአቅኚ ተማሪዎች ቡድን ውስጥ ተገኝቶ ከእነርሱ ጋር ይማር ነበር።

በባንጉዊ ያሉ ጉባኤዎች በተለየ መንገድ ይሁን እንጂ በትምህርት ቤቱ ተካፍለዋል። ለአቅኚ ተማሪዎቹ የሚያስፈልጉትን እንደ ምግብ የመሳሰሉ ሥጋዊ ነገሮች አቅርበዋል። ተማሪዎቹን ለመመገብ ገንዘብ፣ ዶሮዎች፣ ስኳር፣ ሩዝና ማኒዮክ ወይም ካሳቫ አዋጥተውላቸው ነበር።

ቀላል እና ጣፋጭ የሆኑ ምግቦችን የሚያዘጋጁ የወጥ ቤት ሠራተኞችም በአካባቢው ጉባኤ ተደራጅተው ነበር። ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ ማንም ሰው የሚያደንቀውን ኤንጉንዛ የሚባል ምግብ በማዘጋጀት የታወቀች ናት። ለምግቡ ዝግጅት የሚያስፈልጉት ነገሮች ምንድን ናቸው? የካሳቫ ቅጠሎች፣ የተምር ዘይት፣ ሽንኩርት፣ ብዙ ነጭ ሽንኩርት፣ ጥቂት የኦቾሎኒ ቅቤና በደንብ እስኪበስል ድረስ መታገሥ ናቸው። እያንዳንዱ ሠራተኛ የራሱ የሆነ ልዩ አዘገጃጀት አለው። እጅ የሚያስቆረጥም ነበረ።

ከባንጉዊ ውጭ አንዱ በብዋር፣ ሌላው ደግሞ በባምባሬ ሌሎች ሁለት ትምህርት ቤቶች ተካሂደው ነበር። ይህም የተማሪዎቹን ጠቅላላ ቁጥር 68 አድርሶታል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ የአቅኚዎች ቁጥር ሲጨምር ተመልክታለች። በ1992 በጥር ወር 149 የዘወትር አቅኚዎችና 17 ልዩ አቅኚዎች እንዲሁም 78 ረዳት አቅኚዎች ነበሩ። ይህም በአገሩ በሙሉ በአስፋፊዎች ቁጥር ላይ ከተገኘ አዲስ ከፍተኛ ቁጥር፣ ሰዓቶች፣ ተመላልሶ መጠይቆችና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ጭማሪ ጋር ተጨማሪ እንቅስቃሴ አስገኝቷል። ብዙ ሠራተኞች ሲኖሩ የመከር መሰብሰቡ ሥራ ይጨምራል።—ኢሳይያስ 60:21, 22፤ ማቴዎስ 9:37, 38

ስለነዚህ ዝግጅቶችና እነዚህን ትምህርት ቤቶች ስለሚያዘጋጀው ምድራዊ ድርጅቱ የሚመሰገነው ይሖዋ ነው። ተማሪዎቹንም ሆነ አስተማሪዎቹን በዚህ በጨለማ ዓለም እንደ ብርሃን እንዲያበሩ እየረዷቸው ነው።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሁን ገና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ያሉ ሃያ አንድ የአቅኚዎች ትምህርት ቤት ተማሪዎች

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እነዚህ ሁለት ወንዶች ልጆች በእውነት ምክንያት ከቤታቸው ተባረሩ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ