“ሰማያት . . . ይናገራሉ”
ፀሐይ በሰማይ ላይ ሆና አሁን ባላችሁበት ቦታ ላይ እሳታማ በሆነ ድምቀት የምታበራው በግምት 93 ሚልዮን ማይሎች ያህል ርቀት ላይ ሆና ነው። ይህች ባለ ግርማ ሰማያዊ ጎረቤታችን በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት እንደ አምላክ ተደርጋ ስትመለክ ብትቆይም ከዚህ ይልቅ “ሰማይንና ምድርን ለሠራው” ለፈጣሪዋ ኃይል ምስክር ናት። (መዝሙር 115:15) ብርሃን ሰጪነቷና ሙቀቷ በምድር ላይ ላለው ሕይወት አስፈላጊ ነው። የሳይንስ ሊቃውንት ስለ እርሷ ያወቁት ነገር ደግሞ በአድናቆት የሚሞላን ነው።
ፀሐይ ከፍተኛ የሆነ የኃይል መጠን እንደምታስገኝ ተነግሮናል። ፀሐይ ከምታመነጨው ሙቀትና ብርሃን ውስጥ ምድር ጠልፋ የምታስቀረው መጠን ከግማሽ ቢልዮንኛ ያነሰውን ብቻ እንደሆነ አውቃችኋልን? ያም ሆኖ እንኳን ይህ ሽራፊ ክፍል 240,000,000,000,000 የፈረስ ጉልበት የሚያህል ኃይል አለው።
ፀሐይ ይህን ሁሉ ኃይል የምትፈጥረው እንዴት ነው? በውስጧ በሚገኝ በየደቂቃው ወደ አራት ሚልዮን የሚጠጋ ሜትሪክ ቶን ሃይድሮጅንን በማቃጠል ኃይልን በሚፈጥር ከፍተኛ የኑክሌር ምድጃ አማካኝነት ነው። ደስ የሚለው ነገር በፀሐይ ውስጥ ለሰው ልጅ ይህን ሂደት በቢልዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት እንዲቀጥል የሚያስችል ነዳጅ መኖሩ ነው።
የሳይንስ ሊቃውንት ያገኙአቸው አንዳንድ ነገሮች ተጨማሪ ጥያቄዎችን አስነስተዋል። ለምሳሌ ያህል ፀሐይ በመዶሻ እንደተመታ የብረት ጥፍጥፍ ያለማቋረጥ ትርገበገባለች። ለምን? በተጨማሪም ይህን ተመልከቱ፦ በጣም ሞቃቱ የፀሐይ ክፍል የሚያቃጥለው ውስጠኛ ክፍሏ ነው፣ ስለዚህ የአንድ ነገር ውጪያዊ አካል ከውስጠኛው ክፍል በራቀ መጠን ይበልጥ ቀዝቃዛ ነው። ኮሮና ወደሚባለው የፀሐይ ከባቢ አየር ውጪያዊ ክፍል ስንመጣ ግን ሁኔታው ይለወጣል። ኮሮና ከሚያቃጥለው ውስጠኛ ክፍል የበለጠ ያቃጥላል። ለምን?
በተጨማሪም ፀሐይም እንደ ምድር የምትሽከረከር ስትሆን የተለያዩ ክፍሎቿ የሚዞሩት በተለያየ ፍጥነት ነው። ለምሳሌ ያህል ውጪያዊ አካሏ ከውስጣዊ አካሏ ይልቅ በፍጥነት ይሽከረከራል። ለምን? ይህስ እንዴት ሊሆን ይቻላል? ከዚህም ሌላ በፀሐይ ላይ ጣል ጣል ብለው የሚታዩ ጨለማ ክፍሎች አሉ። እነዚህ በፀሐይ ላይ የሚታዩ የፀሐይን መልክ የሚያጠፉ ነጥቦች በየ11 ዓመታት ውስጥ በሚፈራረቅ ዑደት የሚጨምሩና የሚቀንሱ ናቸው። በእንደዚህ ዓይነት የተወሰነና የማያቋርጥ ሁኔታ የሚለዋወጡት ለምንድን ነው?
ስለ ፀሐይ ገና ብዙ የሚታወቅ ነገር ያለ ቢሆንም እስካሁን ያወቅነው ፈጣሪዋን ይሖዋ አምላክን በከፍተኛ አክብሮትና አድናቆት እንድንመለከተው ያደርገናል። ፀሐይን በተመለከትን ቁጥር “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል” የሚለው ትዝ ይለናል።—መዝሙር 19:1