ቤተሰብ ጥቃት እየደረሰበት ነው!
“ቤተሰብ እጅግ ጥንታዊ የሆነ ሰብዓዊ ተቋም ነው። በብዙ መንገዶች ከማንኛውም ተቋም የበለጠ አስፈላጊ ነው። ኅብረተሰብ የሚገነባበት መሠረታዊ ድርጅት ቤተሰብ ነው። አያሌ ሥልጡን ኅብረተሰቦች በቤተሰብ ጥንካሬ ወይም ደካማነት የተነሳ ጸንተዋል ወይም ወድቀዋል።”
ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ በ1973 ከላይ ያለውን ተናግሮ ነበር። ይሁን እንጂ ዛሬ ካለው ሁኔታ አንፃር ሲታዩ እነዚህ ቃላት ልክ እንደ መጥፎ፣ ክፉ ነገርን እንደሚያስከትሉ ቃላት ተደርገው ይወሰዳሉ። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቤተሰብ ሕይወት ላይ ፊት ለፊት ጥቃት ተካሂዷል። ጆን ብራድሾ የተባሉት ታዋቂ አማካሪ ሲጽፉ፦ “ዛሬ ቤተሰብ ትልቅ ውዝግብ ደርሶበታል። . . . የፍቺ ቁጥር መብዛት፣ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የሚፈጽሙት የዓመፅ ድርጊት፣ በአደንዛዥ መድኃኒቶች አላግባብ በብዛት መጠቀም፣ እንደ ወረርሽኝ የተዛመተው በሥጋ ዘመዶች መካከል የሚደረገው የግብረ ሥጋ ግንኙነት መብዛት፣ ከአመጋገብ ሥርዓት ጉድለት ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎች፣ እና መደባደብ አንድ መሠረታዊ የሆነ ስህተት እንዳለ ማረጋገጫ ናቸው” ብለዋል።
በእርግጥ በቤተሰብ ውስጥ “አንድ መሠረታዊ የሆነ ስህተት እንዳለ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች” በዓለም በሙሉ ሊገኙ ይችላሉ። ዘ ዩኔስኮ ኩርየር በአውሮፓ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ከ1965 አንስቶ በአህጉሩ ባጠቃላይ ትልቅ የፍቺ ቁጥር ጭማሪ ታይቷል። . . . በአንድ ወላጅ ብቻ የሚያድጉ ልጆች ያሉባቸው ቤተሰቦች ቁጥር ጨምሯል።” በማደግ ላይ ያሉ አገሮችም እንዲሁ እየጨመረ የሚሄድ የቤተሰብ ችግር እንዳለ ተመልክተዋል። አለን ትሬምብለይ የተባሉት ጸሐፊ የተመለከቱትን ሲጽፉ፦ “ለመቶ ዘመናት ያህል ቋሚነት ያለው፣ በቅድሚያ ሊታወቅ የሚችልና የማይለዋወጥ የአኗኗር ሁኔታ በነበረው ኅብረተሰብ ውስጥ ለሚኖሩት በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ዛሬ ያለው ሁኔታ ብጥብጥ ሆኖባቸዋል።”
በተለይ የሚያሳስበው ደግሞ ዛሬ በብዙ ቤቶች ውስጥ ያለው ሁኔታ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆች የሚያድጉት ጠጪ በሆኑ ወላጆች ነው። ልጆችን መደብደብም በሚሰቀጥጥ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። ተመራማሪዎቹ ሪቻርድ ጄለስና ሙሬይ ስትራውስ በቤት ውስጥ የሚፈጸም ዓመፅ በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ በማለት ዘግበዋል፦ “በይበልጥ አካላዊ ጥቃት የሚደርስብህ፣ የምትደበደበውና የምትገደለው ከየትኛውም ቦታ ይልቅ በራስህ ቤት ውስጥ፣ በኅብረተሰባችን ውስጥ ካለው ከማንኛውም ሰው ይልቅ አንተ በምትወደው ሰው እጅ ነው።”
የሥልጣኔ በሕይወት መቆየት በቤተሰብ ጥንካሬ ላይ በእርግጥ የተመካ ከሆነ ስለ ሥልጣኔ የወደፊት ሁኔታ ለመፍራት ምክንያት ይኖረናል። ቢሆንም የሥልጣኔ የመጨረሻ ዕጣ ከጭንቀቶችህ ሁሉ የመጨረሻ አነስተኛው ሊሆን ይችላል። ይበልጥ የሚያስጨንቅህ እንዲህ ያለው ብጥብጥ በአንተ ቤተሰብ ላይ የሚያመጣው ነገር ሊሆን ይችላል። ውጤቱ ምን ይሆን? ከታመነ ምንጭ የሚገኘው መልስ ያላሰብከውና ያልጠበቅኸው ሊሆን ይችላል።