የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 10/15 ገጽ 8-13
  • የይሖዋ ፍቅራዊ የቤተሰብ ዝግጅት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የይሖዋ ፍቅራዊ የቤተሰብ ዝግጅት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው የቤተሰብ ሁኔታ
  • የክርስቲያን ባሎች ሚና
  • ደጋፊ የሆኑ ክርስቲያን ሚስቶች
  • አመስጋኝ የሆኑ ልጆች
  • የቤተሰብህን ሕይወት አስደሳች ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • የቤተሰብን ኑሮ የተሳካ ማድረግ
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
  • ለባለ ትዳሮች የሚሆን ጥበብ ያዘለ መመሪያ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ቤተሰብህ ደስተኛ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 10/15 ገጽ 8-13

የይሖዋ ፍቅራዊ የቤተሰብ ዝግጅት

“እንግዲህ በእግዚአብሔር አብ ፊት በጉልበቴ ተንበርክኬ የምጸልየው በዚህ ምክንያት ነው። በሰማይና በምድር ያለ ቤተሰብ ሁሉ እውነተኛ ስሙን የሚያገኘው ከእግዚአብሔር ነው።”—ኤፌሶን 3:14, 15 የ1980 ትርጉም

1, 2. (ሀ) ይሖዋ ቤተሰብን የፈጠረው ለምን ዓላማ ነበር? (ለ) ዛሬ ቤተሰብ በይሖዋ ዝግጅት ውስጥ ምን ቦታ ሊኖረው ይገባል?

ይሖዋ ቤተሰብን ፈጥሯል። ይህንንም በማድረጉ ሰዎች ለመወዳጀት፣ ለድጋፍ ወይም ለተቀራረበ ግንኙነት ያላቸውን ፍላጎት ከማሟላት የበለጠ ነገር አድርጓል። (ዘፍጥረት 2:18) አምላክ ምድር በሰዎች እንድትሞላ የነበረው ክብራማ ዓላማ በቤተሰብ አማካኝነት እንዲፈጸም ታስቦ ነበር። የመጀመሪያዎቹን የተጋቡ ባልና ሚስት እንዲህ ብሎ ነገራቸው፦ “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም።” (ዘፍጥረት 1:28) ሞቅ ያለና ልጆችን ለማሳደግ አመቺ የሆነው የቤተሰብ ኑሮአቸው አዳምና ሔዋን እንዲሁም ዘሮቻቸው ለሚወልዱአቸው እጅግ ብዙ ልጆች ጠቃሚ እንደሚሆን የተረጋገጠ ነበር።

2 ይሁን እንጂ እነዚያ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ለእነሱም ሆነ ለዝርያዎቻቸው አውዳሚ ውጤት ያስከተለውን ያለመታዘዝን መንገድ መረጡ። (ሮሜ 5:12) ስለዚህ በዛሬው ጊዜ ያለው የቤተሰብ ኑሮ አምላክ እንዲሆን ከፈለገው ሁኔታ በተዛባ መልኩ ይገኛል። ቢሆንም ቤተሰብ ለክርስቲያናዊ ማኅበር መሠረታዊ ክፍል ሆኖ ስለሚያገለግል በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ትልቅ ቦታ እንደያዘ ቀጥሏል። ይህን ስንል ግን በመካከላችን የሚገኙት ያላገቡ ብዙ ክርስቲያኖች ለሚሠሩት መልካም ሥራ አድናቆት ማጣታችን አይደለም። ከዚህ ይልቅ ቤተሰቦች ለመላው ክርስቲያናዊ ድርጅት መንፈሳዊ ጤንነት የሚያበረክቱትን ትልቅ አስተዋፅኦ ማስታወሳችን ነው። ጠንካራ ቤተሰቦች ጠንካራ ጉባኤዎችን ይመሠርታሉ። ታዲያ ያንተ ቤተሰብ ዛሬ ያሉትን ተጽዕኖዎች ተቋቁሞ የዳበረ ሊሆን ይችላልን? ለመልሱ መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብን ዝግጅት በሚመለከት ምን እንደሚል እንመርምር።

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው የቤተሰብ ሁኔታ

3. ሕጉ ከመሰጠቱ በፊት አባቶች ለቤተሰባቸው የሃይማኖት መሪ በነበሩበት የቀድሞ ዘመን ባልና ሚስት ምን ማድረግ ነበረባቸው?

3 አዳምና ሔዋን ሁለቱም ለአምላክ የራስነት ዝግጅት ንቀት አሳይተዋል። እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ኢዮብ ያሉ የእምነት ሰዎች ግን የቤተሰብ ራስነት ቦታቸውን በትክክለኛው መንገድ ተቀብለው ሠርተውበታል። (ዕብራውያን 7:4) ሕጉ ከመሰጠቱ በፊት አባቶች ለቤተሰባቸው ሃይማኖታዊ መሪ በነበሩበት የቀድሞ ዘመን ቤተሰብ፣ አባት እንደ ሃይማኖታዊ መሪ፣ አስተማሪና ዳኛ ሆኖ የሚሠራበት እንደ አነስተኛ መስተዳድር ያለ ነበር። (ዘፍጥረት 8:20፤ 18:19) ሚስቶችም እንደ ባሪያ ሳይሆን ለቤተሰቡ የበታች ሥራ አስኪያጅ ሆኖ የማገልገል ትልቅ ሚና ነበራቸው።

4. በሙሴ ሕግ ሥር የቤተሰብ ኑሮ የተለወጠው እንዴት ነበር? ይሁን እንጂ ወላጆች ምን ሚና መጫወታቸውን ቀጥለው ነበር?

4 በ1513 ከዘአበ እስራኤል እንደ አንድ ብሔር ሆኖ በተቋቋመ ጊዜ የቤተሰብ ሕግ በሙሴ በኩል ለተሰጠው ብሔራዊ ሕግ ተገዥ ሆነ። (ዘጸአት 24:3-8) አሁን የሕይወትና የሞት ጉዳዮችን ጨምሮ የፍርድ ጉዳዮችን የመወሰን ሥልጣን ለተመረጡት ዳኞች ተሰጠ። (ዘጸአት 18:13-26) በአምልኮ ረገድ መሥዋዕት የማቅረቡን ሥራ ደግሞ ሌዋውያን ካህናት ወሰዱ። (ዘሌዋውያን 1:2-5) ይህም ሆኖ አባት ትልቅ ሚና መጫወቱን ቀጥሏል። ሙሴ አባቶችን እንዲህ ሲል አጥብቆ መከራቸው፦ “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው።” (ዘዳግም 6:6, 7) እናቶችም ከፍተኛ የሆነ ተሰሚነት ነበራቸው። ምሳሌ 1:8 ወጣቶችን “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ምክር ስማ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው” ሲል ይመክራቸዋል። አዎን፣ ዕብራዊት ሚስት በባልዋ ሥልጣን ሥር ሆና ለቤተሰቡ ሕግ የማውጣትና ያንን ሕግ ማስከበር ትችል ነበር። ካረጀችም በኋላ እንኳን በልጆቿ ልትከበር ይገባ ነበር።—ምሳሌ 23:22

5. የሙሴ ሕግ ልጆች በቤተሰብ ዝግጅት ውስጥ ያላቸውን ቦታ እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል?

5 የልጆችም ቦታ በአምላክ ሕግ ውስጥ በግልጽ ተቀምጦ ነበር። ዘዳግም 5:16 እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] አምላክህ እንዳዘዘህ አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም፣ መልካምም እንዲሆንልህ።” ለወላጆች አለመታዘዝ በሙሴ ሕግ ሥር በጣም ከባድ ጥፋት እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። (ዘጸአት 21:15, 17) ሕጉ “ማናቸውም ሰው አባቱን ወይም እናቱን ቢሰድብ [ቢረግም አዓት] ፈጽሞ ይገደል፣ አባቱንና እናቱን ሰድቦአልና” በማለት ይገልጻል። (ዘሌዋውያን 20:9) በወላጆች ላይ ማመፅ ልክ በአምላክ በራሱ ላይ እንደ ማመፅ ተደርጎ ይታይ ነበር።

የክርስቲያን ባሎች ሚና

6, 7. በኤፌሶን 5:23-29 ላይ ያሉት የጳውሎስ ቃላት ለመጀመሪያው መቶ ዘመን አንባቢዎቹ እንደ አዲስ መስለው ሊታዩ ይችሉ የነበሩት ለምንድን ነው?

6 ክርስትና በቤተሰብ ዝግጅት ላይ በተለይም የክርስቲያን ባሎችን ቦታ በሚመለከት ተጨማሪ ብርሃን አብርቷል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ያሉ ባሎች ሚስቶቻቸውን ሸካራና ጨቋኝ በሆነ ሁኔታ መያዛቸው የተለመደ ነበር። ሴቶች መሠረታዊ የሆኑ መብቶችና ክብርን ይነፈጉ ነበር። ዘ ኤክስፖዚተርስ ባይብል እንዲህ ይላል፦ “ግሪኮች በባሕላቸው ሚስት የሚያገቡት ልጆችን ለመውለድ ሲሉ ነበር። ሚስቲቱ በጾታ ፍላጎቱ ላይ ገደብ እንዲኖረው ለማድረግ ምንም ዓይነት መብት አልነበራትም። በጋብቻቸው ውል ውስጥ ፍቅር የለበትም። . . . ሴት ባሪያም ምንም መብት አልነበራትም። ባለቤቷ አካልዋን በፈለገው መንገድ ሊጠቀምበት ይችል ነበር።”

7 እንዲህ ያለ መንፈስ ባለበት ሁኔታ ጳውሎስ በኤፌሶን 5:23-29 ላይ ያሉትን “ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና። . . . ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ . . . ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ . . . እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፣ ነገር ግን . . . ይመግበዋል ይንከባከበውማል” የሚሉትን ቃላት ጽፏል። ለመጀመሪያው መቶ ዘመን አንባቢያን እነዚህ ቃላት የነበረውን ባሕል የሚገለብጡ ነበሩ። ዘ ኤክስፖዚተርስ ባይብል “ወራዳ ከሆነው የጊዜው ሥነ ምግባር አንፃር ሲታይ እንደ ክርስቲያናዊ የጋብቻ አመለካከት በክርስትና ውስጥ አዲስና ትክክለኛ ሆኖ የቀረበ ምንም ነገር የለም። . . . ለሰው ልጆች አዲስ ዘመን ከፍቷል” ብሏል።

8, 9. ሴቶችን በሚመለከት በወንዶች ዘንድ ያለው የተለመደ ጤናማ ያልሆነ አመለካከት ምንድን ነው? ክርስቲያን ወንዶች ግን እንዲህ ያሉትን አመለካከቶች ማስወገድ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

8 መጽሐፍ ቅዱስ ለባሎች የሚሰጠው ምክር ዛሬም ቢሆን የቀድሞውን ባሕል የሚገለብጥ ነው ሊባል ይቻላል። የሴቶች ነፃነት ብዙ የተወራለት ጉዳይ ቢሆንም አሁንም ወንዶች ሴቶችን የጾታ ፍላጎታቸው ማርኪያ ብቻ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ሴቶች ሲጫኑአቸው፣ ሲቆጣጠሩአቸውና ሲደበድቧቸው ደስ ይላቸዋል የሚለውን መሠረተ ቢስ የሆነ አስተሳሰብ በማመን ብዙ ወንዶች ሚስቶቻቸውን በአካልም ሆነ በስሜት ያጎሳቁሏቸዋል። አንድ ክርስቲያን ወንድ ዓለማዊ በሆነ አስተሳሰብ ተስቦ ሚስቱን ያለ አግባብ ቢይዛት እንዴት የሚያሳፍር ነገር ይሆናል! አንዲት ክርስቲያን ሴት “ባለቤቴ ዲያቆን ነበር፤ የሕዝብ ንግግሮችንም ይሰጣል። ይሁን እንጂ እኔ ከሚደበደቡ ሚስቶች አንዷ ነበርኩ” ስትል ገልጻለች። እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ከአምላክ ዝግጅት ውጭ እንደሆኑ ግልጽ ነው። እንዲህ ያለው ሁኔታ በአብዛኛው የማይከሰት ነገር ቢሆንም ይህ ሰው የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ተስፋ የሚያደርግ ከሆነ ይህን ቁጣውን ለማስቀረት እንዲችል እርዳታ መጠየቅ ያስፈልገዋል።—ገላትያ 5:19-21

9 ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው እንዲወድዱ በአምላክ ታዘዋል። ይህን ትእዛዝ ለመፈጸም እምቢተኛ መሆን በአምላክ ዝግጅት ላይ ማመፅ ማለት ስለሆነ ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ሊያመነምንበት ይችላል። “እናንተ ባሎች ሆይ፣ ደካማ ፍጥረት ስለሆኑ ከሚስቶቻችሁ [ሚስቶቻችሁን እንደ ደካማ ዕቃ እያከበራችሁ ከእነርሱ አዓት] ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል፣ . . . አክብሯቸው” የሚሉት የሐዋርያው ጴጥሮስ ቃላት ግልጽ ናቸው። (1 ጴጥሮስ 3:7) አንድ ሰው ሚስቱን የሚይዛት ሸካራ በሆነ ሁኔታ ከሆነ በመንፈሳዊነቷና በልጆቻቸው መንፈሳዊነት ላይ አፍራሽ ውጤት ይኖረዋል።

10. ባሎች የራስነት ሥልጣናቸውን የክርስቶስን በሚመስል ሁኔታ ሊጠቀሙበት የሚችሉባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

10 ባሎች ሆይ፣ ቤተሰባችሁ በራስነት ሥልጣናችሁ ሥር ሊያብብ የሚችለው ይህን የራስነት ሥልጣን የክርስቶስን በሚመስል ሁኔታ የምትጠቀሙበት ከሆነ ነው። ክርስቶስ ሸካራ ወይም ሰውን የሚያዋርድ አልነበረም። በተቃራኒው ግን “ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” ለማለት ችሎ ነበር። (ማቴዎስ 11:29) የአንተስ ቤተሰብ ስለ አንተ እንዲህ ብሎ ሊናገር ይችላልን? ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን እንደ ጓደኞቹ አድርጎ ይይዛቸውና ያምናቸው ነበር። (ዮሐንስ 15:15) ለሚስትህ ይህን የመሰለ ክብር ትሰጣታለህን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “ባለሞያ ሚስት” ሲናገር “የባልዋም ልብ ይታመንባታል” ይላል። (ምሳሌ 31:10, 11) ይህም ማለት ምክንያታዊ ያልሆኑ ገደቦች በማድረግ ፈንታ መጠነኛ ነፃነትና የመወሰን መብት ይሰጣታል ማለት ነው። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ስሜታቸውንና አስተያየታቸውን እንዲገልጹ ያበረታታቸው ነበር። (ማቴዎስ 9:28፤ 16:13-15) አንተስ ለሚስትህ እንዲህ ታደርግላታለህን? ወይስ ስሜቷን ባለመደበቅ በአንዳንድ ነገሮች አለመስማማቷን ስትገልጽ ሥልጣንህን እንደ መገዳደር አድርገህ ትመለከተዋለህ? የሚስትህን ስሜቶች ችላ ከማለት ይልቅ ስሜቶችዋን ግምት ውስጥ በማስገባትህ ለራስነት ሥልጣንህ ያላትን አክብሮት ትገነባለህ።

11. (ሀ) አባቶች ልጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ነገሮች ሊያሟሉ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ቤተሰብን በመንከባከብ ረገድ ጥሩ አርዓያ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?

11 አባት ከሆንክ ልጆችህ የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ፣ ስሜታዊ እና አካላዊ ነገሮች በማሟላት ረገድ የመሪነቱን ቦታ እንድትወስድ ይፈለግብሃል። ይህም በመስክ አገልግሎት አብረሃቸው መሥራትን፣ ለእነርሱ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራትን፣ የዕለት ጥቅሱን አብራችሁ መወያየትንና ባጭሩ ቤተሰቡ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ እንዲኖረው ማድረግን ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሽማግሌ ወይም ዲያቆን “የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር” መሆን እንደሚገባው ይናገራል። ስለዚህ እንዲህ ባሉ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚሠሩ ወንዶች ለቤተሰብ ራስነት ጥሩ ምሳሌ መሆን ይኖርባቸዋል። ከባድ የሆኑ የጉባኤ ኃላፊነቶች ሸክም ቢኖሩባቸውም ለራሳቸው ቤተሰብ ቅድሚያ መስጠት አለባቸው። ጳውሎስ ይህ ለምን እንደሆነ ሲገልጽ “ሰው የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል?” በማለት አስረድቷል።—1 ጢሞቴዎስ 3:4, 5, 12

ደጋፊ የሆኑ ክርስቲያን ሚስቶች

12. በክርስቲያናዊው ዝግጅት ውስጥ ሚስት ምን ሚና ትጫወታለች?

12 ክርስቲያን ሚስት ነሽን? እንግዲያው አንቺም በቤተሰብ ዝግጅት ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሚና መጫወት ይኖርብሻል። ክርስቲያን ሚስቶች “ባሎቻቸውን የሚወዱ፣ ልጆቻቸውን የሚወዱ፣ ራሳቸውን የሚገዙ፣ ንጹሖች፣ በቤት የሚሠሩ፣ በጎዎች፣ ለባሎቻቸው የሚታዘዙ እንዲሆኑ” ተመክረዋል። (ቲቶ 2:4, 5) ስለዚህ አንቺም ቤትሽን ንጹሕና ደስ የሚል በማድረግ አርዓያ የምትሆኚ የቤት እመቤት ለመሆን መጣር ይገባሻል። የቤት ውስጥ ሥራ አንዳንድ ጊዜ አሰልቺ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ክብር የሚቀንስ ወይም ዋጋ ቢስ የሆነ አይደለም። እንደ ሚስትነትሽ መጠን ‘ቤትሽን ልታስተዳድሪ’ እንዲሁም በዚህ ረገድ ባለሽ የመወሰን ነፃነት ልትደሰቺ ትችያለሽ። (1 ጢሞቴዎስ 5:14) ለምሳሌ “ባለሞያ ሚስት” ለቤት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ትሸምታለች፣ ቋሚ ንብረቶችን ትገዛለች፣ እንዲያውም አነስተኛ ንግድ በማካሄድም ገቢ ታስገኛለች። ከባልዋ ምስጋና ማግኘቷ አያስደንቅም! (ምሳሌ ምዕራፍ 31) እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን የማመንጨት ችሎታ የሚኖራት ባልዋ እንደ ራስ ሆኖ በሚሰጣት መመሪያዎች ሥር እንደሚሆን የታወቀ ነው።

13. (ሀ) ለአንዳንድ ሴቶች መገዛት አስቸጋሪ ሊሆንባቸው የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያን ሴቶች ራሳቸውን ለባሎቻቸው ማስገዛታቸው ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ይሁን እንጂ ራስሽን ለባልሽ ማስገዛት ሁልጊዜ ቀላል ላይሆንልሽ ይችላል። ለመከበር የሚጋብዝ ሁኔታ ያላቸው ሁሉም ወንዶች አይደሉም። አንቺ ደግሞ ገንዘብ ነክ የሆኑ ነገሮች በመቆጣጠር ረገድ፣ ዕቅድ በማውጣት ወይም በማስተባበር በኩል ጥሩ ችሎታ ይኖርሽ ይሆናል። ምናልባት ዓለማዊ ሥራ ይኖርሽና ለቤተሰቡ ገቢ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ታደርጊ ይሆናል። ወይም ደግሞ በፊት በወንዶች ጭቆና የተነሣ በአንዳንድ መንገዶች ሥቃይ ደርሶብሽ ከሆነ ለወንድ መገዛትን ከባድ ሆኖ ታገኚው ይሆናል። ሆኖም ለባልሽ ‘ጥልቅ አክብሮት’ ወይም ‘ፍርሃት’ ማሳየት ለአምላክ ራስነት አክብሮት እንዳለሽ ያስረዳል። (ኤፌሶን 5:33፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3) መገዛት ለቤተሰባችሁ ኑሮ ስኬታማነት ወሳኝነት አለው። ጋብቻችሁን አላስፈላጊ ወዳልሆነ ጭንቀትና ውጥረት እንዳይገባ ለማድረግ ይረዳል።

14. አንዲት ሚስት ባልዋ ባደረገው ውሳኔ የማትስማማ ከሆነ ምን ማድረግ ትችል ይሆናል?

14 ታዲያ ይህ ማለት ባልሽ የቤተሰቡን ጥቅም የሚፃረር ውሳኔ እያደረገ እንዳለ ሲሰማሽ ዝም ማለት አለብሽ ማለት ነውን? ላይሆን ይችላል። የአብርሃም ሚስት ሣራ በልጅዋ በይስሐቅ ደኅንነት ላይ አስጊ ሁኔታ እንዳለ በተገነዘበች ጊዜ ዝም አላለችም። (ዘፍጥረት 21:8-10) አንቺም በተመሳሳይ አንዳንድ ጊዜ ስሜትሽን የመግለጽ ግዴታ እንዳለብሽ ሆኖ ይሰማሽ ይሆናል። አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ ‘በትክክለኛው ጊዜ’ እንደዚያ ካደረግሽ አምላካዊ የሆነው ክርስቲያን ወንድ ይሰማሻል። (ምሳሌ 25:11) ሆኖም ምክርሽ ተቀባይነት ባያገኝና የተፈጸመው ነገር የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት የሚፃረር ካልሆነ የባልሽን ፍላጎት የሚቃወም ነገር ማድረግ ሽንፈት አይሆንብሽምን? “ብልሃተኛ ሴት ቤትዋን ትሠራለች፤ ሰነፍ ሴት ግን በእጅዋ ታፈርሰዋለች” የሚለውን ቃል አስታውሺ። (ምሳሌ 14:1) ቤትሽን የምትገነቢበት አንዱ መንገድ ባልሽ የፈጸማቸውን ስህተቶች ሳትበሳጪ ለማስተካከል እየሞከርሽ ላከናወናቸው ነገሮች ምስጋና በማቅረብ ለራስነት ሥልጣኑ ደጋፊ ሆኖ መገኘቱ ነው።

15. አንዲት ሚስት ልጆችን ሥርዓት በማስያዝና በማሰልጠን በኩል በምን በምን መንገዶች ልትካፈል ትችላለች?

15 ቤትሽን የምትገነቢበት ሌላው መንገድ ደግሞ ልጆችን ሥርዓት በማስያዙና በማሰልጠኑ በኩል በመካፈል ነው። ለምሳሌ ያህል የቤተሰቡን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቋሚና የሚያንጽ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ባንቺ በኩል እርዳታ ልታደርጊ ትችያለሽ። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ አብረሻቸው ስትጓዢ ወይም ገበያ ስትሄዱም እንኳን የአምላክን ቃል ለልጆችሽ በማካፈል ረገድ ‘እጅሽን አትተይ።’ (መክብብ 11:6) በስብሰባዎችና በቲኦክራቲካዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍላቸው ላይ የሚሰጧቸውን ሐሳቦች እንዲዘጋጁ እርጃቸው። ውሎአቸው ከነማን ጋር እንደሆነ ተከታተይ። (1 ቆሮንቶስ 15:33) አምላካዊ የሆኑ የአቋም ደረጃዎችንና ሥነ ሥርዓቶችን በሚመለከት አንቺና ባልሽ አቋማችሁ አንድ እንደሆነ ልጆችሽ እንዲያውቁ አድርጊ። ልጆቹ አንቺንና ባልሽን አጋጭተው የፈለጉትን ነገር እንዲያገኙ አትፍቀጂላቸው።

16. (ሀ) ነጠላ የሆኑ ወላጆችንና የማያምን ያገቡትን ለማበረታታት የሚያገለግል ምን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌ አለ? (ለ) በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች እንዲህ ያሉትን እንዴት ሊረዷቸው ይችላሉ?

16 ነጠላ ወላጅ ከሆንሽ ወይም የማያምን የትዳር ጓደኛ ካለሽ በመንፈሳዊ በኩል የመሪነቱን ቦታ መያዝ ይኖርብሻል። ይህ አስቸጋሪና አንዳንድ ጊዜም ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ጥረት ማድረግሽን አታቁሚ። የጢሞቴዎስ እናት ኤውንቄ የማያምን ሰው ያገባች ብትሆንም ጢሞቴዎስን “ከሕፃንነቱ” ጀምራ ቅዱሳን ጽሑፎችን በማስተማር በኩል ተሳክቶላታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:15) በመካከላችን ያሉ ብዙዎች ይህን የመሰለ መልካም ውጤት በማግኘት እየተደሰቱ ነው። በዚህ ረገድ አንዳንድ እርዳታ የሚያስፈልግሽ ከሆነ ሽማግሌዎች ችግርሽን እንዲያውቁ ልታደርጊ ትችይ ይሆናል። ወደ ጉባኤ እንድትመጪና ለመስክ አገልግሎት እንድትወጪ የምትረዳሽ እህት ሊያዘጋጁልሽ ይችሉ ይሆናል። ለመዝናናት በሚወጡበት ወይም ለጨዋታ በሚገናኙበት ጊዜ የአንቺንም ቤተሰብ እንዲጨምሩ ሌሎችን ያበረታቱ ይሆናል። ወይም ደግሞ ተሞክሮ ያላት አስፋፊ የቤተሰብ ጥናት ለመጀመር እንድትረዳሽ ዝግጅት ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል።

አመስጋኝ የሆኑ ልጆች

17. (ሀ) ወጣቶች ለቤተሰቡ ደኅንነት አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) በዚህ ረገድ ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቷል?

17 ክርስቲያን ወጣቶች በኤፌሶን 6:1-3 ላይ ያለውን፦ “ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፣ ይህ የሚገባ ነውና። መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት” የሚለውን ምክር በመከተል ለቤተሰቡ ደኅንነት አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይችላሉ። ከወላጆቻችሁ ጋር በመተባበር ለይሖዋ ያላችሁን አክብሮት ታሳያላችሁ። ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ስለነበር ፍጹማን ላልሆኑ ወላጆች መገዛት ክብሬን ይቀንስብኛል ብሎ ሊያሳብብ ይችል ነበር። ሆኖም “ይታዘዝላቸውም ነበር። . . . ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።”—ሉቃስ 2:51, 52

18, 19. (ሀ) ወላጆችን ማክበር ማለት ምን ማለት ነው? (ለ) ቤቱ አእምሮን የሚያድስ አስደሳች ቦታ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

18 እናንተስ በተመሳሳይ ወላጆቻችሁን ማክበር የለባችሁምን? እዚህ ላይ “ማክበር” የሚለው ቃል በሚገባ የተቋቋመን ሥልጣን አምኖ መቀበል ማለት ነው። (ከ1 ጴጥሮስ 2:17 ጋር አወዳድር።) የአንድ ሰው ወላጅ የማያምን ወይም ጥሩ ምሳሌ የማያሳይ ቢሆንም እንኳን በአብዛኞቹ ሁኔታዎች እንዲህ ያለው አክብሮት ሊሰጠው ይገባል። ወላጆቻችሁ ምሳሌ የሚሆኑ ክርስቲያኖች ከሆኑ ደግሞ በይበልጥ ልታከብሩአቸው ይገባል። በተጨማሪም በወላጆቻችሁ የሚሰጣችሁ ተግሣጾችና መመሪያዎች በእናንተ ላይ ተገቢ ያልሆነ ገደብ ለመፍጠር የታሰቡ አለመሆናቸውን አስታውሱ። ከዚህ ይልቅ ‘በሕይወት ለመኖር’ እንድትችሉ እናንተን ለመጠበቅ የሚረዱ ናቸው።—ምሳሌ 7:1, 2

19 እንግዲያው ቤተሰብ እንዴት ያለ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው! ባሎች፣ ሚስቶችና ልጆች ሁሉም አምላክ ለቤተሰብ ኑሮ የሰጣቸውን መመሪያዎች ሲከተሉ ቤቱ አእምሮ የሚታደስበት የማረፊያ ቦታ ይሆናል። ሆኖም በሐሳብ ግንኙነት ረገድና ልጆችን በማሰልጠን በኩል ችግሮች ሊነሱ ይችላሉ። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ከእነዚህ ችግሮች አንዳንዶቹ እንዴት ሊፈቱ እንደሚችሉ ያብራራልናል።

ታስታውሳለህን?

◻ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩት ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ባሎች፣ ሚስቶችና ልጆች ምን አርአያ ትተዋል?

◻ የባሎችን ሚና በተመለከተ ክርስትና ምን አዲስ ብርሃን አብርቷል?

◻ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ሚስት ምን ሚና መጫወት ይገባታል?

◻ ክርስቲያን ወጣቶች ለቤተሰቡ ደኅንነት አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ የሚችሉት እንዴት ነው?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ወራዳ ከሆነው የዛሬ ጊዜ ሥነ ምግባር አንፃር ሲታይ እንደ ክርስቲያናዊ የጋብቻ አመለካከት በክርስትና ውስጥ አዲስና ትክክለኛ ሆኖ የቀረበ ምንም ነገር የለም። . . . ለሰው ልጆች አዲስ ዘመን ከፍቷል።”

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያን ባሎች ሚስቶቻቸው ስሜታቸውን እንዲገልጹ ያበረታቷቸዋል፤ እነዚህንም ስሜቶች ችላ ብለው አያልፉም

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ