የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 11/15 ገጽ 24-25
  • በናሚቢያ እውነትን ለሰዎች በሚገባ መንገድ ማቅረብ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በናሚቢያ እውነትን ለሰዎች በሚገባ መንገድ ማቅረብ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • አዲስ ምዕራፍ ላይ መድረስ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 11/15 ገጽ 24-25

በናሚቢያ እውነትን ለሰዎች በሚገባ መንገድ ማቅረብ

“አልገባኝም” የሚለውን ቃል በምን ያህል ቋንቋ ሰምታችሁታል? “ሄ ኖኩዙቫ” አለች ባሕላዊ ረዥም ቀሚሷን ለብሳ የቀንድ ቅርጽ ያለው ሻሽ ያሰረች አንዲት የሄሬሮ ወይዘሮ። አንዲት ክዋኛማ ልጃገረድ ደግሞ ፈገግ ብላ “እንጌ ኡዴቶ ኮ” በማለት መለሰች። አንድ የንዶንጋ መንደረተኛ ደግሞ ትከሻውን በመነቅነቅ “ካንዱ ቬቴ ኮ” በማለት መልስ ሰጠ። አንድ የክዋንጋሊ ፍየል ጠባቂ ደግሞ “ካፔ ና ኩዙቫ” በማለት መልስ ሰጠ።

እነዚህ ሰዎች በሙሉ “አልገባኝም” ማለታቸው ነበር። ይህም በናሚቢያ ያሉ የይሖዋ ምስክሮች 824,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ክልል ላይ የሚኖሩ 1,370,000 ነዋሪዎች ዘንድ ለመድረስ በሚሞክሩበት ጊዜ የሚያጋጥማቸውን የቋንቋ ችግር ጥሩ አድርጎ የሚያስረዳ ነው!

በእርግጥም የሚያስደንቅ አይደለም! የሄሬሮና የናማ ሕዝቦች ብቻ ሳይሆኑ በናሚቢያ የሚኖሩት የኦቫምቦ፣ የካቫንጎ፣ የስዋና፣ የካፕሪቪያን፣ የሂምባ፣ የቡሽማንና የዳማራ ሕዝቦችም የየራሳቸው ቋንቋዎች አሏቸው። ምስክሮቹ ደግሞ በአንፃሩ ያላቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ በእንግሊዝኛና በአፍሪካንስ ቋንቋዎች ብቻ ነበር። በግልጽ እንደሚታየው እውነት ለተጨማሪ ሕዝቦች እንዲገባቸው ለማድረግ የትርጉም ሥራ አስፈላጊ ነበር። ይህ የትርጉም ሥራ ከብዙ ዓመታት በፊት ቀደም ሲል ደቡብ ምዕራብ አፍሪካ በመባል ትታወቅ ለነበረችው አገር ዋና ከተማ በነበረችው ዊንድሆክ በትንሹ ተጀምሮ ነበር።

“በዊንድሆክ ለምስክርነት ሥራችን ከቤተ ክርስቲያንና ከፖሊስ ጽኑ ተቃውሞ ነበር” በማለት ዲክ ዎልድረን ያስታውሳል። ዎልድረን ከጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተመርቆ ከሚስቱ ከካረሌ ጋር ወደዚህ አገር የመጣው በ1953 ነበር። “ጥቁሮች ወደሚኖሩባቸው አካባቢዎች እንዳንደርስ እንከለከል ነበር። አንዳንድ ጊዜም ለጥቁሮች ስንናገር ከተገኘን ማስፈራሪያ ይደርስብን ነበር። በመጨረሻም ማንም ሳይረብሸን የምንኖርበት ቦታ እርሱም የጋማንስ ወንዝ መውረጃ የሆነ ደረቅ ሥፍራ አገኘን! ይህም ከከተማው ወጣ ብሎ የሚገኝ ነበር። እንዳንታይ በግራር ዛፎች ቁጥቋጦ ውስጥ ተደብቀን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንመራ ነበር።”

የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎችም ወደ አካባቢው ቋንቋዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተተረጎሙት እዚሁ ሥፍራ ነበር። የተተረጎሙት ጽሑፎችም በክዋኛማ ቋንቋ የተተረጎሙ አንዳንድ ጽሑፎችንና በናማ ቋንቋ የተተረጎመውን “ይህ የመንግሥት ምሥራች” የተሰኘውን ቡክሌት መጽሐፍ ይጨምሩ ነበር። ወንድም ዎልድረን ይህን ቡክሌት ሲተረጉም ይረዳው ከነበረ ፍላጎት ካለው ሰው ጋር ይህን መጽሐፍ በተመለከተ አንድ አስቂኝ ተሞክሮ ያስታውሳል። “አዳም ፍጹም ሰው ነበር” ለሚለው ዓረፍተ ነገር ተመሳሳዩን የናማ ፍቺ አላገኙም ነበር። ስለዚህ ፍላጎት የነበረው ሰውዬም “ዝም ብለህ አዳም እንደ በሰለ ኮክ ነበር ብለህ ጻፍ። የናማ ሰዎች አዳም ፍጹም እንደነበረ ይገባቸዋል” አለው። የናሚቢያ ተወላጆች ከሆኑት መካከል ለብዙዎቹ የቅዱስ ጽሑፉን ዕውቀት ለማስተላለፍ የተጀመረው በዚህ ዓይነት ነበር።—ከዳንኤል 11:33 ጋር አወዳድር።

አዲስ ምዕራፍ ላይ መድረስ

በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለው መጽሐፍ ወደ ንዶንጋና ክዋኛማ ቋንቋዎች በተተረጎመ ጊዜ አንድ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። ከዊንድሆክ በስተሰሜን 720 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በኦቫምቦላንድ የሚኖሩት ብዙ የናሚቢያ ሕዝቦች የሚናገሯቸው ሁለት ዋና ዋና ቋንቋዎች እነዚህ ናቸው። ያኔ የኦቫምቦላንድ ግዛት በሆነችው በዶንዳንግዋ የአቅኚ ቤት ተቋቁሞ ነበር። በዚህ አካባቢ ያሉ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በመጠበቂያ ግንብ ላይ ከተመሠረተው ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት እንዲጠቀሙ ለመርዳት በኦቫምቦላንድ የሚያገለግሉት ልዩ አቅኚዎች የእንግሊዝኛውን የጥናት ርዕሰ ትምህርት ፍሬ ነገር ወደ ንዶንጋና ክዋኛማ ቋንቋዎች እንዲተረጉሙ ይመደቡ ነበር።

የትርጉም “ቢሮው የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች በአንድ ያረጀ የማባዣ መኪና ከሚባዙበት ከአንድ ጋራዥ ግድግዳ ማዕዘን ተከፍሎ የተሠራ ነበር። የዚህ የማባዛት ሥራ ሁኔታዎች ዘመናዊ ስላልነበሩና የበጋው ወራት ሙቀት በ100 እና በ110 ዲግሪ ፋረንሃይት መካከል ድረስ ከፍ ይል ስለነበር በዚህ አድካሚ ሥራ ላይ ማተኮር ቀላል አልነበረም። የሆነው ሆኖ አዳዲስ ብሮሹሮችና በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተሰኘው መጽሐፍ የተተረጎሙት እዚህ ነበር።

በኦቫምቦላንድና በሌሎችም የናሚቢያ ክፍሎች ጉባኤዎች እየተቋቋሙ በሄዱ ቁጥር የሕዝቡ ተቀባይነት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የተሻለ ግቢና ሕንፃ ማግኘት ያስፈልግ ነበር። በተጨማሪም በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ላሉት ሥፍራዎች ትኩረት መስጠት እንዲቻል ይበልጥ ማዕከላዊ የሆነ ሥፍራ ያስፈልግ ነበር። በመሃሉም በመንግሥቱ ስብከት ሥራ ላይ የነበረው አግባብ የሌለው ጥላቻ ቀንሶ ነበር። ስለዚህ በዊንድሆክ ከሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች በአንዱ በተለገሠ ሠፊ መሬት ላይ የሕንፃ ሥራ ይጀመር ዘንድ ፈቃድ ተገኘ። ወዲያው ከ40 የሚበልጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች በግንባታው ሥፍራ ተገኙና ታህሣስ 1990 የትርጉም ቢሮዎቹ ተሠርተው አበቁ።

አሁን በዚህ ዘመናዊ ሕንፃ ላይ በምቹ ቢሮዎችና ክፍሎች ሆኖ በመሥራት ለብዙዎች ዕውቀትን የማድረሱ ሥራ እየተፋጠነ ነው። አዳዲስ ጽሑፎች ወደ ሄሬሮና ክዋንጋሊ ቋንቋዎች ያለማቋረጥ በመተርጎም ላይ ይገኛሉ። የንዶንጋና የክዋኛማን ቋንቋዎች በተመለከተ በሁለቱም ቋንቋዎች የሚቀርብ ወርሃዊ ባለቀለም የመጠበቂያ ግንብ እትም በመውጣት ላይ ነው። እትሙ ሁሉንም የጥናት ርዕሰ ትምህርቶችና ሌሎችንም ጽሑፎች ይይዛል። ይህም ከብዙ ዓመታት በፊት በደረቁ ወንዝ ከነበረው አነስተኛ ጅምር በጣም ልቆ የሄደ ነው።

አሁን “አልገባኝም” የሚለው ቃል እምብዛም አይሰማም። በዚህ ፈንታ በናሚቢያ የሚገኙ ከ600 በላይ የሆኑ የይሖዋ ምስክሮች ለሰማያዊ አባታቸው በጣም አመስጋኞች በመሆናቸው “የቃልህ ፍቺ ያበራል፣ ሕፃናትንም [ተሞክሮ የሌላቸውን] አስተዋዮች ያደርጋል” ሊሉ ይችላሉ።—መዝሙር 119:130

[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በሄሬሮ ሕዝቦች መካከል የምሥራቹን ማወጅ

የናሚቢያን ሕዝቦች ለመጥቀም ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን መተርጎም

በናሚቢያ የሚገኘው የትርጉም ቢሮ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ