የአንባብያን ጥያቄዎች
ዕብራውያን 11:26 የሚናገረው ሙሴ ራሱ “ክርስቶስ” እንደሆነ ነው ወይስ የክርስቶስ ምሳሌ እንደሆነ?
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ሙሴ እምነት ሲገልጽ ሙሴ “ከግብፅ ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና . . . ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቷልና” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 11:26) ጳውሎስ እዚህ ላይ ሙሴን እንደ “ክርስቶስ” ወይም ቅቡእ አድርጎ የጠቀሰው ይመስላል።
ሙሴ በብዙ መንገዶች ለመጪው መሢሕ አምሳል መሆኑ እሙን ነው። ሙሴ ራሱ ነቢይ የነበረ ቢሆንም ‘እንደ እርሱ’ ያለ ታላቅ ነቢይ እንደሚመጣ ተንብዮአል። ብዙ አይሁዶችም ኢየሱስ “ነቢይ” እንደነበረ ተሰምቷቸው ነበር። ይህንንም ደቀ መዛሙርቱ አረጋግጠዋል። (ዘዳግም 18:15-19፤ ዮሐንስ 1:21፤ 5:46፤ 6:14፤ 7:40፤ ሥራ 3:22, 23፤ 7:37) ሙሴ የሕጉ ቃል ኪዳን መካከለኛም ነበር፤ ኢየሱስ ግን በክብራማው አዲስ ኪዳን ውስጥ “በሚሻል ኪዳን ደግሞ መካከለኛ” በመሆን “በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል አገልግሎት” ተቀብሎአል። (ዕብራውያን 8:6፤ 9:15፤ 12:24፤ ገላትያ 3:19፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5) ስለዚህ ሙሴ በአንዳንድ ሁኔታዎች ረገድ የመጪው መሢሕ አምሳያ ነበር ሊባል ይችላል።
ነገር ግን የዕብራውያን 11:26 ዋና ትርጉም ይህ አይመስልም። ሙሴ ስለ መሢሑ ዝርዝር ነገሮችን በማወቅ በግብፅ ሳለ ያለፈባቸውን ችግሮች በሙሉ ስለ መሢሑ ብሎ ወይም የእርሱ ወኪል እንደሆነ አድርጎ በመቁጠር ሆን ብሎ እንዳደረገው የሚያሳይ ማስረጃ የለም።
በዕብራውያን 11:26 ላይ ያሉት የጳውሎስ ቃላት “የክርስቶስ ሥቃይ” በክርስቲያኖች ላይ እንደበዛ ከተናገረው ጋር አንድ ዓይነት ሐሳብ የሚያስተላልፉ ናቸው ብለው ሐሳብ የሰጡ አሉ። (2 ቆሮንቶስ 1:5) ቅቡአን ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተሰቃየና እነርሱም ‘ከእርሱ ጋር ቢሰቃዩ [በሰማይ] ከእርሱ ጋር አብረው እንደሚከበሩ’ ያውቁ ነበር። ሙሴ ግን መጪው መሢሕ ምን ሥቃይ እንደሚደርስበት አያውቅም ነበር፤ እንዲሁም ሙሴ ሰማያዊ ተስፋ አልነበረውም።—ሮሜ 8:17፤ ቆላስይስ 1:24
ይሁን እንጂ ሙሴ “ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት” እንደሆነ እንዴት እንዳሰበ በቀላሉ መረዳት ይቻላል።
ጳውሎስ በዕብራውያን 11:26 ላይ “ክርስቶስ” በማለት በጻፈ ጊዜ ከዕብራይስጡ ማሺያክ ወይም መሢሕ ጋር የሚመሳሰል ትርጉም ባለው ክሪስቶ የተሰኘ የግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። “መሢሕ”ም ሆነ “ክርስቶስ” የሚሉት ቃላት ሁለቱም ትርጉማቸው “የተቀባው” ማለት ነው። ስለዚህ ጳውሎስ የጻፈው ‘ስለ ተቀባው መነቀፍን’ ሙሴ እንዴት እንደተመለከተው ነበር። ታዲያ ሙሴ ራሱ “የተቀባው” ተብሎ ሊጠራ ይችል ነበርን?
አዎን። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ሰው በራሱ ላይ ዘይት ይፈስና አንድ ልዩ ሹመት ይጸድቅለት ነበር። “ሳሙኤልም የዘይቱን ብርሌ ወስዶ [በሳኦል ራስ] ላይ አፈሰሰው።” “ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ [ዳዊትን] በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም [የይሖዋም አዓት] መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ።” (1 ሳሙኤል 10:1፤ 16:13፤ ከዘጸአት 30:25, 30፤ ከዘሌዋውያን 8:12፤ ከ2 ሳሙኤል 22:51፤ ከመዝሙር 133:2 ጋር አወዳድር።) ሆኖም ነቢዩ ኤልሳዕንና የሶርያ ንጉሥ አዛሄልን የመሳሰሉ አንዳንድ ሰዎች ቃል በቃል ዘይት በራሳቸው ላይ ስለመፍሰሱ የሚገልጽ ማስረጃ ባይኖርም “ቅቡአን [የተቀቡ]” እንደሆኑ ተነግሮላቸዋል። (1 ነገሥት 19:15, 16፤ መዝሙር 105:14, 15፤ ኢሳይያስ 45:1) ስለዚህ አንድ ግለሰብ ለአንድ ነገር ሲመረጥ ወይም ልዩ ተልእኮ ሲሰጠው “የተቀባ” ሊሆን ይችል ነበር።
በዚህ መንፈስ ሙሴ ራሱም በአምላክ የተቀባ ነበር፤ እንዲያውም አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ለዕብራውያን 11:26 “የአምላክ ቅቡእ” ወይም “የተቀባው” የሚሉ ትርጉሞች ይሰጣሉ። ሙሴ የይሖዋ ወኪልና እሥራኤልን ከግብፅ መርቶ የሚያወጣ በመሆን የተላከ ነበር። (ዘጸአት 3:2-12, 15-17) ሙሴ በግብፅ ባለጠግነትና ክብር መካከል ያደገ ቢሆንም እንደ ትልቅ ሀብት የቆጠረው አምላክ የሰጠውን ተልእኮ ሲሆን እርሱንም ተቀብሎ ፈጽሞታል። በዚህም መሠረት ጳውሎስ “ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቦአልና” ብሎ ስለ ሙሴ ሊጽፍ ችሎአል።