በቤልጂየም ለሚገኙ ‘ለሁሉም ዓይነት ሰዎች’ እውነትን ማዳረስ
ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክ ፈቃድ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና ትክክለኛውን የእውነት እውቀት ወደማወቅ እንዲደርሱ’ መሆኑን ለክርስቲያን ቅቡዓን መሰሎቹ አስታውሷቸዋል። ለዚህም ሥራ “ጸጥና ዝግ” ብለው አድማጭ ጆሮ ላላቸው የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ ይችሉ ዘንድ እንዲጸልዩ ተመክረዋል።—1 ጢሞቴዎስ 2:1-4
በዛሬው ጊዜ ‘ለሁሉም ዓይነት ሰዎች’ ምሥራቹን ማዳረስ በቤልጂየም ውስጥ ለሚገኙት የይሖዋ ምስክሮች ልዩ ትርጉም አለው። የታንጋኒካን ሐይቅ ወይም የሚሺጋንን ሐይቅ ግማሽ የምታህለው ትንሽ አገር የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ጊዜ ጀምሮ በነገዶቿና በባሕሏ ላይ ከፍተኛ ለውጦችን አድርጋለች። ካሏት ሦስት ባሕላዊ ማኅበረሰቦች ከፍሊሚሾች (ደች)፣ ከፈረንሳዮችና ከጀርመኖች በተጨማሪ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችና ባሕላዊ ቡድኖች አሉባት። ጥቂቶቹን ብቻ ለመጥቀስ ያህል ዓረቦች፣ ቱርኮች፣ ሕንዶች፣ ቻይናውያን፣ ፊሊፒናውያን፣ አፍሪካውያንና አሜሪካውያን ይገኙበታል። በቤልጂየም ውስጥ ከሚገኙ ከ10 ሰዎች አንዱ ከሌላ አገር የመጣ እንደሆነ ይገመታል።
በዚህም ምክንያት በቤልጂየም የሚገኙ ምስክሮች በዓለም ዙሪያ እንደሚገኙት ክርስቲያን ወንድሞቻቸው ሁሉ የምሥራቹን ‘ለሁሉም ዓይነት ሰዎች’ ለማዳረስ ተፈታታኝ ሁኔታ ገጥሟቸዋል። እንደዚህ የተለያየ ብሔረሰቦች ባላቸው ሕዝቦች መካከል መስበኩ ምን ይመስላል? አንድ ሰው ፍጹም የተለያየ ባሕልና ሃይማኖታዊ መሠረት ያላቸውን ሰዎች እንዴት ቀርቦ ሊያነጋግራቸው ይችላል? ለመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክትስ የሚሰጡት ምላሽ ምንድን ነው?
በራስ አነሳሽነት የተደረገ ጥረት ውጤት አስገኘ
‘ሁሉንም ዓይነት ሰዎች’ ስለ መንግሥቱ ምሥራች ማናገር ደስ የሚያሰኝና አስደናቂ ተሞክሮ ነው። በተጨናነቁት መንገዶች፣ በገበያ ቦታዎች፣ በሕዝብ መጓጓዣዎች፣ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ከሁሉም አህጉራት የመጡ ሰዎች ይገኛሉ። የመንግሥቱ ሰባኪዎች በራስ አነሳሽነት ትንሽ ጥረት በማድረግ በቀላሉ ውይይት ለመክፈት ይችላሉ። ይህም ብዙውን ጊዜ ወደ ጥሩ ውጤት ይመራል።
በአንድ የአውቶቡስ ፌርማታ ላይ አንዲት ምስክር ለአንዲት አፍሪካዊት ወይዘሮ ሞቅ ያለ ፈገግታ በማሳየት ብቻ ውይይት ጀመረች። ወይዘሮዋም ስለ አምላክ መንግሥት በመስማቷ ደስታዋን ገለጸችና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ ለማወቅ እንደምትፈልግ ገለጸችላት። የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችን ተቀበለችና አድራሻዋን ለምስክሯ ሰጠቻት። ምስክሯ በቅርቡ መጥታ እንደምትጎበኛት ስትነግራት ወይዘሮዋ ተቃወመችና “የለም! የለም! ስትመጪ እቤት እንድታገኚኝ ቁርጥ ያለ ቀጠሮ እንያዝ” አለቻት።
ምስክሯ ከሦስት ቀን በኋላ ወደ ሴትየዋ ቤት ለመሄድ ስትዘጋጅ የሴትየዋ አድራሻ እንደጠፋባት አወቀች። ሆኖም የመንገዱን ስም ስለምታስታውሰው በመንገዱ ላይ በሚገኘው እያንዳንዱ ቤት ውስጥ አፍሪካዊት ስም ያላት ወይዘሮ ታገኝ እንደሆነ ከቤቷ ወጥታ በመሄድ መጠየቅ ጀመረች። የምትፈልገውን ሳታገኝ እስከ መንገዱ መጨረሻ ድረስ ሄደች። ምንኛ የሚያሳዝን ያልታሰበ ነገር ነበር! ወደ ቤቷ ለመሄድ ስትዘጋጅ የምትፈልጋት ወይዘሮ ከየት መጣች ሳይባል ከፊቷ ለፊቷ ቆመች። ጊዜውም ልክ ለመገናኘት የተስማሙበት ሰዓት ነበር! የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ።
ስለተለያዩ ልማዶች፣ እምነቶችና ባሕሎችስ ምን ሊባል ይቻላል? ለምሳሌ ያህል ስለ ሒንዱ እምነት ምን ሊባል ይቻላል? አንዲት አቅኚ ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክንያቱን ማስረዳት ከተባለው መጽሐፍ ላይ ያነበበችውን ታስታውሳለች። እንዲህ ይላል “በሒንዱ ሃይማኖት ውስጥ ባለው ግራ የሚያጋባ ፍልስፍና ላይ በመወያየት ፈንታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የሚያረካ እውነት ተናገር። . . . በቃሉ ውስጥ የሚገኘው ግልጽ እውነት ጽድቅን የተራቡና የተጠሙ ሰዎችን ልብ ይነካል።”
አቅኚዋ እህት ካሺ የምትባል ሕንዳዊት ባገኘች ጊዜ ያደረገችው ይህንኑ ነበር። ካሺም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ የቀረበላትን ግብዣ ተቀበለች። ካሺም ፈጣን ዕድገት አደረገችና ብዙም ሳይቆይ እየተማረች ያለችውን ነገር ለጓደኞቿ መናገር ጀመረች። አንድ ቀን የአንድ አምባሳደር ሚስት አቅኚዋን እህት አገኘቻትና እንዲህ ስትል ጠየቀቻት፦ “ካሺን መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠኚያት አንቺ ነሽ? ምን ዓይነት ጥሩ አስተማሪ ናት! በብዙ ነጥቦች ላይ ልታሳምነኝ ችላለች። የሒንዱ ሃይማኖት ተከታይ የሆነችው እሷ እኔን ካቶሊኳን መጽሐፍ ቅዱስ ስታስተምረኝ እስቲ ይታይሽ!” ብላ ስትነግራት አቅኚዋ እህት በጣም ተደንቃ ነበር።
ፊሊፒናውያን ሲያጋጥሟችሁ ከእነሱ አብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚወዱ ወዲያው ትገነዘባላችሁ። ሞቅ ያለ መንፈስ ያላቸውና እንግዳ ተቀባይ ናቸው። ከእነርሱ ጋር ውይይት መጀመር በጣም ቀላል ነው። አንዲት ፊሊፒናዊት ወይዘሮ ሁለት መጽሔቶች ተቀበለችና ካቶሊክ ስለሆነች ጣለቻቸው። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ እንደገና ሁለት መጽሔቶች ተቀበለችና ቦርሳዋ ውስጥ አስቀመጠቻቸው። አንድ ቀን ምሽት ማንበብ ስላሰኛት የሚነበብ ነገር ስትፈላልግ ከቆየች በኋላ መጽሔቶቹን አገኘቻቸው። እያመነታች ማንበብ ጀመረች። ፍላጎቷም እያደገ ሄደ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ምስክሯ ወደ ቤቷ መጣችና አነጋገረቻት። ሴትየዋም ብዙ ጥያቄ ጠየቀቻት። የካቶሊክ እምነቷን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚለው ጋር ስታወዳድር ይህ የመጀመሪያ ጊዜዋ ነበረ። የቀረበላትን ምክንያታዊ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ መልእክት በመጨረሻ እውነትን እንዳገኘች እንድታምን አደረጋት።
“እንጀራህን በውኃ ላይ ጣለው”
በቤልጂየም የሚኖሩ የውጭ ዜጎች በንግድ ምክንያት ወይም ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ 150 ኤምባሲዎች በአንዱ ወይም በአውሮፓ ኮሚዩኒቲ ኮሚሽን ውስጥ ለመሥራት የመጡ ናቸው። አብዛኞቹ የሚቆዩት ለጥቂት ዓመታት ብቻ ነው። ለእነርሱ መመስከርና እነርሱን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት መጀመሪያ ላይ ፍሬ የሌለው ይመስላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው፣ ከብዙ ቀን በኋላ ታገኘዋለህና” በማለት ያሳስበናል። (መክብብ 11:1) ብዙውን ጊዜ ያልታሰቡ አስደናቂ ውጤቶች ይገኛሉ።
ከአንዲት ምስክር አዘውትራ መጽሔት በምትቀበል አሜሪካዊት ወይዘሮ ላይ ይህ ሁኔታ ደርሷል። ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በየጊዜው የማጥናትን ጥቅም ምስክሯ አስረዳቻትና ከእርሷ ጋር እንድታጠና ጋበዘቻት። ሴቲቱ ግብዣውን ተቀበለችና ፈጣን ዕድገት አሳየች። ብዙም ሳትቆይ በሐሰተኛ እና በእውነተኛ ሃይማኖት መካከል ያለውን ልዩነት ተረዳች። ስለዚህ ቤቷን በሙሉ ከሃይማኖታዊ ሥዕሎች አጸዳች። ከዚያም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የምትመለስበት ጊዜ ደረሰ። ታዲያ መንፈሳዊ ዕድገቷ በዚሁ ይቀጭ ይሆን? ምስክሯ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ካለች አንዲት ምስክር የስልክ ጥሪ ደርሷት ያች ወይዘሮ ጥናቷን ቀጥላ ራሷን ለይሖዋ አምላክ ከወሰነች በኋላ መጠመቋን ስትሰማ ደስታዋ ምን ያህል እንደሆነ ገምቱት! እንዲያውም በዚያን ጊዜ ረዳት አቅኚ ሆና በማገልገል ላይ ነበረች።
ቀደም ብለው የተጠቀሱት የሕንዳዊቷ የካሺና የፊሊፒናዊቷ ወይዘሮም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ካሺ ወደ ሕንድ ስትመለስ ከባለቤቷ ጋር ጥናታቸውን እንደገና ቀጠሉ። በኋላም ሁለቱም ራሳቸውን ለይሖዋ ወሰኑና በስብከቱ ሥራ መሳተፍ ጀመሩ። ሌሎች ምስክሮች በሌሉበት አካባቢ ይኖሩ ስለነበር ቤታቸውን የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት እንዲደረግበት ፈቀዱ። ካሺ ጤንነቷ እስከፈቀደላት ድረስ ረዳት አቅኚ ሆና በማገልገል 31 ሰዎችን ያቀፉ ስድስት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ትመራለች። በተመሳሳይም ፊሊፒናዊቷ ሴት ከጊዜ በኋላ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄደች። እዚያም ራሷን ወስና ከተጠመቀች በኋላ የዘወትር አቅኚ ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች። እነዚህ አስደሳች ውጤቶች በቤልጂየም ያሉት አስፋፊዎች በክልላቸው ውስጥ ላሉ ሰዎች መስበክ በመቀጠላቸው ከሚደሰቱባቸው ውጤቶች መካከል ናቸው።
ቋንቋዎች ያስከተሉት ተፈታታኝ ሁኔታ
ቅርንጫፍ ቢሮው ‘ለሰዎች ሁሉ’ የመስበኩን ሥራ ለማከናወን ከ100 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች እንዲኖረው አስፈልጎታል። አሁን ቤልጂየም ውስጥ በአሥር ቋንቋዎች የሚጠቀሙ ጉባኤዎች አሉ። ካሉት 341 ጉባኤዎች መካከል 61ዱ በውጭ አገር ቋንቋዎች የሚደረጉ ሲሆኑ ከ26,000 መንግሥት አስፋፊዎች መካከል 5,000ዎቹ የውጭ አገር ዜጎች ናቸው። አንድ ጉባኤ ከ25 የተለያዩ አገሮች የመጡ ወንዶችና ሴቶች ይገኙበታል። በስብሰባቸው ላይ የሚኖረውን የቆዳ ቀለምና ልዩ ልዩ የብሔራዊ፣ የባሕልና የዘር ባሕርይ ሁኔታ ገምቱ! ሆኖም በወንድሞች መካከል የሚታየው ፍቅር እና አንድነት እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆናቸው ጠንካራ ምስክር ነው።—ዮሐንስ 13:34, 35
በቤልጂየም ውስጥ በውጭ አገር ቋንቋ የምሥራቹን መስማት የሚገባቸው ነዋሪዎች ስላሉ አንዳንድ አስፋፊዎች እንደ ቱርክኛ፣ አረብኛ እና ቻይንኛ የመሳሰሉ ትዕግሥትን የሚፈታተኑ ቋንቋዎችን ለመማር ፈቃደኞች ሆነዋል። የጥረታቸውንም ዋጋ በገፍ አግኝተዋል።
አረቦች በሚኖሩበት አካባቢ የሚያገለግሉ ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ተግባራዊነት በማጉላት ፍላጎታቸውን ማቀጣጠል የሚቻል ሆኖ አግኝተውታል። አንድ የመንግሥቱ አስፋፊ ከአንድ አረብ ፕሮፌሰር ጋር አስደሳች የሆነ ውይይት አድርጎ ነበር። ሆኖም ከዚያ በኋላ ለመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ፕሮፌሰሩን እንደገና ሊያገኘው አልቻለም። አስፋፊው በቀላሉ ተስፋ ሳይቆርጥ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች በመጻፍ እቤቱ ማስታወሻ እየተወለት መሄድ ጀመረ። ይህ ነገር ፕሮፌሰሩን በጣም አስገረመውና መጽሐፍ ቅዱስን አመዛዝኖ ለመመርመር ወሰነ። ባገኘው ነገር በጣም ተደንቆ እርሱም ሆነ እንደ እርሱው የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆነችው ሚስቱ አንድ ላይ በመሆን የተወሰኑ ምሽቶች ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ወሰኑ።
በትላልቅ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩትን በርካታ ቻይናውያን ነዋሪዎችን ለመርዳት የሚሞክሩ ወንድሞች ከቋንቋው ልዩነት ባሻገር መወጣት የሚገባቸው ሌላ እንቅፋት ነበር። አብዛኞቹ ቻይናውያን ፈጣሪ አምላክ መኖሩን ወይም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን አያምኑም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ስለምን እንደሚናገር ለማወቅ ጉጉት አላቸው። በተጨማሪም ማንበብ የሚወዱ ናቸው። የተሰጣቸውን ማንኛውም ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ አለማንበባቸው ያልተለመደ ነገር ነው። አብዛኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንኳን በጥቂት ቀኖች ውስጥ ያነባሉ። ቅን ልብ ካላቸው የአምላክ ቃል ያለው ኃይል ይገፋፋቸዋል።
አንዲት ቻይናዊት ወይዘሮ ስለ ፈጣሪ የተነገራትን ሐሳብ ለመቀበል በጣም ተቸግራ ነበር ሆኖም በሁለተኛ ጥናቷ ወቅት “አሁን በይሖዋ አምላክ አምናለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን ለመጻፍ 1,600 ዓመታት ያህል ፈጅቶ 40 በሚያክሉ የተለያዩ ሰዎች የተጻፈ ቢሆንም በአንድ አጠቃላይ መልእክት ላይ ያተኮረ መሆኑ ይሖዋ አምላክ እነርሱን አነሳስቶ እንዳስጻፈው ያሳያል። ይህ ትክክለኛ አስተሳሰብ ነው” ብላ ስትናገር ዓይኖቿ እንባ አቅርረው ነበር።
ሌላ ቻይናዊት በአውቶቡስ ስትጓዝ አንዲት ምስክር ቀረብ ብላ አነጋገረቻት። ወይዘሮዋም “ክርስቲያን ነሽ?” ብላ ምስክሯን ጠየቀቻት። ቀጥላም ክርስቲያን ነን በሚሉት መካከል ባለው ቅራኔ እንደምታዝን ገለጸችላት። ምስክሯም በተናገረችው ነገር ተስማማችና መጽሐፍ ቅዱስ ግን እርስ በርሱ እንደማይጋጭ ገለጸችላት። እንደዚህ እየተባባሉ ሳሉ ወይዘሮዋ መውረጃዋ ደረሰና አድራሻዋን ለምስክሯ ሰጠቻት። ምስክሯም እቤቷ ሄዳ ወይዘሮዋን ስትጎበኛት “እንዲህ መሆኑን ባውቅ ኖሮ ከአንድ ዓመት በፊት በአውቶቡሱ እሳፈር ነበር” በማለት በደስታ ተናገረች። ምን ለማለት እንደፈለገች ስትጠየቅም “ወደ ዩኒቨርሲቲ በአውቶቡስ ስሄድ ይህ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበር። አንድ ዓመት እንዳቃጠልኩ መገመት ትችያለሽ!” ስትል አባባሏን አብራራች። ወደ ቻይና ከመመለሷ በፊት ለጥቂት ወራትም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናቷ ደስተኛ ነበረች።
እነዚህን የመሰሉ ተሞክሮዎች የቤልጂየምን ምስክሮች አንድ ትምህርት አስተምሯቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወይም ይህ ወይም ያ ማናቸው እንዲበቅል ወይም ሁለቱ መልካም እንዲሆኑ አታውቅምና በማለዳ ዘርህን ዝራ፣ በማታም እጅህን አትተው” ይላል። (መክብብ 11:6) ቋንቋ፣ ልማድና ባሕል የፈጠሩትን ችግር ለመወጣት የተደረገው ጥረት ከውጤቱ አንፃር ሲታይ ተገቢ ነበር ለማለት ይቻላል። ልብን ሞቅ የሚያደርገው የሰዎቹ ምላሽ አምላክ በእውነትም “ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደሆነ” ያሳያል።—ሥራ 10:34, 35