የወደፊቱን የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታ መተንበይ
አካውንታንሲ ኤጅ የተባለው የለንደን መጽሔት የኢኮኖሚው ገበያ ሁኔታ አለመረጋጋት እንዲሁም የ1987ቱን የገበያ ውድቀት መተንበይ ባቃታቸው የኢኮኖሚ ተንታኞች ላይ እምነት ማጣታቸው አንዳንድ የንግድ ሰዎች የወደፊቱን የገንዘብ ነክ ጉዳዮቻቸውን ለመተንበይ ወደ ኮከብ ቆጠራ ዞር እንዲሉ አድርጓቸዋል ብሏል። መጽሔቱ “ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን በሚመለከት ኮከብ የሚቆጥሩ ሰዎች በሚያደርጉት ዝርዝር የሆነ የገበያ ትንበያቸው ስመ ጥር የሆኑ ሰዎች የሚገኙት አስደናቂ የሆነ የደንበኞች ቡድን ዝርዝር ማግኘታቸውን” ጠቅሷል።
አንድ አማካሪ ለ30 ዓመታት ሲከታተለው የነበረውን የየዕለቱን የገንዘብ ነክ ጉዳዮች ዝርዝር ዑደት ከፕላኔቶች እንቅስቃሴ ጋር አነፃፅሮታል። በዚህም መሠረት ትንበያውን አቅርቧል። ምንም እንኳን ብዙ ደንበኞች ከ1987 በፊት ምክሩን ለመከተል የማይፈልጉ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን እሱን ለመስማት የተዘጋጁ በምንም ነገር የማይበገሩ የገንዘብ ሥራ አዋቂዎችን አግኝቷል።
ሌላው ገንዘብ ነክ የሆኑ ጉዳዮችን በሚመለከት ኮከብ የሚቆጥር ሰው የሰዎችን የትውልድ ቀን መሠረት በማድረግ የአንድን ሰው ባሕርይ ለመገመትና “በንግድ በኩል ሊኖረው ስለሚችለው ዕድገት ምልክቶችን ለመጠቆም” የሚረዳ ቻርት አዘጋጅቷል። ሆኖም ሌላው ደግሞ የጨረቃ ዓመትን ተከትሎ ያለው ዑደት የብሩን ገበያ እንዲዋዥቅ ያደርገዋል ብሎ ያምናል። ይሁን እንጂ ከመደበኞቹ የገንዘብ ነክ ጉዳይ ተንታኞች ጋር ሲወዳደር ደንበኞቹ የዚህ ኮከብ ቆጣሪ ትንቢት “ለመሳሳት ያለው ዕድል በጣም አነስተኛ” ሆኖ አግኝተውታል።
ይሁን እንጂ እውነትነቱ የተረጋገጠለት አንድ የገንዘብ ጉዳዮችን የሚመለከት ትንቢት አለ። ከኮከብ ቆጠራ ጋር ግን ምንም ግንኙነት የለውም። ይህ ትንቢት ‘ምንም ዓይነት የመሳሳት ዕድል የሌለው’ አምላክ በሆነው በይሖዋ መንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። እርሱም “የማይዋሽ አምላክ” ነው። (ቲቶ 1:2) ነቢዩ ሕዝቅኤል “ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ፤ ወርቃቸውም እንደ ጉድፍ ይሆናል፤ . . . ብራቸውና ወርቃቸው ያድናቸው ዘንድ አይችልም” ብሎ ትንቢት እንዲናገር አድርጓል።—ሕዝቅኤል 7:19
ይህ የሚፈጸመው መቼ ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ እንደሚመጣ በተናገረለት “ታላቅ መከራ”ና ሕዝቅኤልም “የእግዚአብሔር [የይሖዋ አዓት] መዓት ቀን” ብሎ በጠራው ጊዜ ነው። (ማቴዎስ 24:21፤ ሕዝቅኤል 7:19) ምንም እንኳን ኮከብ ቆጣሪዎች ይመጣል ብለው ቢተነብዩም የገንዘብ ብልጽግና ለደኅንነት ማረጋገጫ አይሆንም። ሁሉም ዓይነት የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የንግድ የሥነ ምግባር ብልሹነት በሚወገድበት በዚህ ዓለም አቀፍ የሆነ ጥፋት ወቅት ድኅንነት ለማግኘት ዋስትና ሊሰጥ የሚችለው በታላቁ አዳኝ በይሖዋ አምላክ መታመን ብቻ ነው።—ምሳሌ 3:5, 6፤ ሶፎንያስ 2:3፤ 2 ጴጥሮስ 2:9