በታላቁ ፈጣሪያችን መደሰት
“እሥራኤል በፈጣሪው ደስ ይበለው፣ የጽዮንም ልጆች በንጉሣቸው ሐሤት ያድርጉ።”—መዝሙር 149:2
1.“በመጨረሻ ነፃነት አገኘን ” የሚሉ ጩኸቶች ቢኖሩም እውነተኛው የሰው ልጅ ሁኔታ ግን ምንድነው?
የዛሬው ዓለም “በጭንቀት ጣር” ተውጦአል። ይህ አባባል ኢየሱስ በ1914 በአንደኛው የዓለም ጦርነት የጀመረው መዓተኛ ዘመን ማለትም “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ስለሆነው ዘመን በተናገረው ትንቢት ላይ የተጠቀመበት ነው። (ማቴዎስ 24:3-8 አዓት) ብዙ የፖለቲካ ሰዎች ስለመጪው ጊዜ ተስፋ ከሚያስቆርጥ ሁኔታ በስተቀር ሌላ ነገር አይታያቸውም። በምሥራቅ አውሮፓ “በመጨረሻው ነፃነት አገኘን” እየተባለ ቢለፈፍም ባንድ ወቅት የዚያ አካባቢ ፕሬዘዳንት የነበሩ ሰው ሁኔታውን እንደሚከተለው በማለት አጠቃለው ገልጸውታል:- “የሕዝብ ቁጥር ፍንዳታ፣ የምድር ከባቢ አየር መሞቅ፣ የኦዞን መበሳትና ኤድስ፣ የኑክሌር አሸባሪነት ሥጋትና በሀብታሙ ሰሜናዊ ዓለምና በድሃው ደቡባዊ ዓለም መካከል በአስደንጋጭ ሁኔታ እየሠፋ የሄደው የኑሮ መራራቅ፣ የረሀብ አደጋ፣ ሕይወት ሊያኖር የሚችለው የመሬት ክፍልና የፕላኔታችን የማዕድን ሀብት መመናመን፣ አስተሳሰቡና ዝንባሌው በንግድ ቴሌቪዥን ሥርጭት የተቀረጸው ኅብረተሰብና በየአካባቢው የጦርነት ስጋት መኖሩ እነዚህ ሁሉ ከሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ ምክንያቶች ተዋሕደው ለሰው ልጅ አስጊ የሆነ አጠቃላይ ሁኔታ መኖሩን ያመለክታሉ”። ይህን የመጨረሻ የጥፋት ስጋት ሊያስወግድ የሚችል ምንም ዓይነት ሰብአዊ ኅይል የለም።—ኤርምያስ 10:23
2. ለሰው ልጆች ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ያለው ማን ነው? ከዚህ በፊትስ ምን እርምጃዎችን ወስዷል?
2 ይሁን እንጂ ታላቁ ፈጣሪያችን ለእነዚህ ችግሮች በሙሉ ዘላቂ መፍትሔ ያለው በመሆኑ ልንደሰት እንችላለን። በኢየሱስ ትንቢት ላይ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ከማይታየው “መገኘቱ ጋር ተያይዞ ተገልጿል። (ማቴዎስ 24:3, 37-39) ይሖዋ “አዲሶቹን ሰማያት” ለመፍጠር ኢየሱስን መሢሐዊ ንጉሥ አድርጎ በዙፋኑ ላይ አስቀምጦታል፣ ለዚሁም ይህ ታሪካዊ ክንውን በሰማይ የተፈጸመው 1914 መሆኑን ትንቢታዊው ማስረጃ ያመለክታል።a (2 ጴጥሮስ 3:13) ኢየሱስ ከሉዓላዊው ገዢ ከይሖዋ ጋር ተባባሪ ገዢ በመሆን አሁን አሕዛብን እንዲዳኛቸውና በግ መሰል የሆኑትን የምድር ትሑታን ከእልከኞቹ ፍየል መሰል ሰዎች እንዲለይ ውክልና ተሰጥቶታል። አምላካዊ ባሕርይ የሌላቸው “ፍየሎች” “ለዘላለም ቅጣት” ወይም ለዘላለማዊ ጥፋት ምልክት የተደረገባቸው ሲሆን “በጎቹ” ደግሞ በመንግሥቱ ምድራዊ ግዛት ለዘላለም ለመኖር ምልክት ተደርጎላቸዋል።—ማቴዎስ 25:31-34, 46
3. እውነተኛ ክርስቲያኖች ሐሴት ለማድረግ ምን ምክንያት አላቸው?
3 አሁን የእነዚህ ታዛዥ በጎች ክፍል የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች የተባበሩአቸው በምድር ላይ ያሉ የመንፈሳዊ እሥራኤል ቀሪዎች የዘላለም ንጉሥ የሆነው የይሖዋ ታላቅ ዓላማውን በልጁ መንግሥት አማካኝነት ወደ መደምደሚያው ሲያመጣው የሚደሰቱበት ብዙ ምክንያት አላቸው። “የማዳንን ልብስ አልብሶኛልና . . . በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፣ ነፍሴም በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች። ምድርም ቡቃያዋን እንደምታወጣ፣ ገነትም ዘሩን እንደሚያበቅል፣ እንዲሁ ጌታ እግዚአብሔር [የይሖዋ አዓት] ጽድቅንና ምስጋናን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ያበቅላል” ሊሉ ይችላሉ። (ኢሳይያስ 61:10, 11) ይህ “መብቀል” አሁን ከአሕዛብ ሁሉ መካከል የይሖዋን ምስጋና ለመዘመር እየተሰባሰቡ ባሉት በሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች እየታየ ነው።
‘የመሰብሰቡን ሥራ ማፋጠን’
4, 5. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች መሰብሰብ በትንቢት አስቀድሞ የተነገረው እንዴት ነበር? (ለ) በ1992 የአገልግሎት ዓመት ምን ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል?
4 የሰይጣን ሥርዓት ፍጻሜ እየተቃረበ ሲመጣ የማሰባሰቡ ሥራ እየተፋጠነ ነው። ታላቁ ፈጣሪያችን “ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ . . . እኔም እከብር ዘንድ የአታክልቴን ቡቃያ፣ የእጄ ሥራ የምትሆን ምድሪቱን ለዘላለም ይወርሳሉ። ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሽ ብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ” በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 60:21, 22) ይህ ማፋጠን በዚህ መጽሔት ከገጽ 12 እስከ 15 ላይ በቀረበው የ1992 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምስክሮች ዓለም አቀፍ ሪፖርት ላይ በአስደናቂ ሁኔታ ተገልጿል።
5 በዚህ ሪፖርት ላይ ጎላ ብሎ የሚታየው የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች አዲስ ከፍተኛ ቁጥር 4, 472, 787 ደርሶአል። ካለፈው ዓመት በ193, 967 የሚበልጥ ሲሆን 4.5 በመቶ ጭማሪ አለው ። በ1992 301, 002 አዲስ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መጠመቃቸው እጅግ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እየተቀበሉ መሆናቸውን ያመለክታል። በዚህ “የጨለማና የጭጋግ ቀን . . . ታላቅና ብርቱ ሕዝብ” እንደ አንበጣና ደጎብያ እንዲሁም እንደኩብኩባና ተምች ሠራዊት የመንግሥቱን ምስክርነት “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ” ሲያሠራጩት ምንኛ እንደሰታለን! (ኢዩኤል 2:2, 25፤ ሥራ 1:8) የይሖዋ አገልጋዮች የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር አይሮፕላን በበረዶማ ቀበሌዎች ላይ ከ50 በላይ ጉብኝት ካደረገበት ከቀዝቃዛው አላስካ እስከ ማሊና ቡርኪናፋሶ እንዲሁም እስከ ማይክሮኔሽያ የተበታተኑ ደሴቶች ድረስ “የይሖዋን ማዳን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይመጣ ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን” በመሆን እያበሩ ነው።—ኢሳይያስ 49:6 አዓት
6, 7. በቅርብ ዓመታት ምን ያልተጠበቀ የሁኔታዎች መለወጥ ነው የታየው? የይሖዋ አገልጋዮችስ ለዚህ ለውጥ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው?
6 ይሖዋ ሕዝቡን በመጠበቅና በሕይወት በማኖር ረገድ እንደ ምሽግና ጠንካራ ግንብ ሆኖ ቆይቷል። በብዙ የምድር ክፍሎች የይሖዋ ምስክሮች በብዙ አሥርተ ዓመታት ለሚቆጠር ጊዜ የጭካኔ ጭቆናና ስደት ተቋቁመው ለመኖር ተገድደዋል። (መዝሙር 37:39, 40፤ 61:3, 4) በቅርብ ግዜ ግን እንደተአምር በሚቆጠር ሁኔታ የአምላክ ሕዝቦች ታላቁ ፈጣሪያችን በምድር ላይ ክርስቶስን ንጉሥ አድርጎ እንደሾመው በነፃነት ማስታወቅ ይችሉ ዘንድ እገዳዎችና መሰናክሎች 21 ከሚያህሉ አገሮች ተነስተዋል።—መዝሙር 2:6-12
7 የይሖዋ ሕዝቦች አዲስ ያገኙትን ነፃነት በሚገባ እየተጠቀሙበት ነውን? ቡልጋሪያ፣ ሮማኒያና በምሥራቅ አውሮፓ የሚገኘውን የቀድሞውን የሶቪየት ኅብረት ክፍልና በአፍሪካ ደግሞ አንጎላ፣ ቤኒንና ሞዛምቢክ ያገኙን ጭማሪ በሠንጠረዡ ላይ ተመልከቱ። እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ችግር ባለበት በዛየር እንኳን ሳይቀር ዕድገቱ አስደናቂ ነው። ነፃነት ያገኙ ወንድሞቻችን ከልብ ደስ እያላቸው “እናንተ ሕዝቦች ይሖዋን አመስግኑ፤ እርሱ ጥሩ ነውና፣ . . . እርሱ ብቻውን ድንቅና ታላላቅ ነገሮችን ለሚያደርገው። ፍቅራዊ ቸርነቱ ለዘላለም ነውና” ለሚለው ጥሪ መልስ ሊሰጡ ይችላሉ። (መዝሙር 136:1, 4 አዓት) እነዚህ ምስጋናዎች የተገለጹት ሌሎች በግ መሰል ሰዎችን ከመንግሥቱ ጎን ለመሰብሰብ በተደረገው የቅንዓት አገልግሎት ነው።
8. በምሥራቅ አውሮፓ እንዲሁም በአፍሪካ ይሖዋን የሚያወድሱ አዲሶች “እንደ ደመና እየበረሩ” የመጡት እንዴት ነው?
8 ባለፈው የአውሮፓ የበጋ ወራት የይሖዋ ሕዝቦች በቀድሞዎቹ ኮሚኒስታዊ አገሮች ባደረጓቸው ስብሰባዎች አስደናቂ የተሰብሳቢዎች ቁጥር አግኝተዋል። ይበልጥ አስገራሚ የሆነው ደግሞ አባሪው ሠንጠረዥ እንደሚያሳየው የተጠማቂዎች ቁጥር መብዛቱ ነው። በተመሳሳይም በአፍሪካ በምትገኘው በቶጎ ታኅሣስ 10, 1991 በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተጣለው እገዳ ተነስቶአል። እገዳው እንደተነሳ በቀጣዩ ወር አገር አቀፍ ትልቅ ስብሰባ ተደረገ። የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር 25, 467 የደረሰ ሲሆን ይህም በየወሩ በመስክ ከሚያገለግሉት 6,443 አስፋፊዎች ጋር ሲወዳደር በጣም ብዙ ነው። በተጨማሪም 556 ሰዎች ተጠምቀዋል። ይህም በዚያ ጊዜ ከነበሩት አስፋፊዎች 8.6 በመቶ የሚያክሉት የተጠመቁት በዚህ ጊዜ ነበር ማለት ነው። ኢሳይያስ 60:8 እንደሚገልጸው ይሖዋን የሚያወድሱ አዲሶች “ርግቦች ወደ ቤታቸው እንደሚበርሩ፣ እንደ ደመና” እየበረሩ ወደ ይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎች በመምጣት ላይ ናቸው።
9. በቅርቡ ነፃ በወጡ አገሮች ያሉ ምስክሮች ‘ይበሉና ይጠግቡ’ ዘንድ ምን ዝግጅቶች ተደርገዋል?
9 በምሥራቅ አውሮፓና በአፍሪካ የተነሳው የመንፈሳዊ ምግብ ረሀብም ጋብ እያለ ነው። በጀርመን፣ በኢጣሊያና በደቡብ አፍሪካ ያሉት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፋብሪካዎች በበርካታ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎችን በመንፈሳዊ ወደተራቡ አገሮች በብዛት እየጫኑ በማከታተል ሰደዋል። ቀደም ሲል ብዙዎቹ በመተሻሸት ብዛት ያረጁ መጽሔቶችን እየተቀባበሉ ያነቡ ነበር። አሁን ግን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ይደርሳቸዋል። “ብዙ መብል ትበላላችሁ፣ ትጠግቡማላችሁ፤ ከእናንተም ጋር ተአምራትን የሠራውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን [የይሖዋን አዓት] ስም ታመሰግናላችሁ” በማለት በተነገረው ትንቢት ፍጻሜ ተካፋይ በመሆናቸው እየተደሰቱ ነው። —ኢዩኤል 2:26
ለተጨማሪ ዕድገት ሁኔታዎችን ማመቻቸት
10. በመታሰቢያው በዓል ላይ ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ከመኖሩ አንፃር ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች በሙሉ ምን ጥሪ ቀርቦላቸዋል?
10 በዓለም ዙሪያ የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር ካለፈው ዓመት 781,013 ወይም 7.3 በመቶ ጭማሪ ያለው የተሰብሳቢዎች ቁጥር መገኘቱና 11,431,171 መድረሱ በእርግጥም የሚያስደንቅ ነው። አዳዲሶች የሆናችሁ ሁሉ እንኳን ደህና መጣችሁ! እነዚህ ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎች በሙሉ የይሖዋ ምስክሮች ጋር የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቢጀምሩ ምንኛ ግሩም ነበር! (ኢሳይያስ 48:17ን ተመልከት።) የአገልግሎት ዓመቱ ሪፖርት ከእነዚህ ሰዎች መካከል 4,278,068 የሚያክሉት በየወሩ ጥናት እየተመራላቸው መሆኑን ይገልጻል። ይህም 8.4 በመቶ የሆነ ጥሩ ጭማሪ ነው። ይሁን እንጂ ገና ከዚህ የበለጡ ብዙ ሌሎች ሰዎች የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ። የይሖዋ ምስክሮች ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን አዘውትረው ለማነጋገርና በቤታቸው ነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግና ብሎም በዘላለም ሕይወት ጎዳና ላይ እግራቸውን አደላድለው እንዲቆሙ ለመርዳት ደስተኞች ናቸው። (ዮሐንስ 3:16, 36) ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ ጥናት እንዲደረግላችሁ ለምን አትጠይቁም? በመንግሥት አዳራሹ ምን ጊዜም ሞቅ ያለ አቀባበል እንደምታገኙ አስታውሱ!—መዝሙር 122:1፤ ሮሜ 15:7
11, 12. (ሀ) በአንዳንድ አገሮች እያጋጠሙ ያሉት ችግሮች ምንድን ናቸው? (ለ) በሀብታምና በድሃ አገሮች መካከል “ከተለያየ አቅጣጫ የአስተዋጽኦ እኩልነት” እየታየ ያለው በምን መንገድ ነው?
11 ጥሩ የመንግሥት አዳራሾች ያሏቸው ጉባኤዎች በጣም ተባርከዋል። ታማኝ ምስክሮች በእገዳ ሥር ለብዙ ዓመታት በቆዩባቸውና በትናንሽ ቡድኖች በድብቅ ይሰበሰቡባቸው በነበሩት አገሮች ግን ሁኔታው የተለየ ነው። በእንዲህ ዓይነቶቹ ብዙ ቦታዎች ምስክሮቹ አሁን ነፃነት ቢያገኙም ያሏቸው የመንግሥት አዳራሾች ጥቂቶች ናቸው። ለምሳሌ ያህል 93 ጉባኤዎች ባሉበት አንድ በአፍሪካ በሚገኝ አገር ሦስት የመንግሥት አዳራሾች ብቻ ይገኛሉ። ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ ስብሰባዎች የሚደረጉት ክፍት በሆኑ ባዶ ቦታዎች ነው። 150 አባሎች ያሉት ጉባኤ እንደነዚህ ባሉት ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው የሚገኙ እስከ 450 የሚደርሱ ተሰብሳቢዎች ሊኖሩት ይችላሉ።
12 በምሥራቅ አውሮፓ ብዙውን ጊዜ ንብረት መግዛትም ሆነ ሕንፃ መሥራት አስቸጋሪ ቢሆንም አንዳንድ መሻሻል እየተደረገ ነው። በፖላንድ አንድ ጥሩ አዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ ኅዳር 28, 1992 ሊመረቅ ፕሮግራም ተይዞአል። ለዓለም አቀፍ የይሖዋ ምስክሮች ሥራ የተደረጉ የለጋስነት መዋጮዎች አዳራሾችንና ሌላ ዓይነት አገልግሎት የሚሰጡ ሕንጻዎችን ለመሥራት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው። በመሆኑም ከቁሳዊ “ትርፋቸው” የሚለግሱ ወንድሞች ችግረኞች በሆኑ አገሮች ያሉ ጉባኤዎችን መንፈሳዊ ፍላጎቶች ለሟሟላት ስለሚረዱ “ከተለያየ አቅጣጫ የአስተዋጽኦ እኩልነት” እየተደረገ ነው።—2 ቆሮንቶስ 8:13, 14
አንድ ቢልዮን ሰዓቶች!
13. በ1992 በመስበክና በማስተማር ሥራ ላይ ምን ይህል ሰዓቶች ውለዋል? በዚህ ቁጥር የተገለጸውስ የእነማን ጥረት ነው?
13 በአንድ ቢልዮን ሰዓት ምን ታደርጉ ነበር? ወደ ዘላለማዊ ሕይወት የሚደርሱ ሁሉ በውጤታማና ለይሖዋ በሚያረካ አገልግሎት ይህን ያህል ሰዓት፣ እንዲያውም ከዚህም የበለጠ ለማሳለፍ ይችላሉ። በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ይህን ያህል ሰዓት ሥራ ላይ ሊውል መቻሉ ምን ይህል ከፍተኛ እንደሆነ መገመት ትችላላችሁ። የይሖዋ ሕዝቦች በ1992 ይህን የሚያክል ሥራ ለማከናወን ችለው ነበር። የሁሉንም የመንግሥቱን አስፋፊዎች ተናጠል ሪፖርቶች ባንድ ላይ ስንደምር 1,024,910,434 ሰዓት ከሁሉ በሚበልጥ ከፍተኛ ሥራ ላይ ማለትም “በሕዝብ ፊትና ከቤት ወደ ቤት በማስተማር” ታላቁን ፈጣሪያችንን በማመስገን ሥራ ላይ ውሎአል። (ሥራ 20:20 አዓት) በአማካይ 4,290,057 ምስክሮች በየወሩ ሪፖርት ያደርጉ ነበር። ምስክሮቹ ከሁሉም ዓይነት የኑሮ ደረጃ የተውጣጡ ናቸው። አንዳንዶቹ ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን የማቅረብ ኃላፊነት ያለባቸው የቤተሰብ ራሶች ስለሆኑ፣ በዕድሜ የሸመገሉ ስለሆኑ፣ የጤንነት እክል ስላለባቸው ወይም ገና በትምህርት ላይ የሚገኙ ወጣት ልጆች ስለሆኑ በመንግሥቱ ሥራ ላይ ሊያውሉ የሚችሉት የጊዜ መጠን በጣም ውስን ነው። ሆኖም ከእያንዳንዳቸው የተጠራቀመው ሪፖርት ዋጋ ያለውና ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር የሚያንፀባርቅ ነው።—ከሉቃስ 21:2-4 ጋር አወዳድር።
14. ወጣቶች ‘ታላቁን ፈጣሪያቸውን በማስታወስ ላይ የሚገኙት’ እንዴት ነው?
14 ወጣቱ ትውልድ በይሖዋ አገልግሎት እያደገ የመጣ ሲሆን ከእነዚህ ወጣቶች መካከል ብዙዎቹ በመክብብ 12:1 ላይ ያሉትን “በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” የሚሉትን የሰሎሞን ቃላት በሥራ ላይ እያዋሏቸው ነው። በትምህርት ቤት የሚሰጣቸውን ትምህርት በትጋት እየተከታተሉ ለይሖዋ ባደሩ ወላጆቻቸው አማካኝነት የሚሰጣቸውን መንፈሳዊ ሥልጠና በመከታተል ላይ ናቸው። በአሥራዎቹ ዓመታት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች በቅርቡ በተደረጉ ስብሰባዎች ራሳቸውን ለጥምቀት ሲያቀርቡ ማየት የሚያስደስት ነገር ሆኗል። ብዙዎች አንድ ዓይነት ሙያ በመማር ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኃላ አቅኚዎች ለመሆን ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ማወቅም የሚያስደስት ነው። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ አንዳንድ ጊዜ ድንኳን እየሰፋ ራሱን ይረዳ እንደነበረ ሁሉ እነርሱም ራሳቸውን ለመርዳት ይችላሉ።—ሥራ 18:1-4
15, 16. አቅኚዎችና ሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ለመንግሥቱ ሥራ ዕድገት አስተዋጽኦ ያደረጉት እንዴት ነው? አንዳንዶቹስ ምን በረከት አግኝተዋል?
15 አቅኚዎች ሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችም ለመንግሥቱ ሥራ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው። የአቅኚዎች ቁጥር ባለፈው ዓመት 931,521 ወደሆነ ከፍተኛ ቁጥር አድጓል። እነዚህ አቅኚዎች የቀኑ ከቤት ወደ ቤት ስለሚሰብኩና ለሰዎች በየቤታቸው የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ስለሚመሩ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ሐሳባቸውን በመግለጽ ረገድ በጣም ውጤታማ ሊሆኑ ችለዋል። ከዚህም በላይ ብዙዎቹ የአምላክን ሥራ ለመሥራት የበለጠ ችሎታና ደስታ እንዲኮተኩቱ በሚረዳቸው የሁለት ሳምንት የአቅኚዎች ትምህርት ቤት ለመካፈል ብቃት አግኝተዋል።
16 እነዚህ ታማኝ አቅኚዎች እያንዳንዳቸው “የደከመውን በቃል እንዴት እንደምደግፍ አውቅ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] የተማሩትን ምላስ ተሰጥቶኛል” በሚሉት የኢሳይያስ 50:4 ቃላት ይስማማሉ። በአሁኑ ጊዜ በዙሪያቸው ያለው ብልሹ ዓለም የሰለቻቸውና በታማኝ አቅኚዎች በኩል በሚነገሩት ቃላት የሚጽናኑ በርካታ ግለሰቦች አሉ።—ከምሳሌ 15:23 እና ከሕዝቅኤል 9:4 ጋር አወዳድር።
ታላቅ የግንባታ ፕሮግራም
17. በቅርብ ዓመታት ከመንፈሳዊው ሕንፃ ሥራ በተጨማሪ ምን ቁሳዊ የሕንፃ ሥራ ታይቷል?
17 አለም አቀፍ የይሖዋ ምስክሮች መንፈሳዊ ብልጽግና የድርጅቱ ቁሳዊ ንብረቶች እንዲስፋፉ የሚጠይቅ ሆኖአል። የማተሚያ ሕንጻዎችን፣ የቢሮዎችና የቤቴል ቤቶችን፣ የመንግሥት አዳራሾችንና የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሾችን ማስፋፋትና መሥራት አስፈላጊ ሆኖአል። ስለዚህ የይሖዋ ምስክሮች ቃል በቃል ሕንፃ ሠሪዎች መሆን አስፈልጎአቸዋል። ይህንን የሚመስል የሕንፃ ሥራ በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ተከናውኖ ነበር። ሰሎሞን ለይሖዋ አምልኮ የሚሆነውን ቤተ መቅደስ የሠራው ይሖዋ ለአባቱ ለንጉሥ ዳዊት “በመንፈስ በገለጸው . . . የሕንፃ አሠራር” መሠረት ነበር። (1 ዜና 28:11, 12) ስለዚህ ሰሎሞን አድማጮቹን እጅግ ውድ በሆኑ የጥበብ ቃላት ከማነጽ በተጨማሪ በታላቅነቱ በሥጋዊው ዓለም ያልታየ ግዑዝ ሕንፃ ለመሥራት መሪ ሆኗል።—1 ነገሥት 6:1፤ 9:15, 17-19
18, 19. (ሀ) በይሖዋ ድርጅት በፍጥነት በመካሄድ ላይ ያሉት ምን የሕንፃ ሥራ ፕሮጀክቶች ናቸው? (ለ) በቁሳዊና በመንፈሳዊም ሕንፃ ሥራ የይሖዋ መንፈስ የታየው እንዴት ነው?
18 በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምስክሮች ሕንፃ የሚሠሩት በአምላክ መንፈስ በተገለጠ የሕንፃ አሠራር ጥበብ ባይሆንም የአምላክ መንፈስ አላቸው። ይህ መንፈስ በእሥራኤል ዘመን እንዳደረገው የዓለምን ሰዎች የሚያስደንቅ የሕንጻ ሥራ እንዲሠሩ አስችሎአቸዋል። (ዘካርያስ 4:6) ጊዜው አጭር ነው። የመንግሥት አዳራሾችና ሌሎችም ሕንፃዎች በአፋጣኝ ይፈለጋሉ። በአንዳንድ አገሮች በፍጥነት የሚሠሩ የመንግሥት አዳራሾች በጣም የተለመዱ ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ካናዳ እያንዳንዳቸው ከሁለት ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተሠርተው ያለቁ 306 አዳራሾች እንደሠራች ሪፖርት አድርጋለች። በዓለም ዙርያ የይሖዋ ሥራ በፍጥነት እያደገ ስለሚሄድ በአሁኑ ጊዜ በጠቅላላው 43 አዳዲስ የቅርንጫፍ ሕንፃዎች ላይ ተጨማሪ እየሠሩ ወይም ሊሠሩ እየታቀዱ ናቸው። ከዚህም በላይ በብሩክሊን ወደ 1,000 የሚጠጉ የቤቴል ፈቃደኛ ሠራተኞችን የሚይዝ ባለ 30 ፎቅ መኖሪያ ሕንፃ ተሠርቶ ሊያልቅ እየተቃረበ ነው። እንዲሁም በኒው ዮርክ ክፍለ ሐገር በፓተርሰን የሚሠራው እስከአሁን የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ከሠራቸው ሕንጻዎች ሁሉ የሚበልጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መስጫ ማዕከል ከታሰበው በላይ እየተፋጠነ ነው።
19 እነዚህ ፕሮጀክቶች የዓለምን ዕውቅ የሕንፃ ሥራ ኩባንያዎች በሚያስደንቅ ቅልጥፍናና ጥራት እየተካሄዱ ነው። ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ? ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ምስክሮች በሚያደርጉት ከፍተኛ መዋጮ ምክንያት ነው። የይሖዋ መንፈስ ቁሳዊ ድጋፍ እንዲሰጡ ብቻ ሳይሆን ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በሙሉ ልብ እንዲሰጡም ያንቀሳቅሳቸዋል። ሕንፃ በሚሠራባቸው ቦታዎች ሁሉ ጥሩ ሥልጠና ያገኙ ታማኝ ሠራተኞች በብዛት ይሰማራሉ። ምንም ዓይነት የሥራ ማቆም አድማም ሆነ በሥራ መለገም የለም። የይሖዋ መንፈስ በሙሴ ዘመን የመገናኛ ድንኳን የሠሩትንና በሰሎሞን ዘመንም ቤተ መቅደሱን የሠሩትን ሰዎች እንዳነቃቃቸው ሁሉ ዛሬም ለሕዝቦቹ ማነቃቂያ ይሰጣቸዋል። ከእነዚህ ሠራተኞች የሚፈለገው ባሕርይ የላቀ መንፈሳዊነት ነው።—ከዘጸአት 35:30-35፤ 36:1-3፤ 39:42, 43 እና ከ1 ነገሥት 6:11-14 ጋር አወዳድር።
20. (ሀ) የምሥራቹ የሚሰበከው እስከምን ደረጃ ድረስ ነው? (ለ) የይሖዋ ሕዝቦች ወደፊት የሚጠብቃቸው ምን የተባረከ ተስፋ ነው?
20 ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላም የሕንፃ ሥራ ፕሮግራሙን ቀጥሎበታል። (2 ዜና 8:1-6) የዘመኑ ምስክርነት የመስጠት ሥራና አብሮት ጎን ለጎን የሚሄደው የአዳራሾችና የሌሎችም ግልጋሎት መስጫ ሕንፃዎች ሥራ እስከምን ደረጃ እንደሚስፋፋ አናውቅም። ይሁን እንጂ ይህ የመንግሥት ምሥራች ይሖዋ እስከወሰነው መጠን ድረስ ከጫፍ እስከ ጫፍ ከተሰበከ በኋላ “ታላቁ መከራ” እንደሚመጣ እናውቃለን። (ማቴዎስ 24:14, 21) ይሖዋ ያዘጋጃቸው “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ከዚያ በኋላ በስስታም ሰዎች በማትበከል ምድር ላይ ለሰው ልጆች ይህ ነው የማይባል በረከት ያመጣሉ። እንግዲያስ ለታላቁ ፈጣሪያችን ማንኛውንም ምስጋና ሁሉ በመስጠት ‘ይሖዋ በሚፈጥረው ለዘላለም ሐሴት እናድርግ።’—ኢሳይያስ 65:17-19, 21, 25
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “መንግሥትህ ትምጣ” የተሰኘውን በኒው ዮርኩ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀ መጽሐፍ ገጽ 105-16, 186-9 ተመልከት
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ በታላቁ ፈጣሪያችን ለመደሰት የሚያስችሉ ምን ምክንያቶች አሉን?
◻ በ1992ቱ የአገልግሎት ዓመት ምን ጭማሪዎች ሪፖርት ተደርገዋል።?
◻ ቀደም ሲል የምስክርነቱ ሥራ በታገደባቸው አገሮች የተገኙ ምን ብዙ በረከቶች ሪፖርት ተደርገዋል?
◻ ወጣቶችና አቅኚዎች በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ለታየው ታላቅ ጭማሪ አስተዋጽኦ ያደረጉት እንዴት ነው?
◻ የይሖዋ ሕዝቦች በቁሳዊም ሆነ በመንፈሳዊ የሕንፃ ሥራዎች ሥራ የበዛላቸው እንዴት ነው?