የእርዳታ ዝግጅቶች ክርስቲያናዊ ፍቅርን ያንጸባርቃሉ
“ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ” በማለት ሐዋርያው ጴጥሮስ መሰል ክርስቲያኖችን አሳሰባቸው። (1 ጴጥሮስ 2:17 አዓት) እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የዘር፣ ማህበራዊና ብሔራዊ ድንበሮችን አልፎ በመሄድ ሕዝቦችን በእውነተኛ ወንድማማችነት የሚያቀራርብ ሆኖ ተገኝቷል። በቀድሞ ክርስቲያኖች መካከል ቁሳዊ ችግር ሲያጋጥም ሐዋርያት እርዳታው ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሚያከፋፍሉት መዋጮ እንዲሰጡ ብዙዎቹን ክርስቲያኖች ፍቅር ያነሳሳቸው ነበር። “ያላቸውንም ሁሉ አንድነት አደረጉ” በማለት መዝገቡ ይነግረናል። — ሥራ 2:41–45፤ 4:32
በ1991 መጨረሻ ላይ የይሖዋ ምስክሮች የአስተዳደር አካል በምዕራብ አውሮፓ ላሉት አያሌ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፎች በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት አንዳንድ ክፍሎች ያሉትን ጨምሮ በምሥራቅ አውሮፓ ላሉ ችግረኛ ወንድሞቻቸው ምግብና ልብስ እንዲያቀርቡ ጥሪ ባቀረበላቸው ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ተገልጿል። ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ቅርንጫፎች መካከል አንዳንዶቹ ያቀረቡትን ተከታታይ ሪፖርት ቀጥሎ እናቀርባለን።
ስዊድን
ታህሣስ 5, 1991 ችግሩን የሚገልጽ ደብዳቤ በስዊድን ለሚገኙ 348 ጉባኤዎች በሙሉ ተላከላቸው። ምላሽ የሰጡት ወዲያው ነበር። በጥቂት ቀናት ውስጥ የመጀመሪያው መለስተኛ ተሳቢ የጭነት መኪና 150 ኩንታል ዱቄት፣ የመብል ቅቤ፣ በቆርቆሮ የታሸገ የከብት ሥጋ፣ ዱቄት ወተትና የመሳሰሉትን ጭኖ ሩስያ ወደሚገኘው ሴይንት ፒተርስበርግ ጉዞ ጀመረ። በሥፍራው የሚገኙት የይሖዋ ምስክሮችም ጭነቱን አራገፉና 750 ጥቅልሎቹን በችግር ላይ ላሉት በፍጥነት አከፋፈሉ። ቆየት ብሎም ሁለት መለስተኛ ተሳቢ የጭነት መኪናዎች ምግብ ወደ ሩስያ አጓጉዘዋል። በጠቅላላው ከስዊድን ከ515 ኩንታል በላይ የሆነ የእርዳታ ቁሳቁስ ወደ ሩስያ ተልኮአል።
ልብስና ጫማ ለማዋጣት የታየው ፈቃደኛነት ከተጠበቀው በላይ ነበር። የተጠቀለሉ የልብስ ክምሮች በየመንግሥት አዳራሹ በፍጥነት ተሰበሰቡ። ብዙ ክርስቲያኖች እርዳታ የሰጡት የራሳቸውን ልብስ ነበር። ሌሎች ደግሞ አዳዲስ ልብሶችን ገዝተው ሰጡ። አንድ ወንድም አምስት የወንድ ሙሉ ልብሶችን ገዝቷል። ወንድም አምስቱን ሙሉ ልብሶች በአንድ ጊዜ በመግዛቱ የተደነቀው የሱቁ ባለቤት ዓላማውን ባወቀ ጊዜ እርሱም አምስት ተጨማሪ ሙሉ ልብሶች ረዳ። አንድ ሌላ ወንድም ሣጥን ሙሉ የእግር ሹራቦችን፣ ጓንቶችንና ያንገት ፎጣዎችን ገዝቷል። ዓላማውን ለባለሱቁ በገለጸለት ጊዜ በሁለት ሙሉ ልብሶች ዋጋ 30 አዳዲስ ሙሉ ልብሶችን ሰጠው። አንድ የስፖርት ልብሶች ባለሱቅ አዳዲስ 100 ጥንድ ጫማዎችንና ቦት ጫማዎችን በእርዳታ ሰጠ።
ይህ ሁሉ ዕቃ በየዓይነቱ ተለይቶ እንዲጠቀለልና እንዲጫን ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ተወሰደ። 40 መለስተኛ ተሳቢ የጭነት መኪናዎች የሚሞላ ልብስ በቅርንጫፍ ቢሮው ሠፊ ቦታ ላይ ተዘርግፎ ነበር! ወንድሞችና እህቶች ለወንዶች፣ ለሴቶችና ለልጆች የሚሆኑትን ልብሶች በየዓይነታቸው በመለየት በካርቶን ሣጥኖች ለማሸግ ለሳምንታት ሲሠሩ ቆይተዋል። ልብሶቹን ወደ ሩስያ፣ ዩክሬንና ኢስቶኒያ በሠላም ለማድረስ በአሥራ አምስት የተለያዩ መለስተኛ ተሳቢ የጭነት መኪናዎች ተጠቅመዋል።
ከማኅበሩ የጭነት መኪናዎች አንዱን ይዞ ወደ ቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ስምንት ጊዜ የተመላለሰ አንድ ወንድም እንደሚከተለው ብሏል:- “በተላክንበት ቦታ ያሉት ወንድሞች ያደረጉልን አቀባበል ራሱ በቂ የድካማችን ካሣ ነበር። ልብ በሚነካ ሁኔታ እንቅ አድርገው በማቀፍ ይስሙን ነበር፤ ያላቸው በጣም አነስተኛ ቢሆንም ክርስቲያናዊ ልግስናን በማሳየት በኩል እነርሱ ለእኛ ጥሩ ትምህርት ሰጥተውናል።”
ፊንላንድ
ፊንላንድ ከባድ የኢኮኖሚ ድቀት፣ በየቦታው የሥራ አጥነት የበዛባትና የኢኮኖሚ ችግሮች ያሉባት ብትሆንም በግምት 18,000 የሚሆኑ የፊንላንድ ወንድሞች በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ያሉትን ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ያሳዩት ፈቃደኛነት በጣም ከፍተኛ ነበር። ከ580 ኩንታል የሚበልጥ ምግብ በ4,850 ካርቶን አሽገው ወደ ሴይንት ፒተርስበርግ፣ ኢስቶኒያ፣ ላቲቪያ፣ ሊቱዋንያና ካሊኒንግራድ ልከዋል። በጭነት መኪናዎቹ ላይ የቀረውን ክፍት ቦታ 420 ኩብ ጫማ በሆነ ልብስ ሞልተው ልከውታል። 25 ያህል ያገለገሉ መኪናዎችና የጭነት መኪናዎችም ለመንግሥቱ ሥራ እንዲያገለግሉ በእርዳታ ተሰጥተዋል።
አንዳንዶቹ የምግብ ካርቶኖች በሴይንት ፒተርስበርግ አካባቢ ለሚገኘው 14 አስፋፊዎች ላሉት የስላንቲ ጉባኤ ደርሶ ነበር። ከፍተኛ አድናቆታቸውን በደብዳቤ ገለጹ። “በጉባኤያችን ውስጥ በዕድሜ የገፉ 10 እህቶች አሉ። በጣም በመታመማችን ተሰልፈን ምግብ ለመግዛት አንችልም። ይሁን እንጂ ሰማያዊው አባታችን በእነዚህ አስቸጋሪ ቀኖች ልባችንን በመብልና በደስታ ሞላው እንጂ ተስፋ እንድንቆርጥ ሰበብ አልሰጠንም። 43 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንመራለን።” በሴይንት ፒተርስበርግ አንዲት እህት የእርዳታ ጥቅልሉን ስታገኝ ልቧ በጣም በመነካቱ ጥቅልሉን ከመክፈቷ በፊት ለሁለት ሰዓት አለቀሰች።
ዴንማርክ
በቦልቲክ ባሕር መግቢያ ላይ በሚገኘው በዚህ ትንሽ አገር ያሉ 16,000 የሚሆኑ የይሖዋ ምስክሮች አንድነት ተሰባሰቡና በ4,200 ሣጥኖች ውስጥ 640 ኩንታል ምግብ፣ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው 4,600 ሣጥን ልብሶችና 2,269 አዳዲስ ጥንድ ጫማዎች ወደ ዩክሬን ላኩ። በጀርመን ያለ አንድ ወንድም የጀርመኑ ቅርንጫፍ እንዲጠቀምባቸው ፈቅዶለት የነበሩትን አምስት የጭነት መኪናዎች ለዩክሬን ወንድሞች በእርዳታ ሰጠ። ከሾፌሮቹ አንዱ ዩክሬን ደርሶ ሲመለስ “ከወሰድነው የሚበልጥ ነገር ይዘን መመለሳችንን ተገንዝበናል። የዩክሬን ወንድሞቻችን ያሳዩን ፍቅርና የራስን ጥቅም የመሰዋት መንፈስ እምነታችንን በጣም አጠንክሮታል” ብሎአል።
ሾፌሮቹ በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት መንገድ ሲጓዙ ከዘራፊዎች መጠንቀቅ ነበረባቸው። የዴንማርክ የጭነት መኪናዎች ከማለፋቸው ከጥቂት ቀናት አስቀድሞ በዚህ መንገድ ላይ ዝርፊያ አጋጥሞ ነበር። ሄሊኮፕተሮችና አውቶማቲክ መሣሪያ የያዙ ዘራፊዎች በሌላ የእርዳታ ድርጅት የተላኩ አምስት የተለያዩ ኮንቮዮች አስቁመው ነበር። ሾፌሮቹን በመንገድ ላይ ጥለው አምስቱንም የጭነት መኪናዎች በሙሉ ወሰዱ። እንዲህ ዓይነቱ አደጋ ቢኖርም ከዴንማርክ የተላከው የእርዳታ አቅርቦት በሙሉ ለወንድሞች በደህና ደርሶላቸዋል። በምላሹም አንዱ ሹፌር ወደ አገሩ ሲመለስ በብዙ ችግር በእንግሊዝኛ የተጻፈ እንዲህ የሚል ማስታወሻ ሰጥተውታል:- “የተወደዳችሁ የዴንማርክ ወንድሞችና እህቶች፣ እርዳታችሁን ተቀብለናል። ይሖዋ ዋጋችሁን ይከፍላችኋል።”
ኔዘርላንድስ
የኔዘርላንድስ ቅርንጫፍ በ2,600 ጥቅልሎች በማሸግ 520 ኩንታል ምግብ ልኮአል። ምግቡ በሁለት የተለያዩ ኮንቮዮች ወደ ዩክሬን ተላከ። በሁለቱም ጊዜ ስድስቱ ሾፌሮች እየነዱ የወሰዷቸውን የጭነት መኪኖች ጥለው መጥተዋል፤ ምክንያቱም የጀርመን ወንድሞች በምሥራቁ ዓለም ለሥራው ማካሄጃ እንዲውሉ ለግሶአቸው ነበር። የዩክሬን ወንድሞች አብዛኛውን ምግብ ከፍተኛ ችግር ወዳለባቸው ሞስኮ፣ ሳይቤሪያና ሌሎችም ቦታዎች ልከውታል። ከዚህም በላይ 736 ሜትር ኩብ ልብስና ጫማ በዳች ወንድሞች በእርዳታ ተሰጥቷል። እርዳታው በግል መኪና ሸኚነት በተላኩ 11 የጭነት መኪናዎች ኮንቮይ በዩክሬን ወደሚገኘው ለቬፍ መጥቷል።
የመኪናዎቹ ኮንቮይ ጀርመንና ፖላንድን አቋርጦ ብዙ ከተጓዘ በኋላ የዩክሬንን ጉምሩክ ያላንዳች ችግር አልፎ ከሌሊቱ በ9 ሰዓት በለቬፍ ዳርቻ ላይ ደረሰ። ሾፌሮቹ እንደሚከተለው ሪፖርት ያደርጋሉ:- “የጭነት መኪናዎቹን ለማራገፍ ባጭር ጊዜ ውስጥ 140 ወንድሞችን የያዘ የሰው ኃይል በሥፍራው ተገኘ። እነዚህ ትሑት ወንድሞች ሥራውን ከመጀመራቸው በፊት የህብረት ጸሎት በማቅረብ በይሖዋ ላይ ያላቸውን ትምክህት አሳዩ። ሥራው ሲያልቅ ለይሖዋ ምስጋና ለማቅረብ እንደገና ለጸሎት ተሰበሰቡ። ያለቻቸውን ትንሽ ነገር በማትረፍረፍ የሰጡን የአካባቢው ወንድሞች ባደረጉልን መስተንግዶ ከተደሰትን በኋላ ወደ ዋናው መንገድ ሸኙንና ትተውን ከመመለሳቸው በፊት በመንገዱ ዳር ጸሎት አቀረቡ።
“ወደ አገራችን ስንመለስ በረዥሙ ጉዞ ላይ የምናስበው ብዙ ትዝታ ነበረን:- የጀርመንና የፖላንድ ወንድሞችን የእንግዳ አቀባበልና የለቬፍ ወንድሞችን የእንግዳ አቀባበል፣ ጠንካራ እምነታቸውና የጸሎተኛነት መንፈሳቸው፣ ራሳቸው ችግረኞች ሆነው ሳሉ ማረፊያና ምግብ በማቅረብ ያደረጉልን መስተንግዶ፣ እርስ በርሳቸው ያላቸው ህብረትና መቀራረብ እንዲሁም አመስጋኝነታቸው ሁሉ ትዝታችን ነበረ። ይህን ያህል በለጋስነት ስለሰጡት የአገራችን ወንድሞችና እህቶችም አሰብን።”
ስዊዘርላንድ
የስዊዘርላንድ ቅርንጫፍ ሪፖርቱን የሚከፍተው በያቆብ 2:15, 16 ላይ “ወንድም ወይም እህት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፣ ከእናንተ አንዱም:- በደህና ሂዱ፣ እሳት ሙቁ፣ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል?” የሚለውን በመጥቀስ ነው። ከዚያም ሪፖርቱ “የይሖዋ ምስክሮች የአስተዳደር አካል ለችግረኛ ወንድሞቻችን ቁሳዊ እርዳታ እንድንሰጥ ጥሪ ሲያቀርብልን ይህ ጥቅስ ትዝ አለን” በማለት ይቀጥላል።
“ወዲያውም እያንዳንዱ መጣደፍ ጀመረ፤ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ በ600 ጥቅልሎች የተያዘ 120 ኩንታል ምግብ በዩክሬን ላለው የመንግሥት ሥራ ከጀርመን በእርዳታ ከተሰጡት ሦስት የጭነት መኪናዎች ጋር ወደ ዩክሬን ተላከ። የተላከው ሁሉ በሠላም መድረሱን የሚገልጽ ዜና ሲመጣልን እዚህ ላሉት ወንድሞቻችን ታላቅ ደስታ ሆኖላቸዋል። እስከዚያው ድረስ ጉባኤዎቹ ልብስ አሰባሰቡና ብዙም ሳይቆይ ቅርንጫፋችን በካርቶኖች፣ በልብስ ሻንጣዎችና በከረጢቶች ተጥለቀለቀ! ከእነዚህ መካከል የልጆችን ልብስ በያዙት ውስጥ በሩቁ ሰሜን ለሚገኙ ለማያውቁአቸው ጓደኞች ከስዊዘርላንድ ልጆች የተላኩ አንዳንድ አሻንጉሊቶች ነበሩባቸው። ብዙ ቸኮላቶችም በልብሶቹ እጥፋት መካከል ተደርገው ነበር።”
ይህ ሁሉ በምን ሊላክ ነበር? ሪፖርቱ እንዲህ ይላል:- “የፈረንሳዩ ቅርንጫፍ ሁለት መለስተኛ ተሳቢ ያለው የጭነት መኪናዎችንና አራት ሾፌሮችን በፈለግንበት ጊዜ በማቅረብ ረድቶናል። 720ውን ኩንታል ጭነት ወደ ዩክሬን ለማጓጓዝ የቅርንጫፋችን ንብረት የሆነ አንድ የጭነት መኪናና ንብረትነታቸው የአካባቢው ወንድሞች የሆኑ አራት ተጨማሪ የጭነት መኪናዎች አስፈልገውናል። 150 ሜትር ርዝመት ያለው ኮንቮይ 100 የሚያህሉ የለቬፍ ወንድሞች ጭነቱን ለማራገፍ ወደሚጠባበቁበት የለቬፍ ዴፖ በሠላም ደረሰ። የወንድሞች አድናቆት በፊታቸው ላይ ይንፀባረቅ ስለነበረ የቋንቋ ልዩነት ምንም ችግር እንዳልፈጠረ ሾፌሮቹ ገልጸዋል።
ኦስትሪያ
የኦስትሪያ ወንድሞች በዩክሬን ወዳሉት ለቬፍና ኡዥጎሮድ 485 ኩንታል ምግብ፣ 5,114 ካርቶን ልብስና 6,700 ጥንድ ጫማዎችን ልከዋል። በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ላሉት የቤልግሬድ፣ የሞስታር፣ የኦሲየክ፣ የሳራየቮና የዛግሬብ ከተሞችም 70 ኩንታል ምግብ፣ 1,418 ሣጥን ልብስና 465 ጥንድ ጫማ ልከዋል። የቅርንጫፉ ሪፖርት “34,000 ኪሎ ሜትር የሚጓዙ 12 መለስተኛ ተሳቢ የጭነት መኪናዎች ጭነናል። ይህ ሥራ በአብዛኛው የተከናወነው የጭነት ሥራ በሚያካሂድ አንድ ወንድምና በወንድ ልጁ አማካኝነት ነበር” ይላል።
የልብስ እርዳታ መላክን በተመለከተ ሪፖርቱ ቀጥሎ እንዲህ ይላል:- “ማዕከላዊ ግምጃ ቤት አድርገን የተጠቀምንበት የትልቅ ስብስባ አዳራሹን ነበር። ቦታ እስኪታጣ ድረስ ልብስ በጭነት መኪናዎች እየተጫነ ይጎርፍ ነበር። በሙሴ ዘመን እንደተደረገው ሁሉ አሁንም ሰዎቹ ሌላ እንዳያመጡ መታገድ አስፈልጓቸዋል። (ዘጸአት 36:6) የይሖዋ ምስክሮች ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎችም እንኳን ‘ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንደሚደርስ እናውቃለን’ በማለት የገንዘብ እርዳታ ሰጥተዋል። ከአንዳንድ ዓለማዊ ድርጅቶችም ብዙ ባዶ ካርቶኖችን ያላንዳች ክፍያ አግኝተናል።” ሁሉንም ነገር በየአይነቱ እየለዩ ያሸጉት ወንድሞችና እህቶች ከ9 ዓመት እስከ 80 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ነበሩ። እንዲያውም ለያንዳንዱ የወንድ ሙሉ ልብስ የሚስማማውን ክራቫት ለማስማማትም እንኳን ሳይቀር ጥረት አድርገዋል።
ሪፖርቱ እንዲህ ይላል:- “በኦስትሪያና በድንበር ላይ ያሉት ባለሥልጣኖች የተለያዩ የእርዳታ ጓዞቻችን እንዲያልፉልንና ዕቃዎችን የማድረሱ ሥራ ያለችግር እንዲከናወን የሚረዱ አስፈላጊ ወረቀቶችን በመስጠትም በጣም ተባብረውናል።”
ኢጣሊያ
ከሮም 1880 ኩንታል ያህል ብዛት ያለው ምግብ በሁለት ትላልቅ የጭነት መኪናዎች ኮንቮይ በኦስትሪያ፣ በቼኮዝሎቫኪያና በፖላንድ አቋርጦ ወደ ቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ተልኳል። እያንዳንዱ የኮንቮይ ቡድን ስድስት ሾፌሮችን፣ አንድ መካኒክ፣ አንድ አውቶ ኤሌክትሪሺያን፣ አንድ አስተርጓሚ፣ አንድ የጉምሩክ ጉዳዮች አስፈጻሚ፣ አንድ ወጥ ቤት ሠራተኛ፣ አንድ ዶክተር፣ በጂፕ መኪና የሚጓዝ አንድ የኮንቮይ መሪና በጎዞ ላይ ሳሉ በድንኳን ማደር በሚያስፈልጋቸው ጊዜ የሚጠቀሙባቸውን የድንኳን ዕቃዎች የያዘ አንድ ወንድም የሚጨምር ነበር።
ምግቡና ዕቃው የተገዛው ከሰባት አቅራቢ ድርጅቶች ነበር። ቅርንጫፉ እንደሚከተለው በማለት ሪፖርት አድርጓል:- “አቅራቢ ድርጅቶቹ ምግቡና ዕቃው የሚሰባሰብበትን ዓላማ ሲሰሙ አንዳንዶቹ እርዳታ በመስጠቱ ሥራ እነርሱም ለመሳተፍ ፈለጉ። ዕቃና ምግብ የሚያቀርቡልን ዓለማዊ ድርጅቶች በብዙ መቶ ኪሎ ግራም የሚቆጠር ፓስታና ሩዝ፣ እንዲሁም የማሸጊያ ሣጥኖች በእርዳታ ሰጥተዋል። አሁንም ሌሎች የጭነት መኪናዎቹ በበረዶማ መንገድ ላይ ሲሽከረከሩ እንዳይንሸራተቱ የሚያስችሉ ጎማዎችን በእርዳታ ሰጥተዋል አለዚያም ገንዘብ ለግሰዋል።
“በኢጣሊያ ያሉ ወንድሞች እርዳታ ለመስጠት ያስቻላቸውን ይህን አጋጣሚ አድንቀዋል። ልጆችም ሳይቀር ለማዋጣት ፍላጎት ነበራቸው። አንድ የአምስት ዓመት ልጅ ለሩስያ ወንድሞች ‘የቶኖ ዓሣ የታሸገበት ቁመቱ ሰማይ የሚደርስ ጣሳ ይገዛል’ ብሎ በማሰብ አነስተኛ መዋጮ ልኳል። አንዲት ትንሽ ልጃገረድ በትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት በማምጣቷ ለወላጆቿ ስጦታ እንድትገዛበት አያቶቿ የገንዘብ ሽልማት ሰጥተዋት ነበር። እርሷም ‘ብዙ ወንድሞቼ እኔ እንደምበላው ዓይነት ጥሩ ምግብ እንደሌላቸው ስገነዘብ ለወላጆቼ ልገዛላቸው የምችለው ከሁሉ የበለጠ ስጦታ እነዚያን ወንድሞች መርዳት እንደሆነ አሰብኩ’ ብላ ጻፈች። በመዋጮ ሣጥኑ ውስጥ በዛ ያለ ገንዘብ አስቀመጠች። ‘ተጨማሪ ገንዘብ ለመላክ እንድችል አሁንም ጥሩ ውጤት በማምጣት እንደምቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ’ ብላለች።” የቅርንጫፉ ሪፖርት ሲያጠቃልል በዩክሬን ካሉ ወንድሞች የደረሱን የጋለ አድናቆት መግለጫ ደብዳቤዎች፣ የኢጣሊያ ወንድሞች የላኩልን የአድናቆት ቃላትና ምግቡና ዕቃው ሲዘጋጅና ቦታው ላይ ሲደርስ ያጋጠማቸው ሁኔታ መንፈስን የሚቀሰቅስ፣ የሚያበረታታና አንድነትን የሚያጠነክር እንደነበር ገልጿል።
በሺዎች ለሚቆጠሩ ከየቦታው ለመጡ ተሰብሳቢዎች ምግብ ማቅረብ
በቀድሞዋ የሶቭዬት ኅብረት ውስጥ የመጀመሪያው የይሖዋ ምስክሮች ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ሰኔ 28–30 1992 በሩስያ በሴይንት ፒተርስበርግ ውስጥ በኪሮቭ ስቴዲየም ተደርጎ ነበር። “ብርሃን አብሪዎች” የሚል አጠቃላይ መልዕክት ባለው በዚህ ምዕራፍ ከፋች ስብሰባ ላይ ከ28 የተለያዩ አገሮች የመጡ 46,000 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። ስብሰባው “ለመላው የወንደማማቾች ማህበር” ክርስቲያናዊ ፍቅር ለማሳየት ሌላ አጋጣሚ ሰጥቷል። — 1 ጴጥሮስ 2:17
ከዴንማርክ፣ ከፊንላንድ፣ ከስዊድንና ከሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የመጣ በብዙ ኩንታል የሚቆጠር ምግብ ከቀድሞዋ ሶቪየት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ሩስያ መጥተው በስብሰባው ላይ ለተገኙ በሺዎች ለሚቆጠሩ ተሰብሳቢዎች ስብሰባው እስኪያበቃ ድረስ እንዲበሉት በነፃ ታድሏል። የስብሰባው የመጨረሻ ክፍል ካበቃ በኋላ ወደየቤታቸው ሲሄዱ በጉዞ ላይ ስንቅ የሚሆናቸው የምግብ ጥቅልል ይዘው እንዲሄዱ ተሰጥቷቸዋል።
ስጦታው ወደ አንድ አቅጣጫ ማለትም ወደ ምሥራቅ ብቻ የተላከ አለመሆኑን እዚህ ላይ የተጠቀሱት ሪፖርቶች ይገልጻሉ። የስጦታ ልውውጥ ተደርጓል። ምግብና ልብስ ወደ ምሥራቅ ይላክ እንጂ ወደ ምዕራብ ደግሞ ልባዊ የሆነ የፍቅር መግለጫና በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምስክሮች ለአሥርተ ዓመታት ባሳለፉት ችግርና መከራ ያሳዩትን ጽናትና ታማኝነት የሚያንጸባርቁ እምነት የሚገነቡ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ተሞክሮዎች ተልከዋል። ስለዚህ ሁለቱም ወገኖች “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ አለው” በማለት ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት እውነተኝነት አይተዋል። — ሥራ 20:35 አዓት
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕል]
1. ከፊንላንድ:- ሴይንት ፒተርስበርግ፣ ሩስያ፤ ታሊን እና ታርቱ፣ ኢስቶኒያ፤ ሪጋ፣ ላቲቪያ፤ ቪልኒየስ እና ካውኑስ፣ ሊቱዋኒያ፤ ካሊኒንግራድ፣ ሩስያ፤ ፔትሮዛቮዲስክ፣ ካሬሊያ
2. ከኔዘርላንድስ:- ለቬፍ፣ ዩክሬን
3. ከስዊድን:- ሴይንት ፒተርስበርግ፣ ሩስያ፤ ለቬፍ፣ ዩክሬን፤ ኒየቪነሚስክ፣ ሩስያ
ሩስያ፤ ለቬፍ፣ ዩክሬን
5. ከኦስትሪያ:- ለቬፍ፣ ዩክሬን፤ ቤልግሬድ፣ ሞስታር፣ ኦሲየክ፣ ሳራየቮ፣ ዛግሬብ (በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ)
6. ከስዊዘርላንድ:- ለቬፍ፣ ዩክሬን
7. ከኢጣሊያ:- ለቬፍ፣ ዩክሬን
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልብሶችን የያዙ ካርቶኖች በስዊድን ቅርንጫፍ
የእርዳታ ጭነት ዝግጅቶች
በአንድ ጥቅልል የታሸጉ የምግብ ዕቃዎች
ሥጋና ማር ከዴንማርክ
11 የጭነት መኪናዎችና አንድ የቤት መኪና የያዘ ኮንቮይ
የምግብ ጥቅልሎችና የልብስ ሻንጣዎች በኦስትሪያ ቅርንጫፍ
በለቬፍ ዩክሬን የጭነት መኪና ሲራገፍ