አእምሮአችሁ የተለወጠ ልባችሁም ብርሃን የበራለት ይሁን
“እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንዲመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ፣ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ።” — ኤፌሶን 4:17
1. አእምሮአችንና ልባችን ምን ተግባሮችን ያከናውኑልናል?
ለሰው ልጅ ከተሰጡት አስደናቂ ሥጦታዎች ሁለቱ ልብና አእምሮ ናቸው። የልብንና የአእምሮን አሰራር ዘርዝሮ ለመጨረስ የማይቻል ከመሆኑም በላይ የእያንዳንዱ ሰው አእምሮና ልብ የተለያየ ነው። ጠባያችን፣ ምግባራችን፣ አነጋገራችን፣ ስሜታችንንና ለተለያዩ ነገሮች የምንሰጠው ዋጋ በልባችንና በአእምሮአችን አሠራር በጥልቅ ይነካል።
2, 3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ “ልብ” እና “አእምሮ” የተባሉትን ቃላት እንዴት ይጠቀምባቸዋል? (ለ) ስለ ልባችንና ስለ አእምሮአችን አጥብቀን ማሰብ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ልብ” አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው ግፊትን፣ ስሜትን፣ ውስጣዊ ፍላጎትን ሲሆን “አእምሮ” ደግሞ የሚያመለክተው የማስተዋልና የማሰብ ችሎታን ነው። ይሁን እንጂ አእምሮና ልብ ተነጣጥለው ለየብቻቸው የሚሠሩ አይደሉም። ለምሳሌ ያህል ሙሴ እሥራኤላውያንን “ይሖዋ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ለልብህ ማስታወስ [የግርጌ ማስታወሻ፣ ለአእምሮህ ማሳሰብ] ይኖርብሃል” በማለት አጥብቆ መክሯል። (ዘዳግም 4:39 አዓት) ኢየሱስ ያሴሩበት የነበሩትን ጻፎች “ስለምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ?” ብሎአቸዋል። — ማቴዎስ 9:4፤ ማርቆስ 2:6, 7
3 ይህም አእምሮና ልብ በጣም የተዛመዱ ነገሮች መሆናቸውን ያሳያል። እርስበርስ መልዕክት ይለዋወጣሉ። ተባብረውና ተቀናጅተው አንድን ውሳኔ የሚያጠናክሩበት ጊዜ ቢኖርም አብዛኛውን ጊዜ አንዳቸው በሌላው ላይ የበላይ ለመሆን እርስበርስ ይታገላሉ። (ማቴዎስ 22:37፤ ከሮሜ 7:23 ጋር አወዳድር) በዚህ ምክንያት የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ከፈለግን ስለ አእምሮአችንና ስለ ልባችን ሁኔታ እርግጠኞች በመሆን ብቻ ሳንወሰን ሁለቱም በስምምነትና በቅንጅት በመሥራት ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲያመሩ ልናሰለጥናቸው ይገባል። በአእምሮአችን መለወጥና ልባችንም ብርሃን የበራለት መሆን ይኖርብናል። — መዝሙር 119:34፤ ምሳሌ 3:1
‘የአሕዛብ አካሄድ’
4. ሰይጣን በሰዎች ልብና አእምሮ ላይ ተጽእኖ ያሳደረው እንዴት ነው? ይህስ ምን ዓይነት ውጤት አስከትሎአል?
4 ሰይጣን በማታለልና ሰዎችን በቁጥጥር ሥር በማድረግ ረገድ ተራቅቆአል። ሰዎችን በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ በአእምሮአቸውና በልባቸው ላይ ማነጣጠር እንደሚኖርበት ያውቃል። የሰው ልጆች ታሪክ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሰዎችን አእምሮና ልብ ለመቆጣጠር የተለያዩ ዘዴዎችን ሲጠቀም ቆይቶአል። በዚህ ምክንያት “ዓለም በሙሉ በክፉው” ሊያዝ ችሎአል። (1 ዮሐንስ 5:19) እንዲያውም ሰይጣን የዓለምን ሰዎች ልብና አእምሮ በመቆጣጠር ረገድ በጣም የተሳካ ውጤት በማግኘቱ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሰዎች “መጥፎና ጠማማ ትውልድ” ሲል ጠርቶአቸዋል። (ፊልጵስዩስ 2:15) ሐዋርያው ጳውሎስ የዚህን ጠማማና መጥፎ ትውልድ የልብና የአእምሮ ሁኔታ ሕያው አድርጎ ይገልጻል። እነዚህ የጳውሎስ ቃላት በዚህ ዘመን ለምንኖረው ሁሉ በማስጠንቀቂያነት ያገለግሉናል። ለምሳሌ ያህል ኤፌሶን 4:17–19ን አንብብና በሮሜ 1:21–24 ላይ ከሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ጋር አወዳድር።
5. ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ጠንካራ ምክር የጻፈው ለምን ነበር?
5 ኤፌሶን በሥነ ምግባር ርኩሰትዋና በጣዖት አምልኮትዋ ምን ያህል ያዘቀጠች ከተማ እንደነበረች ስናስታውስ ጳውሎስ እነዚህን ጠንካራ ቃላት ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የጻፈበትን ምክንያት ለመረዳት እንችላለን። ግሪካውያን ከፍተኛ ዝና ያተረፉ ፈላስፎች የነበሩአቸው ቢሆንም የግሪካውያን መማር ሕዝቡ ክፋት እንዲፈጽም የበለጠ ነጻነት የሰጠው ይመስላል። ባሕላቸውም ቢሆን በክፋታቸው እንዲራቀቁ አድርጎአቸዋል። ጳውሎስ እንዲህ ባለ ሁኔታ ተከበው ይኖሩ የነበሩት የክርስቲያን ባልንጀሮቹ ሁኔታ በጣም አሳስቦት ነበር። ብዙዎቹ ከአሕዛብ የመጡና ‘እንደዚህ ዓለም ሥርዓት ሲመላለሱ የቆዩ እንደነበሩ’ ያውቃል። አሁን ግን እውነትን ተቀብለዋል። አእምሮአቸው ተለውጦአል፣ ልባቸውም ብርሃን በርቶለታል። ከሁሉም በላይ ጳውሎስ ‘ለተጠሩበት ጥሪ እንደሚገባ እንዲመላለሱ’ ፈልጎአል። — ኤፌሶን 2:2፤ 4:1
6. የጳውሎስን ቃላት ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገባን ለምንድን ነው?
6 ዛሬም ቢሆን ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም። የምንኖረው ሥነ ምግባር ባዘቀጠበት፣ የሐሰት ሃይማኖት ልማዶች በተስፋፉበትና ሰዎች ለነገሮች የሚሰጡት ዋጋ በተጣመመበት ዓለም ውስጥ ነው። በመካከላችን ከሚገኙት ብዙዎቹ ከዚህ ዓለም ሥርዓት ጋር ተስማምተው ይኖሩ የነበሩ ናቸው። ሌሎቻችን ደግሞ በየቀኑ ከዓለም ሰዎች ጋር አብረን ለመዋል እንገደዳለን። አንዳንዶቻችን የምንኖረው ዓለማዊ መንፈስ ባየለበት ቤት ውስጥ ነው። ስለዚህ የጳውሎስን ቃላት ትርጉም መረዳታችንና በምክሩ መጠቀማችን በጣም አስፈላጊ ነው።
ከንቱና የጨለመ አእምሮ
7. ጳውሎስ “የአእምሮአቸው ከንቱነት” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
7 ጳውሎስ ክርስቲያኖች ‘እንደ አሕዛብ እንዳይመላለሱ’ የሰጠውን ምክር ሲያጠናክር በመጀመሪያ የጠቀሰው ስለ “አእምሮአቸው ከንቱነት” ነው። (ኤፌሶን 4:17) ይህ ምን ማለት ነው? “ከንቱነት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ዘ አንከር ባይብል እንደሚለው “ባዶነትን፣ የማይረባ መሆንን፣ ከንቱነትን፣ ሞኝነትን፣ ዓላማ ቢስነትንና ፍሬቢስነትን ያመለክታል።” ስለዚህ ጳውሎስ የግሪካውያንና የሮማውያን ዓለም ዝናና ክብር እንደ ታላቅ ነገር ሊቆጠር የሚችል ቢሆንም ከእነርሱ ዓለም የሚገኘውን ክብርና ዝና ለማግኘት መጣጣር ባዶነት፣ ሞኝነትና ዓላማ ቢስነት እንድሆነ ማመልከቱ ነበር። ለክብርና ለዝና የሮጡ ሁሉ ያመኑት ነገር ሲከዳቸውና ሲበሳጩ እንጂ የተሻለ ነገር ሲያገኙ አይታዩም። ዛሬ በምንኖርበት ዓለምም ላይ ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት ይሠራል።
8. ዓለማዊ ጥረቶች ከንቱ የሆኑት በምን መንገዶች ነው?
8 ይህ ዓለም ‘ሕይወት ከየት መጣ? ዓላማውስ ምንድን ነው?’ ለሚሉትና ለመሳሰሉት ጥልቅ ጥያቄዎች መልስ ሊሰጡ ይችላሉ ብሎ የሚታመንባቸው ሊቃውንትና ጠቢባን አሉት። ይሁን እንጂ ምን ዓይነት ጥልቅ ዕውቀትና መመሪያ ሊሰጡ ይችላሉ? እነርሱ ሊሰጡ የሚችሉት ከጥንቶቹ አጉል እምነቶችና የአምልኮ ሥነ ሥርዓቶች የተሻለ ብርሃን የማይሰጡትን እርስበርሳቸው የሚቃረኑትን የአምላክ የለሽነት፣ የተጠራጣሪነት፣ የዝግመተ ለውጥና ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም የሚለውን ንድፈ ሐሳብ ነው። በተጨማሪም ዓለም የሚሮጥላቸው ብዙ ነገሮች መጠነኛ እርካታና ደስታ የሚያስገኙ ይመስላል። ሰዎች በሳይንስ፣ በሥነ ጥበብ፣ በሙዚቃ፣ በስፖርት፣ በፖለቲካ፣ ወዘተ ጥሩ እንደተራመዱ ይናገራሉ። በሚያገኙት አላፊ ዝና ይፈነጥዛሉ። ይሁን እንጂ የታሪክ ማኅደሮችና ዛሬ ያሉት ዝነኛ ሰዎች የሚመዘገቡባቸው መጻሕፍት በተረሱ የጀግኖች ታሪክ የተሞሉ ናቸው። ይህ ሁሉ ባዶነት፣ የማይረባ ነገር፣ ከንቱነት፣ ሞኝነት፣ ዓላማ ቢስነትና ተስፋ ቢስነት እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
9. ብዙዎች ከንቱ የሆኑ ምን ነገሮችን ወደማሳደድ ዘወር ብለዋል?
9 ብዙዎች እነዚህን ነገሮች መከታተል ከንቱ መሆኑን ይገነዘቡና ቁሳዊ ሀብት ማለትም ገንዘብንና ገንዘብ ሊገዛ የሚችላቸውን ነገሮች ማካበትን እንደዋነኛ የሕይወታቸው ግብ አድርገው ማሳደድ ሊጀምሩ ይችላሉ። ደስታ የሚገኘው ከሀብት ከንብረትና ተድላን ከማሳደድ ነው በማለት እርግጠኞች ሆነው ይናገራሉ። መላ አእምሮአቸው በእነዚህ ነገሮች ላይ እንዲያስብ ከማድረግ አልፈው ለእነዚህ ነገሮች ሲሉ ምንም ነገር ይኸውም ጤናቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሕሊናቸውን ጭምር መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው። ታዲያ ውጤቱ ምን ይሆናል? እርካታና ደስታ ከመጨበጥ ይልቅ “በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።” (1 ጢሞቴዎስ 6:10) ስለዚህ ጳውሎስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን የዓለም አስተሳሰብ ከንቱነት መሆኑን ተገንዝበው እንደ አሕዛብ መመላለሱን እንዲያቆሙ አጥብቆ ማሳሰቡ አያስደንቅም።
10. የዓለም ሰዎች በ“አእምሮ ጨለማ” ውስጥ የሚገኙት እንዴት ነው?
10 ጳውሎስ ቀጥሎ ዓለም የሚያስቀና ወይም ሊከተሉት የሚገባ ምንም ነገር እንደሌለው ሲያመለክት “እነርሱ . . . ልቡናቸው ጨለመ” ይላል። (ኤፌሶን 4:18) እርግጥ ነው፤ ዓለም በእያንዳንዱ የሥራ መስክ የተሰለፉ አዋቂዎችና ምሁራን አሉት። ያም ሆኖ ጳውሎስ በልቡና ጨለማ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ተናግሮአል። ለምን? እርሱ የተናገረው ስለ አእምሮአቸው ዕውቀት ወይም ችሎታ አይደለም። “ልቡና” የሚለው ቃል የሰብዓዊ ማስተዋል ማዕከል፣ የመረዳት ችሎታ መቀመጫ የሆነውን ውስጣዊ ሰው ያመለክታል። በሥራዎቻቸው ሁሉ የሚመራቸው ብርሃን ወይም አቅጣጫ አመልካች የሆነ ነገር ስለሌላቸው በጨለማ ውስጥ ናቸው። ይህንንም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት ከሚያጋጥማቸው ግራ መጋባት መመልከት ይቻላል። ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ተስፋፍቶ የሚገኘው ‘ማንኛውም ነገር ትክክል ሊሆን ይችላል’ የሚለው የተዛባ አስተሳሰብ የዕውቀትና የሥልጣኔ ውጤት ነው ይሉ ይሆናል። ጳውሎስ እንደተናገረው ግን የልቡናቸው መጨለም ያስከተለው ውጤት ነው። በመንፈሣዊ ሁኔታ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ በመደናበር ላይ ይገኛሉ። — ኢዮብ 12:25፤ 17:12፤ ኢሳይያስ 5:20፤ 59:6–10፤ 60:2፤ ከኤፌሶን 1:17, 18 ጋር አወዳድር።
11. በዓለም ውስጥ የጨለመ ልቡና ለመስፋፋት ምክንያት የሆነው ምንድን ነው?
11 ሰዎች በብዙ ነገሮች ረገድ ጠቢባንና አዋቂዎች ሲሆኑ በመንፈሣዊ ነገሮች ግን ጨለማ የዋጣቸው ሊሆኑ የሚችሉት ለምንድን ነው? ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 4:4 ላይ “ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ” በማለት መልሱን ይሰጠናል። በእውነቱ ክብራማውን ምሥራች የተቀበሉ ሁሉ በአእምሮአቸው መለወጣቸውና ልባቸው ብርሃን የበራለት መሆኑ እንዴት ያለ ታላቅ በረከት ነው!
የደነቆሩና የደነዘዙ ልቦች
12. ዓለም “ከእግዚአብሔር ሕይወት” የራቀው በምን መንገድ ነው?
12 ጳውሎስ በአእምሮአችን የተለወጥንና ልባችን ብርሃን የበራለት ሰዎች መሆን የሚገባን ለምን እንደሆነ በተጨማሪ ሐሳብ ለማስገንዘብ የዓለም አካሄድ “ከእግዚአብሔር ሕይወት” የራቀ መሆኑን ጠቅሶልናል። (ኤፌሶን 4:18) ሰዎች በአምላክ ማመናቸውን ትተዋል ወይም ሙሉ በሙሉ አምላክ የለሾች ሆነዋል ማለታችን አይደለም። አንድ የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ እንደሚከተለው በማለት ነገሩን በጥሩ ሁኔታ ገልጸውታል:- “አምላክ የለሽ ከማለት ይልቅ አምላክን ገሸሽ ማድረግ የሚል አዲስ ቃል እንፍጠር። ሰዎች አምላክን በሳምንቱ ቀኖች በሙሉ በዓለማዊ የፖለቲካ አመለካከታቸው ወይም በግል ሕይወታቸው ላይ ምንም ዓይነት ተጽእኖ እንዳያሳድር ሣጥን ውስጥ ቆልፈው ካቆዩት በኋላ እሁድ ዕለት ጠዋት ብቻ ብቅ ያደርጉታል። እንዲህ እያደረጉ ደግሞ በአምላክ በማመናቸው ምሥጋናና ክብር ለማግኘት ይፈልጋሉ። . . . ይነስም ይብዛ በአምላክ ያምናሉ። በዘመናዊው ኅብረተሰብ ውስጥ ግን ለመናገር መብት ያለው ሆኖ አይታያቸውም።” ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን” አላከበሩትም በማለት ሁኔታውን ገልጾታል። (ሮሜ 1:21) በየቀኑ ለአምላክ ምሥጋናና ክብር ማቅረብ ይቅርና በምንም ዓይነት መንገድ ስለእርሱ የማያስቡ ሰዎች እንመለከታለን።
13. “የእግዚአብሔር ሕይወት” የተባለው ምንድን ነው?
13 “የእግዚአብሔር ሕይወት” የሚለው ሐረግ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። አእምሮአዊና መንፈሳዊ ጨለማ ሰዎች ለነገሮች የሚሰጡት ዋጋ እንዴት እንደሚዘበራረቅባቸው ያሳየናል። እዚህ ላይ “ሕይወት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (እንደ ባዮሎጂና ባዮግራፊ የመሰሉት) ቃላት የተወሰዱበት ባዮስ ከሚለው ቃል የመጣ አይደለም። ባዮስ ማለት የኑሮ ዘይቤ ወይም አኗኗር ማለት ነው። ከዚህ ይልቅ ዞኤ (እንደ ዙ እና ዙኦሎጂ የመሰሉት የእንግሊዝኛ ቃላት ከዚህ ቃል የተገኙ ናቸው) ከተባለው የግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ነው። የብሉይና የአዲስ ኪዳን ቃላት ገላጭ የሆነው የቫይን መዝገበ ቃላት እንደሚለው “ሕይወት ማለት በመሠረታዊ ትርጉም የተሟላውንና ፍጹም የሆነውን ሕይወት፣ አምላክ ያለውን ዓይነት ሕይወት” የሚያመለክት ቃል ነው። . . . አዳም በኃጢአት በመውደቁ ምክንያት የሰው ልጅ ያጣው ይህን ዓይነት ሕይወት ነው።” ስለዚህ ጳውሎስ አእምሮአዊውና መንፈሳዊው ጨለማ የዓለምን ሰዎች ወደ ሥጋዊ ጥፋትና ብልሽት ከመምራቱ በተጨማሪ አምላክ ከዘረጋው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ለይቶአቸዋል። (ገላትያ 6:8) እንዲህ የሆነው ለምንድን ነው? ይህ የሆነበትን ምክንያት ጳውሎስ ቀጥሎ ይገልጽልናል።
14. ዓለም ከአምላክ ሕይወት ከራቀባቸው ምክንያቶች አንዱ ምንድን ነው?
14 በመጀመሪያ ደረጃ “በውስጣቸው ባለው ድንቁርና” ምክንያት እንደሆነ ተናግሮአል። (ኤፌሶን 4:18) “በውስጣቸው ባለው” የሚለው ሐረግ የደነቆሩት የማወቅ አጋጣሚ አጥተው ሳይሆን ሆን ብለው የአምላክን ዕውቀት ለመቀበል አሻፈረኝ በማለታቸው ምክንያት መሆኑን ያመለክታል። ሌሎች ትርጉሞች “አምላክን ለማወቅ ያለመፈለግ ባሕርይ ስላላቸው” (ዘ አንከር ባይብል ) “ልባቸውን በመዝጋታቸው ምክንያት ዕውቀት የለሽ ስለሆኑ” (ጀሩሳሌም ባይብል ) ነው ይላሉ። የአምላክን ትክክለኛ ዕውቀት ስለናቁ ወይም ለመቀበል ፈቃደኞች ስላልሆኑ ይሖዋ አምላክ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ሲል በተናገረው ልጁ ለሚያምኑ ሰዎች የሚሰጠውን ዓይነት ሕይወት ለመቀበል የሚያስችላቸው ምንም ዓይነት መሠረት የላቸውም። — ዮሐንስ 17:3፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:19
15. ይህ ዓለም ከአምላክ ሕይወት እንዲርቅ አስተዋጽኦ ያደረገው ነገር ምንድን ነው?
15 ዓለም በአጠቃላይ ከአምላክ ሕይወት የራቀበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ጳውሎስ እንደገለጸው “የልባቸው ደንዳናነት” ነው። (ኤፌሶን 4:18) “ደንዳናነት” የሚለው ቃል መሠረታዊ ትርጉም በደረቀ የቆዳ ቅርፊት እንደተሸፈነ ሥጋ ወይም መጅ መጠጠር ነው። የደረቀ የቆዳ ቅርፊት ወይም መጅ እንዴት እንደሚፈጠር ሁላችንም እናውቃለን። በመጀመሪያ ላይ ቆዳው የለሰለሰና ስሜት ያለው ሊሆን ይችላል። በተደጋጋሚ ከሌላ ነገር ጋር ሲፋተግና ጭነት ሲደርስበት ግን ወፍሮና ጠንክሮ መጅ ይፈጥራል። ከዚያ በኋላ የሚደርስበት ፍትጊያና ጭነት አያሳምመውም። ሰዎችም በተመሳሳይ የጠነከረ ወይም መጅ ያበጀ ልብ ኖሮአቸው ወይም ለአምላክ ምንም ዓይነት ስሜት የሌላቸው ሰዎች ሆነው አይወለዱም። ይሁንና በዓለም ውስጥ ስለምንኖር ለዓለም መንፈስ እንጋለጣለን፤ ልባችንም ካልተጠበቀ ብዙ ሳይቆይ ጠንክሮ መጅ ያበጃል። ጳውሎስ “ከእናንት ማንም በኃጢአት መታልል እልከኛ እንዳይሆን [ልቡ እንዳይደነድን አዓት]” በማለት ያስጠነቀቀው በዚህ ምክንያት ነው። (ዕብራውያን 3:7–13፤ መዝሙር 95:8–10) ስለዚህ አእምሮአችን እንደተለወጠና ልባችንም ብርሃን እንደበራለት ሆነን መኖራችን ምንኛ አጣዳፊ ነው!
“የሥነ ምግባር ስሜታቸው ስለጠፋ”
16. ዓለም በአእምሮ ጨለማ ውስጥ መሆኑና ከአምላክ ሕይወት መራቁ ምን ውጤት አስከትሎአል?
16 እንዲህ ያለው ጨለማና ከአምላክ መራቅ የሚያስከትለው ውጤት በሚከተሉት የጳውሎስ ቃላት ተጠቃልሎ ተገልጾአል:- “ደንዝዘውም [የሥነ ምግባር ስሜታቸው ስለጠፋ አዓት] በመመኘት ርኩሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ።” (ኤፌሶን 4:19) “የሥነ ምግባር ስሜታቸው ስለጠፋ” የሚለው ሐረግ ቃል በቃል ሲተረጎም “የሕመም ስሜት (የሥነ ምግባር ሕመም) ስለማይሰማቸው” ማለት ነው። መጅ ያወጣ ልብ የሚሆነው ልክ እንደዚህ ነው። የሕሊና መቆርቆር ወይም በአምላክ ዘንድ ተጠያቂ እንደሚሆን መሰማቱ ካቆመ የሚገታው ወይም የሚገድበው ነገር ይጠፋል። በዚህም ምክንያት ጳውሎስ “ራሳቸውን ወደሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ” አለ። ሆን ብለው በፈቃደኝነት የወሰዱት እርምጃ ነው። “ሴሰኝነት” ወይም “መዳራት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እፍረተ ቢስነትን፣ ሕግንና ባለ ሥልጣኖችን መናቅን ያመለክታል። “ርኩሰት ሁሉ” የተባለው ደግሞ ጾታዊ ብልግናዎችን ብቻ ሳይሆን በኤፌሶን በነበረው የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ይከናወኑና የጳውሎስ አንባቢዎች በሚገባ ያውቋቸው የነበሩትን የመሰሉ የመራባት ክብረ በዓሎችና የአምልኮ ሥነ ሥርዓቶች የመሰሉትን በሃይማኖት ስም የሚፈጸሙ ወራዳ ተግባራት ጭምር ያመለክታል። — ሥራ 19:27, 35
17. ጳውሎስ የሥነ ምግባር ስሜታቸው የጠፋባቸው ሰዎች ኃጢአት ለመሥራት እንደሚስገበገቡ የተናገረው ለምን ነበር?
17 እነዚህ ሰዎች አለምንም ገደብ በሴሰኝነትና በርኩሰት ተግባሮች መካፈላቸው ሳያንስ ‘በስግብግብነት ይመላለሳሉ።’ በማለት ጳውሎስ አክሎ ገልጿል። እነዚህ “የሥነ ምግባር ስሜታቸው የጠፋባቸው አዓት” ሰዎች ኃጢአት ለመሥራት ይስገበገባሉ። በመጠኑም ቢሆን የሥነ ምግባር ስሜታቸውን ያላጠፉ ሰዎች ኃጢአት ሲሠሩ ሌላው ቢቀር ነገሩ ይጸጽታቸውና ኃጢአቱን ላለመድገም ብርቱ ትግል ያደርጉ ይሆናል። “የሥነ ምግባር ስሜታቸው በጠፋባቸው ሰዎች” ግን በስግብግብነት ኃጢአት ይሠራሉ። (“ተጨማሪ ኃጢአት ለመሥራት ይፈልጋሉ። ዘ አንከር ባይብል ) አንድ የሬዲዮ ትችት አቅራቢ እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል:- “ዛሬ ማታ ስትፈነጥዙ ብታድሩ ነገ ከዚያ የበለጠ ለመፈንጠዝ ትፈልጋላችሁ።” ሊገታ በማይቻል የውድቀት አዘቅት ውስጥ በጉጉት ይገቡና እስከ መጨረሻው ውርደት ያሽቆለቁላሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን መጥፎ ነገር ያደረጉ አይመስላቸውም። “የአሕዛብን ፈቃድ” በጥሩ ሁኔታ የሚገልጽ እንዴት ያለ ሕያው መግለጫ ነው! — 1 ጴጥሮስ 4:3, 4
18. ለማጠቃለል ያህል ጳውሎስ የዓለም አእምሮአዊና መንፈሳዊ ሁኔታ ምን ዓይነት መልክ እንዳለው ገልጾአል?
18 ጳውሎስ በኤፌሶን 4:17–19 በሚገኙት ሶስት ቁጥሮች ብቻ የዓለምን እውነተኛ የሥነምግባርና መንፈሳዊ ሁኔታ ጥሩ አድርጎ አጋልጦአል። በዓለማዊ ሊቃውንትና ፈላስፎች የሚስፋፉት ምክሮችና ንድፈ ሐሳቦች፣ እንዲሁም ለሀብትና ለተድላ የሚደረገው የማያቋርጥ ሩጫ በእርግጥም ከንቱ መሆናቸውን አመልክቷል። ዓለም በአእምሮና በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ስለሚገኝ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ በሥነ ምግባር ማጥ ውስጥ ዘቅጦ ይገኛል። በመጨረሻም ዓለም ራሱ ፈቅዶ በራሱ ላይ ባመጣው ድንቁርናና ድንዛዜ ምክንያት ተስፋ በሌለው ሁኔታ ከአምላክ ሕይወት ርቆአል። በእርግጥም በአሕዛብ አካሄድ እንዳንመላለስ የሚያደርጉን በቂ ምክንያቶች አሉን።
19. ሊብራሩ የሚገቡ ምን አስፈላጊ ጥያቄዎች ገና ይቀራሉ?
19 ዓለም ከአምላክ እንዲርቅ ያደረገው የአእምሮና የልብ ጨለማ ስለሆነ ማንኛውንም ዓይነት ጨለማ ከአእምሮአችንና ከልባችን ልናስወግድ የምንችለው እንዴት ነው? የብርሃን ልጆች ሆነን በመላለስ እንድንቀጥልና የአምላክ ሞገስ እንዳይለየን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ይህ ጉዳይ በሚከተለው ርዕሰ ትምህርት ይብራራል።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ጳውሎስ በኤፌሶን 4:17–19 ላይ የሚገኘውን ጠንካራ ምክር እንዲሰጥ ያነሳሳው ምን ነበር?
◻ የዓለም መንገዶች ከንቱና ጨለማ የሆኑት ለምንድን ነው?
◻ “ከእግዚአብሔር ሕይወት ራቁ” የሚለው አነጋገር ምን ማለት ነው?
◻ የጨለመ አእምሮና የደነዘዘ ልብ ምን ውጤት ያስከትላሉ?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤፌሶን በሥነ ምግባር ርኩሰትዋና በጣዖት አምልኮትዋ የታወቀች ነበረች
1. ሮማዊ ግላዲያተር በኤፌሶን
2. የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ፍርስራሾች
3. በኤፌሰን የነበረ ቲያትር ቤት
4. የኤፌሶኗ አርጤምስ፣ የመራባት ሴት አምላክ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዓለም ጠቢባን ምን ሊሰጡን የሚችሉት ዕውቀት አላቸው?
ኔሮ
[ምንጭ]
Musei Capitolini, Roma